ይህ ማስታወሻ የተጻፈው በሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም “መንግስታችን” በጠራው የአይ.ሲ.ስ የአሸባሪ ቡድን በኢትዮጲያውያን ወንድሞቻችን ላይ የፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ ተቃውሞ ሰልፍ ስለደረሰብኝ ነገር ነው፡፡ በዚሁ ዕለት ከእህቴ ጋር በመሆን የተቃውሞ ተካፋይ ለመሆን ወደ መስቀል አደባባይ ሄደን ነበር…ሆኖም ብዙም ሳንቆይ የነበረው ድባብ ጥሩ ባለመሆኑ ወደ ቤታችን ተመለስን፡፡ ሰልፉ ከተበተነ፤ አካባቢው ጭር ካለ በኋላ ተመልሰን ወጣን፡፡ የነበርነው ደምበል አካባቢ ሲሆን በወጣንበት ሰዓት ምንም አይነት ግርግር የሌለ፤ ምንም አይነት ሩጫ፣ ድንጋይ ውርወራም ሆነ ተቃውሞ አልነበረም፡፡
እኛም ነገሮችን ቃኝተን ወደ ቤታችን በተረጋጋ ሁኔታ በመመለስ ላይ ሳለን በድንገት ከየት እንደመጣ ያላየነው የፌደራል ፖሊስ መኪና አጠገባችን መጥቶ ቁሙ ሲለን ሁላችንም እግሬ አውጪኝ ብለን ለመሸሽ ሞከርን…ዕድል የቀናው ሮጦ አመለጠ፤ እኛ ግን አልቻልንም ነበር፡፡ ከመኪናው ሮጦ የወረደ አንድ ፌደራል ፖሊስ በጎማ ዱላው ፌቴን መትቶኝ ወደቅሁ….ወድቄም ለወንድ ልጅ እንኳ የማይሰነዘር ምትን ደጋግሞ አሳረፈብኝ….በወቅቱ አብሮኝ የነበረ ወንድሜ ሮጦ ያመለጠ ሲሆን እህቴ እና እኔ ተይዘን ጫማችንን እንድናወልቅ ተደርጎ ከደምበል እስከ ስቴዲየም በባዶ እግራችን እንድንሄድ ተደረገ…….በትንሿ ስቴዲየምም አስቀመጡን፡፡ አብረውን ከነበሩት ሰዎች መካከል ሕፃናትን የያዙ እናቶች ነበሩበት፡፡
ይዘውን ለነበሩት የፌደራል ፖሊስ አባሎች ሁኔታውን ልናስረዳ ብንሞክርም…ብናለቅስም እነርሱ የምናወራውን ለመስማትም ሆነ የሰሙትን ለመረዳት የሚችል ጆሮ እና አዕምሮ አልነበራቸውም…..ልጅ የያዙ እናቶች ልጆቻችንን ከትምህርት ቤት አውጥተን እየተመለስን ነው…እኛ ምንም አላደረግንም እባካችሁ ልቀቁን ቢሉ የሰማቸው አልነበረም፡፡ እኔ እና እህቴም ከቤታችን መውጣታችን ነው….ምንም አላደረግንም ለምን ተያዝን ብንልም እንኳን ልንግባባ ይቅርና እራሳቸው ደብድበው ያሳበጡትን ፊቴን ድንጋይ ስትወረውሪ ነው ፊትሽ ያበጠው በማለት ጭራሽ ወንጅለውኝ ቁጭ አሉ፡፡ በዚህ መሀል እህቴ እራሷን ስታ ወደቀች….እሷን ለማዳን አብረውን የነበሩ ወንዶች ልጆች ይዘዋት ሊወጡ ቢያስቡም እንዴት በማለት እነርሱን ደብድበው ለእርሷም ምንም አይነት እርዳታ ሳይሰጡ ቀሩ፡፡
ይህ አረመኔ እና ጨካኝ ልባቸው ይራራ እንደሆን በማለት በለቅሶ ብንለምናቸው…ስለ አንድ ሀገር ልጅነታችን…ስለ ኢትዮጲያዊነታችን ብናነሳ….ሰብዓዊነት እንዲሰማቸው ብንለምን ምንም እንዳልተፈጠረ….አሸባሪዎች ናችሁ በማለት ለ5 ሰዓታት አሰሩን፡፡ እኛም ከአሁን አሁን ወደ እስር ቤት ተወሰድን ወይም ራርተውከተማችን ተለያይተን እንድንቀመጥ ተደረገ፡፡ በዛም የየወረዳው የወጣት ሊግ ተብዬዎች መጥተው “አሸባሪውን” ከደጋፊው ለይተው እንዲያወጡ ተጠየቁ….እኛን ያተረፈን አልነበረም…እንደማያውቁን…ከዚህ በፊት ስናሸብር እንደኖርን ተደርገን ሳንመረጥ ቀረን፡፡ በኋላም በሰው ሰው ባለስልጣን ዘመድ ተፈልጎ በዚ በዚያ ተብሎ ተለቀቅን፡፡
ሀገር አለኝ ብዬ አስብ ነበር አሁን ግን ለአይሲስ ካለኝ ጥላቻ ባልተናነሰ “መንግስታችንን” ጠልቼዋለሁ…. ህሊና የሌላቸው ወታደሮቻችንን ጠልቼአቸዋለሁ፡፡ እኔስ በቤተሰቦቼ ርብርብ ወጣሁ የእነዚያ እናቶች እና ሕፃናት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን? አሁንም በዚህ ሁኔታ የታሰሩ ወገኖቻችንስ? እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን….ጸሎቴ ከእናንተ ጋር ነው!!! ውይ ውይ ኢትዮጲያ…..
Frehiwot Nuri
Average Rating