www.maledatimes.com ምሥጋና ለሾባት ፋውንዴሽን ወልደማርያም ዘገዬ (አዲስ አበባ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ምሥጋና ለሾባት ፋውንዴሽን ወልደማርያም ዘገዬ (አዲስ አበባ)

By   /   April 24, 2015  /   Comments Off on ምሥጋና ለሾባት ፋውንዴሽን ወልደማርያም ዘገዬ (አዲስ አበባ)

    Print       Email
0 0
Read Time:10 Minute, 59 Second

 

“Shoebat Foundation” የሚባል ክርስቲያኖች በአክራሪ ሙስሊሞች የሚደርስባቸውን ጥቃት እየተከታተለ የሚያጋልጥና ለመታደግም አቅሙ በፈቀደ የሚታገል ድርጅት አለ፡፡ የተቋቋመው ቀድሞ ሙስሊም በነበረና እምነቱን ወደ ክርስትና ሃይማኖት በለወጠ ሰው ነው፡፡ በፓኪስታንና አፍጋኒስታን ታሊባኖች፣ በአልቃኢዳዎች፣ በቦኮሃራም፣ በአልሻባቦችና በአይሲሶች ምሥኪን ክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸሙ ደባዎችንና ጭፍጨፋዎችን ዘወትር በድረገጹ ይዘግባል፤ የተከታይ አባላቱንና የኔ ዓይነት የሚዲያ ተከታታዮቹን ንቃተ ኅሊናም በልዩ ልዩ በሳል መጣጥፎቹና ሀተታዎቹ ለማጎልበት ይተጋል፡፡ በስሙ ገብቶ subscribe በማድረግ ተቋሙ የሚሰጠውን የሚዲያ አግልግሎት በኢሜል አካውንት በኩል በነፃ ማግኘት ይቻላል፡፡ “ሁሉን እዩ የሚበጃችሁን ግን ያዙ” ይላል መጣፉ፡፡

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን የሕይወትና የንብረት ውድመት አደጋ ተከትሎ የሰሞኑ ልቅሷችን አቅጣጫ ወደሊቢያ ዞሯል፡፡ በሊቢያ ዜጎቻችን በጭካኔ ታርደዋል፤ ወደባሕር ተጥለውየሞቱም አሉ – የአንድ ጎረቤቴ ልጅ በዚህ መልክ ሕይወቱን አጥቶ ልቅሶ ተቀምጠናል፡፡ በሠይፍ የታረዱት የታረዱበት ምክንያትና የዜግነታቸው ማንነት አራጆቹ ራሳቸው በአንደበታቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል፤ ክርስቲያንነት የመረሸናቸው ምክንያት ሲሆን በዜግነታቸው ደግሞ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ተገልጾኣል፡፡

በዚህ አሳዛኝ ክስተት ያላለቀሰ ኢትዮጵያዊ ቢኖር አንድም ክስተቱን ያልሰማ ነው፤ አለበለዚያም እንደወያኔ ያለ ለሕዝብና ለሀገር ባለው ጥላቻ ልቡ የደነደነ ድንጋይ ራስ ነው፡፡ እኔ አዲስ አበባን ታዝቤያለሁ፡፡ ብዙ ሕዝብ የራሱው የአብራኩ ክፋይ የሆኑ ልጆቹ የተገደሉበት ያህል ጨርቁን ጥሎ አልቅሷል፡፡ ወጣቱም አዛውንቱም በጣም አዝኗል፡፡ በታዘብኩት ነገር እኔም በኢትዮጵያዊነቴ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ምናልባት ለመጀመሪያ ጊዜ ኮርቻለሁ፡፡ የኩራቴ መንስዔ በሀዘን በመነጨ የተመለከትኩት የመተዛዘን መንፈስ መሆኑ ኩራቴን ማደብዘዙ ከፋ እንጂ ይህን መሳይ ትብብርና አንድነት ለሀገራዊ ነፃነትና ክብር ብናውለው ኖሮ የተሰማኝ ኩራት ምሉዕ በሆነ ነበር፡፡ ሕዝባችን ይተዛዘናል፤ ይለቃቀሳል፡፡ ወጣቱም እንዲሁ ነው፡፡ በዚህ ብሔራዊ ሀዘን በጣም ተነክቷል፡፡ ከመነካቱም የተነሣ እንደሰማሁት ካለወያኔ ፈቃድ ሠልፍ ወጥቶ እስከመገደል ደርሷል፡፡ መረጃየን ማመን ይቸግረኛል እንጂ ከአራት ያላነሱ ወጣቶች በዚሁ ሰላማዊ ሠልፍ ጠንቅ ማክሰኞ ዕለት በፌዴራል ተብዬ የወያኔ መንግሥት ቅልብ ወታደሮች በተተኮሰ ጥይት ሕይወታቸው ማለፉን በተባራሪ ሰምቻለሁ፡፡ ነገሩ እውነት ከሆነ በርግጥም ወያኔ የሚሠራውን በጭራሽ አያውቅም ማለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ዜጎችን ማጽናናት ሲገባ ተጨማሪ ግድያ ማካሄድ ከሰውነት ተራ የወጣ የለዬለት በሽተኛነት ይመስለኛል፡፡ “ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው” ይባላል፡፡ ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ በወገኖቹ መታረድ የሚሆነውን አጥቶ ሰማይ ምድር ተደፍቶበት ሳለ አጠገቡ ሆኖ ሊያጽናናው የሚገባው መንግሥት፣ ችግሩን በግምባር ቀደምትነት ሊጋራለት የሚገባው “የሕዝብ ተመራጭ መንግሥት” እንደዚያ ያለ ብልግና ፈጽሞ ከሆነ ሰማይም ምድርም ይቅር የማይሉት ትልቅ ኃጢኣትና ይሙት በቃ የሚያስፈርድ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ ወያኔዎች ጭራሽ ተስፋ ቆርጠው ጨርቃቸውን ካልጣሉ በስተቀር እንዲህ ያደርጋሉ ብዬ ማመን ይቸግረኛል፡፡ በርግጥ ፌዴራሎች ያን ወንጀል ፈጽመው ከሆነ ከአይሲስ ይልቅ የኛው መንግሥት ጭፍጨፋ ይከፋል፡፡ አንድ ሰው ምን ህል ቢያብድ እንዲህ ያለ አዋራጅ ቅሌት ውስጥ አይገባም፡፡

አይሲሶች ያን ወንጀል የሚፈጽሙት በሆነ ጣዖታዊ አምልኮት አእምሯቸው ተይዞ ነው – በዚህ ማንም በጣም እርግጠኛ ሊሆን ይገባል፡፡ በጤናቸው እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ እስልምናም እንዲህ አያዝም፡፡ በተወሰነ ደረጃ ቅ. ቁርዓንን በል ሲለኝ እቀራለሁ – በሃይማኖት ካንተ የተለዬን ሰው እረደው የሚል ጥቅስ አላየሁም ወይም ብሎም ከሆነ አልገባኝም ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከአምልኮት ጋር በተያያዘ ሊያስደስቱት የሚገባቸው የነሱው የሆነ ፈጣሪ አለ፡፡ እነዚህ ሴቴኒስቶች የሚሠሩትን እንደማያውቁ የምናምን እኛ እንጂ እነሱ አይደሉም፤ እነሱ የሚሠሩትን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ግን ምንም ማድረግ አይችሉም – በመንፈሱ ኃይል ተይዘዋል፡፡ ለመንፈሱ ገብረዋል፡፡ የገበሩትም ሁለ ነገራቸውን ነው፡፡ ነፍሳቸውንም ሥጋቸውንም ለጨለማው ጌታ ለዲያብሎስ አስገዝተዋልና ስለሚያደርጉት ክፋት ጸጸት አይሰማቸውም፡፡ በእንግሊዝኛው አጠራር there are two terms – they are called ‘obsession’ and ‘possession’. These ISIL people are then obsessed and possessed by the devil; and it’s no wonder that they behead any person who believes in other entity other than their idol whom they mistakenly call Allah. I intentionally used the word ‘mistakenly’ because I want to use the word ‘Allah’ to address the nomenclatural synonym to mean the equivalent of Christians’ ‘God’ in Islamic religion, a religion I accept as benign and harmless according to the preaching of my favorite scholar, Dr. Zakir of Peace TV. Hence, we should realize that not every Muslim is obsessed and possessed by the same evil spirit. As there are evil Christians who pretend to be Christians but act differently, likewise, to my understanding, there are also some Muslims who act against the true essence of the Holy Koran. There are millions of Muslims who condemn the evil acts of fanatic fundamentalists like ISIL and the like and again, there are many Muslims who strictly abide by the core principles of Islam; after all, Islam is meant ‘peace’. But it is a matter of interpretation and in the main a matter of satanic infiltration to religions, whether it is religion ‘X’ or “Y’, that creates cleavages. ይቅርታ ለወረት ጣልቃ ባስገባሁት ወልጋዳ እንግሊዝኛየ ብዙ ተወራጨሁ መሰለኝ፡፡ ምን ላድርግ – የጨነቀው እርጉዝ ያገባል የባሰበት እመጫት ትሉ የለም ሀበሾች? “እህሉ አንድ ዓይነት ሴቱ አሥራ ሁለት”እንዲሉ ሆኖብን ክፉኛ ተጨነቅን እኮ፡፡ ለዓለም ችግሮች መግፍኤ ሰበብ በዋናነት የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብት ቅርምት ሆኖ ሳለ ሃይማኖትና ዘርም ጣልቃ እየገቡ ያምሱን ያዙ፡፡ የሰው ዘር ወደኋላው ቢሳብና ወዳልነበረበትም እንበለው ወደነበረበት የጥንት ምሽጉ ቢሰተር ዞሮ ዞሮ ከአሁኑ የሰባት ሚሊዮን ሕዝብ ብዛቱና ከሦስት ዋና ዋና ቀለማቱ ወደ አንድና ሁለት ሰዎች የአንድ ዓይነት የቀለም ይዞታነት ነው ወርዶ የሚሸጎጠው – ወደአዳምና ሔዋን፡፡ አሁን ግን መልክዓ ምድራዊ ስፋት አንቦረቀቀንና፣ ያንንም ተከትሎ በዘመናት የመለያየት ሂደት የዘርና የቀለም ልዩነቶች ተከሰቱና፣ ከዚያም በመቀጠል የሃይማኖትና የባህል ጽንሶች ተፈልፍለው እያደጉ መጡና፣ ይህም ሳይበቃን የሥልጣኔና የኋላ ቀርነት ስንጥቃቶች አንዱን ታች ሌላውን ላይ ማኖር ጀመሩና፣ በዚህም ሳንወሰን እኛው ለኛው የፈጠርናቸው ድንበሮችና መንግሥታት የልዩነት ቀዳዳዎችን አበጅተው ሽብልቆቻቸውን ገጠገጡብንና አንድ ሊሆን የሚገባው የሰው ዘር በጥቂቱ በሁለት መቶዎች በሚቆጠሩ ሉዓላዊ ተብዬ ሀገራዊ ጎራዎች ተቧድኖ በፉክክር መጨራረሱን ተያይዞታል፡፡ የአሁኑ ግን ከምንጊዜውም ባሰ፡ ይቺ አይሲስ የሚሏት ነገር ደግሞ እንደቀልድ ብቅ ብላ አሁን አሁን የምሬቷ መጎምዘዝ ይህችን ምድር አልፎ ወደሌላኛዎቹ ዓለማትም ሳይዛመት የቀረ አይመስለኝም፡፡ በየትኛውም መለኪያ ቢታይ ሰውን ከሜዳ ተነስቶ ማረድ የበሽተኝነት እንጂ የጤናማነት ምልክት ሊሆን አይችልም፡፡ ይህን አካሄድ የሚቀበል ክርስቲያንም ይሁን ሙስሊም ወይም ሌላ ጤንነቱ እንዲመረመርና ህክምና ከተገኘም እንዲከታተል ወደሚቀርበው ሆስፒታል መወሰድ አለበት፡፡

እንግዲህ አይሲሶች የሚያደርጉትን የሚያደርጉት አምላካቸውን ለማስደሰት ነው ካልኩ ዘንዳ ወያኔዎችስ ይህን በለቀስተኛ ላይ ሳይቀር የሚፈጽሙትን ዐረመኔያዊ ድብደባና ግድያ ለማን ብለው ነው የሚፈጽሙት ብለን መጠየቅ አግባበነት አለው፡፡ እንደሚመስለኝ ወያኔዎች እንዲህ ያለ ጭካኔ የሚፈጽሙት ለሰይጣን ግብር ሣይሆን ከጥቅምና ከሥልጣን እንደተጣበቁ ዘላለማቸውን ለመቆየት ካላቸው ጽኑ ፍላጎት በመነጨ ነው፡፡ እርግጥ ነው – ክፋትን እንደባህል የሙጥኝ ብሎ የሚፈጽም ሰብኣዊ ፍጡር ሁሉ እናት ምድቡ ከሰይጣን መሆኑን መካድ አይኖርብንም፡፡ ከዚህ መሠረታዊ ነጥብ አኳያ ወያኔዎች የአጋንንት ጭፍሮች መሆናቸውን ብክድ እነሱ ራሳቸውም ታዝበው ፍርፍር ብለው የሚስቁብኝ ይመስለኛል፡፡ የሚያደርጉት ነገር ሁሉ ለጽድቅ እንዳልሆነ ያውቁታል፤ ዋጋ እንደሚያስከፍላቸውም ጭምር አስተማሪ ሣያስፈልጋቸው ከታሪክ ማኅደር ይረዱታል፡፡ ነገር ግን ሥልጣንና ሀብትን የመሰለ ግሩም ነገር በደብዳቤ ወይም በሥልክ አሜሪካና አውሮፓ ለሚገኝ ተቃዋሚ እንካልህ ብለው ሊሰጡ አይችሉምና ጠንከር ያለ ነገር መጥቶ ከመንበራቸው እስኪገፈትራቸው ድረስ ያለ የሌለ ተንኮላቸውንና ጭካኔያቸውን በመጠቀም አራት ኪሎን የሙጥኝ እንዳሉ ይቆያሉ፡፡ ከዚህ አንኳር ነጥብ ጋር በተያያዘ መገንዘብ የሚገባን ቁም ነገር በውጪ ሀገራት ሆኖ መጯጯሁ ወይም በየሀገራቱ በሚጠሩ ሰላማዊ ሰልፎች በስሜት መፎግላቱ ጊዜያዊ የሆነ ሥነ ልቦናዊ እፎይታ ያመጣ እንደሆነ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ የማያመጣ መሆኑን ነው፡፡ ወያኔዎቹ ራሳቸው እንደሚተርቱብን “ግመሎቹም ይራመዳሉ፤ ዉሾቹም ይጮሃሉ” እየተባለልን ምናልባትም እስከዓለም ፍጻሜ በዚህ የእፉኝት አገዛዝ እንዳክራለን፡፡ …

በሰሞኑ የወገኖቻችን ስቃይ ፀሐዩን መንግሥታችንን ታዝበነዋል፡፡ የዜጎቹን መብት ማስከበር ይቅርና በእሳት ቃጠሎም ይሁን በጥይትም ይሁን ወይም በሠይፍ ከተገደሉ በኋላ እንኳን ሬሣቸውን በተደጋጋሚ ሲገድላቸው ታዝበናል፡፡ የሞተ ሰው በድጋሚ አይገደልም፤ የዜግነቱን ነገር ለጊዜው እንተወውና ከሞራል፣ ከሰብኣዊነትና ከሃይማኖት አንጻር የሞተን ተራ ዜጋ እንኳንስ ምንም ጥፋት ሳይኖርበት ቢያጠፋ እንኳን ገና ሣይቀበር ሬሣው ሣሎን ውስጥ ተጋድሞ አይወቀስም – ነውር ነው፤ ለነገሩ የመንግሥታችን ሰዎች ምንም ዓይነት የሞራልም ሆነ የሃይማኖትና የሰብኣዊ ስሜት ጥፍጣፊውም የላቸውም ስለሚባል እንዲህ መናገሩ ራሱ ድንጋይ ላይ ውሃ እንደማፍሰስ ነው – ሊያውም ባልጩት ድንጋይ ላይ፡፡ በነገራችን ላይ ሞኝ አትበሉኝና ግን መንግሥት አለን እንዴ? ግዴለም – በቅርጽ ደረጃ መንግሥት አለን ብለን እንመን፡፡ ግን መሪው ማን ነው? የትስ ነው ያለውና እንዴትስ ነው የሚኖረው? “መሪ አለን – እሱም ክቡር ጠቅላይ ታዛዥ ማነው ጠቅላይ ሚኒስትር ደሳለኝ ኃይለ ማርያም ነው” ብላችሁ ታዲያ በሣቅ ጦሽ አድርጋችሁ እንዳትገድሉኝ አደራችሁን፡፡ የልጆች አባት ነኝና ሳላሳድጋቸው በሣቅ ሞቼ እንዳላስኮንናችሁ፡፡ እንደሚፈልጉት በአባትነት አንቀባርሬ ባልይዛቸውም ውዬ መግባቴ ራሱ ለነሱ ጠጋ ነው፡፡ እናሳ መሪያችን ማን ነው አላችሁኝ? አባይ ፀ.? አባይ ወ.? አቦይ? ጌታቸው አ.? ሣሞራ? ቴዎድሮስ?… ?

በበኩሌ መሪ የለንም፡፡ መለስ ከሞተ ወዲህ ርዕሰ ብሔር ሳይኖራት ሦስት ዓመታትን ለሚጠጋ ረጂም ጊዜ ያለ መሪ የቆየችና እስከመቼ በዚህ ሁኔታም ለመዝለቅ እንዳሰበች ማንም የማያውቅላት ብቸኛዋ የአፍሪካ ሀገር ኢትዮጵያ ነች – ዕድሉና መንገዱ ያላችሁ በ“ጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ” አስመዝግቡልን ይህን ጉዳችንን፡፡ ታሪክ ራሱን ደገመ – አንድም በምኒልክ አንድም በመለስ፡፡ አጤ ምኒልክም ለሰባት ዓመታት ያህል በአጥማቸው ገዝተዋል አሉ፡፡ መለስ አራት ዓመት ይቀራዋል ሰባት ለመሙላት፤ ይሠውረን፡፡ ኧሯ! ይህንን ሲያስቡትስ ይጨንቃል፡፡ ከእንግዲህ ወያኔ ስድስት ወር እንኳን ከቆየች ብዙዎቻችን ለይቶልን ጨርቃችንን የምንጥል ይመስለኛል፡፡

ለማንቻውም በአሁኑ ወቅት መሪ የለንም፡፡ ጥርጣሬየ ግን አራት አምስት የሚሆኑ የሕወሓት ቀንዳም ማለቴ ቀንደኛ አባላት ሌሊት ሌሊት በምሥጢር እየተሰበሰቡ ጅሉ ቤተ መንግሥት ጠባቂያቸው ኃ/ማርያም የሚናገረውን ንግግር የሚሰጡት ይመስለኛል፡፡ በጽሑፍና በሥልክ ከደንቆሮ ጉዳይ አስፈጻሚ ጋር በሚደረግ ያልተቋረጠ የመልእክት ምልልስ የምነመራ ብቸኛ ሕዝብም ነንና ይህም በዚያ የድንቃ ድንቅ ነገሮች መመዝገቢያ ስንክሳር የፊት ገጽ ላይ ይመዝገብልን፡፡ ይህ አሳዛኝ ሰውዬ ኢትዮጵያ ነፃ በምትወጣበት ሰዓት በመንገድ እንዴት አድርጎ እንደሚሄድ ካሁኑ ሳስበው ለራሱ አዝንለታለሁ፡፡ ኮንዶም አንዳልለው አንዳንድ ኮንዶም ልብ አግኝቶ ይፈነዳና ተጠቃሚን ጉድ ይሠራል – ስለዚህም ኮንዶምም ያምፃልና ከኃይለ ማርያም በበለጠ የራስ ማንነት መገለጫ አለው፡፡ አሻንጉሊት እንዳልለው ለዚያ ደረጃ ለመብቃትም ወግና ሥራት አለው፡፡ ለምሳሌ የራሽያው ሜድቬዴቭ የፑቲን አሻንጉሊት እንደነበር ይወራለታል – በበኩሌ እውነት ነበር፡፡ ደሳለኝ ግን ከአሻንጉሊት በታች ነው፡፡ የተሰጠውን ንግግር እንኳን አስተካክሎ መናገር የማይችልን ሰው፣ የራሱን ኅልውና በሟች ሰው ጥላ ሥር ሸጉጦ የአነጋገርን ድምፀትና የሰውነትን እንቅስቃሴ(gesture) ጭምር የመለስን ለመኮረጅ የሚጥር ሰው ለአሻንጉሊትነትም አይበቃም፡፡ ደሳለኝ መለስን ለመሆን ከተመኘና ከጣረ እኛ በደሳለኝ ውስጥ የምናገኘው መለስን ሊሆን ነው፤ ታዲያ ያኔ ደሳለኝ የት ገባ ልንል ነው? ደሳለኝ መለስ ከሆነ የሞተው ማን ነው? ኃይለማርያም ሊሆን ነው? ከየት ወዴት እንደመጣሁ ለራሴም ጠፋኝ፡፡

ሟች ወገኖቻችንን መንግሥታችን አይስደብብን፤ ሞታችንና ሞታቸው ይበቃል፡፡ በሕገወጥ መንገድ በመሄዳቸው ሀገራዊ ዜግነታቸው አይቀማም፡፡ ደግሞም በሕገወጥም ይሁን በሕጋዊ መንገድ ከወጡ ዜጎች በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ነው ሀገራችን እየተንቀሳቀሰች ያለቺው፡፡ በአዘቦቱ ቀን የስደተኞችን ወይም የዲያስፖራን ዶላር እየተጠቀሙ ችግር ሲደርስባቸው ግን ያልተገባ ነገር ማውራት ነውረኛነት ነው፡፡ በምንም መንገድ ካገሩ የወጣ ሰው በሚሄድበት ሀገር የሚገኘው የሀገሩ ኤምባሲ በሥነ ሥርዓት ተቀብሎ የማስተናገድ ግዴታ አለበት፡፡ እንደመጥፎ ዕድል ሆኖብን የኛ ኤምባሲዎች ኃላፊዎችና ሠራተኞቻቸው ከዕውቀትና ችሎታ እንዲሁም ከሀገር ፍቅር ስሜት ሣይሆን በአብዛኛው ከዘርና ከእበላ ባይነት ጋር በተያያዘ ያለአንዳች ችሎታና ዕውቀት ይመደባሉ፡፡ ሥራውን ስለማይችሉትም ብዙውን ጊዜ በሀብት ማጠራቀም ብቸኛ ልክፍት ተጠምደው ይታያሉ፤ የትም ብንሄድ ዜጎችን በቅጡ አያስተናግዱም፤ የዐይናቸው ማረፊያ ብር ነው አሉ፡፡ ዜግነት አፈር በልታለች፡፡ “በዜግነቴ… ፣በመብቴ.. ፣ በምንትሴ…” ማለት ዱሮ ቀረ፡፡ “አሁን ካለህ አለህ፣ ከሌለህ የለህም” የሚለው የጥሌ ዘፈን ተዘፍኖብህ የኤምባሲውን በር ወጥተህ ከመጨረስህ ደጁ ይጠረቀምብሃል አሉ – እኔማ እንደዋሊያ ከሀገሬ መቼ ወጥቼ አውቅና፡፡ ለማንኛውም መንግሥታችን ሟቾችን ለቀቅ ያድርግ፡፡ የይምሰል ሀዘኑም ብዙም አይረባንም፡፡ ምን ያደርግልናል? ስንተዋወቅ አንተናነቅ እኮ ነው ነገሩ፡፡ በዚህ ይገድላል – በዚያ በኩል ለሞቱ ያዘነ በማስመሰል በውሸት ደረት ያስመታል፤ ቲያትረኛ መንግሥት፡፡

ያ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተባለ ሰው ዛሬ አንጀቴን ቅቤ አጠጣው – ሲኖዶስ ተብዬው የሠራውን ነገር በማጋለጥ፡፡ ሃይማኖቱ ወያኔ ጉያ ሥር መሸጎጡን በደንብ ተረዳሁ፡፡ እርሱ ጣቶቹን ቁርጥማት አይንካብኝ እንጂ እኔ በሱ ላይ ጨምሬ የምላቹ ምንም የለኝም፡፡ የዳንኤል ጽሑፍ አሁኑኑ ከዘሀበሻ ወይም ከሌላ ድረገፅ ፈልጋችሁ አንብቡት – አያምልጣቹ፡፡ በደንብ አንብባቹ የወያኔ ሥራሥር የት ድረስ ጠልቆ እንደገባና የሃይማኖቱን መሠረት እስከምን እንዳናጋ ትረዳላቹ፡፡ አቤት የ“ቹ” መዓት! በነገራችን ላይ ይቺን አማርኛ ደሳለኝም እየረመረማት መጣ፡፡ ኦ! የአማርኛ ጉዳይ አይደለም ለካንስ – የሃሳብን ቅደም ተከተል የመለየት ችግር ይመስለኛል፡፡ ቅድም በቲያትሩ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ሲናገር ምን አለ መሰላቹ – የማስታውሰውን ያህል ልጥቀስለት አይደል? “… ችግሩ እንዲህ የተወሳሰበ ይሁን እንጂ ሕዝቦቻችን መረዳት ያለባቸው ቁም ነገር የሽብርተኝነት ችግር ዓለም አቀፍ ችግር ብቻ ሣይሆን ሀገራዊ ችግር መሆኑን ነው፡፡…” ይህ የሽብርተኝነት ችግር በኢትዮጵያ ብቻ የተወሰነ ሣይሆን የመላው ዓለም ችግር መሆኑን ለማስረዳት ነው ሰውዬው ሃሳቡን ገለባብጦ ያቀረበው – እርግጥ ነው ፣ የጻፉለት ሰዎች ናቸው የስህተቱ ባለቤቶች፤ የ “equivocally” ግሩም አጠቃቀም ባለቤት ባለቤት ጠቅላይ አሽከር ኃ/ማራም ደሳለኝ – የተማረና የተመራመረ እንደመሆኑ አስቀድሞ በማንበብ ወይም እያነበበ ሳለም ቢሆን ሊያስተካክለው ይቻለው ነበር፡፡ ይህ የሚያሳየን አንድም ሰውዬው ደደብ ነው አለዚያም ከመጋረጃ በስተጀርባ ካሉ ሥውር መሪዎቻችን ተጽፎ የሚሰጠውን ነገር ድምቡሎ ሳይጨምር ወይ ሳይቀንስ እንደመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንዳለ ለማቅረብ የሚገደድ መሆኑን ነው፡፡

ለምን ወደምሥጋናየ አልሄድምና ‹አልፋታችሁም›?

ሾባት ፋውንዴሽንን በናንተ ስም እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ፡፡ “የኛ መንግሥት” የታረዱ ወገኖቻችንን ዜግነት በማጣራት ሂደት ላይ ተወጥሮ በነበረበት ሰዓት ይህ ድረገፅ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ሚያዝያ 19 (ልክ ወንድሞቻችንና ልጆቻችን አንገታቸው በተቀላበት ዕለት) ይህን ክስተት ዘግቧል – ሊያውም ብዙዎች ሊጠቀሙበት የኮሩበትን ቃል “ሰማዕታት” ብሎ ሣይሆን “ቅዱሣን” ብሎ ነው የመስዋዕትነት ደረጃቸውን በአንድ እርከን ከፍ አድርጎ የገለጻቸው – ሲያንሳቸው ነው፤ እኔ ብሆን ገና በልምጭ ነበር ማተቤን በጥሼ የምጥለው – እንኳንስ ጎራዴ በአንገቴ ዙሪያ ተጠምዶብኝ፡፡ አዘጋገቡም ከአንጀትና ከከፍተኛ የመቆጨት ስሜት በመነሳት ነው፡፡ ከዚሁ ድረገጽ ጥቂት ነገር ላስነብባችሁና ላብቃ – ቀሪውንና ሆን ብዬ የዘለልኳቸውን እናንተው ወደዋናው ድረገጽ ገብታችሁ ልታነቡት ትችላላቹ፡፡ በየትም ሀገርና በምንም ሁኔታ የሚሞቱ ወገኖቻችንን፣ የሌሎች ሀገራት ዜጎችንም ጭምር እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማርልን፡፡ የሰው ግርድና አመሳሶ ስለሌለው እንደመንግሥታችንና እንደኦርቶዶክስ ሲኖትራካችን ማለትም ሲኖዶሳችን ሽል ምንጠራ እየገባን “ዜግነታቸው እስኪጣራ ‹ነፍስ ይማር› አንልም” አንልምና የሁሉንም ነፍስ በገነት ያኑርልን፡፡ ከምቀኝነት የጸዳ መንግሥትና የሃይማኖት መሪዎችን ደግሞ ይስጠን፡፡ ምቀኝነት ካልሆነ ታዲያ አንድ ሲኖዶስን ያህል ትልቅ ነገር እንዴት በደህንንት ተጽፎ የተሰጠው እስኪመስል ድረስ “የሰዎቹ ማንነትና ዜግነት እየተጣራ ስለሆነ ለጸሎት ፍትሓት አትቻኮሉ!” ሊል ይችላል? አቤት ውርደት! አቤት ቅሌት! አቤት ሀገራችንና እኛ የገባንበት የሞራልና የሃይማኖት ግሽበት!!

 

The Amazing 30 Brave Christians Slaughtered Telling the `Murderers` to Go to Hell and Refusing to Bow to the False God of the ISIS.

We translated the words of ISIS spokesperson, his name is Anas Al-Nashwan (code name Abu Malik Al-Tamimi) of Saudi Arabia and has an MA in Sharia. He gave a way out saying:

We tell the Christians everywhere that the Islamic state will spread by Allah’s will. It [the Islamic State] will get to you even if you are safe in your fortresses. Whoever converts to Islam, he will have peace and who accepts the Dhimmi status will be at peace. But who rejects our terms he will receive nothing from us except the sharpness of the sword. Men will be slaughtered and the women and children will be enslaved and their moneys are confiscated as booty. This is the rule of Allah and his prophet. And to Allah is the pride and also to the believers but the hypocrites do not understand. …

The ‘ISIS’ know that it is extremely rare that Copts and Ethiopians convert. It is perhaps fitting to call these “stubborn for Jesus”.

So of course, the rest is translated in the English in which it is all about breaking the cross as the message is clear, it is the breaking of the will of the Christians which ISIS failed to do with these saints. …

 

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on April 24, 2015
  • By:
  • Last Modified: April 24, 2015 @ 8:25 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar