www.maledatimes.com ጥያቄ ወ ትዝብት (በተለይ ለአዳማዊያን) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ጥያቄ ወ ትዝብት (በተለይ ለአዳማዊያን)

By   /   November 30, 2014  /   Comments Off on ጥያቄ ወ ትዝብት (በተለይ ለአዳማዊያን)

    Print       Email
0 0
Read Time:2 Minute, 44 Second

 

እዚህ ፌስቡክ ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች የደራሲ አዳም ረታን ድርሰት ለመረዳት እንደሚከብድና የሆነ የረቀቀ የመረዳት ችሎታ ወይም የላቀ መሰጠት ወይም በጥበብ መቀባት ወይም በንባብ መበልጸግ ወይም በሃሳብ መራቅና መራቀቅ ምናምን እንደሚያስፈልግ ከአንጋፋ እስከ ፈላስፋ ፌስቡካዊያን ሲሰበኩ ሰምተናል… ‘የሰማነውን በልባችን ያሳድርልን!’ ስንልም ዱአ አድርገናል… ያሳዳርልን እስቲ…. አሚን!

ግን እውነት የአዳም ጽሁፍ ይከብዳል እንዴ?!
እውን ቅድመ ዝግጅት ያስፈልገዋልን?… እውን የመጠቀ መረዳትን ይሻልን?… መክበድ ማለትስ ምን ማለት ነው?… ርቀቱስ በምን ተለክቶ ነው?!… ማንስ ነው የለካው?… በነማን ላይስ ነው ልኬቱ የተካሄደው?… የትና እንዴትስ ታወቀ?… በምን ጥናትስ ነው የተስማማችሁት?.. እንዴትስ እንዲህ ልትደመድሙ ቻላችሁ?…

ኧረ ተዉ!… የሆነ የተለየ መሠረት እንደሚያሻው የሳይንስ ግኝት አታድርጉት እንጂ!… የምናወራው እኮ በመጽሐፍት ስለታተመ ድርሰት ነው… ማንም የማንበብ ፍቅር ወይም ፍላጎት ያለው ሰው ስራዎቹን አንብቦ ያሻውን ሊልበት ይችላል!… ኻላስስስ!… ‘አይ የለም!.. አዳምንማ ማንም ምንም ሊልበት አይችልም!’… ካላችሁም ያካሄዳችሁትን ጥናት አሳዩንና ዳታችሁን መርምረን ለየራሳችን ውሳኔ እንስጥ… የአንባቢንም ደረጃ እንሰይምበት!… አሊያ እንዲሁ በጨበጣ ከሆነ በግርታ የሚገነባ የመንጋ ሰልፍ ይሆንና ምክኒያት ያሳጣል!…

ለምናወራው ነገር ሁሉ የራስ እይታን ማስቀመጥ ብልህነት ነው!… እንዲሁ በጅምላ መስማማት ብቻውን መንጋውን አዋቂ አያሰኘውም!… ያልገባው… የከበደው… ግራ የገባው አንባቢ ቢኖር… “እኔ ከበደኝ!… “እኔ ግራ ገባኝ!”… “እኔ አልተረዳሁትም!”… ይበል… የግል ስሜቱ ነውና እንቀበላለን!… በተረፈ አዳምን ለመረዳት ‘እንዲህ ያስፈልጋል!’… ‘እንዲያ አይነት ሊቅነት ይጠይቃል’… ‘አንዳች ጥልቀት ሊኖርህ ግድ ነው!’ አይነት ማስፈራሪያና ድምዳሜን ማስቀመጥ አይጠቅምም!… አንብበው ስሜታቸውን መተንፈስ የሚፈልጉ ሰዎችን በጅምላ ለማሸበር መሞከር ለንባብም ሆነ ለስነ ጽሁፍ እድገት አይረዳም!… ሰዎች በስራዎቹ ላይ ያሻቸውን እንዳይተነፍሱም የራሱን የሆነ የእስራት ተፅዕኖ ይፈጥራል…

እርግጥ ነው!…
ሁሉም ጸሐፊ የራሱ የሆነ የአፃፃፍ ቴክኒክና የተለያየ የምናብ ርቀት ሊኖረው ይችላል… ያም ነው የተለያዩ እይታዎችን እንድናደንቅ የሚያስገድደን… ያም ነው በተለያዩ የቋንቋ አጠቃቀም ዘይቤዎች እንድንደመም የሚያደርገን… አዳምም የራሱ መንገድ አለው!.. እሱንም ነው የምናደንቅለት!… እንደው እኔ የደራሲውን ስራ መረዳት ቢያቅተኝ አንተ ወይም አንቺ በገባችሁ ልክ የተለየ እይታን ታመላክቱኝ እንደሁ እንጂ ‘የተለየ ልምምድ ያስፈልጋል’… ‘መራቅና መበልጸግ አለብህ!’… ‘አንተኮ ገና ስለሆንክ ነው’ አይነት ባዶ ዝብዘባ መንዛት ብቻውን ለኔ ለተራ አንባቢው አይጠቅመኝም!… አዳምን ተአምረኛ አንተን ወይም አንቺን ደግሞ ሊቅ አንባቢም አያሰኛችሁም!…

እኔ እንደገባኝና እንደሚገባኝ…
አንድን ድርሰት አንብቦ በራስ መንገድ ለመረዳት ምንም የተለየ ጥልቀትም ሆነ ርቀት አያስፈልግም… ሙያዊ ትንተና ለመስጠት አካዳሚያዊ እውቀት ሊጠይቅ ይችላል ከዛ ውጭ ያለው ግን የስሜት ጉዳይ ነው!… ነገር ሁሉ ከፍላጎትና ከስሜት ጋር ነው የሚሄደው እንጂ ከጥልቀት ጋር አይደለም… የአዳምን ድርሰት የወደደና ያደነቀ ‘አዋቂ’ … ‘ልሂቅ’… ‘ተመራማሪ’… ‘ድንቅ አንባቢ’… አይነት ካባ ሲደራርብ ያላደነቀነ ወይም አንብቦ ያልተመቸው ወይም አዳምን የተቸ ደግሞ ‘ደነዝ’… ‘ያላነበበ’… ‘የማያውቅ’… ‘ነፈዝ’… ምናምን የሚሆንበት ምንም መለኪያ የለም!… አዳምን አንብበህ ካልተመቸህ ከፍላጎትህ ጋር አልተጣጣመም ወይም የሱ ስታይል ያንተ ስሜት አይደለም እንጂ ካንተ ብቃት ጋር ዝምድና እንዳለው ማሳያ ነገር የለም…

እናም!…
ይሄ መውደድና ማምለክን ማደባለቅ… ማድነቅና ማሳቀቅን ባንድ ማጨመላለቅ ይቁም!… ይህ ሁሉ ሲባል ግን አዳም ተራ ጸሐፊ ነው ለማለት አይደለም!… በስራዎቹ ላይ የተሰጠ ትችትም አይደለም!… ይልቁንም በአድናቂዎች ዙሪያ የተስተዋለ ትዝብት ነው…ደግሞ አንዳንዱ እንከፍ አድናቂ ነኝ ባይ ይመጣና ‘አንተ ማን ሆነህ ነው!’… ‘ቀድመህ አንብብ’ አይነት ፊሽካውን ፒርርርርር ሊያደርግ ይችላል እኮ!… ይሁን እንችላለን… ደሞ ለፊሽካ… አገሩ ሁሉ ፊሽካ ብቻ ነው… aha

የሆነው ሆኖ አዳም አሪፍ ደራሲ ነው!…
ቢሆንም ግን ስራዎቹን ለመረዳት የሚከብድና የተለየ ብቃትን የሚጠይቅ አልመሰለኝም… የማይወደው ቢኖር ከስሜቱ ጋር ስላልሄደለት ወይም የዛ አንባቢ ምርጫ ስላልሆነ እንጂ አዳምን ለመረዳት የተለየ መገራት ወይም መሰጠት ወይም ብቃት ስለሚያስፈልግ አልመሰለኝም… ያው የኔ ስሜት ነው… ስራዎቹንም ልንረዳቸው ከባድ አይደሉም!… አሁን መዝገቡን ለመረዳት የተለየ ጥበብ ይጠይቃል?… ማክዳን ለማወቅስ?.. እዝራን ለመረዳትስ?… ዓላዛርን ለመመርመርስ?… ቴቢን ለማበጠርስ?… ማህሌትን?.. ሁሉ አገርሽን?… ነጻነትን?… እትዬ ግምጃን?… ሺበሺን… ወልዴና ወልደሰንበትን… ምናምን እያልን ብንቀጥል… (ዝም ብሎ ትዝ ያሉኝ ናቸው)…

በመጨረሻም አዳምም ይጻፍልን!
እኛም ክባዳችንን ያንሳልን!
እንደ ስሜታችሁ አንብቡ!
እንደ አቅማችሁም ተቹ!

ብጥስጣሽ ሃሳቦች (bT’sT’ash) . . .

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on November 30, 2014
  • By:
  • Last Modified: November 30, 2014 @ 3:51 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar