የመረጃ ግብአት .. በ4ኛው ቀን ዘመቻ …
==============================
* ትናንት ቅዳሜ መጋቢት 19 ግብጽ ሻርማ ሸክ ተሰብስበው የነበሩት 22 የአረብ ሊግ ሀገራት መራሄ መንግስታት በ26 ኛው መደበኛ ስብሰባ የየመንን ጉዳይ በሰፊው ተነጋግረውበታል
* መራሔ መንግስታቱ የሁቲ አማጽያን በኃይል ከያዘው ስልጣን ለማስወገድና ህጋዊውን የፕሬ አብድልረቡ መንግስት ወደ ቦታው ለመመለስ ተስማምተዋል !
* የሳውዲው ንጉስ ሰልማን ” ዘመቻው ግቡን እስኪመታ አያቆምም !” ሲሉ የግብጽ ፕሬ አል ሲሲ በበኩላቸው የጽንፈኝነትን መንሰራፋት በማውሳት በአረብ ሀገራትን አደጋና ከኢራን ትንኮሳ ለመታደግ ጥምር የጦር የአረብ ሀገራት ሰራዊት እንደሚያስፈልግ በስብሰባው ላይ በአጽንኦት ተናግረዋል
* ጉባኤው በአረብ ጥምር የህብረት ጦሩን ጉዳይ ከመከረ በኋላ በስብሰባው መዝጊያ የአብ ሊግ ዋና ጸሃፊ ነቢል አል አረቢ ባሰሙት የአቋም መግለጫ ከዚህ ቀደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ያቀረቡት ረቂቅ ህግ ተጠንቶ በአጠቃላይ ጉዳይ በአንድ ወር ውስጥ ተገናኝተው በመምከር ታሪካዊ ያሉትን የህብረት ጦሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመመስረት እቅድ መያዙን አስታውቀዋል
* የኩዌትን አሚር ጨምሮ የተለያዩ አረብ ሀገራት ኢራን የአካባቢውን ሀገር ሰላም ለመንሳት በተዘዋዋሪ የምታሳየውን ተደጋጋሚ ፍላጎት ተቃውመውታል
* ፖለቲካ ነውና ያልተጠበቀው ይሆናል ፣ የፍልስጥኤም መሪ ፕሬ መሀሙድ አባስ በአረብ ሊግ ስብሰባ የተገኙ ሲሆን ከኢራን ድጋፍ ያገኛል የሚባለው የፍልስጥኤሙ ሽምቅ ተዋጊ ሃማስ የአረብ ሀገራቱን አቋም የሚደግፍ አስገራሚ የድጋፍ መግለጫ አውጥቷል
* የየመንን ህጋዊ መሪ ፕሬ አብድልረቡ መንሱር አልሃዲን መንግስት ወደ ስልጣን ለመመለስ በሳውዲ የሚመራውን ዘመቻ እንደሚደግፈው ፍልስጥኤምን ነጻ ለማውጣት ጠመንጃ ያነሳው ሽምቅ ተዋጊው ሃማስ ዘመቻውን ደግፎ መግለጫ ማውጣቱ ብዙዎችን አስገርሟል
* ስድስቱ ኦማንን ሳይጨምር የባህረ ሰላጤ ሀገራትን ሳውዲ ፣ ኢምሬት ፣ ቃጣር ፣ ኩዌትና ባህሬንን ጨምሮ ዮርድያኖስ ፣ ግብጽ ፣ ሱዳን ፣ ሞሮኮ በዘመቻው ተሳታፊ ሲሆኑ ፣ ቱርክ፣ ሞሮኮ ፣ አሜሪካ ፣ እንግሊዝ ፈረንሳይ እና ቤልጅየም ድጋፍ መስጠታቸው ይጠቀሳል በአንጻሩ ሶርያ ፣ ኢራን ፣ ራሽያና ቻይና ዘመቻውን አጥብቀው ተቃውመውታል
* ኢራን የሁቲ ሸማቂዎችን በማስታጠቅና በመደገፍ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተች የየመን ፕሬ አብድልረቡ መንሱርና የአረብ ሀገር መራሔ መንግስታት ቢጠቁሙም ኢራን የሚቀርብባት ውንጀላ ሁሉ ” መሰረተ ቢስ ውንጀላ ነው! ” ስትል አስተባብላለች
የትዕንግርተኛው የመን ” ድብደባውን አቁሙ! ” ተማጽኖ …
===================================
* የቀድሞው የየመን ፕሬ አሊ አብደላ ሳላህ ከ30 ዓመት በላይ የመንን ሲያስተዳድሩ አቀማጥለው የደገፏቸው ፣ የአረብ አብዮት መጥቶ ሀገር የመን ስትታመስና ፕሬ አብደላ ሳላህ በአጥፍቶ ጠፊ ሲጎዱ አፈፍ አድርገው ህይወታቸውን የታደጉትንና ወደ ኋላም የመን በተቃውሞ ስትናጥና ስልጣናቸው አልረጋ ሲል መውጫ መንገድ ያበጁላቸው በቅርብ ሳውዲዎች ፣ በርቀት የባህረ ሰላጤ ሀብታም አረብ ሀገራትና ምዕራባውያን ናቸው
* ዛሬ የቀድሞው ፕሬዚደንት ከቁርጥ ቀን ደጋፊያቸው ከሳውዲ ፣ ከአረብ ሀገራትና ከምዕራባውያን በተቃራኒ ጎራ መሰለፋቸው ይጠቀሳል ፣ የቀድሞ ታዛዥ አጋራቸውና ስልጣናቸውን ሳይወዱ በግድ ያስረከቧቸውን የፕሬ አብድልረቡ መንበረ ስልጣን እንዳይረጋ እንደ ኢራን በድብቅም ባይሆን በግላጭ ሁቲዎችን በመደገፍ የቀድሞው መሪና ልጃቸው አህመድ የመንን ለዚህ ውጥንቅጥ እንዳደረሷት ይጠቀሳል
* የቀድሞው የየመን ፕሬ አሊ አብደላ ሳላህ በ26 ኛው የአረብ ሊግ የመሪዎች ስብሰባ ለተቀመጡት መራሔ መንግስታት ሳውዲ መራሹ ዘመቻ ያቆም ዘንድ ” ችግሩ የተፈጠረው በፕሬ አብድልረቡ የአስተዳደር አቅም ማነስ ነው ፣ ድብደባውን አቁሙ ፣ መፍትሔው በድርድር እንጅ በጦርነት አይደለም! ” የሚል አንድምታ ያለው ትንግርተኛ ተማጽኖ በአንድ ታዋቂ የአረብኛ ቴሌቪዥን በኩል መልዕክት አስተላልፈዋል
* የቀድሞው ፕሬዚደንት የቆየውን የሳውዲና የሀገራቸውን መልካምና ጠንካራ ግንኙነት ፣ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ የመናውያን በሳውዲ በተለያዩ ስራዎች ተሰማርተው የመገኘታቸውን መልካም ጉርብትና በማውሳት ሳውዲ መራሹ ጦር በየመን ላይ የከፈተውን ዘመቻ ልጆቻችንና ሀገራችን እያወደመ ነው ሲሉ ድብደባው በአስቸኳይ ያቆም ዘንድ ልዩ መልዕክትን ለሳውዲ መንግስት አስተላልፈዋል
* የቀድሞው የየመን ፕሬ አሊ አብደላ ሳላህ በዚሁ ንግግራቸው የመንን በድርድር የማረጋጋቱ ስራ ቅድሚያ ይሰጠው ሲሉ የየመን ወቅታዊ ችግር በድርድር ከተፈታ በቀጣይ ምርጫ ቢደረግ እርሳቸውም ሆኑ የቤተሰብ አባሎቻቸው ወደ ስልጣን መንበር የመውጣት ፍላጎት እንደሌላቸው በንግግራቸው አስታውቀዋል
* የቀድሞው የየመን ፕሬ አሊ አብደላ ሳላህ ልጆች መካከል የጦር መኮንኑ አህመድ በሶስተኛው ቀን የአየር ላይ ድብደባ እንደቆሰሉ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ጠቁመዋል ። የተረጋገጠ መረጃ ነው ማለት ግን አይቻልም። ይህ በእንዲህ እንዳለ በቀድሞው የየመን አስተዳደር በከፍተኛ የጦር ኃላፊነት ያገለግሉ ከነበሩት ውስጥ የቀድሞው ፕሬዚደንት ልጅ አህመድ በሳውዲ የተመራው ጦር የዘመቻ ጥቃት ከመደረጉ አስቀድሞ የሁቲ አማጽያንን ከስልጣን ለማስዎገድ እድሉ እንዲመቻችለት ጥያቄ አቅርቦ ተቀባይነት አለማግኘቱን አል አረቢያ ዘግቦታል
የሁቲዎቻ ዛቻና የዘመቻው መምሪያ መግለጫ
============================
* የሁቲ ከፍተኛ ባለስልጣን አብል ሙንኢም አል ቁረሽ የሳውዲን ጣልቃ ገብነት በዚህ ከቀጠለ ሳውዲ ልትቆጣ ጠር የማትችለው ጥቃት እንሰነዝራለን ሲሉ ለኢራን አል ፋሪስ ዜና ወኪል በሰጡት መግለጫ ዝተዋል
* በሁቲዎች ዛቻና በዘመቻው ዙሪያ ትናንት መግለጫ የሰጡት በሳውዲ የተመራው የህብረት ጦር ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀኔራል አህመድ አሲሪ ስለ አራተኛው ቀን የአየር ድብደባ መግለጫ ሰጥተዋል
* ብርጋዴር ጀኔራል አህመድ አሲሪ በተለያዩ ከተሞች በዘመቻው መምሪያ በተጠኑ የሁቲ አማጽያን ወታደራዊ ኢላማዎች አልፎ ወደ ሳውዲ የመን ድንበር የጀዛንና ነጅራን ዘልቀው ጥቃት ሊሰነዝሩ የነበሩ የሁቲ ቡድን አባላት እግር በእግር እያታሰሰ የመደምሰሱ ስኬታማ ስራ መስራቱን የዘመቻው ቃል አቀባይ አስረድተዋል
* ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀኔራል አህመድ አሲሪ በዚሁ መግለጫቸው በሳውዲ የተመራው የህብረት ጦር በሁቲ አማጽያን እጅ የነበረውን የብላስቲክ ሚሳየል ክምችት ballistic missile stockpile በአብዛኛው ማውደሙን አስታውቀዋል
* ከየመን ሰንአ የህብረቱ የአየር ኃይል ጦር የደቡብ ከተማዋ በዳሊያ ባደረገው ወታደራዊ ይዞታዎች ኢላማ ያደረገ ድብደባ የሁቲ አማጽያን ጸረ አውሮፕላን በመተኮስ መልስ መስጠታቸውም ተጠቁሟል
* ወደ ሶስት መቶ የሚጠጉ የሳውዲ ፣ የምዕራባውያን ሀገር ዲፕሎማቶች እና የተባበሩት መንግስታት ሰራተኞችን በተለያየ ዘመቻ ሰንአ የመንን ለቀው መውጣታቸው ታውቋል
እስኪ ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
መጋቢት 20 ቀን 2007 ዓም
Average Rating