‹‹መንግሥት ባለበት አገር በጠራራ ፀሐይ ቤቴን ተቀማሁ›› ወ/
ሮ ዘውዴ ወልደማርያም፣ የየካ ክፍለ ከተማ ነዋሪ
የዛሬ ‹‹ምን እየሠሩ ነው?›› ዐምዳችን እንግዳ ወ/ሮ ዘውዴ
ወልደማርያም ይባላሉ፡፡ ዕድሜያቸው 70 መሆኑን ይናገራሉ፡፡
የሚኖሩት በየካ ክፍለ ከተማ በቀድሞ ቀበሌ 11/12 ወይም
በአሁኑ ወረዳ ሰባት ውስጥ ነበር፡፡ ወ/ሮ ዘውዴ በ2001 ዓ.ም.
በ1,700,000 ብር የገዙትን ቤት ላለፉት ስድስት ዓመታት
የኖሩበት ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉም ባይሆን የተወሰነ ግንባታ
አካሂደውበታል፡፡ በቆርቆሮና እንጨት ታጥሮ የነበረን ግቢ፣
በግንብ ዙሪያውን ከሠሩና ሰርቪስ ቤቶችን ካደሱ በኋላ፣ ዋናውን
ቤት ለመሥራትም ዲዛይንና የግንባታ ፈቃድ አግኝተው ነበር፡፡
ቤቱን ሲገዙ አስፈላጊ ናቸው የተባሉ ሕጋዊ ሰነዶችን
ከመንግሥት ተቋማት ያገኙ ቢሆንም፣ ከስድስት ዓመታት ቆይታ
በኋላ ‹‹የገዙት ቤት ይዞታነቱ የሌላ ሰው ነው፡፡ ከእርስዎ ቀደም
ብሎ በ1985 ዓ.ም. ለሌላ ሰው ተሸጧል፡፡ በመሆኑም
አስረክበው እንዲወጡ›› የሚል የፍርድ ቤት ትዕዛዝ
ይደርሳቸዋል፡፡ በሁኔታው የተደናገጡት ወ/ሮ ዘውዴ፣ ወደ ፍርድ
ቤት ሄደው ቢያመለክቱም እንዲወጡ ይነገራቸዋል፡፡
‹‹በሕጋዊ መንገድ የገዛሁትን ቤቴንማ ዝም ብዬ አላስረክብም››
ያሉት ወ/ሮ ዘውዴ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትን ውሳኔ
በመቃወም ይግባኝ ብለው ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይሄዳሉ፡፡
እዚያም ይወሰንባቸዋል፡፡ ተስፋ ባለመቁረጥ ወደ ሰበር ሰሚ
ችሎትም ሄደዋል፡፡ ውሳኔው ግን ሊቀለበስ አልቻለም፡፡
የመጨረሻ ጉዟቸውን ወደ ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ
ቢያደርጉም፣ ‹‹የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚያስፈልገው
አይደለም›› በሚል የሦስት መስመር ምላሽ ተስፋቸው ተሟጦ
አለቀ፡፡ መንግሥትንና የመንግሥትን ተቋማት በማመን ከልጅነት
እስከ ዕውቀት ያፈሩት ገንዘባቸው አግባብ ባልሆነ መንገድ
እንደተነጠቁ የሚናገሩት ወ/ሮ ዘውዴ፣ እግዚአብሔርና
የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደኝ ይላሉ፡፡ ታምሩ ጽጌ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የደረሰብዎት ችግር ምንድነው?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- ቤቴን በጠራራ ፀሐይ፣ መንግሥት ባለበት አገር
ተነጠቅሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ማነው የነጠቀዎት? ለምንና በምን ሁኔታ ተነጠቁ?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- በ2001 ዓ.ም. በሕጋዊ መንገድ ወ/ሮ ጽጌ
ተሾመ ከሚባሉ ሴት መኖሪያ ቤት ገዛሁ፡፡ ከመግዛቴ በፊት
ሕጋዊ መሆኑን አረጋገጥኩ፡፡ ሴትየዋ ባለትዳር ቢሆኑም
ባለቤታቸው አብረዋቸው አይኖሩም፡፡ ነገር ግን ሕጋዊ ውክልና
ያላቸው መሆኑንም ሰነድ ተመልክቼ አረጋገጥሁና ገዛኋቸው፡፡
ሪፖርተር፡- የት ክፍለ ከተማና ወረዳ ነው?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- የካ ክፍለ ከተማ ድንበሯ የእናቶችና ሕፃናት
ሐኪም ቤት አካባቢ ነው፡፡ ለገዛኋቸው ሴትዮ ክፍያ ከመፈጸሜ
በፊት፣ ወደ ክፍለ ከተማው ሄደን ስናረጋግጥ፣ በቤቱ ላይ ዕዳም
ሆነ እገዳ የለበትም፡፡ ካርታ የተሠራውም በወ/ሮ ጽጌ ስም
ነው፡፡ መሬት ልማትና አስተዳደርም ስንሄድ ከዕዳና እገዳ ነፃ
ነው፡፡ ውልና ማስረጃም ስንሄድ ከዕዳና እገዳ ነፃ ነው፡፡ ከዚያ
በኋላ አሹራ እንድከፍል ደብዳቤ ተሰጥቶኝ ለመሬት ልማትና
አስተዳደር 103,000 ብር አሹራ ከፍዬ ካርታው በእኔ ስም
ዞረልኝ፡፡
ሪፖርተር፡- በስንት ነው የገዙት?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- ቤቱን የገዛሁት 1,700,000 ብር ነው፡፡ ስፋቱ
449 ካሬ ሜትር ነው፡፡ ሕጋዊነቱን አረጋግጨ፣ ይዞታነቱ የእኔ
ለመሆኑ ማረጋገጫውን ማለትም ካርታውን በስሜ አዙሬ
ስጨርስ፣ የነበረውን የቆርቆሮና የጽድ አጥር አፍርሼ ዙሪያውን
በድንጋይ ግንብ አጠርኩ፡፡ የፍሳሽ ማስወገጃ ካስገባሁ በኋላ
ግቢውን በድንጋይ አስነጠፍኩ፡፡ ይኸንን ሁሉ ያደረግኩት ዝም
ብዬ ሳይሆን ቤቱ የሚገኝበትን ወረዳ ሰባት አስፈቅጄና የግንባታ
ፈቃድ ወስጄ ነው፡፡ ዋናውን ቤት ተውኩና ሰርቪሶቹን
አደስኳቸው፡፡ ሌላ ገቢ ስለሌለኝ እነሱን አከራይቼ እየኖርኩ
እያለሁ ክስ መጣብኝ፡፡
ሪፖርተር፡- የምን ክስ ነው የመጣብዎት?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- ‹‹የገዛሺው ቤት ለሌላ ሰው የተሸጠ ቤት ነው፡፡
በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክስ ስለተመሠረተብሽ
ትፈለጊያለሽ›› ተባልኩኝ፡፡ በደረሰኝ ጥሪ መሠረት የመጀመሪያ
ደረጃ ፍርድ ቤት ስሄድ፣ ‹‹ቤቱ በ1985 ዓ.ም. ተሸጧል››
ተባልኩኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ለማንና በስንት ብር ነው የተሸጠው?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- ቤቱ የተሸጠው ወ/ሮ አልማዝ ተሰማ ለሚባሉ
ግለሰብ ሲሆን፣ ነዋሪነታቸው ጣሊያን አገር ለሆኑ የኤርትራ ዜጋ
በ160,000 ብር ተሸጧል፡፡ ሻጭ ወ/ሮ ጽጌ ተሾመ ቀብድ
88,000 ብር ተቀብለዋል፡፡ 60,000 ብር ይቀራቸዋል
ተባልኩኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ምን ምላሽ ሰጡ?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- እኔ ማጣራት ያለብኝን ሁሉ አጣርቼ ቤቱ ከዕዳና
እገዳ ነፃ መሆኑን አረጋግጨ በ1,700,000 ብር ገዝቻለሁ፡፡
የመጨረሻው አጣሪ የመንግሥት ተቋም ውልና ማስረጃም
ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለበት አረጋግጦልኝ የይዞታ
ማረጋገጫ ካርታ በስሜ ዞሮ ቤቱ የእኔ ነው፡፡ አሁን የመጣብኝ
ነገር ምንም የማላውቀው ዱብ ዕዳ በመሆኑ ቀጠሮ ይስጠኝ
ብዬ አስቀጥሬ ተመለስኩኝ፡፡ ቤቱን ገዝተዋል የተባሉት
ኤርትራዊቷ ወ/ሮ አልማዝ፣ የሚከራከሩት በወኪል ነው፡፡
በቀጠሮው ቀን ስንቀርብ፣ የፍርድ ቤቱ ዳኛ ወኪሎቹን
‹‹ምንድነው የምትፈልጉት?›› የሚል ጥያቄ አነሱላቸው፡፡
‹‹ቦታውን የገዛነው በ1985 ዓ.ም. ከማኅበሩ ነው፡፡ ውላችንም
በማኅበሩ አማካይነት የተደረገ ውል ነው፡፡ ቦታውን እንፈልጋለን፡፡
ቦታውን የማናገኝ ከሆነ የተሸጠበትን ዋጋ እንፈልጋለን›› አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ቤቱ የተሠራው በማኅበር ነው?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- አዎ ቤቱ የተሠራው በማኅበር ነው፡፡ የሰማሁት
ግን የወ/ሮ አልማዝ ወኪሎች በፍርድ ቤት ሲናገሩ ነው፡፡
የማኅበሩም ስም ዕድገት በኅብረት ይባላል፡፡ ወኪሎቹ ቤቱን
ወይም የተሸጠበትን ዋጋ እንደሚፈልጉ ገልጸው ተከራከሩ፡፡ ፍርድ
ቤቱ ካዳመጠ በኋላ ለፍርድ ቀጠረ፡፡ በቀጠሮው ቀን ስንቀርብ
‹‹ቤቱን ወይም የተሸጠበትን ዋጋ አስረክቡ›› ብሎ ፍርድ ቤቱ
ፈረደብን፡፡
ሪፖርተር፡- ከእናንተ በኩል የቀረበው መከራከሪያ ሐሳብ ምን
ነበር?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- ምንም ዓይነት ክርክር አላቀረብንም፡፡ ፍርድ
ቤቱም የጠየቀን ነገር የለም፡፡ የእኔ ጠበቃ ካርታ እንዳለን
አስረዱ፡፡ ቤቱን የሸጡልኝ ወ/ሮ ጽጌም አብረው ስለተከሰሱ፣
የእሳቸው ጠበቃ ‹‹ይኸ ፍርድ ቤት የዚህን ዓይነት ጉዳይ የማየት
ሥልጣን የለውም›› በማለት ተከራከሩ፡፡
ሪፖርተር፡- ፍርድ ቤቱ ምን አለ?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- ‹‹እኛ የነገርናችሁ ከፍተኛው ፍርድ ቤት
የወሰነውን እንጂ ውሳኔውን እኛ አልሠራነውም›› አለን፤ ፍርድ
ቤቱ፡፡
ሪፖርተር፡- ከፍተኛው ፍርድ ቤት የወሰነውን ውሳኔ የመጀመሪያ
ደረጃ ፍርድ ቤት የሚናገርበት የሕግ አግባብ መኖሩን
ጠይቃችኋል?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- እኔ በግሌ አላውቅም፡፡ ጠበቆቻችን ግን
ጠይቀዋል፡፡ የሻጭ ወ/ሮ ጽጌ ጠበቃ በመጠየቃቸው ነው ፍርድ
ቤቱ እንደዚህ ብሎ የተናገረው፡፡ አሠራሩ ትክክል አለመሆኑን
በመገንዘባችን ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠየቅን፡፡
ይግባኝ ያስገባንበት የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ‹‹ይኸ ነገር
አያዋጣችሁም፡፡ ቢቀርባችሁ ይሻላችኋል›› አሉን፡፡ ለምን? ብለን
ጠየቅን፡፡ ‹‹የተሸጠ ቦታ ስለሆነ እያዋጣችሁም›› አሉን፡፡
ሪፖርተር፡- ዳኛው ‹‹አያዋጣችሁም›› ያሏችሁ የሥር ፍርድ ቤት
ውሳኔን መርምረው ነው?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- አይደለም፡፡ ይግባኙን ሳይመረምሩ ነው፡፡ እኛ
ሕጋዊ ካርታ እንዳለን ገለጽንና ‹‹እንዴት ይኸ ሊሆን ይችላል››
በማለት ስንጠይቅ፣ ‹‹እኔ የዳኝነት 20,000 ብር እንዳትከስሩ
ብዬ ነው›› አሉና የይግባኙን አቤቱታ ተቀበሉን፡፡ አቤቱታችን ገና
በቀጠሮ ላይ እያለ፣ ባለመብት ነን ያሉት የሥር ፍርድ ቤት
