==================================
* ” የሳውዲና የኢትዮጵያ የሰራተኛ ውል ተፈረመ! “ወገን ለወገን – በሳውዲ ” ፊስ ቡክ ገጽ
* ትክክለኛ መረጃ ህይዎት ነው ፣ የተሳሳተ መረጃ ጎጅ ነው!
* የተሳሳተ መረጃ እንዳይጎዳን የመንግስት ተወካዮች ለመረጃ በራቸውን ይክፈቱ !
* በአዲሱ ኮንትራት ዙሪያ ባለድርሻው ስደተኛ ይምከርበት
ከቀናት በፊት የሳውዲ ታዋቂ ጋዜጣ አረብ ኒውስ #arabnews ያወጣውን መረጃ ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን በቀረበው መረጃ ዙሪያ ግራ የተጋቡ መረጃዎች ግራ እንዳጋባቸው በተለያዩ መንገዶች ገልጸውልኛል ። ይህንኑ በአረብ ኒውስ የቀረበውን መረጃ ተከትሎ የሳውዲ ሰራተኛ ቀጣሪዎች ከኢትዮጵያ ሰራተኛ ማስመጣት እንደሚችሉ መመሪያ መሰጠቱንና የሁለት ዓመት እግዱ መነሳቱን በማለዳ ወጌ መረጃ ማቅረቤ አይዘነጋም ። የአረብ ኒውስ #arabnews መረጃ እንደተለቀቀ በበርካታ ማህበራዊ ገጾች ውሉ ስለመፈረሙ ተጨማሪ ዝርዝርና የተሳሳቱ መረጃዎችን በመሰላቸው መንገድ ሲያሰረጩ ተስተውሏል ! አንዳንዶችማ የተለያዩ ያልተጨጡ ትንታኔዎችን በመጨመር ” ሳውዲና ኢትዮጵያ የሰራተኛ ውሉን ተፈራረሙ ! ” በሚል መረጃ በማቅረብ ወደ ሳውዲ ለመምጣት የቋመጡትን ወገኖች ነፍስ አማልለዋል ።
እንደኔው ሳውዲ ላለን ስደተኞች መረጃ በማቀበሉ ረገድ እየተጋ ያለ አንድ የመረጃ አቅራቢም የተሳሳተ መረጃ ማቅረቡን ታዝቤያለሁ ። የአንድ ወገን የፖለቲካ ፓርቲ ዘመም መረጃ ቅበላውን አሻሽሎ አሁን አሁን ወደ ህዝባዊና ሚዛናዊ የመረጃ ቅበላ ደረጃውን ከፍ እያደረገ በመጣው የ“ወገን ለወገን – በሳውዲ ” ፊስ ቡክ ገጽ ” የሳውዲና የኢትዮጵያ የሰራተኛ ውል ተፈረመ! “ በሚል መረጃ ማቅረቡ ይጠቀሳል። የ“ወገን ለወገን – በሳውዲ ” መረጃ ጉዳዩን ሲያብራራ እንዲህ ይላል ” በመስከረም ወር ይፈረማል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውን የኢትዮጵያና የሳውዲ አዲሱ የኮንትራት ሰራተኞች ውል ተፈረመ። የሳውዲ ሰራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር ከሶስት ሀገሮች ጋር ተፈራረምኩ አለ። ከነዚህ ሶስት ሀገሮች በግልፅ ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ ስም ብቻ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ሌላ ከሁለት ሀገሮች መፈራረሙን ግን ይፋ አድርጓል። “ ሲል አረብ ኒውስን በመረጃ ምንጭነት ጠቁሟል ። ከላይ የጠቀስኩት በማለዳ ወግ ያቀረብኩት መረጃና የ“ወገን ለወገን – በሳውዲ ” “ውሉ ተፈረመ !” የሚለው መረጃ ምንጭ የሳውዲ ታዋቂ ጋዜጣ አረብ ኒውስ ሆኖ እያለ የተለያየ መረጃ መቅረቡ ነዋሪውን ግራ አጋብቶ ሰንብቷል!
በርካቶች ይህን መረጃ ተከትሎ ከሀገር ቤት ሳይቀር ወደ ሳውዲ መምጣት ለሚፈልጉ ኤጀንሲዎች ምዝገባ መጀመራቸውን ተሰምቷል ። በስምምነቱ ዙሪያ የተፈረመ ውል ይኖር እንደሁ በሳውዲ የመንግስ ት ኃላፊዎች በኩል ያደረግኩት ማጣራት የሁለቱ ሀገራት የስምምነት ውል አለመፈረሙን ማረጋገጥ ችያለሁ። በ” ወገን ለወገን – በሳውዲ “ ምንጭነት የተጠቀሰው አረብ ኒውስ ስለ ውሉ መፈረም የጠቀሰው ምንም መረጃ የለም። የአረብ ኒውስን ዘገባ የሚያትተው በማለዳ ወግ የመረጃ ግብአት እንደ ጠቆምኩት የሳውዲ ሰራተኛ ቀጣሪዎች ከኢትዮጵያ ሰራተኛ ማስመጣት እንደሚችሉና የሁለት ዓመት እግዱ መነሳቱን ከመጥቀስ ባለፈ የሳውዲና የኢትዮጵያ የሰራተኛ ውል ተፈረመ የሚል መረጃ አላቀረበም !
የአረብ ኒውስን ዜና የተሳሳተ ትርጉም እየተሰጠው ሲሰራጭ መረጃውን እውነት ያስመሰለው በአዲሱ አመት 2008 ዓም ከመግባቱ አስቀድሞ በሳውዲ የኢትዮጵያ ኢንባሲ አንድ ሃላፊ ” የኢትዮጵያ መንግስት በአዲሱ ዓመት ከሳውዲ መንግስት ጋር የሰራተኛ ውሉን ይፈራረማል! ” በሚል የሰጡት መግለጫ መሆኑ ይጠቀሳል ። በአዲሱ አመት የሰራተኛ ስምምነት ውሉ ይደረጋል የሚለው በሪያድ የኢትዮጵያ ኢንባሲ ያያኔ መግለጫ በፋናና በተለያዩ የኢትዮጵያ መንግስት ዜና ምንጮች ቀርቦ ነበር ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአረብ ኒውስ መረጃው ኢትዮ ጵያ ተጠቅሳ ስለሰራተኞች ማስመጣት መረጃ ከተሰረጨ ወዲህ በተለያዩ ማህበራዊ መገናኛ ገጾች ” የሰራተኛ ውል ተፈርሟል ” የሚል መረጃ መተላለፉን በሪያድ የእትዮጽያ ኢንባሲ ” ሀሰት ነው !” ብሎታል ። መረጃው መሰረተ ቢስ መሆኑን የጠቀሰው ኢንባሲው ባወጣው ማስታዎቂያ ስምምነቱ በሁለቱም መንግስታት ህግ አውጭዎች ከጸደቀ በኋላ በድርድር የሚፈጸም መሆኑን ጠቁሟል !
ትክክለኛ መረጃ ህይዎት ነው ፣ የተሳሳተ መረጃ ጎጅ ነው ! የተሳሳተ መረጃ እንዳይጎዳን የመንግስት ተወካዮች ለመረጃ በራቸውን ይክፈቱ ፣ በስምምነቱ ዙሪያም ሆነ በተለያዩ ወቅታዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መረጃ ያቀብሉ ! በአዲሱ ኮንትራት ዙሪያ ባለድርሻው ስደተኛ ይምከርበት !
ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
መስከረም 6 ቀን 2008 ዓም
Average Rating