የአንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ስርዓተ ቀብር ዛሬ በስደት በኖረበት በሰሜን አሜሪካ ቨርጂኒአ ዛሬ ማለዳ ተፈጽሟል።የዘ-ኢትዮጵአያ አዘጋጅና አሳታሚ ጋዜጠኛ ደረጄ ደስታ ባለፉት ጥቂት ቀናት በብዙ ድካም በርከት ያሉ ወዳጆቹንና የሙያ አጋሮቹን አነጋግሮ መረጃ አገላብጦ የሕይወት ታሪኩን አዘጋጅቶ ለስርዓተ ቀብሩ አድርሷል።ስለ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ወደፊትም የሚያውቁ ብዙዎች ቀረ የሚሉትን ጨምረው የእውቁን ባለሙያ ግለ ታሪክ ይጽፉ ወይ ደረጄ ደስታ በነካ እጁ ቢያስነብበን መልካም ነው። ለዛሬ ለስርዓተ ቀብሩ አዘጋጅቶት የነበረውን አስከትለን እናቀርባለን።
ሙሉጌታ ሉሌ ሐምሌ 1933 – መስከረም 23 ቀን 2008 ( July 12, 1941 – Oct 4, 2015)
ያለፉት 50 ዓመታት ስመ ገናናው ጋዜጠኛ፣ ፀሐፊ፣ የታሪክና ፖለቲካ ተንታኝ ሙሉጌታ ሉሌ በ1933 ቀን ዓ.ም በጎጃም ክፍለ አገር ቢቸና ይልማና ዴንሳ በምትባል ሥፍራ ተወለደ። በአምቦ ከተማ ማዕረገ ሕይወት ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ትምህርት ቤት አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀ። በደብረ ብረሀን ኃይለማርያም ማሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም ተከታትሏል።
በ1950 ዎቹ መጀመሪያ ላይ፣ ወደ ናዝሬት የባይብል አካዳሚ በመግባት፣ ብዙ ነገር የገበየበትን ትምህርትና፣ ዘላቂ መሠረት የሆነውን እውቀት በመውሰድ፣ የሥራ ዓለምን አንድ ብሎ የጀመረው፣ እዚያው በሰለጠነበት የባይብል አካዳሚ መምህር በመሆን ነበር። በቆይታውም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እውቅ የሆኑትን እንደነ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ዶ/ር ላጲሶ ጋዴቦ፣ አቶ ሌንጮ ለታና የመሳሰሉትን ማስተማሩ ተዘግቦለታል። ጋሽ ሙሉጌታ የስነ መለኮትና የቤተክርስቲያን ታሪክን በጥልቀት ማወቁም ይነገርለታል።
በ1955 አካባቢ አንስቶ የምስራች ድምጽ ሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ ሲሰራ የቆየ ሲሆን፣ ሥራውንና ብዕሩን በአድናቆት የተመለከቱ የሥራ ባልደረቦቹና አለቆቹ የሆኑት፣ እነ ጳውሎስ ኞኞና ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር መጥቶ እንዲሠራ አግባብተውታል። በዚህ መሠረት አቶ ሙሉጌታ በ1957 ግድም በአዲስ ዘመን ተቀጠረ። ለበርካታ ዓመታት አቶ ሙሉጌታን በወዳጅነት የሚያውቁት አቶ አሰፋ ጫቦ እንደተናገሩት፣ አቶ ሙሉጌታ አዲስ ዘመን ላይ ይቀጠር እንጂ በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ጽሑፎቹን የሚያሳትም ዘርፈ ብዙ ጋዜጠኛ ነበር። እንደ ሔራልድ፣ የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ድምጽ፣ መነንና አዲስ ሪፖተር የመሳሰሉት ጋዜጦች ላይ በአማርኛና በእንግሊዝኛ በርካታ ጽሑፎችን አቅርቧል፣ የመነን መጽሔት ዋና አዘጋጅ የነበረም ሲሆን ፣አንዳንዶቹም ላይ በረዳት አዘጋጅነት ሰርቷል።
ከ1954 ጀምሮ ጽሑፎችን በማቅረብ ኋላም የቀድሞው መንግሥት የባህልና ማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት ሻለቃ ግርማ ይልማ አቶ ሙሉጌታ ሉሌን በአካል የሚያውቁት ከ1963 ጀምሮ መሆኑን ገልጸዋል። መቸም ኢትዮጵያ ውስጥ
ከህትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ጋር ግንኙነት አለኝ የሚል ሰው ሙሉጌታ ሉሌን ያውቃል። ያነበበም እንዲሁ ነው። ህዝብን በሚያኮራ መንገድ ሲያገልግል የኖረ በመሆኑም ግዴታውን ተወጥቶ ያለፈ ትልቅ ሰው ነው።
አቶ ሙሉጌታ በ1968 ወደ ኤርትራ፣ በልዩ የግዳጅ ሥራ ተጉዞ “ኢትዮጵያ” የተሰኘችዋን ሳምንታዊ ጋዜጣ በዋና አዘጋጅነት እንዲያጠናክር ተመድቦ መሄዱን፣ በሪፖርተርነት አብሮ ተመድቦ የሄደው፣ የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች ፕሬዚዳንት ክፍሌ ሙላት ገልጿል። እዚያም ጥቂት እንዳገለገለ የምስራቁን የሶማልያን ወረራ ለመመከት የሚያስችል ልዩ የፕሮፖጋንዳና ሥነ ጽሑፍ ክፍል በማስፈለጉ በማስታወቂያ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጋር ልዩ መመሪያ ሲቋቋም መምሪያውን እንዲመራ የታጨው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ መሆኑን ክፍሌ ገልጧል። በዚህ መሠረት መንግሥት በ1970 መጀመሪያ ላይ አቶ ሙሉጌታ ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያንቀሳቅስ የፕሮፖጋንዳና ሥነጽሑፍ ሥራ እንዲመራ አድርጓል። አሉ የተባሉ ከየመምሪያው የተውጣጡ ባለሙያዎችና የሥነጽሁፍ ሰዎችን በመምራት ይህንንም ግዳጁን በብቃት የተወጣና ለአገሪቱ ድልም ከበስተጀርባ ሆኖ ትልቁን ድርሻ የተጫወተ ጀግና መሆኑን አንጋፋው ጋዜጠኛ ክፍሌ ሙላት መስክሯል።
ይህ መሆኑን በትክክል የሚያስታውሱት አቶ አሰፋ ጫቦም ሙሉጌታ ሉሌ፣ የሶማልያና የኤርትራን የፖለቲካና ታሪክ ነክ ጉዳዮች በሚገባ አንብቦና ተንትኖ የሚያውቅ ባለሙያ ነው። ባልደረቦቹንም እየሠራ ጭምር ሲያስረዳና ሲያማክር እንደነበር ማወቃቸውን ተናግረዋል። አቶ አሰፋ እንኳን የአገሩን ታሪክና የፖለቲካ ትንታኔና ትችቶች ቀርቶ፣ የአውሮፓንና የአሜሪካን የፖለቲካ ትንታትኔዎችን የሚያነብና አሳምሮ የሚያውቅ ሰው ነው። ይህንንም በጽሑፎቹ ውስጥ የሚጠቃቅሳቸው ከመሆኑም ሌላ “ይህን መጽሐፍ አንብበሃል ይህን ተመልክተኸዋል?” እያለ አዲስ አበባ ተቀምጦ አሜሪካ ያለን ሰው የሚፈትን አንባቢ መሆኑን ገልጧል።
በኤርትራም የቀይ ኮከብ ዘመቻ ሲጀመር፣ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ፣ በበዓሉ ግርማ የተመራውን የጋዜጠኞች ቡድን በምክትልነት እየመራ ሥራውን ያከናውን እንደነበረ ክፍሌ ገልጧል። የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዘዳንትና አንጋፋው ጋዜጠኛ ክፍሌ ሙላት ራሱ በደረሰበት አደጋ ከሚያገግምበት ሆስፒታል አልጋ እያቃሰተና እያለቀሰ – የሙያ አባቴ ስለሚለው አቶ ሙሉጌታ ሉሌ ተናግሮ የሚጠግብ አልሆነም። ሙሉጌታ ለሱ ተገልጾ አያልቅም። ምክንያቱም “ብዙ ሰዎችን አፍርቷል። ለኢትዮጵያም ሞቶላታል። እንደ ወታደር ተዋግቶላታል፣ እንደ ከያኒ ዘምቶላታል… “እያለ ይቀጥላል ክፍሌ።
እስከ 1975 ድረስ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ኃላፊነት በመሾም ሲሰራ የነበረው አቶ ሙሉጌታ ሉሌ፣ በፖለቲካና የቅስቀሳ ሥራዎች ብቻ ሳይወሰን፣ ተወዳጅ የሆኑ ማህበራዊና የመዝናኛ ዝግጅቶችንም በመምራትና ጽሑፎችንም በማበርከት ይታወቃል። እውቁ የቪኦኤው ጋዜጠኛ አዲሱ አበበ ስለዚሁ ሲገልጽ “ በተለይ በወቅቱ የእሁድ ፕሮግራም ሲዘጋጅ አቶ ገዳሙ አብርሃ የእሁዱ ጧት ፕሮግራም ኃላፊነት ተረክቦ እኔና ንጉሤ አክሊሉን በሟቹ ታደሠ ሙሉነህ አስተብባሪነት እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ አንዳንዴ ስክሪፕት ጽፎ ይሰጠናል። ይሄ ጽሑፉ እንጨት እንጨት ይላል ማነው የጻፈው ይላል? ወይ እኔ ንጉሤ ነው እላለሁ፣ ወይ ንጉሤ አዲሱ ነው ይላል። “ሁለታችሁም ያው ቄሶች ናቸው ዞር በሉልኝ!” ብሎ ይቀልድብናል። ከዚያ ደላልዞ እንደገና የመጻፍ ያህል አስተካክሎ ይሰጠናል።
አዲሱ እንደሚለው ልክ እንደ ጽሑፉ ለሬዲዮም የሚጠቀምባቸው የተለያዩ የብዕር ስሞች ነበሩት። በእሁድ ጧት ፕሮግራም በተለመደ ስም በየሳምንቱ የማይቀር ጽሑፍ ነበረው። አቶ ሙሉጌታ ሉሌ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ በመሆን ከ 1975እስከ 1983 አገልግሏል። በዚህ ቆይታው በሥሩ- አዲስ ዘመን፣ ኢትዮጵያን ሄራልድ፣ የዛሬዪቱ፣ በሪሣ (በኦሮምኛ የሚታተም) እና አል አኻረም የተባለ የአረብኛ ጋዜጦችን መርቶ አስተዳድሯል። ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያን ሄራልድ አዲስ ዘመንና የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጽሑፎችን ሲያበረክት ርዕሰ አንቀጽ ሳይቀር ጽፎ እየሰጠ ሠርቶ ሲያሠራ ኖሯል።
የመንግሥት ለውጥ እስከ ተካሄደበት እስከ 1983 ድረስ ሲያገለግል ከቆየ በኋላም እንደ ብዙዎቹ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ለዓመታት ካገለገለበት ከሥራ ገበታው ተፈናቅሏል። ከሥራው ይፈናቀል እንጂ፣ ከሙያው ያልተፈናቀለ ባለመሆኑ፣ ገና በለውጡ የመጀመሪያው ዓመት (በ1984) ከሙያ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን የጦቢያ መጽሔትን አቋቋሟል። ይበልጥ ገናና የሆነበት ብዕሩን በጉጉት ከሚጠበቅ መጽሔት ጋር ለህዝብ ማብቃቱን አሳይቷል። እነ ፀጋዬ ገብረ መድህን አርአያ የተባሉት ስመ ጥር የብዕር ጀኔራሎች የተወለዱትም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው። ጋሽ ሙሉጌታ ተርቡ፣ ስንሻው ተገኝ፣ ስልቁና የመሳሰሉ ሌሎች የብዕር ስሞችም ነበሩት።
. የነጻውን ፕሬስ ጫናና የነፀጋዬ ገብረመድህንን ጡጫ መቋቋም ያልቻለው መንግሥት፣ የሙያ አባት የሆኑትን፣ እነ አቶ ሙሉጌታ ሉሌን ሳይቀር፣ በክስና እስራት ያጣዳፍ ጀመር። አቶ ሙሉጌታ ብዙ ወጥቶ ወርዷል። ከ16 ጊዜ በላይ ክሶች የተመሰረቱበት ሲሆን ለተደጋጋሚ ጊዜ ታስሯል። በደህንነት ሰዎች መኪና ተድጦ ሊገደል ከአፋፍ ተርፎ የወጣ መሆኑ ሁሉ በሰፊው የተነገረበት፣ ቢሮው በእሳት የጋየበት ጋዜጠኛ ነው። አገር ቢቀማም ብዕሩን ያልተቀማ ጀግና ነበር። ወዳጆቹ እንደሚናገሩት በተለይ በግድያ ሙከራነቱ ሰለሚጠረጠረው የመኪና አደጋ ፣ በተአምር ተርፎ ሆስፒታል በተኛበት ወቅት ሆስፒታልም ድረስ እየተከታተሉ ያስቸገሩትን የደህንነት አባላት ለመሸሽ ህክምናውን በመኖሪያ ቤቱ ተኝቶ በወዳጅ ሐኪሞች ለመከታተል የተገደደበት ሁኔታ ሁሉ ነበር። “እንኳን እጄን አልቆረጡኝ ፣ብዕር የምይዝበት እጄ እስካለ ድረስ ተርፌያለሁ” እያለ ወዳጆቹን ያጽናና እንደነበር በቅርብ የሚያውቁት ወዳጁ አቶ ዮሐንስ አበበ ተናግረዋል።
ሁኔታው እየበዛ በመምጣቱም በብርቱ የወዳጅ ጉትጎታ አገር ትቶ እንዲወጣ ተወስኖ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በወዳጆቹ ድጋፍ እንዲወጣ ተደርጓል። ምክንያቱም እስከ 16 የሚደርሱ ክሶች የተመሠረቱበት ሰው ነበር። “ለምን አትወጣም እስኪገድሉህ ነው እንዴ የምትጠብቀው?” ሲባል “በአንድ ስሙ ወይ 20 ወይም 30 ይሙሉና ጊነስ ቡክ ውስጥ ይመዘገባል” እያለ ይቀልድ ነበር፡፡ ነገሩ ግን የሕይወት እንጂ የቀልድ አልነበረም። ስለ እስር እንግልቱ ለምን በአደባባይ በብዛት እንደማያወራ ሲጠየቅ “ የእነዚህን ድንክ ሰዎች ሥራ ማውራት ሌሎች ታዳጊ ጋዜጠኞችን ማስበርገግ ይሆናል” የሚል መልስ ይሰጥ ነበር። እሱ ግን ለሌሎቹ የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች መብት ሁሌም እንደቆመ እንደተቆረቆረ ነበር።
አቶ ሙሉጌታ የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜኞች ማህበር መስራች አባል ሲሆን እነ አቶ ከፍያለው ማሞ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ ም/ፕሬዚዳንት ሆኖ አገልግሏል። እንደ ሲፒጄ ካሉ ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለሙያ ልጆቹና አጋሮቹ መብት ጥብቅና ሲቆም ኖሯል።
ጋዜጠኛ ክፍሌ ሙላት “ሙሉጌታ አፍርቶናል ፤ እኛ ፍሬዎቹ ነን። የኢትዮጵያን ፕሬስ ያነጸና ለኢትዮጵያ ያነባላት ሰው ነው። በአጽሙ እኮራለሁ። የኔ የሙያ አጋሮች የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ተጽናኑ! ተበራቱ! ጋሽ ሙሉጌታ በአምባገነኖች ፣በዘረኞችና በትምክህተኞች ጫማ ስር አልወደቀም! አልተንበረከከም። ቃሉን አላጣፈም። እኛን አፍርቷል። የሙሉጌታ ልጆች ስለሆንን እጽናናለሁ።” በማለትም የሙያ አጋሮቹ ጋዜጠኞቹ እንዲጽናኑ መክሯል።
በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞችም “መልካም ስም ከመቃብር በላይ ዘላለማዊ ሆኖ ይኖራል” በሚል ርዕስ ባወጡት የሐዘን መግለጫ፣ አንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ለአዲሱ የፕሬስ ትውልድ ፈር ቀዳጅ ነው” ብለዋል። አንጋፋው ጋዜጠኛ “በአንደበቱ እውነትን የመሰከረ፤ በሰላ ብዕሩ ሃቅን የፈነጠቀ ለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ምሳሌ ሆኖ ያለፈ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነው” ሲሉም አክብሮታቸውን ገልጠውለታል።
Mulugeta_05
ጋዜጠኞቹ “እንደታላቅ ወንድም፤ እንደሙያ አጋር እና እንደ ጥሩ ምሳሌ እያነሱ መልካም ተጋድሎውን ያስታውሳሉ። የነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች ገድል ሲታወስ ደግሞ፤ የጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ መልካም ስም እንደ ፈርጥ ያንጸባርቃል። በውጭ አገር የምንገኝ የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች፤ የጋሽ ሙሉጌታ ሉሌን መልካም ስም ከመቃብር በላይ ይውላልና የጋሽ ሙሉጌታ ስራ እና ስም ለዘለአለም በክብር ይታወሳሉ።” የሚል መግለጫ አውጥተውለታል።
አቶ ሙሉጌታ ባለሞገስ ነበር። ሆይ ሆይታ አይጥመውም። ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌም ይህንኑ ነው ያሉት “ ረጋ ያለ ነው። ነገርን ግራና ቀኝ ማስተዋል ይችላል፡፡ እውነትን ለመፈለግ ብዙ ይጥራል፡፡ እውነትን ለመናገር ወደኋላ አይልም- አርቆ ያያል። ሙሉጌታ ሰበር ዜና፣ ትኩስ ዜና የሚጥመው ሰው አይደለም። እሱ የሚያተኩረው ትምህርት ሰጪና ጠለቅ ያሉ ነገሮች ላይ ነው። በሰውነቱ ታጋሽ ነገሮችን በትዕግስት ማለፍ የሚችል ነው። ብዙ ጽሑፎችን ትቷል። አርአያ ሊሆን የሚችል ሰው ነው። ራሱ አውቃለሁ ብሎ ከሚያውቀው በላይ የሚያውቅ ሰው ነው። ትሑት ነው። ቢያውቅ እንኳ እንደማያውቅ ሆኖ ይጠይቃል። ከኔ ሰው ይማራል የሚል እምነት የለውም። ይሄን የዘመናችንን ፖለቲካና ታሪክ ያውቀዋልና እኔም ሁሌ ደውዬ እጠይቀዋለሁ።
ያን ያህል እየታመመ እሱ ስለ ሰው ጤንነት ይጠይቃል እንጂ ስለራሱ አይናገርም። እስከመጨረሻ ለአገሩ ለኢትዮጵያ ያስብ ነበር፤፡ አጫጭር ድርሰት አያውቅም። ምክናያቱም ብዙ ያነባል። ስለሆነም ብዙ ያውቃል። ብዙ የሚያውቀው ነገር ስላለ ደግሞ ያንን ተናግሮ ማቆም ያቅተዋል። ያ የእውቀቱን ምልክት ነው የሚያሳየው። እኔ እንደታናሽ ወንድሜ ነበር የማየው እሱም እንደ ታላቅ ወንድሙ ነበር የሚመለከተኝ። ቤተሰቦቹን እግዚአብሔር ያጽናቸው ከማለትና እኔም አቅም እያነሰኝ ከቤት ሆኜ ስለሱ ብቻዬን ከማልቀስ በቀር ምን አደርጋለሁ?
ንባብ አፍቃሪነቱ ገና ከልጅነት ከተማሪነቱ ነው። የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ የሼክስፒር መጻሕፍትን እነ ሐምሌት ማክብዜ እና ኦቴሎ የመሳሰሉትን በቃሉ ይወጣቸው ነበር። ጽፈትም ይሆንለታል። እንዲያውም ካንዳዊው መምህር ይህን ሌላ ሰው
ጽፎልህ ይሆናል እንጂ፣ የዚህ ጽሑፍ ባለቤት እንደምን አንተ ልትሆን ትችላለህ ብሎ ያመጣውን ጽሑፍ ለመቀበል ያንገራግር እንደነበር በጨዋታ ማንሳቱ ተሰምቷል፡፡ ወደፊት ትልቅ ጸሐፊ ትሆናለህ ብሎኝም ያውቃል እያለም ይቀልድ ነበር። ከትህትናውና ይሉኝታው ብዛት ራሱን የሚያሽሟጥጥ ሰው በመሆኑ አንተ ግን ስለራስህ የማትጽፈው ስለምንድነው ተብሎ ሲጠየቅ እሽም እምቢም ሳይል በፈገግታ ይሸኛል። ስለ ግለ ታሪኩ እንኳ ቃለ መጠይቅ ሲጠየቅ ማውራት የማይፈቅድ ሌላውን ግን ሲተነትን ለሰዓታት ቢቀመጥ የማይታክተው ሰው ነው። ልጻፍ ብሎ የተነሳማ እንደሁ ፍጥነቱ አይደረሰበትም።
“እኔም በጣም የሚደንቀኝ ችሎታው እሱ ነው” ብሏል ሰሎሞን ክፍሌ። ቀድሞ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አሁንም የቪኦኤ እውቅ ጋዜጠኛ የሆነው ሰሎሞን ክፍሌ ጋሽ ሙሉጌታ እንደፎቶግራፍ ያየውን ያነበበውን የሰማውን ቀርጾ ማስቀረት የሚችል የተለየ ጭንቅላት አለው። ሀሳቡንም እንዲሁ አንዴ ፎቶ ያነሳዋል መሰለኝ ወረቀት ላይ ቁጭ ሲያደርገው ወዲያው ነው። ለምሳሌ አንድ ጊዜ በመኪና ረጅም መንገድ እየተጓዝን ነበርን። ያኔ ከወጣም በኋላ ጦቢያ መጽሔት ላይ ይሠራ በነበረበት ጊዜ ነው። እና ለካ እሱ ሁለት አርቲክል አሁኑኑ አድርስ ተብሎ ኖሯል። መኪና ውስጥ ሆኖ ከጎኔ ተቀምጦ ይሞነጫጭራል። እረ ጎሹ ለጦቢያ መጽሔት አድርስ ያለኝ ሁለት አርቲክል አለ እያለ አንድ ጊዜ መሞነጫጨር ጀመረ። በኋላ ገረመኝ ከዲሲ ተነስተን ቦልቲሞር እስክንድረስ አንደኛው አልቋል አለኝ። ፔንሲልቪኒያ ስንደርስ ሁለተኛውን ጨርሶታል። በል አሁን እዚህ እንውረድና ጽሁፎቹን እንላክላቸው ሲለኝ በጣም በጣም ደነቀኝ። ያንን ሲያደርግ ከከኪሱ የሚያወጣቸው የሚያመሳክራቸው ምንም ነገር የለም። ብዙ ሰዎችን ብዙ ቀኖችን ዓመተ ምህረቶችን ነው የሚጠቅሰው። እና እነዚያን አርቲክሎች ሌላ ጊዜ በትክክል አንብቤያቸዋለሁ። ጥልቅ ናቸው። ይህ ሁል ጊዜም ይገርመኛል።” ብሏል ሰለሞን።
ባህርይው ከሥራው ውጭ ሌላው የሚያስደንቀኝ ደግሞ ይሄ ትልቅ ሰው ነው፣ ይሄ ትንሽ ሰው ነው የሚለው ነገር የለውም። ከሁሉም ጋር ቁጭ ብሎ በማንኛውም ርዕስ ላይ ይወያያል። እኔ ብቻ አውቃለሁ የሚል አይደለም። ለማስረዳት የሚያደርገው ጥረት ይገርመኛል።
በመጨረሻዎቹ ጊዚያት ከበውት ከሚዉሉ አድናቂዎቹ ወጣቶች አንዱ የሆነው ተስፋዬ ተሰማ ይህንኑ የሰሎሞን አባባል አረጋግጧል። “ እኛ ወደሱ ከፍ እያልን ሳይሆን እሱ ወደኛ ዝቅ ብሎ እየመጣ ነው ፣ ምንክንያቱም ጋሽ ሙሉጌታ ውሎው ትንሽ ትልቅ ብሎ የሚለይ አይደለም ብሏል። ደግ ሰው ፣ጋባዥ ትሁትና ተጫዋች ነው።
ሰሎሞን ክፍሌ እንደሚለው ጋሽ ሙሉጌታ የተለያየ ሰው የሚያገኝ ብቻ ሳይሆን ለተለያ ሰው የሚሆን ብዕርም አለው። በተለያየ የብዕር ስም ነበር የሚጽፈው። ይህን ሁሉ ነገር የአንድ ሰው የተሸከመው አይመስለኝም የብዙ ሰው ጭንቅላት የተሸከመ ነው የሚመስለኝ፡፤ የዛሬ 30 ዓመት የተለያየኸውን ሰው ስትጠይቀው እስከ እነ አባቱ እስከነ ቅድመ አያቱ ይነግርሃል። እዚህ አገር ቆይቶ ቢሆን ኖሮ እንደኛ የሶሻል ሴኩሪቲውን ቁጥር የጫማ ቁጥሩን ሁሉ ሳይነግረን አይቀርም ብሎ ቀልዷል።
በሀዘኑ እጅግ ከተነኩት አንዱ የሆነው ሰሎሞን “ጋሽ ሙሉጌታ ለአገሩ አፈር አለመብቃቱ ያሳዝነኛል፡፡ ወደመጨረሻው ላይ ዓይኑን አሞት እረ ታውሬ አይኔ ከሚታወር ለአገሬ አብቁኝ ቢፈልጉ ይግደሉኝ ይል ነበር። እሱ ሁሌም አብሮኝ ኖሮ ይረብሸኛል።”
በመረበሹስ ላይ ታማኝ በየነም አለበት። አባቴና ልጄ በሚባባሉት ታማኛና ሙሉጌታ ሉሌ መካከል ከ1988 ጀምሮ የሰነበተ ፍቅር መኖሩን ታማኝ ተናገሯል። እንዲያውም ያኔ ጋሽ ሙሉጌታን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁበት ነው እንጂ በጽሑፍ ከረታኝ ቆይቷል። ጋሽ ሙሉጌታን በጦቢያው ፀጋዬ ገ/መድህን ነው ይበልጥ የማውቀው። ከዚያም ውጭ አንባቢነቱን ስለማውቅና አክብሮትና ፍቅሬም ገደብ ስላልነበረው እሱን የምተዋወቅበትን ቀን እናፍቅ ነበር። መጽሐፍ እጅግ እንደሚወድ እስማ ስለነበር አንድ ቀን በዚያውም ትንሽ ፈገግ አደርገው እንደሁ ብዬ ከለንደን ጠረጴዛ የሚያክል ግዙፍ መጽሐፍ ይዤለት ወደ ኢትዮጵያ ቤቱ ድረስ ልጠይቀው ሄድኩ። ጊዜው የአድዋ በዓልም አካባቢና ጋሽ ሙሉጌታ በግጭቱ ጉዳት ደርሶበት የነበረበት እለት ነበር። እና ገና ከመነሻው ሳውቀው ተጎድቶ ነው። ከዚያ በኋላ ይበልጥ ያየሁትና የተዋወቅሁት ደግሞ እዚህ ነው። እዚህም በደህና ነገር ሳይሆን የአባቴን ሞት ሊያረዳኝ ቤቴ ድረስ መጥቶ ነው ያወቅኹት። እና ከዚያ በብዙ እየተቀራረብን መጣን። “የሚቆጣኝ ይህን በል ያን አትበል” የሚለኝ ሰው ነበር። “ይሄን ደግሞ በየወቅቱ እየወጣህ እኔ ትንሽ ሰው ነኝ የምትለውን ነገር ተው!” ይለኛል።
ደግሞ ሌላ ጊዜ በማደርገው ነገር ሰዳቢዎቼ በዝተው በጣም ሳዝን ይመጣብኛል። በተለይ በአንድ ወቅት የተናገረኝ ነገር መቼም አልዘነጋውም “ ስማ ታማኝ አንድ የፈረንሳይ ፈላስፋ ምን ይል ነበረ መሰለህ፣ “ሐውልቴ የሚሠራው ጠላቶቼ ከሚወረውሩብኝ ድንጋይ ብዛት ነው” ካለ በኋላ… እና ግን ምን ያደርጋል ጋሽ ሙሉጌታ ቀርቶብናል…. ብሏል።
ታማኝ የሚያዝነው በሁለት ነገር ነው። አንድም ጋሽ ሙሉጌታ ስለራሱ መጽሐፍ ሳይጽፍ በመሄዱ እና ትልቁና ዋነኛው ደግሞ ለአገሩ አፈር ሊበቃ አለመቻሉ ነው። ምክንያቱም ጋሽ ሙሉጌታ ስለአገሩ የነበረውን ፍቅርና ተመልሶ የማየት ጉጉት ያውቃል። ጋሽ ሙሉጌታን ለመጨረሻ ጊዜ የተሰናበተው ኢሳት ቢሮ ውስጥ አቀርቅሮ ሲጽፍ ነበር። ሁሌም “ማንበብ ምን ያደርጋል? ቁምነገሩ መጻፍ ነው እያለ..” የቀልዱን ያበሽቀው እንደ ነበር ይታወቃል።
ጋሽ ሙሉጌታ ከአገር ከወጣ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ጦቢያን ከዚያም የልሳነ ሕዝብን መጽሔት ላይ ተሳትፎውን የቀጠለ ቢሆንም ሁሉቱም እንዲቆሙ በመደረጋቸው ለተወሰነ ጊዜ የጽሑፍ አምሮቱን አምቆ ቆይቷል። አልፎ አልፎ በየዌብሳይቶቹ ላይ ቢጽፍም አያረካውም።
ወደ ኋላው ላይ ከአገር ወዳድ ወዳጆቹና ታማኝንም ጨምሮ ከተወሰኑ ጋዜጠኞች ጋር የጀመረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ (ኢቲኤን) ከህልሙ የቻለውን ያህልም ቢሆን ፈጽሞ አልፎአል። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ (ኢቴ ኤን) ሥራ አስኪያጅ ሆኖ በመስራችነት ጭምር የሠራባት ያቺ ጊዜ ለብዙዎች ጋሽ ሙሉጌታ ጽሑፍ ሳይሆን፣ ከጽሑፍም በላይ የሚወደድ ሰብዕናው የተነበበት አጋጣሚ ነበረች።
አቶ ሙሉጌታ ከኢ.ቲ.ኤን ቀጥሎ ንቁ ተሳትