መኪና ለመዝረፍ በማሰብ አሽከርካሪና ረዳቱን ገድለው ገፈርሳ ወንዝ ውስጥ የከተቱ ሁለት ተጠርጣሪዎች ዛሬ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ የወንጀል ችሎት ቀርበው ወንጀሉን መፈጸማቸውን አመኑ። ወቅቱ ነሐሴ 14፣ 2007 ምሽት 2 ሰዓት ነው፤ ሟች ኤፍሬም ተሾመ እና ሰለሞን አድነው የተሰኙ የ22 እና የ13 ዓመት ረዳት ሚኒባስ ታክሲ ኮንትራት እንፈልጋለን ከሚሉ ሰዎች ጋር ይገናኛሉ። እንደፖሊስ የምርመራ መዝገብ ወጪ ወራጅ ብቻ ከመስራት በኮንትራት መስራት ዳጎስ ያለ ገንዘብ ያስገኛል በሚል መነሻቸውን ቤቴል ማዞሪያ በማድረግ እነዚህን ሰዎች ይዘው ጉዞ ይጀምራሉ። የታመመ ሰው ሆስፒታል ታደርሳላችህ የተባሉት አሽከርካሪና ረዳት ኤፍሬም ተሾመ እና ረዳቱ ብዙም ሳይጓዙ በሶስት ሰዎች በገመድ ተጠፍረው ይታሰራሉ። የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንደሚያሰረዳው የታመመ ሰው ሆስፒታል እንድታደርሱ ነው በሚል በሟች መኪና ውስጥ የግድያ ወንጀል የፈፀሙ ተጠርጣሪ ግለሰቦችም ሸምሱ ሰኢድ፣ አምሩ ሙኒር እና ሲራጅ አህመድ ናቸው። ዛሬ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድቤት አራዳ ምድብ ችሎት ተረኛ የወንጀል ችሎት ቀርበው ወንጀሉን መፈፀማቸውን አምነዋል። የወንጀል አፈፃፀማቸውንም ለችሎቱ በቅደም ተከተል ያስረዱ ሲሆን፥ አንደኛው ተጠርጣሪ ሸምሱ ሰኢድ ሰው ለመግደል ሃሳቡ እንዳልነበራቸው፣ ችግር ገጥሟቸው ስለነበር ግን አንድ ያለተያዘ ግብረ አበራቸው መኪና እንደምንም ብላችሁ ካመጣችሁ በፍጥነት የሚገዛ ሰው አለ ሲለን ልባችን ተነሳሳ በማለት አስረድቷል። ከዚያም የታመመ ሰው ሆስፒታል ለማድረስ መኪና እንደሚፈልግ ሰው ሆነው ታክሲ ውስጥ መግባታቸውን፣ አሽከርካሪውን በገመድ አስሮ በማስተኛት ከአፍታ በኋላ ሲመለከተው ህይወቱ ማለፉን አስረድቷል። ሁለተኛው ተጠርጣሪ አምሩ ሙኒርም የ13 ዓመቱን ታዳጊ ሰለሞን አድነውን በገመድ አስሮ ህይወቱ እንዲያልፍ ማድረጉን ተናግሯል። ሁለቱም ተጠርጣሪዎች ያልተያዘው ግብረ አበራቸው በእንዲህ መልኩ የሚሸጥ መኪና ካመጣችህ በ15 ደቂቃ ውስጥ ሸጠን እናንተም የዕለት ችግራችሁን ትወጣላችሁ ብሎን የነበር ቢሆንም የሆነውን ስንነግረው ግን አፈገፈገ ብለዋል። ከዚያም የሟቾቹን አስክሬን ሰው የማይደርስበት ቦታ ስናፈላለግ ቆይተን ገፈርሳ ወንዝ ወስደን ጥለናል በማለት ለችሎቱ የወንጀሉን ሂደት አስረድተዋል። ታክሲዋን እሸጥላችኋለሁ ያለው ግለሰብም በመሰወሩ ምክንያት ታክሲዋን ለሁለት ቀናት ከተዟዟርንባት በኋላ ታርጋውን መነሻ በማድረግ ያልሆነ ቦታ ለምን መኪና አቆማችሁ የሚል ጥያቄ ከሟች አሽከርካሪ አባት መሰንዘሩን አትተዋል። ወንጀሉ በተፈፀመ በቀናቶች ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎችም ወንጀሉን መፈፀማቸውን በሰጡት ቃል አረጋግጠዋል። ወንዙ ውስጥ የተከተቱት የሁለቱ ሟቾች( የአሽከርካሪ እና የረዳቱ) አስከሬን በመከላከያና በፖሊስ ሀይላት ፍለጋ ተገኝቷል። ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ሶስተኛው ግብርአበራቸው በወንጀሉ የለበትም ቢሉም፤ ፖሊስ ግለሰቡ ተሳትፎ እንደነበረው ያገኘሁት ማስረጃ ያሳያል ፣ ያልጨረስኩት መረጃ ስላለ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ ብሏል። ችሎቱ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመፍቀዱም ውጤቱን ለመጠባበቅ ለመስከረም 13፣ 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል
መኪና ለመዝረፍ አሽከርካሪና ረዳቱን ገድለው ገፈርሳ ወንዝ ውስጥ የከተቱ ግለሰቦች ወንጀሉን መፈጸማቸውን አመኑ
Read Time:1 Minute, 43 Second
- Published: 9 years ago on September 12, 2015
- By: maleda times
- Last Modified: September 12, 2015 @ 2:48 am
- Filed Under: Ethiopia
Average Rating