የዛሬ 105 ዓመት ጥቅምት 7 ቀን 1902 ዓ.ም አንድ ሕጻን ወደ ምድር መጣ፡፡ የበቀለበት ደብር እንዶር ኪዳነ ምህረት ትሰኛለች፡፡ የህጻኑ አባት ካህን ሲሆኑ አባ አለማየሁ ሰሎሞን፣ እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ ደስታ ዓለሙ ይባላሉ፡፡
የህጻኑ ወላጆች በአካባቢው ልማድ መሰረት ልጃቸውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የትምህርት ስርአት ውስጥ እንዲያልፍ አድርገውታል፡፡ በዚህም በደብረ ኤልያስ በደብረ ወርቅ እና በዲማ ትምህርቱን እየተከታተለ በመንፈስም በአካልም አድጓል፡፡ በኋላም ወደ አዲስ አባባ በመምጣት በሲዊዲሽ ሚሽነሪ ት/ቤት እና በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ ኋላም በአዲስ አበባ በመምህርነት በጎጃም በጉምሩክ ሥራ ባለሙያነት ሠርቷል፡፡ በተጨማሪም ሐገሩን በአርበኝነት፣ በዲፕሎማትነት በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አገልግሏል፡፡
(በኢጣሊያ ወረራ ወቅት 1929-1933 ዓ.ም. ከልዑል ራስ አምኃ ኃ/ስላሴ ጦር ጋር በአርበኝነት ሲጋ ቆይቶ በምእራብ ኢትዮዽያ በጣሊያን ተማርኮ፥ ወደ ኢጣሊያ በግዞት ከቆየ በኋላ በ1936 ዓ.ም. ወደ ሀገሩ በነፃነት ተመልሷል።)
ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ታላቅ ክብር እና ሞገስን ያሰጠው በህዝብም ልብ ውስጥ ያስቀመጠው ለኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ያበረከተው አስተዋጽዖ ነው፡፡ አስቀድሞ ሌሎች ሁለት መጸሐፍትን ማሳተም ቢችልም ከሁሉ በላይ ስሙን በደማቅ ቀለም እንዲጻፍ ያደረገው ዘመን አይሽሬ ሥራው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነጽሁፍ ዐምድ መሆኑ የተመሰከረለት “ፍቅር እስከ መቃብር” (1958) የተሰኘው ልብ ወለዱ ነው፡፡ ይህ መጸሐፍ ከወጣ ግማሽ ክፍለ ዘመን ሊያስቆጥር እየተቃረበ ሲሆን ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ መለኪያ ሆኖ ሲጠቀስ ይስተዋላል፡፡
የዚህ መጸሐፍ ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ከዚህ በተጨማሪ፡-
የአበሻና የወደፊቱ ጋብቻ (1929 ተውኔት)
ተረት ተረት የመሰረት (1948)
ኢትዮዽያ ምን አይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል? (1966)
ትዝታ (1985 ግለ ታሪክ)
ወንጀለኛው ዳኛ (1974)
የልምዣት (1980) የተሰኙ መጸሐፍትን ለንባብ አብቅተዋል፡፡
በህይወታቸው መጨረሻ አካባቢ ነሐሴ 27 ቀን 1991 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሰጣቸው ሲሆን ኅዳር 28 ቀን 1996 ዓ.ም. በ94 ዓመታቸው ከ10 አመት በፊት ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡ እኒህ የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ባለታሪክ ሰው ከተወለዱ ጥቅምት 7, 2007 ዓ.ም ልክ 105 ዓመታቸው ሆናል፡፡
ምንጭ፡https://www.facebook.com/Ethiopianwritersassociation?hc_location=timeline (
Getenet Yet)
ይህንን መልዕክት ሼር በማድረግ አድናቆታችሁን – የመልካም ልደት መልዕክታችሁን – ግለጡ፡፡
Share, Comment and like it. Lot’s of thanks
Average Rating