ይሄይስ አእምሮ
በዚያን ጊዜ ሰዎች ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ ይገድሏችኋል፤ በስሜም ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፡፡ በዚያን ጊዜ ብዙዎች ሃይማኖታቸውን በመካድ ይሰናከላሉ፤ አንዱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል፤ ሰዎችም እርስ በርሳቸው ይጣላሉ፡፡ ብዙ ሃሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ፤ ከክፋት ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች፡፡ እስከ መጨረሻ በትዕግስት የሚጸና ግን ይድናል፡፡ ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል በመላው ዓለም ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜ መጨረሻው ይመጣል፡፡ (ማቴ. 24፣ 9 – 14)
በሀገር ውሰጥና በየዓለሙ ማዕዘን እንደጨው ዘር የተበተናችሁ ውድ የሀገሬ ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ፡፡
ወንድምና እህቶቻችን ለቤት ቀጋ ለውጭ አልጋ የሆነውን የወያኔ መንግሥት ፈርተው የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ ወደ ውጪ ቢሰደዱ ብዙዎቹ በሚሄዱባቸው ሀገራት ውስጥ የሚደርስባቸው መከራና ስቃይ የሚሰቀጥጥና ለጆሮም የሚቀፍ መሆኑን በየጊዜው እየተከታተልን ነው፡፡ በተለይ በኛ በኢትዮጵያውያን ላይ ሰማይና ምድር ተመሣጥረው አንዳች የመከራ አዙሪት የጫኑብን ይመስላል፡፡ ይህ ሁለንተናዊ የመከራ ዶፍ እንዲያበቃ ከእያንዳንዱ ወገን የሚጠበቅ ብዙ ነገር መኖሩን አንርሳ፡፡ እርግጥ ነው – አሁን ቆመን ማውረድ ያቃቱንን ብዙዎቹን ችግሮቻችንን እኛው ቁጭ ብለን የሰቀልናቸው ናቸው፡፡ የዱርይነት ተፈጥሯዊ ባሕርያቸውን በግማሽ ምዕተ ዓመት እንኳን መለወጥ ያልቻሉ እነዚህ በጣት የሚቆጠሩ ሽፍቶች 90 ሚሊዮን ሕዝብ እንደከብት ሊነዱን የበቁት በኛ ግዴለሽነትና ምናልባትም የተዞረብንን አፍዝ አደንግዝ ለማክሸፍ የጋራ ጥረት አለማድረጋችን እንጂ በኃይልና በጥበብ በልጠውን እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ ሁሉንም እየደረሰብን ያለውን ችግር ሲያጤኑት በእጅጉ የሚያሣዝን ነው፡፡ እኔማ የመሸናነፍ ትርጉም ውሉ እስኪጠፋኝ ድረስ ግርም ይለኛል፡፡ በርግጥም መሸናነፍ ምን ይሆን?
ከደቂቃዎች በፊት የቢቢሲን ድረገፅ ስጎበኝ የጊዜው ፋሽን የሆነውን አሰቃቂ ዜናዎችን ተመለከትኩ፡፡ እነዚህ አይ ኤስ የሚባሉ ጭራቆች ከፈጣሪ በቀር አንድም አለኝታ የሌላቸውን ስዱዳን ኢትዮጵያውያንንም በሊቢያ በረሃ አንገታቸውን እየቀሉ ካለደም ግብር ለማይታዘዝላቸው መንፈስ ጭዳ እያደረጓቸው ነው፡፡ ወደ 30 የሚጠጉ ክርስቲያን ወገኖቻችንን በሃይማኖታቸው ሰበብ ብቻ ሠይፈዋቸዋል፡፡ ሀዘናችንንም ሆነ ዘመን-ወለድ ነባራዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ የሚሰማንን ስሜት ለመግለጽ ቃላት የምናገኝ አይመስለኝም፡፡ የምንገኝበት ወቅት በቀላል አማርኛ “አሳሳቢ ነው” ብለን የምናልፈው አይደለም፡፡ የሰው ልጅ አላበሳው በሚከተለው ሃይማኖት ብቻ አንገቱ የሚቀነጠስ ከሆነ ዓለማችን በለየላቸው ዕብዶችና ወፈፌዎች እጅ እየገባች ነውና ሁሉም የዓለም ዜጋ ቆም ብሎ ስለጋራ ኅልውናው ማሰብ የሚገደድበት ጊዜ ላይ ይገኛል፡፡ እንደተረቱ “የፋሲካው በግ በገናው በግ ይስቃል” እንዲሉ ሆኖ እንጂ በመካከለኛው ምሥራቅ የተወሰኑ አካባቢዎች የተጀመረው ይህ ሰይጣናዊ እንቅስቃሴ ዛሬ የሜዲትራኒያንን ባሕር ተሻግሮ ሊቢያና ናይጄሪያ በመግባት የንጹሓን ዜጎችን ሕይወት ሲቀጥፍ እንደወትሮው ሁሉ ዝም ከተባለ ነገና ከነገ ወዲያ ይህ አዲስና የመጨረሻው ዘግናኝ የአገዛዝ ሥልት የዓለም ዋና የአስተዳደር ይትበሃል እንዳይሆን ያሰጋል፡፡
በመሠረቱ ትንቢትን ማስቀረት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ በዓለማችን ዙሪያ ሲደረጉ የሚታዩ ብዙ አስቀያሚ ነገሮች ቀድመው የተነገሩ ናቸው ማለት እንችላለን፡፡ በመሆኑም ከእምነት አኳያ እነዚህን በዘግናኝነታቸው ወደር የማይገኝላቸውን ዐረመኔያዊ ተግባራት እንደትንቢት ፍጻሜ መመልከት ይቻላል፡፡ የጥንት አባቶችና እናቶች አንድን የመከራ ዘመን ፈጽሞ ማስቀረት ባይችሉም እንዲያጥር የሚያደርጉበት ዘዴ ግን ነበራቸው፡፡ እኛም ይህ የፍዳ ዘመን እንዲለዝብና የእስካሁኑ በቅቶን የደስታና የፍስሐ ዘመን እንዲብት ማድረግ የምንችልበት ብልሃት አለን፡፡ ቀላልም ነው፡፡ ትንሽ ቆየት ብዬ ልመለስበት፡፡
ከቢቢሲ ዜና እንዳነበብኩት ሙስሊምና ክርስቲያን ስደተኞች በአንዲት ጀልባ(መርከብ?) ተሣፍረው ወደዚያች ወደፈረደባት ጣሊያን ይሄዳሉ፡፡ እየሄዱ ሳሉ የባሕር ሞገድ ይነሣና መርከቢቷ ትናወጣለች፡፡ ያኔ አንዱ ናይጄሪያዊ ክርስቲያን ስደተኛ ወደ እግዚአብሔሩ ይጸልያል፡፡ አጠገቡ የነበረ ሙስሊም ደግሞ ወደ አላሁ መጸለዩን ትቶ “ለምን ለአላህ አትጸልይም፤ ከአላህ በስተቀር እግዚአብሔር የሚባል ሌላ ፈጣሪ የለም፤ እሱ ሀሰት ነው፡፡ እውነተኛው አምላክ አላህ ብቻ ነው …” በሚል ከክርስቲያኑ ስደተኛ ጋር ጠብና ንትርክ ይጀምራል፡፡ ተመልከቱልኝ፡፡ ከዚህ የበለጠ አይሲሳዊ ድንቁርና የለም፡፡ ይህ ሙስሊም ስደተኛ በችግር ሰንሰለት ታስሮ እንኳን ድንቁርናውን ለአፍታም ቢሆን ሊዘነጋ አልቻለም – በእግዜር እጅ ተይዞም “የሚሞላቀቅ” ጉደኛ ሰብኣዊ ፍጡር ነው፡፡ ከባሕር ወጥቶ መሬት ይረግጥ አይረግጥ ሳያውቅ በዚያች በጠባብ ጭንቅላቱ ውስጥ የተሰነቀረችበትን ክፉ የሃይማኖት ዶክትሪን እውን ለማድረግ ሲጥር ይታያችሁ፤ አንዳንድ ሰዎች “እንደማይምነት ያለ ክፉ በሽታ የለም፤ አደገኛነቱም ከሁሉም ይከፋል” ሲሉ እምሰማው ትክክል ነው፡፡ እነማርክስ “ሃይማኖት ናርኮቲክቲክስ ነው” ያሉት ከዚህ ልዩ ክስተት አንጻር መሆን አለበት፤ ከዚህ አንጻር ተናግረውት ከሆነ ደግሞ በበኩሌ ትክክል ናቸው፤ የአእምሮን ሚዛናዊነት የሚያጠፋ “ሃይማኖት”፣ የሌሎችን እምነት በኃይል አስደፍጥጦ የእምነቱ ተከታዮች “የኔ ሃይማኖት ብቻ ነው ትክክሉ! በርሱ ካላመናችሁ እቆራርጣችኋለሁ” እንዲሉ የሚያደርግ የሃይማኖት ፍልስፍና ካለ ዕብደት እንጂ እውነተኛ ሃይማኖት ሊሆን አይልም፡፡ “ከባልሽ ባሌ ይበልጣልና ሽሮ አበድሪኝ” አለች አሉ አንዷ ሞኝ ሚስት፡፡ ሃይማኖት እንዲህ ከሆነ፣ ሃይማኖት በሠይፍ እየቀሉና በጎራዴ እየመተሩ የሰውን ልጅ ክቡር ገላ ማርከስ ከሆነ ባፍንጫየ ይውጣ፡፡ እናላችሁ በዚያ አላስፈላጊ ጠብ ብዙ ክርስቲያኖች ወደባሕር ተጥለው ሕይወታቸው ሊያልፍ፣ ሥጋቸውንም የባሕር ዐውሬ ሊቀራመተው ቻለ፡፡ የሰው ልጅ አስተሳሰብና አመለካከት ወዴት እያመራ ነው? በውነቱ ምን ነካን? ያ ሰው ለእግዚአብሔር ቀርቶ ለጨረቃና ለፀሐይ ቢጸልይና ቢሰግድስ ሙስሊሙን ምን ጥልቅ አደረገው?
የሰው ዘር ባጠቃላይ የትም ይኑር የትም በአሁኑ ወቅት ክፉኛ እየተቸገረና እየተሰቃዬ ነው፡፡ ሀብታምም ይሁን ድሃ ከሞላ ጎደል ሁሉም የሰው ልጅ በመከራ ውስጥ ይገኛል፡፡ በአንጻራዊ ሁኔታ የአንደኛው ሀገር ሕዝብ ከሌላኛው ጋር ሲነጻጸር በተሻለ ሁኔታ የሚኖር ቢመስልም ችግሮች በደረጃና በዓይነት ቢለያዩ እንጂ ሁሉም ሰው በአንድ ወይ በሌላ ችግር የሚጠቃ መሆኑ መረሳት የለበትም፤ ዘመኑ የመጨረሻው መጀመሪያ ይመስላልና፡፡ ማየት ማመን ነውና በአራቱም አቅጣጫ እንመልከት፡፡
ሀብት ደግሞ ምናልባት የችግር ምንጭ እንጂ የእውነተኛ ደስታና እርካታ መንስዔ እንዳልሆነ መረዳት አለብን፡፡ በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት ሰባ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ያለው አንድ ሰው ሰባ ዘጠኝ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ያለውን ሰው በሀብት ቀድሞ ለመገኘትና ስሙን በፎርብስ የክብር መዝገብ የመጀመሪያ ተርታዎች ለማስፈር እንቅልፍ አጥቶ ያድራል፡፡ በዚህ የሀብት ማካበት እሽቅድምድም ምክንያት በሚሠሯቸው “ወንጀሎች”ና ተገቢ ያልሆኑ ገንዘባዊ ግንኙነቶች ኅሊናቸው እንደወተት ሲናጥ የሚያድር፣ ያንን ጤናማነት የሚጎድለው ውድድርና የሚያስከትለውንም የኅሊና ቀውስ ለጊዜውም ቢሆን ለመርሳት በመጠጦች ኃይል ናላቸውን የሚያዞሩ ሀብታሞች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ የምኞታቸው አለመሳካት እያበሳጫቸው፣ ምናልባትም በአላስፈላጊ ሁኔታ የገቡበት ዕዳ እያስጨነቃቸው፣ የሠሩት ግብር ነክ ማጭበርበር እያሣፈራቸው፣ ለሀብት ብለው ያደረጉት ጸያፍ ነገር ኅሊናቸውን እየሸነቆጣቸው፣… በሽጉጥና ባመቻቸው መንገድ ሁሉ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሀብታሞች ቁጥርም ቀላል አይደለም – ከኢትዮጵያም ከሌሎች ሀገራትም አንዳንድ በዚህ ሁኔታ ራሳቸውን ያጠፉ ሚሊዮኔሮችን መጥቀስ በተቻለ – አይገባም እንጂ፡፡
በሌላም በኩል ካየነው ገንዘብን የሚያሳድድ ሰው ቤተሰባዊ ፍቅሩና ትዳርን አያያዙ “ከዓለም አቀፍ ስታንዳርድ” በታች ስለሚሆን በቤታቸው ውስጥ ስንጥቃት እየተፈጠረ፣ ስንጥቃቱ ወደለዬለት አምባጓሮና ጦርነት እያመራ፣ በውጤቱም የትዳር መበተን እየተከተለ፣ በማከያው የልጆች ሕይወት በወላጅ ፍቅር ዕጦትና ያን ተከትሎ በሚከሰት የሀሽሽ፣ የጫትና የመጠጥ ሱስ እየተመሰቃቀለ … ስንቶች ጉድ እንደሚሆኑ መገንዘብ አያቅተንም (በበኩሌ የሀብታም ልጆች ከሚማሩባቸው ት/ቤቶች አካባቢ ከበቂ በላይ የሆነ መረጃ ስለማገኝ ይህን ነገር በሚገባ ዐውቃለሁ)፡፡ ስለዚህ የተሟላ ጌትነት የለም ወዳጄ፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ጥርት ያለች “ንጹሕ” ድህነት ወርቅ መሆኗን የሚያስታውስ አስጠሊታና ሰቅጣጭ ገጠመኞችን እንሰማለን – በድህነት ቢያንስ ጥሩ እንቅልፍ አለ፤ በየደቂቃና ሴከንዱ እየታወሰ የሚረብሽ የዕለት ገጠመኝ የለህም – በአብዛኛው፡፡ እህቴ – እግዚአብሔር ያልባረከው ገንዘብ የሚያመጣው ጠንቅ ብዙ ነው፡፡ እንግዲህ ማለት የፈለግሁት ምንድነው – የትም ኑሪ የትም፣ ምንም ይኑርሽ ምን … በአሁኑ የዓለማችን ሁኔታ ከአንድ ወይ ከሌላ ችግር የሚያመልጥ ሰው የለም ነው፤ ዘመኑ ነው ማለት ከፈለግሽ መብትሽ ነው፡፡ ይህ ግን እንደመጽሐፉ የምጥ መጀመሪያ እንጂ መጨረሻው አይደለም፡፡ “አለ ገና”ን የሚያዘፍን ብዙ ክስተት በግምባር እንደሚከሰት እንጠብቃለን፡፡ እኛ ግን ራሳችንን ለመጠበቅ እንትጋ፡፡
የሀገራችን ስደተኛ እየደረሰበት ያለውን መከራና ስቃይ በቃላት ለመግለጽ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሰሞኑን እንኳ በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ የደረሰብን ውርደትና እንግልት በጣም የተለዬ ነው፡፡ በእንግዳ ጠሎቹ የደቡብ አፍሪካ ወመኔዎች የተቀጣጠለው የይውጡልን ዐመጽ ብዙ ጉዳት አስከትሏል፡፡ በሊቢያ የተከሰተው የአይሲስ አንገት ቆረጣም ለኢትዮጵያውያን በተለይ በአደጋው ግዝፈት በዓይነቱ የመጀመሪያ ነው፡፡ በየመን ያሉ ወገኖቻችን እየደረሰባቸው የሚገኘው መከራም እንዲሁ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፡፡ በጥቅሉ በመላው ዓለም በሚኖሩ በርካታ ዕድለቢስ ወገኖቻችን ላይ ተነግሮ የማያልቅ ብዙ መከራና ስቃይ እየደረሰ እንደሆነ እንሰማለን፡፡ አንድዬ በምሕረቱ ይጎብኘን እንጂ በኢትዮጵያውያን ላይ እየወረደ ያለው የመከራ ዶፍ ከብዷል፡፡
ለመብታችን ተከራካሪና ዋስ ጠበቃ የሚሆን መንግሥት የሌለን በመሆናችን የኛ ችግር ከሌሎች ሀገሮች ሕዝቦች ችግር አንጻር ሲታይ ዕጥፍ ድርብ ነው፡፡ የኞች ጉዶች ከሀገሩ የሚወጣ ሁሉ እነሱን የሚቃወምና የሚጠላ ስለሚመስላቸው በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጸም ማናቸውም ስቃይና ሞት አይሰማቸውም ብቻ ሣይሆን እንዲያውም ቢጠየቁ ስፖንሰር ከማድረግ የሚመለሱ አይመስለኝም፡፡ በአንድ በኩል እነዚህ ጉዶች ያሳዝኑኛል፡፡ አእምሯቸውን አቶ ክፋት የተባለ ረቂቅ ፍጡር ግዘፍ ነስቶ በሊዝ ሣይከራየው አልቀረም፡፡ እንጂ ኢትዮጵያን በኢትዮጵያዊነት ስም የሚገዛ ኃይል ካልታመመ በስተቀር ቢያንስ ለስሙ ሲል እንኳን – እንዲያው ለፖለቲካው ቅርጻዊ ማማር ሲባል – አንዳንዴ “እየተሳሳተ”ም ቢሆን – “ዜጎቻችንን የመታደግ ኃላፊነት ስላለብን አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን” ቢል ስንት ነገር ባተረፈበት ነበር፡፡ እነዚህ ወያኔዎች ግን ነገረ ሥራቸው ሁሉ በእልኽ የሚነዳ ስለሆነ የሚጠላቸውንና እውነተኛ ምርጫ ኖሮ የማይመርጣቸውን ከሚመርጣቸው እኩል የማየት፣ እኩል የማስተዳደር፣ እኩል የመዳኘት… ግዴታ እንዳለባቸውና በሕገ ወጥም ይሁን በሕጋዊ መንገድ ከሀገር የወጣን ዜጋ ችግር በእኩል ደረጃ መቅረፍ ያለባቸው መሆኑን እንኳን ባለመረዳት የመጨረሻውን የድንቁርና መንገድ መከተልን መርጠዋል፤ ለምሳሌ በሠለጠነው ዓለም እንበል በአሜሪካ ዴሞክራቶች ሲያሸንፉ ሪፐብሊካኖችን አያስሯቸውም፤ አይገድሏቸውምም፡፡ ይልቁንም አለመምረጥ መብት መሆኑን ስለሚረዱ ከመረጧቸው ዜጎች እኩል መብታቸውን ጠብቀው ዙራቸውን እስኪጨርሱ ድረስ ሁሉንም በእኩል ያስተዳድራሉ፡፡ ሀገሪቱም የእኩል ስለሆነች ማንም ማንንም ከሥልጣንም ሆነ ከሀብት አይነጥልም፡፡
እነዚህ ወያኔዎች ታዲያ ከየትኛው ሰማይ መጡብን? ተግባራቸው ሁሉ እንደሕጻን ነው፤ በነዚህ በመገዛታችን በጣም አዝናለሁ፡፡ በዚህ ታላቅ የቴክሎጂና “የሰው ልጅ ሥልጣኔ” ዘመን እንዴት በሕጻናት እንገዛለን? በትንሹም በትልቁም የሚያኮርፍና ለምቦጩን የሚጥል አንድም ህጻን ነው፤ አለበለዚያም አእምሮው ዘገምተኛ የሆነና ዕድሜውን ባላገናዘበ ሁኔታ በዝቅተኛ ደረጃ የሚያስብ በሽተኛ ነው፡፡ እነዚህ ወያኔዎች ግን … አይ፣ በውነት አሁንስ ከምር ቃላት አጠሩኝ፡፡(ዘግይቶ የሰማሁት መረጃ፡- የወያኔው መንግሥት አሁን ቆይቶም ቢሆን ሊቢያ ውስጥ የታረዱ ወገኖቻንን በሚመለከት ብሔራዊ የሀዘን ቀን እንዳወጀ ማታ ሰዎች ሲያወሩ ሰማሁ፡፡ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ ምንም ወጪ ላያወጡበት እንዲህ ያለ የ“ያገባኛል፣ የኔው ጉዳይ ነው” የሚል ስሜትን የሚያስላልፍ መንግሥታዊ መልእክት ለምን እንደማያወጡ ሁሌም ይገርመኛል፡፡ የመካሪ ማጣት ወይም በወሰንየለሽ የሀገርና የዜጎች ጥላቻ ታውረው እንጂ ይህ ዓይነቱ ዓለም አቀፍ የመንግሥታት ቀዳሚና በጣም ቀላል ተግባር ምን ይጎዳቸው ነበር?)
ከፍ ሲል እንደተገለጸው በየሀገሩ ለቁጥር የሚያታክት ብዙ ፍዳ እየቆጠርን ነው፡፡ ለመከራ የጣፈን እኛን ኢትዮጵያውያንን ብቻ እስኪመስል ድረስ በተለይ ላለፉት 40 ዓመታት በኛ ላይ የማይደርስ ግፍና በደል የለም፡፡ ይህ ግፍና በደል ደግሞ በቤትም በደጅም ነው፡፡ ይህኛው ከዚያኛው ወይም ያኛው ከዚህኛው በማይተናነስ ሁኔታ በሁሉም ረገድ አበሳችን በዝቷል፡፡ የአንዱ መከራችን ቁስል ሳይጠግና ሳንረሳው ሌላው ይተካል፡፡ በቅርቡ እንኳን በሳዑዲ ዐረቢያና በሌሎች የአካባቢው የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ሀገራት በወገኖቻን ላይ የደረሰው የውጡልን እንግልትና ኢሰብኣዊ ጭፍጨፋ፣ በየመንና በሊቢያ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ አሁንም ድረስ እየደረሰባቸው የሚገኘው መፈጠርን የሚያስረግም ስቃይ፣ “ከወያኔ የሚብስ የለም” ከሚል አጠቃላይ እውነት በመነሣት ሊደርስባቸው የሚችለውን ውጣ ውረድ ለማሰብ ባለመፈለግ የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ እግር ባወጣ ሲሰደዱ በባሕርና በየብስ የሚያጋጥማቸው በእንስሳት የመበላትና በዐረመኔ “ሰዎች” የውስጥ አካላቸውን ለመለዋወጫነት የመቦጥቦጥ አደጋ፣ በሚሠሩባቸው ቦታዎች ከፎቅ መወርወርና ደሞዛቸውን እየተከለከሉ በዝጉብኝ የስቃይ ሕይወት ደም ማንባት ወዘተ. የሚያሳየን ብቸኛ ነገር የመከራ ደብዳቤያችንን የሚቀድ አንዲት ራሔልና አንድ ሙሤ ማጣታችንን ነው፡፡ የወላድ ማሕጸን ጨከነ፡፡
እኛ አሁን በወያኔ ፈርዖኖችና ናቡከደነፆሮች እየተሰቃየን እንደምንገኘው የጥንት እስራኤላውያንም በሀገረ ግብጽ በዚያን ጊዜዎቹ የግብጽ ፈርዖኖች ተገድደው ፒራሚዶቻቸውና ሌሎች ሕንፃዎቻቸው ሲገነቡ ጭቃ ያቦኩና ብዙ የጉልበት ሥራዎችን ይሠሩ ነበር፡፡ ያኔ ጭቃ ከሚያቦኩት ሰዎች መካከል አንዷ የነበረችው ራሔል የምትባል እስራኤላዊት ምጧ ይመጣና “ምጤ መጣ” ብላ ጭቃውን ለሚያስቦካቸው ፈርዖናዊ ዐለቃ(ካቦ) በፈራ ተባ ትገልጽለታለች፡፡ በጭካኔው ልክ እንደወያኔ ወደር የማይገኝለት ጭቃ አስረጋጭ ዐለቃም በትዕቢት “እዚያው ውለጂውና እርገጪው – ጭቃውን ያጠነክረዋል!” ይላታል፡፡ ያኔ ራሔል አምርራ ታለቅሳለች፡፡ የራሔል እምባ በጽርሃ አርያም ይሰማል፡፡
ያ እንባ ገነትን ከሲዖል ያንቀጠቅጥና ፈጣሪን ክፉኛ ያስቆጣል፡፡ ያኔም የፈርዖኖች ግፍ ጽዋውን ሞልቶ ኖሮ ያ የራሔል እንባ እግዚአብሔር ሙሤን እንዲያስነሣ የወዲያው ምክንያት ይሆናል፡፡ ሙሤም በፈጣሪው ተዓምራዊ ረድኤት ታግዞ ባሕረ ኤርትራን በማቋረጥ ወደ ቃልኪዳኒቱ ምድር ወደከንዓን ሕዝቡን ይዞ ወደነፃነት አምባ ያመራል፡፡ እንግዲህ ካልረሳሁት እንዲህ የመሰለ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ አለ፤ እንደሚመስለኝም ታዲያ አንዲት አምርራ የምታለቅስ ራሔልና አንድ ነፃ ሊያወጣን የሚችል ሙሤ ከ90 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል ልናገኝ አለመቻላችን የኃጢኣታችን ቁልል ከግዙፉ የኤቨረስት ተራራ የሚብስ መሆኑን ያመላክታል ወደሚል ድምዳሜ ደርሻለሁ፡፡ ችግራችን እንዳይሰማን፣ የደደረ ልብም እንዲኖረን፣ የጭካኔ አገዛዝን አሜን ብለን እንድንቀበል፣ በአካል እንጂ በመንፈስ እንዳንኖር ያደረገንን ልዩ ምትሃታዊ ኃይል ባውቅ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ብዛታችን ለመለያየታችን፣ ዕውቀታችን ለግል ብልጽግናና ዝናችን፣ የሚደርስብን ግፍና በደል ለመበታተናችን መደላድል እየሆኑ እስካሁን ለጠላት እንደተመቻቸን አለን፡፡ ምን ዓይነት ውርጅብኝ ነው? አመክሮ የሌለው ዕድሜ ይፍታህ የሰቆቃ ሕይወት!!
በበኩሌ እግዚአብሔር ለሰዎች ሁሉንም ነገር አያደርግም (ብዬ ማመን እፈልጋለሁ)፡፡ ይህች ዓለም በሰዎች የምትመራና ከእግዚአብሔር ወይም ከፈጣሪ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ነፃ የሆነች ትመስለኛለች፡፡ ስለሆነም የመኖርም ሆነ ያለመኖር መብቱ በእጃችን ነው – የመጨቆንና የመጨቆንም እንዲሁ፡፡ አፍኣዊውንና ዘወትር በ“አንተ ታውቃለህ” የታጀበውን የብዙዎቻችንን አባባል ለአፍታ ያህል ሆን ብዬ ልርሣውና ብዙ መብቶች እንዳሉን የሚሰማኝ መሆኔን ባልተለመደ ግልጽነት ልጠቁም እፈልጋለሁ፡፡ እንደልማድ ሆኖብን ብዙዎቻችን ስለማንኛውም ጥቃቅን ነገር ሁሉ ፈጣሪን አላግባብ እንወቅሳለን ወይም እናወድሳለን(በውዳሤው እንኳን ቅዋሜ እንዲኖረኝ አልፈልግም)፡፡ ይሁንና አንዳንዴ ሳስበው እግዚአብሔር በያንዳንዱ ደቃቃ የዕለት ተለት ሕይወታችንና እንቅስቃሴያችን ውስጥ በአላስፈላጊ ሁኔታ ጣልቃ የሚገባና በበጎም ሆነ በክፉ ጎኑ ተፅዕኖ የሚያደርግ አይመስለኝም፤ እንዲህ የምለው ታዲያ የኔን እውነት ለመግለጽ እንጂ ኢ-አማኒ ሆኜ እንዳይመስላችሁ፤ ከእግዚአብሔር ውጪ ሕይወት የለኝምና፡፡ በምድር ስንኖር ከፈጣሪ የተሰጠንን አንጻራዊ ነፃነታችንን እየረሳን ፈጣሪን በትንሹም በትልቁም ከመውቀስ ብንቆጠብ ደስ የሚለኝ መሆኔን በዚህ አጋጣሚ ባልጠቁም ደግሞ በጣም ቅር ይለኛል፡፡ ነፃነት ስላለን እኮ ነው ከራሱ ትዕዛዛት ውጪ እየተጓዝን የዓለምን ቅርጽ እንዲህ ቅጥ የለሽ ያደረግናት፡፡ እንጂ እንደርሱ ፍላጎት ቢሆንማ ኖሮ ገነትን ባስመሰልናት ነበር – ኧረ እንዲያውም ቀድሞ ነገር ከገነትም ባልወጣን፡፡
ለዚህ እኮ ነው የመንግሥት አካላትና አባላት ሕዝባቸውን በትክክለኛው የፍትህ መንገድ ማስተዳደር እየቻሉ ክፉውን አማራጭ በመከተል ግን በደልንና ኢፍትሃዊነትን የሚያሰፍኑትና የጦርነትንና የርሀብን ሰቆቃ “በሕዝባቸው” መሀል የሚያነግሡት፡፡ ለዚህ እኮ ነው ሰዎች በደገኛዋ ጠባብ መንገድ በመጓዝ የዓለማችንን የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል ፍትሃዊ ማድረግ ሲችሉ አንዱ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ገዢ ሌላኛው ደም መጣጭ ቢሊዮነር ሆኖ በ“አንድሽ አንባቢ አንድሽ ተርጓሚ” ዓይነት የመደጋገፊያ ቴዎድሮሳዊ ብሂል እየተሻረኩ ቢሊዮኖችን ወደርሀብና ወደበሽታ ሲነዱ የምናየው፡፡ ለዚህ እኮ ነው አንዱ በማተቡ ወይም በአቋሙ ምክንያት ብቻ አንገቱን ሲቀነጠስ ሌላው ደግሞ በደም ማፍሰስ ሰይጣናዊ ልክፍት ተመርዞ ጭንቅላታቸው ከሰውነታቸው ተቀልቶ እፊቱ በሚወድቁ ምሥኪን የዓለም ዜጎች ሲደሰት የምናየው፡፡ … ይህ እንግዲህ የምርጫ ጉዳይ ነው፤ የመብትም ጭምር፡፡ ፈጣሪ ጣልቃ ቢገባማ ኖሮ ከመነሻው ማን የማንን አንገት ሊቆርጥ ይደፍራል? ቆርጦስ ወዴት ሊያመልጥ ወይም ወዴት ሊደበቅ ይቻለዋል? ስለዚህ ኩታ በየፈርጁ እንደሚለበስ የምድርንና የሰማይን ፍርዶች አለመላው ለማዛነቅ ባንሞክር የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ብዙና ብዙ ሥልጣንና ኃይል ተሰጥቶናልና ያንን በአወንታዊ መንገድ ብንጠቀምበት ሀብታምም ድሃም፣ ገዳይም ሟችም፣ ቸርም ንፉግም ሣኖር በቅጡ መኖር በቻልን ነበር – ምኞት ነው – ምኞት ደግሞ አይከለከልም፡፡
የሆነው ሁሉ ቢሆን ግን ለማንኛውም በጎም ሆነ ክፉ ምድራዊ ተግባራችን የዞረ ድምር መኖሩን ማስታወስ የሚገባኝ አይመስለኝም፤ የኅሊና መታወር ካልገጠመው በስተቀር ማንም የዓለም ዜጋ በ“ለለአሃዱ በበምግባሩ” የተፈጥሮና የአምላክ የማይሻር ሕግ መሠረት ሁሉም የድካሙን ውጤት መሰብሰብ እንዲችል የዘሩትን ማጨድ መኖሩን የሚዘነጋ ሰው ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ ዕብሪትና ትምክህት ያላቸውን አሉታዊ ሚና ግን አልረሳም፡፡ ዐይነ ኅሊናችን በደንብ እንዳያይ እነዚህ ነገሮች ሞራ ይጥሉበታል፡፡
እንደመፍትሔ የምጠቁመው መብታችንን ማወቁና በአግባቡ መጠቀሙ ተገቢ መሆኑን ነው፡፡ ለአብነት እኔ አሁን ያሻኝን ያህል ሰው መግደል እችል ይሆናል – ምናልባትም እስክገደል ወይም ሕግ አስከባሪ ኖሮ በቁጥጥር ሥር እስክውል ድረስ፤ አሁን የሰውን ሀብት ካለላብና ካለ ልፋት መበዝበዝ እችል ይሆናል፤ አሁን ሰማይና ምድር ሊሰሙት የሚሰቀጥጣቸው ወንጀል መሥራት እችል ይሆናል፤ አሁን በዘረኝነት ክፉ ደዌ ተመትቼ ወያኔ እንደሚሠራው ያለ እጅግ አስነዋሪ ተግባር እፈጽም ይሆናል፤ አሁን በንግድ ስም ወይም ለከት ባጣ የሙስና ሰንሰለት ከቢጤዎቼ ጋር በማበር ሕዝቡን እስከመቅኒው ድረስ ዘልቄ ጥሪቱን እቦጠቡጥ ይሆናል፤ አሁን ከመሰሎቼ ጋር እየተመሣጠርኩ በኑሮ ውድነት ጅራፍ አጥንቱ እስኪፋቅ ድረስ ማኅበረሰቡን እሸነቁጥ ይሆናል፤ አሁንና ዛሬ በለስ ቀንቶኝ … ብዙና ብዙ ሰቅጣጭ ዕኩይ ተግባራትን ብቻየን ወይም ከጓደኞቼ ጋር በቡድን አከናውን ይሆናል፡ ነገር ግን ይህን ሁሉ የማደርገው ጤናማ ኅሊናየን ሆዴ ውሥጥ ሸጉጬ፣ ጤናማ አስተሳሰብን ክጄና ሃይማኖቴንም ወደገንዘብ ለውጬ ለሥጋዊ ፍላጎቴ ብቻ በማደር መሆኑን መዘንጋት አይገባኝም፤ ክፋትን መፈጸም ደግሞ ችግሩ መዳረሻው ላይ እንጂ መነሻውና ግስጋሴው አልጋ ባልጋ የሆነ ጣፋጭ ነገር ነው፡፡ በዚህ የክፋት መንገድ መጓዝ ከፈለግሁ ደግሞ ለዚህ ዓይነቱ ድውይ አመለካከቴ ስኬታማነት አብሮኝ የሚቆምና የሚያግዘኝ ከጨለማው ገዢ ጠንካራ ሠራዊት እንደሚላክልኝ መካድ ብልህነት አይመስለኝም፡፡ ምርጫየን ለማስፈጸምና ሕልሜን እውን ለማድረግ የምመኘው ኃይል ከ“ምርጫ ቦርድ” ይላክልኛል፡፡ ሰው በወደደው ይቆርባል ወንድሜ፡፡
ቢሆንም ይህ ኃይል ለዘላለሙ ከኔ ጋር እንደማይኖር መርሳት የለብኝም፡፡ ዕድሜየ ሲገፋ ወይም የዕውቀትና የጥበብ ጭላንጭል ወደ አንጎሌ መግባት ሲጀምር አንድ ቀን ይህ የጨለማ ኃይል ለኅሊና ጸጸትና ለሥነ ልቦናዊ ቀውስ አጋልጦኝ ዘወር እንደሚል መረዳት የኔው ድርሻ ነው፡፡ ይህን መሰሉን አደገኛ የነገሮች ግጥምጥሞሽም መጠበቅና አስቀድሞ መፍራትም ተገቢ ነው፡፡ ሁልጊዜ ጌትነት የለም፤ እንደወጡ መቅረት የለም – በወጡበት መውረድ ወይም ከላይ ተነስቶ በአንዴ ወደመሬት መፈጥፈጥም አለ፡፡ ያለንን መብት ሁሉ በተለይም ከክፋት ድርጊቶች አንጻር አጣጥቦ እስከ‹ፑንት› መጠቀሙ የሚያስከትለውን የኋላ ዳፋ ማወቁ የመጨረሻውን የነገሮች አካሄድ እንድንገነዘብ ያደርጋልና የሰውን ልጅ ልደት፣ ዕድገትና ሞት ሂደታዊ ዑደትን ማጤን ይገባል፤ ቀድሞ ነገር የሰው ልጅ ዕድሜ ያን ያህል የሚያጓጓ ርዝማኔ ኖሮት ነፍስንና ሥጋን ለሚያቆራርጥ ወንጀሎች ሊዳርገን አይገባም፤ የግንዛቤ ዕጥረት እንጂ ሕይወት በጣም አጭር ናት – እንኳንስ ክፉ ነገር ጥሩ ነገር ለመሥራትም የማትበቃን በጣም ቅጽበታዊ ናት፡፡ እንደእሳት ራት እየዘለልን የምንገባበት የሀብት፣ የሥልጣንና የወሲብ ቱማታ ሁሉ በመጨረሻው ውድ ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችል ከወዲሁ መገንዘብ ይገባናል፡፡ የብዙ ነገሮች የመጨረሻ ዕጣ ፋንታ ከነዚህ ሦስት በጣም ጠቃሚ ነገር ግን በአግባብ ካልተያዙ እጅግ ጎጂ ነገሮች ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነውና! ….
እናም ለወረሩን ኆልቁ መሣፍርት የሌላቸው ችግሮች መፍትሔው የሚመስለኝ በተደጋጋሚ እንደሚባለው ወደኅሊናችን መመለስ ነው፤ ልቅ ፍላጎትን መገደብ፣ አስተዋይነትን ገንዘብ ማድረግ፣ ሞትን አለመርሳት፣ እንደሰውም ለማሰብ መጣር ፡፡ በዕውር ድምብር መጓዝ ለባሰ ችግር ያጋልጣል፤ በእልኽ መጓዝ ለባሰ መጋጋጥ ይዳርጋል፤ በማይምነት ፈረስ መጋለብ የግልና የሀገር ውድመትን ያፋጥናል፤ በቂም በቀል መጓዝ የበለጠ የከራማ(የኅሊና) መቆሸሽን ያስከትላል፤ በጥላቻ መታወር የኅሊና ሠሌዳን እያሳደፈ የባሰ ክፉ ሥራ እንድንሠራ ያደርጋል፤ በሀብት ፍቅር መክነፍ – በሥልጣን ሱስ ማበድ – በልቅ የወሲብ ፍትወት ታውሮ ካገኙት ጋር ሁሉ መሤሰን ለግለሰብ ቀርቶ ለሀገር ጠንቅ ነው፡፡ የተያያዝኩት የሃይማኖት ስብከት አይደለም፤ በደንብ ተረዱልኝ፡፡ ለምሳሌ አንድ የሕዝብ ሰው ነኝ የሚል ሰው በነዚህ ነገሮች ላይ ልዩ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ እንደአስረጂ ያህል አንድ የሕዝብ ሰው ሌላውን ትተን በፆታዊ ግንኙነቱ ለሌሎች ዜጎች አብነት ወይም አርአያ ሆኖ ካልተገኘና እንደካባ ለባሹ አቶ እንቶኔ ከልጅ ልጆቹ ጋር በግልጽ ሲወሳልት የሚታይ ከሆነ ባህልንና ሃይማኖታዊ ዕሤቶችን ከማጥፋቱም በተጨማሪ አዲሱን ትውልድ ሞራለቢስ ከማድረግ አንጻር የሚጫወተውን አሉታዊ ጎን መገመት አይቸግርም፡፡ ወጣቱ ትውልድ አርአያዎችን(Iconic figures) ማየትና እነሱን መከተል ይኖርበታል፤ አርአያነት ደግሞ ጎደሎ ሊሆን አይጠበቅበትም፡፡ በመልካም ሥነ ምግባር፣ በመልካም የትዳር ሰውነት፣ በመልካም መስተጋብር፣ በመልካም ሃይማኖታዊ ትውፊት፣ በመልካም ማኅበራዊ ተምሳሌትነት፣ በመልካም ባህልና ወግ፣ በመልካም የልጅ አስተዳደግ፣ በአመርቂ የትምህርት ስኬት፣ ታማኝነትንና ሃቀኝነትን መሠረት ባደረገ ውጤታማ ግለሰባዊ ሕይወት… በተለይ ለወጣቱ አርአያ የሚሆኑንን ሰዎች ማግኘት ይኖርብናል – ከቁጣ የራቁ፣ ትዕግሥትን የተላበሱ፣ ተደማጭና ስንጣላ አስታራቂ የሕዝብ ሰዎችን ማግኘትና ማሳደግም ይገባናል፤ በሃይማኖቱ ረገድም እንዲሁ በሕዝብ ዘንድ የሚከበሩ ተሰሚና ንግግራቸው ከምግባራቸው የሚገጥም አባቶች ሊኖሩን ይገባል፡፡ ከነዚህ ማኅበረሰብኣዊ መልካም ገጽታዎች በራቀ ሁኔታ ውስልትናና ሥርቆት የዕድገት መሰላል መሆናቸውን እየታዘበ የሚያድግ ወጣት የሀገር ፀር እንጂ የልማትና የዕድገት አንቀሳቃሽ አወንታዊ ኃይል ሊሆን አይችልም፡፡ ያልዘሩት አይበቅልም፤ በበጋ ያልሰበሰቡት እህል በክረምት ቢፈልጉት ባዶ ማጀትን እንጂ የሞላ ሞሰብን አያገኙም፡፡
ከዚህ መሠረታዊ ጠቃሚ ነጥብ አኳያ በአሁኑ ወቅት ብዙ አሳሳቢ ነገር ይታየኛል፡፡ በወያኔ የፈራረሱ ማኅበረሰብኣዊ ድልድዮችንና የተበጣጠሱ የሃይማኖትና የባህል ክሮችን ለመቀጠል እንዲቻል ከነፃነቱ ትግል ባልተናነሰ እንዲያውም በበለጠ ሁኔታ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ሰው ልብስ ለብሶና ቆሞ በመሄዱ ብቻ ሰው እንደሆነ ያህል ሊቆጠር የሚገባው አይመስለኝም፤ ከቁጥር አኳያም ቢሆን እንደዚሁ ነው፡፡ ጥራት ብዛትን እንደሚበልጥ መርሳት አይገባም፡፡ የሰው ሰውነት መለኪያዎች ብዙ ናቸው፡፡
የቤት ሥራችን እልህ አስጨራሽ መሆኑ በበኩሌ ይታወቀኛል፤ ወያኔ በ24 ዓመታት ውስጥ እያለን እንደሌለን ያህል እንዲሰማንና እንድንሆንም ጭምር አስገድዶናል፡፡ በትምህርት ዜሮ፣ በባህል ዜሮ፣ በሞራል ዜሮ፣ በሃይማኖት ዜሮ፣ በአስተሳሰብ ዜሮ፣ … በብዙ ነገሮች ዜሮ አድርጎን ሲያበቃ ራሱም ዜሮ ሆኖ ወደታሪክ መዝገብነት ሊቀየር ዳር ዳር እያለ ነው ወያኔ – ስድስተኛው የስሜት ሕዋሴ ሹክ እንደሚለኝ ከሆነ፡፡ በሚገባ የማውቀውንና የምታውቁትን ነው የምናገረው – እናም ባለሽጉጥ ፓትርያርክና ጫት ቃሚ ቀዳሽ ካህን ከማምረት የበለጠ ሥርዓታዊ ብልሹነትና ወንጀለኛነት አይገኝም፤ የግል ጥቅምን ለማሳደድ ሲባል በኪዮስኮች መሀል ሣይቀር የኪራይ “ቤተ ክርስቲያኖችን” እንደአሸን ከማፍላትና በራስ ሕይወት በተግባር ሊታይ በማይችል አስመሳይ ስብከት ሞኛሞኝ ተከታይን ከማደንቆርና ቅኝቱና ይዘቱ የማን መሆኑ በማይታወቅ ስሜት ቆንጣጭ የ“መዝሙር” ዳንኪራ ጮቤ ከማስረገጥ የበለጠ የሞራልና የሃይማኖት ኪሣራ የለም፡፡ ከአንጀት ለክርስቶስ መንግሥት ቀናኢ ከመሆን አንጻር ሣይሆን “የዚህ አካባቢ ሕዝብ ይህን ዓይነት ጽላት ይፈልጋልና ወደዚያው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እንዳይሄድብን እዚሁ እንያዘው” ከሚል የምዕመን ሽሚያ በመነሣት በውድቅት የሚገነቡ የጨረቃ አብያተ ክርስቲያናትን ስናይ በርግጥም የሃይማኖት መላላትና ከፈጣሪ ይልቅ የገንዘብ መንገሥ እንደሚስተዋልበት ቀድሞ የተነገረለትን የስምንተኛውን ሺህ ዘመን መባት እንገነዘባለን፡፡ “በዚህ ዘመን ባልተፈጠርኩ ኖሮ” የሚያስብሉ እጅግ ብዙ የሞራል ዝቅጠቶች በሀገራችን ከላይ እስከታች ይታያሉ፡፡ በጥቅሉ የውድቀታችንን ልክ በምንም ዓይነት መሣሪያ ለክተን ማወቅ በማንችልበት ከፍተኛ የኪሣራ አዘቅት ውስጥ እንገኛለን፡፡ እግዚአብሔር ይሁነን፡፡
እንደ እውነቱ ታዲያ ጭንቅላትን በዕውቀትና በግንዛቤ ከማበልጸግ ይልቅ በዓለማዊ ብልጭልጭ ነገር ብቻ እንዲማረክ ማድረግ የሕይወትን ትርጉም ያሳጣል፤ ከቁሣዊ አስተሳሰብ በአፋጣኝ መውጣትና ወደተሻለ የአእምሮ ዕድገት መግባት ይጠበቅብናል፡፡ መለወጥ አለብን፡፡ አካሄዳችንን መቀየር አለብን፡፡ ብዙዎቻችን ከምንንቦራጨቅበት ዝቅተኛ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ደረጃ ወጥተን በጋርዮሻዊ ጤናማ አስተሳሰብ በመመራት ለጋራ ኅልውና መትጋት ይገባናል፡፡ ሌኒን እንዳለው (ያላለው ነገር የለም ቢባልም) “መማር.፣ መማር፣ አሁንም መማር” ነውና እኛም በተመሣሣይ ቅኝት “ማንበብ፣ ማንበብ፣ አሁንም ማንበብ” የሚል መመሪያ ቀርጸን በጠቃሚና አእምሮኣችንን በአወንታዊ መንገድ ሊመግቡ፣ ሊያበለጽጉና ሊያሳድጉ በሚችሉ ዕውቀቶች ልንገነባው ያስፈልገናል፡፡ ጭንቀታችን ገንዘብና ሥልጣን በማግኘቱ ዙሪያ ብቻ ሣይሆን መንፈሣዊና ኅሊናዊ ልዕልና ሊያስገኙልን በሚችሉ የስብዕና የዕድገት ትልሞች ላይም ትኩረት ማድረግ አለብን፡፡ የሆድ ነገር ጠፊ ነው፤ የመንፈስ፣ የኅሊናና የነፍስ ጉዳይ ግን ዘመን ተሻጋሪና የማይሞትም ነው፡፡ ዕብለትንና በሀሰት መመሥከርን፣ ጉረኝነትንና እዩኝ እዩኝ ባይነትን፣ ግልብነትንና ተመፃዳቂነትን፣ ራስ ወዳድነትንና አስመሳይነትን፣ ዘረኝነትንና በትውውቅ፣ በዘመድ አዝማድና በጎጥ ልጅነት አድልዖ መሥራትን፣ … ልንጠየፋቸው ይገባል፡፡ በምትካቸው ሃቀኝነትን፣ ለራስ ኅሊና ጭምር ለሀገርና ለወገን ታማኝነትን፣ ፍትሃዊነትን፣ ቅንነትንና ቅን ፍርድን፣ መተዛዘንን፣ አስተዋይነትንና ጥበበኝነትን፣ ከዘውግ ባለፈ ብሔራዊ የጋራ ማንነትን፣ ሰብኣዊነትን፣ የኅሊናን ዳኝነት ጥሶ ለምንም ዓይነት ጠያፍ ነገርና ለምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ የማይንበረከክና ለድርድር የማይቀርብ ንጹሕ ስብዕናን፣ … መላበስ ይገባናል፡፡ የችግሮቻችን መባቀያ በአብዛኛው እዚህ አካባቢ የምጠቃቅሳቸው ነገሮች ይመስሉኛል፤ በነዚህ ነገሮች የመሸነፋችን አስቀያሚ ዕጣ ነው አሁን ለምንገኝባቸው ዝብርቅርቅና ውስብስብ ችግሮች ያጋለጠን፡፡ በነዚህ ነገሮች ዙሪያ ብዙ የበቁ “ኢንቬስተሮች” ያስፈልጉናል፡፡ እንደምታዘበው በቁም የጠፋን ሆነናል፤ አብዛኞቻችን በፍርሀትና በራስ ወዳድነት ወጥመዶች ተቀይደናል፡፡ ቄሱም ሆነ ሼሁ ለሥጋው አድልቶ ጭቆናና በደልን በቤተ አምልኮ ስብከቱም ሆነ በአስተምህሮው ተስቶት እንኳን አያነሣም፡፡ የፍርሀት ድባብ በየቦታው ነግሦአል፤ ምናባዊ ሞቱን ወድዶና ፈቅዶ እንደተቀበለ የምናውቅለት መነኩሴ ሣይቀር ሞትና እስርን በመፍራት ስለሕዝብ መበደል በአደባባይ ትንፍሽ ሲል አይደመጥም – መርፌ ቢወድቅ የትም ሆነው የሚሰሙበት አስደንጋጭ የፀጥታ ዘመን በሀገራችን ተከስቷል! ወያኔዎች ከምንጊዜውም በላይ በርትተዋል፤ የኋላ የኋላውን እንጃ እንጂ ለጊዜው የተሣካላቸውም ይመስላሉ፡፡ የሁሉንም አፍ አዘግተዋል፡፡ የዘጠና ሚሊዮን ሕዝብ አንደበት ማዘጋት የቀላል ኢንቬስትመንት ውጤት አይመስለኝም፡፡
በሥጋዊ የሀብት ክምችትና የሕንፃና አስፋልት መንገዶች ግንባታ የማይናቅ እመርታ ብናሳይም በመንፈስ ድቀት ግን በዓለም አንደኞች ሣንሆን የምንቀር አይመስለኝም፡፡ ይህም ሆን ተብሎ በታወጀብን ሀገርንና ሕዝብን የማውደም አጠቃላይ ጦርነት የተነሣ ነው ማለት እንችላለን – ምክንያቱም በመንፈስና በኅሊና በነፍስም የተራቆተን ሕዝብ በቀላሉ መግዛትና እንደከብት መንዳት እንደሚቻል ትላልቆቹና ትናንሾቹ ጠላቶቻችን የሃይማኖት ያህል ያምኑበታልና ይህን ሕዝብን የሚያጫጫ ዕኩይ ዓላማ በመግዣ መሣሪያነት እንደዋና መርኅ ይከተሉታል፡፡ በነገራችን ላይ ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ መጻፉ አሰልቺ ነው እንጂ የወያኔን ዴሞክራሲያዊነትና አርበኞች ግንቦት ሰባትን ጨምሮ ሁሉም ተቃዋሚዎች አሸባሪዎች እንደሆኑ ቅንጣት ሣታፍር የተናገረቺው ያቺ አሜሪካዊት ባለሥልጣን በቁስላችን ምን ዓይነት መርዝ የተለወሰ ጨው እንደነሰነሰች የበኩሌን መተንፈስ ፈልጌ ነበር፡፡ እውነተኛ ዴሞክራሲ አለ በሚባልበት ሀገር የተወለደና አድጎ ለሥራ የደረሰ ሰው ዓለም በግልጽ የሚያውቀውን አምባገነናዊ የወያኔ ሥርዓት እስከዚህን ወርዶ መኳሸት ጥቅሙ ምን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ በኛ ላይ ጦሩን የማይሰብቅና ስድ አንደበቱን የማይከፍት የለም ማለት ነው፡፡ የወደቀ ግን ምሣር ይበዛበታል፡፡ ሁሉም የክፋት ጦሮች በኢትዮጵያ ላይ አነጣጥረዋል፤ በጣም ያሳዝናል፡፡
እኛም እንደፈለጉ የሚጋልቡን የምንመቻቸው መጋዣዎች ሆነናል፡፡ ምርጫችን ስደትና ሙስና እንጂ ከዚያ የተሻለ ለሁላችንም የሚሆን ነገር ለጊዜው ያገኘን አይመስልም፡፡ ደግሞም የሚገርመው አንናደድም፡፡ ካልተናደድንና እኛው ለኛው መፍትሔ ካላመጣን ደግሞ እንነዳለን እንጂ ነፃ የሚያወጣን የተለዬ ውጫዊ ኃይል አናገኝም፡፡ በቃኝ እባክህ – ምንም ሳልናገር የምጽፍበት ወረቀት በተሎ ያልቅብኛል፡፡
yiheyiseaemro@gmail.com
Average Rating