www.maledatimes.com እናት ምንጊዜም እናት ናት…የተመስገን ደሳለኝ እናት.. - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

እናት ምንጊዜም እናት ናት…የተመስገን ደሳለኝ እናት..

By   /   February 11, 2015  /   Comments Off on እናት ምንጊዜም እናት ናት…የተመስገን ደሳለኝ እናት..

    Print       Email
0 0
Read Time:3 Minute, 24 Second
እናት ምንጊዜም እናት ናት…የተመስገን ደሳለኝ እናት..10408164_10204132508173871_4529305850262563878_n
የፍትህ ያለህ!….የሰሚ ያለህ!!!….
በግሩም ተ/ሀይማኖት
የመናገርና የመጻፍ መብት ተከብሯል ተብሎ በ1985 ህጉ ከፀደቀ ጀምሮ በርካታ የፕሬስ ውጤቶች ለህዝብ ደርዋል፡፡ ከመድረሳቸው ጀርባ ደግሞ እድገታቸው እንዲጫጫ ከማድረግ ጀምሮ ጋዜጠኞቹን እስከመታፈን በገዢው መንግስት ራሱ ያወጣውን ህገ-መንግስት እና ህግ የጣሰ ድርጊት ተፈጽሟል፡፡ ነፃ-ፕሬሱ እንዲቀጭጭ ብቻ ሳይሆን እንዲጠፋም ጭምር አፋኙ መንግስት ጋዜጠኞችን ማፈን፣ ማሰር፣ መደብደብ፣ ቤተሰብን ማሰር እና ማሰቃየትን ተግባሩ አድርጎ ቆይቷል፡፡
በእስክንድር አሳታሚ ስር የሚታተም ‹‹ኢትዮጵስ›› የተባለ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ተፈራ አስማረ በከፍተኛ እንግልት ታፍኖ መደብደቡ፣ መሰቃየቱ ብቻ ሳይሆን በፍትህ ስም ፍትህን በሚያጠፋው ፍርድ ቤት 2 አመት እስራት ተፈርዶበት ታስሮ ወጣ፡፡ በዛን ወቅት ደጋግሞ መደብደቡ እና መታመሙ ህይወቱ አለፈ፡፡ ወንድሙ ቴዎድሮስ አስማረ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ እንደወጣ ቀረ፡፡ እስክንድርም በኢትዮጵ ጋዜጣ አማካኝነት ቢንገላታም ከነጻ-ፕሬሱ አልራቀም፡፡ ዘ-ሀበሻ የሚል በእንግሊዘኛ የሚታተም ጋዜጣ ጀመረ፡፡ ሀይለኛ ድብደባ ተፈጽሞበታል፡፡ እጁን ተሰብሮ እስካሁንም ድረስ እንደሚያመው አውቃለሁ፡፡ አሰፋ ማሩ በአደባባይ አፍንጮ በር የሚባል ቦታ ላይ በጠራራ ጸሀይ በጥይት ተገደለ፡፡
ምን ያልተከፈለ መስዋዕትነት አለ? ማንስ ያልታሰረ፣ ያልተደበደበ ጋዜጠኛ አለ? ከ120 በላይ ጋዜጠኞች ሀገራችንን ለቀን እንድንሰደድ ያደረገን የአፋኙ መንግስት ህግ አለማክበር እና ጋዜጠኛን እንደ ሽብርተኛ ከማየት አልፎ በሽብርተኛነት መፈረጅ ነው፡፡ በተለይ ከ1997 ምርጫ በኋላ አይን ያወጣ ያፈጠጠና ያገጠጠ አምባገነንነቱን በስራው ለአለም አሳወቀ፡፡ በሀገር ክህደት ወንጀል የጅምላ ክስ ከፍቶብን ያመለጥን አመለጥን የቀሩትን ሰብስቦ ቃሊቲ አጎረ፡፡ ከዛን ጊዜ በኋላ የነጻ ፕሬሱ ህልውና ጭርሱኑ ብርሃን መፈንጠቅ ሳይሆን ድቅድቅ ጨለማ ዋጠው፡፡
በዚህን ወቅትም እጅ አንሰጥም ያሉ ከእስርና ስደት የተረፉ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ለማስከበር ትግሉን ቀጠሉ፡፡ ተመስገን ደሳለኝ የፍትህ መጥፋትን፣ የፍትህ መጓደልን፣ የመታፈን..መታሰርን፣ ህገ-ወጥነትን በመቃወም ‹‹ፍትህ›› የሚል ጋዜጣ ጀመረ፡፡ በዚህን ጊዜም ቢሆን ነጻፕሬስ ውስጥ የነበሩት ጋዜጠኖች የተጋፈጡት፣ የተቀበሉትን ስቃይ ታሪክ የማይረሳው ነው፡፡ ደፋሩና ስለ እውነት ወደ ኋላ አልልም ያለው ተመስገን ትግሉን አጠናክሮ ቀጠለ፡፡
እነ አንዱዓለም፣ ውብሸት..እስክንድር ርዕዮት በተቀነባበረ ውንጀላና በተዛባ ፍርድ ለእስር ተዳረጉ፡፡ እስር ቤት ሆነውም ለማንኛውም እስረኛ የሚፈቀድ የጥየቃ መብት ተገፈዋል፡፡ ህጉም ሆነ ህገ-መንግስቱ ለነጻ ፕሬሱ አባላት አይሰራም የተባለ ይመስላል፡፡ ለነገሩ ራሱ ህጉን ያወጣው አካልም ሲተገብረው አልታየም፡፡ ለማንኛውም የህግ ታራሚ የሚፈቀድ መብት ለእነሱ ክልክል ነው፡፡ ይህ የሆነውም የህግ ታራሚ ሳይሆኑ በመንግስት ጠላትነት ታይተው በሀሰት ተኩለውና ተወንጅለው ፍትህ ተጣሞ የታሰሩ መሆኑ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሶስት አመት እስራ እንዲቀጣ የተፈረደበት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ምንም አይነት ጠያቂ እንዳይጠይቀውም፤ ስንቅ እንዳይገባለት ተክልክሏል፡፡ የፈለገው ሰው ይከልከል ግን እንዴት እናት ትከለከላለች፡፡ እነዚህ ሰዎች ጫካ ከርመው ሲገቡ ከእናት መወለዳቸውን ረስተውታል እንዴ? እናት ለልጇ ያላትን ፍቅር እንዴት እንደምትንሰፈሰፍ እንዴት መገንዘብ አቃታቸው? የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ እነሆ..
ጉዳዩ፡- የልጄ ተመስገን ደሳለኝን ጉብኝት ይመለከታል
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከአብራኬ የወጣ ሁለተኛ ልጄ ነው፡፡ ገና ከህፃንነቱ ጀምሮ ለሰው አሣቢ፣ ሀገር ወዳድና ታታሪ ስለመሆኑ ከእኔ በላይ የሚያውቁት ይመሰክራሉ፡፡ ልጄ ተመስገን ለወገኔ አሰብኩ ባለ በእስር ቤት ያለጎብኚ እየተሰቃየብኝ ይገኛል፡፡ መቼም፣ የእናት ሆድ አያስችልምና እባካችሁ ልጄን ታደጉት፡፡ እባካችሁ ቢያንስ ካለበት እየሄድኩ የልጄን አይን እንዳይ እንዲፈቀድልኝ ተባበሩኝ፡፡
የልጄን ድምጽ ከሠማሁ ይኸዉ አንድ ወር ሞላኝ፡፡ ታናሽ ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ለወንድሙ ብሎ የቋጠረዉን ምሣ ይዞ ዝዋይ ማረሚያ ቤት ቢሄድም በማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች ተደብድቦ የያዘውን ምግብ እንኳ ሣያደርስ ሜዳ ላይ ተደፍቶ ተመልሷል፡፡ መቼም እናንተም ልጆች ይኖራችኋል፤ ደግሞም የልጅን ነገር ታውቁታላችሁ፡፡ እኔ አሁን በእርጅና ዕድሜዬ ላይ እገኛለሁ፡፡ ከአሁን በኋላ ብቆይም ለትንሽ ጊዜያት ነው፡፡ በዚህች ጊዜ ውስጥ ልጄን እየተመላለስኩ እየጠየኩ፣ ድምፁን እያሰማሁ፣ አይዞህ እያልኩ ብኖር ለእኔ መታደል ነበር፡፡ እባካችሁ እርዱኝ የልጄ ድምጽ ናፈቀኝ፡፡ እሱን መጎብኘት የተከለከለበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንኳን እስካሁን አላወቅሁም፡፡ ከወንድሙ ድብደባ በኋላም ጥር 10 ወደ ጠዋት አካባቢ የሄዱት ጓደኞቹ እና ወንድሞቹ ሳያዩት ተመልሰዋል፡፡
ተምዬ ስታመም የሚያስታምመኝ፣ “አይዞሽ እማዬ” የሚለኝ ረዳቴ ነው፡፡ ሌላ ዘመድ የለኝም፡፡ የምተዳደረውም ልጆቼ ለፍተውና ደክመው በሚያመጧት ትንሽ ብር ነው፡፡ ዛሬ ግን ይኸዉ ልጆቼም ወንድማቸውን ለማየት እየተንከራተቱ ነው፡፡
በእናታችሁ ይዣችኋለሁ፤ ከቻላችሁ ልጄ እንዲፈታልኝ እና እኔም ያለችኝን ቀሪ የእድሜ ዘመን አይን አይኑን እያየሁ እንድኖር እንድታደርጉልኝ፤ ይህን ማድረግ ከአቅም በላይ ከሆነ ደግሞ ካለበት ድረስ እየተመላለስኩ እኔና ሌሎች ልጆቼ እንዲሁም ወገኖቹ እንዲጠይቁት ቢደረግልኝ ስል በአክብሮት እጠይቃችኋለሁ፡፡ ልጄን አውቀዋለሁ፡፡ አንድ ነገር ሲገጥመዉ ሆድ ይብሰዋል፡፡ ቢያንስ እንኳን ቤተሰቦቹን ሲያይ ስለሚፅናና ይኸዉ እንዲፈቀድልኝ እማፀናለሁ፡፡ እኔ ምንም አቅም የሌለኝ አሮጊት ነኝ፡፡ ሁሉንም ለናንተ ሠጥቻችኋለሁ፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር እንደምታስተካክሉልኝ እና እንደገና የልጄን ፊት እንዳይ እንደምታደርጉኝ ሙሉ ተስፋ አለኝ፡፡
እንግዲህ የየካዉ ቅዱስ ሚካኤል ይከተላችሁ፡፡ መቼም የእናትን ሆድ ታውቁታላችሁ፤ የልጅ ነገር አያስችልም፡፡ ሆድም ቶሎ ይሸበራል፡፡ ስለዚህ እባካችሁ እኔንም ልጆቼንም እርዱን እንላለን፡፡
ከሰላምታ ጋር
ወ/ሮ ፋናዬ እርዳቸው
ግልባጭ
– ለጠ/ሚኒስተር ፅ/ቤት
– የህግና፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ – ለአፈ-ጉባኤ ፅ/ቤት – የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) – ለእምባ ጠባቂ – ለአሜሪካ ኢምባሲ – ለእንግሊዝ ኢምባሲ

 

About Post Author

Abby

Internet reporter, freelancer and webmaster.
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on February 11, 2015
  • By:
  • Last Modified: February 11, 2015 @ 3:55 pm
  • Filed Under: Ethiopia

About the author

Internet reporter, freelancer and webmaster.

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar