ከዋስይሁን ተስፋዬ
መጋቢት 8 ቀን፣ 2007 እ.ኢ.አ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “የሌላውን ተቃዋሚ ስብስብ የትግል አካሄድ መተቸት ትግሉን ስለሚያዳክም ተገቢ አይደለም።”፣ “የተለየ ሃሳብ ማመንጨት በተቃዋሚው መካከል ልዩነቶችን ማስፋት ነው።”፣ “ጠላታችን ወያኔና ወያኔ ብቻ በመሆኑ፤ጦራችንን እርሱ ላይ ብቻ ማነጣጠር አለብን።”፣ “ተቺዎች ስራ መስራት የማይፈልጉና ዋጋ ቢሶች ናቸው።” እና ሌሎች መሰል አባባሎች በተቃዋሚው ዙሪያ በስፋት እየተስተጋቡ የሚገኙ አባባሎች ሆነዋል። በሌላ በኩል ደግሞ እነኝህ አባባሎች ዋና ዋና የዴሞክራሲ እሴቶች የሚባሉትን የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመጠራጠር፣ የመቃወም፣ ባጠቃላይ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነቶችን የሚገድቡ በመሆናቸው፤ የህወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓትን እንድንቃወም መሰረታዊ መንስኤዎች ከሆኑን መካከል ዋንኞች ስለመሆናቸው በተለያዩ መንገዶች ይነገራል።
በእርግጥም በሃገራችን ኢትዮጵያ ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት ይሰፍን ዘንድ አንድነታችን እንዲጠናከር ለሚመኝ ቅን ዜጋ የጠቃሚነታቸው አባዜ የጐላ ይመስላል። እነኝህ አባባሎች በሚዲያዎች ላይም ከፍተኛ ተፅእኖ ሳይኖራቸው አልቀረም። ለዚህም ይመስላል፤ አብዛኞቹ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ የመናገር ነፃነት አለመኖሩን በስፋት የሚናገሩና የሚቃወሙ ሆነው ሳሉ፤እነኝህኑ ሃሳቦች በስፋት ያሰራጫሉ። በነዚህ አስተሳሰቦች ተውጠውም፤የመልእክታቸው ፍሬ ነገር ከግምት ውስጥ ሳይገባ፤ የተለዩ ሃሳቦችን ላለማስተናገድ ብቻ፤ ምክንያቶችን በመደርደር፣ ጥሩ የሚመስል ቀለም በመቀባትና፣ በህብረተሰቡ መካከል በማሰራጨት፤ የአንድን ወገን ሃሳብ ብቻ በተደጋጋሚ ሲያስተጋቡ ይስተዋላሉ። በዚህ ረገድ ከሻቢያ ጋር በመተባበር ነፃነትን በጠመንጃ ሃይል እውን እናደርጋለን የሚሉ ሃይሎች በአጋጣሚው ለመጠቀም እድለኞች በመሆናቸው፤ ሚዲያዎች የነኝህን ሃይሎች ሃሳብ ብቻ ማቅረቡን ቀጥለውበታል። በተለይ የህዝብ አይንና ጆሮ እንደሆነ በሚነገርለት ሚዲያ (ኢሳት) የብዙ ሺህ እህቶቻችንንና ወንድሞቻችንን ህይወት ቀርጥፎ የበላው አረመኔ አምባገነን (የሻቢያው ቁንጮ ኢሳያስ አፉወርቂ)፤ በጎ ጎኖች ብቻ፤ ተደጋግሞ መቅረቡ ተገቢ ካለመሆኑም በላይ፤ በርካታ ቅራኔዎችን የሚያስነሳና ይህም በትግሉ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል። የተቃዋሚ ድርጅቶች አመራሮች፣ አክቲቪስቶችና፣ ጋዜጠኞችም ቢሆኑ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከዚህ ተፅዕኖ ያመለጡ አይመስልም። በመሆኑም አንኳር የሃገር ጉዳይ ላይ እንኳ አንድ ድርጅት ስህተት አየሰራ እንደሆነ እያዩ እየሰሙ፤ አካሄዱ ሃገሪቱን ወደ ሌላ ችግር እንደሚከታት እየተገነዘቡ፤ ልዩነቶችን ላለማስፋት በሚል እሳቤ፤ እንደ ሶስተኛ ወገን በሩቁ እየተመለከቱ ይገኛሉ።
ለመንደርደሪያ ይሆነኝ ዘንድ ይህንን ካልሁ፤ በግሌ ህዝብ ነፃነቱን ተጐናፅፎ ዘለቄታዊ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፤ ብሎም የምንወዳት ሃገራችን ያለምንም ልዩነት ለሁላችንም እኩል እንድትሆን፤ ህዝባዊ የሰላማዊ ትግል ብቸኛው መንገድ እንደሆነ በፅኑ የማምን ብሆንም፤ የሃገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም እስካልነካና ለህዝብ ችግሮች ዘለቄታዊ መፍትሄን ለማምጣት የሚሰራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል እስከሆነ ድረስ፤ ሁሉም በሚችለውና በመረጠው መንገድ መታገል እንደሚችል በፅኑ የማምን መሆኔን ለአንባቢያን በማስገንዘብ፤ ወደ ዋናው ሃሳቤ ልሸጋገር። በዚህ አጋጣሚ፤ የአንድ ወገን ሃሳብ ብቻ ተደጋግሞ በሚስተጋባበት ወቅት፤ የዝምታውን ድባብ ሰብሮ የሁሉም ወገን አስተሳሰብ ይሰማ ዘንድ፤ ፈር ቀዳጅ ለሆነልን ለአዲስ ድምፅ ሬድዮ (ለአበበ በለው) ምስጋና ይግባውና፤ እነሆ እኔም ሃሳቤን በድፍረት እንድገልፅ መነሻ ሆኖ ይህችን ፅሁፍ ለአንባቢ ማቅረብ ችያለሁ። ለዚህም ምስጋናና አድናቆቴን መግለፅ እወዳለሁ።
ዛሬ በሃገራችን ኢትዮጵያ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ነፃነት እንዲሰፍን ባላቸው ፅኑ እምነትና ተስፋ አንድያ ህይወታቸውን መስእዋት ለማድረግ በረሃ ወርደው የሚገኙት ውድ የኢትዮጵያ ልጆች የመንፈስ ጥንካሬና ቁርጠኝነት ላቅ ያለ ክብር የሚገባው ትእይንት ነው። በአንፃሩ ደግሞ የሃገራችን የነፃነት ትግል ታሪክ እንደሚያመለክተው ባለፉት አስርት አመታት አያሌ ዜጐች ተሰውተዋል፣ ከሃገር ተሰደዋል፣ ለሌሎች በርካታ ውስብስብ ችግሮች ተዳርገዋል። ይሁንና አያሌ ኢትዮጵያውያን ዜጐች የከፈሉት ከፍተኛ መሥዕዋትነት የተመኙትን ነፃነት እውን ማድረግ ተስኖት፤ የታገሉለት አላማ በጥቂት ቅንነት የጐደላቸው ግለሰቦች በተደጋጋሚ ተቀልብሶ መና በመቅረቱ፤ እንሆ ዛሬም የተጨማሪ እህቶቻችንንና ወንድሞቻችንን ህይወት ለመገበር እየተሰናዳን መሆኑ እጅግ የሚያሳዝን ክስተት ሆኗል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንደሚገነዘበው፤ የህወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓት በተቃዋሚ ሃይሎች ላይ እያደረሰ የሚገኘው ከልክ ያለፈ ግፍና አፈና፤ በሠላማዊ መንገድ እየታገሉ የሚገኙ ሃይሎችን ወዳልተፈለገ የሃይል እርምጃዎች በእጅጉ እየገፋቸው እንደሆነ ይታወቃል። እዚህጋ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ፤ ቀድሞውኑ እንደ ህወሓት/ኢህአዴግ ካለ አረመኔ የአምባገነን ሥርዓት ከዚህ እጅግ የባሰ ጭካኔ ሊደርስ እንደሚችል መጠበቅ እንዳለብን ነው። ይሁንና የተቃዋሚ ሃይሎች ፤የሚመጡ አስተያየቶችን ገፍተው በችኮላ የሚከተሉትን የትግል ስልት ወደ ሃይል እርምጃ ከመቀየር በፊት፤ የሰላማዊ ትግሉን ሙሉ ለሙሉ ለመጠቀም ቢሰሩ የተሻለ ይሆናል። በእርግጥም የህወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓት እየሰራቸው የሚገኙትን ግፎችና በደሎች ከማሳወቅ ባሻገር፤ የሰላማዊ ትግል ማለት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግና በምርጫ መወዳደር ብቻ አለመሆኑን ለህዝቡ ግንዛቤዎችን ማስጨበጥ ይጠበቅባቸዋል። ነገሮችን ባላገናዘበ ሁኔታ “የሠላማዊ ትግል አበቃለት” የሚለውን የተሳሳተ መረጃ ከማስተጋባት በፊት የሠላማዊ ትግል ምንነትን ለመለየት መሞከር፤ ሠላማዊ ትግል በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ውጤት ተገንዝቦ መጠቀም ከማስቻሉም በላይ፤ ለህዝብ የተሳሳተ መረጃን ማስተላለፍ ነውና እንጠንቀቅ።
የሰላማዊ ትግል የተቃውሞ ሰልፎችን ከማካሄድና በምርጫ ከመሳተፍ እጅግ ያለፉ ሌሎች በርካታ ተግባራትንና ሂደቶችን በውስጡ ያካተተ ሰፊ ፅንሰ ሀሳብ ነው። የሰላማዊ ትግል የህዝብን ፍላጐት ለአገዛዙ ከማሳወቅና መብትን ከመጠየቅ የሚጀምር ሲሆን፤ አገዛዙ ጥያቄዎቹን ፈቅዶ ሊመልስ ካልቻለ፤ደረጃ በደረጃ ትግሉን ወደ ሁለተኛው እርከን በማሳደግ፤ማለትም ወደ ህዝባዊ እምቢተኝነት በማሳደግ፤ህዝብ ለአገዛዙ ተገዢ ባለመሆንና ባለመተባበር ጫና በመፍጠር፤ አገዛዙ የህዝብን ጥያቄ መመለስ እንዲችል ማስገደድ፤ ይህም ካልሆነ ደግሞ፤ሠላማዊ ትግሉን ወደ ሦስተኛውና የመጨረሻው እርከን በማሸጋገር ለአገዛዙ በህይወት መኖር ወሳኝ የሆኑ ቋሚ ዘንጐቹን፤ የተለያዩ የሰላማዊ ትግል ህዝባዊ እርምጃዎችን በመተግበር፤ አሽመድምዶ ከጥቅም ውጭ በማድረግ፤ አገዛዙን ከስልጣን ማስወገድን ያካትታል። በእርግጥ ይህንን መሠል የሠላማዊ ትግል በተሳካ ሁኔታ ለመተግበር፤ ህዝብ የትግሉን ምንነትና ምክንያቶቹን በሚገባ ተረድቶ ለመብቱ እንዲታገል በሰፊው የማስተባበር ሂደትን ይጠይቃል። በእርግጥ በሃገራችን የሠላማዊ ትግል ታሪክ ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት አብይ እርከኖች መካከል፤ የመጀመሪያው አካል ከሆኑት በርካታ እርምጃዎች ውስጥ ጥቂቶቹን ከማከናወን ያለፈ ምንም አይነት ህዝባዊ እርምጃ ተወስዶ አያውቅም። ይሁንና በደል እስካለ ድረስ ህዝብ መተባበሩ አይቀርምና፤ በአካሄድ ተስማምቶ በአንድነት ለአንድ አላማ ከተሠራ በተገቢው ፍጥነት ወደ ውጤት መድረስ አስቸጋሪ አይሆንም። ስለሆነም ባልተጠና ሁኔታ የትግል ስልትን ወደ መሳሪያ ትግል ከመቀየር በፊት፤ በተለይ ለኢትዮጵያ ፈፅሞ በጐ ከማይመኝና ስር ከሰደደ ታሪካዊ ጠላት ጋር በመተባበር፤አካሄዱ የሚያስከትለው መዘዝ እጅግ አስከፊ ሊሆን ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል።
አበው እንዳሉት፤የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል ነውና፤ ኢትዮጵያ ሃገራችንን ለዚህ ውስብስብ ችግር ከዳረጓት ቡድኖች መካከል የዝሆኑ ድርሻ ከነበረው ከሻአቢያ ጋር በመተባበር የሚደረግ ትግል፤ ፈጣሪ በቃችሁ ብሎ አንዳች ታምር ካልተፈጠረ በቀር፤ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ፤ ወደ ሌላኛው የችግር አዙሪት የሚከተን መሆኑ እሙን ነው። በመሆኑም “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው”፤ “ወያኔን ለማስወገድ ከሰይጣንም ጋር ቢሆን እወዳጃለሁ።” በሚል የጠበበና የሃገሪቱን የወደፊት እጣፈንታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ብሂል ተገድበን፤ ህዝብን ዳግም ወደ መከራ መግፋት ፍፁም ተቀባይነት እንደማይኖረው ከወዲሁ በመረዳት፤ የአስተሳሰብ አድማሳችንን ቀስፎ ያሰረውን ሻቢያ የተሰኘ አልባስ አውልቀን፤ ነፃና ቅን በሆነ መንገድ ነገሮችን አስፍተንና አርዝመን በመመልከት፤ የሚበጀውን መስመር መከተል ብቸኛውና እጅግ አስፈላጊ አማራጭ መሆኑን ልንረዳ ግድ ይለናል።
ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር!
Average Rating