ከሃዊ ኦላኒ ከሰሳ
“የራበው ሥራ ፈልጐ ማግኘት የማይችልና ልጆቹን ለማስተማር አቅም ያጣ ሰው ከባርነት ነፃ ነው ማለት አይቻልም፡፡” የሚለው የአሜሪካዊው ፕሬዚዳንት ሊንደን ቢ. ጆንሰን ንግግር እውነትነት አሁን አሁን በጆሮዬ መደወሉ ራሴን እያስገረመኝ መጥቷል፡፡ የዛሬ አምስትና ስድስት ዓመት ገደማ ሰዎች፤ ስለኑሮ ውድነት ሲጽፍ ብዙዎቻችን እያነበብን ፈገግ ከማለት በቀር ብዙ ልባችን አልተነካም ነበር፡፡ ምናልባትም በጣም አልፎ አልፎ ከምናነባቸው መጣጥፎች ይልቅ መንግስት ስለ ልማት የሚነፋው ጥሩንባ አደናቁሮን ይሆናል፡፡ አሁን አሁን የመንግሥት መዝገበ ቃላት “ልማት” የሚለው ትርጓሜ ግራ እያጋባን መጥቶ ጭራሽ ወደ ብስጭት የተመነዘረብን ብዙ ነን ብዬ አስባለሁ፡፡ መንግስት ልማት የሚለው ከእኛ አፍ “ቫት” እያለ የሚነጥቃትን ገንዘብ ሰብስቦ ለሌቦች ካጠገበ በኋላ፣ በፍርፋሪዋ የሚሠራትን መንገድና ጤና ጣቢያ ወይም ትምህርት ቤት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ “ኮንደሚኒየም”እየተባሉ የተሠሩት ቤቶች አካባቢ ያለውን ግድየለሽነት ተመልከቱ፡፡ የውሃ መፍሰሻ ቦዮቹ ገና ተሠርተው ሳያልቁ ይፈርሣሉ። ሕንፃው ውስጥ ያሉትን የግብር ይውጣ ሥራዎች ተውአቸው፡፡ ለመሆኑ ልማትና ዕድገት ምንድነው? ወረቀት ላይ የሃሰት ሪፖርቶችን ከምሮ መቀለድ ነው። ቀልድና ውሸትስ እስከ የት ያዘልቀናል? ከወር ወደ ወር ሰዎች በልተው የማደር አቅማቸውን እያጡ፣ ልጆቻቸውን ማስተማር ተራራ መቧጠጥ እየሆነባቸው ሲመጣ — እንዴት ስለ ዕድገት ይወራል? ካድሬዎች ስለልማትና እድገት ብዙ ቢለፈልፉም ከሕዝቡ የበለጠ ጓዳውን የሚያውቅ ማንም ሊኖር አይችልም፡፡ አለ ቢባልም ከተራ ቀልድነት አያልፍም፡፡ እርግጥ ነው፤ ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ጥቂት ሰዎች በኑሯቸው አድገው ይሆናል፤ ለስላሳ መጠጣት የማይችሉ ዛሬ ቤታቸው ውስኪ ደርድረው የሚመርጡበት ዕድል ደርሷቸው ይሆናል፡፡ያ ግን ዕድገት አይደለም፡፡
የማሕበረሰብ ሳይንስ ምሁራን የዕድገትና ልማትን ዓላማዎች እንዲህ ያስቀምጡታል – የሕዝቡን የገቢ መጠን በፍጥነት ማሳደግ ለዜጐች የሥራ ዕድልን መፍጠር መሠረታዊ የሆኑ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጐቶችን ማርካት፤ ማህበራዊ ፍትህን ማስፈን ሥራንና የቁጠባ ባህልን በሕብረተሰቡ ማስረጽ መልካም አስተዳደርና አሣታፊ የሆነ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም ተጨማሪ ነጥቦች የአንዲት ሀገርንና ሕዝብን ዕድገት መንገድ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ያለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ከዚህ በተቃራኒ መቆሙ ግልፅ ነው፡፡ ቁጠባውንም በውድም ሆነ በግድ በየሰበቡ ለማስለመድ የሚደረገው ጥረት አይተናል፡፡ የፖለቲካው አሣታፊነት ጉዳይ የሕፃን ልጅ ዕቃ ዕቃን የመሰለ ቀልድ ስለሆነ ጉዳዩ ለሰለቸው አንባቢ ይህን አንስቶ እንዲህና እንዲያ ማለት እንደ ደንቆሮ መቁጠር ሊመስልብኝ ይችላል፡፡ ጠቃሚ ባህሎችን ማሳደግ በሚለውም መሥመር እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ ሥነ ጽሑፉንና ባህሉን ማሳደጉን እኔ በግሌ እደግፈዋለሁ፡፡ ልክ ነው ብዬም አምናለሁ፡፡ አንዱ በባህሉ እየኮራ፣ ሌላው እያፈረ የሚደበቅባት ሀገር አሁንም እኩልነት የጐደላት ስለሆነች ያንን ሕልም ማለም ጠባብነት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሰዎች በወጣትነት መንፈስ በስሜታዊነት ያደረጉትን ነገር ምራቅ ሲውጡ እንኳን ለማስተካከል ያለመቅናታቸው የሚገርም ነው፡፡
ሰው በገዛ ሀገሩ ባዕድ እየሆነና እየተገፋ መኖሩ የሚያመጣው ልማት ፈፅሞ ግልጽ አይደለም፡፡ ለመሆኑ መንግስት ማለትስ የሰዎች ስብስብ አይደለም እንዴ? እንዴት ይህንን ነገር ማሰብ ያቅታቸዋል? ባለሥልጣን ሲኮን ተከትሎ የሚመጣው አጃቢ ወታደር፣ ያበጠ ወንበር፣ የነገን ጉዳይ ያዘናጋልና መሪዎችም ሊያስቡበት የሚገባ ይመስለኛል። አብዛኛው ሕዝባችን ከእጅ ወደ አፍ እንኳን ኑሮ እያቃተው ከመጣ፤ የመኖር ዕድሉ እየጠበበ ከሄደ ሊፈጠር የሚችለው ነገር ምንድነው ብሎም ማሰብ ደግ ይመስለኛል፡፡ የህውሃት አማካሪዎች ምናልባት እውነት የማይናገሩ አሸርጋጆች እንደሆኑ የሚካድ አይደለም። ሕዝቡ እየተራበ “ጠግቧል”፣ እየተማረረ “ደስተኛ ነው” እያሉ ከሆነ ፍፃሜው አያምርም። በርግጥ ሥልጣን ላይ ያሉ አባገነኖች እኛ ብቻ ነን ሰው የሚሉትን አባዜ ቢተው መልካም ነው።ህዝብ ምንም አናመጣም የሚለውን ፈሊጥ መልካም አይደለም፣ ሥልጣን ያላቸው ናቸው ለችግሩ መቋጫ መፍትሄ ሊያበጁለት የሚገባቸው በኋላ በሰፈሩት መሰፈር አይቀርምና፡፡
ቶማስ ጀፈርሰን፤ ሁሉም ሰው የየራሱ ዘመን አለው፣ በሕይወት የሌለ ሰው በሕያው ሰው ዘመን ሊወስን አይችልም እንደሚል፣ አሁን ያለውን ኑሮና ሕይወት የማያዩት መሪዎች ራዕይ ሊያዘልቀን ይችላል ብሎ ማመን ያስቸግራል፡፡ ባለስልጣን ተብዬዎች ግን በጤፍ ዋጋ፣ በስኳርና በትራንስፖርት ጉዳይ ያለውን ጣጣ ዛሬ ቢያዩ፣ እራሳቸው ደንግጠው ጭንቅላታቸውን ይይዙ ነበር ዳሩ እነሱ ማን ሆኑና?፡፡ በዓመት ውስጥ ለአንድ የሆቴል ተመጋቢ ቢያንስ ሦስቴና አራቴ ዋጋ ይጨምርበታል፡፡ ታዲያ ሆዱ ባልጠገበ ሲቪል ሠራተኛ ተሠርቶ፣ ሀገርን ማሳደግ ይቻላል እንዴ? ህውሃቶች የውሸት አዲስ ሕልም ያልሙ እንጂ — የውሸት አዲስ ራዕይ ያምጡ! ተግባራቸው ግን ዜሮ ነው። የስነ አመራር ምሁሩ ጆን ሲ ማክስዌል እንደፃፉት፤ በየዓመቱ ዶሮዎቹን የክረምት ጐርፍ የሚወስድበት ዶሮ አርቢ፣ ሁልጊዜ በዶሮ ላይ የሙጢኝ ማለት የለበትም፤ ይልቅስ ጐርፉ ላይ ዋኝቶ አልፎ ሀብት የሚሆን ዳክዬ የማርባት ጥበብና ዘዴ ሊኖረው ይገባል። መቼም መንግስት ተብዬው ሁልጊዜ በሕይወት በሌሉት ላይ መንጠልጠል ያለበት አይመስለኝም፤ ፕሬዚዳንት ሊንደን ቢ. ጆንሰን እንዳሉት፤ ድሀና ሀብታም በጠብደል ግድግዳ ሲለይ ጥሩ አይደለም። ይልቅስ ግድግዳው የመስተዋት ነውና በኋላ የሚያመጣው መዘዝ መጥፎ ነው፡፡ ከፊሉ በሌብነት እየበለፀገ፣ ሌላው በጨዋነት እየተራበ – ለዘላለም – አይኖርምና መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ዶክተር መረራ ጉዲና እንደሚሉት፤ የራበው ሕዝብ – መሪውን ለመብላት እንደሚነሳ – ካሁኑ ማሰብ የግድ ይላል፡፡ ታዲያ – የኛም ምርጫ ይኸው ነው።
ከሃዊ ኦላኒ ከሰሳ
ለአስተያየቶ በዚህ ኢ_ሜል ያገኑኛል
Hawiolani@gmail.com
Average Rating