www.maledatimes.com ጠ/ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የ “ያ ትውልድ” “ሞገደኛ አባል” አለመሆናቸው በሪሁን መኮንን - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ጠ/ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የ “ያ ትውልድ” “ሞገደኛ አባል” አለመሆናቸው በሪሁን መኮንን

By   /   September 25, 2012  /   Comments Off on ጠ/ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የ “ያ ትውልድ” “ሞገደኛ አባል” አለመሆናቸው በሪሁን መኮንን

    Print       Email
0 0
Read Time:33 Minute, 13 Second
የባለፉት  30 እና 40 ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛ ተዋናዮች በአብዛኛው የአንድ ትውልድና አስተሳሰብ ውጤቶች ናቸው፡፡ እድሜና ስልጣን ጠገቡን ንጉሰ ነገስት ከዙፋናቸው አውርደው ስልጣኑን የሙጥኝ ያሉ ወጣት ወታደሮች፣ ወታደሮችን ስልጣን ለመንጠቅ የተለየዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሲያደራጅና ዙሪያውን አሰፍስፎ ሲጠባበቅ የነበረው ምሁር፣ ብረት አንስተው እርስ በራሳቸው ከዛም አሸናፊ ሆኖ ከወጣው እስከ አፍንጫው የታጠቀ መንግስት ጋር የተፋለሙ፣ የእርስ በርሱ ጦርነት ካበቃም በኋላ አንዳንዴ በኃይል አንዳንዴ በፖለቲካ ጨዋታ አሸንፎ ስልጣን ለመያዝ “የፖለቲካ ሜዳው ጠቧል፣ ሰፍቷል” እያሉ እሰጥ አገባና ንትርክ፣ የገቡ ፖለቲከኞች ….. ሁሉም የተመሳሳይ ትውልድና አስተሳሰብ ውጤቶች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ በትምህርት ቤት፣ በፖለቲካና ጦር ሜዳዎች ጭምር ግለሰባዊ ቂምና ጥላቻ ያላቸው መሆኑ በፖለቲካ ጨዋታቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡ የብዙዎቹ የፖለቲካ ትግል እልህና ቂም የተቋጠረበት ቁርሾና ‘አውቅሃለሁ አውቅሻለሁ’ የነገሰበት የ ‘’ሞገደኛ’’ ትውልድ ጨዋታ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሁኔታ ወደ ፖለቲካ ስልጣኑ ማማ ላይ የወጡት አቶ ኃይለማሪያም፤ የእዚህ ትውልድ አባል አለመሆናቸው  ከላይ በሰፈሩት ሃሳቦች በከፊል ብቻ ለሚስማማም ቢሆን አገሪቷን በተሻለ ሁኔታ ለመምራት እድል ይሰጣቸዋል ብሎ ለማሰብ የሚከብደው አይመስለኝም፡፡
አቶ ኃይለማሪያም በዚያ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ዘመን እድሜያቸው ባለመድረሱ ተካፋይ አለመሆናቸው፣ በኮሚኒዝምና ሶሽያሊስት ርዕዮተ ዓለም  ንትርክና አምባጓሮ ውስጥ አለማለፋቸው /እነዚህን የፖለቲካ አመለካከቶች አያውቁም ወይም አይወዷቸውም ማለቴ ሳይሆን በእነሱ ዙሪያ በሚነሱ አለመግባባቶችና ከእዚህ አለመግባባት ጋር ተያይዘው በሚመጡት በሽታዎች አልተለከፉም ለማለት ነው) ቢያንስ በመጪዎቹ ሶስት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር ላይ ተቀምጠው የተጣሉባቸውን ኃላፊነቶችና  ስራዎችን በተለይም በፖለቲካው መስክ ከዚህ ቀደም ካየናቸው ግለሰቦች በተሻለ ሁኔታ የማከናወን እድል የሚሰጣቸው ይመስለኛል፡፡
ይህ በካቢኒያቸውና በፓርቲያቸው ውስጥም ሆነ በተቃዋሚው ጎራ ካሉ የተለያየ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር በተሻለ መግባባትና፣ ሃሳቡን ከያዘው ሰው ይልቅ በሃሳቡ ላይ ብቻ በማተኮር መልካም ስራዎችን ለመስራት ያግዛቸዋል፡፡ የሚቃወሟቸውንም ሆነ የተለየ ሃሳብ የሚያቀርቡላቸውን ሰዎች  በጠላትነት ከመፈረጅና ለማሸነፍና ላለመሸነፍ በሚደረግ የሞት ሽረት ትግል ወስጥ ከመግባት ይልቅ የተሻለ የመግባባትና ጠቃሚን ሃሳብ ወደ ተግባር እንዲለወጥ የማድረግ እድሉ ይኖራቸዋል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ በፖለቲካው መስክ የተሻለ መግባባትና በጋራ የመስራት፤ መጪውን ምርጫም የተሻለ ለማድረግና ሁሉንም ዜጎች በነጻነት የሚያሳትፍ ምርጫ ለማካሄድ ያስችላቸዋል፡፡ ምናልባትም በእነዚህ ሶስት ዓመታት የሚያከናውኗቸው ተግባራት ለድጋሚ ህዝባዊ ምርጫና ድል ያበቋቸውም ይሆናል፡፡
ለበርካታ ዓመታት በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ተሳታፊ አለመሆናቸው፣ ከራሳቸው የግል ባህሪ ውጭ በእነዚህ የግጭትና የጦርነት ሁነቶች አንጻር ያደገ ስለማሸነፍና መሸነፍ የከረረና የመረረ ስሜት ስለማይኖራቸው፣ በሃሳብ ወይም ሌላ የመሸነፍና የማሸነፍ ውጤት በሚያስከትሉ የፖለቲካና መሰል ወሳኔዎች ላይ የሚኖራቸው አቋምም በሰለጠነው ዓለም የዳበረውን ሁለቱንም በጸጋ የመቀበል አቅም ይፈጥርላቸዋል፡፡
እርግጥ ነው ከእሳቸው በፊት እንደነበሩት የተከበሩ አቶ መለስ ዜናዊ በየመድረኮቹ አስደማሚ የሆኑ የተጠላለፉ ሃሳቦችንና መርሆዎችን በማብራራትና ወደ ፈለጉት አቅጣጫ በመውሰድ፣ ለምዕራባዊያን መሪዎችና ምሁራን ሳይቀር ሌክቸር አከል ንግግርና አስተሳሰብ በማስተጋባት ተቀባይነትን ለማግኘት አይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በአገር ውስጥ ካሉት ጋር በመግባባትና በመተጋገዝ እንዲሁም ሰጥቶ በመቀበል ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርዓት በማስፈን፤ በውጭና በዓለም አቀፉ ግንኙነት የዲፕሎማሲ ዘርፍ ደግሞ ከዚህ ቀደም አቶ መለስ የገነቧቸውን ጠንካራ የወዳጅነትና የተወዳዳሪነት መንፈስ በማጠናከር ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችላቸው እድል  በእጃቸው ነው፡፡ በዙሪያቸው ያሉ ካቢኔዎቻቸውና ከፍተኛ የፓርቲው አመራር አባላትም በተደጋጋሚ እንደተገለጸው ሊያግዟቸውና አብረዋቸው ሊቆሙ ይገባል፡፡
እድሜያቸውና ትምህርታቸው
በአፍሪካ በርካታ መሪዎች ወደ ስልጣን ሲመጡ ከትምህርታቸው አናሳነት በተጨማሪ ከእድሜያቸው ወጣትነት ጋር የተያያዙ የልምድ ማነስ፣ የእልህና የማንአለብኝነት ስሜቶቻቸው በርካታ ጉዳቶችንና ጥፋቶን ሲያስከትሉ ተመልክተናል፡፡ ባለፉት 40 ዓመታት ወደ ስልጣን የመጡ የኢትዮጵያ መሪዎች ስልጣኑን የያዙት ገና በ30ዎቹ የእድሜ ዘመናቸው ላይ እያሉ ነበር፡፡ ይህ ቢያንስ በመጀመሪያዎቹ የአስተዳደር ዘመናቸው አሉታዊ ተጽኖ አላመጣባቸውም ማለት ዘበት ነው፡፡ የኢህአዴግ መንግስት፣ ደርግን አሸንፎ የሽግግር መንግስት በመሰረተበት ወቅት ይሰነዘርበት ከነበሩት ወቀሳዎች አንዱና ዋነኛው፣ የመንግስቱን ከፍተኛ ስልጣን የያዙ ግለሰቦች ልምድ የሌላቸውና በትምህርታቸውም ያልገፉ መሆናቸው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አሁን የደረሱበትን የአመራር ችሎታና እውቀት፣ የዛሬ 21 ዓመት ወደ ስልጣን ሲመጡ ኖሯቸው ቢሆን ኖሮ፤ አልያም ረዥም እድሜ ኖሯቸው በመጭዎቹ አስር ዓመታት የጀመሯቸውን የልማት ስራዎች ለማስቀጠል እድል ቢያገኙ ኖሮ፣  የአመራር ብቃታቸው፤ ምን ዓይነት የሃገር ዕድገትና ጥቅም ሊያስገኝ እንደሚችል ለመገመት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡
አቶ ኃይለማሪያም በእድሜያቸው ለከፍተኛ አመራር ትክክለኛ ወቅት ላይ ያሉ ሲሆን በልምድም አንፃር ከክልል ፕሬዝዳንት እስከ የውጭ ጉዳይና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት የሰሩ፣ ለአጭር ጊዜ ቢሆንም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በነበራቸው የጠበቀ የስራ ግንኙነት ጠቃሚ አሰራሮችንና አካሄዶችን መማራቸውና መቅሰማቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ አቶ መለስም ቢሆኑ ወደዚህ የስልጣን ርካብ እንዲወጡ መንገዱን የጠረጉላቸው፣ ካላቸው ትጋትና የስራ ቁርጠኝነት በመነሳት እንደሆነ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች በተደጋጋሚ የሚገልጹት ነው፡፡
አሁን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሆነው በቀድሞው የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በመምህርነትና በተለያዩ የኃላፊነት እርከኖች አገልግለዋል፡፡ በኋላም በተቋሙ ፕሬዝዳንትነት በማገልገል፣ ከ 13 ዓመታት በላይ የስራ ልምድ /ሲቪያቸውን/ ማዳጎስ የጀመሩት አቶ ኃይለማሪያም ወደ ፖለቲካው ከተቀላቀሉም በኋላ በአጭር ጊዜ “በሙስናና በአቅም ማነስ” በሚል ከስልጣናቸው የተነሱትን የቀድሞውን የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ አባተ ኪሾን ተክተው የክልሉ ፕሬዝዳንት በመሆን ለአምስት አመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ ከዚያ በፊት የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ከመስራታቸውም ባሻገር በፓርቲውም ውስጥ በንቃት ይሳተፉ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ትምህርታቸውን በተመለከተም አቶ ኃይለማሪያም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፣ በመቀጠልም ፊንላንድ ከሚገኘው የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በሳኒቴሽን ምህንድስና የማስተርስ ዲግሪያቸውንና በአሜሪካ ካሊፎርኒያ በሚገኘው አዙሳ ዩኒቨርሲቲ በ ኦርጋናይዜሽናል ሊደርሽፕ ተጨማሪ የማስተርስ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡ ብዙ ዲግሪ መያዝ  ለመሪነት ብቁ ያደርጋል ባይባልም እገዛው ግን የላቀ መሆኑ የማያከራክር ሃቅ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ለመጠቃቀስ ከሞከርኳቸው በተጨማሪ እድሜያቸው፣ ከአዲሱ ትውልድና ከቀድሞዎቹ ጋር በጋራ ለመስራትና የሁለቱን አስተሳሰብና ፍላጎት በማስታረቅ እንደ ድልድይ ሆነው እንዲያገለግሉ ያግዛቸዋል፡፡ ትምህርታቸው ደግሞ ለአመራርም ሆነ ለቀን ተቀን ስራዎቻቸው ሳይንሳዊ ዘዴዎችንና ጽንሰ ሃሳቦችን በተግባር እንዲያውሉ ስለሚረዱዋቸው ይህም ለእሳቸው የተለየ እድል ይሆናል፡፡
የሃይማኖታቸው፣ የትውልድና ያደጉባቸው አካባቢ ተጽዕኖ
አንድን ሰው ከዚህ አካባቢና ብሔር ስለመጣ ባህርዩ እንዲህ ነው፣ እንደዛ ነው ማለት /stereotyping/ ተገቢ ያልሆነና ምክንያታዊ የሆነ ሰውም ሊያቀርበው የማይገባ ሃሳብ መሆኑ ብዙዎቻችንን ያግባባናል፡፡ ያም ሆኖ እንደመጣንባቸው አካባቢዎች፣ በተለይም የልጅነት ጊዜያችንን ያሳለፍንበትንና ያደግንበትን ማህበረሰብ ልማድና ወግ እንዲሁም የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና መንፈሳዊ ትውፊቶች መጋራታችን አይቀሬ ነው፡፡
ስለ ልዩ ልዩ የኢትዮጵያ አካባቢ ሰዎች የተለየ ባህርይና መገለጫ ወዘተ በሰፊው መነጋገርና መወያየትም ምንጊዜም አይቀሬ ነው፡፡ የማዕከላዊና ሰሜናዊ ኢትዮጵያ ሰዎች ከተለያዩ ማህበራዊና ታሪካዊ ሁነቶች ጋር የተያያዘ ሊሆን በሚችል ምክንያት (እንደብዙዎች ግምት)፣ በተወሰነ ደረጃ ከደቡባዊ የሃገሪቱ ዜጎች ይልቅ የሃይለኝነትና “እኔ ያልኩት ይሁን” የማለት ባህርይ የሚያሳዩ ሲሆን በአንጻሩ በደቡባዊ የአገሪቱ አካባቢ የሚገኙ ሰዎች ደግሞ ሰላማዊና ሆደ ሰፊዎች ናቸው ይባላል፡፡ ይህ እውነት ከሆነ አቶ ደሳለኝ የመጡበት አካባቢ የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ በመሆኑ፣ አገርን ያህል ጉዳይ ለመምራት ቀርቶ አንዲት ግሮሰሪን ለማስተዳደር እጅግ ከሚያስፈልጉ ባህርያት ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት ዋነኞቹ ናቸውና በዚህም የተሻለ እድል አላቸው ማለት ነው፡፡አቶ ኃይለማሪያም ተወልደው ያደጉት በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ በወላይታ ዞን ቦሎሶ ሶሬ በተባለ አካባቢ ነው፡፡ ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት  የልጅነት ዓመታትም እንደማንኛውም የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ልጆች አስተዳደግ፣ ቤተሰቦቻቸውን በልዩ ልዩ ስራዎች በመርዳት ማደጋቸውን በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአካባቢው ህዝብ በብዛት በሚከተለው የፕሮቴስታንት ሃይማኖት በተገቢው መንገድ ታንጸው ያደጉ ከመሆናቸው ባሻገር አሁንም  ጠንከር ያሉ ሃይማኖተኛ መሆናቸው በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ታይቷል፡፡ እንዲያውም በቅርቡ ለአንድ ሃይማታኖዊ መጽሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ “በማከናውናቸው ስራዎች አንድም ሰው ላይ ቢሆን ችግር ከምፈጥር ራሴን ብጎዳ ይሻላል” ማለታቸው ፖለቲካዊ ይዘት የሌለው ሃይማኖታዊ ሰውነታቸውን የሚያመላክት አቋማቸው ይመስለኛል፡፡በአሜሪካ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ሃገሪቱ አሁን ለደረሰችበት የእድገትና የስልጣኔ ደረጃ ከፍተኛ እገዛ እንዳረገ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ ለዚህ ደግሞ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ የማርቲን ሉተርና ጆን ካልቪን እንቅስቃሴዎች የፈጠሩት የፕሮቴስታንት ሃይማኖት አድናቂዎችና ተከታዮች፣ አሮጌውን አህጉር ትተው ወደ አዲሱ የነጻነት ተስፋ ምድር ወደ  አሜሪካ መጓዛቸው እና ሃይማኖቱ የሚሰብካቸው ጠንክሮ መስራት፣ ሊበራልነት፣ ከአዲስ አሳቦችና የካፒታሊዝም ስርዓት ጋር ስምሙ መሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉ ይነገራል፡፡
በእኛ አገር ምንም እንኳ ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩ ቢሆኑም የእሳቸው የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታይ መሆንና በዚያም ባህል ማደግ በርካታ መልካም ጎኖች ይዞ የሚመጣ ይመስለኛል፡፡ የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ መሆኑና ጉዳዩ ሃይማኖቶችን ማበላለጥ ሳይሆን ከሃይማኖቶቹ ጋር ተያይዞ ያለው የፖለቲካና የማህበራዊ ጉዳዮች አመለካከትን ለማሳየት ነው፡፡ በእኔ አስተያየት የኢትየጵያ ነባር ሃይማኖቶች ለአዲስ አስተሳሰብና ለውጥ ብዙም ክፍት ያልሆኑ፣ ወግ አጥባቂና በነበረው ይቀጥል የሚሉ መሆናቸውን ለመካድ የሚቻል አይደለም፡፡በመሆኑም አቶ ኃይለማሪያም ያደጉባቸው አካባቢና ሃይማኖታቸው ተፅዕኖ ከዚህ ቀደም በሃገሪቱ ከፍተኛውን ስልጣን ይዘው ከነበሩ ግለሰቦች የተለየና አዲስም በመሆኑ የተሻለ ነገር ለመስራት ያግዛቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ አዳዲስ አስተሳሰቦችን፣ የተለያዩ አቋሞችንና ተቃውሞን ለመቀበል፤ ለአገርና ለዜጎች የሚጠቅም ተግባር ለመስራት ያግዛቸዋል የሚል ተሰፋ አለኝ፡፡ ይህም ሌላኛው ከዚህ ቀደም አገሪቱን ለመምራት ከቻሉት ግለሰቦች የተለየ እድል ነው፡፡
የኃይል ሚዛን
ምንም እንኳ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትር አቶ በረከት ስምኦን፤ የኢህአዴግ ጉባኤ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝን በሙሉ ድምጽ የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል ቢሉም፤ አቶ ኃይለማሪያም ወደ ስልጣን የመጡበትና እዚህ የደረሱበት ሁኔታ የተለየ ነውና አቶ መለስ  በመንግስትና በደርጅታቸው እንዲሁም በመከላከያው፣ በደህንነቱና በፖለቲካው ክፍል የነበራቸውን ፍጹም የበላይነት እሳቸውም ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይሆናል፡፡
ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም በጦር ሰራዊቱ ላይ በነበራቸው ፍጹም ፈላጭ ቆራጭነት (እሳቸው ራሳቸውም ወታደር ስለሆኑ) ወታደሩን በእሳቸው ፍላጎት ወደ ጦርነት ሲማግዱ መቆየታቸው ሳያንስ፤ በእሳቸው አምሳል በፈጠሩት ፓርቲ (ኢሰፓም) ውስጥ የነበሩ ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚሳሮችና ባለስልጣናት ፍጹም የእሳቸው ታዛዦች መሆናቸው ሃገሪቱን በአምባገነንነት በ17 ዓመታት በመምራት መቀመቅ ውስጥ ከተዋት መሄዳቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡
ውሉ የተለያየ ቢሆንም በትጥቅ ትግሉ ወቅት በነበራቸው የጠበቀ ቁርኝት የአገሪቱ የጦር አዛዥ የሆኑት አቶ መለስም ቢሆኑ በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ያላቸው ተደማጭነትና ረዥም እጅ የተነሳ መከላከያው ለእሳቸው ፍጹም ታዛዥና ታማኝ እንዲሆን ማድረግ ችለው ነበር፡፡ በፓርቲውም ውስጥ ያላቸው ተደማጭነት ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃርም በአገሪቱ ውስጥ ያለው የኃይል ሚዛን በእሳቸው ቁጥጥር ስር እንደነበር ለመካድ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ስልጣንን ሙሉ በሙሉ መያዝና “ሃይ ባይ” የሌለው መሆን ስህተቶችን ለማረም እድል አይሰጥም የሚለው መከራከሪያም ሚዛን አልደፋም ለማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ እንዲያውም ከተባረሩት የሕወሓት አመራር አባላት አንዱ አቶ ስዬ አብርሐ በአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ላይ ሲናገሩ፤ “አቶ መለስ ሕግ ነው፤ እርሱ ያለው ነገር ሕግ ሆኖ ይወጣል፡፡ አቶ መለስ ፍርድ ቤትም ነው፤….. ስለዚህ አንድ ሰው እንደጎደለ ተደርጎ መታየት የለበትም” ሲሉ  የተደመጡትም ምንም እንኳ ንግግሩ የፖለቲካው ጨዋታ አካል ቢሆንም የአቶ መለስን ፍጹማዊ ስልጣን የሚያመለክት መሆኑ በትዝብት መልክ ሊታይ ይችላል፡፡ በአንድ መንግስት አስተዳደር ወስጥ የተለያዩ ተቋማት መኖራቸውና አንዱ ሌላው ላይ የቁጥጥርና የማረም ተግባራት መፈፀሙ፣ ግለሰቦች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ይረዳል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የቁጥጥሩና የእርምት ተግባሩ በመጀመሪያ ከምንፈልጋቸው ጉዳዩች ዋናው የሕግ የበላይነትን መከበር የሚያረጋግጥ መሆኑ፣ ህገ መንግስቱና ሌሎች ተዛማች የአገሪቱ ህጎች በአስተማማኝ መሰረት ላይ እንዲቆሙ ያደርጋል ብለን እንድንገምት ያስችለናል፡፡
አቶ ኃይለማሪያም የሚመሰርቱት መንግስትና ተቋማትም “ከበላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው” ከማለት ይልቅ በሕግና በደንብ ላይ በተመሰረተ አሰራር ላይ በመመስረት ስራዎቻቸውን ለማከናወን እንዲችሉና እራሳቸውም ቢሆኑ በህግና በተደነገገ አሰራር ውስጥ ብቻ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያስችላቸዋል፡፡አቶ ኃይለማሪያም በህግ ከተደነገገው ውጭ በተለይም በመከላከያና በጸጥታ ኃይሉ ላይ ረዥም እጅ ላይኖራቸው ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሆኖም እነዚህን አካላት በህግ ይመሩዋቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ምናልባትም የፓርቲና የልዩ ልዩ የመንግስት ተቋማትን አልፎ አልፎ የሚያደናብር ግንኙነትም የጠራ መልክ ሊያሲዙት ይችላሉ፡፡ ይህና ሌሎችም ተዛማጅ ጉዳዮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውን ስልጣንና ኃላፊነት በህግ ብቻ በተደነገገው መሰረት ስለሚያደርጉት፣ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን በተደላደለ መሰረት ላይ ለማስቀመጥ  የተሻለ ዕድል ይኖራቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የመንግስትን ስራ በዋናነት የማስፈጸም ስልጣን በተሰጠው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውስጥ ያሉ ጓዶቻቸው ጋርም የሚኖራቸው የትከሻ ለትከሻ የኃይል ሚዛን ሌሎች ችግሮችን ሊያመጣ አይችልም ባይባልም፣ በአግባቡ ከያዙትና ይህን አውቀው ለተግባራዊነቱ በቅንነት ከሰሩበት ጠቀሜታው “ከአንድ ሰው አገዛዝ” (one man rule) የተሻለ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ይህም እድል በእጃቸው ያለው አቶ ኃይለማያም ቆይታቸውን መልካምና አርአያ የሚሆን ሊያደርጉትም ይገባቸዋል፡፡ ምኞታችንም ይሄ ነው!!
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 25, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 25, 2012 @ 10:45 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar