www.maledatimes.com ፓርላማው በስህተት ዲሞክራሲያዊ ሆኖ የዋለበት ቀን - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ፓርላማው በስህተት ዲሞክራሲያዊ ሆኖ የዋለበት ቀን

By   /   October 15, 2012  /   Comments Off on ፓርላማው በስህተት ዲሞክራሲያዊ ሆኖ የዋለበት ቀን

    Print       Email
0 0
Read Time:19 Minute, 59 Second
በዚያው ሰሞን በተካሄደ አንድ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ታዲያ፤ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት(ማለትም አዲስ ዘመን፣ኢትዮጵያን ሄራልድ፣ በሬሳ፣ አልዓለም..) ተጠሪነታቸው ለአዲሱ ማስታወቂያ ሚኒስትር እንዲሆን፤ በሌላ አገላለፅ አቶ በረከት እነዚህን ሚዲያዎች በቦርድ ሰብሳቢነት እንዲመሩ፤ የወቅቱ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሪት ነፃነት አስፋው ደግሞ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን በቦርድ ሰብሳቢነት እንዲመሩ የሚጠይቅ የሹመት ፕሮፖዛል በምክር ቤቱ የባህልና መገናኛ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አማካይነት ለፓርላማው ይቀርባል። እንደተለመደው የኢህአዴግ አባላት …ሃሳቡን እየደገፉ፤ተቃዋሚዎች ደግሞ እየተቃወሙ ውይይቱ ቀጠለ….
…በመሀከል ግን አንድ ያልተጠበቀ ሀሳብ- ካልተጠበቁ ሰው ተሰነዘረ።የቤቱ አጠቃላይ ድባብ ከመቅፅበት ተለወጠ…አዎ! አንድ ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለስልጣን እጃቸውን በማውጣት በፕሮፖዛሉ ላይ ከፍ ያለ ተቃውሞ ማቅረባቸው፤ የውይይቱን መንፈስ ፈፅሞ ወዳልተጠበቀ መንገድ መራው።
ባለሥልጣኑ በቁጣ ድምጽ ተቃውማቸውን ቀጠሉ፦”….በፍፁም! በፍፁም! ተቀባይነት የሌለው ፕሮፖዛል ነው!አስፈፃሚው አካል በሚመራቸው መስሪያ ቤቶች የቦርድ ሰብሳቢ ይሁን ማለት፤አፈናን ማጠናከርና ራሱ ከተጠያቂነት እንዲያመልጥ መንገድ ማመቻቸት ነው…” ቁጣቸው እየጨመረ መጣ፦ “… ሰሞኑን የ ኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅን ወይዘሪት ሰሎሜ ታደሰን አግኝቻታለሁ።አቶ በረከት የማስታወቂያ ሚኒስትር ሆኖ ከተሾመ በሁዋላ አሠራራቸው ነፃነት ማጣቱን ነው የነገረችኝ…”
“…አቶ በረከት ገና በሹመቱ ማግስት ነባሩን የማስታወቂያ ሚኒስቴር ህንፃ በመልቀቅ ቢሮውን ወደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን 9ኛ ፎቅ አዛውሮታል።ከቅርብ ሆኜ ሁሉን ካልተቆጣጠርኩ ለማለትና ነፃነት ለማሳጣት ነው ይህን ያደረገው። እሱን ዝም ስንል ይባስ ብሎ አሁን ደግሞ በሥሩ የሚገኙ መስሪያ ቤቶችን በቦርድ ሰብሳቢነት ይምራ የሚል ኢ-ዲሞክራሲያዊ የሹመት ሰነድ ቀርቦልናል።ይህ ፈፅሞ ሊፀድቅ ቀርቶ ሊታሰብ የማይገባ ነው። ስለዚህ ይህ ምክር ቤት ይህን ፕሮፖዛል ሊያፀድቀው አይገባም!” አመሰግናለሁ!”
በቤቱ ውስጥ የፀጥታ ድባብ ሰፈነ። ተናጋሪው በስብሰባው ላይ ከነበሩት ከፍተኛ የኢህአዴግ ሹመኞች ዋነኛው በመሆናቸው፤ ለተባሉት ነገር በሙሉ እጅ ማውጣት የለመዱት የኢህአዴግ “እጅ ሥራዎች” ማለትም የፓርላማ አባላቱ ግራ ተጋቡ።አለቃቸው አቶ በረከት በሌሉበት የሹመት ፕሮፖዛሉን አቅርበው ያፀድቁ ዘንድ የቤት ሥራ ተሰጥቷቸው የመጡት የባህልና መገናኛ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ አህመድ ሀሰን በበኩላቸው መድረኩ ላይ እንደወጡ ዐይናቸው ፈጦ ቀረ። ነገሩ አላምር ያላቸው ምክትላቸው አቶ አማኑኤል አብርሐም ወደ መድረኩ በመውጣት የተሰጣቸውን የቤት ሥራ በድል ለማጠናቀቅ የተቻላቸውን ያህል ጥረት ቢያደርጉም፤ የሹመቱን ኢ-ዲሞክራሲያዊ አለመሆን ማስረዳት አልቻሉም።ድምፅ ሳይኖረው አይድል ሊወዳደር እንደመጣ ጎረምሳ በደፈናው ነው ድርቅ ያለ ሙከራ ያደረጉት። ውጤቱም፦”ለዛሬው አልተሳካም” የሚል ሆነ። ተንደርድረው ሲወጡ “ታሪክ ሊሠሩ ነው” የተባሉት አቶ አማኑኤል ፤እንደ አቶ አሕመድ ሁሉ ዐይናቸውን አፍጥጠው ቀሩ። የድሮው እረኛ ስንኝ ጆሮዬ ላይ አንቃጨለብኝ፦
ዳገት ዳገት ስሄድ አገኘሁ ሚዳቆ፣
ጅራቷን ብይዛት ዐይኗ ፍጥጥ አለ።
አዎ! በስተመጨረሻም ሁሉም የኢህአዴግ አባላት፤ እጃቸውን ተቃውሞ ላቀረቡት ባለስልጣን ሰጡ።ፓርላማው የአቶ በረከትን ሹመት ውድቅ አደረገ።
የአቶ በረከትን የቦርድ ሰብሳቢነት ሹመት አጠንክረው በመቃወም ለአንድ ጊዜም ቢሆን ውድቅ እንዲሆን ያስደረጉት እኚህ ሰው፤ በወቅቱ የመንግስት ቃል-አቀባይና የፓርላማው የመከላከያና የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ቋሚ ሰብሳቢ የነበሩት የህወሀቱ አቶ ሀይለ-ኪሮስ ገሠሰ ናቸው።
በወቅቱ ውስጥ አዋቂዎች አቶ ሀይለ-ኪሮስ የአቶ በረከትን የቦርድ ሰብሳቢነት ያን ያህል ርቀት ሄደው የተቃወሙት፤ ሲጠብቁት የነበረውን የማስታወቂያ ሚኒስትርነት ስልጣን ስለወሰዱባቸው ነው ቢሉም፤ለመቃወም የሰነዘሩዋቸው ሃሳቦች ግን “ሎጂካል “ ነበሩ።
እናም… በስብሰባው መጨረሻ እንደተለመደው አፈ-ጉባኤው ፦”የሹመቱን ፕሮፖዛል የምትደግፉ..” በማለት ቤቱን ጠየቁ።…. አንድም እጅ አልታየም-አንድስ እንኳ።
“እሽ የምትቃወሙ…”ሲሉ፤ ተቃዋሚዎች በድል አድራጊነት፤ኢህአዴጋውያኑ ደግሞ አቶ ሀይለ-ኪሮስን ተከትለው በአንድ ላይ እጃቸውን አወጡ።
ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ ተቃዋሚዎችና የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ተመሣሳይ አቋም ያንፀባረቁበት፤ የኢህአዴግ ድርጅታዊ ሃሳብ-በራሱ ሰው ውድቅ የሆነበት ታሪካዊ ቀን።
በነገሩ እጅግ የተደነቀው ይህ ፀሀፊ፤ሁኔታውን በወቅቱ ይሠራበት በነበረው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ፦” ወደ ዲሞክራሲ አቡጊዳ ልንገባ ይሆን?” በሚል ርዕስ ለህትመት አብቃው።
ዳሩ ምን ያደርጋል?
በቀጣዩ ሣምንት የፓርላማው ስብሰባ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ የቀረበው፤ ይሄው በሁሉም የምክር ቤት አባላት ውሳኔ ውድቅ ተደርጎ የተቋጨው የአቶ በረከት የቦርድ ሰብሳቢነት ሹመት ጉዳይ ሆነ።
ሁኔታው የልጆች ዕቃ ዕቃ የሆነባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፤በፓርላማው ውሳኔ የፀደቀን አጀንዳ ቆፍሮ በማውጣት እንደገና ለውይይት እንዲቀርብ የተደረገበት አሠራር ሊገባቸው ስላልቻለ ስብሰባውን እንደሚቃወሙ ቢገልፁም፤ የኢህአዴግ ዋነኞቹ ሹመኞች፦” እኛው የሠራነው ፓርላማ የኛን ሃሳብ ውድቅ አድርጎ የታባቱ ሊገባ?” በሚል መንፈስ እንደገና ታጥቀው ስለመጡ፤”የምን ህግ?” በሚመስል አመለካከት ስብሰባው እንዲጀመር አስደረጉ።በሌላ አገላለፅ የአቶ መለስ ቅኔ ተመዘዘ ፦
“ለጨዋታ ታህል-ሣሳያት መንገዱን፣
እሷ የምር አርጋው-ካወጣችው ጉዱን፣
ህጉን አዳፍኑልኝ-አስፉና ጉድጓዱን” የሚለው።
እናም ”… በአንድ ሣምንት ውስጥ ፤ሳይጨመርበት፤ ሳይቀነስበት ያው የሹመት ሰነድ በተመሣሳይ ሰዎች እንደገና ለዛው ምክር ቤት ቀረበ። በጣም በሚያስገርም ፍጥነት የድጋፍ ሀሳቦች ከኢህአዴጋውያኑ የፓርላማ አባላት መጉረፍ ጀመሩ…
”…ተገቢ የሆነ፣ተጠያቂነትን የሚያጠናክር…ዲሞክራሲያዊና አሳታፊ “ወዘተ እየተባለ ያው ሰነድ መወደሱን፣መሞገሱን፣መሞካሸቱን ቀጠለ።
ግን…ግን እዚህ ላይ.…ሹመቱን በመደገፍ የመጀመሪያው ተናጋሪ የሆኑት ማን ይመስሏችሁዋል?
ብዙ አትመራመሩ።ባለፈው ሣምንት ፕሮፓዛሉን ወድቅ እስከማስደረግ ድረስ ጠንካራ የተቃውሞ አርበኛ ሆነው የታዩት አቶ ሀይለ-ኪሮስ ገሠሰ ናቸው።ልብ በሉ! አቶ ሀይለ ኪሮስ“ኮከብ ተጨዋች” ተብለው ከተመረጡ ገና አንድ ሳምንት አላለፋቸውም። ባለፈው ሣምንት ፦”አፋኝና ጨቋኝ” ያሉትን ፕሮፖዛል፤ ነው ዛሬ “ዲሞክራሲያዊ” ያሉት። ከጥቂት ቀናት በፊት ውድቅ እንዲሆን ሽንጣቸውን ይዘው የሞገቱትን ሀሳብ ነው፤ ዛሬ ይፀድቅ ዘንድ ቀበቷቸውን አጥብቀው እየተማፀኑ ያሉት።
ነገሩ፤ በሰዓታት ልዩነት ነጩን ጥቁር፤ እውነቱን ሐሰት ማለት ለለመዱት ለኢህአዴግ መሪዎች፣ ለካድሬዎቻቸውና ለሆደ-ትላልቅ ደጋፊዎቻቸው ምንም ላይመስል ይችላል-“የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ!” በሚል ብሂል ላደግነው ኢትዮጵያውያን ግን ይህን ማየትና መስማት እጅግ ከባድ ህመም ነው።አዎ!የጥላሁን ገሠሰን፦” ቃልሽ አይለወጥ እባክሽን..”፤ለመደነስ ያህል ሳይሆን ከልባችን እየሰማን ያደግን ኢትዮጵያውያን፤ለስምም ቢሆን ”የአገሪቷ ትልቁ የሥልጣን አካል ነው” በሚባል ፓርላማ ደረጃ የዚህ ዓይነት “በቃል መጨማለቅን” ስናይ፤ እንዴት ጤንነት ሊሰማን ይችላል?
አዎ! ከቀናት በፊት አቶ ሀይለኪሮስን ተከትለው የሹመት ፕሮፖዛሉን ውድቅ ያደረጉ ጭራሮ እጆች፤ዛሬም እርሳቸውን ተከትለው ሹመቱን ሊያፀድቁ ብቅ ብቅ ብለዋል። እንደኔ በቅርበት ለተከታተለው ነገሩ፦”አጃኢብ!”የሚያሰኝ ነው። መሥሪያ ቁሣቁሳቸው ችግር ያለበት ለወንበርና ጠረጴዛ የተመረጡ እንጨቶች እንኳ አላግባብ ሲመቱ፤ከአናፂያቸው ፈቃድ ውጭ ሢሰነጠቁና በራሳቸው ፍላጎት ወደ ተለየ አቅጣጫ ሲሄዱ ብዙ ጊዜ አይቻለሁ- የኢህአዴግ አባላት ከግዑዝ እንጨት ያነሱበትና በራሳቸው ሀሳብ መሄድ ያልቻሉበት ምሥጢር ግን ሊገባኝ አልቻለም።
በስተመጨረሻም; ጉደኛው ፓርላማ ውድቅ አድርጎት የነበረውን የነ አቶ በረከት ሹመት አጽድቆ ስብሰባው ተጠናቀቀ። መቅረፀ-ድምፄን እንዳነገብኩ ከፎቅ ወደ ምድር ሮጬ በመውረድ መውጫ በሩ ላይ ቆምኩ። ከስብሰባው አዳራሽ ከሚወጡት የፓርላማ አባላት መካከል አንድ ሰው እየጠበኩ ነው። ሰውዬው ጓደኞቻቸውን ተሰናብተው ወደ መኪናቸው ሲያመሩ ተመለከትኳቸውና በፍጥነት ደረስኩባቸው፦
“ጤና ይስጥልኝ አቶ ሀይለኪሮስ፤” አልኳቸው።
“ለቃለ-ምልልስ ከሆነ ሰዓት የለኝም፤ እቸኩላለሁ”አሉኝ።
“ረዥም አይደለም፤ ባለፈው ሳምንት የተቃወሙትን የሹመት ፕሮፖዛል እንዴት ዛሬ ደገፉት? የሚለውን ብቻ እንዲመልሱልኝ ነው”
“ከየትኛው ጋዜጣ ነህ?” በማለት ጠየቁኝ
“ከአዲስ አድማስ” አልኳቸው።
ትንሽ እንደማቅማማት ካሉ በሁዋላ፦“ እህ…ባለፈው ሣምንት ያላየሁዋቸው አንዳንድ ነጥቦች ነበሩ፤ በሁዋላ ግን ረጋ ብዬ ሰነዱን ሳየው ተገቢና ዲሞክራሲያዊ ፕሮፖዛል እንደሆነ ተረዳሁ፤ስለዚህም ደገፍኩት” በማለት በአጭሩ መለሱልኝ-የመኪናቸውን በር ከፍተው ወደ ውስጥ እየገቡ።
“እነዚያን ነጥቦች ሊገልፁልኝ ይችላሉ?”
አልመለሱልኝም።መኪናዋ የፓርላማውን ቅጥር ለቅቃ ቁልቁል ሸመጠጠች…
እኔም ቀጣይ ዘገባዬን፦”አቡጊዳ ወይስ ሀሁ?” በሚል ርዕስ ለአንባቢዎቼ አቀረብኩ። የአቶ በረከት ሹመት ውድቅ ተደርጎ የነበረበት ያ ታሪካዊ ቀንም በጋዜጦች፦”ፓርላማው በስህተት ዲሞክራሲያዊ ሆኖ የዋለበት ቀን “ተባለ።
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on October 15, 2012
  • By:
  • Last Modified: October 15, 2012 @ 10:07 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar