የመን ምጥ በቁና ሆና በአየር ስትደበደብ አደረች
በግሩም ተ/ሀይማኖት
ረቡዕ እለት ለሀሙስ አጥቢያ ከሌሊቱ 8፡30 አካባቢ የየመኗ ዋና ከተማ ሰነዓ በፍንዳታ ተናወጠች፡፡ ቀጥሎም የአነስተኛ እና ከባድ መሳሪያ ተኩስ ቀጠለ፡፡ የመጀመሪያው ፍንዳታ ከተሰማ በኋላ ደጋግሞ ቀጠለ፡፡ ሳዑዲ አረቢያ ካስተባበረቻቸው 10 አረብ ሀገራት ጋር በመሆን በ200 በላይ ጀቶች የአየር ድብደባ እያደረጉ ነው፡፡ የየመን መገናኛ ብዙሀን እና ሌሎችም ይህንኑ እየጠቀሱ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የነበረው ተኩስ እስኪነጋ ቀጠለ፡፡ የአየር ጥቃቱ የተደረገው በወታደራዊ ተቋማት ላይ ነው፡፡ የቀድሞው ፕሬዘዳንት አሊ አብደላ ሳላህ ቤትም መመታቱ ተነግሯል፡፡
ንጋት ላይ ግን የወትሮውን እንቅስቃሴ የቀጠለ ቢመስልም አልቀጠለም፡፡ ቀኑንም ጭር ብሎ እንቅስቃሴው ተገታ አልፎ አልፎ የተኩስ እና ከባድ መሳሪያው ከርቀትም ከቅርበትም ይሰማል፡፡ በአየር የሚደረግ ጥቃቱ ግን ከከተማው ውጭ እንደቀጠለ ነው፡፡ ከተማ ውስጥም ከሁለት ጊዜ ያላነሰ ቦታ በአየር ተመቷል፡፡
አሁን ምሽቱን ደግሞ በጣም በተጠናከረ ሁኔታ አሁን ተጀምሯል፡፡ ከአየር የሚጣለው መሳሪያ መሬት ሲያርፍ ከፍተኛ የሆነ ብርሃን አካባቢውን ያወርስና ወዲያው በጭስ የታጀበ እሳት እና አቧራ ይነሳል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ የተመቱት ወታደራዊ ተቋማት ብቻ ናቸው ቢባልም የተፈለጉ ሰዎች ቤት እና ቦታዎችም እየተመቱ ናቸው፡፡ ሰነዓ ያለ ሀበሻ በሰቀቀን አለቅን በሚል ፍርሃት ውስጥ መሽጎ ነው ያለው፡፡ በእርግጥ እንኳን እኛ ስደተኞቹ ባለሀገሮቹ የመናዊያኑም በከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ ነው ያሉት፡፡ እግዚአብሄር ሆይ በብዙ ነገር የተገፋን ህዝቦች ነን በመንግስታችንም ተገፍተን ተደፍተን ነው ያለነው፡፡ አረቦቹ እንኳን ሲጫወቱብን ለምን የሚል መንግስት የለንም፡፡ ለመንግስት ባለስልጣኖችም ቀና ልቦና ለወገናቸው አሳቢነት ስጣቸው፡፡ ወገን ሊያልቅ ተጨንቆ እያዩ በዝምታ ተቀምጠዋል እና ችግሩን የሚያዩበት አይን ብቻ ሳይሆን የሚገነዘቡበት ልቦና ስጣቸው፡፡ ከሁሉ ከሁሉ ግን የአንተ ጥበቃ አይለየን አምላኬ፡፡……..
ኦ….. ፍጣሪ አምላኬ ስደተኛ ልጆችህን ጠብቅ በአሁኑ ሰዓት ሰነዓ በከፍተኛ ተኩስ ተናውጣለች፡፡ የአየር ድብደባው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የመናዊያኑ አንድ ጄት መጣላቸውን ይናገራሉ፡፡ እንደነሱ አባባል ከሆነ ከረቡዕ ሌሊት 8፡30 ጀምሮ እስካሁን 4 ጄቶች እንደጣሉ ነው፡፡
Average Rating