www.maledatimes.com የ ደብረ ሲናዋ ቆሎ ሻጭ (ጉዞ ከ አዲስአበባ በጣርማ በር ደብረ ሲና እስከደሴ ) በሳሙኤል ተመስገን - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የ ደብረ ሲናዋ ቆሎ ሻጭ (ጉዞ ከ አዲስአበባ በጣርማ በር ደብረ ሲና እስከደሴ ) በሳሙኤል ተመስገን

By   /   December 13, 2014  /   Comments Off on የ ደብረ ሲናዋ ቆሎ ሻጭ (ጉዞ ከ አዲስአበባ በጣርማ በር ደብረ ሲና እስከደሴ ) በሳሙኤል ተመስገን

    Print       Email
0 0
Read Time:5 Minute, 24 Second

ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ ለመሄድ ሰማዩ በብርሃንና ጨለማ ግብግብ መከራዉን ሲያይ ገስግሼ አውቶብስ ተራ ተገኘሁ ። የምጓዘው 401 ኪሎ ሜትር ነው ለዚህም ስንቅ ይሆነኝ ዘንድ በር ላይ ከሚርመሰመሱት ጋዜጣ ና መፅሔት አዟሪዎች የነ እንቶኔ እጅ የሌለባቸውን መረጥ መረጥ አድርጌ ይዤ ወደ አውቶብሱ አቀናሁ ። ጋዜጣ አዟሪዎችን ሳይ የአይዛክ ኒውተን እና የህሩይ ሲናስ ታሪክ ያስታውሷል። ሁለቱም ጋዜጣ አዟሪዎች ነበሩና። እርግጠኛ ነኝ ስለ አይዛክ ኒውተን ብዙ ታውቃላቹህ ስለ ደራሲ ህሩይ ሲናስ ግን ጥቂት ማለት ወደድሁ፦ ደራሲ ህሩይ በጎጃም ክፍለ ሐገር ብቸና ተወለዱ እድሜያቸው ለጋዜጣ አዟሪነት ሲደርስ አዲስ አበባ በመክተም ጋዜጣ ማዞርና ማንበብ ጀመሩ ሲሉ …ሲሉ …ሲሉ አሮጌ መጽሐፍት መሸጥ ቀጠሉ ::

የወቅቱ ድልድዮች (ከእንቁላል ሻጭነት ወደ ‘ሪል ስቴት’ ባለቤትነት ) አያሸጋግሩም ነበርና ደራሲ ህሩይ ሲናስ ከመጽሐፍ ሳይወጡ እራሳቸው የፃፉትን መጽሐፍ መሸጥ ጀመሩ። የበኩር ልቦለድ መጽሃፋቸው ስምም “ወይ አዲስ አበባ” ይሰኛል።

deberesina qolo

ቲኬቴ ላይ ያለውን ቁጥር ስመለከት መ.ወ.ቁ1 ይላል! ‘ቪ አይ ፒ ‘ መሆኑ ነው ያ ቲኬት ቆራጭ ለ’ቲፕ’ ይህን ቦታ ከሰጠኝ ጉቦ ብሰጠውማ የሹፌሩን ቦታ ነበር የሚሰጠኝ ።
አሁን አሁን ተሻሽሎ በቁጥር ሆነ እንጅ በፊትማ የአውቶብስ ቦታ ለመያዝ የሞት ሽረት ትግል ማድረግ ይጠይቅ ነበር። እኔን የሚገርመኝ ከጥቂት ስዓታት በሗላ ጥለንው ለምንወርደው እንዲህ ከሆንን መርካቶ ላይ የሱቅ ቦታ በሰልፍ ብንከፋፈል እንዴት እርስ በርስ እንበላላ ይሆን?ለነገሩ አሁንም የታክሲው ግፊያ ለጉድ ነው አሉ።