የወሰነላቸው የወ/ሮ አልማዝ ተወካዮች፣ አፈጻጸም አምጥተው
በቤቴ ላይ ለጠፉ፡፡ ይግባኝ ጠይቀን ገና በቀጠሮ ላይ በመሆኑ፣
እግድ ለማምጣት ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ስንሄድ፣ ያስገባነው
የይግባኝ አቤቱታ ጠፍቷል፡፡ ወዲያውኑ ጉዳዩን ለሚያዩት ዳኛ
ስናመለክት ‹‹እኔ አያገባኝም፡፡ መዝገብ ቤት ከሌለ አቤቱታ
ስታስገቡ ባላችሁ ቀሪ አስገቡ›› አሉን፡፡ በድጋሚ ጽፈንና ቃለ
መሀላ አድርገን አፈጻጸሙን አሳገድን፡፡ ክርክራችንንም ቀጠልን፡፡
ሪፖርተር፡- ቤቱ በ1985 ዓ.ም. ወ/ሮ አልማዝ ለሚባሉ ግለሰብ
መሸጡን እያወቁ ወ/ሮ ጽጌ እንዴት ለእርስዎ በድጋሚ
ሊሸጡልዎት ቻሉ?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- ቤቱን እንደገዙትና 88,000 ብር ቀብድ
እንደከፈሉ ለፍርድ ቤት የሚያስረዱት ተወካዮች፣ ክስ
የመሠረቱት በእኔና በወ/ሮ ጽጌ ላይ ነው፡፡ ወ/ሮ ጽጌ በፍርድ
ቤት ያቀረቡት ክርክር፤ ቤቱን መሸጣቸውን አምነው፣ ነገር ግን
ገዢ ወ/ሮ አልማዝ ቀብዱን ከከፈሉ በኋላ፣ ለሁለት ዓመታት
በመጥፋታቸው ክስ መሥርተው በፍርድ ቤት ውሳኔ
ማግኘታቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ውሳኔ ያገኙትም
በመጀመሪያና በከፍተኛ ፍርድ ቤት መሆኑንም ለፍርድ ቤቱ
አረጋግጠዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ወ/ሮ ጽጌ የሥር ፍርድ ቤቶች የወሰኑላቸው ለመሆኑ
የሚያስረዳውን የውሳኔ ሰነድ እርስዎ አይተውታል?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- ለእኔ አላሳዩኝም፡፡ ለፍርድ ቤቱ ግን
‹‹አቅርቤያለሁ›› ብለውኛል፡፡ ባለይዞታ ነን ባዮቹ የወ/ሮ
አልማዝ ተወካዮች፣ ሰበር ደርሰው ማስወሰናቸውንም የሰማሁት
ቆይቼ ነው፡፡ እኔ በቀጠሮዬ ቀን ከፍተኛው ፍርድ ቤት ስቀርብ፣
መጀመሪያውኑ ገና አቤቱታውን ሳያዩ ‹‹አርፋችሁ ተቀመጡ››
ያሉኝ ዳኛ ‹‹አስረክቡ›› ብለው ወሰኑብኝ፡፡ ተስፋ ባለመቁረጥ
ወደ ሰበር ሄድን፡፡ ቤቱ የተሸጠ መሆኑንና የተሸጠ ቤት እንዴት
ልንገዛ እንደቻልን ሦስት ዳኞች ጠየቁን፡፡ መንግሥት
ባስቀመጣቸው ተቋማት ማለትም በወረዳ፣ በመሬት ልማትና
አስተዳደር እንዲሁም በውልና ማስረጃ አረጋግጠን፣ ከዕዳና
እገዳ ነፃ መሆኑን ስናውቅ እንደገዛነው ሙሉና ሕጋዊ ሰነዱን
አሳይተን ምላሽ ሰጠን፡፡ ሦስቱ ዳኞች ምላሻችንን አዳምጠው
‹‹ያስቀርባል›› በማለት አምስት ዳኞች እንዲያዩት ተለዋጭ
ቀጠሮ ሰጡን፡፡ በቀጠሮው ቀን ስንቀርብ ቤቱን ከሸጡልኝ ከወ/
ሮ ጽጌ፣ በ1985 ዓ.ም. ቤቱን ገዝተዋል የተባሉት ወ/ሮ
አልማዝ፣ ቀሪውን 60,000 ብር እንዲከፍሉ፣ እኔ ደግሞ ለወ/ሮ
አልማዝ የቤቱን ካርታ አስረክቤ እንድለቅ ውሳኔ ተሰጠብን፡፡ እኔ
ከቤቴም ሆነ ከገንዘቤ ሳልሆን አስረክቢ ተባልኩኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ቤቱን አስረከቡ?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- እኔ በሌለሁበት ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም.
በግዳጅና በጉልበተኛ ዕቃዬ እየተወረወረ እንድለቅ ተደረገ፡፡ እኔ
ሕገወጥ ሰው አይደለሁም፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ
እንደሚያደርገው የመንግሥት ተቋማት የሚሰጡትን ማረጋገጫ
ይዤ፣ ልጆቼን ለማሳደግ ያለኝን ጥሪት በሙሉ አሟጥጨ
የገዛሁትን ቤት፣ እንዴት እነጠቃለሁ? ለስድስት ዓመታት በስሜ
ግብር ከፍያለሁ፡፡ ቤቱን አልምቸዋለሁ፡፡ በዋናው ቤት ላይ ፎቅ
ለመገንባት ዲዛይን አሠርቼና የግንባታ ፈቃድ ወስጄ ነበር፡፡
ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አውጥቼበታለሁ፡፡ ይኸንን
ደግሞ የወረዳው ሹማምንት ያውቃሉ፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱን
እንቅስቃሴ ያደረግኩት እነሱን እያማከርኩና ፈቃድ እየወሰድኩ
ነው፡፡ ግንባታ ለማካሄድ ድንጋይና አሸዋም አስገብቼ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን በምን ሁኔታ ላይ ነው ያሉት?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- እኔ ቤቱን ከገዛሁት በኋላ ከሁለት ሚሊዮን ብር
በላይ ውጪ አውጥቼበታለሁ፡፡ የሸጡልኝ ሴትዮ ገንዘቤን
እንዲመልሱልኝና ባለይዞታ ነን ባዮቹም በቤቱ ላይ ያወጣሁትን
ወጪ እንዲከፍሉኝ ክስ መሥርቻለሁ፡፡ ክሱን የመሠረትኩት ሰበር
የወሰነው ውሳኔ ወደ አፈጻጸም ሳይሄድ በመሆኑ፣ አፈጻጸም
ይዘው መጥተው ንብረቴን ወደ ውጭ እየወረወሩ በጉልበት
ሲያስወጡኝ፣ የፍርድ ቤት ክርክር ያለበት ንብረት መሆኑን
በመግለጽ፣ ለፍርድ ቤት አመልክቼ ክርክሩ እስከሚጠናቀቅ
ድረስ እንዳይሸጥ፣ እንዳይለወጥና ለሦስተኛ ወገን
እንዳይተላለፍ ታግዳ በቀጠሮ ላይ ነን፡፡ ዕድሜዬ ገፍቷል፡፡ 70
ዓመቴ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ተሯሩጨ የማድር ሴት አይደለሁም፡፡
በመጦሪያዬ አሁን ያለሁት በዘመድ ላይ ነው፡፡ ወዴትስ ልሂድ?
እኔ ዜጋ ነኝ፡፡ ከ20 ዓመት በኋላ እውነተኛ ሴት ትሁን አትሁን
በማላውቃትና ኑሮዋን ጣሊያን አገር አድርጋለች በተባለች
የኤርትራ ዜጋ አማካይነት፣ በሕገወጥ መንገድ በመንገድ ላይ
ተጣልኩ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደኝ፡፡ ሕጋዊ ካርታ በእጄ ላይ
ይዤ እንዴት መንግሥት ባለበት አገር ቤቴን እነጠቃለሁ?
የመጨረሻው የመንግሥት አካል የሕገ መንግሥት ጉዳዮች
አጣሪ ጉባኤ እንዲያይልኝ ባመለከትም የተሰጠኝ መልስ አሳዛኝ
ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ምን አልዎት?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- ጉባኤው ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም.
