www.maledatimes.com የአፄ ሀይለ ሥላሴ እናት ማን ናቸዉ? - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የአፄ ሀይለ ሥላሴ እናት ማን ናቸዉ?

By   /   July 24, 2015  /   Comments Off on የአፄ ሀይለ ሥላሴ እናት ማን ናቸዉ?

    Print       Email
0 0
Read Time:3 Minute, 9 Second

ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ የሚለዉ መጽሐፍ ላይም ይሁን በማንኛዉም አጋጣሚ ልጃቸዉ ቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ የእናታቸዉን ፎቶግራፍ አሳይተዉም ሆነ የአባት ስም ተናግረዉ አያዉቁም። ታሪክ ጸሐፊዎችም በመፍራት ሊሆን ይችላል የቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴን የአባት ወላጆች ሲዘረዝሩ የእናታቸዉን አባት ስም ግን አይጠቅሱም። የሚገርመዉ ደግሞ ከልጃቸዉ ህልፈተ ሕይወትም በሗላ የእናታቸዉን አባት ስም በጽሑፍ ወይም በይፋ ለመጥቀስ ብዙዎች እስካሁን አልደፈሩም። ስለኾነም በምንም ይፋ ነገር ላይ የወይዘሮ የሺ እመቤት (የአፄ ሀይለ ሥላሴ እናት) ምስል ለሕዝብ አልተናኘም። ወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስ ወይም ወይዘሮ ቂቶ የወይዘሮ የሺ እመቤት እናት ቁመታቸዉ አጭር ሲሆን ብስል ቀይና በጣም ዉብ የሆኑ ሴት ነበሩ። ትዉልዳቸዉም የስልጤ ጉራጌ ናቸዉ ይባላል። ከአንዲት ጉራጌ የሚወለድ ልጅ ትልቅ ንጉስ ይሆናል የሚል ትንቢት ስለነበረ የሸዋ መኳንንት ሁሉ የጉራጌ ሚስት እየፈለገ ያገባ ነበር። በተለይ የወለኔ ሴቶች ቆንጆዎች ስለነበሩ ብዙ መኳንንቶች ተረባርበዉባቸዋል። ወለኔ ወሊሶ ከተማ አጠገብ ያለ አገር ሲሆን ነዋሪዎቹ ጉራጌዎች መልካቸዉ ቀያይና ቆንጆዎች ስለሆኑ ይመረጡ ነበር። የመኳንንቶቹ አማራ ሚስቶች በቅናት ጉራጌዎቹን ሴቶች “ምርኮኞች” ይሏቸዉ ነበር። ራስ ዳርጌ ወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስን በይፋ ሚስትነት ሳይሆን በዕቁባትነት አስቀምጠዉ ሦስት ልጆች ወልደዋል። ይሁንና ወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስ ሌሎች ልጆችም ከተለያዩ ሰዎች ወልደዋል።

ራስ ዳርጌ በምርኮ ጎንደር ሄደዉ በእስር ብዙ አመት ከቆዩ በሗላ ተለቀዉ ሸዋ ላይ ለመሾም በደጅ ጥናት ላይ እንዳሉ አንዱ ወንድማቸዉ አቤቶ ሠይፉ ሣህለ ሥላሴ ከእስር ቤት አመለጠ። እርሳቸዉም ከዚሁ ሁኔታ ጋር በተያያዘ መልኩ ስለተጠረጠሩ መቅደላ ላይ ታስረዉ ነበር። አፄ ቴዎድሮስ ሸዋ ላይ ራስ ዳርጌን ለመሾም አስበዉ አንድ ቀን አስጠርተዋቸዉ “ልፈታህ ነበር ግን ፈራሁህ!” አሏቸዉ ይባላል። አፄ ቴዎድሮስ የሸዋ እስረኞችን ብቸኝነት ተመልክተዉ አዘኑና ሚስቶቻቸዉ እንዲጠይቋቸዉ ስለፈቀዱ ራስ ዳርጌ ወለተ ጊዮርጊስ ትምጣልኝ አሉ።

ወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስ ራስ ዳርጌን ለመጠየቅ ወደ መቅደላ ለመሄድ በወረኢሉ በኩል ሲጓዙ በእንግድነት ዘመድ ቤት ያርፋሉ። በዚህ መሃል ደጃዝማች ዓሊ ጋምጮ የሚባል የወረኢሉ ተወላጅ የነድድና የካቤ ወረዳ ባላባት የሙስሊም ሃይማኖት ተከታይ የኾነና በጠገራ ብሩ ብዛት እጅግ የታወቀ ሃብታም የወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስን ቁንጅና በመመልከት እንደሚስት ያስቀምጣቸዋል። እርሳቸዉም የሺ እመቤትን (የአፄ ሀይለ ሥላሴ እናት)ና ልክምየለሽን ከዓሊ ጋምጮ ወለዱ። ወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስ ካስቀመጣቸዉ ዓሊ ጋምጮ ኮብልለዉ ወደ ሸዋ ተመለሱና ሸዋን በወቅቱ ያስተዳድሩ የነበሩት በዛብህ አባድክር ስለነበሩ እሳቸዉም የወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስን ቁንጅና በመመልከት እንደ ዕቁባት አስቀምጠዋቸዉ። በመሃሉ ከደጃች በዛብህ ሌላ ወንድ ልጅ ወለዱና ስሙም ማሞ ተባለ። ምኒልክ ወደ ሸዋ ሲመጡ የአፄ ቴዎድሮስ እንደራሴ የነበሩት በዛብህ አባድክር አላስገባም ብለዉ ተዋግተዉ ድል ሆኑና ተማረኩ። አፄ ምኒልክም የሸዋ ንጉሥ ሲሆኑ ደጃች በዛብህ ከእስር አምልጠዉ በድጋሜ ተዋጉና ተይዘዉ ሞቱ። በዚህን ጊዜ የተቀመጡበት አልጋ በጥይት እሳት ተያይዞ ሬሳቸዉ ጭምር ነደደ። ይህን አስመልክቶ ሕዝቡ የሚከተለዉን ገጠመ።

አንተም ክፉ ነበርክ ጨካኝ አዘዘብህ
እንደ ገና ዳኖ እሳት ነደደብህ።

ራስ ዳርጌም አፄ ቴዎድሮስ ሲሞቱ ከታሰሩበት ከመቅደላ ተለቀዉ ይመለሱና ወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስ አግኝተዉ እንደገና አብረዉ መኖር ጀመሩ። ይሁንና ወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስ ከተለያዩ ሰዎች ልጆች ወልደዉ ስለጠበቁዋቸዉ መኖሪያቸዉ ከመጀመሪያዉ አጥር ጊቢ መሆኑ ቀርጦ በሁለተኛዉ አጥር ግቢ ቤት ሠርተዉ አስቀመጧቸዉ። ከወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስ የተወለዱት ሴት ልጆች አድገዉ ልክምየለሽ ግራዝማች ባንተ አይምጣን አግብታ ሦስት ወንዶች ልጆች ወለደች። እነሱም በላይ፣ ተፈሪና ከበደ ናቸዉ። የሺ እመቤት ደግሞ ለራስ መኮንን ተዳረች። የራስ መኮንን ባለቤት ወይዘሮ የሺ እመቤት እንደ እናቷ ቀይ፣ ጠጉርዋ ሉጫና መልከ ቀይ ነበረች። የሺ እመቤት ዓሊ ከራስ መኮንን በተደጋጋሚ ልጅ እየወለደች ሲሞትባትና ስትሰቃይ ቆይታ መጨረሻ ላይ ተፈሪን (አፄ ሀይለስላሴን) ወለደች። ቀጥሎም ለስምንተኛ ጊዜ ነፍሰጡር ሆና በወሊድ ምክንያት ሞተች።

የተፈሪ እናት ወይዘሮ የሺ እመቤት በአንድ ወገን ከጉራጌነ አማራ የተወለዱ ሲሆን በሌላ ወገን ከወረኢሉ ተወላጅ ከደጅአዝማች ዓሊ ጋምጮ እንደኾነ ቢነገርም ጃንሆይ ግን ስለ እናታቸዉ አባት ዝምታን መርጠዉ የወላጅ እናታቸዉን ታሪክ እንዲታወቅ አላደረጉም። ዓሊ የምትለዉን ስም ጃንሆይ ለመጥቀስ ያልደፈሩበት ምክንያት ልጅ ኢያሱን የወነጀሉበት ጉዳይ ራሳቸዉንም እዳይመለከታቸዉ በመፍራት ይሆናል። እንዲያዉም ጃንሆይን ይኸ ሁኔታ ከልጅ ኢያሱ በላይ የከበባቸዉ ይመስላል። ይኸዉም የሴት አያታቸዉ አባት ስም ሁሴን፣ የእናታቸዉ አባት ስም ዓሊ፣ የባለቤታቸዉ አያት ስም ዓሊ ቡንኝ የአፋር ተወላጅ በመሆናቸዉ ነዉ።

ተፈሪ መኮንን ገጽታቸዉ እናታቸዉን ይመስላሉ የሚሉ ሰዎችም ነበሩ። ከጣሊያን ወረራ በሗላ ጃንሆይ የእናታቸዉን ፎቶግራፍ ከየዘመዶቻቸዉ ያፈላልጉ እንደነበርና ለሚያቀርብላቸዉም ሰዉ የገንዘብ ወሮታ ለማድረግ ሞክረዉ ነበር ይባላል። የወይዘሮ የሺ እመቤት ፎቶግራፍ ይኑር አይኑር በእርግጠኝነት ባይታወቅም የተወሰኑ ሰዎች እጅ እንደሚገኝ አንዳንድ ፍንጭ ተሰምቶ ቢጠየቁም ሰዎቹ ግን ፎቶግራፉን ለማሳየትም ኾነ አለመኖሩን ለማረጋገጥ ፈቃደኛ አልሆኑም።
ምንጭ፡ ጥላሁን ብርሃነ ሥላሴ “የ20ኛዉ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ” አንደኛ መጽሐፍ (ገጽ 128-133)

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 9 years ago on July 24, 2015
  • By:
  • Last Modified: July 24, 2015 @ 11:41 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar