መንገዱ አያገናኘኝ አያሰኛኝ የለም ፣ እኔም የሰማሁትን ያየሁትን አካፍላችሁ ዘንድ ለምዶብኛል: ) የማካፍለውን መረጃ የሚቀበሉ ይማሩበት ይሆናል ፣ የማይቀበሉ የማያምኑት ግን እንዳላመኑ ይቀራሉ ፣ ጊዜው ይርዘም እንጅ አንድ ቀን ይቀበሉታል ! እኔ ህሊናየ ፈቅዶ የማውቀውን ፣ የቻልኩትንና የሚጠበቅኝን የዜግነት ድርሻ መወጣቴን ነው ፣ ከዚህ ባለፈ ስላመኑኝ ፣ስለተቀበሉኝ ደስ ይለኛል ፣ ስላላመኑ ስላልተቀበሉኝ ፣ እዝነ ልቦናቸውን ይፍታላቸው ከማለት ውጭ የምለው አይኖርም !
ይህን ያልኩበት ዋናኛ ምክንያት እኩለ ቀን ላይ ራስ የሚበጠብጥ ፣ የሚያዞረውን የደማም ሐሩር ተቋቁሜ ስራየን ለመከዎን ተፍ ተፍ ስል አንድ ወዳጀ ደውላ እንዲህ ያለችኝን እሳቤ በማድረግ ነው፣ መልዕክቱ እንዲህ ይላል ” ነቢዩ እኔ የሚገርመኝ በተጓዝኩበት ቦታ ሁሉ የምታቀርበው ነገር አታጣም ፣ ዛሬ ደግሞ በጨረፍታ የነገርከን በሪያድ ደማም መካከል አገኘሁት ያልከን የመሀመድ ታሪክ ያሳዝናል ። ካንድ ጓደኛየ ጋር ስለዚህ ጉዳይ እያወራን ነበር ። በጉዞ ማስታዎሻዎችህ ዙሪያ ብዙ ተከራከርን ፣ አሷ እንደኔ ስለማራውቅህ አልፈረድኳትም ፣ አጥብቃ እንዴት በየሄደበት እንዲህ አስገራሚ ነገር ይገጥመዋል ብለሽ ታምኛለሽ ? ያለችው እኔንም ግራ አጋባኝ ፣ ይቅርታ አሁን አሁን እየፈጠርክ የምትጽፈው ሁሉ የሚመስለው አለና የእረኛው መሀመድን ታሪክ ቢቻል በቪዲዮ ካልተቻለ በድምጽ ብታቀርበው ብዙ መረጃህን ለመቀበል ለሚቸገሩ ማሰረጃ ይሆናል ፣ እባክህ አቅርበው ! እኔ ግን የሚገርመኝ አንተ በምትሄድበት ሁሉ ባለጉዳዮች ይከተሉሃል ልበል ? ” የሚል መልዕክት አስተላለፈችልኝ !
አንዳንድ ወገኖችን ግራ ያጋባው ይህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ እኔንም ቢሆን አልፎ አልፎ ግራ ሳያጋባኝ አልቀረም። በየመን ደላለሎች አይናቸው የጠፋ ብልታቸው ተገዝግዞ የተቆረጠ ፣ ስደተኛው ሸዋን ግዛው ንጉሴን ፣ እረኞቹን ፣ ተምር ለቃሚዎችን ፣ ተገፊ የኮንትራት ሰራተኞቻችን ጨምሮ በርካታ ወገኖቸን እና ሌላም ሌላ የስደተኛ ወገኖቸን ታሪኮች መንገዱ አሳይቶኛል ። ” ጋዜጠኛ ነህና ይህን በደል ተመልከት ” ተብየም አንድም መረጃ ደርሶኝ ያውቃል ፣ በደረሰኝ መረጃ መሰረት ባለቤቶቹን አፈላልጌ አግኝቸ የምስክርነት ቃላቸውን ተቀብያለሁ ! ከሁሉም የማይረሱኝን ምስክርነቶች የማገኛቸው በጅዳ ቆንስልና በሪያድ ኢንባሲ ዙሪያ ነው ። የመብት ጥበቃው ጎድሎባቸው በመጠለያ ተብየው ማጎሪያ የተጠለሉ ምንዱባንን ግፍ ሊሸፋፍኑ ከሚፈልጉ ያልታደሉ ወገኖች ጋር ተፋጥጨ መረጃ ሰብስቤ አውቃለሁ ። በኩባንያ ስራ ምክንያት ሳውዲን ከጫፍ እስከ ጫፍ ስጎበኝ መንገዱ ተበዳዮችን በየአጋጣሚ እያገናኘኝ እንደ ጨው ከተበተነው ወገኔ ላይ የደረሰውን ግፍ በደል የስደቱን መከራ “እህ ” ብየ አድምጫለሁ !
ይህ ሁሉ ሲሆን መረጃ ቅበላየ የማይመቻቸው ሹማምንትና አሸርጋጆቻቸው የሚጨነቁት ራሳቸስ ለሚያጠለሹት የገጽታቸው ግንባታ ነውና መብት ማስከበሩን ፈነጋግለው እኔኑ እንደ ተቃዋሚ ያዩኛል ። ድክመታቸውን እንዲያርሙ በመረጃ ማስረጃ በደሉን የማቀርብላቸው ሹሞች ሁሌም እየተፈታተኑኝ ከመንገዴ ባያቆሙኝም መረጃ አቅራቢውን እኔኑ ደካማውን በአምላክ ተጠባቂ ለመጉዳት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም !
የፈጣሪ ስራ ይገርመኛል ፣ በምሄድበት ቦታ ሁሉ ማንነቴን የማያውቁኝ ወገኖቸ በደል ተፈጽሞባቸውና ስደቱ ጎድቷቸው አውቀው የተከተሉኝ ይመስል የስደት ዳፋውን ያደረሰባቸውን በደል ያጫውቱኛል። እናም በአካል የሚገጥመኝን ፈቃደኝነታቸውን እየጠየቅኩ ካስተማረን በሚል የማለዳ ወግ ግብአት ለመረጃ ያህል ቀነጫጭቤ አቀርበዋለሁ ! ” አንተ በምትሄድበት ሁሉ ባለጉዳዮች ይከተሉሃል ልበል ? ” ብለው ግራ ለተጋቡት ሁሉ ምላሽ አዎ ይከተሉኛል ነው !
ዛሬ ማለዳ በሪያድ ደማም መካከል ባለው በርሃ ስጓዝ መንገዱ ያገናኘኝን ከጨነቀው ከጠበበው ወንድም ጋር ያደረግኩትን መረጃ ተከታተሉት! በዚህ አጋጣሚ መሀመድ የእሱ መከራ ለቀሪው አስተማሪ ይሆን ዘንድ እንዳስተላልፈው ፈቃድ ጠይቄው በሰጠኝ አዎንታ መሰረት ማስተላለፊን እንድትረዱልኝ መጠቆም እወዳለሁ !
ስደት ክፉ ነው ፣ ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
መስከረም 11 ቀን 2008 ዓም
Average Rating