www.maledatimes.com በአሸባሪነት የሚፈርጀንን የወንበዴ አገዛዝ ታግለን ለማስወገድ ተባብረን እንነሳ!!! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

በአሸባሪነት የሚፈርጀንን የወንበዴ አገዛዝ ታግለን ለማስወገድ ተባብረን እንነሳ!!!

By   /   March 12, 2015  /   Comments Off on በአሸባሪነት የሚፈርጀንን የወንበዴ አገዛዝ ታግለን ለማስወገድ ተባብረን እንነሳ!!!

    Print       Email
0 0
Read Time:4 Minute, 21 Second

 

ኢትዮጵያውያን ለነጻነታችን ዋጋ መክፈል የጀመርነው ከጥንት ጀምሮ መሆኑ ይታወቃል:: በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ የሚገኘው የዘረኛውና ቡድናዊው አገዛዝ በዜጎች ላይ ከፍተኛ በደል በማድረስ ላይ ይገኛል:: ከዚህ ጨቋኝ አገዛዝ ለመገላገል በአንድነትና በመተባበር ለነጻነታችን መታገል አለብን:: ላለፉት 24 አመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ የተቀመጠውን ዘራፊውን እና ጨቋኙን የወያኔ ጁንታን ለመቅበር የአንድነት እና የለውጥ ሃይሎች ልዩነቶቻችንን በማቻቻል በጋራ ልንታገል የሚገባና ለውጥ ልናመጣ የሚገባ ችላ የማይባል ዋነኛ ጉዳይ ነው። በህዝባችን ላይ ከፍተኛ እንግልት፣ እስር፣ ሰቆቃ፣ ግድያ ወዘተ እየፈጸመ የሚገኘው የህዝባችንና የሃገራችን ጠላት ወያኔ እና ወያኔ ብቻ ነው::

 

ባሳለፍናቸው መራር የትግል አመታት ውስጥ በቅርቡ እንዳየነው የተቃዋሚዎች በመዋሃድና አንድነትን ከመፍጠር ይልቅ እርስ በእርስ መፈራረጅና መወነጃጀል ለስልጣን መሮጥ እንዲሁም ለስም እና ለዝና መትጋት ነው:: ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተረፈው ነገር ቢኖር ከጭቆና ወደ ባሰ ጭቆና ማቅ ውስጥ ከመዘፈቅ ውጪ ፍጹም የናፈቀውን የነጻነት አየር እንዲተነፍስ አላደረግነውም። የተቃዋሚ ሃይሎች ጥንካሬ እንዲጎለብት በየድርጅቱ ውስጥ ያሉትን እንከኖች በማጥራት በጋራ እና በተመቻቸ የሃሳብ መግባባት ተቻችሎ እና ተግባብቶ የትግል ስትራቴጂን ከግብ ለማድረስ ህብረ-ብሄር የሆኑት የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር እና ግንቦት 7 እንዳደረጉት ለአንድነትና ለትብብር ተግቶ መስራት ይጠበቅብናል። በአሁኑ ወቅት ይህንን ዘረኛ ስርዓት ለማውረድ በውስጥም ሆነ በውጭም ትግሉ በስፋት ቀጥሎ ይገኛል:: ወያኔ እስኪወድቅና ህዝባችን ድል እስኪቀዳጅ   ድረስ ሊቀጥል የሚገባው ትግል እንደመሆኑ መጠን ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ የተያዘው ትግል በአሁኑ ሰአት ወያኔን እያፍረከረከ በፍርሃት እንዲሸበር አድርጎታል::

 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለውጥ ይፈልጋል! የኛ የኢትዮጵያውያን ጥያቄ አብዮታዊ የለውጥ ጥያቄ ነው። የፖለቲካ አስተዳደር ለውጥ ፣ የኑሮ ውድነት የሚያላቅቅ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ፣ በጋራ ህብረተሰባዊነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተ አገዛዝ ወይንም መንግስት እንደምናገኝ የሚያረጋግጥልን ለውጥ እንፈልጋለን፡፡ የማህበራዊና ፍትህ እኩልነት ለውጥ፣ የነጻነት እና የመብት ማግኘት ጥያቄ፣ ከመንግስት ነጻ የሆነ ፍርድ ቤት፣ በሃገራችን ተዘዋውረን በፈለግነው ቦታ የመስራት እና የመኖር ጥያቄ የሚያረጋግጥልን ለውጥ እንፈልጋለን፡፡ በሃገራችን ላይ የሃገራችን ባለቤቶች ስንሆን የሚገኘው ብልጽግና እና እድገት ባለቤት መሆናችንን የሚያረጋግጥልን ለውጥ እንፈልጋለን፡፡ ይህ ሳይታለም የተፈታ እና የሁሉም የነጻነት ፈላጊ ሃይሎች ጥያቄ ነው። ሰብአዊ መብቶች ለዲሞክሪያሲያዊ ስርአት ግንባታና ለአንድ ሀገር ልማትና ብልፅግና መሰረታዊ ነገሮች ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡ ዜጎች የሃገራቸው ሃብት ባለቤትና የመጠቀምም መብት እንዲሁም ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ መብት ሊኖረን ይገባል::

 

በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉትን ፓርቲዎች መዋቅሮቻቸውን በማጠናከር የውስጥ ድክመቶቻቸውንም በመቅረፍ እንዲጠነክሩ የማድረግ ግዴታ ከሁላችንም ከለውጥ ፈላጊ ሃይሎች ይጠበቃል።

ስለዚህ ይህንን አምባገነን ስርዓት ታግለን ለመጣል የግዴታ እያንዳንዱ ዜጋ እስር ቤት ገብቶ መታሰርን እና መገረፍን መመልከት ሳይሆን ወንድም እህቶቻችን በእስር ቤት ያሳለፉት መከራ እንደመከራችን አይተን ሲነጋ ደግሞ ወደ እኛ ቤት እንደሚመጣ አስበን ያለአግባብ ለታሰሩት ሃቀኛ ፍትህን ለኛም የማይሸራርፍ ሰብአዊ መብቶቻችንን ለማግኘት መታገል ግዴታችን መሆኑን ማወቅ ያስፈልገናል። ለዘመናት ተሳስሮ እና ተከባብሮ የኖረን ህዝብ ለማፋጀት ዘመን በወለዳቸው የዘመኑ ቋንቋ “አሸባሪ” ወይ “አክራሪ” እየተባሉ ዜጎች የሚደርስባቸው መከራ እንዲቆም እያንዳንዳችን የበኩላችንን በማድረግ የድርሻችንን ማበርከት አለብን። የአብሮነታችን ተምሳሌት ለአለም ያስተማረውን የአያቶቻችንን የአንድነት ወዳድነትን ደግመን ለወያኔው መንግስት ማሳየት አለብን ። አምባገነኖችን ጠንክረን ከታገልናቸው ቀዳዳው ሁሉ ስለሚጠብባቸው ተፍረክርከው ይጠፋሉ። ሃገራችን እና ወገናችን በጨለማ ውስጥ እየዳከረ ባለበት በዚህ የወያኔ አገዛዝ ወቅት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በመረባረብ የዜግነት ግዴታውን አውቆ ለህዝቦች መብት እና ለሃገር ነጻነት መታገል አለበን።

 

ወያኔን ለአንዴና ለመጨረሻ አንኮታኩቶ ለመጣል ሁላችንም የአንድነት ሃይሎች ከተከባበርን፣ ከተደማመጥን፣ ከተስማማንና ከተባበርን ለውጥ ለማምጣት ፈቃደኝነቱና ቆራጥነቱ ካለን ለጋራ ዓላማ ለህዝብ ነጻነትና ለእኩልነት ትግሉን በአንድነት እንቀርጻለን፣ በጋራ እንቆምለታለን፣ በጋራ ከምንፈልገው ግብ አብረን እንደርሳለን ካልን አገራችንን ከጥፋትና አደጋ፣ ህዝባችንንም ከሥቃይና መከራ በቶሎ እንታደጋለን ማለት ነው ፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀጣይ ትግላችን በነጠረ ዓላማና በህዝባዊ መሰረት ላይ የቆመ/የተገነባ መሆኑን እርግጠኛ መሆን የሚገባን፡፡ መሪዎች የሚወጡት ከህዝብ ውስጥ እንደመሆኑ ህዝብን አደራጅቶ የትግሉ አካልና ንቁ ተዋናይ የማድረግና ለዚህም ወደ ህዝቡ ተደራሽነታችንን የማስፋት ተግባራት ከፊታችን ይጠብቁናል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የጋራ ጠላታችንን በአንድነት ሆነን የአቅማችንን በማድረግ ለእናት ኢትዮጵያ እንድረስላት፡፡

 

ሌላው በመናገርና በመጻፍ እንዲሁም ሃሳብን በነጻነት መግለጽ የተከለከለባት ሃገራችን ጋዜጠኝነት እንደወንጀልና አሸባሪነት ከተፈረጀ ከረምረም ብሏል፣ “ጋዜጠኝነትን እና የፖለቲካ ድርጅትን ሽፋን በማድረግ የሀገሪቱንና የሕዝቦቿን ሰላም ለማደፍረስ ከሚያስቡና ከሚፈልጉ ‘ሀይላት’ ጋር ግንኙነት በማድረግ፣ህገ-መንግስቱን በሃይል ለመናድ የተለያዩ የሽብር ተግባራትን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር አውለናቸዋል።“ ይህ አባባል የወያኔ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ 652/2001 እንደ ካብ ድንጋይ የተደረደረ ይመስል ”ህገ-መንግስትን ለመናድ“ የምትል ተደጋጋሚ ማስፈራሪያ ትሁን ቀልድ ያልታወቀች አባባል መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህች ሃረግ የኢትዮጵያ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ 652/2001 ከወጣበት ከነሀሴ 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ጋዜጠኞችና በሰላማዊ መንገድ ተመዝግበው የፖለቲካ ምህዳሩን የተቀላቀሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት በወያኔ መራሹ ቡድን ከታሰሩ በኋላ በመንግስት አካላት የሚሰጥ የተለመደ የመወንጀያ አባባል ነው። የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ መስከረም 2007 ዓ.ም ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥም ከጋዜጠኛ እስከ ፖለቲከኛ፣ ከሀይማኖት መሪዎች እስከ ጦማሪያን፣ ከታጣቂ ወታደሮች እስከ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች በዚሁ አዋጅ አማካኝነት ‘ሽብርተኝነታቸው ተረጋግጦላቸዋል’ ወይም ‘ይረጋገጥባቸው ዘንድ ፍርዳቸውን እየጠበቁ ይገኛሉ።’ ለመሆኑ ይህ ከ14 ዓመት ህፃን እስከ 80 ዓመት አዛውንት በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ የሚያስቀጣው፣ ይህ ከምሁራን እስከ ገበሬዎች ድረስ የሚያስረው ዜጎችን የሚያሰቃየው ሰነድ የህዝብን የመናገርና ሃሳብን የመግለጽ መብት በእጅጉ የሸበበና በተጨባጭ መንግስት እንደፈለገ እያመካኘ ህዝብንና ንጹሃን ዜጎችን እንዲያንገላታና እንዲያሰቃይ ትልቅ በር የከፈተ የአምባገነኖች መሳርያ ሆኖ እያገለገለ ነው።

 

ስለዚህ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አንዱ ለሌላው መረጃዎችን በማስተላለፍ ወያኔ እና ሚዲያዎቹ የሚጠቀሙበትን የማደናበሪያና የማደናገርያ ስልት በማጋለጥ እና ሊደናበር የሚችለውን የዋሁን ኢትዮጵያዊ በማስረዳት የዜግነት ግዴታችንን እየተወጣን በጋራ በመታገል ይህንን ውሸታም እና አጭበርባሪ አደናባሪ ዘረኛ ስርአት ልናስወግደው እና ለመጪው ትውልድ እውነትን የተሞላች ከአባቶቻችን በደምና በአጥንት የተከበረችውን ውዲቱን ሃገራችንን ለተተኪው ትውልድ የማስረከብ ሃላፊነት እንዳለብን ለማሳሰብ እወዳለሁ። በጋራና በአንድነት ከአንድነት ሃይሎች ጋር በመታገል ቀጣይ ድሎቻችንን ለኢትዮጵያ ህዝብ እናመጣለን፣ ሃገራችን በዚህ አደጋ ውስጥ ባለችበት ሰአት ላይ ህዝብ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ለኑሮ ውድነት፣ ለሞት፣ ለስደትና ለኢሰብአዊ ድርጊቶች እየተዳረገ እንዲሁም ኢትዮጵያዊነት እየተዋረደ ከመሆኑም ባሻገር ሃገሪቷን ወደ ፍርስራሽነት ለመቀየር የሚሮጡ ጥቂት ዘረኞች ኢትዮጵያን ከመበታተንና ህዝቧንም ከማጥፋት ልናቅባቸውና ባሉበት ልንቀብራቸው ይገባል። መላው ኢትዮጵያውያን ለዚህ አሸባሪ እና አጭበርባሪ አደናጋሪ መንግስታዊ አክራሪ ሳንዘናጋ በጋራ ተያይዘን በአንድ ሃገራዊ አጀንዳ አምባገነኖችን በመቅበር በእጃችን ያለውን ነጻነት በማረጋገጥ ለገነው ትውልድ አዲሲቷን የጋራ ኢትዮጵያችንን በማስረከብ ታላቅ የሆነውን የዜግነት ድርሻችንን እና ሃላፊነታችንን እንድንወጣ ለማሳሰብ እወዳለሁ::

 

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

Meron Ayele

www.meronayele.info

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on March 12, 2015
  • By:
  • Last Modified: March 12, 2015 @ 7:50 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar