ሚያዝያ2007/2015
ሰሞኑን በማህበራዊ ድህረ- ገፆች ላይ የተለቀቀናአንድ ኤርትራ ደርሶ የተመለሰ የኢሳት ጋዜጠኛ በኤርትራ ቆይታው ያገኘውን ነዋሪነታቸው በአውሮፓ የነበረና የትጥቅ ትግል ለማካሄድ ግንቦት7 ህዝባዊ ሃይልን ለመመስረት( ለመቀላቀል) ኤርትራ በረሃ ከወረዱ ሶስት ወጣቶች ጋር ያደረገውን አጭር ቃለመጠይቅ ለማየት ችዬ ነበር
እነዚህ በቪዲዮ ላይ የምንመለከታቸው ወጣቶች እነማን ይሆኑ፤ ከየት ይምጡ፤ ከየትም ይግቡ ከባድ የሆነውን በረሃ ተቛቁመውና መኖሪያቸው አድርገው ቀላል የማይባል አቅምያለውን ኃይል ታግለው ለመጣልና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈለገውን ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደርን ለማምጣት መንቀሳቀሳቸው ኢትዮጵያውስጥ ለውጥ መምጣት አለበት ብለው ከሚያምኑ ሊሰጣቸው የሚችለው አድናቆት ከፍያለ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል ለሚልና በትግሉ ቀጥታ ታሳታፊ መሆን የሚፈልግን ሰው ወደዚህ ትግል ለመጥራትና ለማነሳሳት የሚያስችልም ነው፡፡
በከዚህ ቀደም ፅሁፎቼ ለመናገር እንደሞከርኩት ሶስቱ ወጣቶች በሚገኙበት ቦታ ላይ በነበረኝ ቆይታ የነዚህንም ሆነ የሌሎች የህዝባዊ ሃይሉ አባላትን ከምር የሆነን ጠንካራ የትግል ስሜት ስረዳ በግንቦት7 እቃ እቃ ጨዋታ ውስጥ ሳያውቁት ገብተው የተገኙ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ፡፡
በግርድፉ ኢሳት ከነዚህ ሶስት ወጣቶች ጋር ያደረገውን ቆይታ ስንመለከት ብዙ ነገሮች ወደ አእምሮዬ ተመላለሰ፡፡
ለመጀመሪያ ግንቦት7( ኢሳት) ጀመርኩት ከሚለው የትግል ባህሪ አንፃር የፋይናንስ ምንጭ ከመሆን ባለፈ ፋይዳው ብዙም ያልሆነውን ዲያስፖራ ቀልብ ለመሳብ ከመታገል ውጪ ውሃ የሚቛጥር ነገር ለማሳየት እንዳልቻለ አልያም እንዳልሞከረ፤ ከዚህ ትግል አንፃር ዋነኛ ተዋናይ መሆን የሚገባው ሀገር ቤት ያለው ህዝብ ውስጥ ለመግባት አለመቻሉን ወይም ተቀባይነትን ማግኘት እንዳቃተው ማየት ችያለሁኝ፡፡
ይህ የግንቦት7 ህዝባዊ ሃይል ሲመሰረት 6 ከደቡብ አፍሪካ፤ 1 ከኬኒያ፤ 1 ከኡጋንዳ፤ 1 ከአሜሪካ፤ 1 ከሱዳን፤ 2 ከአውሮፓና የተቀሩት ከኢትዮጵያ ከተሰባሰቡ በጠቅላላው 17 ወጣቶች ነበር፡፡ ከምስረታው ጀምሮ ውሸት ሲደሰኮርለት የነበረው ይህ ስብስብ ከዚህ ቁጥር መዝለል ባልቻለባቸው ግዚያቶች ውስጥ ኢሳትና ሌሎች ለግንቦት7 አጋር የሆኑ ሚዲያዎችና ድህረገፆች እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ወጣት ምሁራን ህዝባዊ ሃይሉን ለመቀላቀል ከአውሮፓ፤ከአሜሪካ፤ ከአውስትራሊያና ከተለያዩ የአለማችን ሀገሮች ወደ ኤርትራ በረሃ እየጎረፉ ነው ብለው ሲነግሩን ነበር፡፡ ልክ እንደ ከዚህ በፊቱ ኢሳት ራሱ ያሰራጨውን ወሬ ሀሰትነት የሚያረጋግጥ ሌላ ወሬ ከሁለት አመት በኋላ ይዞልን መጣ፤ በሰሞኑ ቪደዮው ሶስት ከአውሮፓ ገቡ የተባሉ ወጣቶችን በቃለ መጠይቁ ይዞልን ብቅ አለ፡፡ በየግዜው ጎረፉ የተባሉ ወጣቶችስ? ከአሜሪካ
ና ካናዳ የገቡትስ? መቼም ከአንድ ጋንታ ማለፍ ያቃተትን ስብስብ ለመጎብኘት የሄደው ይህ ጋዜጠኛ “በገፍ የገቡት ሌሎቹን በተለያየ ካምፕ ስለተቀመጡ ወይም ስለሚኖሩ ላገኛቸው አልቻልኩም” ብሎ አያሾፍብንም፡፡ ከኤርትራ ተመለስው ከወጡ የተለያ ሰዎች በተደጋጋሚ ለመስማት እንደተቻለውና በቦታው የነበረው የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ እንዳስተዋለው ሌሎች ወጣቶች ከተለያዩ የአለም ሃገራት በገፍ ሊገቡ ይቅርና ከላይ የተጠቀሱት ከመስራቾቹ መሃል ምናልባትም ከአስራሁለት በላዩ የጠበቁትንና መሆን የነበረበትን ማግኘት ባለመቻላቸውና ፍፁም ትግል ገዳይናተስፋ አስቆራጭ ነገሮችን በተደጋጋሚ ማየት በመቻላቸው የኤርትራን በረሃለቀው ወደ መጡበት ሃገርና ወደተለያዩ ቦታዎች ለመበተን ችለዋል፡፡
በዚህ ቪዲዮ ላይ የምንመከተውና ህዝባዊ ሃይሉ ከተመሰረተ በኋላ ከአውሮፓ የተቀላቀለውን አንዱን ጨምሮ ከሚታዩ ሶስት ወጣቶች ሌላ ከሌላ ዓለም የተቀላቀላቸው ወጣት አለመኖሩን በተለያየ መንገድ ማወቅና ማረጋገጥ ቢቻልም ግንቦት7ና ኢሳት አሁንም የትጥቅ ትግል መቀስቀሻቸውና አጀንዳቸው አድርገውት ዘወትር ይደሰኩሩልናል፡፡
በየትኛውም ትግል ውስጥ የዲያስፖራው አስተዋፆኦ ቀላል ባይሆንም በሃገር ቤት ውስጥ ምንም ዓይነት የትግል መሰረት ባልተጣለለበት ሁኔታ የሚደረግ ግብግብ ሁል ግዜ እንደምናየው በየሀገሩ የገንዘብ ማሰባሰቢያ የሚደረጉ ስብሰባዎች ከማድረግና የምስረታ ዕድሜን እየቆጠሩ ከማክበር የዘለለ ፋይዳእንደማይኖረው ከግንቦት7ና መሰል ስብስቦች በላይ ማሳያ የለም፡፡
ምርጫ 97ን ተከትሎ የመጣውን የህዝብ የፖለቲካ ተሳትፎና መነቃቃትን እንዲሁም የመንግስት ለውጥ በሰላማዊ መንገድ ይመጣል የሚሉ ጥቂት የማይባሉ ሰዎቸ ተስፋ ቆርጠው ሌላ የትግል አማራጭን መፈለግ በጀመሩበት ወቅት ተመስርቶ እከተለዋለሁ ከሚለው “ሁለገብ ትግል” አንፃር ምቹ ሁኔታ የተፈጠረለት ግንቦት7 ህዝብ ውስጥ ለመድረስና ( በተለይ ዲያስፖራው ጋር) በርካታ ደጋፊዎችንና አባላትን ለማፋራት ብዙ ሳይለፋ የተሳካለት ነበር፡፡ ይህ አጋጣሚ የፈጠረው በህዝብ ተቀባይነት ማግኘት መንግስት ላይ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሮ እንደነበር ከፀረ- ሽብር ህጉ አዋጅ እስከ በፓርላማው በሽብርተኝነት መፈረጅ የተካሄው ጉዞን ማንሳት በቂ ነው፡፡
በተደጋጋሚ በተለያዩ ሰዎች ሲገለፅ እንደምንሰማው ግንቦት7 በዚህ ሁሉ ግዜ ቆይታው ዲያስፖራን ከማደራጀት ወይም በደጋፊነት ከመሰብሰብ ባለፈ በሃገር ቤት ውስጥ ይህንን ሰራ(ሞከረ) ተብሎ የተጠራለትን ወይም የተጠራበትን ሰበብ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ግንቦት7 አገር ቤት ውስጥ ስሙ ሊጠራ ከቻለም ዘወትር በመንግስት ቁጥጥር ስር ውለው ወህኒ ወረዱ አልያም ተሰደዱ ለሚባልላቸው የሰላማዊ ፖለቲካ መሪዎችና አባላት፤ አክቲቪስቶች፤ጋዜጠኞችና ብሎገሮች ለሚለጠፍባቸው ታርጋ ሰበብ ሲሆን ብቻ ነው፡፡
በሃገር ቤት ህጋዊ ሆነው ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች መፈራረስና መዳከም፤ ጠንካራ ለሚባሉ የህትመት ውጤቶች መታገድና መቛረጥ፤ ህዝብን በማንቃትና መረጃን በማቀበል ከፍተኛ ሚናን ይጫወቱ ለነበሩ ጋዜጠኞች መታሰርና ሀገር ጥሎ መሰደድ ከኢህአዴግ መንግስት እኩል የተጠያቂነት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው ግንቦት7 ነው፡፡ ለእነዚህ ኪሳራዎች ሁሉ ምክንያት ከመሆን ባለፈ ይህን ሊተካልን ወይም ሊያካክስልን የሚል አንዳችም ነገር ሰርቶ ለማሳየት አቅም ማጣቱ በብዙዎች ተስፋ የተጣለበትና ፋይዳ ቢስ ሆኖ ከመታየት ባለፈ ለተቃውሞ ፖለቲካው መፈራረስ ሰበብ ሆኖ እንደጠላትነት የተፈረጀባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡
ለግንቦት7 ውጤት አልባ ረጀም ጉዞ ብዙ ምክንያቶችን እዚሁ ማንሳት ይቻላል፡፡ ከዚህም መካከል እከተለዋለሁ ላለው “ሁለገብ የትግል” ፤ትግሉን ያሳካልኛል ብሎ የሚቀርፃቸው የትግል ስትራቴጂዎች በሙሉ ዲያስፖራውን ብቻ ማዕከል ያደረገና የትግሉ ዋና ባለቤት የሆነውን ሃገር ቤት ያለውን ህዝብና ሁኔታ ግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑ ከምክንያቶቹ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ በሌላ ፅሁፍ የምመለስበትና ብዙ የሚያወያይ ቢሆንም የተመሰረተበትን የዲያስፖራ ሰፈር ውስጥ ጎርምሶ የውስጥ ችግሩን ሃገር ውስጥ በሚደረገው ትግል ላይ ይህ ነው የሚባል አስተዋፅኦ ለማበርከት ያልቻለ ስብስብ መሆኑን በግልፅ አስቀምጬ ማለፍ እፈልጋለሁ፡፡
ሌላው ለግንቦት7 እንዲህ ሆኖ መቅረት ምክንያት ተደርገው መነሳት የሚገባቸው ውስጥ የሚሞክራቸው ያልተጠኑ የትግል መንገዶች ላይ እየተገኘ የሚደርስበት ቀላል የማይባል ተደጋጋሚ ኪሳራ ነው፡፡ “ሁለ -ገብ” የሚለው ስልት የቱን እንደሚያካትትና እንደማያካትት አይደለም ለማንም ለአባላቱ እንኳን ግልፅ ማድረግ ያልቻለው ግንቦት7 መንግስትን የሚያዳክመው ወይም የሚጥሉ መስለው ስለታዩት ብቻ ለተለያዩ ጉዳዮች እጁን በመሰንዘር ትልቅ የፖለቲካ ኪሳራን በሚያስከትሉና ደጋፊና አባላትን ባስቆጡ ብሎም ተስፋ አስቆርጠው በሚያሸሹ ነገሮች ውስጥ ተዘፍቆ በተደጋጋሚ አይተነዋል፡፡
ከዚህም መካከል“እስከአሁን ምንሰራችሁ?” የሚለውን የዲያስፖራን ጥያቄ ሽሽት የተገባው የኤርትራው ትግል አንዱ ነው፡፡ይህ ውሳኔ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ሰዎቸ የደገፉት ቢሆንም ኤርትራ ከገባ ግዜ ጀምሮ የደረሰበትንና እየደረሰበት ያለውን ኪሳራ ቀድመው አስልተው የተነበዩና አጥበቀው የተቃወሙት ብዙዎች ነበሩ፡፡ ኤርትራ መግባቱን የደገፉትም ቢሆን ከወደዚያ አካባቢ የሚሰማው ተደጋጋሚ ዜና ጥሩ ባለመሆኑ ሃሳባቸውን ለመቀየርና ከግንቦት7 ለመራቅ አሊያም ለመቃወም ብዙ ግዜ አልወሰደባቸውም፡፡
ሌላውና ዋናው ለግንቦት7 አቅም ማጣት ሰበብ ሆኖ የምናገኘው ምርጫ97ን ተከትሎ የመጣውን የሃገር ውስጥ የተቃውሞ ፖለቲካ መቀዛቀዝ ደግሞ እንዲያንሰራራ ሲታገሉ የነበሩ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች፤ አባላት፤ አክቲቪስቶች ፤ጋዜጠኞና ብሎገሮች እንቅስቃሴ በተለያየ መንገድ በመንግስት ሲገታ አይተናል፡፡ ግማሹ እስከ እድሜ ልክ በሚያሳስር ወንጀል ተከሰው ወህኒ ሲወርዱ የተቀሩት ሃገር ጥለው ሲሰደዱና በፍርሃት ተሸብበው ሁሉን እርግፍ አድርገው ትተው የግል ህይወታቸውን ብቻ ሲመሩ እየተመለከትንም ነው፡፡ ቀድሞውንም ከግንቦት7 ጋር መነካካት በከባድ የሽብር ወንጀል እንደሚያስጠይቅ የደነገገው መንግስት ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረውለት በአብዛኛዎቹ ላይ የሃሰት ውንጀላና ክስ በመመስረት የተከናወነ ቢሆንም ከነዚህ መካከል ቀላል የማይባሉት ግን ግንቦት7 ባበጀው ዝርክርክ መንገድ ላይ ተገኝተው የነበሩ ናቸው፡፡ ራሱን ችሎ ይህ ነው የሚባል የሰራውን ነገር ማሳየት ያልቻለው ግንቦት7ሰላማዊ ትግሉ ምንም ተስፋ የሚጣልበት አለመሆኑንን ለማሳየትና ሁሉም የግንቦት7 መንገድን ብቻ እንዲከተሉ የሚፈልግ በሚመስል መልኩ ለብዙዎቹ መታሰር ፤ ቤተሰብ መፍረስ፤ መሰደድ እንዲሁም የሃገር ውስጥ ተቃውሞ ፖለቲካባለቤት አልባ ሆኖ እንዲቀር ሲታትር እያየን ነው፡፡
ከወራት በፊት ጎንደር ውስጥ የተቃውሞ ፖለቲካ አስተዋፅኦቸው ከፍተኛ የነበረ የሰማያዊ ፓርቲ አምራርና አባላት ክዚህ ጋር በተያያዘ ከአላማቸው መሰናከልና መታሰር ሰበብ ከመሆን ባለፈ ስራ ውስጥ ያልታየው ግንቦት7 በአሁኑ ሰአት በብዙዎቹ ዘንድ መረር ያለ ተቃውሞ እየገጠመው እያየን ነው፡፡
የግንቦት7 አካሄድ የትም እንደማያደርስ የተረዳው የኢትዮያን ፖለቲካ በየቀኑ የሚከታተል ህዝብ ብቻ ሳይሆን ቀድሞ ከምስረታው ጀምሮ ነገ ጥቅም እናገኝበታለን ብለው ሲረዱትና ድጋፋቸውን ሲያደርጉለት የነበሩት ምዕራባውያን ሳይቀሩ ስሙን ጠቅሰው ለአሸባሪ አምስት ጉዳይ የሆነው ስም ሲሰጡት ተመልክተናል፡፡ የሰሞኑን የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ዌንዲ ሸርማን ንግግርን የተመለከተ ግንቦት7 የሚተማመንበትን የዲስፖራውን ሰፈርና መድረኩንም በቀላሉ እየተነጠቀ መሆኑንና የግንቦት7 ህልውናን ጥያቄ ውስጥ እንደገባ ማየት ይችላል፡፡
Average Rating