ስንገፋ…ስንገፋፋ…ስንገፋ…ስንገፋፋ ይሄው ስንቱ አገር ለቀቀ። ባስ ላይ ፊት ወንበር ውይይ ሲደብር! ወደሗላ ገልመጥ ብየ ስመለከ ስንት ቆነጃጅት አለ መሰላችሁ? ታዲያ እኔ እዚህ ለምን ሱባኤ እንደገባ ባህታዊ ብቻየን እቀመጣለሁ? ድጋሚ ወደሗላ ሳይ መንደሪን የሚመሰል ቀለም ካለው ቆዳ የተሰራች ሴት ላይ አይኔ እርፍ። አይቶስ ዝም ቢል ምን አለበት ለመላ ሰውነቴ በተለይ ወደግራ ደረቴ አካባቢ ለልቤ መሰለኝ የሆነ መልዕክት አስተላለፈልኝ። አንዳንዶቹ ይሄን አይነቱን ስሜት ” ‘ውርር’ ወይንም ‘ንዝር’ አደረገኝ ” ይሉታል። ብቻ የሆነ ስሜት ተሰማኝ። ይህን አይነት ስሜት ግዮን ሆቴል ዋና ላይ እንደነበርን አንዷ ቦሌኛ ቅላፄ ያላት ልጅ እግር ዋና አለማምዳት ዘንድ ጠይቃኝ በልምምድ ላይ እያለች እንዳትሰጥም ከስር የዘረጋሁት እጄ ከጡቷ ጋ ሲተሻሽ ተሰማኝ ። እርሷም ለመንሳፈፍ ስትጥር እኔም ለመደገፍ እንቅስቃሴዎች ነበሩ ታዲያ ጡቷ ወደ እጄ? ወይንስ እጄ ወደ ጡቷ ? ዛሬም ያልተመለሰ ጥያቄ! ለማንኛውም ከዚህች ልጅ ጋር የከንፈር ወዳጆች ሆነን ነበር ። ዳሩ ምን ያደርጋል አንዴ በስልክ እያወራን ሳለ እናቷ መሰሉኝ” ከማን ጋር ነው ይህን ሁሉ ስዓት ወሬ ?” ሲሏት እርሷ ደግሞ “እማዬ ደግሞ ዋና አሰልጣኜ ነው ::”ብላ እርፍ እናትየዋ ምን ቢሉ ጥሩ ነው? “ታዲያ ስልጠናው የርቀት ሆነ እንዴ? የለም ልጄ ይሄ ነገር ካርድ ይበላል አያዋጣሽም። እሱስ ከሞላ ሙያ ዓሳ ይመስል ዋናን ምን አስመረጠው እቴ ምነው ሸዋ! “
ለነገሩ እኔ ዋና የለመድሁት ኤርትራ ከመገንጠሏ ቀደም ብሎ በቀይ ባህር አቋርጨ ከሐገር ለመውጣት በሚል ነበር። እንዳለመታደል ሁኖ እኔ በደንብ ዋና ስችል ኤርትራ ‘ሰማንያዋን’ ቀደደች። እኔም በብስጭት ገና ያልተገነጠሉ ክልሎቻችን ባሉት ወንዞችና ሐይቆች እየዘለልሁ መግባት ጀመርሁ ግን አንዳቸውም ራቅ አድርገው አልወሰዱኝም። ለምሳሌ ጣና ባህርዳር ላይ ከማንጐ መናፈሻ አካባቢ ገብቼ ስዋኝ ጐንደር ገባሁ ያው ኢትዮጵያ! ወዳጆቼ “እስኪ ባሮን ሞክረው ” ብለውኝ እሱ ይሻላል ወደ ሱዳን ጠጋ አልኩ።

ሱዳን ገብቼ አንድ ታዋቂ የባህላዊ መድሃኒት ቀማሚ ሸክ ጋር ተዋወቅሁ የወዳጅነታቸውን “መስተፋቅር ልስራልህ?” ሲሉኝ ምን አሻኝ ብየ አንዲት ፈረንጅ አገር የምትኖር አብራኝ የተማረች ልጅ አስታወስኩ ውበቷስ ያንያህል ነው እንደው ክንፍ አውጥታ መጥታ እኔንም ወዳለችበት ብትወስደኝ ብየ እንጅ። “የልጅቷ ስም ማን ይባላል ይባላል?” ‘ኢትዮጵያ!’ የሴት ፍቅር ሰራው ብለው በስህተት የሐገር ፍቅር አድርገውት ኑሯል አንድ ቀን ሳላድር በርሬ ወደ ኢትዮጵያ!! አይ ሸኩ ሰሩልኝ።

tarmaber tunnel

አውቶብሶቹ ማምቧተር ጀመሩ መንሐርያውን ጭስ በጭስ አደረጉት ላያቸው ላይ በተከሉት የድምፅ ማጮህያ የሚለቀቀው መዝሙር አካባቢውን ቤተልሔም አስመስሎታል። የማይጠሩ የኢትዮ ጵያ ከተሞች የሉም ማለት ይቻላል። “ጐንደር፣ሑመራ፣መተማ ፤ሸኽዲ፤!!በበራሪው።” “መቀሌ፣አዲግራት፣ውቅሮ፤!! ባዲሱ ሰላም ባስ ” “ደሴ፣ኮምቦልቻ፣መርሣ፣ኬሚሴ፣ሚጢቆሎ!!፣ዱፍቲ፣ሠመራ፣በተወለወለው።”
“ሐረር ፣ ድሬዳዋ፣ ቸኳይ ካለ።”
“ወላይታ ሶዶ፣ አዋሳ፣ዝዋይ፣ ‘በካቻማኔው’።” አንዱ ረዳት ለረጅም ጊዜ ወደ ኤርትራ ከሚሄደው አውቶብስ ጋር ይሰራ ስለነበር ዛሬም እየረሳው “አስመራ፣ምፅዋ፣አሰብ፤” እያለ ይጣራል። ብቻ ብዙ ባጠቃላ ለጆሯቹህ እንግዳ የሆኑ ስሞችን ልትሰሙ ትችላላቹህ።
“ጥቁር ውሃ፣ሙከጡሪ፣ወንዶ፣ዴምቢዶሎ፣…”

አውቶብሱ መንቀሳቀስ ሲጀምር ከቆንጆዋ ጐን የተቀመጡ በእድሜ ጠና ያሉ ሽማግሌ ጋ ሄጄ ‘አባቴ ቦታ ልቀይሮት ? ያ የሚመችዎትከሆነ ማለቴ ነው?’ ብየ ስጠይቃቸው አላቅማሙም ፊት ማን ይጠላል ?!
……………………………………………..
ስሜን ስነግራት ፈገግ ብላ “ፎዚያ” አለችኝ። ስትስቅ ደግሞ ገዳይ ነች። በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት አቆራርጠን ፣ኮተቤን አጋምሰን ፣በሰንዳፋ አድርገን ቼ! ወደ ደሴ !!
መንገዱም አላጠረም አውቶብሱም አልፈጠነም ነገር ግን ከፎዚያ ጋር የሞቀ ጨዋታ ስለጀመርን ጉዞው መዋከቡን ያወቅሁ ጣርማ በር ዋሻ ስንደርስ ነበር ።
የጣርማ በር ዋሻ ተራራው ተፈልፍሎ ውስጥ ለውስጥ ወደ አንድ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርዝመት ያለው የዋሻ መንገድ ነው። ደግ ደጉን እናውራ ካልንም ጣልያን ከሰራቸው በጐ ነገሮች አንዱ ይህ ነው። ለነገሩ የውድነህ ክፍሌን “የታፈነ ጩኽት” የተሰኘ ይህ ዋሻ ተደርምሶ ሰዎች መውጫ አጥተው የሚያሳይ ቲያትር ካየሁ በሗላ በባህር ዳር እየዞርሁ መሄድ ጀምሬ ነበር። ‘ሌላም መንገድ አለ!’ ይሉሃል ይሄ ነው!!

ደብረ ሲና እንደደረስን ለምሳ ወረድን ። ረዳቱ “ሃያ ደቂቃ ብቻ !” በማለት ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጠ።
የእውቁ ደራሲና ገጣሚ ዳኛቸው ወርቁ ሃገር
የደብረሲናን መሬት እንደረገጥን በቆሎ ሻጮች ተከበብን።
“ጋሼ ቆሎ፣ፋዘር ጦስኝ ፣ እትየ ቆሎ ልጋብዝሽ ? እስኪ ቅመሰው ፣ ያዝ ልጋብዝህ፤ ምርጥ የሻይ ቅመም ይዣለሁ ትፈልጋለህ?”

ወደሆቴሉ በር ስንጠጋ የጥበቃ ሰራተኛው ከአካባቢው አባረራቸው። አንዳንዶቹ ይሰድቡታል። አንዳንዶቹ “መብቴ!! ይሄን ደግሞ ልትከለክለን ነው? ከሆቴልህ አልገባንብህ እዚህ መቆም ዴሞክራሴ መብቴ!” ሲሉት እርሱም ዝም አይልም “ውይ ዴሞክራሴውን አግኝተሽው ሞተሽ? ድንቄም መብት! መብትስ ባሳዩሽ!” ይላል። ምሳ ከፎዚ ጋር በላን ። በሚያምሩ ከንፈሮቿ ሚሪንዳ ስትጠጣበት የብርቱካን ዘለላ መሰሉ። ሚሪንዳ እንደዚህ ከንፈር ያሳምራል እንዴ? ብዙ ሰው ባንድ ወቅት ከሚሪንዳ ጋር ተኮራርፎእንደነበር አስታውሳለሁ። ሼኹ በዚህም የተነሳ “ታዲያ እኔ ነገዳዴ ና ገፈርሳን ብገዛው የአዲስ አበባ ህ ህዝብ ውሃ አልጠጣም ሊል ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል አሉ።ወይ ፀባይ ማጣት አዲስ አበባ ፀባይ ቢኖርሽ ኖሮ ዛሬ ውሃ ሲጠፋ ፔፕሲና ሚሪንዳ በቧንቧ ይከፋፈል ነበር።
ወደ አውቶብሱ ስንመለስ ቆሎ ሻጮቹ መልሰው ከበቡን ። “ጋሼ ቆሎ ልጋብዝህ ?” በማለት እጄ ላይ በመስፈሪያው አስጠጋችልኝ። ተቀበልኳት። ለመሸጥ ያላት ከፍተኛ ጉጉት ይገርማል። ገዛሗት። ስምሽ ማን ይባላል? አፈረች ቆሎ ሻጯ ተቅለሰለሰች “እ?” ‘ስምሽን ንገሪኛ?’ አንገቷን ደፋች። ‘ተማሪ ነሽ ?’ ጥያቄ ቀየርኩላት። በአዎንታ እራሷን ነቀነቀች። ስንተኛ ክፍል ነሽ ? አምስት ጣቷን ዘርግታ አሳየችኝ፡፡

ሁሉም ቦታ ቦታውን ይዞ አውቶብሱ መንቀሳቀስ ሲጀምር አንዱ በመስኮት እጁን አሾልኮ በርከት ያለ ቆሎ ከተቀበላት በሗላ ገንዘቡን እንዲከፍላት እጇን ብትዘረጋለትም ሊከፍላት አልቻለም፡፡
አውቶብሱ መንቅሳቅስ ሲጀምር ‘ቆይ ሂሳቧን አልከፈላትም’ በማለት ትኩር ብየ ሳየው “ምን አባህ ታፈጣለህ !?” በሚል ስሜት ገላመጠኝ፡፡

አውቶብሱ ጉዞውን ቀጠለ….ሳንቲሜን!.. ….ገ…ን…ዘ…ቤ…ን! በማልት ጮኽች አውቶብሱን ጎትታ ማስቀረት ሁሉ ፈልጋ ነበር፡፡ ግን በምን አቅሟ ለራሷ ቆሎ ተሸክሞ መዞር አጠውልጓታል፡፡ አውቶብሱ ራቀ—- እርሷም ራቀች— ድምጿም ራቀ ” ሳ–ን–ቲ–ሜ–ን ! — ገ—ን—ዘ—ቤ—ን!” በሩቁ እየሮጠች አውቶብሱን ስትክተል ንፋሱ ቀሚሷን ሲያነሳባት ‘ሃፍረቷን’ መልሳ ለመሸፈን ጥረት ስታደርግ በቁና የያዘችው ቆሎ ተበተነባት ፡፡ አይኖቼን ጨፈንሁ ራሴንም መዳፎቼ ውስጥ ቀበርሁት፡፡
……….,,,,,………….,,,,,,,,,……………

ደሴ ከፎዚ ጋር በተቀጣጠርንው መሰረት በቀጣዩ ቀን ምሽት ቃሉ ሆቴል ለራት ተገናኘን፡፡
አልኮል እንደማትጠጣ ነገረችኝ፡፡ ባይሆን ወይን አትሞክሪም ፎዚያ? “ሓራም ነው!” አለች ኮስተር ብላ፡፡
ከፎዚያ ጋር ባለኝ ቆይታ ደስተኛ ነኝ ነገር ግን የደብረ ሲናዋ ቆሎ ሻጭ ሁኔታ እንዳስቆዘመኝ ነኝ፡፡
የእንዳለ አድምቄን “ሽልንጌን” የተሰኘ ዜማ አስታወሰቺኝ፡-
“ሽልንጌን ——ሽልንጌን—-ሽልንጌን
ሽልንጌን –ሽልንጌን– እያለች
ያላደላት — ድሃ–ውድቃለች፡፡

ቆሎ—————ቆሎ ሽልንጌን ——ሽልንጌን—-ሽልንጌን
ሽልንጌን –ሽልንጌን– እያለች
ያላደላት — ድሃ–ውድቃለች፡፡”

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on December 13, 2014
  • By:
  • Last Modified: December 13, 2014 @ 10:22 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar