Reeyot-Alemu_002
በአዲሱ አመት ዋዜማ የፖለቲካ እስረኞችን ለመጠየቅ ወደ ቂሊንጦ እስርቤት ከእህቴ ጋር ሄጄ ነበር፡፡ ስማችንን እና የምንጠይቃቸዉን እስረኞች ስም ካስመዘገብን በኋላ መታወቂያችን አሳይተን ወደዉስጥ ልንገባ ስንል መታወቂያዉን የምትመለከተዉ ፖሊስ ስማችንን ካነበበች በኋላ “ቆይ ቆይ የእናንተማ መጠየቅ አለበት” አለችንና መታወቂያችንን ይዛ ከበር መለሰችን፡፡ ከበሩ አጠገብ በሚገኝ ጎብኝዎች ወረፋ በሚጠብቁበት የእንጨት መቀመጫ ላይ አረፍ እንዳልን በሃሳብ ላይ ታቹን ማለት ጀመርኩ፡፡ እንድንገባ ይፈቅዱልን ይሆን ወይስ የቃሊቲዎቹ እንዳደረጉት “ፍቃድ የላችሁም” የሚል አስቂኝና አናዳጅ መልስ በመስጠት ይመልሱን ይሆን? ለሚለዉ ጥያቄ መልሱ እኔዉ ጋር ያለ ይመስል አጎንብሼ ማሰቤን ቀጠልኩ፡፡ ቀና ስል ከፊት ለፊቴ “ማረሚያ ቤቱ” ለእስረኛ ቤተሰቦች መልካም ምኞቱን የገለፀበት ወረቀት ተለጥፎ ተመለከትኩ፡፡ ከአራት አመታት በላይ በመኖር የእስርቤቶቹን አሰራር አዉቀዋለሁና ተመሳሳይ የመልካም ምኞት መግለጫ የያዘ ወረቀት ለእስረኛዉም ተለጥፎ እንደሚሆን አልተጠራጠርኩም፡፡
ሰላም እየነሳ ሰላም “የሚመኝ”፣ ህክምና እየከለከለ ጤንነትን “የሚመኝ”፣ የሚዋደዱ ሰዎችን ከሽቦ ወዲያና ወዲህ ሆነዉ እንኳን እንዳይተያዩ እየከለከለ ፍቅርን “የሚመኝ” . . .ተቋም ! አንድ ፖሊስ ወደኛ እየቀረበ ሲመጣ ሀሳቤ ተቋረጠ፡፡ መታወቂያዬን እየመለሰልኝ መግባት እንደማልችል ነገረኝ በኋላ ለእህቴም ተቀራራቢ መልስ በመስጠት መታወቂያዋን መለሰላት፡፡ ለምን ለሚለዉ ጥያቄያችን “አላዉቅም፡፡ የተወሰነውን ንገር ተብዬ ነው” የሚል ምላሽ ሰጠን፡፡ ምን አይነት አምባገነንነት ነው? እስር ቤት እያለሁ በሌሎች የመጎብኘት መብቴን የነፈገው ስርዐት ዛሬ ደግሞ የጠያቂነት መብቴን እየነፈገው ነው፡፡ ሙሉውን ቀን ሊባል በሚችል መልኩ ስለፖለቲካ አሳሪዎቻችን ጉዳይ እያሰብኩ ስብሰለሰል ዋልኩ፡፡ የእኔና የሌሎች በርካቶች መብሰልሰል ምክንያት የሆኑት የኢህአዴግ ባለስልጣናት ደግሞ በአሉን ምክንያት በማድረግ ፍትህ እያዛቡበተ፣ እያሰሩትና እየገደሉት ላሉት ህዝብ የመልካም ምኞት መግለጫቸዉን ሲያዥጎደጉዱለት ዋሉ፡፡ ይህንን የኢህአዴግ ምኞትና ተግባር መራራቅ እያሰብኩ እያለሁ “ኢህአዲግን ለመለወጥ የምንፈልግ ሰዎች ምኞትና ተግባርስ ምን ይመስላል? ” የሚል ጥያቄ ሽው አለብኝ፡፡ ጥያቄው በርካታ መልሶች ቢኖሩትም በዚህ ጽሁፍ ለማቅረብ የመረጥኳቸው ግን ሁለቱን ብቻ ነው፡፡
አጉል ህልመኞች
በዚህ ስርዓት ተጠቃሚ በመሆናቸው ብቻ የሌሎችን ወገኖቻቸውንና የሀገርን ጉዳት ማየት ካልቻሉ ወይም ካልፈለጉ ሆዳሞችና በህወሓት የዘረኝነት መርዝ ከተበከሉ ጥቂቶች በቀር የኢህአዴግን መሰንበት የሚፈልግ ዜጋ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች የማገኛቸዉ ሰዎች ምኞትም የስርዓት ለውጥን ማየት ነው፡፡ ነገር ግን “እነዚህ ሁሉ ሰዎች የሚፈልጉትን ለውጥ ለማየት ምን አይነት አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው?” ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ አስደሳች አይደለም፡፡
አንዳንድ ለዉጥ ፈላጊዎች ቁጭ ብሎ ከመመኘት በቀር ለለዉጡ መምጣት የሚያደርጉት ምንም ነገር የለም፡፡ ለምን አንዳች ነገር እንደማያደርጉ ስትጠይቋቸው ከምታገኟቸዉ መልሶች መሃከል “እነዚህን መዥገሮች እሱ ይንቀላቸዉ እንጂ በሰው ሃይልማ የሚሆን አይደለም፤ ህዝቡን ከፋፍለውታል እኮ ምን ማድረግ ይቻላል? . . .” የሚሉት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ሰዎች ምንም እንዳይሰሩ ያደረጋቸዉ ትልቁን ምክንያት ጠጋ ብላችሁ ስትመረምሩ ግን ፍርሃት ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡ ፕ/ር መሳይ ከበደ “The Impasse of Fear in Ethiopia and the Necessity of Comprehensive struggle ” በተሰኘ ፅሑፋቸዉ እንዳስቀመጡት ፍርሃት የጨመደደው ህዝብ ሁሌም ምንም ላለማድረጉ የሚያቀርባቸው በርካታ ምክንያቶች ይኖሩታል፡፡
ሌሎቹ ለዉጥ ፈላጊዎች ደግሞ ለዉጥ ሊያመጡ የሚችሉ እንቅስቃሴዎቸን በማድረግ ረገድ ከላይኞቹ የተሻሉ ቢሆኑም የጀመሩትን መጨረስ ግን የማይሆንላቸው ናቸው፡፡ እያደረጉ በነበረዉ እንቅስቃሴ ሳቢያ አንዳች ችግር ሲደርስባቸው ከመንገዳቸው ይወጣሉ፡፡ “በዚህኛው አመተምህረት በተደረገው ምርጫ ሳቢያ ለእስር ተዳርጌ ነበር፤ በዛኛው ወቅት በተደረገው ሰልፍ ላይ ተገኝቼ ተደብድቤያለሁ” ማለት ይቀናቸዋል፡፡ አሁንስ? ስትሏቸው ግን መልሳቸው “ጎመን በጤና” ነው፡፡ እንደነዚህ አይነቶቹ ሰዎች መጀመሪያዉኑ እየታገሉት የነበረውን መንግስት ግፈኝነት በሚገባ ያወቁት አይመስሉም፡፡
የቆረጡ ለዉጥ ፈላጊዎች
እነዚህኞቹ አስቀድሞ ከተጠቀሱት ጋር የለዉጥ ፍላጎታቸው ቢያመሳስላቸውም ለውጥን ለማምጣት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መኖሩና ቁርጠኝነታቸው ደግሞ የተለዩ ያደርጋቸዋል፡፡ “እሱ ያመጣዉን እሱ እስኪመልሰው” በማለት እጃቸውን አጣጥፈው አይቀመጡም፡፡ ለለውጡ እዉን መሆን የሚችሉትን ሁሉ ያዋጣሉ፡፡ ከነዚህ ሰዎች መሀከል በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀስ የሚገባው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን መዉሰድ ይቻላል፡፡ እስክንድር ለለዉጡ ያለውን ሁሉ እየከፈለ ያለ ሰው ነው፡፡ ወደስምንት ጊዜ ያህል ሲታሰርና ሲፈታ፣ የመፃፍ መብቱን ሲገፈፍ፣ ሲደበደብ፣ ንብረቱ ሲወረስና ከሚወዳት ባለቤቱና ልጁ ጋር በአካል መለያየት ግድ ሲለዉ ሁሉ በአላማው ከመጽናት ውጭ ለአፍታ እንኳን ሸብረክ ሲል አልታየም፡፡ እስክንድርና መሰሎቹ ዲሞክራሲ እንዲሰፍንና ነፃነት እንዲገኝ ካስፈለገ ከምኞት ባለፈ ስራና መስዕዋትነት እንደሚጠይቅ ገብቷቸዋል፡፡ ለገባቸው እውነት ደግሞ እየኖሩ ነው፡፡ እነ እስክንድር ይሄን ሁሉ መስዕዋትነት ሲከፍሉ ታዲያ ሁኔታው ያማያማቸው ሆኖ አይደለም፡፡ ህመሙን ጥርሳቸውን ነክሰው እየቻሉ እንጂ!
አቶ ኤፍሬም ማዴቦ “ከዊሃ እስከ ኦምሃጀር-አንድ ሰሞን ከአርበኞች ጋር” በሚል ርዕስ በቅርቡ ባስነበቡን ጽሑፋቸዉ የአርበኞች ግንቦት 7 ጦርን ለመቀላቀል ከአሜሪካን ሀገር ከተደላደለ ኑሮዋቸው ተነስተው ሲሄዱ ይሰማቸው የነበረዉን ከሚወዱት ልጃቸው የመለየት ህመም በዉብ አገላላፅ ተርከዉልናል፡፡ አቶ ኤፍሬም አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ ሊሸኛቸው የመጣዉን የ17 አመት ልጃቸውን ሲሰናበቱ “ልጄ ይሄን ማድረግ አልፈልግም ነገር ግን ማድረግ አለብኝ” ያሉት ፊታቸው በእንባ እየታጠበ ነበር፡፡ የማይፈልጉትን ነገር ለማድረግ እራሳቸዉን ያስገደዱበትን ምክንያት የገለጹት “የምወደውን አንድ ልጄንና ጥሩ ስራዬን ደህና ሁኑ ብዬ በረሃ የገባሁት ሃገሬ ዉስጥ ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ አብቦ ለማየት ነው” በማለት ነው፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድርና አቶ ኤፍሬም ምንም እንኳን ለውጥን ለማምጣት የሚሄዱበት መንገድ ለየቅል ቢሆንም ሁለቱም ግን ለለውጡ ያላቸውን ሁሉ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል፡፡ አንደኛቸው ለውጡ ግድ ብሎአቸው ቤታቸው እስርቤት ሲሆን ሌላኛቸው ዱርቤቴ ብለዋል፡፡ ሁለቱም ከሚወዷቸው ወንዶች ልጆቻቸው ጋር ተለያይተዋል፡፡ ሁለቱም ለውጥ በምኞት ብቻ እንደማይመጣ ያውቃሉና እራሳቸው ሄደው ይገናኙት ዘንድ በተለያየ መንገድም ቢሆን በጉዞ ላይ ናቸው፡፡ በመጨረሻም . . .
በኢትዮጵያ እኩልነት ዴሞክራሲ ነፃነትና ፍትህ እንዲሰፍን የምንመኝ ሁላችን ከቀን ህልማችን መንቃትና ምኞቶቻችንን ወደ ተግባር ለመለወጥ መንቀሳቀስ ያስፈልገናል፡፡ ከመንቀሳቀስ ያገደን ፍርሃታችን ከሆነ በቀደመው ንዑስርዕስ ስር የጠቀስኩት የፕ/ር መሳይ ጽሑፍ ፍርሃትን ለመዋጋት የሚያስቀምጠው አንድ መፍትሄ አለ፡፡ ድርጊት! ራሳችንን ለፈሪነት የተመደብን አድርገን የምንቆጥርና በሌሎች ደፋርነት መንፈሳዊ ቅናት የሚያድርብን ሰዎች ካለን ፕ/ሩ የጠቀሱት የፈላስፋው አርስቶትል ሃሳብ ሳይጠቅመን አይቀርም፡፡ አርስቶትል “ጀግና ለመሆን ጀግንነትን መለማመድ ያስፈልጋል” ይለናል፡፡ ለአርስቶትል ድፍረት እንደሌሎቹ የሞራል እሴቶች ሁሉ አብሮን የሚወለድ እምቅ ሃይል ሲሆን እውን ለመሆንና ለመዳበር እንዴሎቹ እሴቶች ሁሉ ልምምድ ያስፈልገዋል፡፡ አስፈላጊዉ ጥንቃቄ እንደዳለ ሆኖ እስኪ እስከዛሬ ያላደረግነዉን አንድ ድፍረት የተሞላበት ድርጊት እናድርግ፡፡ ፕ/ሩ እንደሚሉንና እኔም እንደማምነው ድርጊት ስኬትን ያመጣል፡፡ ስኬቱ የቱንም ያህል ትንሽ ቢሆን በራስ መተማመንን ይወልዳል፡፡ በራስ በተማመን ሲኖር ደግሞ ፍርሃት ይጠፋል ወይም ችግር ሊሆን በማይችልበት ደረጃ ዝቅ ይላል፡፡
ከፍርሃታችን ወጥተን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ሳለን ከኢህአዴግ በሚወረወርብን ዱላ ተሰብረን ከመንገዳችን ላለመውጣት ደግሞ የገዢዉን ፓርቲ ማንነት ጠንቅቆ ማወቅና ቢያንስ የስነልቦና ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለማንጠብቀው ነገር አንዘጋጅም፡፡ ያልተዘጋጀንበት ነገር ደግሞ ሁሌም ይጥለናል፡፡ በመሆኑም የምንታገለው ስርዓት ስልጣኑን ላለማጣት የቱንም አይነት ጭካኔ የተሞላው እርምጃ እንደሚወስድ ማወቅና ለዛም እራስን ማዘጋጀት ግድ ይላል፡፡ ደግሞስ ኢህአዴግ ምን ሊያደርገን ይችላል? ሊያደርግብን የሚችለው ሁሉ አስቀድሞም ከአፈር በታች እንዲዉል የተወሰነበት ስጋችን ላይ አይደለምን?
መልካም አዲስ አመት!
መስከረም 3/ 2008
Average Rating