ጉንፋን ቀላል በሽታ አይደለም፣ ሰውነትን አዳክሞ፣ እንቅልፍን አሳጥቶ፣ እያነጫነጨ ሥራ እንዳንሰራ የሚያደርግ በሽታ ነው። አሁን ደግሞ ጊዜው የከባድ ጉንፋን ወይም ፍሉ ነውና ድንገት በከባድ ጉንፋን ብንያዝ ቤታችን ውስጥ በምን ልናክመው እንደምንችል ስናነብ ያገኝነውን እናካፍላችሁ ዘንድ ወደ አማርኛ መለስነው።
ማር
በቤት ውስጥ ራስን ከሳልና ከጉንፋን ለማከም ዋነኛ ተመራጭ ከሆኑት አንዱ ማር ነው። የህክምና ጠበብቶችም ከመኝታ በፊት ማር መብላት ሳልን ከመከላከሉ በተጨማሪ ጥሩ እንቅልፍ እንዲኖረን እንደሚያደርግ ይስማሙበታል። በዚህ አጋጣሚ ግን ማር ዕድሜው ከአንድ ዓመት በታች ለሆነ ህጻን መስጠት አይመከርም።
የሎሚ ጭማቂና ማር
በአንድ ማንኪያ ማር ላይ የሎሚ ጭማቂ ቀላቅሎ በአንድ ብርጭቆ ለብ ያለ ውሃ ጋር በማድረግ ቢጠጡት የጉሮሮ ማሳከክን (ሶር ትሮት) ይከላከላል።
ሽንኩርትና ስኳር
የሽንኩርት ጭማቂ ብዙዎችን በተለይ ከደረቅ ሳል እንዳሻላቸው ይናገራሉ። ይህ የቆየና በአባቶቻችን ጊዜ የነበረ ፍቱን መፍትሄ ነው። አዘገጃጀቱ እንደሚከተለው ነው።
ሽንኩርቱን ይላጡና ከታች (ከሥሩ) በኩል ይቁረጡት፣ ከዚያም ከላይ በኩል ጫፉን እንዲሁ ይቁረጡትና መሃሉን ፈልቅቀው ጉድጓድ ያብጁ፣ ታዲያ ከታች ቀዳዳ እንዳይኖረው ይጠንቀቁ፣ ወዲያው በላይ በኩል ሁለት ወይም ሶስት ማንኪያ ስኳር ይጨምሩበትና ብርጭቆ ውስጥ ቀስ ብለው አስቀምጠው ያሳድሩት። ሌሊት ስኳሩ ቀልጦ ያድራል፣ ያን ጊዜ ሽንኩርቱም የራሱን ውሃ ወይም ጭማቂ ያወጣል፣ ፣ በሚቀጥለው ቀን ጠዋት የቀረውን ስኳር ከሽንኩርቱ ውስጥ አውጥተው እዚያው ብርጭቆ ውስጥ በመገልበጥ እንደ ሽሮፕ ይጠጡት፣ የሚመር ከመሰለዎ ጥቂት ማር ማድረግ ይቻላል።
ሽንኩርት፣ ዝንጅብል እና ማር
እኩል በሆነ መጠን ውሃና ማር በግማሽ ብርጭቆ ይቀላቅሉ፣ ከዚያ አንድ የተከተፈ ሽንኩርት እና የተከተፈ ዝንጅብል ይጨምሩበት፣ ይህን አድርገው ሌሊት ፍሪጅ ውስጥ ያሳድሩት፣ በማግስቱም እንደ ሽሮፕ ይጠጡት። ለሳል ግሩም መፍትሄ ነው።
የተቀቀለ ሽንኩርት እና ማር
የተከተፈ ሽንኩርትን፣ እስኪሳሳ ድረስ ይቀቅሉት፣ ከዚያ ሽንኩርቱን ከቀቀሉበት ድስት ላይ ያውጡትና በቀሪው ውሃ ውስጥ ትንሽ ማር ያድርጉበት፣ ይህንን በማንኪያ በየ አራት ሰአቱ ይውሰዱ።
ለመሆኑ ጉንፋን እና ሳልን በተመለከተ ዶክተር ማየት ያለብን ምን ከሆነ ነው? እነዚህን ምክሮች ያገኘንበት ጤና እና ጤንነት ወይም ሄልዝ ኤንድ ሄልዚ ድረገጽ የሚከተለውን ጨምሮ ይነግራል።
ዶክተር ማየት ያለብን
– የሰውነት ሙቀታችን መቶ ዲግሪ ፋራናይት (38 ዲግሪ በሴንቲግሬድ) እና ከዚያ በላይ ከሆነ
– አየር በምንስብበት ወይም በምንተነፍስበት ጊዜ የተለየ ድምጽ የሚወጣን [የሚሰማን] ከሆነ፣
– ደረታችን ላይ የሚያቃጥል ስሜት ከተሰማን
– ስንስል አረንጓዴ፣ ሮዝ ወይም ደም የሚስል ፈሳሽ የሚወጣን ከሆነ ..
– ከአንድ ሳምንት በላይ ህመሙ ካልተሻለን፣
ራሳችንን ከከባድ ጉንፋን ወይም ፍሉ እንጠብቅ። መልካም ጊዜ።
Average Rating