www.maledatimes.com ተደራራቢ ፈተናና ጫና የበዛበት የግሉ ፕሬስ – በጠባብ መንገድ ላይ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ተደራራቢ ፈተናና ጫና የበዛበት የግሉ ፕሬስ – በጠባብ መንገድ ላይ

By   /   April 7, 2014  /   Comments Off on ተደራራቢ ፈተናና ጫና የበዛበት የግሉ ፕሬስ – በጠባብ መንገድ ላይ

    Print       Email
0 0
Read Time:7 Minute, 24 Second

 

07 April, 2014  Written by  አበባየሁ ገበያው እና አለማየሁ አንበሴ

“መንግስት መረጃን በሞኖፖል በያዘበት ወቅት፣ስለ ፕሬስ ነፃነት ማውራት አይቻልም”   ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ

“ጋዜጦች የሀብታም መሆናቸው ቀርቶ ድሃ ተኮር የሚሆኑበትን ስልት መንደፍ ያስፈልጋል”  ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ

“የጋዜጣ ኢንዱስትሪው አልተዳከመም፤አዳዲስ ጋዜጦች እና መፅሔቶች እየታተሙ ነው”   አቶ አንተነህ አብርሃም

ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የጋዜጣ ደንበኛ እንደሆኑ ይናገራሉ -አቶ ያለው ደግፌ፡፡ በተለይም የግል ፕሬስ ውጤቶችን ሳያሰልሱ ያነቡ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ኢህአዴግ ሀገሪቷን ከተቆጣጠረና የነፃ ፕሬስ አዋጅን ካወጀ በኋላ፣አብዛኞቹ ጋዜጦች ትኩረታቸውን ወደ ፖለቲካና አገራዊ ጉዳዮች ማድረጋቸውን አቶ ያለው ያስታውሳሉ። በተለይ ከኤርትራ መገንጠል፣ ከደርግ ውድቀት፣ ከፌደራሊዝም ስርአቱ ብሄር ተኮር መሆን ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በእነዚህ ጋዜጦች በስፋት ይዳሰሱ ነበር፡፡ ጋዜጦቹ ፍራቻ እንዳልነበረባቸው ለመዳሰስ የሚያነሷቸው ጠንካራና አይነኬ የሚመስሉ ጉዳዮች ማሳያ ናቸው – ይላሉ፣የረጅም ጊዜ የጋዜጣ አንባቢው አቶ ያለው፡፡

የጋዜጦች ዋጋም ኪስ የማይጎዳ እንደነበርና የአንድ ጋዜጣ ዋጋ ከ75 ሳንቲም እንደማይበልጥ ያስታውሳሉ፡፡ አብዛኛው አንባቢም ጋዜጣ ገዝቶ የማንበብ ልማድ ነበረው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ነገሮች ተለውጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በ2005 ዓ.ም ባወጣው የዳሰሳ ጥናት ላይ እንደተመለከተው፤የህትመት ዋጋ ንረት በፈጠረው ተፅዕኖ፣ ጋዜጣን ገዝቶ ከሚያነበው ይልቅ ከአዟሪዎች በኪራይ የሚያነበው ይበልጣል፡፡ በጥናቱ ከተካተተው ጠቅላላ አንባቢ አብላጫው /35.24 በመቶ ያህሉ/  ተከራይቶ ሲያነብ፣በሁለተኛነት /32.75 በመቶው/ ገዝቶ ያነባል፡፡ የተቀረው በመስሪያ ቤት በኩል በቤተ መጻሕፍት እና በተለያዩ መንገዶች እንደሚያነብ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ ያነጋገርናቸው አንዳንድ አዟሪዎች በበኩላቸው፤በኪራይ ንባብ ብቻ በቀን ከ70 ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኙ ጠቅሰዋል፡፡ በ1998 ዓ.ም የአንድ ጋዜጣ መሸጫ ዋጋ 2ብር ከ50 የነበረ ሲሆን በ8 ዓመት ውስጥ በ4 እጥፍ ጨምሮ አሁን በ10 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

የሽግግር ወቅቱ የፖለቲካ መስመሮች ያልጠሩበት መሆኑ ለጋዜጦች መስፋፋት አስተዋፅኦ አበርክቷል የሚል እምነት እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ ያለው፤ በዚያው ልክ ጋዜጦቹ ፅንፈኝነት፣ ዘረኝነትና ጥላቻ በህብረተሰቡ ውስጥ ቦታ እንዲኖራቸው አድርገዋል ሲሉ ይተቻሉ፡፡ በተቃራኒው ስለ ሀገር አንድነትም የሚወተውቱ ጋዜጦች እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ ከእነዚህ ጋዜጦች መካከል በሐምሌ እና ነሐሴ 1985 ዓ.ም ወደ ገበያው የተቀላቀሉ “ጦማር” እና “ጥንቅሽ” ጋዜጦችን ጨምሮ በ1986 ዓ.ም ወደ ስርጭት የገቡት “መብረቅ”፣ “ሞገድ”፣ “ሰይፈነበልባል”፣ “አዕምሮ”፣ “ኢትዮጵ”፣ “ጎዳናው”፣ “ጦቢያ”— በወቅቱ ተነባቢነት የነበራቸው ጋዜጦች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጋዜጦች መካከል ከሁለት እና ሶስት ዓመት እድሜ ያልዘለሉ ቢኖሩም አብዛኞቹ ሥርዓተ ፍፃሜያቸው የተከናወነው ግን በምርጫ 97 ማግስት ነው፡፡

በፖለቲካ ጉዳይ ላይ ብቻ አተኩረው እስከ 1998 ዓ.ም ሲታተሙ ከቆዩት የግል ጋዜጦች መካከል “ልሣነ-ህዝብ”፣ “ሐዳር”፣ “ምኒልክ”፣ “ሩህ”፣ “ሣተናው”፣ “ነፃነት”፣ “አስኳል”፣ “አዲስ ዜና”፣ “ክብሪት”፣ “እለታዊ አዲስ”፣ “ጎህ” እና “ዘ ፕሬስ” ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እነዚህም ቢሆኑ የበረከቱት እስከ 1998 ዓ.ም ብቻ ነው፡፡ እነዚህን ጨምሮ 23 ጋዜጦች ያህል የተዘጉት በምርጫው ማግስት በማተሚያ ቤቶች አናትምም ባይነት ነበር፡፡ እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ ወደ 106 የሚደርሱ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ጋዜጦች እየታተሙ ለገበያ ይቀርቡ ነበር፡፡

ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ከሚያተኩሩት ጋዜጦች ባሻገር፣ወሲብና ስነ-ወሲብን እንዲሁም ፍቅርና ፆታዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ጋዜጦች ከ1987 ጀምሮ እስከ 1990ዎቹ አጋማሽ እንደ አሸን ፈልተው ነበር፡፡ “ኤሮቲካ”፣ “እውነተኛ ፍቅር”፣ “የፍቅር ህይወት”፣ “የፍቅር ማህደር”፣ “የፍቅር ረመጥ”፣ “የፍቅር ጨዋታ”፣ “ፍቅረኞች”፣ “ፍቅር”፣ “ማዶና” ወዘተ— የተሰኙት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ በ1990ዎቹ አጋማሽ በህዝብ ተቃውሞ እንዲታገዱ ተደርገዋል። እንዲያም ሆኖ ተወዳጅ እንደነበሩ የሚናገሩም አሉ። ከእነዚያ ጋዜጦች የአንደኛው አዘጋጅ ሲናገሩ፣ ከመወደዳቸው የተነሳ ከዋጋቸው በላይ እስከ 10 ብር ይሸጡ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የፍቅርና ወሲብ ጋዜጦች የአንባቢውን የትኩረት አቅጣጫ በማስቀየር ረገድም የተሳካላቸው ነበሩ የሚሉት አዘጋጁ፤በዚህም ምክንያት የፖለቲካ ጋዜጦች ገበያ መቀዛቀዝ አሳይቶ እንደነበር ያወሳሉ፡፡ ጋዜጦቹ በ1990ዎቹ አጋማሽ በህዝብ ተቃውሞ መዘጋታቸው ለፖለቲካ ጋዜጦች ገበያ መጨመር ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል።

በአገሪቱ የፕሬስ ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጋዜጦች የታተሙት በምርጫ 97 ወቅት ሲሆን ከ100 ሺህ በላይ ቅጂዎች የሚያሳትሙ ነበሩ። አንድ ጋዜጣ በቀን ሁለት እና ሶስት ጊዜ እስከ መታተም ደርሶ እንደነበረም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአሁን ወቅት ግን ከፍተኛው የቅጂዎች ብዛት በአማካይ ከ10 ሺህ ኮፒ እንደማይበልጥ የብሮድካስት ባለሥልጣን ጥናት ይጠቁማል፡፡

ድህረ ምርጫ 97 እና የግሉ ፕሬስ

ከ1999 እስከ 2005 ባለው ጊዜ ውስጥ የአንባቢን ትኩረት አግኝተው ከነበሩት ከ22 በላይ በአማርኛ ቋንቋ የሚታተሙ ጋዜጦች መካከል በአሁን ወቅት በገበያው የቀሩት 6 ጋዜጦች ብቻ ናቸው፡፡ በዘንድሮ ዓመት  ወደ ገበያው የገቡት ደግሞ በሰማያዊ ፓርቲ የሚታተመው “ነገረ-ኢትዮጵያ” እና ከተጀመረ ሳምንታት ያስቆጠረው “አፍሮ-ታይምስ” ናቸው፡፡ እንደ ሰማያዊ ፓርቲ ጋዜጣ ሁሉ መኢአድ “አንድነት” የሚል፣ አንድነት ፓርቲ ደግሞ “ፍኖት ነፃነት” የተሰኘ ልሳናት ያሳትሙ የነበረ ቢሆንም በማተምያ ቤት ችግርና በሌሎች ምክንያቶች ከህትመት ውጭ ሊሆኑ በቅተዋል፡፡

የግል ፕሬሱ ለምን ተዳከመ?

ለጋዜጦች መዘጋት የህትመት ዋጋ ንረት ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዝ የተለያዩ የጋዜጣ ባለቤቶች ይናገራሉ፡፡ በአንድ ወቅት በገበያው ጥሩ ተፎካካሪ ከነበሩት መካከል “አዲስ-ነገር” ጋዜጣን የመሳሰሉት ደግሞ ምንም አይነት የፋይናንስ ችግር ባይገጥማቸውም አዘጋጆቹ “ከመንግስት ጫና ተደረገብን” በሚል ምክንያት ዘግተው ከአገር ተሰደዱ፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የ2005 ጥናት፣የጋዜጦች ድክመቶች ተብለው ከተጠቀሱት መካከል በየጊዜው ዋጋ መጨመራቸውና የተደራሽነት ክፍተት ይገኙበታል፡፡ በጥናቱ ተሳታፊዎች ከተጠቆሙ የማሻሻያ ምክረ ሀሳቦች (recommendation) መካከል፣ፕሬሶች ፍራቻን አስወግደው በትክክለኛ መረጃዎች ላይ የተመሰረቱ ዘገባዎችን ለህብረተሰቡ በነፃነት ቢያቀርቡ፣የህትመት ዋጋን ለመቀነስ የሚያስችል ሁኔታ ቢፈጠር፣ እና መንግስት ዘርፉን የሚያበረታታ የፖሊስ እርምጃ ቢወስድ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኑኬሽን ትምህርት ክፍል ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው፤የሃገራችን የግል ጋዜጦች ሮጠው ሳይጠግቡ ግብአተ መሬታቸው ለመፈፀሙ ምክንያት ያሏቸውን ይጠቅሳሉ። ጋዜጦቹ ሰፊውን ህዝብ ተደራሽ ያላደረጉ መንደረኛ ባህሪ ያላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ብቻ ማተኮራቸው፣ ሚዛናዊ ባለመሆናቸው የእነ እከሌ ጋዜጣ ነው እስከመባል በሚያደርሱ ፍረጃ ውስጥ ራሳቸውን ከተው መገኘታቸው እንዲሁም የበሰለ ሙያዊ መሰረት የሌላቸው ወይም በትክክለኛው ባለሙያ ያለመዘጋጀታቸው ለጋዜጦቹ ውድቀት መፍጠን አስተዋፅኦ ካበረከቱ ጉዳዮች ተጠቃሽ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ በመንግስት ስርአት ውስጥም ገና በዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት ላይ መገኘቱ በራሱ ሚዲያውም በሙያ ለመዳበር፤ይበልጥ ነፃና ለብዙሃን ተደራሽ መሆን ላለመቻሉ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ዶ/ር ነገሪ ገልፀዋል፡፡

ከምርጫ 97 በፊት የነበሩት ጋዜጦች ልክ የፕሬስ ነፃነት ሲታወጅ መብቱ ምን ድረስ ነው የሚለውን ከግንዛቤ ባለማስገባት፣ራሳቸውን የመንግስት ተቃዋሚ አድርገው እስከመፈረጅ መድረሳቸውን የሚጠቅሱት ሌላው ስሜ አይጠቀስ ያሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር፤በወቅቱ የፅንፈኝነት ባህሪ ማንፀባረቃቸው ለውድቀታቸው ዋነኛው መንስኤ እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ገበያው የተቀላቀሉ አንዳንድ የፕሬስ ውጤቶችም በዘገባ አሰራር ስነ-ልኬት በሚገባ ያልዳበሩ በመሆናቸው፣ ራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ሁኔታ ለመንግስት ጫናና አፈና እንደተዳረጉ እኚሁ ምሁር ያስረዳሉ፡፡ በፋይናንስ እጥረት እስከ መዘጋት የደረሱ ጋዜጦች መኖራቸውን እንደሚያውቁ የጠቆሙት ምሁሩ፤የፋይናንስ ችግሩም የህትመት ዋጋ ንረቱም ሆነ ተያያዥ ጉዳዮች በመንግስትና በግሉ ፕሬስ መካከል የቆመው ሊታረቅ ያልቻለ የፅንፈኝነት ሃውልት ውጤት ናቸው ይላሉ፡፡

ዶ/ር ነገሪ በበኩላቸው፤ በቅድመ 97 ምርጫ ይታተሙ የነበሩ አንዳንድ ጋዜጦች አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት “ህጋዊ መንግስት አይደለም፣ ሰርቆ የመጣ ነው” የሚሉ ዘለፋዎችን መጠቀማቸው ለፖለቲካዊ ጫና ዳርጓቸዋል ይላሉ፡፡ ሙያው ገና ባልዳበረበትና ስልጣን ላይ ያለው መንግስት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮት ዓለም አራማጅ ሆኖ ሳለ፣ ሚዲያዎች የሚገባውን ብስለት ተጠቅመው ባለመስራታቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል ብለዋል – ዶ/ር ነገሪ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በመንግስት የተረቀቀውና ተግባራዊ የተደረገው የፀረ-ሽብር አዋጅ ይበልጥ በመንግስትና በግል ፕሬስ መካከል አለመተማመን መፍጠሩን ዶ/ር ነገሪ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ የሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የፈጠረው ህግ ስለሆነ፣ሚዲያዎች የኢትዮጵያ ሚዲያ እንደመሆናቸው ምዕራባዊያኑን ሳይሆን ኢትዮጵያን መምሰል እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡

በቀጣይም ቢሆን ይበልጥ የግል ጋዜጦች እንዲያብቡ ሰፊ ስራ መሰራት አለበት የሚሉት ዶ/ር ነገሪ፤ ጋዜጦች የገፅ ብዛታቸውን በመቀነስ የዋጋ ትመናቸው ዝቅ እንዲል በማድረግ፣ የሀብታም መሆናቸው ቀርቶ ድሃ ተኮር የሚሆኑበትን ስልት መንደፍ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ጋዜጦች በውስን ከተሞች ብቻ እንደሚነበቡ የጠቀሱት ምሁሩ፤ይህም የሚያሳየው ሰፊውን ህዝብ ተደራሽ አለማድረጋቸውንና ሃገር አቀፍ ባህሪ አለመላበሳቸውን ነው ይላሉ፡፡

አሁን በገበያ ላይ ያሉትንም ፕሬሶች ከውድቀት ለመታደግ እንዲሁም አዲስ የሚፈጠሩትን ተስፋ ለማለምለም የህብረተሰቡ የማንበብ ባህል መዳበር አለበት የሚሉት ዶ/ር ነገሪ፤ ህብረተሰቡ ጋዜጣ ገዝቶ ሲያነብ፣ ገንዘቡን ከምግብ በላይ ለሆነ የእውቀት ግብይት እንዳወጣው መገንዘብ አለበት ይላሉ፡፡ “ዘርፉ ሙያውን በሚያውቁትና በተማሩት ዜጎች ቢያዝ የበለጠ አዋጭ ይሆናል፣ ማደግም ይችላል” የሚሉት ዶ/ሩ፤ “በርዕሰ ጉዳይ መረጣ ወቅትም ከመንደርተኝነት ይልቅ ሃገራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት ቢያደርጉ ተመራጭ ነው” ሲሉ ይመክራሉ፡፡

“መንግስት መረጃን በሞኖፖል በያዘበት ወቅት ስለ ፕሬስ ነፃነት ማውራት አይቻልም” የሚሉት ደግሞ የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ናቸው፡፡

መንግስት መረጃን በስስት አንቆ በያዘበት ሁኔታ እነዚህ ሁሉ ሚዲያዎች ብልጭ ብለው በቅፅበት ቢጠፉ የሚያስደንቅ አይደለም የሚሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤አሁን በህይወት መቆየት የቻሉት ጋዜጦችም ቢሆኑ በብዙ መዳከር መረጃ ለማቅረብ የሚታትሩት ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡ ለምሳሌ አንድ ጋዜጣ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የበሰለ ዘገባ ሊሰራ ቢፈልግ፣የግል በመሆኑ ብቻ መረጃው ተቆንጥሮ ለቅምሻ ያህል አሊያም በተንዛዛ ውጣ ውረድ ለማግኘት ይገደዳል፡፡ የራሱ የፕሬሱ ድክመቶች ብለው የዘረዘሯቸውም አሉ፡፡ ነፃ ፕሬሱ ክህሎት ባላቸው ሰዎች የተደራጀ አለመሆኑ፣ ጋዜጣን ፅንፍ ለመያዝ እና ግለሰቦችን ለመስደቢያነት መጠቀም የሚሹ አካላት መኖራቸው–በማለት፡፡

“ስልጡን የሆነ ነፃ-ፕሬስ እንዲኖር ስልጣን ላይ ያለው መንግስት የሚያራምደው ርዕዮተ ዓለም አይፈቅድም” የሚሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ “ደርግ በግልፅ አትናገር ይላል፤ይኸኛው ደግሞ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍልን ከፍቷል፣በህገ-መንግስቱም የመናገር ነፃነትን ደንግጓል፣ በእርግጥ ይህ ድንጋጌ እየተተገበረ ነው ወይ የሚለው ለኔም ጥያቄ ነው” ብለዋል፡፡ ጋዜጦች ተደራሽነታቸው ጨምሮ ይነቃቁ ዘንድም መረጃን ያለ ስስት መለገስ፣ ክህሎቱ ያላቸው ባለሙያዎች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ማበረታታት ያስፈልጋል ሲሉ ዶ/ር ዳኛቸው አስረግጠው ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጋዜጠኞች ህብረት ፕሬዚዳንት አቶ አንተነህ አብርሃም፤ ፕሬሱ እየተዳከመና እየጠፋ ነው የሚለው አያስማማኝም ባይ ናቸው፡፡ የብሮድካስት ኤጀንሲ፣ የፕሬስ ፈቃድ ጠያቂ ቁጥር እጅግ እየጨመረ መሆኑን እየገለፀ ነው ያሉት አቶ አንተነህ፤ የጋዜጣ ኢንዱስትሪው አልተዳከመም በማለት ለማነቃቃት ይሞክራሉ፡፡ ምክንያታቸውን ሲጠቅሱም፣ አዳዲስ ጋዜጦች እና መፅሔቶች በብዛት እየታተሙ ዘርፉን እየተቀላቀሉ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ “አዳዲስ ጋዜጦችና መጽሔቶች ወደ ገበያው መቀላቀላቸውም ዘርፉ ይበልጥ እየፋፋ ነው ያስብላል” የሚሉት የህብረቱ ፕሬዚዳንት፤“ይህ ሂደት የሚቀጥለው ምን አልባት እስከ ምርጫ 2007 ድረስ ሊሆን ይችላል፤ ከዚያ በኋላ እየተቀዛቀዘ ይጠፋ ይሆን? እሱን አብረን የምናየው ይሆናል” ብለዋል፡፡

ጋዜጦች የገበያ ችግር እንዳለባቸው የጠቀሱት የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ መንግስት ሚዲያውን ከማስታወቂያ፣ ከገበያና ከስርጭት አንፃር መደገፍ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ የወረቀትና የቀለም ዋጋ ንረት እንዲሁም  የምንዛሬ እጥረት የዘርፉ ማነቆዎች እንደሆኑ ጠቅሰው፤ከአንባቢያን አንፃርም ገዝቶ ከማንበብ ይልቅ ተውሶ ማንበብ ባህል እየሆነ መምጣቱ የዘርፉ ፈተና ነው ብለዋል – አቶ አንተነህ።

በመቋቋም ሂደት ላይ ያለው “የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” ሊቀመንበር አቶ በትረ ያዕቆብ በበኩላቸው፤ የህትመት ውጤቶች ላይ ከመንግስት ከሚደርስባቸው ጫና ባሻገር፣ በንግድ ስርአቱም ለጫና ተዳርገዋል ይላሉ፡፡ “የኢኮኖሚ ችግር ከመንግስት ጫና ጋር ተደማምሮ አብዛኛዎቹን ጋዜጦች ለመዘጋት አብቅቷቸዋል” ያሉት ሊቀመንበሩ፤በቅርቡ በአንድ መጽሄት ላይ የደረሰውን ተመሳሳይ ውድቀት ጠቅሰው፣ ብዙዎቹም ለስደትና ለጉስቁልና ኑሮ ተዳርገዋል ባይ ናቸው፡፡ ወደፊት ማህበራቸው በሁለት እግሩ መቆም ሲችል፣እነዚህን ችግሮች በሂደት ለመፍታት እንደሚጥሩም አቶ በትረ ተናግረዋል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on April 7, 2014
  • By:
  • Last Modified: November 28, 2014 @ 4:03 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar