www.maledatimes.com ተስፋዬ ገ/አብና የፓንዶራው ሳጥን - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ተስፋዬ ገ/አብና የፓንዶራው ሳጥን

By   /   November 28, 2014  /   Comments Off on ተስፋዬ ገ/አብና የፓንዶራው ሳጥን

    Print       Email
0 0
Read Time:31 Minute, 47 Second

የአዘጋጁ አፍዬር ማስታወሻ፡- የዚህ ጽሁፍ ፀሐፊው – አማን ሄደቶ ቄረንሶ – በስድስት ክፍል አደራጅቶ የጻፈው እና አራቱን በፌስቡክ ገጹ አትሞ የነበረና ሁለቱን ደግሞ ጠይቀነው የላከልን ሲሆን፤ አንድ ወጥ ጽሑፍ በማድረግ አቅርበነዋል፡፡

(አማን ሄደቶ ቄረንሶ)

እንደ መግቢያ

“ ተውን አትቀስቅሱን አትንኩን በነገር፡
እኛም ትኋን በልቶን አልተኛንም ነበር።”

ስንኙን ያገኘሁት ገጣሚው ካልተገለጸው የአማርኛ ግጥም ሲሆን የአጠቃላዩን ሃተታ ይዘት ተሸክሟል ብዬ እገምታለሁ። ወደ በኋላ እንመጣበታለን። እግረ መንገዴን፡ማለት የምፈልገው ግን፡ በአማርኛ ስጽፍ የሚያስቅ ስህተት ከሰራሁ እንድትስቁ ፈቅጄላችኋለሁ ሳቁ። ተገኝቶ ነው። ከሁለት ቀናት በፊት በማህበራዊ ድህረ ገጾች ያተምኩትን ይህንን ጽሁፍ ትንሽ አስተካክዬ ነው የላኩት። እንቀጥል።

አንዳንዴ ከጓደኞቼ ጋር ስንገናኝ ስለ ተስፋዬ ገብረአብ ስራዎች አንስተን ማውጋት የተለመደ ነው። ከኦሮሞ ህዝብ አንጻር ስለ ጻፋቸው ስለ እነ የቡርቃ ዝምታ፡ ስለ ዳንገጎ /Dhangaggoo/ ፈረሶች፡ ስለ አቶ ደራራ ከፈኒ፡ ስለ ኢብሳ ገዳ፡ ስለ ታሰረው አንበሳ፡ ስለ ቀዌሳ አመጽ፡ ስለ የሻምቡ ንጉስ፡ ስለ ሮሮ እና ይቅርታ፡ ስለ ቦረና የስልጣኔ ዋሻነት እና ሌሎችም…

አንድ ቀን በ “የቡርቃ ዝምታ” እና በ “ጫልቱ እንደ ሄለን” ምክንያት በኢትዮ ብቸኛ ልጆች ስለደረሰበት እርግማን፡ ውግዘት፡ ስድብና ስም ማጥፋት አንስተን ስናወራ የሰሙን አንድ የኦሮሞ አዛውንት ሲያዳምጡን ከቆዩ በኋላ “ተስፋዬ ማለት ማነው? ለምንስ ይወገዛል?” ብለው ይጠይቁናል። ስናወራ የነበረውን ደገምንላቸው። ስለማንነቱ ብቻም ሳይሆን ስለ ውልደቱና እድገቱም ነገርናቸው። አዳምጠውን ከጨረሱ በኋላ “እንግዲያውስ ተስፋዬ ምንም አልሰራም” አሉ። “እንዴት?” አልናቸው። “እንዲህ መሆኑ ካልቀረ ትልቁን ሳጥን ነው መክፈት የነበረበት” አሉን። ትልቁ ሳጥን የትኛው እንደሆነም ጠየቅናቸው። “ምን ማለታችሁ ነው?” ብለው ጀመሩ። “ተስፋዬ እኮ የትልቁን ሳጥን ቁልፍ ነካካው እንጂ አልከፈተውም። እነዚህ ሰዎች የሚበርድላቸው እነሱ በሚያቁት ቋንቋ ትልቁ ሳጥን ሲከፈት ብቻ ነው።” አሉን። ከዚያ የኦሮሞ አዛውንት ከተለየን በኋላ ቤት ገብቼ “የተነካካው የሳጥኑ ቁልፍ” ብዬ ብጫቂ ወረቀት ላይ ጻፍኩት።

Photo-Tesfaye  Gebreab signing Ye-Jemila Enat-book

Photo-Tesfaye Gebreab signing Ye-Jemila Enat-book

በተፈጥሮዬ (የአማርኛን ጨምሮ) የማንኛውም ቋንቋ የስነጽሁፍ ውበት ይማርከኛል። በኦሮምኛዬ አሳምሬ እጽፋለሁ። አንድ ሁለት ልቦለድ መጽሃፍቶችም አሉኝ። አማርኛን ግን አነባለሁ እንጂ ደፍሬ ብዙ አልጽፍበትም። እፈራለሁ። በልጅነቴ “ሀ ሁ” ቆጠራ ላይ የመጀመሪያው “በ” እና አራተኛውን “ባ” እንዲሁም “ቢ” እና “ብ” ን ለይቶ መጥራት መከራ ነበር። በዚህም መገረፌን አልረሳም።

አንደኛ ክፍል እያለን ነበር። አንድ ቀን መምህሩ ለተወሰኑ ቀናት ፊደል ካስቆጠረን በኋላ ፊደል መለየታችንን ሊያውቅ ፈልጎ አንድ በአንድ ይጠይቀን ጀመር። የተወሰኑ ልጆች እሱን ተከትለው እንዲሉ ነገራቸው። በሁሉም ደስተኛ ባይሆንም እኔ ጋ ደረሰ። ተከትዬው እንድል ነገረኝ። “በ” ብሎ ጀመረ። “ባ” አልኩት። እንዳላስተካከልኩት እየነገረኝ “በ በል” ሲለኝ አሁንም ደግሜ “ባ” አልኩት። አሁንም ተከትዬው እንድደግም ነገረኝ። “በ” ሲለኝ አሁን ቀይሬ “ቤ” አልኩት። ሳስቸግረው ተናዶ “ባ… ! ቤ… !” እያለ ከፎገረኝ በኋላ አርጩሜ ሊያስመጣ አንዱን ልጅ ላከ። አርጩሜውም መጣ። ስራውን ሰራ። በርግጥ “በ” ን ብቻ ሳይሆን “ብ” ንም ለመጥራት ተመሳሳይ መከራ ነበር ያየሁት። እኔ ብቻ ሳልሆን ኦሮምኛ አፍ መፍቻችን የሆነ ሁሉ “ብ” ስንባል “ቢ” ነበር የምንለው። ኋላ ላይ አድጌ፡ የዚያ ሁሉ ችግር ምንጭ በቋንቋዎች መሃል ያለው የድምጾች ልዩነት እንጂ የኛ ችግር የነበረ አለመሆኑን ስረዳ በነዚያ መምህራን በጣም ነበር ያዘንኩት።

በግእዝ ፊደል ቆጠራ “ግእዝ” የሚባሉ የመጀመሪያ እና ካልተሳሳትኩ “ሳድስ” የሚባሉ ስድስተኛ ድምጾች በኦሮምኛ ቋንቋ ድምጽ የሉም። በምሳሌ ለማስቀመጥ “ባ” እንጂ “በ” ድምጽ “ላ” እንጂ “ለ”፡ “ማ” እንጂ “መ” ድምጾች በኦሮምኛ የሉም። በተጨማሪም “ቢ” እንጂ “ብ” ድምጽ፡ “ሊ” እንጂ “ል” ፡ “ሲ” እንጂ “ስ” ድምጾች የሉም። እናም ኦሮምኛ ተናጋሪዎች እነዚህን ድምጾች ለመጥራት ይቸገራሉ። የግእዝ ፊደል ለኦሮምኛና አብዛኛዎቹ ኩሽ ህዝቦች ቋንቋዎች የማይሆንበት አንዱ ምክንያትም ይህ ነው።

ሌላው፡ በልጅነቴ ስለ አማርኛ የማልረሳው “ፍሰሃ” ተብሎ ስለሚጠራው ልጅ ስም ነበር። በሙሉ ማለት የሚቻል የኦሮሞ ተማሪ በትክክል መጥራት ከማይችላቸው ስሞች አንዱ ፍሰሃ ነበር። “ፍሰሃ” ን “ፊሳ” ነበር የምንለው። “ፊሳ /fiissaa/” ቃሉ በኦሮምኛ ፍቺ ስላለው ለመጥራት አንቸገርም ነበር። “ፊሳ /fiissaa/” በኦሮምኛ የሚያፏጭ ማለት ነው። አማርኛ ተናጋሪዎች እኛ “ፊሳ” ብለን ስንጠራ ይስቁብን ነበር። “ፊሳ” እያሉም ይተርቡን ነበር። ያኔ ፍሰሃን “ፍሰሃ” ብሎ እንደ አማርኛው አስተካክሎ መጥራት በአንዳንድ መምህራን ሳይቀር የእውቀት መለኪያ ተደርጎ የሚታይበት ዘመን ነበር። የማልረሳው ያልኩት ግን ፍሰሃን “ፍሰሃ” ብዬ ለመጥራት አንድ ቀን ያየሁት መከራ ነው። በዚያን ቀን ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ገብቼ “ፍሰሃ” ን፡ ሞቼ ተሟሙቼ ተለማምጄ በሚቀጥለው ቀን አስተካክዬ ለማጥራት በመቃረቤ ተጨብጭቦልኝ ነበር። ሌሎችም የኔን አርአያ እንዲከተሉ ሲነገራቸው የተሰማኝ ኩራት ታላቅ ነበር። አማርኛን መውደድ ጀምሬም ነበር።

ሆኖም እኔና አማርኛ ወድያው መልሰን ተቀያየምን ብቻ ሳይሆን ተጣላን። ፍቅራችን በአንድ አጋጣሚ ተበላሸ። ተቆራርተን ባንቀርም ጠጠር እንደ ገባው ጫማ እየቆረቆረኝ እስከመጨረሻው ዘለቅን። ለኔ የሚሆን ጥሩ የአማርኛ መምህርም ጠፋ። ጥሩዎች ቢኖሩም ለኔ ጥሩ አልነበሩም። ነገሩ የሆነው ሁለተኛ ክፍል ስማር ነበር። በዚህኛው ቀን ደግሞ መምህሩ በአማርኛ አረፍተነገር እንድሰራ ጠየቁኝ። እኔ ግን፡ እንኳን አረፍተነገር ልሰራ ቃሉንም አላውቀውም ነበር። መምህሩ በዘመኑ መምህራን ሞገስ ጥያቄውን ደገመልኝ። ያኔ፡ ለመምህር መልስ ሲሰጥ ቆሞ በመሆኑ ተነስቼ ቆምኩ። መልስ ግን አልነበረም። መምህሩ መልስ ጠብቆ ሲያጣ “ሰነፍ!” እያለ አከታትሎ አርጩሜውን አንጣጣብኝ። ያኔ የተገረፍኩት ዛሬም ያመኛል ብል ማጋነን ነው አትሉኝም። ከዚያ ቀን ጀምሮ አማርኛን ጠላሁት። እሱም ጠላኝ መሰለኝ ማትሪክ ላይ እንኳን ከኤፍ /መውደቂያ ውጤት/ ያመለጥኩት ለጥቂት ነበር። የ “ዲ /D/” ውጤት ካርዴ ላይ ሳይ ግን አልደነገጥኩም። ከኔና ከአማርኛ ዝምድና ሲመዘን በርግጥ ውጤቱ የሚያመረቃ ነበር። ይሁንና ከዚህ በፊት አማርኛን ምን ያህል እንዳስቸገርኩት አላውቅሁም። አሁንም ይኁው ማስቸገሬን አልተውኩም። በዚያ ላይ እናንተም “ድፈር” ብላችሁኛል። ይሄው ደፍሬያለሁ።

ወደ ቁም ነገራችን እንመለስ። የተነካካው የሳጥኑ ቁልፍ ላይ ነው ወደ ትዝታ ጎራ ያልነው። እንቀጥል።

በአንድ ወቅት፡ ተስፋዬ ገብረአብ፡ አበበ በለው ከሚባል የሬድዮ ጋዜጠኛ ጋር “የቡርቃ ዝምታ” መጽሃፍን በተመለከተ ቃለምልልስ አድርጎ ነበር። በዚያ ቃለምልልስ ላይ አበበ በለው “የቡርቃ ዝምታ” ኦሮሞንና አማራን የሚያጋጭ መጽሃፍ መሆኑንና በመጽሃፉ ላይ የተለያዩ ነጥቦችን ከተስፋዬ ጋር ካነሱ በኋላ ተስፋዬ መልሶ ጥያቄ ጠየቀው። ቃል በቃል የተስፋዬ ጥያቄ “አበበ በለው፡ኦሮምኛን ታውቃለህ?” የሚል ነበር። የጋዜጠኛ አበበ መልስም አጭር ነበር። “አላውቅም!።” መለሰ ተስፋዬ። “ችግሩ ያ ነው።” ብሎ ነገረው። በተጨማሪም ቋንቋውን ችሎ፡ የኦሮሞ ህዝብ ውስጥ ዞሮ የኦሮሞን ህዝብ ስሜት የማዳመጥ እድል ቢያገኝ በ “የቡርቃ ዝምታ” እንደማይበረግግ በሚያውቀው አማርኛ ነገረው። ከዚህ የምንረዳው ሃበሾች ኦሮሞን ግፍ ፈጸሙበት እንጂ አያውቁትም።

አዛውንቱ እንዳሉት፡ ተስፋዬ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የደረሰውን ግፍ ነካካው እንጂ መች ነካው። እኔም “ተስፋዬ ገ/አብና የፓንዶራው ሳጥን[1]” ብዬ ስጀምር፡ በዚህ አጭር መልእክት እነዚያ የተከመሩ ግፎችን ለመንካት አይደለም። ያ፡ ራሱን የቻለ ትልቅ ፕሮጀክት ነው። ቢሆንም የኦሮሞ ምሁራን ማለት እነ ፕሮፌሰር መሃመድ ሃሰን፡ እነ ፕሮፌሰር አባስ ሃጂ፡ እነ ፕሮፈሰር አሰፋ ጃለታ፡ ከዚህ ቀደም ይህንን የፓንዶራ ሳጥን ከፍተው ነካክተዋል። መጽሃፍ ሳይጽፉ ራሳቸው መጽሃፍ የሆኑ እንደነ ዶ/ር ገመቹ መገርሳ ሲነካኳቸው የፓንዶራውን ሳጥን ከፍተው ይነካሉ። ከውጭ ደግሞ፡ የሪቻርድ ፓንክረስት፡ የጆን ማርከኪስ፡ እና የፕ/ር አስመሮም ለገሰ መጽሃፍት ስለ ፓንዶራው ሳጥን በጣም ግዙፍ የሆነ ግንዛቤ ይሰጣሉ። የኔ አነሳስ፡ ግን ተስፋዬ ስለ ኦሮሞ በመጻፉ ከሚደርስበት ውግዘትና ርግማን አኳያ የተሰማኝን ለማለት ፈልጌ እንጂ ትልቁን ሳጥን በዚህ አጭር ሃተታ ላነሳ ፈልጌ አይደለም። እንደዚያ ከተግባባን እንቀጥላለን።

ከላይ እንዳልኩት ዛሬ አማርኛ የራሱ ያደረገኝ ሰው ባልሆንም መጥፎ የምባል አይደለሁም። በአማርኛ የሚጻፈውን ማንበብ የጀመርኩት በተስፋዬ ስራዎች ባይሆንም ዛሬ ስራዎቹ የበለጠ እንዳነብ አድርገውኛል። የሆነ ሆኖ “የተነካካው የሳጥኑ ቁልፍ” በተስፋዬ ብእር ቢነካካ ብዬ ተመኘሁ።

“የአለማችንን ምርጡን ቋንቋ የተማርኩት ከእናቴ ነው”

በመግቢያው ለመነካካት እንደተሞከረው፡ በኢትዮጵያ የሚኖሩ አማርኛ ተናጋሪ ያልሆኑ ህዝቦች ባለፉበት የዘመናት ሂደት በአማርኛ ቋንቋ የደረሰባቸው በደል ቀላል አልነበረም። ይህን ስንል ግን በምንም ይሁን በምን የተማሩት የአማርኛ ቋንቋ በፍጹም አልጠቀማቸውም ማለት አይደለም። ቋንቋ መሳሪያ ነውና ህዝቦች ይጠቀሙበታል። ይግባቡበታል። በተጨማሪም የሌሎችን ህዝቦች ቋንቋ ለማይናገሩ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መልእክቶቻቸውን ማስተላለፍ በመቻላቸው መልእክቶቻቸውን ማስተላለፍ ከማይችሉት ይሻላሉ ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን፡ ከአማርኛ በስተቀር ሌሎች የአገሪቱን ቋንቋዎች የማይችሉ፡ የገዢዎች መዘምራን የነበሩና ዛሬም ለዚያው የሚታገሉ ወገኖች ሌሎች በአገሪቱ የሚነገሩ ቋንቋዎችን አለማወቃቸው የጠቀማቸው አይመስለኝም። ምክኒያቱም አማርኛን ለማያውቁ የዚያ አገር ህዝቦች መልእክቶቻቸውን ሊያስተላልፉ አይችሉም ነበርና። ያ ችግር ዛሬም አብሯቸው አለ። የተቀየረው ዘመን ብዙ ነገሮችን የቀየረ ከመሆኑ አንጻር ደግሞ ችግሩን የበለጠ አክብዶታል።

በሌላ በኩል ማንኛውንም ቋንቋ ማወቅ አይጠቅምም ይሆናል። እንደማይጎዳ ግን አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ። የሚጎዳ ከሆነ ግን (በኛው አገር ሲሆን እንደነበረው) ህዝቦች ህግ ፊት ቀርበው፡ በማያውቁት ቋንቋ ተዳኝተው ፍትህ ሲያጡ ነው። ያ ቋንቋ ሌሎችን ቋንቋዎች ለማጥፋት ከሰራ ነው። ህዝቦች በሚችሉት ቋንቋ ትክክለኛ ስሜታቸውን እንዳይገልጹ የስነልቦና ጫና በመፍጠር ጭምር በአደባባይ እንዳይነገር መከልከል ነው። ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ “የስደተኛው ማስታወሻ” በሚል ርእስ ባሳተመው መጽሃፉ፡ “ጫልቱ እንደ ሄለን” በሚለው ንኡስ ርእስ፡ በዚያ አገር ይደርሱ የነበሩ በደሎችን በጫልቱ ሚዳክሳ (Caaltuu Midhaksaa) በኩል በተባ ብእሩ አስነብቦናል። ጫልቱ ላይ የደረሰው መከራ (የቋንቋን ተጽእኖ ጨምሮ ማለት ነው) እስከ ህይውቷ ፍጻሜ የተከተላት ነበር።

የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ ከላይ በመግቢያው ካነሳው ሌላ “የጫልቱ ሚደክሳን ያህል ከባድ አይደለም” ሊባል የሚችል ሌላም (የአማርኛ ቋንቋ ተጽእኖ) ገጠመኝ ነበረው። ገጠመኙ የቋንቋን ተጽእኖ የሚያሳይ ሲሆን የሆነው በደርግ ዘመን ነበር። ልጁ በ6 አመቱ ት/ቤት አንደኛ ክፍል ይገባል። እንደሚታወቀው በዘመኑ ተማሪዎች ክፍል ውስጥ ስማቸው የሚጠራው በቁጥር ነበር። በመጀመሪያ ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት የሚጠሩበት ቁጥር በአማርኛ ይነገራቸዋል። በክፍል ውስጥ ወደ 87 ከሚሆን ተማሪ የዚህ ልጅ የክፍል ቁጥር 34 ነበር። አማርኛን የማያውቀው ይህ ልጅ “34 ቁጥሩ” ከነ አራት፡ አስራ አራት፡አርባ አራት፡ ሃምሳ አራት ወዘተ ጋር ተምታቶበት ሲጠራ “አቤት” ሳይል ይቀራል። መምህሩ ለአራት ቀናት በቁጥሩ ጠርተው ሲያጡት በአምስተኛው ቀን በስሙ ለመጥራት ይሞክራሉ። የሚገርመው ስሙም ሲጠራ ተደናገረ። ስሙ “ጉተማ /Gutama/” ነበር። እሱንም ቀይረው “ከተማ” ብለው የበለጠ አደናገሩት። እናም “ከተማ” ተብሎ ሲጠራ ስሙ ስላልሆነ ዝም አለ። መምህሩ ለአራት ቀናት የት እንደነበረ ብቻ ሳይሆን ሲጠራ ለምን “አቤት” እንዳላለ በማያውቀው አማርኛ ያምባርቁበታል። መልስ አልነበረም።

አፉን በፈታበት ቋንቋ ቁጥር መለየት የማይችል ልጅ አልነበረም። በሚያውቀው ቋንቋ ቢጠየቅ “ስሜ ከተማ ሳይሆን ጉተማ ነው” ብሎ መመለስ የማይችል ልጅም አልነበረም። በማያውቀው ቋንቋ የተጠየቀውን ባለመመለሱ ግን ተገረፈ። አልቅሶም ዝም ይላል። በኋላም 34 ቁጥሩን ጠብቆ አቤት እንዲል አሁንም በዚያው በአማርኛ ከማስጠንቀቂያ ጋር ይነገረዋል። ያች የተረገመችዋ 34 ቁጥር ከዚያ በኋላም ማምታታቷ አልቀረም። ልጁ ግን እነኛን አራቶች መለየት ባይችልም በሚቀጥለው ቀን ላለመገረፍ በልጅነት አእምሮው መላ ዘየደ። አራትና የአራት ዘሮችን (አራትን፡ አስራአራትን፡ ሃያአራትን፡ አርባአራትን፡ ሃምሳአራትን…) በሙሉ ጠብቆ አቤት ሊል ወሰነ። በመሃል ያች መዘዘኛዋን ቁጥር አግኝቶ ከመመታት ይድናልና። ለሶስት ቀናት ችግሩን በዚያዉ ዘዴ ከተወጣ በኋላ በአራተኛው ቀን ተያዘ። “ይሄ ልጅ ሁሉንም ቁጥር አቤት ይላል” ብለው አማርኛ ተናጋሪ ልጆች ጠቆሙት። ዛሬም ግርፍ ሆነ። በቃ! የዚያ ልጅ የትምህርት አለም እዚያ ላይ አከተመ። ልጁ ወደ ት/ቤት እንዲመለስ በቤተሰብ ቢገደድም አሻፈረኝ አለ። ወደ /ቤት እንዲመለስ በቤተሰብ የተገረፈው ግርፍ ምናልባትም ት/ቤት ከተገረፈው ይበልጥ ነበር፡ አልተሳካም እንጂ።

በርግጥ ነገሩ የሚያስቅና ቀላል ሊመስል የሚችል ነው። ነገር ግን ቢማር፡ ቢያንስ በኑሮው የተሻለ ሰው ይሆን ይችል የነበረ ልጅ የማያውቀው ቋንቋ ባደረሰበት ተጽእኖ በምናውቃት አገር /ኢትዮጵያ/ አፈር ገፊ /ገበሬ/ ሆኖ ቀረ። (ልጁ የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ ወንድም ነው። ሁነቱ አሳዛኝ ቢሆንም ዛሬም ድረስ በቤተሰብ ውስጥ ከትውስታ መሳቂያዎች አንዱ ነው።) የህዝቦችን ህይወት ያበላሹ፡ ከዚህና ከ “ጫልቱ እንደ ሄለን” የከፉትን ብዙ ማንሳት ይቻላል። ተስፋዬ ገብረአብ ከፓንዶራው ሳጥን ግፎች አንዷን ሰበዝ መዞ፡ከላይ ያነሳሁትን ማለት ”ጫልቱ እንደ ሄለን” ን አቅርቦልን ነበር። ይህ ጸሃፊም፡ በዚህ አጋጣሚ፡ “የስካር መንፈሱ ፊርማ” በሚል ርእስ አንዷን ከፓንዶራው ሳጥን መዞ ወደፊት ሊያቀርብላችሁ ቃል ይገባል።

በሌላ በኩል፡ ማንኛውም የሰው ልጅ ከየትኛውም ቋንቋ በላይ የሚመቸው አፉን የፈታበት ቋንቋ ነው። አፉን የፈታበት ቋንቋ ከምንም ይበልጥበታል። ይህን ስንል ግን ሌላውን ቋንቋ ይጠላል ማለት አይደለም። ነገር ግን በኛ አገር አማርኛ ተናጋሪ ያልሆኑ ህዝቦች አማርኛን ትተው የእናት አባቶቻቸውን ቋንቋ ሲጠቀሙ፡ በአማርኛ ቋንቋ ጥላቻነት ይፈረጃል። አንዳንዴ፡ በጠባብነትም ያስፈርጃል። በርግጥ ህዝቦች አፋቸውን ባልፈቱበት የአማርኛ ቋንቋ ትክክለኛ ስሜታቸውን ማስተላለፍ ሳይችሉ ሲቀሩ “ተብታባ” እየተባሉ ሲሰደቡ መኖራቸውና በአማርኛ ሌሎችን ቋንቋዎች ለማጥፋት ሲሰራ የኖረው በደል በቋንቋው ላይ የራሱን ተጽዕኖ ማሳረፉ ባይቀርም ህዝቦች የእናት አባቶቻቸውን ቋንቋ አጥብቀው የሚፈልጉት ግን የአማርኛን ቋንቋ ስለሚጠሉ አይደለም። እውነተኛ ስሜታቸውን መግለጽ የሚችሉት አፋቸውን በፈቱበት ቋንቋ በመሆኑ እንጂ። ልጅት ነበረች አሉ፡ በአንድ ወቅት። “የአለሙን ምርጥ ቋንቋ የተማርሽው ከማነው?” ስትባል “የአለማችንን ምርጡን ቋንቋ የተማርኩት ከእናቴ ነው” አለች ይባላል።

ከትክክል በላይ የሆነ አባባል

እ አ አ 1991! ደርግ በወደቀበት ዘመን! ዛሬም የሰዉ ህይወት የማይበላ ስረዐት በኢትዮጵያ ምድር ባይፈጠርም፡ የዛሬ ሃያ ሶስት አመታት ገደማ፡ ሰው በላው የደርግ ስረዐት በመወገዱ ህዝቦች የሰላም አየር መተንፈስ የቻሉበት ወቅት ነበር:: ለዘመናት ታፍነው የነበሩ ህዝቦች የተካደ ማንነታቸውን መልሰው ያገኙበት ወቅትም ነበር:: ለውጡ ለዘመናት የቆዩ የህዝቦችን ጥያቄዎች እስከተወሰነ ደረጃ የመለሰም ነበር:: በራስ ቋንቋ የመናገር፡ በራስ ባህል የመኩራትና ማንነትን የመግለጽ መብቶች የሚደነቁ ባይሆኑም የሚናቁ አልነበሩም:: ለዘመናት የኖረው የዚያ ምድር ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚፈታ መስሎ ነበር:: በወቅቱ የደርግ ስረዓትን የተካው ወያኔ ኢህአዲግ ከሁሉም በላይ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን ለማስፈን ምሎ የሚገዘት የነበረ በመሆኑ ብዙ ተስፋ ተሰንቆ ነበር:: አዎን! ወያኔ/ ኢህአዲጎች የተራቡ አንበሶች ከመሆናቸው በፊት ለዘመናት ሲጨቆኑ ለኖሩ ህዝቦች የተሻሉ መስለው ነበር። ነገር ግን በጠመንጃ ያገኙትን ስልጣን ዴሞክራሲ ለተባለው ቀልድ እንደማያስረክቡና ማስረከብም እንደማይችሉ ለሁሉም ቃል ገቡ::

እንኳን ለሃገሪቱ ችግሮች መፍትሄ መስጠትና የተጠበቀው የህዝቦች ነጻነትም መንፈቅ ሳይሞላን የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ:: ቃሉም ቃል እንደሆነ ዛሬ ደረስን:: ህዝቦች ከአንዱ ጨቋኝ ወደ ሌላ ጨቋኝ ተሸጋገሩ። መንግስት ማፍያ ገዳዮችን በመዋቅሩ ውስጥ አስመሸገ። ዛሬም እንደመሸጉ ነው። አልሞ ተኳሽ ገዳዮች ከደርግ የሚብሱ እንጂ የሚያንሱ አልነበሩም፡ ዛሬም አንደነበሩ አሉ። ባጭሩ ጉልቻዉ ተለወጠ፡ እሳቱ እንዳለ ሳይነካ ተቀመጠ። የእስር ቤት በር ጠባቂዎች ተቀየሩ፡ እስር ቤቶች መታደስ ጀመሩ። ዛሬም ይታደሳሉ። የእስር ቤት በሮች ከአገሪቱ ድንበር በላይ ይጠበቃሉ። ይህ የአገሪቷን ህዝቦች በጠላትነት የመፈረጅ፡ እንደ ውጭ ጠላት የመፍራትና የመጠበቅ ስራ ደግሞ ዛሬ አገሪቷን እየገዛ ባለው ወያኔ/ኢህአዲግ የተጀመረ እንዳልሆነ ይታወቃል።

በአንድ አገር የሚፈጠሩ ችግሮችም ሆኑ በህዝቦች መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶች በአብዛኛው የአስተዳደር ብልሹነት ውጤቶች ናቸው:: እነዚህ ችግሮችና አለመግባባቶች ደግሞ ለሰላም መደፍረስ፡ ለህይወትና ንብረት መጥፋት መነሻ ምክንያቶች ሆነው ባለማችን ለዘመናት ኖረዋል:: ዛሬም አሉ:: ይሁንና ብዕርተኛው የኦሮሞ ብሄረተኛ ሞቲ ቢያ በአንድ ወቅት እንዳለው ‘ባለንበት ዘመን ጤናማ አመለካከቶች በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች እየጎለበቱ ያሉ ቢሆንም ወደ ኋላ ቀርተው በዘመናት ግፊት ከመጣው ለውጥ ፊት ቆመው የሚጨቃጨቁ ወገኖች ዛሬም በሽበሽ ናቸው::’[2]

እና በ19ኛው ክ/ዘ መጨረሻ አካባቢ በግፍ የተመሰረተችውን ኢትዮጵያን እያስቸገራት ብቻ ሳይሆን ሊያጠፋትም ያለው የወያኔ/ ኢህአዲግ የአስተዳደር ብልሹነትና የግፍ አገዛዝ ብቻ አይደለም:: ኢትዮጵያ በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተች አገር አለመሆኗም አይደለም:: በአመሰራረቷ ሂደት በህዝቦች ላይ የተፈጸመው ግፍ እስከዛሬም አለመቆሙ ብቻም አይደለም:: አገሪቱ የተመሰረተችበትን አዳፋ ታሪክ በስሙ መጥራት የለመቻል ችግር ብቻም ሳይሆን በህዝቦች ላይ የተፈጸሙ ዘግናኝ ግፎችን እንደ ጀግንነት የሚቆጥሩ፡ እንደ ቅዱስ ስራ የሚሰብኩ፡ ካልሆነም ለመካድ የሚሞክሩና በህዝቦች ማንነት፡ መብትና ነጻነት የሚያላግጡ ወገኖች ፖለቲካ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወተ ነው::

በንጉሱ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ጋሽ አክሊሉ ሃብተወልድ ኦሮሞን ቢያንስ በአንድ ክፍለ ዘመን ወደ ኋላ አስቀርተው መምራትና የህዝቦችን ማንነት ጨፍልቀው የአማራን ማንነት ለመፍጠር ይመኙ እንደነበረ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ፈጥረን የምናወራው ሳይሆን ከአንደበታቸው የወጣ የግላቸው ምስጢር ነበር። ለሚያምኑት ሰው የሚያዋዩት የነበረ የአገር ጉዳይ!!

በንጉሱ ዘመን በትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩት የአቶ ተድላ ሃይሌ አባት፡ ጋሽ ሃይሌ ጸዳሉ የኦሮሞን ማንነት በአማራ ውስጥ ለማቅለጥ ተግተው ሲሰሩ የነበሩ ነበር። ለዚህም ልምድ ለመቅሰም ወደ ፈረንሳይና ቤልጂየም ሲመላለሱ በነበረበት በዚያ ዘመን(ወደ በኋላ ዝሆኑን መግደሉ ባይሳካላቸውም)ወደ እንግሊዝም ጎራ ብለው ጆርጅ ኦርዌል እንግሊዞች በህንዶች ላይ ይፈጽሙ የነበረውንና “Killing the Elephant” ብሎ የጻፈውን ሳያነቡ እንዳልቀሩ እንገምታለን። እኚህ የኢትዮጵያን ቀደማዊነትና አንድነት ለማጽናት የአረመኔዎችን ቋንቋዎች በህግ አግደውና አስወግደው ግእዝና አማርኛ በአገሪቱ እንዲነግሱ ይሰሩ የነበሩ ሰው ነበሩ።

ይሄም የጥቂት ጠባቦች የፈጠራ ስራ ቢባል አንገረምም። እና ዛሬ በህዝቦች መብትና ነጻነት የሚያላግጡ ወገኖች የነ ጋሽ አክሊሉ፡ የነ ሃይሌ ጸዳሉ እና የልጃቸው የነ ልጅ ተድላ ሃይሌ መዘምራን ናቸው። ይሁንና “የህዝቦችን ማንነት ማጥፋት” የሚለው የነ ጋሽ አክሊሉ ውጥን በዘመኑ ሊሆን የሚመስል ሆኖ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እነ ጋሽ አክሊሉ በሚቻል ዘመን ያልቻሉትን የዛሬዎቹ ልጆች ወይም የልጅ ልጆች በማይቻልበት ዘመን ዛሬ ሲሞክሩት ያሳዝናል።

የሆነው ሆኖ ያ “የአንድ ብሄር፡ የአንድ ቋንቋ፡ ያንድ ባህል: ያንድ ማንነቱ” የፖለቲካ ቅኝት የመጨረሻው መጨረሻ የደርግ ስረአት ነበር። ደርግ በመውደቁ ለዘመናት ሲያቀነቅኑት የነበረው የአሃዳዊው ስረዓት ጀርባም አብሮ ተመታ። አቀንቃኞቹ ግን አላረፉም። በርግጥ “አርፈው ይቀመጣሉ” ብሎ ያሰበም አልነበረም። ለዘመናት በጠመንጃ ሊያጠፉ ያልቻሉትን የህዝቦች ማንነት በብዕራቸው ቆፍረው ሊቀብሩ የደርግን መለዮ አውልቀው ጥለው በጓሮ በር ዞረው ሲመጡ ግን የተሸወደ አልነበረም። በርግጥ አካሄዳቸውም የሚሸውድ አይነት አልነበረም። የተለመደው “የአባቶች አደራ” መፈክራቸውና 3001 የማይሞላው “የ3000 ዘመናት” ትረካቸው ለማንም ግልጽ ነበር። እያወቀ የሚያምታታ ብቻ ሳይሆን ሳያውቅ የምምታታም ሳይቀር “የጎሳ ፖለቲካ አገር አመሰ” እያለ የጋዜጣና መጽሄት ላይ ጩኅቱን ተቀላቀለ።
እዚህ ጋ ቆም ብለን “ጎሳ” የሚለውን ቃል እንመልከት። ቃሉ የተወሰደው ከኦሮምኛ ቋንቋ ነው። ትርጉሙም ከኦሮሞ ህዝብ በጣም ንኡስ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል ነው። ስለ ቃሉ ትርጉም የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ከሁለቱ የኦሮሞ የዘር ግንዶች (ቦረናና ባሬንቱ /Booranaa fi Bareentuu) ስንነሳ እንደሚከተለው ይሆናል። በኦሮሞ ሁለቱም (ቦረናም፡ባሬንቱም) ጎሳ አይደሉም። ለምሳሌ መጫና ቱለማ የቦረና ቅርንጫፎች ናቸው። እነሱም ጎሳ አይደሉም። እነ ባሬንቱ እነ አርሲን፡ እነ ኢቱንና፡ ወሎ የመሳሳሉትን ያቅፋል። እነሱም ጎሳ አይደሉም። አሁንም የአንዱን ጫፍ ስበን እንይ። አርሲ ሁለት ልጆች አሉት። ሲኮ እና ማንዶ (Sikkoo fi Mando) ተብለው የሚጠሩ። እነዚህም ጎሳ አይደሉም። አሁንም ይወርዳል። የሲኮ ልጆች አምስት ናቸው። ሻናን ሲኮ (አምስቱ የሲኮ ልጆች /hanan sikkoo) በመባል ይታወቃሉ። ማንዶ ሰባት ልጆች አሉት። ሰባቱ መንዶዎች (torban Mandoo) ይባላሉ።

እንግዲህ በኦሮምኛ ቋንቋ፡ የሲኮና የማንዶ ልጆችም ሳይሆኑ ከዚያ በታች ያሉት ልጆቻቸው ወይም የልጅ ልጆቻቸው ናቸው ጎሳ ተብለው ሊጠሩ የሚችሉት። የቃሉ ትርጉም “የጦቢያ ልጆች” ማለት የፈለጉትን ባይገልጽም እነሱ ዘንድ ኦሮሞም፡ ትግሬም፡ ሶማሌም፡ ጎሳ ናቸው። የሚገርመው ግን እነዚህ ሰዎች ሌሎችን ህዝቦች “ጎሳ” ብለው የሚጠሩትን ያህል የአማራን ህዝብ “ጎሳ” ሲሉ ብዙ አናይም። ነብሱን ይማረውና ጥላሁን ገሰሰ በሞተበት ወቅት በማንነቱ ላይ ኦሮሞና አማራ ተወዛግበው ነበር። ኦሮሞች፡ ጥላሁን እናቱ ከመጀመሪያ ባሏ፡ ከአባቱ ስትለይ፡ ገሰሰ ንጉሴ የሚባል ሰው አግብታ ተቀየረ እንጂ ትክክለኛ ስሙ “ደንደና አያኖ ጉደታ” እንደነበረ ማስረጃ እየጠቀሱ ይከራከራሉ። በአንጻሩ አማሮች ጥላሁን፡ ገሰሰ፡ ንጉሴ፡ የኋላዬ፡ ዘ ብሄረ ቡልጋ፡ ብለው ወደ ሰሜን ይወስዱታል። ታድያ በወቅቱ “ዘ ብሄረ ቡልጋ” የሚለው ስም የገረመው አንድ ኦሮሞ “ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ወደ ጎሳ በወረዱበት እንዴት እንዴት ሆና ቡልጌ ብሄር ሆነች?” ሲል ጠይቆ ፈገግ አሰኝቶን ነበር።

እነዚህ የኢትዮጵያ ብሄረተኞች (በቅንፍ ሳይሆን በሽፍን የአማራው ብሄረተኞች) የአማራን ስም ጎሳ ብለው አይጠሩም። ይህን ስንል ግን በጣም የጨከኑ የሉም ማለት አይደለም። አልፎ አልፎ እንሰማቸዋለን። ቁም ነገሩ ግን “ለምን ራሳቸውን ጎሳ ብለው አልጠሩም?” ሳይሆን ለራሳቸው የማይፈልጉትን ለምን ሌላውን ይጠሩበታል ነው። ለነገሩ እነሱ ሌላውን መች በስሙ ጠርተው ያውቃሉ። ስራቸው መለጠፍ ነው። በርግጥ አያቶቻቸውና አባቶቻቸውም ኢትዮጵያን የፈጠሩት (ዛሬ ዛሬ ባይበጃትም) በዚሁ ልጠፋ አይደል!! ከጠመንጃው በተጓዳኝ ጨካኝ! አረመኔ! ያልሰለጠነ! እያሉ። የሚያሳዝነው፡ የነዚያ አያቶችና አባቶች የሆኑት የዛሬዎቹ የልጅ ልጆችና ልጆች የዘመኑን ቅኝት ማወቅ ተስኗቸው በዚያው ልጠፋ አገሪቱን ለማኖር መሞከራቸው ነው።

ወደ ደርግ ዘመን ውድቀት ድራማቸው እንመለስ። በወቅቱ ስለተጨቋኝ ህዝቦች መብት ደግ እንዲያወሩ ባይጠበቅም ሌላው ቀርቶ ወያኔ/ኢህአዲግ እንደ ዲሞክራሲ ማሳያ ወስዶ ህዝቦችን የሚያጭበረብርበትን ሽርፍራፊ መብቶች እንኳን መቀበል አቃታቸው። ብእራቸውንና ምላሳቸውን አሹለው በወቅቱ ነጻ ፕሬስ የተባለውን መድረክ ለማጣበብ ጊዜ አልወሰደባቸውም:: መፈክራቸው ያገር አንድነት ነበር:: የሃገርን አንድነት ጥቅም አለነሱ የሚረዳ የሌለ ያህል ጮሁ:: በርግጥ ዛሬም ይጮሃሉ። ጩኅታቸው ለእውነተኛው የአገር አንድነት ከማሰብ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ክፋት አልነበረውም:: ዞር ብሎ ላስተዋለ ግን የነሱ አንድነት ሌላ ነው:: የአንድ ህዝብ፡ የአንድ ቋንቋ፡ የአንድ ባህልና የአንድ ብሄር አገር! የነሱ የበላይነት የነገሰበት አንድነት! የእነ ጋሽ አክሊሉ ሃብተወልድ ፍልስፍና! የነ ጋሽ ተድላ ሃይሌ ህልም!

ስለዚህ ሲደሰኩሩ ደግሞ ያኔ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ሁሉም የሚያምናቸውና የሚቀበላቸው ይመስላቸዋል:: ወይንም ደግሞ ይመስላሉ። እርግጥ በአንድ ወቅት፡ ይናገሩ የነበረውን ያለምንም ማንገራገር እንዲቀበል የሚያስገድዱት ትውልድ ነበር:: አንድ ዘመን ሰብስበው አስገብተው ከኋላ ቆልፈውብንም ነበር። ህዝቦች ዛሬም በሌላ አሳሪ እጅ ቢሆኑም ከነሱ እስር ቤት ወጥተዋል። ዛሬም በነሱ እስር ቤት ያለ የጠፋ በግ ባይጠፋም ህዝቦች የነሱን እስር ቤት ለቀዋል። እስረኞቹ ከእስር ቤቱ መውጣታቸው ብቻ ሳይሆን የእስር ቤቱን ቁልፍም በተወሰነ ደረጃ ጨብጠዋል። ዛሬ ትላንት ሊሆን ይችላል:: የጊዜ ሂደት ግን በአንድ አቅጣጫ ብቻ ነው። ወደ ኋላ አይቆጥርም። እናም ትላንት ዛሬ ሊሆን አይችልም:: ያ ብቻም አይደለም። ዘመኑም ተቀይሯል:: ጊዜው ደርሶ፡ ሲሰሩ የኖሩት ግፍ ከውስጥ ወደ ውጭ መገልበጥ ጀምሯል።

ተስፋዬ ገ/አብ ላይ የሚዘምቱት ያን፡ ከውስጥ ወደ ውጭ መገልበጥ የጀመረውን፡ በጣም ትንሹን ስእል በቋንቋው አሳያቸው። በቃ! “ተስፋዬ ገ/አብ የሚባል የኢትዮጵያ ጸር ለያንዳንዱ ኦሮሞ ጠመንጃ አድሎ አማራ ላይ አሰማራ!” የሚል ፈሊጥ ተነዛ። የተስፋዬን እውነት ፈላጊ ጥበበኛ ብእር እንፈልጋለን። እናደንቃለንም። ከዚህ በኋላም የተደበቁ እውነቶችን ፈልፍሎ አውጥቶ ለአንባቢ እንደሚያቀርብ እናምናለን፡ እንጠብቃለን።

አውቀው ለሚያምታቱትም ሆነ ሳያውቁ ለሚምታቱት፡ ማለት የምንፈልገው ግን ኦሮሞ ለነጻነቱ መታገል የጀመረው የቡርቃ ዝምታን አንብቦ አለመሆኑን ነው። በ “ጫልቱ እንደ ሄለን” ታሪክ ወደ ዱላ የሚሮጥ ህዝብ አይደለም። ኦሮሞን ሊያነሳሳው የሚችለው ያለፈው ግፍ ታሪክ ሳይሆን የዚያ ክፉ ታሪክ አምላኪ ዘማሪ ነው። እነዚህ ወገኖች ባለፉት ዘመናት ቅድመ አያቶቻቸውና አባቶቻቸው በህዝቦች ላይ በሰሩት ግፍ ብቀላ ይፈጸምብናል ብለው መፍራት አልነበረባቸውም። ምኒልክ በሰራው ግፍ ልጆቹ ወይም የልጅ ልጆቹ ይጠየቁ የሚል ኦሮሞ የለምና። በራሱ እግር የሚሄድና በምኒልክ ጭንቅላት የሚያስብ በርግጥ መፍራት አለበት። የቴዲ አፍሮ “ቅዱስ ጦርነት” ልብ ይባል! “ስሜታዊነት በሩን ሲከፍት ምክንያታዊነት በሩን ቆልፎ ገብቶ ቁጭ ይላል።” ያለው ማን ነበር? በርግጥ መጽሃፍ እንጂ ስሜት ይለበድ ይሆን?

እንቀጥል። “ያጣነውን የበላይነት መልሰን ልንቀዳጅ ህልም አለን!” ብለው እስኪነግሩት የሚጠብቅ በግ ዛሬም ባናጣም የሚሰጠውን ሳያኝክ የማይውጥ ብቻ ሳይሆን ሳያይ የማያኝክ ትውልድም ተፈጥሯል። የኛዎቹ ብቸኛ የአገር ወዳዶች ግን ይሄን አይረዱም ወይም ለመረዳት አልፈለጉም:: ዛሬም እዚያው ቆልፈውብን በነበረው ቤት ውስጥ ያለን ይመስላቸዋል። ወይም ያስመስላሉ። አሮጌ ቁልፍ ይዘው፡ ባዶ ቤት በራፍ ቆመው፡ ብዙ የአለማችን አገሮች አመሰራረት ሰላማዊ ሂደት የልነበረ በመሆኑ የኢትዮጵያን አመሰራረትም በዚያው አይን እንድናይ ብዙ ምሳሌ እየጠቀሱ ይነግሩናል። ይሄን እኛም እንገነዘባለን። የምንለያየው ግን አብዛኛዎቹ የአለማችን አገሮች የተመሰረቱበትን አዳፋ ታሪክ በትክክለኛ ስሙ በመጥራትና እንደማስተማሪያም በመጠቀም ለህዝቦች ሰላማዊ ግንኙነትና አብሮ መኖር ጥሩ መሰረት መጣላቸውና እነሱ ከዚህ በተቃራኒ መቆማቸው ነው።

ለምሳሌ፡ የዛሬዋ የአለም ቁንጮ የአሜሪካ አመሰራረት በጣም! በጣም! ዘግናኝ በሆነ የታሪክ ሂደት ውስጥ ያለፈ ስለመሆኑ እኛም አንበናል። በቀይ ህንዶችና በጥቁሮች ላይ የተሰራው ኢሰብአዊ ድርጊት በጣም የሚሰቀጥጥ ነበር:: ይሁንና ዛሬ ያለው የአሜሪካ ትውልድ ያንን መጥፎ ታሪክ ለመደበቅና ለመካድ መከራውን ሲያይ አናይም። እንዲያውም ተማሪዎች በነባር ህንዶች ላይ የተፈጸመውን “Trail of Tears” ፡ በጥቁሮች ላይ የደረሰውን “Good By Tom” እና የመሳሰሉትን ዘግናኝ ዶክመንታሪ ታሪኮች ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለው ይመለከቱታል:: “Twelve Years Slave” የመሳሰሉ ፊልሞች ዛሬም ተሰርተው ይወጣሉ። እነዚህ ያለፉ መጥፎ ታሪኮቻቸው እንዳይደገሙ ቀጣይ ትውልዶች መማር ያለባቸው የሰላምና የአብሮ መኖር ዋስትና መሰረቶች መሆናቸውን አጥብቀው ያምኑበታል። ያ ብቻም አይደለም። ተማሪዎች እነዚህን ታሪኮች ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለው ከተከታተሉ በኋላ ምን እንደሚሰማቸው እንዲጽፉ ወይም እንዲናገሩ ይጠየቃሉ:: እነዚህን ታሪኮች በመንተራስ የመመረቂያው የጥናት ወረቀት (research paper) እንዲያዘጋጁ የቤት ስራ ይሰጣቸዋል:: በሂደቱ ግን ለተፈጸሙ ለነዚያ ግፎች የዛሬን ትውልድ ተጠያቂ የሚያደርግ እብድ አይኖርም።

ሁሉንም የሚያስማማ ጠንካራ ህግም አላቸው:: ባለፉት ዘመናት ለተፈጸሙ ግፎች ማረጋገጫ /justification/ የሚሰጥ ካለ በህግ ይጠየቃል:: ከላይ እንዳልኩት የኛ አገር አስተምህሮ ከዚህ ይለያል። የህዝቦችን ማንነትና መብት ላለመቀበል ብቻ ሳይሆን ለማጥፋት የሚታገሉ የኛዎቹ “ብቸኛ አገር ወዳዶች” ትላንትም ሆነ ዛሬ ለዚያች አገር ችግር የሚያቀርቡት መፍትሄ ከወያኔ/ አህአዲግ ያልተሻለ ብቻ አይደለም:: በህዝቦች ትግል የተገኙ አንጻራዊ መብቶችን ለመቀልበስ ከማለም ባሻገር በአያቶቻቸውና በአባቶቻቸው በህዝቦች ላይ ለተሰሩ ግፎች ከተቻለ ጥሩ ስም ለመስጠት፡ ካልሆነ ለመካድ፡ ካልተመቸም ማረጋገጫ /justification/ ለመስጠት የማይምሱት ጉድጓድ የላቸውም። በዚህም አያቆሙም:: የግፈኞችን ስራ እንደ ጀግንነት ይሰብኩናል:: “ምኒልክ ኢትዮጵያን አንድ ያደረጉ ጀግና! ያካሄዱት ጦርነት ቅዱስ” እየተባለ በጨካኞች በፈሰሰው ደምና በጠፋው የሰው ልጅ ህይወት ዛሬም እንደሚላገጠው ማለት ነው::

የነዚህን ወገኖች ፖለቲካ ባስታወስኩ ቁጥር ትዝ የሚለኝ አንድ አባባል አለ። አባባሉን ማን እንዳለው አላስታውስም:: ማንበቤን ግን አልረሳም። አባባሉ ግን ከትክክል በላይ ነው:: “ኢትዮጵያን የሚያጠፋት የጭቁን ህዝቦች የነጻነት ትግል ሳይሆን የአንድነቷ አቀንቃኞች ፖለቲካ ነው።” በርግጥ እነዚህ ወገኖች የህዝቦችን ተፈጥሮአዊ መብቶች መጨፍለቅ የቻሉት እንዴት ነበር?እንዴትስ ተሳካላቸው?ብቻቸውን ነበሩ? ዛሬ ያለውን ጨካኝ ገዢ ጨምሮ በህዝቦች መብቶች ሲያላግጡ ከነማን ጋር ነበሩ /ናቸው?

የጠፉ በጎችና የትሮይ ፈረሶች

ኦሮሞም ሆነ በሃገሪቱ የሚገኙ ሌሎች ተጨቋኝ ህዝቦች እንዴት በግፈኞች እጅ እንደወደቁና ዛሬም በተመሳሳይ ጭቆና ስር ስለመቆየታቸው ሳስብ ሁለት ታዋቂ የአለማችን የስነ ጽሁፍ ውጤቶች ይታወሱኛል:: በመጀመሪያ የእነዚህ ስነ ጹሁፍ ውጤቶች ይዘት በህዝባችን ላይ ከደረሰውና እየደረሰ ካለው ችግር ጋር ያለዉን ተመሳሳይነት ከመግለጼ በፊት ለግንዛቤ እንዲረዳ ስለ ስነ ጽሁፎቹ አጭር መልዕክት ላስቀምጥ።

አንደኛው በ19ኛው ክፍለ ዘመን በሃሪየት ቢቸር ስቶው የተጻፈውና በአሜሪካ ምድር በጥቁሮች ላይ ይፈጸም የነበረውን ግፍ የሚተርከው “Uncle Tom’s Cabin” በመባል የሚታወቀው መጽሃፍ ነው:: ስቶው በወቅቱ በዚህ መጽሃፏ በአሜሪካ ጥቁሮች ላይ ይደርስ የነበረውን ኢሰብአዊ ድርጊት በልቦለድ መልክ ጥሩ አድርጋ ተርካ ነበር:: የመጽሃፉ ዋና ገጸ ባህሪይ “Tom” የሚባል ጥቁር ጎልማሳ ባሪያ ሲሆን በጥቁሮች ላይ ይፈጸም የነበረውን ግፍ የፈጣሪ ድርሻው አድርጎ የሚያምን ፍጡር ነበር:: በነጭ ጌታ ላይ ማመጽና ቃሉን አለማክበር ሃጢአት ብቻ ሳይሆን ገነትን ከመውረስ የሚያስቀር አድርጎም የሚሰብክ ነበር:: ያ ብቻም አይደለም:: ከአንዱ ነጭ ጌታ ወደ ሌላው እየተቀባበለ መሸጡ በዚህ ምድር የተሰጠው ድርሻው መሆኑን የሚያምን የእግዚአብሄር በግ ነበር:: በርግጥ “Tom” ይህንን እምነቱን ሳይለቅ ነው ወደ መጨረሻ በገዛው ጌታ ሲደበደብ ህይወቱ ያለፈው:: የገዥዎቹን የበላይነት የፈጣሪ ድርሻ አድርጎ እንዳመነ አለፈ። የጠፋ በግ!

ሁለተኛው በግሪክ ስነ ጽሁፍ በሰፊው የሚተረከውና ወደ አፈ ታሪክ በሚያዘነብለው በ “Iliad” ና በ “Odyssey” በትሮጃን ጦርነት የሚጠቀሰው “Trojan Horse” ወይም “የትሮይ ፈረስ” የሚባለው ነው:: እንደ አፈ ታሪኩ ጦርነቱ የተካሄደው በግሪኮችና በፓሪሶች መካከል ነበር:: መንስዔው የትሮይ ንጉስ ልጅ የነበረው ልኡል “Priam” የስፓርታ ንጉስ የ ‘Menelaus’ ባለቤት የሆነችውንና በወቅቱ ከምድራችን በቁንጅና ትደነቅ የነበረችውን “Helen of Sparta” የተባለችውን ሴት ልጅ ከስፓርታ ጠልፎ ትሮይ ወደተባለችው ከተማ ይወስዳታል። አጋመምኖን የተባለው የሚናሎስ ወንድም ቆንጆይቱን ለማስለቀቅ ብዙ ሺህ የጦር መርከቦችን አሰልፎ ይዘምታል። “በሺህ የሚቆጠሩ የጦር መርከቦችን ያሰለፈ ቁንጅና” ተብሎ ይጠራ የነበረው ይኀው ዘመቻ ግን እልህ አስጨራሽ ነበር። አመታትም ፈጀ። ግሪኮች በትሮይ አካባቢ ያሉትን ከተሞች ቢደበድቡም በጠንካራ ግንብ የታጠረውን ትሮይን ሊደፍሩ አልቻሉም። ሳይሳካላቸው ለዘጠኝ አመታትም ቆዩ። እስከመሸነፍም ደርሰው ነበር። ግን ተስፋ አልቆረጡም።

ኦዲሲየስ የተባለው የጦር መሪያቸው አንድ ዘዴ ያቀርባል። ስፓርታዎች /ግርኮች/ ከእንጨት የተሰራና ዉስጡ ባዶ የሆነ ትልቅ የፈረስ ሃውልት እንዲሰሩ ያዛል። የፈረስ ሃውልቱ ተሰርቶ ካለቀ በኋላ የታጠቁ ወታደሮች ውስጡ እንዲደበቁ ተደርጎ የትሮይ ሰዎች እንዲመጡ ይጠበቃል። ስፓርታዎች /ግሪኮች/ በትሮይ ሰዎች መሸነፋቸውን በጸጋ የተቀበሉ በመምሰል የፈረስ ሃውልቱ ለትሮይ ሰዎች እንደ ገጸበረከት ይሰጣል። የትሮይ ሰዎችም የተደገሰላቸውን ሳይጠረጥሩ ሃውልቱን በደስታ ተቀብለው ወስደው በክብር፡ መሃል አቴና ይተክሉታል። የፈረስ ሃውልቱ በተተከለበት ማግስት ትሮይ ስትባንን ያየችው በተኛችበት መያዟን ብቻ ነበር። አዎን! ፈረሱ ውስጥ በነበሩ ወታደሮች ተወረረች። ከከተማ ውጭ አድፍጦ ይጠብቅ ለነበረው ተጨማሪ የስፓርታ ጦርም ወደ ከተማው መግቢያ መንገዶች ተከፈቱ። ለዘጠኝ አመታት በሺህ ለሚቆጠሩ የጦር መርከቦች ያልተበገረው የትሮይ ጦር በተለበጠው ስጦታ ተታሎ መሸነፍ ብቻ ሳይሆን ሄለንን አጥቶ ተጨማሪ መስዋዕትነትም ከፈለ።

አዎን! ከላይ እንዳልኩት “የጠፉ በጎችና የትሮይ ፈረሶች” በሚል ርእስ “Tom” ስለተባለው የዋሁ ባርያና “Helen of Sparta” የተባለችውን ሴት ከትሮይ ለማስለቀቅ ግሪኮች ስላደረጉት ቴክኒካዊ ትግልና ድል ለመተረክ አይደለም። በኢትያጵያ፡ ኦሮሞን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የደቡብ ህዝቦች በሰሜን ገዢዎች ጭቆና ስር የገቡበትና ዛሬም እየተገዙበት ያለው ሂደት ከነዚህ ታሪኮች ጋር ስለሚመሳሰል ነው። ህዝቦች ለጭቆና ቀንበር የተጋለጡት በነፍጥ ሃይል ብቻ ያልነበረ መሆኑን ለማመልከት ነው። አዎን! ከመሳሪያው በተጓዳኝ የኛዎቹ የጠፉ በጎች ነበሩ። ዛሬም በየቦታው አሉልን። ማንነታቸውን ከውስጣቸው ሰርዞ እነሱነታቸውን ያስካዳችውን ስረአት መታገል ሲገባቸው መልሰው ስለቅዱስነቱ የሚሰብኩን በጎች በሽበሽ ነበሩ። ዛሬም አሉ። ትናንትም ሆነ ዛሬ የጠፉ በጎቻችን ጠፍተው በግ በመሆን አብቅተው ቢሆን ኖሮ ብዙ ባልከፋ። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ከተኩላ በላይ ተኩላ ሆኑብን። ጎበና ዳጪና ገረሱ ዱኪን ከሩቅ፡ ጃጋማ ኬሎን ከቅርብ መጥቀስ ይቻላል።

የሆነው ሆኖ፡ እነዚህን ተኩላዎች ነው፡ አንዳንዶች “ኢትዮጵያን የፈጠሩት ኦሮሞችም ጭምር ናቸው” ከማለት አልፈው “ባለፉት ዘመናት ኦሮሞ ስልጣን ላይ አልነበረም ወይ?” ብለው የሚጠይቁን። አንዳንዶች እንዳውም አልፈው “ምኒልክንም፡ ሃይለስላሴንም መንግስቱንም ‘ኦሮሞች ነበሩ” ይሉናል። “ተባለ እንዴ??” ብሎ በአንድ ዘመን የዘፈነው ማን ነበር? ጸሃዬ ዮሃንስ ይመስለኛል ። እነዚህ ያለፉ ገዢዎችን እሬሳ የሚሸልሙን የዘመናችን የአንድነት ባለአደራዎች መለስንም “ኦሮሞ ነው ይሉናል” ብዬ አልጠረጥርም። ምክንያቱም በአንድ ወቅት ሳያስመስል እቅጩን ነግሯቸው ነበር። አዎን! ወርቅ ከሆነው የትግራይ ህዝብ መወለዱን በአራት ነጥብ ሳይሆን በቃለ አጋኖ አሳምሮ በጥሩ አማርኛ ነግሯቸው ነበር። እነዚህ የዘመናችን ፖለቲከኞች ለፖሊቲካ ፍጆታ ብለው ሊያምታቱ ይፈልጋሉ እንጂ ምኒልክና ተፈሪ መኮንን የዘር ምንጫቸው ከወዴት እንደነበር በግእዝ ሳይሆን በአማርኛ እንዳይረሳ አድርገው ለሁሉም ነግረው ነበር። ካውኬዢያኖችና የሰለሞን ዘሮች! ምን በወጣቸው ከኦሮሞ ይሆናሉ? ዛሬ በህይወት ኖረው ኦሮሞ መባላቸውን የመስማት እድል ቢኖራቸው ምን ይሉ ይሆን???

መንግስቱን በተመለከተ ትናንት በደጉ ዘመን ሳይሆን ዛሬ ከነ ፖሊቲካ ክስረቱ እየቆጠረ “ኦሮሞ ነኝ” ሲል ሰምተነዋል። እንደዚያ ማለቱ አልገረመንም። እዚህ ጋ አንድ ነገር ሳንል ግን አናልፍም። በቅኝ ግዛት ዘመን፡ ቅኝ ገዢ ፖርቹጋሎችን ደግፎ ፓትሪስ ሉሙምባን ያስገደለውና ለኮንጎ ነጻነት ይታገሉ የነበሩትን የኮንጎ ውድ የነጻነት ታጋዮችን ያስፈጀው ቲ. ቾምቤ ዛየር ኮንጎአዊ ስላልነበረ አልነበረም። “ኦሮሞች ስልጣን ላይ አልነበሩም ወይ?” ለሚባለው ደግሞ ምንም የሚያምታታ ነገር የለም። ባለፉት የግፍ ዘመናት ኦሮሞዎች ስልጣን ላይ ነበሩ? አዎን ነበሩ። ነገር ግን እነዚያ ስልጣን ላይ ነበሩ የሚባሉት ኦሮሞች ስልጣን ላይ የነበሩት በማነው? ለማንስ ነበር? እዚህ ጋ ኦሮሞ ስልጣን ነበረው የሚሉንን መልሰን አንድ ጥያቄ እንጠይቃቸው። ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ኦሮሞው፡አማራው፡ሶማሌው፡ ጉራጌው፡ሲዳማው /ሁሉም ማለት ይቻላል/ ግፍ እየደረሰበት ነው። ነገር ግን ይህንን ግፍ ለማስቆም ሁሉም በአንጻሩ እየታገለ ነው። ታድያ ኦሮሞ ዛሬ እየታገለ ያለው ኦሮሞች ስልጣን ላይ ስለሌሉ ነው? አማራውስ የአማራው ሰው ስልጣን ስለሌለው ነው የሚታገለው? ሌሎችም ህዝቦች የሚታገሉት የነሱ ሰው የገዢው መንግስት አካል ስላልሆነ ነው? አይደለም።

“የኦሮሞ ጉዳይ በተለየ አይን ይታያል” ካልተባልን በስተቀር በአጼዎች ዘመን ስልጣን ላይ የነበሩ ኦሮሞች ስልጣን ላይ የነበሩት ለኦሮሞ አልነበረም። በተቃራኒው የገዢው መሳሪያ በመሆን ኦሮሞን ለባርነት ቀንበር ከማመቻቸት አልፈው ሲያስገድሉና ሲገሉ ነበሩ። እነዚህ የገዢ ዘማቾች ከገዢው በላይ የኦሮሞ ጠላቶች ነበሩ። የኦሮሞ ህዝብ ከገዢዎች በላይ ያወግዛቸዋል። የኦሮሞ ህዝብ እነዚህ ከራሱ የወጡ ተኩላዎችን እንደተመረዘ ደም ነው የሚያያቸው። ዛሬም መጠኑ ይለያይ እንጂ የተዋረዱበትንና፡ ማንነታቸው የተካደበትን ታሪክ የሚያመልኩ የባሪያው ቶም አይነት በጎች ሞልተውናል። “የናንተ አይደለሁም” ብለው የከዱን የጠፉ በጎች የመኖራቸውን ያህል፡ የኛ ሳይሆኑ “የናንተ ናቸው” ተብለው ሊያጠፉን የተሰማሩብን፡ የኛ ስም ያላቸው፡ ቋንቋችንን የሚናገሩ /የትሮይ ፈረሶች/ም ከብዙ በላይ ናቸው። እነዚህ የኛ ለመሆን ቋንቋችንን ማወቅና የኛን ስም መያዝ ብቻ ይጠበቅባቸዋል። በቀደሙት ዘመናትም ይሁን በዚህ በኛ ዘመን እነዚህ የትሮይ ፈረሶች እኛ ላይ ለመዝመት የሚታጠቁት ጠመንጃ ነበር። ከዚያስ በኋላ? ከዚያ በኋላማ በቃ! ጠመንጃ ይዘው የኛ ይሆናሉ። ከዚያም የአይኖቻችንን ቀለም እንድናሳምር ይመክሩናል።

በርግጥ የዛሬዎቹ እየተዋጉን ያሉት በጠመንጃ ብቻ አይደለም። ብእርም ታጥቀዋል። በተለያዩ ሚድያዎች ላይ በኦሮሞ ስሞች የሚለጠፉና የኦሮሞን የነጻነት ትግል ከማውገዝ አልፈው ምኒልክን እምዬ እያሉ እዬዬአቸውን የሚያቀልጡትን ብዙ እያየን ነው። በቅርቡ “የኦሮሞ ፈርስት” ጉዳይ የተለያዩ ድህረ-ገጾችንና የሶሻል ሚድያን በተቆጣጠረበት ሰሞን የኦሮሞን ውሸት በሃበሾች እውነት እያጣፉ ማብራሪያ የሰጡን ፍቃዱ ለሜሳ (ማእረጋቸው ፕሮፌሰር ነው፡ የኋላ ስማቸው ኦሮሞ!) ከትሮይ ፈረሶች አንዱና ትልቁ ምሳሌ ነበሩ ወይም ናቸው። እነዚህ የትሮይ ፈረሶች ትናንትም ነበሩ ዛሬም አሉ። ነገም አይኖሩም ብለን አንጠብቅም። የሰው ልጅ እስካለ ድረስ ከሃዲም፡ከራሱ የሚሸሽም ይኖራል። በአብዛኛው የአለማችን ክፍሎች እንደሆነውና እንደሚሆነው ኦሮሞም የትሮይ ፈረሶችና የጠፉ በጎቹ ጠላት ሆነውበት፡ ቀድመውት የአውሮፓውያንን ነፍጥ ለጨበጡ ተስፋፊዎች እጁን አስረው አስረከቡት። ለገዢዎች ጉልበት ከሆኑት መሳሪያዎች ዋነኞቹ እነዚህ ነበሩ። ጎበና ዳጬም ምኒልክን ወግኖ ኦሮሞን ያስፈጀው ኦሮሞ ስላልነበረ አልነበረም። ጦሩ እስከሚዶለድም ኦሮሞን ከወጋው ምንሊክ ጋር ኦሮሞን ያስወጋው የዳጬ ልጅ /የምኒሊክ ፈረስ-አባ ዳኘው/ ኢትዮጵያን ለምኒልክ መሰረተና ምንም የሚደንቅ ነገር የለውም። ጃገማ ኬሎ የሃይለስላሴ ዘበኛ ሆኖ ኦሮሞ ላይ ጨከኖ ኢትዮጵያን ለገዢዎች አቆየና ምን ተአምር ይኖረዋል? በርግጥ እንደተባለው ኦሮሞ ከሆነ መንግስቱንም በዚያው መልክ ነው የምናየው።

ደግ ሰው ትመስለኝ ነበር፡ ለካ ኦነግ ነህ!!

እርግጠኛ ነኝ ይህንን ሃተታ አንዳንዶች ከአማራ ህዝብ ጥላቻ ጋር ያያይዙታል። ግልጽ መሆን ያለበት ነገር የአማራ ህዝብ በፍጹም! በተኣምር! የኦሮሞ ህዝብ ጠላት ሆኖ አያውቅም። ሊሆንም አይችልም። በአማራው ህዝብ ስም የሚነግዱ ወገኖች የሰሩት ግፍ የነዚያው ወገኖች ሃላፊነት እንጂ የአማራው ህዝብ አይደለም። በአንድ ወቅት አንድ የአማራ ተወላጅ ጓደኛ ነበረኝ። አማራ መሆኑን ያምናል። ኦሮሞ መሆኔን ያከብራል።”ኦሮሞ ነኝ” ስለው የማይናደድ ወይም የማያመው ሰው ነበር። እኔም እንደዚሁ። ወላጆቹ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ያደርሱ የነበረውን በደል ያጫውተኝ ነበር። በልጅነቱ በሚሰሩት ስራ ከቤተሰቡ እንደማይስማማም ይነግረኝ ነበር። ከልቡ መሆኑ ደግሞ የበለጠ ጓደኛው እንድሆን አደረገኝ። ዛሬ የየኑሮአችን መንገድ ለይቶን ባንገናኝም ከልቤ ያልጠፋ ደግ ልጅ ነበር። ያለፉ ግፎች በስማቸው ለመጥራት ለምንታገል ሁሉ የአማራ ህዝብ ማለት እንደዚያ ጓደኛዬ ነው።

በአንጻሩ ደግሞ በራፋችን ላይ ቆመው “ኦሮምኛህን ቤትህ ገብተህ አውራ” የሚሉን ደፋሮች ዛሬም አሉ። አንድ ሰው ሊጠራበት የማይፈልገውን ስም “ብትጠራበት ምንድነው?” ብለው የሚከራከሩና ሳይቸግራቸው የሚቸገሩ ደረቆችን ዛሬም እያየን ነው። “ኢትዮጵያውያን ነን።” ይላሉ። “ጥርት ያልኩ አማራ ነኝ!!” ይሉ በነበረበት ዘመን በነሱ የሚገረም አልነበረም። ዛሬ እኛ “ኦሮሞ ነን!” ስንል አብዮት ያውጃሉ። ኢትዮጵያ ማለት ለነሱ አማርኛ ብቻ የሚነገርባት፡ የቴዎድሮስና የምኒልክ ጀግንነት የሚሰበክባት፡ የ3000 ዘመናት አፈታሪክ የሚቀነቀንላት ጥንታዊት አገር!!! ለኛ ግን ኢትዮጵያ ማለት የዛሬ መቶ ከምናምን አመታት በጉልበት የተመሰረተችና ዛሬም ደም ደም የምትሸት፡ በደም በተቦካ አፈር ላይ የተተከለች፡ በጉልበት የታጨቁባት ህዝቦች ዛሬም ድረስ ዜጎቿ መሆን ያልቻሉባት፡ የአንዱ እናትና የሌላው የእንጀራ እናት ነች። በመቃብራችን ላይ የተገነባች!!! “የፓንዶራ ሳጥን!!! ተስፋዬ ገ/ዐብ ቁልፉን የነካካው የፓንዶራ ሳጥን!!

በአንድ ወቅት በአንዱ የኦሮሚያ ከተማ፡ አንድ ትምህርት ቤት፡ አብረን ተምረን፡ ነገር ግን ተለያይተን ብዙ አመታት ከቆየን የአማራ ልጅ ጋር ተገናኝተን ሰላምታ ተለዋወጥን። ሁለታችንም በየፊናችን የህይወት ወከባ ስለነበረብን መልሰን ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘን ተላለፍን። በቀጠሮአችን መሰረት ተገናኝተን ስለ ተለያዩ ጉዳዮች አንስተን ከተጨዋወትን በኋላ ዛሬም ተለያየን። ኋላ ላይ የመገናኘት እድሉ እየሰፋ ሄዶ በየጊዜው እንገናኝ ጀመር። አንድ ቀን ተገናኝተን ስናወራ በጫዋታ መሃል ስለ ፖለቲካ አንስተን ስንቀባጥር ሄደን ሄደን የኢትዮጵያዊነት ብሄራዊ ስሜት ጋ መጣን። ኢትዮጵያዊነት እንደሚያኮራው፡ ለኢትዮጵያዊነት ያለው ብሄራዊ ስሜት ልዩ እንደሆነ በጥሩ አማርኛ ጥሩ አድርጎ ሊያስረዳኝ ሞከረ። አስቀድሜ የማውቀው ቢሆንም በጣም በተለያዩ የአመለካከት አለማት ውስጥ ያለን መሆኑን የበለጠ ተገነዘብኩኝ። ትንሽ ካሰብኩ በኋላ “ታድለሃል!” ስለው የበለጠ ገለጻ ሊያደርግልኝ ተዘጋጀ። ግን አቋረጥኩት። “ይገርምሃል፡ በአመለካከት በጣም በሚራራቁ ጫፎች ላይ ነው ያለነው” ስለው “እንዴት?” አለኝ።

“እንደምትለው የኢትዮጵያዊነት ብሄራዊ ስሜት ባንተ ውስጥ ልዩ ነው። እኔ ግን ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚሰማኝ ስሜት የለም!” ስለው ፊቱ ተለዋወጠ። በዚያ ቅጽበት ሌላ ሰው የሆንኩ ያህል አትኩሮ ሲመለከተኝ ተመለከትኩት። “ይቅርታ! የማወራው የሚያስደስትህ እንዳልሆነ አስቀድሜ አውቃለሁ። ነገር ግን እውነታውን ከመናገር ውጭ አማራጭ የለኝም። ወደድንም ጠላን ኢትዮጵያ የተባለው አገር ተመስርቷል። ያኮራኛል የምትለው ኢትዮጵያዊነት ግን… ” አንጠልጥዬ ተውኩት። “እና?” አለኝ። “ጨርሻለሁ“ አልኩት። ትንሽ ካሰበ በኋላ ነገሩን ወደ ወያኔ አዞረው። እየተከዘ “አይ ወያኔ!” አለ። “ምነው?” ስለው “ጥሩ አድርጎ ኢትዮጵያዊነትን ውስጣችን ገድሏል” አለኝ። “በወያኔ አታመሃኝ። የምትለው ኢትዮጵያዊነት አልተመሰረተም!” ስለው “ወይኔ! ምንድነው የምታወራው? እየቀለድክ መሆን አለበት!” አለኝ።

“ወንድሜ! ምንም ቀልድ የለም። የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ቀድመው የፈረንጅ መሳሪያ የጨበጡ ጀብደኞች የዛሬ መቶ ከምናምን አመታት ገደማ ኢትዮጵያ የተባለችውን አገር በጠመንጃ ፈጥረው መሬቱን ከለሉ። አገራዊ ስሜት ግን በጠመንጃ ሃይል ተከልሎ የሚፈጠር አልነበረም። እንዲያም ሆኖ አገራዊ ስሜት ሊያመጡ ይችሉ የነበሩ ብዙ ተስፋዎች መክነዋል። ዛሬም የህዝቦች ማንነት ካልተከበረ ለዚህች አገር ያስፈራል” ስለው አሁንም ትኩር ብሎ እያየኝ “አንተም እንደ ወያኔዎቹ ነው የምታስበው?” ትንሽ ቆይቶም አከለ። “የኢትዮጵያን የረጅም ዘመናት የመንግስትነት ታሪክ ወደ መቶ አመታት ከሚሸበሽቡት ውስጥ ነህ ማለት ነው?” ሲለኝ ሳቄ መጣ።

መልሼ “ወንድሜ! ትክክለኛ ስሜቴን ልንገርህ?” አልኩት። “አንተ የምትለው ኢትዮጵያዊነት ለኔ የዉሃ ጣእም ነው። ውስጤ የለም። ይሄን ደግሞ ከትግሬ ወደ ስልጣን መምጣት ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም። ትግሬ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ ሩቅ ዘመን በፊት ኦሮሞ ነበርን። ዛሬም ኦሮሞ ነን። ነገም ኦሮሞ እንደሆን እንቀጥላለን። እናም ውስጤ ያለው ኦሮሞነቴ ነው” አልኩት። የበለጠ ያሳቅሁት ግን በሚከተለው አባባሉ ነበር። “ወይኔ! ደግ ትመስለኝ ነበር። ለካ ኦነግ ነህ” አለኝ። አክሎም እንዲህ አለ። “የኦነግን ዘረኛ አመለካከት ታራምዳለህ ማለት ነው።”

በርግጥ አባባሉ “የአንድነት ሃይሎች ነን” ባይ ወገኖች ስለ ኦነግ ያላቸውን ስእል ሳያስታውሰኝ አልቀረም። ገዢ የነበሩ ሃይሎች በህዝቦች ላይ ይፈጽሙ በነበረው በደልና ግፍ የተፈጠረውን ኦነግ ከሌላ ክዋክብት (planet) የመጣ ጭራቅ አስመስለው ባገኙት ሚድያ ሁሉ ሲያብጠለጥሉ መኖራቸውን ሳነብና ሳዳምጥ የኖርኩ በመሆኑ እና ልጁ ደግሞ የነዚያ ወገኖች ጥላቻና ፍራቻ ሰለባ ከመሆኑ አኳያ አባባሉ አልገረመኝም። በአባባሉ እየሳቅሁ “በዚህ አገር በኦሮሞ ህዝብ ላይ ደርሶ የነበረውንና እየደረሰ ያለውን በደል የሚታገል ሁሉ ኦነግ የሚሆን ከሆነ፡ አዎን! ኦነግ ነኝ! ኦነግ የኦሮሞን ህዝብ ችግር የሚረዳ ከሆነ፡ እኔም ኦነግ ነኝ! አላፍርበትም! ስለ ማንነቴ ማንሳት፡ ስለደረሰብኝ በደልና ህመም መናገር ዘረኝነትን ማራመድ ከሆነም ዘረኛ ነኝ። ዘረኝነትን እኮራበታለሁ” ስለው “ጎበዝ ፖለቲከኛ ወቶሃል” ብሎ ካሾፈ በኋላ የተለመደውን የምንሊካውያንን አባባል ሰነዘረ። “ለነገሩ እኔ አልኩ እንጂ ኦነግ የታለ? ፖለቲካው ከስሯል። ደግሞም የኦሮሞን ህዝብ አይወክልም።” አለኝ። እኔን “ኦነግ ነህ” እያለ መልሶ ኦነግ አለመኖሩን ሲነግረኝ ሁለት የሚጣረሱ ሃሳቦችን እየተናገረ መሆኑን ያወቀ አይመስልም ነበር። ምክንያታዊነቱ ሳይሆን ስሜታዊነቱ ጎልቶ ይታይ ነበር። እሱ አለ እንጂ ኦነግ የታለ? በርግጥ የኢትዮጵያ አንድነት አቀንቃኝ ጸሃፊዎችም (በሙሉ ማለት ይቻላል) የሚከተሉት ስሜታቸውን ነው። በመሬት ላይ ያለውን እውነታ ይሸሹታል። ግን እያባረራቸው ነው። እንደጥላ በየሄዱበት ይከተላቸዋል። ሲደነብሩ ቀይ ብእር ያነሳሉ። ወይም ቀዩን ምላሳቸውን ይጠቀማሉ። ቀያይ ቃላትንም ይጽፋሉ ወይንም ይተፋሉ። እነዚያ ቀያይ ብእሮች ወይም ምላሶች ሄደው ሄደው ለዚያ አገር እየበጁ አይደለም።

ያ ጓደኛዬ ያንን ተናግሮኝ ተለየኝ። ከዚያ በላይ ቆሞ ሊከራከረኝ አልፈለገም ወይም አልቻለም። እሱ ከተለየኝ በኋላ የተናገረኝን መልሼ ሳስብ አሁንም ሳቄ መጣ። በርግጥ የዚያን ጓደኛ አባባል ሳስታውስ ከአመታት በኋላ ዛሬም እስቃለሁ። “ደግ ሰው ትመስለኝ ነበር። ለካ ኦነግ ነህ። ለነገሩ እኔ አልኩ እንጂ ኦነግ የታለ? ፖለቲካው ከስሯል። ደግሞም የኦሮሞን ህዝብ አይወክልም።” በርግጥ ኦነግ መኖሩን ለማረጋገጥ ተሰልፎ የጓደኛዬ ቤት በራፍ ድረስ መሄድ ያለበት አይመስለኝም። የኦሮሞ ህዝብም የኦነግን ድጋፍ ለመግለጽ መቶ ሃምሳ ቦታ መሰለፍ ያለበት አይመስለንም። የኦነግ ፖለቲካ የከሰረው ከኦሮሞ ህዝብ ጠላቶች አንጻር ብቻ መሆኑን ጓደኛዬም ሆነ መሪዎቹ ሊያውቁት ይገባል። እነሱ እንደሚሉት የኦሮሞ ህዝብ ኦነግን አይደግፍም እንበል።ኦነግም የኦሮሞን ህዝብ አይወክልም እንበል። ይሄን ማለታቸው አይደንቀንም። የሚደንቀን ግን “የኦሮሞ ህዝብ ባህሉን፡ ማንነቱንና ታሪኩን በጆሯችን መስማት የማንፈልገውን እኛን ነው የሚደግፈው” ከተባልን ግን ስቀንም አናባራም። በርግጥ እነሱ ይሄንንም አይሉም አይባልም። በአንድ ወቅት፡ ቢጨመቅ የኦሮሞ ደም የሚወጣውን አረንጓዴ፡ ብጫ፡ ቀይ የምኒልክ ባንዲራ የለበሱ አማሮች (የትሮይ ፈረሶች) “ኢትዮጵያውያን ኦሮሞች ነን!!” ብለው “ማንንም ከመሆኔ በፊት መሆን የምችለው ኦሮሞ ነው!” ባለው ጃዋር መሃመድ ላይ ሰልፍ ወጥተው ነበር።

ይሁንና ከላይ ያነሳሁትን አባባል ተናግሮኝ ለተለዬኝ ጓደኛዬ ሳይለየኝ የሚከተለውን መልስ ባለመስጠቴ በወቅቱ ሳይቆጨኝ አልቀረም። “የህዝቦችን ማንነት ቆፍረው ሊቀብሩ ባይፈልጉ ኖሮ የኢትዮጵያ አንድነት አቀንቃኞች በሙሉ ደጋግ ሰዎች ናቸው”

የሚሉሽን በሰማሽ…

በኢትዮጵያም ይሁን ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ የ ”አንዲት ኢትዮጵያ” ብቸኛ ባለቤቶች እነሱ ከለመዱት ሃሳብ ውጭ የጻፈ ወይም የተናገረ ሁሉ ያንን አገር ሊያፈርስ የተነሳ ነው። ኢትዮጵያ የምትኖረው እነሱ ባሉት መንገድ ብቻ ነው። በርግጥ ኢትዮጵያን በአንድ ዘመን በራሳቸው መንገድ ብቻ አኑረዋታል። ያ ብቻ አይደለም። በፈላጭ ቆራጭ አገዛዛቸው ህዝቦችን አኖረውበታል። እንደፈለጉም ኖረውበታል። በአንድ ዘመን የነበረ አመለካከት ከጊዜ ጋር ራሱን ማስተካከል ካልቻለ መለወጡ አይቀርምና የነሱ አገዛዝ ጊዜውን ጠብቆ ተሸኘ። ያ ያለፈው ስረአት ገዳይ እንደነበረና ተመልሶ እንደማይመጣ ሲነገራቸው አብዮት ያውጃሉ። ጀዋር ሞሃመድ ምን ነበር ያደረገው? “ኦሮሞ ነኝ” አለ። የሚሰማውን እውነተኛ ስሜቱን ተናገረ። በቃ አብዮት ታወጀ። ከሚነግረን ኢትዮጵያዊነቱ ጀርባ በረዢሙ ቆሞ የሚያየን አማራነቱን የማናይ እየመሰለው ሊያጃጅለን የፈለገው ጋዜጠኛ አበበ ገላው “ጀዋር የጎሳ ብሄረተኛ ነው። እኔ ኢትዮጵያዊ ብሄረተኛ ነኝ “ ብሎ ሲያሾፍ ሰማን። በርግጥ ለሚለቀስላት ኢትዮጵያ የሚሻለው የሚያስመስለው ወይም የህዝቦችን መብት የሚቃወመው አበበ ገላው ሳይሆን እውነተኛ ማንነቱን የተናገረው ጀዋር መሃመድ ነው ብለን እናምናለን።

ስለ ኢትዮጵያ እውነተኛ ገጽታ ሲነገራቸው ጀዋር ላይ ያውጁት አብዮት የመጀመሪያው እንዳልነበረ ሁሉ የመጨረሻውም አልነበረም። በደራሲ ተስፋዬ ገ/አብ ላይ የታወጀው አብዮታቸው ደግሞ ሰንበትበት ብሏል። የተስፋዬ መነሻው የቡርቃ ዝምታ ነበር። የምኒልክ ወንጀል በ “የቡርቃ ዝምታ” ተነካ!! ቀጥሎም ከትልቁ የፓንዶራ ሳጥን “ጫልቱ እንደ ሄለን” የምትል አጭር ሰበዝ ተመዛ ታየችላቸው። በቃ! ሌላ አብዮት ተቀጣጠለ!! እነ ዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ የአለም አቀፉ ፍርድ ቤት አቃቤ ቢሆኑ ተመኙ። ለምን ሲባል ተስፋዬ ገብረአብን ህዝብን በህዝብ ላይ በማነሳሳት ወንጀል ሊከሱ። በርግጥ እነሱ የአለሙ ፍርድ ቤት ዳኛ አለመሆናቸው በጀን!! ቀልድ!

ከዚህ ቀደም እንዳልኩት የኢትዮጵያን ህልውና እየተፈታተነ ያለው የዚያ ያረጀና ያፈጀ አመለካከት ተሸካሚና ያ ስረአት ተመልሶ እንዲመጣ የሚመኝ እንደዚህ ያለ ህልመኛ መሆኑን አንስቼ ነበር። እኛ ያን ያለፈውን አመለካከታቸውን እንዲተውና ከዘመን ጋር ራሳቸውን እንዲያስተካክሉ ነው። አማራጭ ስለሌላቸው የህዝቦችን መብት እየመረራቸውም እንዲቀበሉ ነው። በርግጥ የጊዜው አቅጣጫ የገባቸው እንደነ ወጣት አቤኔዘር እየነገሯቸው ነው። መስማት ግን የሚችሉ አይደሉም። የዘሬን ከተውኩ ያንዘርዝረኝ ሆኖባቸው ነጋ ጠባ፡ ያንኑን የምኒልክ ህልማቸውን ያመነዥካሉ። ምኒልክ የሰራውን ኢፍትሃዊነት “ኢፍትሃዊነት” ብሎ መጥራት ለነሱ አይዋጥም ብቻ ሳይሆን ራሱም ኢፍትሃዊነት ነው። ያለፈውን የማይተው እነዚህ ወገኖች ያለፈውን እንድንተው ግን ይመክሩናል። አዎን! የምኒልክን ወንጀል ስናነሳባቸው እነሱው ወደፊት ተመልካች ሆነው “በምኒልክ ዘመን የተፈጸመውን ማውራት ዛሬ የሚጠቅመው ነገር የለም። ያለፈውን ትተን ወደፊት እንመልከት” ይሉናል። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ይህን አባባል ያላነበብንበት ወይም ያላዳመጥንበት የአንድነት አቀንቃኞች ሚድያ የለም።

ይህንን ባሉበት አንደበታቸው ወይም ብእራቸው መልሰው ስለ ምኒልክ ጀግንነትና ደግነት ያወሩልናል። የድርጅት ተወካይም ይሁን ግለሰብ ስለዚህ አሳምሮ ሲያወራ ከብዙ ጊዜ በላይ ሰምተናል። ለምሳሌ ያለፉትን ስረአቶች ተመልሰው እንዲመጡ የሚመኘውና በኢትዮጵያ አንድነት ስም የሚምለው የአማራ ብሄረተኛው ታማኝ በየነ ስለምኒልክ ጀግንነት፡ ደግነትና አርቆ አሳቢነት አውርቶ አይጠግብም። “የኢትዮጵያ ህዝብ ምኒልክን እምዬ ይላቸዋል” ብሎን ነበር በአንድ ወቅት። እዚህ ጋ ካነሳነው ርእስ ስለሚያስወጣን “ምኒልክን እምዬ’ የሚለው የኢትዮጵያ ህዝብ ማነው?” ብለን ታማኝን አንጠይቅም። እሱ የሚለው የኢትዮጵያ ህዝብ ማን እንደሆነ እንገነዘባለንና። እነዚህ ሰዎች ምኒልክን አይደለም መውደድ ማምለክ ይችላሉ። በተጨባጭ እየሰሩ ያሉትም ያንኑን ነው። ይሄን በማድረጋቸው አንገረምም። መብታቸው ነው። የምኒልክ ገዳይነት ለነሱ ጀግንነት ነው። ለዚህም አንታዘባቸውም። “ገዳያችሁ ምኒልክን አባታችን በሉት” ስንባል ግን ነገሩ ከማስገረምም በላይ ነው። እኛ ምኒልክን እንደነሱ እንድንወድ ብቻ ሳይሆን ጃግንነቱን ከነሱ ጋር እንድንዘምርና “አባታችን” ብለን እንድንጠራው ከሰበኩን (በርግጥ እየሰበኩም ነው።) ችግር ነው። ታማኝን ጨምሮ በሙሉ ማለት የሚቻል የአማራ ብሄረተኞች ምእራባዊው አትላንቲክ ውቅያኖስ አካባቢ የሚገኘውን ቤርሙዳ /የተባለውን ምስጢራዊ ክልል የሚያውቁትን ያህል ከአንድ ክ/ዘ/ በላይ በግፍ የገዙትን የኦሮሞን ህዝብ አያውቁትም።

በምሰራበት ቦታ “ምኒልክ!” የሚባል የስራ ባልደረባ አለኝ። ሰው ሲገናኝ መቸም የሚሰማውን ይናገራልና አንድ ቀን አንድ ኦሮሞ ጓደኛዬ ይህን የስራ ባልደረባችንን ስም ማን እንደሆነ ካረጋገጠ በኋላ “ይሄን ስም ይዘህ ወደ ሃረርና አርሲ አትውረድ” አለው። በአንድነት ፕሮፓጋንዳ የሚያደነቁሩን ወገኖች ምኒልክ እንኳን የፈጸማቸው ወንጀሎች ትክክለኛነት ማውራትና በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ስሙ ራሱ እንደወንጀል እንደሚታይ አያውቁም። ምኒልክ የገደላቸው ወገኖች መቃብር ላይ ቆመው ስለ ደግነቱና ጀግንነቱ ሊቦተልኩ ይፈልጋሉ። “አረ ይሄ ነውር ነው፡ ምኒልክ አራጃችን እንጂ ጀግናችን ሊሆን አይችልም” ስንላቸው “ምኒልክን በመጥላት የተለከፉ” ይሉናል። እነ ምኒልክን እንዴት አድርገን እንደምንወድ ግን አይነግሩንም። እኛ ኦሮሞች ችግራችንን ከምኒልክም ሆነ ከሌሎች ጨቋኝ ገዢዎች ጋር የማቆራኘት አራራ የለብንም። በሃበሻ ገዢዎች የደረሰብንን አብዛኛውን ረስተነዋል። እነሱው እያነሱ ተቸገርን እንጂ።

ግን እስቲ፡ ስለ ምኒልክ ጀግንነት የሚነግሩንን ታማኝና ጓደኞቹን አንድ ቀላል ጥያቄ እንጠይቃቸው። “ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስንና መምህር አሰፋ ማሩን የገደላቸው ማነው?” ብንላቸው፡ እነ ታማኝ፡ አፋቸውን ሞልተው “ይሄማ ምን ጥያቄ አለው? መለስ ዜናዊ ነዋ!” እንደሚሉን ጥርጥር የለውም። “አቶ መለስ ዜናዊ ለፕሮፌሰሩና ለመምህሩ ልጆች ጀግናና አባት መሆን ይችላሉ ወይ?” ብንላቸው ግን የእብድ ጥያቄ የጠየቅናቸው ያህል እንደሚገረሙም አንጠራጠርም። ትክክልም ናቸው። መለስ ዜናዊ ለፕሮፌሰሩና ለመምህሩ ልጆች ጀግናና አባት ሊሆን አይችልም። የአቶቻቸው ገዳይ እንጂ! ይሄን ጥያቄ አንስተን ወደ ምኒልክና ኦሮሞ ህዝብ ብናመጣው ግን የእነ ታማኝ መልስ የሚሆነው ሌላ ነው። ለነሱ መለስ ዜናዊ ገዳይ ነው። ምኒልክ ግን በነሱ አፍ በፍጹም ገዳይ አይሆንም። መለስ ዜናዊ ገዳይ የሚሆንበትንና ምኒልክ የማይሆንበትን ምክንያት ሊነግሩን አይችሉም። የመምህሩንና የፕሮፌሰሩን ግድያ ብቻ ሳይሆን በዚያ አገር በማንም ላይ የሚፈጸመውን ሰብአዊ ጥሰት ከልባችን እንቃወማለን። ነገር ግን ከላይ ላነሳነው ጥያቄ ከነሱ የምንሰማው የተለመደውን መልሳቸውን ነው። “ምኒልክ እጅና ጡት የቆረጠው ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ነው።” የሚል ይሆናል። የምኒልክ ወንጀል የነሱ ምክንያት።

በሌላ በኩል እነዚህ ወገኖች በአሁኑ ወቅት የአኖሌን ሃውልት መቆም እየተቃወሙ ነው። ነገር ግን፡ የኦሮሞን እጅና ጡት የቆረጠው የምኒልክ ሃውልት ከኦሮሞ ምድር ይነሳ የሚለውን የኦሮሞ ጥያቄ እንዴት ይመልሱት ይሆን?? የአኖሌ ሃውልት የማያስፈልግ ከሆነ የምኒልክ ሃውልትም የሚያስፈልግበት ስነ አምክንዮ የለም። የሆነ ሆኖ፡ የአኖሌ ሃውልት አማራ ክልል አልተተከለም። በኦሮሞ ምድር ነው። “የኦሮሞ ህዝብ ለሚተክለውም ሆነ ለሚነቅለው ማንኛውውም ነገር የጎረቤቶቹን ፍቃድ አይጠይቅም!” ገዳ ገ/አብ። ለነዚህ ቡድኖች የሚሆን አጥጋቢ መልስ!

በመጨረሻ፡ ”የሚሉሽን በሰማሽ…” ብለው የሚተርቱት እነሱ ናቸው። ተስፋዬ ገብረአብ ቁልፉን የነካካውን የፓንዶራ ሳጥን የመሰረተውን ምኒልክን የኦሮሞ ልጆች /ተማሪዎች/ ከሚሉት እስቲ አንዱን እንንገራቸው። ይጠይቃል አንዱ ተማሪ። “በ19ኛው ክ/ዘ/ እንጦጦ አፋፍ ቆሞ የኦሮሞን ደም በጀሪካን ይጠጣ የነበረው ሰው ስሙ ማነው ነበር?” “ይቺማ ቀላል ናት! ምኒልክ ነዋ!” ይላል መላሹ። በርግጥ ምኒልክ የኦሮሞን ደም በጀሪካን ሲጠጣ ያየው አልነበረም። ግነት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ምኒልክ የኦሮሞን መሬት በደም ማጠቡ ወይም የኦሮሞን ጥቁር አፈር በደም ማጨቅየቱን፡ የኦሮሞን ጀግና እጅ፡ የኦሮሞን እናት ጡት መቁረጡን አይረሱትም። ታሪክ ነው። ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ይኖራል። ከዚያም አልፎ፡ የኦሮሞ ልጆች ምኒልክን የሚመለከቱት እንደ አፍሪካዊው ሂትለር ወይም እንደ ጭራቅ ነው። “ሂትለር ለአይሁዳውያን አባትና ጀግና መሆን ከቻለ ምኒልክም አባታችን ሊሆን ይችላል” ይላሉ።

—————-
የግርጌ ማስታወሻ፡-

1- የ “ፓንዶራ ሳጥን” ትርጉሙ ሰፋ ያለ ቢሆንም፡ ስናሳጥረው ፡አስቀያሚ ነገሮችን አጭቆ የያዘ እቃ ምሳሌ ነው። በዚህ ሃተታ ደግሞ የፓንዶራ ሳጥን የሚወክለው ኢትዮጵያን ነው።

2- ኦሮሚያ፡ የተደበቀው የግፍ ታሪክ፡ በ ወልደዮሃንስ ወርቅነህና ገመቹ መልካ፡እአአ 1992 የተጻፈ።

*******

* ፀሐፊውን በ gannaa98@yahoo.com የኢሜል አድራሻ ማግኘት ይቻላል።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on November 28, 2014
  • By:
  • Last Modified: November 28, 2014 @ 6:16 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar