በማሕጸን ከነበረበት ጊዜ ጀመሮ እስከአሁን በወያኔዎች ስቃይ እየደረሰበት ያለ ልጅ – ግርማ ካሳ
ከአሥር አመታት በፊት ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የፖለቲካ ክፍተትና ዴሞክራቲክ እንቅስቃሴ መታየት ጀመረ። አስኳል ፣ ሚኒሊክ፣ ሃዳር፣ አዲስ ዜና፣ ሰይፈ ነበልባል ..እያለ ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ነጻ ጋዜጦች ይታተሙ ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአሥራ አራት አመታት ጆሮዉን ሲያደነቁረው የነበረውን የዘር ፖለቲካ አንቅሮ በመትፋት የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካን የሚያራምደውን ቅንጅት በነቂስ መረጠ። በአዲስ አበባ ኮሮጆ ሳይገለብጥ፣ ምንም አይነት ማጭበርበር ሳይደረግ ቅንጅት መቶ በመቶ አሸነፈ። ከጠበቁትና ከገመቱት በላይ ሕዝቡ እንደተፋቸው የተገነዘቡት ወያኔዎች ደነበሩ። ድምጽ ቆጠራዉን አቋርጠው፣ ድምጽ ሰርቀው አሸነፍን ብለው አወጁ። የአሜሪካኖችን ሃምቪና ታንክ መንገድ ላይ እያበረሩ በአቶ መለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትእዛዝ ወገኖቻችን ላይ ተኩሱ። እነ ሽብሬ ደሳለኝና ሌሎች ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ወገኖቻችንን ገደሉ ። የቅንጅት መሪዎችና በርካታ ጋዜጠኞችን አሰሩ።
ይህ ልጅም በዚያ ወቅት ታሰሮ ወደ ቃሊቲ ወረደ። በናቱ ማህጸን ዉስጥ ሆኖ። እናቱም ነፍሰ ጡር ሆና፣ ሲሚንቶ ላይ እንድትተኛ ተደረጋ፣ አስፈላጊው ሕክምና ተነፍጋ ፣ በጭንቅና በመከራ ወለደችው። ከናቱ አር አብሮ ተሰቃየ። ይህ ልጅ አሁን አሥር አመቱ ነው። ናፍቆት እስክንድር ይባላል። የአንጋፋዎቹ ጋዜጠኞች ሰርካለም ፋሲልና እስክንደር ነጋ ልጅ።
ናፎቆት እስክንደር፣ የአገዛዙን ጭካኔ ማየት የጀመረው በናቱ ማሕጸን ዉስጥ ሆኖ ነው። አገዛዙ እናቱን አስሮ በቃሊቲ ሲያሰቃያት። ይኸው እስከ አሁ ድረስ አባቱን እንዳያይ አድርገውት፣ ይህ አንድ ፍሬ ልጅ፣ በአባቱ ናፍቆት እየተቃጠለ ነው።
አባቱ ጋዜጠኛ እስክንደር ነጋ ፣ ሕገ መንግስቱ የሚፈቅደውን መብት በመጠቀም፣ በመጻፉ፣ “ሽብርተኛ” ተብሎ ታስሯል። አቃቢ ሕግ እነ እስክንድር ነጋን በከሰሰበት ጊዜ ፣ ምንም አይነት የተጨበጠ ማስረጃ አቃቤ ሕግ ሳያቀርብ፣ ከደህንንት ጽ/ቤት በተሰጠ መመሪያ ብቻ፣ የመጀመሪይው ፍርድ ቤት እስክንደር ነጋን፣ አንዱዋለማ አራጌና ሌሎችን ጥፋተኛ ናቸው አለ።
እነ እስክንድር ይግባኝ ባሉበት ወቅት፣ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ አማራ አሞኜ፣ የቀረቡትን ክሶች መርምረው፣ “ምንም አይነት ወንጀል በነ እስክንደር ላይ አላገኘሁም” ብለው እነ እስክንደርን ሊፈቱ ባሰቡበት ወቅት፣ አቃቢ ሕጎቹ ዳኛውን አስፈራሩ። ዳኛው አልበገር አሉ። ጉዳዩ የጠቅላይ ሚኒስተር ምክር ቤት ድረስ ደረሰ። እነ ደመቀ መኮንን እነ እስክንድር ይፈቱ ሲሉ፣ በምክር ቤቱ የነበሩ ሕወሃቶች “መለስ ያሰራቸዉን እንዴት አሁን መለስ ሲሞት እንፈታለን። ይሄ መለስን መሳደብ ነው። መለስ አደገኛ ናቸው ብሏቸውል እዚያው በእሥር ቤት ይበስብሱ” ይላሉ። (በአሁኑ ወቅት በወህኒ ያለው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በወቅቱ እንደዘገበው)
ዳኛ አማራ አሞኜ “ጥፋተኛ” አልልም ስላሉ፣ ሌላ ዳኛ እርሳቸውን እንዲተካ ተደረገ። የደህንነትት መዋቅሩን የሚቆጣጠሩት ሕወሃቶች እንደመሆናቸው፣ ሕወሃቶች መለስ ዜናዊ የወሰነውን አንሽርም በማለትና እነ እስክንደር ላይ የግል ጥላቻ ስላላቸው ብቻ፣ ምንም አይነት ወንጀል ሳይሰሩና ሳይፈጽምሙ፣ እነ እስክንደር፣ አንዱዋለም፣ ናታናኤል የመሳሰሉት፣ ይኸው ለአራት አመታት ከልጆቻቸው ተለይተው መከራና ስቃይ እየተቀበሉ ነው። ሕጻን ናፍቆት እስክንድርም አባቴ መቼ ይሆን የሚፈታው እያለ መጠበቁን ቀጥሏል።
እስክንደር ነጋ ጀግና ኢትዮጵያዊ ነው። ወንጀሉ አገሩን መዉደዱ ነው። ወንጀሉ ለመብት መቆሙ ነው። ወንጀሉ ገዢዎች የሚፈጸሙትን በደልና ግፍ ማጋለጡ ነው። ወንጀሉ አደርባይና ለሆዱ ያደረ ጋዜጠኛ አለመሆኑ ነው።
እስክንድር ነጋና ሌሎች በእሥር ቤት እስካሉ ድረስ ትግሉ ይቀጥላል !!!!!
ሰርጎ ገብ ጋዜጠኛ መለካም ሞላ
Read Time:2 Minute, 10 Second
6 people like this.
- Published: 9 years ago on July 10, 2015
- By: maleda times
- Last Modified: July 10, 2015 @ 3:53 pm
- Filed Under: Ethiopia
Average Rating