www.maledatimes.com የእግርኳስ ውበት እና ጠቢብ ሪኬልሜ “በቃኝ” አለ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የእግርኳስ ውበት እና ጠቢብ ሪኬልሜ “በቃኝ” አለ

By   /   September 26, 2012  /   Comments Off on የእግርኳስ ውበት እና ጠቢብ ሪኬልሜ “በቃኝ” አለ

    Print       Email
0 0
Read Time:17 Minute, 58 Second
September 20, 2012 By  www.total433.com 

“ከቡድኑ ጋር ተነጋገርኩ፣ ከክለቡ ፕሬዝዳንት ጋርም በጉዳዩ ላይ ተወያየሁ። እናም እንደማልቀጥል ነገርኳቸው። ለክለቡ ያለኝ እና የከፈልኩት መስዋትነት እጅግ በጣም ብዙ ነው። አሁን ግን ባዶነት እየተሰማኝ ነው። ከዚህ በኋላ ምንም የምሰጠው ነገር የለኝም። እኔ የዚህ ክለብ ደጋፊ ነኝ። በሙሉ ፍላጎቴ መጫወት ካልቻልኩ 50 በመቶ ሀይሌን ብቻ ይዤ ሜዳ ውስጥ መግባት አልፈልግም” ያለው ሁዋን ሮማን ሪኬልሜ ነበር።

ይህ አስተያየት ከሪኬልሜ በቅርቡ ሲሰማ የቦካ ጁኒዬርስ ደጋፊዎች ተገልብጠው ለተቃውሞ ሰልፍ ወጡ። በአካል መውጣት ያልቻሉት ደግሞ “ተክደናል” በሚል በተለያዩ ድረ-ገጾች ከልብ የሚወዱትን የእግርኳስ ንጉሳቸውን ሀሳብ ለማስቀየር ዘመቻቸውን ተያያዙት። ከእነዚህ ተቃዋሚዎች መካከል አንዱ ሌላው ታላቅ የቦካ ጁኒዬርስ ተጨዋች እና ደጋፊ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ነበር። ማራዶና የሪኬልሜን ውሳኔ በመቃወም ተጨዋቹን ያበሳጩ አስተያየቶችን ቢሰነዝርም እሱም ሆኑ ሌሎች ውሳኔውን ማስቀየር አልተሳካላቸውም።
በአርጀንቲናው ግዙፍ ክለብ ቦካ ጁኒዬርስ ደጋፊዎች እንደንጉስ የሚከበረው እና ድንገት ከእግርኳስ ተጨዋችነት እራሱን ያሰናበተው የመሀል ሜዳው መሀንዲስ ሁዋን ሮማን ሪኬልሜ

በርካታ የቦካ ደጋፊዎች እና ሌሎች የእግርኳስ አፍቃሪዎች ለሪኬልሜ ድንገተኛ “በቃኝ” ውሳኔ ምክንያት የክለቡ አሰልጣኝ ሁሊዮ ፋሊሲዮኒ ናቸው በሚል አሰልጣኙ ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል። በተለይ በኮፓ ሊብሬታዶሬስ ዋንጫ ጨዋታ ቦካ በኮረንቲያንስ 2-0 በሆነ ውጤት ከተመራ በኋላ አሰልጣኝ ፋሊሲዮኒ “አንተ ትሰማኛለህ” አሉ ጣታቸውን ወደሪኬልሜ ቀስረው። “አንተ ሳትሆን እኔ ነኝ አሰልጣኙ። እኔ ነኝ ውሳኔዎችን የምወስነው እንጂ አንተ አይደለህም” አሉ። ሪኬልሜ በአሰልጣኙ ንግግር መገረም ብቻ ሳይሆን በጣም ነበር የተናደደው። ከዚህ በኋላ መልበሻ ቤቱን ጥሎ ወጣና “በቃኝ” አለ።

በርግጥ በቅርቡ በይፋ ከእግርኳስ ተጨዋችነት እራሱን ጋዜጣዊ መግለጫ ጠርቶ ሲያሰናብት ውሳኔው ከቦካው አሰልጣኝ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ከመናገሩ በተጨማሪ ብዙዎችን ያስገረመ ነገር የተናገረው ማራዶናን በተመለከተ ነበር። “ያ ግለሰብ ስለእኔ ስለሚያወራው ነገር ቅንጣት ታክል ግድ የለኝም” አለ ሁዋን ሮማን ሪኬልሜ

“ሰነፉ ምትሀተኛ” ይሉታል። “ወደኋላ እየተመለስክ የቡድን ተጨዋቾችህን አግዝ” የሚል ትእዛዝ ከአሰልጣኞቹ ከመጣለት መልሱን በንግግር አይደለም የሚገልጸው። ዘገም እያለ አቀርቅሮ መሀል ሜዳ ላይ በመንጎራደድ እንጂ። ደጋፊዎች እና መላው የእግርኳስ አፍቃሪ ወደስታዲዬም የሚመጣው እና ቴሌቪዥን መስኮቱ ላይ የሚያፈጠው እየተሯሯጠ ሲታገል ሳይሆን ኳስን እንደፈለገ ሲያደርግ እና ምትሀታዊ ኳስ አቀባበሉን ለማየት እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል። አሰልጣኞች እሱን ቀይረው ለማስወጣት መጀመሪያ ደጋፊውን ማስፈቀድ እንዳለባቸው ሆነው እንዲሰማቸው እንዳደረጋቸው ስለሚያውቅ ስራው ኳስን ለመቀበል እራሱን ምንጊዜም ዝግጁ አድርጎ መጠበቅ እና ኳስ እግሩ ስር ከገባች በኋላ ደግሞ እያሽሞነሞነ ቡድኑ ሊያሸንፍባቸው የሚችልባቸውን ቀዳዳዎችና መልሶች ማዘጋጀት ብቻ ነው። ለአሰልጣኞች የማይመች የደጋፊዎችና የውብ እግርኳስ አፍቃሪዎች ንጉስ።

በቅርቡ በፍቅር ከሚወደው እና እንደንጉስ በደጋፊዎቹ አይን ከሚታይበት ቦካ ጁኒዬርስ ጋር መለያየቱ እና ከእግርኳስም እራሱን ማሰናበቱን ካሳወቀ በኋላ አድናቆታቸውን እና አክብሮታቸውን ለሪኬልሜ ከገለጹ ታላላቅ የእግርኳስ ተጨዋቾች መካከል አንዱ በባርሴሎና ክለብ ውስጥ አብሮት የተጫወተው አንድሬስ ኢኒዬስታ ቀዳሚው ነበር።

“ሁልጊዜም ቢሆን ድንቅ የነበረ የእግርኳስ ተጨዋች ‘በቃኝ’ ሲል መስማት እና ማየት ያሳዝናል። ሪኬልሜም ይሄንን ወስኖ ከሆነ በጣም ነው የማዝነው። እግርኳስ አንድ ታላቅና ድንቅ ሰው እንዳጣ አድርጌ ነው የምቆጥረው። ገና በታዳጊ ወጣትነት እድሜዬ እሱን ባርሴሎና ውስጥ በማግኘቴ እጅግ በጣ እድለኛ አድርጌ ነው የምወስደው። በርካታ ድንቅ እና የማይረሱ ጊዜዎችን አሳልፌያለሁ። አብሮኝ በመጫወቱም እድለኛው እኔ ነበርኩ። በተለይ ኳሷ እግሩ ስር ስትገባ የሚሰራው ተአምር፣ ለጓደኞቹ የሚያቀብላቸው አስደናቂ ኳሶችና አጠቃላይ አጨዋወቱ አእምሮዬ ላይ አሉ። በተለይ ኳስን ሰጥቶህ ሊቀበልህ እራሱን አዘጋጅቶ ሲመጣ ስታየው ‘ዋው!’ እንድትል ነው የሚያደርግህ። እንደሱ መጫወትን እና እሱን ሜዳ ውስጥ መሆን ምኞቴ ነበር” አለ ኢኒዬስታ።

ሳን ፈርናንዶ ተብላ በምትታወቀውና ቦነስ አይረስ ውስጥ በምትገኘው ስፍራ ከድሀ ቤተሰቦች የተወለደው ሁዋን ሮማን ሪኬልሜ አስር ሰዎች በሚገኙበት ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደገው። ለአርጀንቲኖስ ጁኒዬርስ ህጻናት ቡድን ሲጫወት ታላላቆቹ የአርጀንቲና ክለቦች ቦካ ጁኒዬርስ እና ሪቨር ፕሌት አይን ውስጥ የገባው ሪኬልሜ እ.አ.አ በ1995 ዓ.ም ከህጻንነት እድሜው ጀምሮ ይደግፈው የነበረውን እና የደሀውን የቦነስ አይረስ ህብረተሰብ እንደሚወክል የሚነገርለት ቦካ ጁንዬርስን በመምረጥ ግዙፉን ክለብ ተቀላቀለ።

ከዚህ በኋላ በሁለቱ መካከል ያለው መፋቀር መጠን የማይገልጸው ነበር። በቦካ አስደናቂ ብቃቱን ገና በወጣትነት እድሜው ያሳየው ሪኬልሜ ከአውሮፓ ግዙፍ ክለቦች “የእንውሰድህ” ጥያቄ ሲቀርብለት በተደጋጋሚ ጥያቄያቸውን ውድቅ ቢያደርግም ቦካ ጁኒዬርስ የገባበት የገንዘብ ቀውስ የመሀል ሜዳው መሀንዲስ ሳይወድ በግዱ የሚወደውን ክለብ እንዲለቅ ቢገደድም ተመልሶ ለቦካ እንደሚጫወት ግን በግልጽ ነበር ያሳወቀው። ቦካን ከገንዘብ ቀውስ ለማዳን በሚል በ11 ሚሊዬን ዩሮ ወደስፔኑ ባርሴሎና እ.አ.አ በ2002 ዓ.ም ከተዛወረ በኋላ በካታላኑ ክለብ ውስጥ የተጠበቀውን ያህል ሊሳካለት አልቻለም። በጊዜው የባርሴሎና አሰልጣኝ የነበሩት ሉዊ ቫን ሀል እና ሪኬልሜ በጭራሽ ሊስማሙ አልቻሉም። ቫን ሀል ልክ እንደሌሎቹ የክለቡ ተጨዋቾች ሁሉ ሪኬልሜም እንዲጫወት የሚታዘዝበት ቦታን ሸፍኖ ስራውን መተግበር እንዳለበት ለማሳየት ቢፈልጉም፣ ሪኬልሜ ግን እንደዛ አይነት ተጨዋች ሆኖ አልተገኘም። “እኔ የምፈልግበት እና ቡድኑን የበለጠ እጠቅምበታለሁ ብዬ በማስበው ቦታ ላይ ነው መጫወት ያለብኝ” የሚል ነበር ሪኬልሜ ለቫን ሀል ያስተላለፈው መልእክት።

ሪኬልሜ እና ባርሳም ባሳዛኝ ሁኔታ ተለያዩና አርጀንቲናዊው በአውሮፓ እግርኳስ ቆይታው ስኬታማ ጊዜን ወዳሳለፈበት ሌላው የስፔን ክለብ ቪያሪያል ተዛወረ። ትንሹን የስፔን ክለብ በግዙፉ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ለግማሽ ፍጻሜ ካደረሰ በኋላ ሌሎች ታላላቅ ክለቦች “ሰነፉን ምትሀተኛ” በእጃቸው ለማስገባት ቢፈልጉም የእርሱ ምርጫ ግን ወደሚወደው ቦካ ጁኒዬርስ መመለስ ነበር። “ምክንያቱም” አለ ሪኬልሜ፤ “ምክንያቱም እኔ ቀላል ግን አስደሳች ህይወትን መኖር የምመርጥ ሰው ነኝ። ያንን ህይወት የማገኘው ደግሞ ቦካ ውስጥ ብቻ ነው።” ሪኬልሜ ወደቦካ ለመመለስ ከፈጸማቸው መስዋቶች መካከል አንዱ ክለቡ ቪያሪያል መክፈል ሳይችል ቀርቶ “ገንዘቡን ስናገኝ እንከፍልሀልን” በማለት የያዘውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር የተለያየ ክፍያ “ወደቦካ ያለምንም ጭቅጭቅ እንድሄድ ከፈቀዳችሁልኝ ያልከፈላችሁኝን ገንዘብ በሙሉ እሰርዝላችኋለሁ” በማለት ገንዘቡ ሳይከፈለው የቀረበት ይጠቀሳል። ሪኬልሜ የከፈለው መስዋት በዚህ ብቻ አላበቃም። ቦካዎች ኮከቡ ተጨዋች አውሮፓ ውስጥ ይከፈለው የነበረውን ከፍተኛ የደሞዝ መጠን መክፈል እንደማይችሉ ሲነግሩት “ግድ የለም፤ እናንተ ብቻ እኔን ለመውሰድ ፈቃደኛ ሁኑ ለአንድ አመት በነጻ ያለክፍያ እጫወታለሁ” የሚል ሀሳብ አቀረበና ወደሚወደው ክለብ ከአምስት አመታት እግርኳሳዊ የስደት ህይወት በኋላ ተመለሰ።

ሪኬልሜ ለቦካ ደጋፊዎች ልክ በአፈታሪክ እንደሚሰሙ ጣኦቶችና አርበኞች ነው የሚታየው። እግሩ ስር ኳስ ከገባች ስታዲዬሙ ይደንሳል። ሪኬልሜ ግራ የሚያጋባም ፍጡር ነው። በትክክል ምን እሱ ምን እንደሚፈልግ ማንም የሚያውቅ የለም ይባልለታል። ግን ቡድን ሲሰራ እሱን መሰረት ያደረገ መሆን እንዳለበት አጥብቆ ይናገራል ይባላል። አሰልጣኞቹ በዚህ ሀሳቡ ከተስማሙ ሪኬልሜ ሜዳ ላይ ይደንሳል። ሪኬልሜ ጨዋታን እሱ በሚፈልገው ፍጥነት እንዲሄድ በማድረግ ይታወቃል። አካባቢው ያለውን እንቅስቃሴ በመርሳት በራሱ አለም መጓዝን እነደ እርሱ የሚያውቅበት የለም። ከውጤት ይልቅ ውበትን፣ ጎል ከማግባት ይልቅ ጎል የሚሆኑ ኳሶችን ለጓደኞቹ ማቀበልን፣ ከሩጫ ፍጥነት ይልቅ የአእምሮ ፍጥነትን የሚመርጥ የኳስ ጠቢብ።

የእግርኳስን ታላቅነት በዋንጫዎች ቁጥር ብቻ የምትለኩ ከሆነ ሪኬልሜ በእርግጥም የእናንተ አይነት እግርኳስ ተጨዋች አልነበረም። እሱ ከዋንጫ እና ከውጤት በላይ ነው። ሪኬልሜ እግርኳሳዊ ውበት እና ጠቢብ ነው። ለዚህም ነው “እራሴን ከእግርኳስ ተጨዋችነት አሰናብቻለሁ” ሲል በርካቶች ውሳኔውን ያልተቀበሉት።

አርጀንቲናዊው የኳስ ጠቢብ ሁዋን ሮማን ሪኬልሜ – ተራኪ ፍስሀ ተገኝ

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 26, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 26, 2012 @ 12:15 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar