(ሰበር ዜና) ካንጋሮው ፍርድ ቤት በነአቡበከር ላይ እስከ 22 ዓመት እስራት ፈረደ
ፍርድ ቤቱ በነአቡበከር ላይ እስከ 22 ዓመት እስራት ፈረደ (ዘ-ሐበሻ) ካንጋሮው ፍርድ ቤት በሚል በብዙሃን የሚተቸው የሕወሓት መንግስት ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የወንጀል ችሎት ሰሚት ምድብ በእነ አቡበክር አህመድ የክስ መዝገብ የተጠቀሱ 18 ተከሳሾችን ዛሬ ከ7 አመት እስከ 22 አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ፈረደባቸው:: በዛሬው ዕለት በካንጋሮው ፍርድ ቤት የቀረቡት የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት 1.አቡበከር አህመድ 2.አህመዲን ጀበል 3.ያሲን ኑሩ 4.ካሚል ሸምሱ 5.በድሩ ሁሴን 6.ሼህ መከተ ሙሄ 7.ሳቢር ይርጉ 8.መሃመድ አባተ 9.አህመድ ሙስጠፋ 10.አቡበከር አለሙ 11.ሙኒር ሁሴን 12.ሼህ ሰኢድ አሊ ጁሃር 13.ሙባረክ አደም 14.ካሊድ ኢብራሂም 15.ሙራድ ሽኩር 16.ኑሩ ቱርኪ 17.ሼህ ባህሩ ኡመር 18.የሱፍ ጌታቸው የነበሩ ሲሆን ፍርድ በሽብር ወንጀል ጥፋተኛ ብሏቸዋል:: 22 ዓመት የተፈረደባቸው 1ኛ. አቡበክር አህመድ 2ኛ.አህመዲን ጀበል 3ኛ. ያሲን ኑሩ 4ኛ. ከሚል ሸምሱ ሲሆኑ በሽብር ወንጀሉ ከፍተኛ ተሳታፊ ነበሩ ሲል ፈርዶባቸዋል:: በሌላ በኩል 18 ዓመት የተፈረደባቸው 1ኛ. ድሩ ሁሴን 2ኛ. ሳቢር ይርጉ 3ኛ. መሃመድ አባተ 4ኛ. አቡበክር አለሙ 5ኛ ሙኒር ሁሴን ናቸው:: 15 ዓመት የተፈረደባቸው 1ኛ. ሼህ መከተ ሙሄ 2ኛ. አህመድ ሙስጠፋ 3ኛ. ሼህ ሰኢድ አሊ 4ኛ. ሙባረክ አደም 5ኛ. ካሊድ ኢብራሂም ናቸው:: 7 ዓመት የተፈረደባቸው 1ኛ. ሙራድ ሽኩር 2ኛ. ኑሩ ቱርኪ 3ኛ. ሼህ ባህሩ ዑመር 4ኛ የሱፍ ጌታቸውን ናቸው:: በዛሬው ችሎት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝበ ሙስሊም ወደ ሲኤም ሲ ወደሚገኘው የቦሌ አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት በችሎቱ ለመታደም የተጓዘ ቢሆንም ፌደራል ፖሊሶች ማባረራቸው ተዘግቧል፡፡ ለዘ-ሐበሻ በደረሰው መረጃ ፍርድ ቤቱ በከፍተኛ ፖሊስ ጥበቃ ስር የነበረ ሲሆን ከቤተሰብ በስተቀር ማንኛውም ሰው ችሎቱ ውስጥ እንዳይገባ በኃይል ሰዎች ሲባረሩ እንደነበር ተጠቅሷል:: በነዚሁ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ የካንጋሮው ፍርድ ቤት ከእስራት ቅጣት በተጨማሪ ተከሳሾች ይህ ውሳኔ ከፀናበት እለት ጀምሮ ለአምስት አመታት እንዳይመርጡ ፣ እናዳይመረጡ ፣ በየትኛውም ቦታ ዋስም ምስክርም እንዳይሆኑ በአጠቃላይ ከማህበራዊ መብታቸው መታገዳቸው ተዘግቧል:: ተከሳሾቹ የቅጣት ማቅለያ አለማቅረባቸው በፍርድ ቤቱ ተገልጿል:: የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ኮሚቴዎቻቸው እንዲፈቱላቸው በሰላማዊ መንገድ ላለፉት ዓመታት ሲጠይቁ ቆይተዋል:: ፍርዱን ተከትሎ ሕዝበ ሙስሊሙ በተለያዩ ቦታዎች ሆኖ ቁጣውን በመግለጽ ላይ ይገኛል:: የፍርድ ሂደቱ ከ3 አመታት በላይ ሲንጓተት ቆይቷል::
Average Rating