ከጣሰው አንተነህ (tasewanete@gmail.com)
ቁጥር 2
አቶ አንተነህ መርዕድ የተባሉ ሰው ”ፕሮፌሰር መስፍንን ለቀቅ” በሚል ርእስ በዘሀበሻ ድህረገጽ ላይ ላቀረቡት መጻጽፍ የመልስ መንደርደሪያ የሚሆን ”ክህደትን ክህደት፣ የካደንም ከሀዲ ለማለት ድፍረት ይኑረን” በሚል ርእስ በኦክቶበር 8/2014 ለዘሀበሻ ድህረገጽ ልኬለት ባያወጣውም ሌሎች በድህረገጻቸው አውጥተውት አይቻለሁ፣ በዚህ አጋጣሚ እውነቱ እንዲነገር እድል ለሚሰጡ ድህረገጾች ምስጋናየን አቀርባለሁ። ባለፈው ጽሁፌ በቀጣይነት አቀርባለሁ ባልሁት መሰረት ለዛሬው የሚከተለውን ይዤ ቀርቤአለሁ። ጊዜና ጉልበት ካገኘሁ ደግሞ እቀጥልበታለሁ።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም በ09-08-2014 ዓም በሸገር ራዲዮ ጣቢያ ባደረጉት ቃለ መጠየቅ በአርባ ጉጉ የሚኖሩ አማሮች በገፍ እንደተገደሉ ብዙ የድምጽ፣ የጽሁፍና የሰው ምስክርነት መረጃዎች እንዳሉ እየታወቀ ”አማሮች አልተገደሉም” ብለው መካዳቸው ሲያስገርመን፤ የፕሮፌሰርን ክህደት ለማስተባበል እንደ አቶ አንተነህ መርእድ አይነት ግለሰቦች የሚፈበርኳቸው የይቅርታ ምክንያቶች ደግሞ ”በሰው ቁስል ላይ እንጨት ቢሰኩበት አያምም” እንደሚባለው ሆኖ ስለተሰማኝ የፕሮፌሰሩን ንግግርና በአማራው ህዝብ ላይ በአርባ ጉጉ አካባቢ የተፈጸመውን እልቂት ባጭሩ አቀርባለሁ።
የፕሮፌሰር መስፍን ንግግር፡
”ለምሳሌ አርባ ጉጉ አማራ ነው የተገደለው የሚባለው፣ አይደለም። ብዙዎቹ የተገደሉት ኦሮሞዎች ናቸው። እንግዲህ እኔ በኢሰመጉ መግለጫ ስናወጣ ይህንን አማራው አላልንም። ስለምን ብዙዎቹ ስማቸው የኦሮሞኛ ነው.” እያሉ ይቀጥላል። (ቀን 09-08-2014 ክፍል ሁለት የድምጽ ቅጂ)
በመጀመሪያው ጽሁፌ እንዳልሁት ፕሮፌሰር መስፍን ይህን ቃለመጠየቅ ባይሰጡ ኖሮ የራሳችንን ቅን ትርጉም እየሰጠን ማንነታቸውን ሳናውቅ እንቀር ነበር። በዚሁ ቃለ መጠይቃቸው ”ኢሰመጉን ያቋቋምሁት ወያኔን ለመደገፍ ነው” ስላሉን በጊዜው በመግለጫው ለምን የተገደሉትን አማሮች እንዳላሉ ያጤነው ሰው አልነበረም። እንዲሁም ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ በጎሳ ሲከፋፍል ፕሮፌሰር መስፍን ደግሞ ህዝብን በስም መከፋፈል እንደሳቸው አበባል ”አጥንተውት” እንደሆነ አናውቅም ነበር። የአማራ ስም ያለው ኦሮሞ፣ ከንባታ፣ ሀዲያ፣ ወዘተ ወይም የሌላ ነገድ ስም ያለው አማራ፣ ትግሬ፣ ከንባታ፣ ኦሮሞ ወዘተ የለም ማለት ነው? ኢትዮጵያዊነት ጨዋነት ሆኖብኝ እንጂ ፕሮፌሰር መስፍን አንቱነት የሚገባቸው ሰው ሆነው አላገኘሗቸውም። ለሁሉም በአርባ ጉጉ የሆነውን ደግሞ እንመልከት፡
በአማራው ህዝብ ላይ በአርባ ጉጉ የተፈጸመው ጭፍጨፋ፤
የአውራጃው የኦህዲድ ተወካይ አቶ ዲማ ጎርሜሳ ግንቦት 26/1984 በአቦምሳ ከተማና አካባቢው የሚኖሩትን የኦሮሞ ተወላጆች ሰብስበው ”አሼ ኦዴ፣ ኢመና፣ አቡሌ በሚባሉ መንደሮች አማሮች ይገደሉ ብላችሁ ፈርሙ” በማለት ትዕዛዝ ሲሰጡ ሐጂ ቃሲም የሚባሉ ”ለረጅም ጊዜ አብረን የኖርንና የተዋለድን ስለሆን አንፈርምም፣ የአማራ ህዝብ አይመታም ህዝብን ከህዝብ የሚአዋጋ ነው መመታት ያለበት” በማለታቸው አቶ ዲማ ጎርሚሳ ”የነፍጠኛ እረዳት ነህ” ብሎ ሽጉጥ በመምዘዙ ስብሰባው ተበትኗል።
በማግስቱ ግንቦት 27/1984 አቡሌ የሚባለው የአማራው ተወላጆች መንደር በኦህዲድ ተከቦ ተኩስ ከተከፈተበት በሗላ በላውንቸር ተደብድቦ መንደሩ ነዷል። 50 የሚሆኑ ነፍሴ አውጪኝ ብለው ሸሽተው ቤተክርስቲያን የተጠጉ ህጻናትን፣ ሴቶችን፣ እንዲሁም አሮጊቶችን ተከታትለው ከበውና ለቅመው አርደዋቸዋል። ቤተክርስትያን የገቡ 30 ህጻናት እና ካህናቱ ከቤተክርስቲያኑ ጋር በላውንቸር ነደዋል። በጠቅላላው 150 ቤቶች በእሳት ነደዋል። ይህንን ግፍ በሀላፊነትና በአዝማች መሪነት ያካሄደው ዲማ ጉሪምሳ የተባለው የኦህዲድ ተወካይና ባለስልጣን ነበር።
አቶ ዲማ ጉርሚሳ ”አማራን መጨረስ ዛሬ ነው” የሚል ትእዛዝ በመስጠት አቦምሳ የሚባለው የአማሮች መንደር ተከቦ ህዝቡ ከቤቱ ሳይወጣ መንደሩ እንዲቃጠል ሆኖዋል። በጠቅላላው 100 ቤቶች ሰው እንደያዙ ተቃጥለው የተረፉ 50 ሰዎች ተይዘው በጥይት እንዲረሸኑ ሆኖዋል።
አሸ በተባለ መንደር የዚሁ አይነት ጭፍጨፋ ተካሄዷል። የኦህዲድ ተከታዮች ነፍሰ ጡሮችን እየመረጡ ጽንሱን ማግኘት፣ መስለብና ሞራውን እያወጡ ማየት፣ ከላይ የተጠቀሱ በአቶ ዲማ ጉርሚሳ መሪነት በአንቦሳ፣ በአቡሌ፣ በአበሳና በአሴ በተባሉ መንደሮች በአንድ ቀን የተፈጸሙ ሲሆን ይትባረክ በተባለው የኦህዲድ ተወካይ በዚሁ እለት በሚከተሉት መንደሮች ተመሳሳይ እልቂት ተፈጽሟል።
በጉና ወረዳ ሶርቢዩ አዲስ አለም በተባለ ቦታ 150 ቤቶች ሲቃጠሉ ሁለት የታወቁ ሽማግሌዎች እጅና እግራቸው ታስሮ በእሳት ተቃጥለዋል።
ዋቄንጥራ በተባለ መንደር 100 ቤቶች ሲቃጠሉ ከነህይወታቸው የተቃጠሉ ሰዎች ቁጥር አይታወቅም።
መሶ በተባለ መንደር ከ100 በላይ ቤቶች እንዲቃጠሉ ተደርጎ ከቃጠሎው የዳኑ 80 ሰዎች እጃቸው ታስሮ በኦህዲድ ጥይት ተረሽነው ቀጥሎም እሬሳቸው በገደል ተወርውሯል።
በተለይ ከ7ወር በላይ የሆኑ ነፍሰጡሮች እየታደኑ እንዲገደሉ ተደርጓል። እንዲሁም በአካባቢው የነበሩ 6 ቤተክርስቲያኖች ተቃጥለዋል። ይህ ሁሉ እልቂት የተፈጸመው ግንቦት 27/1984 በአንድ ቀን ነው። ግን በዚህ አላቆመም፣ ጭፍጨፋው በእቅድ በተሰማራ ሰራዊት ቀጥሎ እንደሴ ባዩ የሚባለው መንደር ነዋሪ የሆኑ አማሮች በተመሳሳይ ሁኔታ በኦህዲድ ሰራዊት እንዲከበቡ ከሆነ በሗላ ከመንደሩ ነዋሪዎች መካከል 80 የሚሆኑ እጅና እግራቸውን ታስረው ተወስደው ወደ ገደል ተወርውረዋል።
ከጥቅምት ወር እስከ ሰኔ 1984 ድረስ በአርባ ጉጉ በኦህዲድ ሰራዊትና በኦነግ ታጣቂዎችና በኢስላሚክ ኦሮሚያ ታጣቂዎች በተወሰዱ ወረራዎች 3500 ቤቶች በእሳት ሲቃጠሉ በዚህ ቃጠሎ በብዙ ሺህ የሚቆጠር የሰው ህይወት ሲጠፋ በአካባቢው የነበረው ሰብል ሙሉ በሙሉ በእሳት እንዲቃጠል ሆኖዋል።
አነ አቶ ሀሰን መሀመድ በመንግስት ምክር ቤት ተወካይ ”የአጼ ሚኒሊክን ስርዓት ማፍረስ ማለት አንገቱን አቀርቅሮ የሚገኘው ነፍጠኛ ወቅትና ጊዜ ጠብቆ ቀና ስለሚል ጨርሶ መቅበር አሁን መሆን አለበት” በማለት ህዝብ ሰብስበው እየሰበኩ ህዝብን በህዝብ ላይ እንዲነሳ ቅስቀሳ ሲያደርጉ፣ በአቶ ኩማ ደመቅሳ የሚመራው ኦህዲድ አማራውን ህዝብ ለይቶ ይህ አይነት እልቂት በሚያካሂድበት ግዜ ድርጊቱን የተቃወሙ የሀገር ሽማግሌዎች በጊዜው ለአቶ መለስ ዜናዊ አቤቱታ አቅርበው፣ መለስ ዜናዊ የሰጣቸው መልስ ”አንዳንድ ግለሰቦች ለብዙ ዜጎች ተጠያቂ ለሆነው ለነፍጠኛ ወገናዊ በመሆን የሚያሳዩት ተግባር አግባብ አይደለም። በዚህ ጉዳይ አለመግባባት አመችነቱ ለነፍጠኛ ብቻ ነው።” ሲል፣ የዘር ማጥፋት ወንጀሉን እንዲቀጥሉበት ለአቶ ኩማ ደመቅሳና ለተባባሪዎቻቸው ይሁንታውን የዘር ማጥፋቱ ቀጥሏል።
እንግዲህ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም በአርባ ጉጉና አካባቢው አንድ ህዝብ አማራ በመሆኑ ብቻ ከላይ በጠቀስሁትና ከዚህም በከፋ መልኩ እንዳለቀ የጽሁፍና የሰው ምስክር እያለ፣ ”የተገደሉት አማሮች አይደሉም” ብሎ መካድ ከሀዲነት ካላሰኘ የፕሮፌሰር መስፍን አድናቂ፣ ሸላሚና ተሟጋች የሆኑ ሰዎች ለከሀዲነት አዲስ ቃል ቢሰጡን ጥሩ ነው። በህይወት ያሉ ምስክሮችን መጥራት እንደሚቻል እየታወቀ ይህንን ሀቅ መካድ፣ ከፕሮፌሰር መስፍን ስር የሰደደ የአማራ ህዝብ ጥላቻ የመነጨ ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ስር የሰደደ የአማራን ህዝብ ጥላቻ ያለሁት ከባድ ቃል ሊመስላችሁ ይችላል፣ ነገር ግን በዚህ ቃለ መጠየቅ ፕሮፌሰር መስፍን ሌላው ቀርቶ አማራ ስለሆኑ ግለሰቦች በቃለመጠይቃቸው ለምሳሌ፣ ስለ ራስ አስራተ ካሳ፣ ስለ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፣ ስለ ቢትወደድ መኮነን እንዳልካቸው የተናገሩትን አዳምጣችሁ ፍረዱ። እንደኔ፣ እንደ አንድ ግለሰብ ከሆነ ደግሞ ፕሮፌሰር መስፍንን ደግፎ አካኪ ዘራፍ ማለት ”ተመሳሳይ ላባ ያላቸው ወፎች አብረው ይበራሉ” እንደሚባለው ተባባሪ ከሀዲዎች አድርጌ አያቸዋለሁ።
Average Rating