www.maledatimes.com ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ /አንድነት/ በተመለከተ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ /አንድነት/ በተመለከተ

By   /   January 29, 2015  /   Comments Off on ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ /አንድነት/ በተመለከተ

    Print       Email
0 0
Read Time:8 Minute, 4 Second
የፓርቲዉ የቦርድ ዕዉቅና ያለዉ መተዳደሪያ ደንብ የ2004 ዓ.ም ስለመሆኑ፣ ቦርዱ የፓርቲዉን እንቅስቃሴ ከዚሁ የቦርዱ ዕዉቅና ካለዉ ደንብ አንጻር ሲመረምር እንደቆየና አሁንም ከዚያዉ አኳያ የመረመረ ስለመሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡
ከፓርቲው ውስጠ ደንብ መግቢያ ስንነሳ፡- መግቢያ አንዱና ዋነኛዉ የህግ አዉጭዉን አካል ሃሳብ የምንረዳበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከፓርቲዉ መተዳደሪያ ደንብ መግቢያ መረዳት እንደሚቻለዉ መተዳደሪያ ደንቡ የፓርቲዉ አመራሮችና አባላት የሚመሩበትና የሚገዙበት እንደሆነ፣ በፓርቲዉ አደረጃጀት መሰረት የተለያዩ አካላት ጤናማና ዴሞክራሰያዊ የሥራ ግንኙነት እንዲኖራቸዉ የሚያስችል፣ የስራና ኃላፊነት ክፍፍል የሚፈጥር እና ግልጸኝነትና የተጠያቂነት መርህ የሚፈጥር እንደሆነ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ይሄንን የህግ አዉጭዉን ሃሳብ ተከትሎ ስራዎች ሲተገበሩ አይታዩም፡፡
ደንብ የሚያወጣዉ የፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ነው፡፡ ሌላ አካል ቦርዱን ጨምሮ ማንም ሊያወጣላቸዉ አይችልም፣ አይገባምም፡፡ ነገር ግን ደንብ ከወጣ እና ለቦርዱ ቀርቦ ዕዉቅና ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ የፓርቲዉ አመራርም ሆነ አባላት ለደንቡ ተገዥ መሆን ይጠበቅባቸዋል፤ ቦርዱም በተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 ዓ.ም. እና በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2ዐዐዐ ዓ.ም. መሠረት ይሄንን ደንብ የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡
አሁን ተመርጠናል በሚሉት በእነ አቶ በላይ ፈቃዱ ቡድን በኩል የተፈጸሙ ዋና ዋና የህግ ጥሰቶች የሚከተሉት ናቸዉ፡፡
1ኛ. የፓርቲዉ ፕሬዝዴንት ጨምሮ ኃላፊዎች አመራረጥ በተመለከተ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 572/2000 አንቀጽ 8/2/ረ/ እና በፓርቲዉ ደንብ አንቀጽ 13.3.1 መሰረት በጠቅላላ ጉባኤ መመረጥ እንዳለባቸዉ የሚደነግጉ ሆኖ እያለ ምርጫዉ በብሔራዊ ምክር ቤት መደረጉ የፓርቲዉንም ደንብ ሆነ ከላይ የተመለከተዉን የምርጫ አዋጅ የጣሰ ህገ ወጥ ተግባር መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
2ኛ. የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 አንቀጽ 19 እስከ 27 ያሉት፣ አንቀጽ 39 እና የተሻሻለዉ የኢትዮጵያ የምርጫ አዋጅ ቁጥር 532/1999 አንቀጽ 7/8/ ጠቅላላ ንባብ ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመመዝገብ፣ የመከታተልና መቆጣጠር ስልጣን እንዳለዉ ይሄንን ኃላፊነቱን እንዲወጣ ለማስቻል ደግሞ ፓርቲዎች ስለ ስራ እንቅስቃሴያቸዉ በተለይም የፓርቲዉ ወሳኝ ክንዉን በተመለከተ ወቅታዊ ሪፖርት ማቅረብ እንዳለባቸዉ እና ፓርቲዎች ይሄንን ኃላፊነታቸዉን ሳይወጡ ሲቀሩ ቦርዱ እስከመሰረዝ ድረስ እርምጃ የመዉሰድ ስልጣን እንዳለዉ ይደነግጋል፡፡ አንድነት ፓርቲ ያካሄደዉን ጠቅላላ ጉባኤ ለሰባት ወራት ሳያሳዉቅ ቀርቷል፤ በስተመጨረሻም በቦርዱ ጽሕፈት ቤት ጥያቄ ተገዶ ማቅረቡ ከፍተኛ የህግ ጥሰት ፈጽሟል፡፡
3ኛ. በአመራር ምርጫ ሂደቱ የፓርቲዉ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 10.2/ለ/ሐ/ቀ/ ከሚያዘዉ ዉጭ አምስት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ ሳይሰየም፣ ከተሰናባቹ ብሔራዊ ምክር ቤት ጥቆማ ሳይቀርብ ወይም ከጉባኤ አባላት መካከል ቀደም ሲል በተደረገ ዉድድር በምስጢር ድምጽ አሰጣጥ/በስብሰባዉ ላይ የተገኘዉ የቦርዱ ተወካይ በሚስጥር ድምጽ አሰጣጥ መደረግ እንዳለበት ማሳሰቢያ ቢሰጥም ሳይቀበሉት አልፈዋል/እና የጠቅላላ ጉባኤ/50+1/ ምልዐተ ጉባኤ ካለመሟላቱም ባሻገር ጭራሽ ጠቅላላ ጉባኤ ባልተሰበሰበበት የተደረገ በመሆኑ ህገ ወጥ ነዉ፡፡
4ኛ. የፓርቲዉ ፕሬዚደንት ከኃላፊነት የተነሱት ከህግ ዉጭ/ከፓርቲዉ ፕሮግራምና ደንብ ዉጭ እየተንቀሳቀሱ ነበር በሚል ከሆነ ብሔራዊ ምክር ቤቱ በ2/3ኛ ድምጽ በማገድ ጠቅላላ ጉባኤ በስድስት ወራት ጊዜ ዉስጥ እንዲካሄድ ማድረግ እንደሚቻል፣ እስከዚያዉ ጊዜ ዲረስ በምክር ቤቱ ሰብሳቢ የሚመራ 7 አባላት ያሉት ጊዜያዊ አመራር መሰየም እንደሚቻል፤ የተጠራዉም ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዚደቱን ወደ ስራዉ የመመለስ ወይም ሌላ ዉሳኔ የማስተላለፍ ስልጣን እንዳለዉ ገልጾ እያለ ከዚህ ዉጭ ፕሬዚደንቱ ስራዉን የለቀቀበትን ምክንያት ለመመርመር ባለመፈለግ ወደ ሌላ አመራር ምርጫ መሄድ የህግ ጥሰት ነዉ፡፡
6ኛ. የእነ አቶ በላይ ፈቃዱ ቡድን እንደሚለዉ ፕሬዚደንቱ በራሳቸዉ ፈቃድ ስልጣናቸዉን ለቀዋል ቢባል እንኳ በፓርቲዉ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 13/3/2/ መሰረት የፓርቲዉ ምክትል ፕሬዚደንት ስራዉን እንደሚያስቀጥሉ ደንግጎ እያለ ይሄንንም ባላከበረ መልኩ ወደ ሌላ አመራር ምርጫ መግባታቸዉ የህግ ጥሰት ነዉ፡፡
7ኛ. የፓርቲዉ አመራር ለሁለት መከፈሉ ግልፅ ሆኖ እየታዬ ቦርዱ ሁለቱን ቡድኖች ለማቀራርብና ልዩነታቸዉን ለጠቅላላ ጉባኤ አቅርበዉ እንዲያስወስኑ ጥረት ቢያደርግም ለመነጋገርና ችግሩን ለመፍታት ያለመፈለግ ማሳየቱ፣ ቦርዱ ከጥር 04 እስከ 19 ቀን 2007 ዓ.ም የሰጠዉን የጊዜ ገደብ ካለመጠቀሙም በላይ የቦርዱ ዉሳኔ አግባብ አይደለም በሚል ተግባራዊ እንደማያደረግ በደብዳቤ አሳዉቋል፡፡
ከዚህ መረዳት የሚቻለዉ የእነ አቶ በላይ ፈቃዱ ቡድን እንቅስቀሴ ህጋዊ የሆነ የቦርዱን አመራር ያለመቀበል፣ የፓርቲዉን ህልዉና አደጋ ላይ የጣለ፣ በአመራሩ መካከል የተከሰተዉን ልዩነት በመያዝ ለጠቅላላ ጉባኤ ለማቅረብና ማስወሰን ያልመፈለግ፣ ለፓርቲዉ አባላትና ደጋፊዎች አክብሮት የሌለዉና ለህግ ያለመገዛት አዝማሚያ በመሆኑ ተቀባይነት የሌለዉ አካሄድ ስለመሆኑ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡
በሌላ በኩል
የእነ ትግስቱ አወሉ ቡድን በተመለከተ፡-
1ኛ. ደንብ ይከበር የሚሉ ወገኖች መሆናቸው፣ የተፈጠረዉን ልዩነት ይዘዉ ለጠቅላላ ጉባኤያቸዉ ለመቅረብ ከጅምሩ ፍላጎት ያላቸዉ በመሆኑ፣ በፓርቲዉ ዉስጥ ከተፈጠረዉ ቡድን ጋርም ለመነጋገር ፈቃደኛ የነበረ ስለመሆኑ፣ ሁለቱም ቡድኖች ተቀራርበዉ ችግራቸዉን በዉስጠ ደንባቸዉ እንዲፈቱ ቦርዱ ያደረገዉንም ጥረት የተቀበሉ ስለመሆኑ፣
2ኛ. ይሄ ቡድን ከላይ እንደተመለከተዉ ከህግ ዉጭ በተደረገ ምርጫና የአመራር ለዉጥ ከኃላፊነታቸዉ ተገፍተዉ የወጡ የስራ አስፈጻሚ አባላትና የፓርቲዉ አባሎች በመሆናቸዉ በፓርቲዉ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 6.1/ሐ/ መሰረት የፓርቲዉ አባላት መብት በሚደነግገዉ መሠረት አመራሮችን ጨምሮ ማንኛዉም የፓርቲ አባል የፓርቲዉ ደንብና ፕሮግራም ተጥሷል ብለዉ ሲያምኑ የማስከበርና እንዲከበር የመታገል መብት ስላላቸዉ የተጣሰዉ ደንብ ይከበር በሚል ጥያቄ ማቅረባቸው ሕጋዊ አካሄድ በመሆኑ፣
3ኛ. አሁንም ቦርዱ በስተመጨረሻ በሰጠዉ የሁለት ሳምንት ጊዜ ዉስጥ ጠቅላላ ጉባኤ በ2004ዓ.ም ደንብ መሰረት በማካሄድ የጠቅላላ ጉባኤዉን ሪፖርት ለቦርዱ ያቀረቡ በመሆኑ እና ከሌለኛዉ ቡድን ጋርም ለመወያየትና ጉዳያቸዉን ለጠቅላላ ጉባኤ በጋራ ለማቅረብ ያደረጉት ጥረት በእነ አቶ በላይ ፈቃዱ ቡድን እምቢተኝነት ባይሳካም የመተዳደሪያ ደንቡን፣ የፓርቲዉን አባላትና ደጋፊዎች እንደዚሁም የቦርዱን ህጋዊ አመራር ለመተግበር ያደረገዉ ጥረት ከፍተኛ መሆኑን፣
4ኛ. ጥር 16 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም. ባደረጉት ጠቅላላ ጉባዔ ጥሪ ከተደረገላቸው 239 አባላት መካከል 193ቱ መገኘታቸው፣ ይህም የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 1ዐ ንዑስ አንቀፅ 2/ቀ/ መሠረት የተሟላ መሆኑ፣
5ኛ. የቀረበው የጉባዔ ሪፖርት የፓርቲው ሊቀመንበር በፓርቲው 2ዐዐ4 መዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 1ዐ ንዑስ አንቀፅ 2/ሐ/ መሠረት በሚስጥር ድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት የተመረጠ መሆኑን የሚያሳየው የሕግ አግባብነት ያለው መሆኑን እንረዳለን፡፡
ማጠቃለያ የፓርቲዉን ህልዉና አመራሮች ከሚፈጥሩት አለመግባባት ለይቶ መመልከት አስፈላጊ በመሆኑ፣ ፓርቲዉ በዚህ ሁኔታ እንዲቀጥል መፍቀድ የበለጠ እንዲጎዳ ስለሚያደርግ፣ ፓርቲዉ እንደተቋም ከአመራሮች ባሻገር የህግ ሰዉነት ያለዉ ተቋም እንደመሆኑ መጠን፣ አባላትና ደጋፊዎች አሉት ተብሎ ስለሚታመን፣ የፓርቲዉን ህልዉና ለማስቀጠል ሲባልና ፓርቲዉን በመምራት ወደ ምርጫ የሚገባ አመራር ስለሚያስፈልግ ከላይ በተመለከቱት ዝርዝር ምክንያቶች የእነ አቶ በላይ ፈቃዱ ቡድን በርካታ የህግ ጥሰቶችን የፈጸመ በመሆኑ፣ አሁንም በዚሁ ተግባሩ የቀጠለ በመሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ የእነ አቶ ትግስቱ አወሉ ቡድን ህግን በማክበር ለመንቀሳቀስ ጥረት እያደረገ ያለ በመሆኑ ይሄንን ፓርቲ ሊመራ የሚያስችለዉ ቁመና እንዳለዉ ጥር 17 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም. ከቀረበዉ የጠቅላላ ጉባኤ ሪፖርት መገንዘብ በመቻሉ ለዚህ ቡድን ዕዉቅና እንዲሰጠዉ ቦርዱ ዉሳኔ ሰጥቷል፡፡
በመሆኑም የእነ አቶ በላይ ፈቃዱ ቡድን ያካሄዱት የአመራር ምርጫ ከፓርቲዉ መተዳደሪያ ደንብ እና ከምርጫ ህጉ ድንጋጌዎች ዉጭ በመሆኑ ዕዉቅና እንደማይሰጠዉ፤ በሌላ በኩል በእነ ትግስቱ አወል ቡድን በቀን ጥር 16 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም. የተደረገዉ ጠቅላላ ጉባኤ በቦርዱ ዕዉቅና ተሰጥቶታል፡፡ በመሆኑም ቦርዱ የእነ አቶ ትግስቱ አወሉ ቡድን ፓርቲዉን በመምራት ወደ ምርጫዉ እንዲገቡ በዛሬው ዕለት ባካሄደው ዐዐ5/2ዐዐ7 አስቸኳይ ስብሰባው ወስኗል፡፡
መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ በተመለከተ
መግቢያ
በቦርዱ ዕዉቅና ያገኘዉና በስራ ላይ ያለዉ የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ የ2001 ዓ.ም ስለመሆኑ፣ ደንቡ የፓርቲዉ አመራሮችም ሆነ አባላት መብትና ግዴታቸዉን አዉቀዉ በእንቅስቀሴዉ ዉስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል እንደሆነ፣ በአመራሩ/በበታች አካሎችና አባሎች መካከል ዴሞክራሲያዊ የሆነ መከባበር ላይ የተመሰረተ አሰራር ለመፍጠር እንደሆነ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ መኢአድ በአሁኑ ጊዜ በሁለት ቡድን በመከፈሉ የፓርቲዉ የስራ እንቅስቃሴ ተገቷል በሚባል ደረጃ ያለ ስለመሆኑ እንረዳለን፡፡
አሁን ተመርጠናል በሚሉት በእነ አቶ ማሙሸት አማረ ቡድን የተፈጸሙ የህግ ጥሰቶችን እንደሚከተለዉ ማንሳት ይቻላል፡፡
1ኛ. የፓርቲዉ ፕሬዚደንትን ከጠቅላላ ጉባኤ አባላት መካከል መመረጥ እንዳለበት፣ የፓርቲዉ ተ/ምክትል ፕሬዚደንት ደግሞ የጠቅላላ ጉባኤ አባል መካከል ከመሆኑ ባሻገር የማዕከላዊ ምክር ቤት አባል መሆን እንዳለበት የፓርቲዉ ደንብ በአንቀጽ 7.4 እና 4.2.2 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ይሁንና አሁን የተመረጡት ግለሰቦች በ2003 ዓ.ም ከፓርቲዉ አባልነት የተሰረዙ ከመሆኑም በላይ ለሶስት ተከታታይ ወራት የአባልነት መዋጮ ያልከፈለ አባልነቱ ቀሪ እንደሚሆን ስለሚደነግግ ለዚህ ኃላፊነት መስፈርቱን የማያሟሉ ሰዎች በመመረጣቸዉ የህግ ጥሰት ተፈጽሟል፡፡
2ኛ. ፓርቲዉ አካሂጃለሁ የሚለዉን የጠቅላላ ጉባኤ ዉጤት ሪፖርት፣ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ጥቆማ ሲያደርግ እና ሌሎች የፓርቲዉን ወሳኝ ክንዉኖችን ሲያሳዉቅ በፓርቲዉ ማህተም የተረጋገጠ ሰነድ ማቅረብ እንዳለበት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 አንቀጽ 20/1/ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ይሁንና ፓርቲዉ በዚህ አግባብ አረጋግጦ ሊያቀርብ አልቻለም፣ ይባስ ብሎ ህጋዊ ማህተም በሌሎች የፓርቲዉ ቡድን እጅ መኖሩ እየታወቀ ተመሳሳይ ማህተም በማስቀረጽ የህግ ጥሰት ፈጽሟል፡፡
3ኛ. የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 572/2000 አንቀጽ 19/2/ለ// ስር የፓርቲዉ ጠቅላላ ጉባኤ ሲካሄድ ወይም ሌሎች ወሳኝ ክንዉኖች ሲኖሩ የቦርዱ ተወካይ መገኘት እንዳለበት ከመደንገጉም በላይ የተለመደ አሰራር መሆኑ ይታወቃል፡፡ የቦርዱ ተወካይ በተገለፀው ቀን በመገኘት ለመታዘብ የሞከሩ ሲሆን አብዛኛው ጊዜ በንትርክና ጭቅጭቅ የታጀበ እንደነበር፣ ስብሰባው በአግባቡ ሊመራ ባለመቻሉ የፓርቲው ኃላፊዎች ምርጫ ለቦርዱ ባልተገለፀበት ቀጣይ ቀን ስለነበር የአካሄድ ችግር ነበረበት፡፡
4ኛ. የፓርቲዉ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 10.2.2 የፓርቲዉ መደበኛ፣ ልዩ እና አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ መጠራት ያለበት በፓርቲዉ ማዕከላዊ ምክር ቤት መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ሆኖም ግን ፓርቲዉ የጠራቸዉን ጠቅላላ ጉባኤዎችና ከቦርዱ ጋር የተደረጉትን የደብዳቤዎች ልዉዉጥ ስንመለከት የፓርቲዉ አመራር ማን እንደሆነ ማወቅ እስኪያስቸግር ድረስ አቶ አበባዉ መሐሪ፣ ኢ/ር ኃይሉ ሻውል እና አቶ ማሙሸት አማረ ያለቦርዱ ዕዉቅና ሲፈራረቁበት ተመልክተናል፡፡ ይሄም የህግ ጥሰት ነዉ፡፡
በሌላ በኩል
በእነ አቶ አበባው መሐሪ ቡድን በኩል ያለዉን እንቅስቃሴ ስንመለከት የሚከተሉትን ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል፡፡
በ2005 ዓ.ም በተደረገ ጠቅላላ ጉባኤ የተመረጡ ስለመሆኑ፣ የፓርቲዉ ጠቅላላ ጉባኤ አባልነታቸዉ ላይ የተነሳ ክርክር የሌለ ስለመሆኑ፣ በወቅቱ የጠቅላላ ጉባኤዉን ሪፖርት ለቦርድ በትክክለኛዉ የፓርቲዉ ማህተም አስደግፈዉ ያቀረቡ ስለመሆኑ፣ ቦርዱ እንዲሟላ የጠየቀዉ የጠቅላላ ጉባኤ ብዛት እንደነበርና ይሄንን የተሰጠዉን የቦርዱን አመራር ተከትሎ 600 አባላት እንዲሆን በሚል በማስወሰን ያሳወቁ ስለመሆኑ፣ በወቅቱ የቦርዱን ህጋዊ አመራር ለመተግበር የተንቀሳቀሰ ቡድን ስለመሆኑ መረዳት እንደሚቻል፣ በስብሰባው ላይ የተገኙት የጠቅላላ ጉባኤ አባላት በወቅቱ ሲታይ 285 ስለነበር እንዲያስተካክሉ በቦርዱ እንደተገለጸ፣ እነ አቶ አበባዉ መሐሪም ይሄንን ተከትሎ የተረሱ ተሳታፊዎች ናቸዉ በሚል የ41 ሰዎች ስም ዝርዝር እንዳቀረቡና በወቅቱ ቀደም ሲል አንድ ላይ ተጠቃሎ ባለመቅረቡ ተቀባይነት እንዳላገኘ ተገልጾ እንደነበር እናስታዉሳለን፡፡
አሁን ጉዳዩን በጥልቀትና በስፋት ስንመረምር በኋላ የመጣዉ የጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች ዝርዝር የጠቅላላ ጉባኤ አባላት በመሆናቸዉ፣ አንዳንዶቹ አባላት ብቻ ሳይሆኑ ኢ/ር ኃይሉ ሻወልን ጨምሮ በአመራር ላይ የነበሩ ሰዎች ስለመሆናቸዉ በመረጋገጡ እና አሁንም ቢሆን ህጋዊ የፓርቲዉን ማህተም በመጠቀም ከቦርዱ ጋር ግንኙነት እያደረገ ያለ በመሆኑ ሰነዱ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከስምምነት ተደርሷል፡፡ ከዚህ ተነስተን ጉዳዩን ስንመረምር ከ600 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት መካከል 326 መገኘታቸዉን ለመገንዘብ ችለናል፡፡ በመሆኑም አቶ አበባዉ መሐሪ የተመረጡበት የ2005 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ ዉጤት ዕዉቅና እንዲያገኝ ተወስኗል፡፡
በአጠቃላይ ከላይ እንደተመለከተዉ ፓርቲዉ በሁለት ቡድን የተከፈለ ስለመሆኑ፣ ከእነዚህ ቡድኖች ዉስጥ ደግሞ የእነ ማሙሸት አማረ ቡድን ከላይ በዝርዝር እንደተገለጸዉ ራሳቸዉም ለመመረጥ በዉስጠ ደንባቸዉ መሠረት መስፈርቱን የማያሟሉ ከመሆኑም በላይ የጠቅላላ ጉባኤዉ ሂደት በአጠቃላይ እና የአመራር ምርጫ ሂደቱ በተለይ በርካታ የፓርቲዉን ደንብ እና የምርጫ ህጉን ድንጋጌዎች የጣሱ በመሆኑ ዕዉቅና ሊሰጣቸዉ እንደማይገባ ቦርዱ ወስኗል፡፡
በሌላ በኩል አቶ አበባ መሐሪ የተመረጠበት አግባብ የፓርቲዉን ደንብ ባከበረ መልኩ በመሆኑ የእርሳቸዉን የምርጫ ሂደትም ሆነ የተመረጡበትን የጠቅላላ ጉባኤ ዉጤት ሪፖርት በቦርዱ ዕዉቅና ተሰጥቶታል፡፡
የሁለቱም ፓርቲዎች ጉዳይ ሲጠቃለል ቦርድ ጥር 21 ቀን 2007 ዓ.ም ባካሄደው በ005/2007 አስቸኳይ ስብሰባ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ /አንድነት/ እነ አቶ ትግስቱ አወሉ እና የመላ ኢትዮጵያዊያን አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ በተመለከተ ደግሞ የእነ አቶ አበባዉ መሐሪ ፓርቲዉን በመምራት ወደ ምርጫዉ እንዲገቡ በአንድ ድምፅ ወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ጥር 21 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on January 29, 2015
  • By:
  • Last Modified: January 29, 2015 @ 5:52 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar