www.maledatimes.com ሳቂታዋ የረጅም ርቀት ሩጫ ንግስት - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ሳቂታዋ የረጅም ርቀት ሩጫ ንግስት

By   /   September 26, 2012  /   Comments Off on ሳቂታዋ የረጅም ርቀት ሩጫ ንግስት

    Print       Email
0 0
Read Time:27 Minute, 39 Second

ሳቂታዋ የረጅም ርቀት ሩጫ ንግስት

September 25, 2012

By  www.total433.com

ኦሎምፒክ ምን እንደሆነ ከማወቄ በፊት የእሷን ስምና ድሏን ነበር የማውቀው። ስሟ በሬዲዮ በተደጋጋሚ ሲጠራ ስለሰማሁት አእምሮዬ ውስጥ ተቀርጾ ተቀምጧል። “የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆነች” የሚለው ጩኸት ልቤን አልሰረቀውም፤ ልጅ ነበርኩና የኦሎምፒክን ዋጋና ምንነት ባለማወቄ። “ሮጣ ተፎካካሪዎቿን እንደ ጭራ ከኋላ አስከትላ አሸነፈች” የሚለው ድምጽን ለማስተናገድ ግን አልተቸገርኩም። ምክንያቱም እየተሯሯጠና አቧራ እያቦነነ ለነበረ ልጅ ሩጫ፣ መቅደምና መቀደም ምን እንደሆኑ ለይቶ ለማወቅ አያስቸግረውምና።

ምን አልባት በተደጋጋሚ ፊቷ ላይ የሚታየው ፈገግታ ደራርቱ ቱሉን በተፎካካሪዎቿና ፊት-ለፊት የሚያየውን ነገር ብቻ ማንበብ በለመደ ሰው አይን ውስጥ ጠንካራና ቆፍጣና ተወዳዳሪ ላያስመስላት ይችላል። ተራራማዋ በቆጂ ውስጥ የተወለደችው ደራርቱ ግን ልክ የውድድር ማስጀመሪያው ሽጉጥ እንደተተኮሰ ነብር ትሆንና በአስደናቂ ብልሀት፣ በጽናት እና በጠንካራ ልምምድ ከታጀበው ውብ አሯሯጧ ጋር ተፎካካሪዎቿን እንዳልነበሩ አድርጋ የማሸነፍ ብቃት ያላት ድንቅ አትሌት ነች። ይሄንን ለማረጋገጥ የፈለገ ወደኋላ ብዙ መመለስ አያስፈልገውም። በህዳር ወር መጀመሪያ 2009 ዓ.ም የተካሄደው የኒው ዮርክ ማራቶን ለተወዳዳሪዎችና ሩጫውን ለመከታተል በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ለተገኘው ተመልካች የአየሩ ሁኔታ እጅግ በጣም ቀዝቃዛ በመሆኑ “ምን አለበት ከሞቀው ቤቴ ባልወጣሁ” የሚያሰኝ የነበረ ቢሆንም፤ ደራርቱ ታስብ የነበረው ግን ከድል በኋላ በደስታ ልታገኘው ስለምትችለው ውስጣዊ ሙቀት ነበር።

“ውድድሩ ሲጀመር አየሩ በጣም ቀዝቃዛ ነበር። እንዲያውም የሆነ ቦታ ላይ ለመውደቅም ተቃርቤ ነበር። ምስጋና ተጨማሪ ብርታት ለሰጠኝ እግዚአብሄር ይግባና ያንን አለፍኩ። ውድድሩን ከጨረስኩ በኋላ የተሰማኝ ግን ፍጹም ሌላ አይነት ስሜት ነው፤ በድል አድራጊነት የተገኘ የደስታ ሙቀት” አለች ተፎካካሪዎቿ የነበሩት ራሺያዊቷ ፔትሮቫን እና ፈረንሳዊቷ ዳውኔን  ቀድማ ውድድሩን በአሸናፊነት ያጠናቀቀችው ደራርቱ ለረኒንግ ታይምስ መጽሄት በጊዜው በሰጠችው አስተያየት።

ደራርቱ – ቁጥር አንዷ የሩጫ ንግስት

እንዲህ ነች ደራርቱ፤ ፈተናዎቿን በፈገግታ በታጀበው የአሸናፊነት ስሜትና ድል ማሳለፍ የለመደች። ደራርቱን በጊዜው ማንም የኒዮርኩ ማራቶን አሸናፊ ትሆናለች ብሎ አልገመታትም። ምክንያቱም በ2006 ዓ.ም ልጅ ወልዳ ስለነበር ከሁለት አመታት በላይ ከሩጫው ከመራቋ በተጨማሪ፤ ውድድሮች ባደረገችባቸው ጥቂት ጊዜያት ውስጥም ጠንካራ የሚባልና ድሮ የስፖርቱን አፍቃሪ ያስለመደችውን አይነት አቋም ባለማሳየቷ ነው። ያደገችበት ባህል ልጅ ከወለዱ በኋላ ወደስራ በቶሎ መመለስን የማይደግፍ በመሆኑ በቶሎ ወደልምምድ ባለመመለሷ ምክንያት በአንድ ውቅት ክብደቷ በአብዛኛው ስትሮጥ ከነበራት 40ዎቹ አጋማሽ ኪሎ ግራም ላይ 18 ኪሎዎች ጨምራ ነበር። ከውድድር መራቅን፣ በወቅቱ የነበረው የኒው ዮርክን ቅዝቃዜ እና በርቀቱ የአለም የማራቶን ክብረወሰንን የያዘችውና ውድድሩን ታሸንፋለች ተብላ ትልቅ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው ብሪታኒያዊቷ ፓውላ ራድክሊፍን የመሰሉ ጠንካራ ተፎካካሪዎቿና አስቸጋሪ ፈተናዎችን ከኋላ አስቀርታ ደራርቱ ቱሉ የኒው ዮርክ ማራቶንን ለማሸነፍ የቻለች የመጀመሪያዋ ሴት ኢትዮጵያዊ አትሌት ሆነች።

“በርግጥ አሸንፋለሁ ብዬ አልጠበኩም። ነገር ግን ጠንካራ ተፎካካሪ እንደምሆን አልተጠራጠርኩም። እስከመጨረሻው ለመታገል ቆረጥኩና ከእግዚአብሄር እርዳታ ጋር ለማሸነፍ በቃሁ። ባለፉት ሶስት አመታት ውስጥ ያሳለፍኩትን ሳስበው አሁን ያገኘሁት ድል የበለጠ እንድደሰት አድርጎኛል” አለች ደራርቱ ከድሉ በኋላ በፈገግታ በታጀበው አንደበቷ በሰጠችው አስተያየት።

በትምህርት ቤቷ በመካከለኛ ርቀቶች ተወዳድራ በተደጋጋሚ በአሸናፊነት ካጠናቀቀች በኋላ፤ እ.አ.አ በ1988 ዓ.ም አርሲን ወክላ በብሄራዊ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ1500 ሜትር ርቀት የነሀስ ሜዳሊያ ያገኘችው ደራርቱ፤ በአለም አቀፍ የሩጫ መድረኮች ላይ መታየት የጀመረችው በሀገር አቋራጭ ውድድሮች ላይ ነበር። ገና የ16 አመት ታዳጊ ወጣት እያለች እ.አ.አ በ1989 ዓ.ም የኖርዌዋ ስታቬንጋር ከተማ ውስጥ በተካሄደው  17ኛው የአለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ 23ኛ ደረጃን አግኝታ ጨረሰች። መሻሻልን እንጂ ወደታች መውረድን የማታውቀው ደራርቱ ምንም እንኳን የሜዳሊያ ፖዲዬም ላይ የሚያወጣት ውጤት ባታገኝም ከአንድ አመት በኋላ በተካሄደው የአለም አገር አቁራጭ ሻምፒዮና ከአለፈው አሻሽላ ውድድሩን 18ኛ ደረጃን አግኝታ አጠናቀቀች።

የመጀመሪያ አለማቀፋዊ ድልን ያገኘችው ግን በሀገር አቋራጭ ውድድር አልነበረም። በትራክ ወይም መም ውድድር እንጂ። እ.አ.አ በ1990 ዓ.ም በቡልጋሪያዋ ፕሎቭዲቭ ከተማ በተካሄደው በታዳጊ ወጣቶች የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር የተካፈለችው ደራርቱ አንደኛ ወጥታ የመጀመሪያ የሆናትን አለም አቀፋዊ የወርቅ ሜዳሊያ አገኘች። ማሸነፏ ሳይሆን ርቀቱን ለማጥናቀቅ የወሰደባት 32 ደቂቃ ከ56.26 ሰከንድ ነበር በጊዜው በሩጫው አለም መነጋገሪያ የሆነው። ወጣቷ ለውደፊት ትልቅ ተስፋ እንዳላት የገመቱ የዘርፉ ባለሞያዎች ጥልቅ ክትትል እያረጉባት እያለና በተለያዩ ብዙሃን መገናኛዋች ተስፋዋን እያስተጋቡ እንዳለ፤ በ1991 ዓ.ም ቶክዮ ጃፓን ውስጥ በተካሄደው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በግማሽ ፍጻሜው 10 ሺህ ሜትሩን 31 ደቂቃ ከ45.95 ሰከንድ በሆነ ጊዜ አጠናቃ በርቀቱ የኢትዮጵያን ክብረወሰን ሰበረችና የአለም የሴቶች ረጅም ርቀት ሩጫ ትኩረት ወደእሷ እንዲዞር አደረገች።

እ.አ.አ 1992 ዓ.ም በደራርቱ የአትሌቲክስ ህይወት ታሪክ ውስጥ ምን አልባት እጅግ በጣም ታላቁ እንደነበረ የሚነገርለት ነው። በዛ አመት በሶስት የ10 ሺህ ሜትር ውድድሮች ላይ ተካፍላ ሁሉንም ስታሸንፍ፤ ከባርሴሎናው ኦሎምፒክ መጀመር ጥቂት ቀደም ብሎ በተካሄደው የአፍርካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ርቀቱን በጊዜው የአህጉሪቷን ክብረወሰን በሰበረ 31 ደቂቃ ከ22.25 ሰከንድ ጊዜ አጠናቃ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አገኘች።

ባርሴሎና ኦሎምፒክ – ደራርቱ ቱሉና ደቡብ አፍሪካዊቷ ኤሌና ሜዬር

በባርሴሎናው ኦሎምፒክ የተፈጠረውን አለም የማይረሳው ነው። “ባርሴሎና ላይ ስካፈል ኦሎምፒክ ምን እንደሆነ ስለማላውቅ ልክ እንደማንኛውም አይነት ውድድር ነበር ያየሁት” ያለችውና በጊዜ 42 ኪሎ ግራም ክብደትና 1.56 ሜትር ቁመት የነበራት ደራርቱ፤ በታላቁ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ታሪክ አስደናቂ የፍጻሜ ውድድሮች ከሆኑት ተርታ የተመዘገበ እንደሆነ በተነገረለት የ10 ሺህ ሜትር ውድድር ልክ የማብቂያው 25ኛ ዙር ደውል ድምጽ ሲሰማ ውድድሩን ትመራ የነበረችው ደቡብ አፍሪካዊቷ ኤሌና ሜዬርን ቀድማ አፈትልካ ወጣችና የመጨረሻውን ዙር (400 ሜትር) በ64 ሰከንዶች በመጨረስ ሜዬርን በ30 ሜትሮች ያህል ቀድማ አንደኛ በመውጣት በኦሎምፒክ ታሪክ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት ሴት ሆነች። አስደናቂ የነበረው ታዲያ ውድድሩን ያሸነፈችበት አጨራረስ ብቃቷ ብቻ አልነበረም፤ ስፖርታዊ ጨዋነቷም እንጂ። አሸናፊነቷን ያረጋገጠችው ደራርቱ ነጯ ደቡብ አፍሪካዊት ኤሌና ሜዬር ሩጫዋን እስክትጨርስ ቆማ ከጠበቀች በኋላ አቅፋት የእንኳን ደስ አለሽ መልእክቷን ማስተላለፏ ድንቅና በኦሎምፒኩ ከማይረሱት ምስሎች መካከል አንዱ ነበር። ከዚህ በኋላ ሁለቱ አትሌቶች የየሀገሮቻቸውን ሰንደቅ ዓላማ አብረው ጎን ለጎን በመሆን እያውለበለቡ የትራኩን ዙሪያ በመሮጥ ለተመልካቹ ድጋፍ ምስጋና ሲያቀርቡ ያየ በሙሉ “ምን አልባት የአድሲቷ አፍሪካ የወደፊት ታሪክ ብርሀናማ ሊሆን ይችላል” ብሎ እንዲያስብ ስድርጓል።

“ኤሌና በእንግሊዘኛ ስታዋራኝ ትዝ ይለኛል” አለች ደራርቱ ሁኔታውን ወደኋላ መለስ ብላ በማስታወስ። “ምንም እንኳን ምን እየነገረችኝ እንደሆነ ባይገባኝም [ፈገግታ] በምልክት መነጋገር ከጀመርን በኋላ በመግባባታችን ለረጅም ጊዜ ጓደኛሞች እንደሆነን አለን።”

ስፖርታዊ ጨዋነት በተግባር – ድጋፍ ለፓውላ

የደራርቱን ስፖርታዊ ጨዋነት በርካታ እሷን የሚያውቋትና የአትሌቲክስ ስፖርት ባለሞያዎች “ፉክክር በበዛበት የስፖርት አለም ለማግኘት የሚከብድ ታላቅ ተምሳሌት” በማለት ይገልጹታል። በ2009 ዓ.ም በተካሄደው የኒው ዮርክ ማራቶን ተወዳዳሪዎቹ የርቀቱን ግማሽ ያህል ከሄዱ በኋላ ደራርቱ ቱሉና ፓውላ ራድክሊፍን ጨምሮ አምስት አትሌቶች ያሉበት የመሪዎቹ ቡድን ኩዊንስቦሮ ድልድይን እንዳቋረጠ ፓውላ ራድክሊፍ ህመም ይሰማትና ያንን ችላ እያቃሰተች ለመሮጥ ስትሞክር ያየችው ደራርቱ ዘውር ብላ “አይዞሽ በርቺ፤ ልንጨርስ ትንሽ ነው የቀረን” የሚል የብርታት መልእክትን ታስተላልፋለች። ሁለቱ አትሌቶች በሩጫው አለም የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላቸው ቀንደኛ ተፎካካሪዎች መሆናቸውን የሚያውቁ ጋዜጠኞችና የስፖርቱ አፍቃሪ ባዩት ክስተት በጣም ነበር የተገረሙት። ታዲያ ውድድሩ ካለቀ በኋላ ሁኔታውን አስመልክቶ እንድታብራራ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላት ፓውላ “ደራርቱ ማለት ይቺ ነች፤ ከፉክክር ይልቅ መከባበርንና መዋደድን የምታስቀድም ጥሩ ሰው። ሌሎቹ ተፎካካሪ አትሌቶች ሲያልፉኝ እሷ ግን እንዳመመኝ ስላወቀች ጠጋ አለችና በኔ ፍጥነት ቀስ ብላ ከጎኔ እየሮጠች ‘አይዞሽ በርቺ’ አለችኝ” በማለት የደራርቱን ታላቅ ስፖርታዊ ጨዋነት ለአለም አስተጋባች።

በስፖርቱ አለም በርካታ አሸናፊዎች ቢኖሩም አስቸጋሪውና ፈታኙ ግን በድል አድራጊነት ለረጅም ጊዜ መቆየት ነው። ይሄንን ማድረግ የሚችሉ ደግሞ እንደ ደራርቱ ያሉ እጅግ በጣም ጥቂት ስፖርተኞች ናቸው። “ለተደጋጋሚ ጊዜያት መሮጥህ ልምድ እንዲኖርህና ከዛ እንድትማር ያደርግሀል። አገኘዋለሁ ብለህ ያሰብከው ቦታ ላይ ለመድረስ ደግሞ ጠንክረህ መስራት፣ በጽናትና በልበ-ሙሉነት መሮጥ አለብህ። በርግጥ እድሜህ በገፋ ቁጥር ጎልበትህና እግሮችህ ሊክዱህ ይችላሉ። ዋናው ትልቁ ችሎታ አእምሮህ ፈጣን እንደሆነ ማቆየቱ ላይ ነው” የምትለው ደራርቱ፤ የሩጫ ህይወቷ በጣም ረጅምና በድሎች ያሸበረቀ ነው። ይህ ድል እረጅም እድሜ ሊኖረው የቻለው በጠንካራ ስራ ምክንያት ነው። በ1996 ዓ.ም በተካሄደው የአትላንታ ኦሎምፒክ ሜዳሊያ ለማግኘት ያልተሳካላት ደራርቱ ቀጣዩ አላማዋ ከአራት አመታት በኋላ በሚካሄደው የሲድኒ ኦሎምፒክ ላይ ወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት ነበር።

ሁለተኛው የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ በሲድኒ

የደራርቱ በረጅም ርቀት ሩጫ ንግስትነትና መንፈሰ ጠንካራነት የፈረንጆቹ አዲሱ ሚሌኒዬም መጀመሪያ አመት ላይ በአውስትራሊያዋ ሲድኒ ከተማ በተካሄደው ኦሎምፒክ በደንብ የተረጋገጠበት ነበር። ከረጅም ጊዜ ጉዳት አገግማና የልጅ እናት ከሆነች በኋላ እንደገና ወደ ሩጫ ውድድር ተመልሳ አሸናፊ በመሆኗ “ምናልባት በቀዳሚነት ከማስቀምጣቸው ድሎቼ መሀል አንዱ ነው” ባለችው የሲድኒ ኦሎምፒክ የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድር፤ እስከመጨረሻው ዙር ድረስ ከመሪዎቹ ጋር አብራ ከሮጠች በኋላ ልክ የደውሉ ድምጽ ሲሰማ ከሀገሯ ልጅ ጌጤ ዋሚ፣ ከፖርቱጋላዊቷ ፈርናንዶ ሮቤሮ፣ ከብሪታኒያዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ እና ከኬኒያዊቷ ቴግላ ላውሩፔ አፈትልካ የወጣችበት ታክቲክ ለእሷ የተለመደ፤ ለተመልካችና ለተፎካካሪዎቿ ግን እጅግ በጣም ድንቅ ክስተት ነበር። በአንድ ወቅት የውድድሮች ርቀት መጨረሻ ላይ ፍጥነት የመቀየር ችሎታዋን አስመልክታ ስትናገር “ውድድር ማብቂያ ላይ ከፊት ለፊቴ አስርም ሆኑ 20 አትሌቶች ቢኖሩ አልፌያቸው እንደምሄድ እተማመናለሁ” ያለችው ደራርቱ ቱሉ፤ የመጨረሻውን 400 ሜትር በ60.3 ሰከንዶች ዞራ መጨረሷ አስደናቂ የፍጥነት መቀየር ብቃቷን አሳይቷል።

የደራርቱን በሩጫው አለም ለረጅም ጊዜ ድል በድል መሆን በቅርበት ስትከታተል የነበረችውና በ1988ቱ የሶል ኦሎምፒክ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው ሮዛ ሞታ፤ እ.አ.አ በሚያዚያ ወር 2001 ዓ.ም የለንደን ማራቶንን ካሸነፈች አራት ወራት ቆይታ በኋላ በካናዳዋ ኤድመንተን ከተማ በተካሄደው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር አንደኛ ወጥታ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው ደራርቱ ቱሉን አስመልክታ በጊዜው በሰጠችው አስተያየት “የምንጊዜም ታላቋ ሴት የረጅም ርቀት ሯጭ” በማለት መስክራላታለች። “ደራርቱ በሁሉም አይነት የሩጫ መድረክ ታላቅነቷን አሳይታለች። በትራክ፣ በጎዳናና በሀገር አቋራጭ ውድድሮች ከሷ የበለጠ ድልን ያገኘ አትሌት ማንም የለም። ለእኔ የምንጊዜም ታላቅ አትሌት ነች” አለች ሮዛ ሞታ።

ስለቀዳሚዋ የረጅም ሩጫ ንግስት ደራርቱ ቱሉ ታላቅነት ጽፎ መጨረስ አይቻልም። ምክንያቱም እሷ ለብዙዎች ከሯጭነት በላይ ነችና። በሲድኒ ኦሎምፒክ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ያስገኘው ገዛኸኝ አበራ “አርአዬ የምትለው የስፖርት ሰው ማነው?” ተብሎ ሲጠየቅ “ያለምንም ጥርጥር ደራርቱ ቱሉ ነች” የሚል አጭርና ግልጽ ያለ መልስ ነበር የሰጠው።

እኔም በዚህ ላብቃ!

ድንቋ እና ፍልቅልቋ ታላቅ ረጅም ርቀት ሯጭ ደራርቱ ቱሉ – ተራኪ ፍስሀ ተገኝ

Related articles on total433.com

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 26, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 26, 2012 @ 12:37 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar