እነዚህን ሁለት ፎቶግራፎች ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፡፡ በመጀመሪያው ፎቶ ላይ የሚታዩት የኢህአዴግ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ እና የኦነግ ም/ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት ሰዎች በደርግ ውድቀት ማግስት የተመሰረተው የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ዋና አጋፋሪዎች ነበሩ፡፡ ፎቶግራፉ የተወሰደውም ኦነግና ኢህአዴግ የሽግግር መንግሥቱን በጋራ ይመሩ በነበረበት ጊዜ ነው፡፡
አቶ ሌንጮ በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ የተሰጣቸው ይፋዊ ስልጣን ባይኖርም በተወካዮች ም/ቤት የመከላከያ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆነው ሰርተዋል፡፡ በወቅቱ የኦነግ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ገላሳ ዲልቦ መሆናቸው ቢታወቅም ድርጅቱን በግልጽ የሚመሩት ግን አቶ ሌንጮ ለታ ነበሩ (በኤርትራው ህግሐኤ በኩልም አቶ ረመዳን መሐመድ ኑር ከ1968 እስከ 1979 ድረስ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ተብለው ቢቀመጡም ድርጅቱን በግልጽ የሚመሩት ም/ዋና ጸሐፊው አቶ ኢሳያስ አፍወርቂ ነበሩ)፡፡
የአቶ መለስ ዜናዊና የአቶ ሌንጮ ለታ የጦፈ ፍቅር ከአንድ ዓመት በላይ ሊቆይ አልቻለም፡፡ በሰኔ ወር 1984 ኦነግ የሽግግር መንግሥቱን ጥሎ ሲወጣ ሁለቱ ሰዎች ወዳጅነታቸውን በመተው የከረረ ጠላት ሆነው ቆይተዋል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ አሁን በህይወት የሉም፡፡ አቶ ሌንጮ ግን በሀገረ ኖርዌይ እየኖሩ ነው (በቅርቡም ODF የሚባል ድርጅት መስርተዋል)፡፡
*****
በሁለተኛው ፎቶግራፍ ደግሞ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ ታምራት ላይኔ እና አቶ መለስ ዜናዊ ይታያሉ፡፡ ይህኛው ፎቶ መቼና እንዴት እንደተወሰደ መረጃው የለኝም፡፡ ነገር ግን ዶ/ር ብርሃኑ በሽግግሩ ዘመን ከአቶ መለስ እና ከአቶ ታምራት ጋር መልካም ግንኙነት እንደነበራቸው በስፋት ሲጻፍ የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ የቀድሞው የኢህዴን ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ያሬድ ጥበቡ በተደጋጋሚ ጊዜያት በጻፏቸው መጣጥፎች አቶ መለስ ዜናዊ በ1982 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሜሪካ በሄዱበት ወቅት በእንግድነት የተቀበሏቸው እሳቸውና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ መሆናቸውንም ገልጸው ነበር፡፡
በሂደት ግን ዶ/ር ብርሃኑ ከነ አቶ መለስ ጋር የነበራቸው ግንኙነት መደብዘዝ ጀመረ፡፡ በተለይም “ምርጫ 92” በተቃረበበት ሰሞን ዶ/ር ብርሃኑ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በጠራው አንድ ምርጫ ነክ ፎረም ላይ “በዚህ ምርጫ ቢያንስ አዲስ አበባን ከኢህአዴግ ነጻ ልናወጣት እንችላለን” የሚል ነገር መናገራቸው ከኢህአዴግ ጋር ክፉኛ አቀያየማቸው፡፡ በዚህም የተነሳ የኢህአዴግ ልሳናት የነበሩት እፎይታ መጽሔትና አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋዜጣ በዶ/ር ብርሃኑ ላይ ሰፊ ዘመቻ ማካሄዳቸው ይታወሳል፡፡
ዶ/ር ብርሃኑ በ1993 የተከሰተውን የተማሪዎች ግርግር ከጀርባ ሆነው መርተዋል በሚል ተከሰው ሲታሰሩ የኢህአዴግ ባላንጣ መሆናቸው በግልጽ ታወቀ፡፡ በምርጫ 97 ዋዜማ ግን ሁሉም ነገር አበቃለትና የድሮዎቹ ወዳጆች በተለያዩ የህይወት ጎዳናዎች ላይ መጓዝ ጀመሩ፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ በአሁኑ ጊዜ “ግንቦት 7” የተባለው ድርጅት ሊቀመንበር ናቸው፡፡
*****
አቶ ታምራት ላይኔ በጊዜያቸው የኢህአዴግ ሁለተኛ ሰው ነበሩ፡፡ በሽግግሩ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን የሽግግሩ ዘመን ሲያበቃ ደግሞ ም/ጠቅላይ ሚኒስትርና የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ይሰሩ ነበር፡፡ በህዳር ወር 1989 ግን “ለስኳር ተንበረከኩ” ተብለው ታሰሩ፡፡ በዚህም የተነሳ ከቀድሞ የትግል ጓዳቸው ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ተቋረጠ፡፡ በ2001 የእስራት ጊዜያቸውን ጨርሰው ከወጡ በኋላ ደግሞ ፖለቲካን እርግፍ አድርገው ተውትና የሃይማኖት ሰባኪ ሆኑ፡፡ አቶ ታምራት ዛሬ አሜሪካ ነው ያሉት፡፡
—–
አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 25/2007
Average Rating