ባደረገው ስብሰባ፣ አቤቱታውን ተመልክቶ የቀረበው ጥያቄ የሕገ
መንግሥት ትርጉም የሚያስፈልገው እንዳልሆነ ገልፆ ውሳኔ
ማሳለፉን አሳወቀኝ፡፡ አሁን ያለሁት ጐዳና ላይ ነኝ፡፡ ሕግና
መመሪያ ተከትዬ ትልቅ ችግር ላይ ወደቅሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ
የቀበሌ ቤት በሌለበት፣ ኮንዶሚኒየም ለመግዛት አቅሜ
በማይፈቅድበት ሁኔታ ላይ ሆኜ፣ ይኸ ተፈጸመብኝ፡፡ ልጆቼን ይዤ
ጐዳና ላይ ተጣልኩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምን
ጨምሮ ይመለከታቸዋል ላልኩት ሰባት ሚኒስቴሮች በአፋጣኝ
መልዕክት እየከፈልኩ በፖስታ ቤት ደብዳቤ ብልክም፣ ምንም
ምላሽ አላገኘሁም፡፡ ሰባት የፖስታ ቤት ደረሰኝ በእጄ ላይ
ይገኛል፡፡ እኔ አቅመ ደካማ ሴት ነኝ፡፡ ኢትዮጵያዊት ዜጋም ነኝ፡፡
ሁሉም ማስረጃዎቼ ትክክለኛና ከመንግሥት ተቋማት የተሰጡኝ
መሆናቸው እየታወቀ፣ እንዴት ቤቴን አስረክቢ እባላለሁ?
የሚያሳዝነኝ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ሰበር ሰሚ ያሉት ፍርድ
ቤቶች በአንድ ዓይነት ንብረቴን ልቀቂ ማለታቸው ነው፡፡ ይኸ
ወገንተኝነት ነው፡፡ እንዴት አንዱ ዳኛ ቆም ብሎ ማስረጃዎቹን
ተመልክቶ ለእኔ አይፈርድም፡፡ እኔ ወገን የለኝም፡፡ ሥልጣን ላይ
የተቀመጠ ዘመድ ቢኖረኝ ኖሮ እንደዚህ አልሆንም ነበር፡፡
ምናልባት ቤቱን በ1985 ዓ.ም. ገዝተዋል የተባሉትና በጣሊያን
ይኖራሉ የተባሉት ወ/ሮ አልማዝ ዘመድ ሊኖራቸው ይችላል፡፡
እሳቸው ባልተገኙበትና አንድ ቀን እንኳን የፍርድ ቤትን ደጃፍ
ሳይረግጡ፣ የተወሰነላቸው ምናልባት ባለሥልጣን ዘመድ
ቢኖራቸው ይሆናል፡፡ በተለይ ሰበር ሰሚ ችሎት ጐድቶኛል
(እያለቀሱ)፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ይፍረደኝ፡፡
በተደጋጋሚ በተወሰነብኝ ውሳኔ ላይ የአንድ ዳኛ ስም በማየቴ
ምናልባት እኝህ ዳኛ የወ/ሮ አልማዝ ዘመድ ሊሆኑ ይችላሉ
የሚል ግምት አድሮብኛል፡፡ አለበለዚያ ከ20 ዓመት ቆይታ
በኋላ፣ ግብር ባልገበሩበትና ይርጋ ባገደው ንብረት ላይ ወ/ሮ
አልማዝ ባለንብረት ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ወ/ሮ ጽጌና ወ/ሮ
አልማዝ ተካሰው የሥር ፍርድ ቤቶች ለወ/ሮ ጽጌ ወስነዋል፡፡
ወ/ሮ አልማዝ ደግሞ በይግባኝ ሰበር ሄደው አስወስነዋል፡፡ እኔ
ጥያቄ ሲመጣብኝ ክስ ስመሠርት በሁለቱ ሰዎች ላይ የነበረው
የፍርድ ቤቶቹ ውሳኔ ከእኔ ክስ ጋር እንዲያያዝ በማድረግ፣ ከሥር
ጀምሮ እስከ ሰበር በእኔ ላይ የተወሰነው ውሳኔ በእነሱ ላይ
የነበረው ውሳኔ እየተጠቀሰ አንድ ዓይነት ነው፡፡ ይኸ የተደረገው
ክርክሩን ሕጋዊ ለማስመሰል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ለእርስዎ ቤቱን የሸጡልዎት ወ/ሮ ጽጌ፣ ቀደም
ብለው ቤቱን ለሌላ ሰው መሸጣቸውንና የፍርድ ቤት ክርክርም
እንደነበረበት ነግረዎት ነበር?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- በፍፁም፡፡ ባለቤታቸው ውክልና እንደሰጧቸው፣
ካርታው በእሳቸው የተሠራ መሆኑን ሰነድ እያሳዩ
አረጋግጠውልኛል፡፡ ስንዋዋልም ማንኛውንም በመንግሥት
በኩል የሚመጣን ተጠያቂነት ኃላፊነት እንደሚወስዱ ሁሉ
አረጋግጠውልኛል፡፡ እኔን ሜዳ ላይ እንድወድቅ ያደረገኝ፣
ያታለለኝ ውልና ማስረጃ፣ ሁሉንም ነገር መርምሮ ከዕዳና እገዳ
ነፃ መሆኑን ገልፆ የሰነድ ማረጋገጫ የሰጠኝ ጊዜ ነው፡፡
ለሴትየዋም ካርታ እንዲሰጣቸው ሁሉንም ነገር አረጋግጦ
የሰጣቸው ውልና ማስረጃ ነው፡፡ ስገብርበት የኖርኩትን፤
ከልጅነት እስከ ዕውቀት የያዝኩትን ጥሪት ሙጥጥ አድርጌ
የወጣሁበትን ቤት ተነጠቅሁ፡፡
ባለሥልጣን ዘመድና ወገን ቢኖረኝ ምላሽ እንዲሰጠኝ እንደዚህ
አልሆንም፡፡ እናት ያለው ባለሥልጣን እንደ እናቱና እንደ እህቱ
አይቶ፣ ሁኔታዬንና ሕጋዊነቴን ገልጨ ብጽፍ ማንም ምላሽ
የሰጠኝ የለም፡፡ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ፣ ከአገር ውጭም
ያላችሁ ፍረዱኝ፡፡ ፍረዱኝ፡፡ ባለቤት ነኝ ካሉ ግብር መገበር
ነበረባቸው፡፡ መሸጡን ሲሰሙም ማሳገድ ይችሉ ነበር፡፡
የባለቤትነት መታወቂያ ሳይኖራቸው በአሁኑ ጊዜ ቢሸጥ
ከአምስት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቤቴን፣ እሳቸው በውጭ
አገር ተቀምጠው (ወ/ሮ አልማዝ) ወሰዱብኝ፡፡ የኢትዮጵያ
ሕዝብ ፍረደኝ፡፡ መብቴ ተገፈፈ፡፡ እኔ አርጅቻለሁ፡፡ ሠርቼ እንኳን
መኖር አልችልም፡፡ ቀን ቀን ቤተ ክርስቲያን ውዬ እስካለሁ ድረስ
ገብቼ እንዳላርፍበት ጉድ ሠሩኝ፡፡ ምን ልሁን፡፡ እኔ ተዘረፍኩ፣
ተነጠቅሁ እንጂ በሕግ አግባብ ተወሰነብኝ አልልም፡፡ እኔ እዚሁ
ሆኜ ሽቅብና ቁልቁል ተሯሩጨ ፍትሕ ሳጣ፣ ወ/ሮ አልማዝ
በውጭ ቁጭ ብላ ተወሰነላት (እውነት አልማዝ የምትባል ሴት
ኖራ ከሆነ)፡፡ ፍትሕ አጥቻለሁ፡፡ ጥፋቴ ምንድነው? የውልና
ማስረጃ ሥራ ምንድነው? ዜጐች እንዳይታለሉ የተጭበረበሩ
ሰነዶችን በመለየት ዜጐችን ከአደጋ መጠበቅ አይደለም? እኔም
ይኸንን አምኜ ሕጋዊነቴን ለመጠበቅ በመሔዴ ፍትሕ ማጣት
አለብኝ?፣ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይፍረደኝ፡፡ መሬት አስተዳደርስ ቢሆን
ሥራው ምንድነው? ሕጋዊ ካርታ እንዳለኝ አምኖና አረጋግጦ፣
ያቀረብኩትን ዲዛይን ተቀብሎ የግንባታ ፈቃድ ከሰጠኝ በኋላ፣
እንዴት ለሌላ ሰው ሊሰጥ ቻለ? የግንባታ ግብዓቶች አስገብቼ
ከጨረስኩ በኋላ አስቆፍሬ ግንባታ ለመጀመር ቀናት ሲቀሩኝ
ተፈረደብኝ፡፡ ይኸ ምን ማለት ነው? ፍረዱኝ፡፡ ከትውልድ
ትውልድ የሚተላለፍ ግፍ ነው የተፈጸመብኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ቤቱን የሸጡልዎት ወ/ሮ ጽጌ ገንዘብዎን
እንዲመልሱልዎት አልጠየቋቸውም?
ወ/ሮ ዘውዴ፡- ‹‹እኔ የሸጥኩልሽ በሕጋዊ መንገድና ሕጋዊ ቤት
ነው፡፡ ሕጋዊ ለመሆኑም ውልና ማስረጃ እንዲሁም መሬት
ልማት አስተዳደር አረጋግጠውልሻል፡፡ ከዚህ ውጭ የእኔ ጥፋት
ምንድነው?›› ብለው ምላሽ ሰጡኝ፡፡ ገንዘቡንም ታመው
እንደታከሙበት በመግለጽ እንደሌላቸው ነግረውኛል፡፡ እኔ ግን
ክስ መሥርቻለሁ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ አጥር ለማጠር፣ ሰርቪሶችን
ለማደስና ግቢውን ለማስነጠፍ ያወጣሁትን ወጪ እንኳን
ለማግኘት ብዬ፡፡ ምን ላድርግ? ግራ ግብት አለኝ፡፡ ወዴትስ
ልሂድ? ማንስ ይቀበለኛል? እግዚአብሔር የኢትዮጵያ አምላክ
ይፍረደኝ፡፡ ውልና ማስረጃ ያረጋገጠው ካርታ ሊሰረዝ
አይገባም፡፡ ቤት ስታከራዩ፣ መኪና ስትገዙና ቤት ስትገዙ ውልና
ማስረጃ ሄዳችሁ ተዋዋሉ ተብሎ በመንግሥት ተነግሯል፡፡ እኔም
ይኸንን ፈጽሜ ኦርጂናል የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ
ተሰጥቶኛል፡፡ ይኸ ሊሰረዝ አይገባም፡፡ ለእሷም (ለወ/ሮ
አልማዝ) እስካሁን የተቀመጠ ገንዘቧን ወ/ሮ ጽጌ ይመልሱላት፡፡
መንግሥት ይርዳኝ፤ ያስመልስልኝ፡፡ በሥር ያሉ ኃላፊዎች ወይም
አስፈጻሚዎች እየሠሩ ያሉትን ግፍ መንግሥት ይመልከትልኝ፡፡
በጠራራ ፀሐይ ቤቴ ተወስዶብኛልና መንግሥትም፣ ሕዝብም
የሁሉ የበላይ የሆነ እግዚአብሔር ፍረዱኝ፡፡ የኢሕአዴግ
መንግሥት እኔን አልበደለኝም፡፡ እሱ ያስቀመጣቸው አንዳንድ
ቦታ ላይ ያሉ የሕዝብን ኑሮሮ የሚያንቁ አሉ፡፡ እነሱን
ይመልከትልኝ፡፡ መንግሥት ቤት ለሌለው ኮንዶሚኒየምና
እንደየአቅሙ እየሰጠ ባለበት፣ እንዲሁም በተለይ ሴቶችን
በማደራጀት እንዲበረታቱ እያደረገ ባለበት ሁኔታ፣ እኔንና እኔን
መሰሎችን ከመኖሪያቸው እያስወጡ በጐዳና ላይ የሚጥሉ አሉ፡፡
በእነሱ ላይ መንግሥት ውሳኔ ሊሰጥ ይገባል፡፡ መንግሥት
ቢያልፋቸው የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ እግዚአብሔር ፍርድ
ይሰጣል (እያለቀሱ)፡፡
‹‹መንግሥት ባለበት አገር በጠራራ ፀሐይ ቤቴን ተቀማሁ›› ወ/ ሮ ዘውዴ ወልደማርያም
Read Time:10 Minute, 33 Second
- Published: 9 years ago on August 3, 2015
- By: maleda times
- Last Modified: August 3, 2015 @ 8:39 am
- Filed Under: Ethiopia
Average Rating