www.maledatimes.com የአቶ መለስ ኑዛዜ በሀብተጊዮርጊስ ለገሰ ከኦስሎ ኖርዌይ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የአቶ መለስ ኑዛዜ በሀብተጊዮርጊስ ለገሰ ከኦስሎ ኖርዌይ

By   /   September 27, 2012  /   Comments Off on የአቶ መለስ ኑዛዜ በሀብተጊዮርጊስ ለገሰ ከኦስሎ ኖርዌይ

    Print       Email
0 0
Read Time:15 Minute, 44 Second

አንዲት እርጉዝ ሴት የመዉለጃዋ ጊዜ እየደረሰና በቅርቡም ልጅዋን እንደምትታቀፍ እንደምታዉቅ ሁሉ ሟች ሰዉም በደመነፍስ ሞት ሊወስደዉ እየመጣ መሆኑን እንደሚያዉቅ የስነልቦና ምሁራን በተለያየ ጹሁፎቻቸዉ ገልፀዋል ፣ ፣ነገር ግን የቤተሰብም ሆነ የህብረተሰብ ባህል ስለሞት እንዳይወራ ስለሚከለክል አብዛኛዉ ሰዉ የእሱ መሞቻ እንደተቃረበ የእሱ ወዳጆችም ሆነ ጠላቶች በገሀድ እንዲያዉቁ ባይፈቅድም በድብቅ ግን ታዋቂ ግለሰቦችን ሽማግሌዎችን ወይም የነፍስ አባት በመጥራት ኑዛዜ እንዲፈጸም ይደረጋል፣ ፣ ይህን በአገራችን ኑዛዜ የምንለዉን የስነልቦና ምሁራን ደግሞ የሟች ተግባራት (tasks of dying) ብለዉ ይጠሩታል፣ ፣

ዶር ኢራ ቢዮክ (Dr Ira Byok) አራቱ አስፈላጊ ነገሮች(four things that matter) በሚለዉ መጽሀፋቸዉ አንድ ሟች የሚወዳቸዉን ከመሰናበቱ በፊት አራት በጣም አስፈላጊ ነገሮች መፈጸም እነዳለበት ያሳስባሉ፣ ፣ የስነ ልቦና ጠበብቱ በመቀጠል ሟች ሰዉ ያበቃለት የወደፊት ተስፋ የሌለዉ ይመስለናል፣ ፣ ነገር ግን ተስፋ አለዉ፣ ፣ተስፋዉ ግን እዉነተኛ የሚሆነዉ ሟች መሞቻዉ ሲቃረብ በሚፈጽማቸዉ የሟች ተግባራት ላይ ተመስርቶ ነዉ፣፣ ምክንያቱም እነዚህ ተግባራት ሟች ዘላለማዊ የሰላም እረፍት እንዲወስደዉ የሚያደርጉ ናቸዉና ይሉናል፣ ፣

ስለዚህ አንድ መሞት አፋፍ ላይ ያለ ግለሰብ የሞት ጊዜ ተግባራትን ካልፈፀመ መሰራት የነበረባቸዉን መሰረታዊ ስራዎች ሳይሰራ እንዳለፈ ይቆጠራል፣ ፣

በመሆኑም አቶ መለስ ከያዛቸዉ በሽታ አስከፊነት አንጻር ሲታይ መሞቻቸዉ መቃረቡን የተረዱ በመሆናቸዉ እነዚህን ተገባራት ለመፈጸም በቂ ጊዜ እንደነበራቸዉ መገመት እንችላለን፣ ፣

የመጀመሪያዉ ተግባር ሟች በህይወት ዘመናቸዉ ለሰሯቸዉ ስህተቶች ይቅርታን መጠየቅ ያካትታል፣ ፣ህይዎታችን ሊያልፍ አቅራቢያ አካላዊ ቁስላችንን ማዳን እንደማንችል ይታወቃል፣ ፣ላጠፋነዉ ጥፋት ግን ይቅርታን በመጠየቅ ለዘላለም አብሮን ከሚኖረዉ የህሊና ቁስል ግን መዳን እንችላለን፣ ፣ እንደ ዶር ቢዮክ አገላለጽ አካላዊ ቁስል(ጉዳት) ከደረሰብን የተመረዘዉ የአካል ክፍላችን በመድሀኒት ከበሽታዉ ታጥቦ መጽዳት ይኖርበታል፣ ፣የህሊና ቁስልን ለማዳን ግን የተረጩት መርዞች ታጥበዉ እንዲጸዱ ማድረጊያዉ ብቸኛ መንገድ ላደረሱት ጥፋትና ስህተት ይቅርታን መጠየቅ ነዉ፣ ፣

አቶ መለስ ዜናዊ በአገዛዝ ዘመናቸዉ ለስልጣናቸዉ ከመጓጓት የተነሳ አመራር በመስጠት ልጆችን በማስገደል ወላጅን አሳዝነዋል፣አባትና እናትን በማስገደል ልጅን ወላጅ አልባ አስደርገዋል፣በእስር ቤት ሰቆቃና ስቃይ የብዙ ሰዎች ህይወት እንዲጠፋና አካለጎዶሎ እንዲሆን ተደርጓል፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጲያዊነትን ማሳነስ ለስልጣናቸዉ መደላድል እንደ አንድ አማራጭ በመዉሰድ የኢትዮጵያን ህዝብ አሳዝነዋል፣በህዝቡ መካከል አንድነትና ፍቅር እነዳይኖር በከፋፋይ ፖሊሲያቸዉ መርዝ በመርጨት ህዝቡን አራርቀዋል፣የህዝቡን ሀብት በማስዘረፍ ጥቂት ወገኖቻቸዉ እንዲከብሩ አስደርገዋል፣ ፣

አቶ መለስ ለነዚህ  ሁሉ የህሊና ቁስሎች ህዝቡን ይቅርታ ጠይቀዉ የሟች ተስፋ የሆነዉን ሰላማዊና ዘላለማዊ የሆነዉን እረፍት ወስደዉ ይሆን? ከነፍስ አባታቸዉ ከአቡነ ጳዉሎስ የሰማነዉ ነገር ስለሌለ እርግጠኛ አይደለሁም፣ ፣

ሁለተኛዉ የሟች ተግባር ሟች በዚህች ዓለም ቆይታዉ በልቡ ዉስጥ ስፍራ ሊሰጣቸዉ የሚገቡ ግለሰቦችን ከልብ በመነጨ ማመስገን ነዉ፣ ፣ ምስጋና ማቅረብ ቀላሉና ከሟች ተግባራትም በጣም አስፈላጊ ነዉ፣ ፣በአቶ መለስ ልብ ዉስጥ ስፍራ ሊሰጣቸዉ የሚችሉ ብዙ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ፣ አቶ መለስ መሞቻቸዉ መቃረቢያ አካባቢ በኢቲቪ በሰጡት ቃለምልልስ ታላላቅ የኢትዮጵያ መሪዎችን በማንኳሰስ የራሳቸዉን ዝና ከፍ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል፣ ፣አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ለመባል የበቁት አጼ ሚኒልክና አጼ ቴዎድሮስ አንድነቷን ጠብቀዉ ባቆይዋት ኢትዮጵያ ላይ መሆኑን ዘንግተዋል፣ ፣እንደ እዉነቱ ከሆነ እነዚህ ሁለት ታላላቅ መሪዎች በመለስ ልብ ዉስጥ ስፍራ ሊሰጣቸዉ የሚገቡ ነበር፣ ፣ነገር ግን በቃለምልልሱ ወቅት አጼ ሚኒሊክ የዉጭ ቴክኖሎጂን የራስ ለማድረግ ሲጥሩ የዉጭ ሙያተኞችን መጠቀም ስህተት እንደነበረ፣ የህበረተሰቡ መሰረታዊ አወቃቀር ሳይቀየር አንዳንድ ዘመናዊ ቅብ ነገሮችን መዉሰዳቸዉ ድህነትን እነዳስከተለ በመተንተን የአሁኑ የልማት አቅጣጫ የተስተካከለ አቅጣጫ መሆኑን አስረድተዋል፣ ፣ይህ ትንታኔአቸዉ በወቅቱ የነበረዉን የህብረተሰብ እድገት፣የህብረተሰቡ ንቃተ ህሊናና የትምህርት ደረጃ፣ የመሪዎቹ የትምህርት ደረጃ፣የህብረተሰቡ ዉስበስብ ባህላዊ ተፅዕኖዎች ከግንዛቤ ያላስገባ በሞሆኑ 21 ዓመት ሙሉ ዋሽተዉ የኢትዮጵን ህዝብ ለማሳመን ጥረት ካደረጉባቸዉ ነግግሮች ዉስጥ በጣም የወረደና ግምት ዉስጥ የከተታቸዉ ነበር ማለት ይቻላል፣ ፣አቶ መለስ ከ100 ዓመት በፊት የዉጭ ሙያተኞችን  መጠቀም ስህተት እንደነበረ ሲናገሩ በአጼ ሚኒልክ የተጀመረዉ ቴሌ በእሳቸዉ ዘመን በፈረንሳይ ኩባንያ እንደሚመራ ጋዜጠኛዋ ብታስታዉሳቸቸዉ ምን ይሰማቸዉ ይሆን? ይህን ያነሳሁት ምስጋና ለማቅረብ ፍላጎት እንዳልነበራቸዉ ለመግለጽ ነዉ፣ ፣

ከሟች ተግባር ዉስጥ ይቅር ማለት ለአብዛኛዉ ሰዉ የሚከብድ ቢሆንም ይቅርታ አድራጊዉ ከንዴትና ከቅሬታ መንፈሱን ነጻ የሚያደርግበት ስለሆነ በጣም አስፈላጊ ነዉ፣ ፣

ይህንን በተመለከተ የስልጣኔ ተቀናቃኝ ናቸዉ ብለዉ የገመቱትን የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ጋዜጠኞችን በእስር ቤት ዉስጥ እንዲሰቃዩና እንዲማቅቁ ማድረጋቸዉ ሳያንስ በመጨረሻዉ የህይወት ዘመናቸዉ ይቅርታ ሳያደርጉላቸዉ ሰቆቃዉና ስቃዩ እንዲቀጥል ለሕወአት ደርግ አሳልፈዉ ሰጥተዋል፣ ፣

የመጨረሻዉ የሟች ተግባር የሚወዱትን መሰናበት ሲሆን ህመማቸዉ ሆነ ሞታቸዉ ከህዝቡና ከቤተሰባቸዉ ተደብቆ ስለነበር ለዚህም አልበቁም፣ ፣ ተጠያቂዎቹ ግን አፋኝ የነበሩት ጓደኞቻቸዉ ናቸዉ፣ ፣

አቶ መለስ የሟች ተግባራትን አለመፈጸም ብቻ ሳይሆን አመራር ላይ በነበሩበት ጊዜ የነበራቸዉን ከፍተኛ ዕድል ባለመጠቀማቸዉ ከታላላቅ የኢትዮጵያ መሪዎች ተርታ የመሰለፍ ዕድል አምልጧቸዋል፣ ፣በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን ለመጀመሪያ ጊዜ የማስፈን ከፍተኛ ዕድል ነበራቸዉ፣ ፣ሕዝቡ ሲናፍቀዉ የኖረዉ የመጻፍ፣ሀሳብን በነጻ የመግለፅ፣የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነት ማረጋገጥ ሲችሉ በእንጭጩ አስቀርተዋል፣ ፣በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ስልጣን በህዝቡ ይሁንታና ምርጫ ብቻ እንዲሆን ማድረግ ሲችሉ አሰናክለዋል፣ ፣የባህር በር የማግኘት መብታችንን አድበስብሰዉ አልፈዋል፣ ፣ለአገራችን ጥንካሬ የሚበጀዉን ፍቅርንና አንድነትን መስበክና ተግባራዊ ማድረግ ሲችሉ ለአገሪቷ መፈረካከስና ለህዝቡ መለያየት መንገድ የሚከፍት መርዝ ጥለዉ አልፈዋል፣ ፣

አቶ መለስ በስራ ዘመናቸዉ ሆነ መሞቻቸዉ ሲቃረብ መስራት ሲገባቸዉ ሳይሰሩ የቀሩትን ተግባራት የኢትዮጵያ ህዝብ በአቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ጊዜ እንዲፈጸም ይጠብቃል፣ ፣ስለዚህ አቶ ሀይለማሪያም ለሚያመልኩት እየሱስ ክርስቶስ ብቻ ሊሰጡ የሚገባዉን ዘላለማዊ ክብር ለአቶ መለስ መስጠታቸዉ እምነታቸዉን እስከ መፈታተን ያደረሰ የግለሰብ አምልኮ ስለሆነ በአስቸኳይ ንሰሐ ሊወስዱ ይገባል፣ ፣ ከወይዘሮ አዜብ የቀዱት የመለስ ራዕይ ሳይበረዝ ሳይከለስ እቀጥላለሁ የሚለዉ አባባላቸዉ ወደ ተግባር ሳይለወጥ በቃል ደረጃ ብቻ ማብቃት አለበት፣ ፣የኢትዮጵያ ህዝብ በአሁኑ ጊዜ የሚፈልገዉ የራሱ ራዕይ ያለዉ መሪ ነዉ፣ ፣ ጠንካራ ጎኖችን አዳብሮ ስህተቶችን አርሞ ኢትዮጵያን ለዕድግት የሚያበቃ መሪ ይፈለጋል፣ ፣ ካለበለዚያ ከህሊና ቁስል ካልዳነዉ በመለስ መንፈስ( Ghost ) ለመመራት የኢትዮጵያ ሕዝብ ዝግጁ አየደለም፣ ፣

 

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

 

ጸሐፊዉን ለማግኘት ከፈለጉ – tgiorgis2005@yahoo,com

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 27, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 27, 2012 @ 6:57 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar