www.maledatimes.com የአብዮቱ ዘመን ..አባ መላ.. ጓድ ቆምጬ አምባው ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው( Abebayhu Gebeyaw) ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የአብዮቱ ዘመን ..አባ መላ.. ጓድ ቆምጬ አምባው ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው( Abebayhu Gebeyaw) ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ

By   /   August 5, 2015  /   Comments Off on የአብዮቱ ዘመን ..አባ መላ.. ጓድ ቆምጬ አምባው ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው( Abebayhu Gebeyaw) ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ

    Print       Email
0 0
Read Time:10 Minute, 2 Second

ክፍል አንድ(1)

.. በ60 ቀን ማንበብና መፃፍ ያልቻለ ፖሊስ ይባረራል.. ተብሏል ብለው ዋሽተዋል – ለምን?
የወረዳ አስተዳዳሪ ሆነው አዛባ ይዝቁ ነበር – ኮሎኔል መንግሥቱ ሲቆጧቸው ምን መለሱ?
የደርግ ባለስልጣን የነበሩትን የኮንስትራክሽን ሚኒስትር የካሣ ገብሬን ቦርጭ ሲያዩ ምን አሉ?
በ13 ዓመት የወረዳ አስተዳዳሪነት የሠሩትን ይናገራሉ
የሶሻሊዝምን ርዕዮተ ዓለም በ1960ዎቹ ማብቂያ ላይ በአገራችን ያስተዋወቁት የደርግ ባለስልጣናት ሶሻሊዝምን የተረዱት የ70 ዓመቱ አዛውንት የጐጃሙ ቆምጬአምባው በተረዱት መንገድ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ታሪክ አሁን ከምናየው ፍፁም የተለየ ይሆን ነበር፡፡ ለእሳቸው ሶሻሊዝም ማለት ሠርቶ ማሰራት ነበር፤ ሶሻሊዝም ሜዳ ተራራውን አረንጓዴ ማልበስ ነበር፤ ለእሳቸው ሶሻሊዝም ብዙ ት/ቤት፣ ክሊኒክ፣ ወፍጮ ቤት፣ መገንባት ሌባን ማጥፋት ነው፡፡ በደርግ ዘመን ለ13 ዓመት የተለያዩ ወረዳዎችን ያስተዳደሩት ቆምጬ፤ በሠሯቸው በርካታ የልማት ሥራዎችና ብልሃት በታከለበት የአመራር ችሎቻቸው ከመንግስትም ከህዝብም ተወዳጅነት እንዳገኙ ይናገራሉ፡፡ እሳቸው ያልተናገሯቸው ብዙ ነገሮች እየተፈጠሩ በስማቸው እንደሚነገሩ አዛውንቱ ቢናገሩም እራሳቸው በትክክል የፈፀሟቸውም ቢሆኑ ከፈጠራዎቹ የሚተናነሱ አይደሉም፡፡ በሃላፊነት በሚመሩት ወህኒ ቤት የነበሩትን በጣታቸው እየፈረሙ ደሞዝ የሚበሉ ያሏቸውን ፖሊሶች በ60 ቀን ማንበብና መፃፍ እንዲማሩ የፈጠሩት ብልሃት ተጠቃሽ ነው፡፡ ኰሎኔል መንግስቱ ሃ/ማርያም በሥራቸው ተደስተው ሽጉጣቸውን ሲሸልሟቸው አልተቀበሉም – ከሽፍታ ያስፈታሁት 18 ሽጉጥ አለኝ በማለት፡፡ በምትኩ ግን ለህዝቡ መብራትናውሃ እንዲገባለት ጠይቀዋል፡፡ በትውልድ አገራቸው በጐጃም ያገኘቻቸው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ሰፊ ቃለምልልስ ያደረገችላቸው ሲሆን አንባቢያን የእኒህ መለኛ አብዮተኛ ታሪክ ከነለዛቸው ይደርሳቸው ዘንድ ቃለምልልሱን እንደወረደ አቅርበነዋል – ከአነጋገር ዘዬአቸው ጋር፡፡
የት ተወለዱ? መቼ?
የተወለድኩት በጠላት ወረራ ዘመን ነው፡፡ በጐዛምን ወረዳ ማያ አንገታም ቀበሌ ገበሬ ማህበር፣ አባላይ በተባለ ቦታ ሜዳ ላይ ተወለድኩ፡፡ እናቴም አባቴም አርበኛ ናቸው፡፡ ስወለድ ማን እንበለው እያሉ ሲመካከሩ ሳለ አንድ አውሮፕላን ትመጣና ክምር ስታቃጥል፣ አባቴ አነጣጥሮ ቢተኩስ ተንከታክታ ወረደች፡፡ ያን ጊዜ ቆምጬአምባው እንበለው፤ ይኼ ልጅ ገዳም ነው ተብሎ ነው ስም የወጣልኝ፡፡
ለትምህርት እንደደረስኩ እዚያው ቀበሌ አንገታም ጊዮርጊስ የቄስ ትምህርት ተምሬ፣ ዳዊት ፆመድጓ ጨርሼ ወደ ቅኔ ቤት ገባሁ፡፡ በሽታ እንደገባ አባቴ ከቅኔ ቤት አውጥተው ወሰዱኝ፡፡ በ15 ዓመቴ የሰባት ደብር የጐበዝ አለቃ ሆንኩኝ፡፡
ቆምጬ ማለት ምን ማለት ነው?
ደፋር፣ ጠንካራ፣ ቆራጥ ማለት ነው፡፡
በሸዋ ግን ትርጉሙ ሌላ መሰለኝ. . .
አዎ፡፡ በእኔ በኩል ግን ቆምጬ ማለት ታይቶ የሚታለፈውን የሚያውቅ፣ ታይቶ የማይታለፈው ላይ ቆራጥ እርምጃ የሚወስድና ሩህሩህ፣ የዋህ ማለት ነው፡፡
ወጣትነትዎ እንዴት አለፈ?
በወጣትነቴ የቤተሰብ ተጽዕኖ ነበረብኝ. . . ሰው ፊት ጠላ መጠጣት አይፈቀድልኝም፤ ውሃ እንኳን ጭልጥ አድርጎ መጠጣት እንከለከላለን፡፡ ስንበላ አፋችሁን ገጥማችሁ አፋችሁን አታጩሁ፤ እየተባልን ነው ያደግነው፡፡ አባቴ ቅዳሴ አስቀድሼ ወጥቼ መሃራ አያስቀምጡኝም ነበር፡፡ ..መሃራ መብላት ያለበት አቅም ያጣ፣ ቤቱ የሚበላው የሌለው ነው፡፡ አንተ ሁሉ ነገር ቤትህ ሞልቶ የተረፈህ ስለሆንክ ምንም እንዳትቀምስ.. እባላለሁ፡፡ ሰርግ ስንሔድ የአባቴን መሣሪያ ይዤ ከበስተጀርባው ነበር የምቀመጠው፡፡ እህል በወሰክንባ(ሞሶብ) ነበር የሚመጣልኝ፡፡ ጨዋታ አምሮኝ ከጉብላሊቱ(ህጻናት) ጋር መደባለቅ አይፈቀድልኝም፡፡ ከፍተኛ ተጽዕኖ ነበረብኝ፡፡ በፆም ቀን ከስምንት ሰዓት በፊት ስንበላ ከተገኘን እንደበደባለን፡፡ የገና ጨዋታ፤ ፈረስ ግልቢያ፣ ዋና፣ አውሬ አደን ምን ልበልሽ ያልተሳተፍኩበት የለም …ከሁሉም ግን ደስ የሚለኝ አደን ነበር፡፡
ምን አድነዋል?
ድኩላው፣ አሳማው፣ ሚዳቋው. . . በለሴ ሆኖ ወደ እኔ ይመጣል፡፡ በቃ ሆ እያልን አገሬ ይዤ እገባለሁ፡፡ ከሰው የተጣላሁ እንደሆን አባቴ አይለቀኝም ነበር፡፡
የደብር አለቃ ሳለሁ ሰው ሲጣላ ባውቀውም ባላውቀውም አስታርቅ ነበር፡፡ በዚያውም የስብሰባን ጥቅምና የአንዳንድ ነገሮችን ሁኔታ ማየት ጀመርኩ፡፡
ስለትዳርና ቤተሰብ ይንገሩኝ. . .
አስር ልጆች አሉኝ፡፡ ባለቤቴ አሁን ያለችት የልጆቼ እናት ናት፡፡ ለሷ የእኔ እና የእሷን ስምንት ስምንት የቀንድ ከብት አማተን ደርሰን ሃብታም ሆነን፤ ኋላ ገንዲ በሽታ መጣና ከብቱን ሲፈጀው ተበሳጨሁና ወደ ጐጃም ጠቅላይ ግዛት መጣሁ፡፡ የምክትል ፀሃፊነት ፈተና ተፈተንኩና አለፍኩ – ጃናቢት በተባለች ስፍራ፡፡
ደሞዙ ጥሩ ነበር?
25 ብር ነው፡፡ ማለፌን ከሰማሁ በኋላ አንድ አህያ ተልባ፣ አንድ አህያ ኑግ ጭኜ ወደ ደብረማርቆስ ገበያ ወጣሁና ቦጋለ በረዳ የሚባል ቦታ ሸጥኩት፡፡ ከዚያ ምክትል ፀሃፊነት አለፍኩ አልኩና ሁለት አዝማሪ ጥሩ ብዬ፣ ሹመቴን እያነሳሳ ሲዘፈን ሲጠጣ ሲበላ ታደረ፡፡ ጥቂት ብር ቀረችኝ፡፡ ማለዳ የሹመት ደብዳቤውን ልቀበል አውራጃ አስተዳደሩ ጋ ስሄድ የወረዳው ገዢ ቀኝ አዝማች ረታ ፈረደ ይባላሉ ..አንተ ነህ ምክትል ፀሃፊ የተሾምከው?.. አሉኝ፡፡ አለባበሴም ደህና ነው ያን ጊዜ፤ ንቁ ነኝ፡፡ ..አዎ.. አልኳቸው፡፡
..አንተማ የዋናው የከበርቴ ልጅ አይደለህ፤ ሰባት ጉልት እያሳረሳችሁ፤ አንተን አንቀጥርም! በል ውጣ ከቢሮዬ.. አሉኝ፡፡ ተበሳጨሁ ገንዘቤን ጨርሻለሁ፤ ሌላ አማራጭ ሳፈላልግ በደብረማርቆስ ወህኒ /ቤት ለወታደርነት ቅጥር የተለጠፈ ማስታወቂያ አየሁ፡፡ ወዲያው እለቱን ተመዝግቤ አለፍኩ፡፡ ሲያዩኝ በቁመትም በክብደትም እኩል መጣሁ፡፡ ወደ ማሰልጠኛ ላኩኝ፡፡ ከማረሚያ ቤት አስተዳደር ወታደሮች አስራ ሰባት፣ ከፖሊስ ሰባት ነበር የተመለመለው፡፡ እዚያ ተደባልቀን ስንማር በፀባይ፣ በተኩስ፣ ህግ በማወቅ አንደኛ ወጣሁ፡፡የዚያን ጊዜው አገረገዥ ደጅአዝማች ፀሃይ እንቁ ኃይለስላሴ፣ የምስክር ወረቀት ሲሰጡ ..በወታደራዊ አቋም፣ በፀባይና በተኩስ ወታደር ቆምጬአምባው ይልማ አንደኛ.. ብለው ሸለሙኝ፡፡ ኮሎኔል አሰፋ ወንድማገኘሁ ከሚባሉ ከወህኒ ቤቱ አዛዥ ጋር ጠሩኝና ..ከአስራ ሰባቱ ወታደር አንተ በጣም ጠንካራ ነህ፤ ወደፊትም እናሳድግሃለን.. አሉና ሃምሳ ብር በግሌ ሰጡኝ፡፡ የወህኒ ቤቱ /ቤት የእስረኞች የህግ አማካሪና የጠቅላይ ግዛቱ ወህኒ ቤት ጠበቃና ነገረ ፈጅ አደረጉኝ፡፡ ኮልት ሽጉጥም ሸለሙኝ፡፡
ከእስረኞች ጋር ስለነበርዎ ግንኙነት ያጫውተኝ
እስረኛው አንዳንድ ጊዜ ..ምግብ ጠቆረ.. ይልና ያድማል፡፡ ..እኛ መነገጃ አይደለንም.. ይላል፡፡ የጐጃም ጠቅላይ ግዛት በሙሉ፣ የ35 ወረዳና የሰባቱ አውራጃ እዚሁ ነበር የሚታሰረው – የመተከል፤ የቤንሻንጉል፤ የባህርዳር ሁሉ ማለት ነው፡፡ እስረኛው ሲያድም እኔ ሽጉጥ ታጥቄ በመሃላቸው እገባና ..እናንተን ያሰራችሁ ሰው አይደለም፤ ያሰራችሁ እግዚአብሔር ነው፡፡ እዚህ እኮ የምትፀልዩበት፣ የምትማፀኑበት፣ ፍርድ እናግኝ ብላችሁ የምትለማመኑበት ነው፡፡ የጐጃም ሰው ሆዳም አይደለም ምግብ አነሰኝ ብሎ አይናገርም፡፡ አናንተ ቆሎ፣ በሶ፣ በግም ፍየልም አሳርዳችሁ ትበላላችሁ፤ አገራችን ተሰደበ.. ብዬ ያንን ጠቆረ አንበላም ብለው የተውትን ጥቁር እንጀራ እነሱ መሃል ሆኜ ቆርሼ እበላዋለሁ፡፡ ያንዜ ያጨበጭባሉ፡፡ ከዛ በኋላ አድማው ይበተናል፡፡ ..አሁን ትፈታላችሁ ግማሻችሁ በአመክሮ፤ ግማሾቻችሁ ደግሞ ፀባያችሁ ጥሩ ከሆነ ሚያዚያ 27 በአርበኞች ድል በዓል ወይም ሐምሌ 16 በጃንሆይ ልደትና ጥቅምት 23 በጃንሆይ የዘውድ በአል ትፈታላችሁ፡፡ እንቢ ካላችሁ ግን ችግር ላይ ትወድቃላችሁ.. ስላቸው በጀ ይላሉ፡፡ የጣቢያው አዛዥ ንግግር ስለማያውቅበት ቀጠሮ ስጡኝ ብዬ እኔ ነበርኩ የማናግራቸው፡፡
ለእስረኛው ያወጡት ህግ ነበር ይባላል?
ህጉ እያንዳንዱ እስረኛ ሰውነቱን በሳምንት አንድ ቀን ፀጉሩን ዕለት ዕለት እንዲታጠብ የሚል ነው፤ አሽቶ የሚያጥበው በወር 1 ብር ከፍሎ ሰው ራሱ ይቀጥራል፡፡ እስረኛው ገንዘብ ነበረው፡፡ ሞልቶታል፡፡ ከዚያ አሰልፋቸውና ከኪሴ ነጭ መሀረብ አውጥቼ የአንዱን ደረት አሸት አድርጌ ..ይሄው እድፍ አለው ውጣ.. እለዋለሁ፡፡ ንፁህ ሆኖ ያገኘሁትን ደግሞ አንድ ብር አወጣና እሸልመዋለሁ፡፡ ያን ጊዜ እስረኛው ሁሉ ንፁህ ለመሆን መሯሯጥ ነው፡፡ የመኝታቸውን ዳትም ክፍላቸው እየገባሁ እፈትሽ ነበር፡፡ ይሄን አይተው ደጃዝማች ፀሃይ (በ1958) የደ/ማርቆስ ቤተመንግስት ሲሰራ ..ይሄ ጐበዝ ልጅ ነው፤ ጠንካራ ሰራተኛ ነው.. ብለው ወሰዱኝና እንደገና ተሸለምኩ፡፡
ንህናውን ያልጠበቀ እስረኛስ? ቅጣት አለው?
አዎ ይቀጣል፡፡ አስር የችግኝ ጉድጓድ አስቆፍረዋለሁ፤ በግቢው ውስጥ የፍራፍሬና የአትክልት ስፍራ ስለነበረ እሱንም አስቆፍራቸዋለሁ፡፡ ሰው ገድሎ የታሰረውን ግን ወታደሩ ስራ አናሰራም ብሎ ይቃወመኛል፤ መሳሪያ ነጥቆን ይሄዳል በሚል፡፡ ..በያዝከው መሳሪያ አጨማደህ አትጥለውም፤ እንግዲህ በእግር ብረት ታስሮ አይሞትም.. እልና፤ የገደለውን ሁሉ ሰብስቤ ..ኑ ተንቀሳቀሱ ይሄ ስራ የእናንተ ነው፣ አካልና አእምሮአችሁን አስተባብራችሁ በሞራል የጠነከራችሁ እንድትሆኑ ስሩ.. እላቸዋለሁ፡፡ በጣም ይወዱኛል፡፡ ፍ/ቤት ለስራ ስሄድ ባዶ ወረቀት ካገኘሁ ሰብስቤ አመጣና አንዳንዱን በሽልማት እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘመድና ለምሽት ደብዳቤ መጠጣፊያ፡፡ ከዚያ ፊደል ሠራዊት የሚባል መሰረተ ትምህርት ተቋቋመ፡፡ በደጃዝማች ፀሃይ ጊዜ፣ አቶ ሸዋቀና የተባሉ የትምህርት ሚኒስቴር ሃላፊ፣ የጠቅላይ ግዛቱን ወህኒ ቤት እሱ ነው ማስተባበር የሚችለው አሉና እኔን ሾሙኝ፡፡ ማንበብ መፃፍ የማይችል፤ በጣቱ እየፈረመ የሚበላ ፖሊስ ሞልቷል – ያኔ፡፡ አዳራሽ ላይ ሰበሰብኩና እስከ ስልሳ ቀን ድረስ ማንበብና መፃፍ ካልቻላችሁ ሚስጢር ነው የምነግራችሁ ..ትባረራላችሁ.. ተብሏል አልኳቸው፡፡ (ሳቅ) መንግስት አቋም ይዟል፤ ማታ ማታ ልጆቻችሁ ቤት ውስጥ ያስተምሯችሁ አልኳቸው፡፡ ማንበብ መፃፍ የማይችል ሠራዊት በፍፁም አይሆንም፤ እየተባለ ነው ስላቸው. . . ማታ ማታ ጥናት ነው፣ ማንበብ ነው፡፡ ሲፈተኑ ደህና ናቸው፡፡ ..ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘኢትዮጵያ.. ብዬ ብላክ ቦርዱ ላይ ፃፍኩና ገልብጡ አልኳቸው – እንዳለ ፃፉት፡፡ በዚህም ተሸለምኩ፡፡
አብዮቱ ሲፈነዳ በአንድ ቀበሌ ውስጥ ህዝቡ ስለሚያውቀኝ የአብዮት ጥበቃ የፍርድ ዳኛ ሸንጐ ውስጥ ገባሁ፡፡ በደብረማርቆስ በድሮው ቀበሌ 8 ዳኛ ሆንኩ፡፡ ስራዬ እርቅ ነበር – ይቅር ተባባሉ ማለት፡፡ ፍርድ የሚሻውን ደግሞ ፍርድ እያሰጠሁ እየቀጣሁ በሬድዮ አስነግራለሁ፡፡ ጉልታዊ አገዛዝን እየኮነንኩ፤ የሠራተኛውን መደብ ንቃ እያልኩ የተናገርኩ እንደሆነ መልእክቴ ሁሉ በሬድዮ ይሰማ ነበር፡፡
በአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ ከሽፍቶች ጋር ተደራድረሃል ይባላል?
የገበሬው አመ በሚባልበት በነ ባምላኩ ጊዜ፣ እነ ደጃዝማች ፀሃይ ከደ/ማርቆስ ይነሱ በሚባል ጊዜ ከብፁዕ አቡነማርቆስ ጋር ደብረወርቅ ሄጃለሁ፡፡ ገበሬው ሰው ቆምጬን ያውቀዋል ብሎ ለከኝ፡፡ በኢሊኮፍተር ነበር የሄድነው፡፡ ከዛ ከኢሊኮፍተሩ ላይ ስንወርድ ከርቀት አነጣጥረው የብፁዕ አቡነ ማርቆስን ቆብ ይመቱታል፤ ..ጐንበስ ይበሉ ጐንበስ ይበሉ.. አልኳቸው፡፡ በኋላ እንደ ምንም ወጣን፡፡
በዚያን ወቅት እንግዲህ ሀገሩ ሁሉ ሸፍቶ ነበር፡፡ ወንበዴ በወንበዴ ሽፍታ በሽፍታ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ማነው አሁን እነሱ ጋ ሄዶ እርቅ የሚለምን ተብሎ አገር ይታመሳል ..እኔ እሄዳለሁ ምን ችግር አለው.. ብዬ ሽጉጡንም፣ ኡዚ አቶማቲክ ጠመንጃም ይዤ በመሃላቸው ገባሁና ..ደህና ዋላችሁ፤ ደህና ዋላችሁ.. ስል ሁሉም ተነስቶ ሰላም አለኝ፡፡
ሽፍቶቹ?
እህሳ! ያ ሁሉ ሽፍታ እኮ ታስሮ የተፈታ ነው፡፡ በእስር ቤት ውስጥ ሁሉም ነበር የሚያውቀኝ፡፡ በኋላ ከፊታቸው ቆሜ ንግግር አደረኩ፡፡ ..እናንተ ብቻችሁን አትችሉም፡፡ ሃገር ልታስደበድቡ ነው፤ ክቡር ዘበኛ መጥቷል፡፡ ዛሬ ምላሻቸውን እንፈልጋለን መልሱን አምጣ ተብዬ ነው.. ስላቸው ..አንተማ የሀገራችን ልጅ ነህ ሌላ ቢሆን በጥሰን በጣልነው ነበር፡፡ በእስር እያለን ከሚስታችን ከዘመዳችን እያገናኘህ ብዙ የረዳኸን ነህ፡፡ አሁንም የምትለንን እንሰማለን፤ ጦርነት አንፈልግም፤ እኛ የምንፈለገው አንድ ብር ከሃምሳ ግብር እንዲነሳልንና ደጃዝማች ፀሃይ እንዲወርዱልን ነው.. አሉኝ፡፡ እዚያው ያሉትን ቁጭ ብዬ ፃፍኩና ..መልስ እስክናመጣላችሁ ወደ ቤታችሁ ግቡ፡፡ እርሻም እረሱ፤ የመጣውም ጦር ይመለስ፤ ጳጳሱም መጥተው ተኩሳችሁ ልትገሏቸው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ነው ያወጣቸው፡፡ አሁን እሳቸው ሊያስታርቁ ቢመጡ ሊያስተኩሱ እንደመጡ ሁሉ እንዲህ ታደርጉ? እኔም ደሞ የሀገር ሰው ነህ፤ ወንድም ነህ ተብዬ ተመርጬ ነው የመጣሁ፡፡ የተከበሩ አቶ መኮንን እውነቴን፤ የተከበሩ በከፋ የኔነህን ታውቋቸዋላችሁ አይደል? በአምስት አመት የጠላት ወረራ ዘመን ከደጃዝማች በላይ ዘለቀ ጋር አብረው የነበሩ፣ የደጃዝማች በላይ ዘለቀን ማህተም ይዘው ይፉ የነበሩ ናቸው. . . ጠላትን ያርበደበዱ የነበሩ፡፡ ዛሬ ደግሞ አስታራቂ ሆነው መጡ፡፡ በሉ እነሱ ይምጡና ሰላም በሏቸው.. አልኳቸው፡፡ ..በቃ እሺ…… ወታደር እንዳይመጣ እነሱ ይምጡ.. አሉ፡፡ ይዤአቸው ሄድኩ፡፡ ብቻ ወዲህ ወዲያ ብለን ደጃዝማች ፀሃይ ወረዱ፡፡ ሰላም ሰፈነ፡፡
የደርግ መንግሥት እንዴት ተቀበለህ?
በደርግ ሥርዓት ሌባ፣ ሴሰኛ፣ ገንዘብ የሚያታልለው፣ ጥቅም ፈላጊ ፓርቲውን አይቀላቀልም ነበር፡፡ እንጃ! በኋላ አበላሽተውት እንደሆነ አላውቅም፡፡ የመደብ ትግሉን ለመቀላቀል የሚፈልግ ሰው የግል ማህደሩ ይታያል፡፡ እኔ በመጀመርያ በሙሉ ፈቃደኝነት ማመልከቻ የፃፍኩት ..የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራምን ተቀብያለሁ፤ ከሰፊው ህዝብ ጥቅም ይልቅ የራሴን ጥቅም አላስቀድምም፤ ከራሴ ጥቅም ይልቅ የሰፊውን ህዝብ ጥቅም አስቀድማለሁ፣ እየተማርኩ ከአብዮቱ ጋር ለመቀላቀል ፈቃደኛ ነኝ.. ብዬ፡፡ ማመልከቻዬ ተመረመረ፤ ጀርባዬን አስጠኑኝ – በደህንነቶች፤ በጐረቤት፡፡ በኋላ በቀበሌ የጥናት ክበብ ውስጥ አስገቡኝ፡፡ በመንግሥት ሥራ ተወጥሮ የጥናት ክበቡ ላይ ያልተገኘ እንኳን ይሰረዛል፡፡ መማር ግድ ነበር፡፡
ትምህርቱ ምንድን ነው?
የካፒታሊስት ስርዓትና፤ የሶሻሊስት ስርዓት ምንድን ነው? ጠቃሚው የትኛው ነው? በሚል ነበር፡፡ ከዛም የሠራተኛው መደብ ንቅናቄ በጀርመን በአሜሪካ ምን ይመስላል የሚለውን. . . ከዛም የምትበይው፣ አረማመድሽ፣ ንቃትሽ፣ ንግግርሽ ሁሉ ይገመገማል፡፡ የገባው ሁሉ አይዘልቅም፡፡ ልክ መንገድ ላይ መኪና እንደሚጥለው ፌርማታ ላይ እየተራገፈ ይሄዳል፡፡ ከብዙ ምልምሎች ጥቂቶች ቀረን፡፡ . . . እኔ እዚህም ምስጉን ነበርኩ፡፡
ምስጉንነትህን ማን ነገረህ?
ጓድ መንግሥቱ ናቸዋ! አፍና ተግባር ይሉኝ ነበር፡፡ አንደዜ እሳቸው በምሠራበት አቸፈር አካባቢ መጥተው ሳለ. . . እኔ አላውቅም ነበር እንደሚመጡ፡፡ የከብቶችን አዛባ እዝቅ ነበር፡፡ ኮረኔል ዘለቀ ..ና ሰላም በል ና ሰላም በል.. አሉኝ፡፡ ሸሚዜን ወደ ላይ ሸበሸብኩና ስጨብጣቸው ..ጓድ ቆምጬ አስተዳድሩ ተባለ እንጂ አዛባ ይዛቁ ተባሉ.. አሉኝ፡፡ ..ጓድ መንግስቱ፤ እኔ ካልሠራሁ ሌላው ስለማይሰራ ነው.. አልኳቸው፤ ዞረው ሁሉን አዩ፡፡ በቆሎው፣ በርበሬው ደርሷል፡፡ በቆሎውን ሸለቀኩና አንዱን ወታደር እንካ ጥበስ አልኩት፡፡ በኋላ ጠብሶ ሲሰጠኝ እንኩ አልኳቸው፤ ሰበር አድርገው እሸቱን በሉ፡፡ ቀሪውን ለአጃቢው ሰጠሁት፡፡ ያሉት ሁሉ አንዳንድ በቆሎ በሉ፤ ቆሎ በኑግ ከመንደር መጣ፡፡ ጠላ በዋንጫ ቀዳሁና እኔ መጀመሪያ ..ፉት.. አልሁና ሰጠኋቸው፡፡ ..ለምን ነው? ለምን ነው? ዝም ብለው ያምጡት አሉኝ.. መቸም ኸዱ ብዬ አላማቸውም፡፡ ..ለምን ቀመሱት ጓድ ቆምጬ ያምጡት በሉ.. አሉኝ ..አይ የጎጃም ባህል ነው፡፡ ማንም እንዲህ ሲሰጥ ቀምሶ ነው ሚሰጥ፤ እንቆቆ ወገርት መድኃኒት ሲሰጥ እንኳን ቢሆን ቀምሶ ነው፤ የሀገሩን ባህል ለማንፀባረቅ ነው.. አልኳቸው፡፡ በኋላ በርበሬ ጧ ብሎ ደርሷል፤ ይዩት ብዬ እሱን አሳየኋቸው፡፡ ጓድ ካሣ ገብሬ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴሩ ወፍራም ነበሩ፤ እኔ አላውቃቸውም ነበር፡፡ እንደዛሬው ቴሌቪዥን የለም፡፡ ሳያቸው ሆዳቸው ቦርጫቸው ሌላ ነው ..እስዎም አሁን ኮሚኒስት ተብለው ነውን?.. አልኳቸው፡፡ መሀረባቸውን ከኪሳቸው አውጥተው እምባ በእምባ እስቲሆኑ ድረስ ከት ከት ከት ብለው ሳቁ፡፡
አንተስ ቀጭን ነበርክ?
በጣም፡፡ ይኸውልሽ ወንበዴ እየመጣ ሁልጊዜ ተኩስ ነው፡፡ ሀሳብ ነበረብኝ፡፡ በዚያ የተነሳ ሃሳቡ ነው መሰለኝ በጣም ቀጭን ነበርኩ፡፡ በኋላ ጓድ መንግሥቱ ..እስቲ የወረዳውን ተፈጥሯዊ ገታና አጠቃላይ ሁኔታ አምጣ.. አሉኝ፡፡ ..አውራጃ አስተዳዳሪው ጓድ መስፍን አለ አይደል.. አልኳቸው፡፡ ..ከወረዳው መስማት ነው የምንፈልግ.. አሉ – እሳቸው፡፡ ያለውን ነገር ሁሉ ቁጭ አደረኩላቸው፡፡ በመሠረተ ትምህርት ቅስቀሳው አንዳንዶች አትማሩ እያሉ እየቀሰቀሱብን ነው እንዲያውም አስራ ሁለተኛ ክፍል የጨረሰውን ሥራ ሳያሲዙ እያሉ እንደሚያሳምፁና ወረዳውም በከፍተኛ ሁኔታ ኋላ ቀር መሆኑን፣ የመብራትና የውሃ ችግር መኖሩን፣ የአቸፈር ልጅ ለአብዮቱ በየተራራው እንደሚዋጋ ሃቁን ስነግራቸው ..እነዚህ ወረበላዎች ምን እያሉ ነው የሚቀሰቅሱ.. አሉኝ፡፡ አይ ይሄን የነገርኩዎን ነው አልኳቸው፡፡ የወረዳውን ለእኛ ተውት፤ ግን ነገሩ በውይይት ቢፈታ አልኳቸው ..በውይይት ሲሉ ምን ዓይነት ነው?.. አሉኝ፡፡ ..ሰውን የሚያጣላው የስልጣን ጥያቄ ነው ጓድ ሊቀመንበር.. አልኳቸው፡፡ ..ለመሆኑ እርቅና ድርድር ቢጀመር ትኩረት ሰጥተው ይከታተሉታል.. አሉኝ፡፡ ..አዎ.. አልኳቸው፡፡ ..እንዴት.. አሉኝ፡፡ ..በክቡር አቶ አማኑኤል አምደሚካኤል የሚመራ ቡድን ሦስት ጊዜ ሂዶ እርቁ ከሸፈ፡፡ በሬዲዮ የሰማሁትም የኢትዮጵያ መንግሥት እምቢ አለ የሚል ነው.. አልኳቸው፡፡ ..ለማንኛውም ጥሩ ግንዛቤና የሀገር ፍቅር አለህ፡፡ አፍና ተግባር ትክክል ሆኖ ያየሁት ባንተ ነው.. አሉኝ፡፡ ተዚያም ሽጉጥ አውጥተው ..ገንዘብ የለኝም.. አሉና ሊሰጡኝ ሲሉ ..ኧረ እኔ ተሽፍታ ያስፈታሁት አስራ ስምንት ሽጉጥ አለ፡፡ እንደውም ከቸገራችሁ ውሰዱ አልፈልግም.. አልኳቸው፡፡ ..ታዲያ ምንድነው የሚፈልጉት.. ሲሉኝ ..መብራት እና ውሃ ለሰፊው ህዝብ.. አልኳቸው፡፡ ጓድ ፍቅረስላሴ ወግደረስ አብረው ነበሩ፡፡ ..ጓድ ፍቅረሥላሴ፤ ቀን ሰጥቼሀለሁ. . . በተገኘው ገንዘብ ሁሉ መብራትና ውሃ እንዲገባ.. ብለው መመሪያ ሰጡልኝ፡፡ ስልሳ ቀን ሳይሞላ መብራትና ውሃ ገባ፡፡
ለአስተዳዳሪነት የተመደብክበት የመጀመሪያ ቦታ የት ነበር?
ቢቡኝ ነበረ፡፡ ቢቡኝ ማለት እስታሁንም አረንጓዴ ትርዒት ማለት ነው፡፡ በሄድኩበት ወረዳ የተፈጥሮ ሀብት እንክብከቤ በማድረግ የደን መራቆት እንዳይኖር ሳልታክት እሠራ ነበር፡፡ ከዚያ ደግሞ ሁለት እጅ እነሴ ወረዳ ነው የሰራሁ፡፡ እዛም እንደዚያው ደብረ ወርቅ ተዛውሬ አበት አለፍ የሚባል ተራራ አለ፤ የሬዲዮ መገናኛ ያለበት ነው፡፡ እዚያ ወጥቼ ሳየው ተራራውን ገበሬው እህል ያበቅልበታል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 9 years ago on August 5, 2015
  • By:
  • Last Modified: August 5, 2015 @ 6:09 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar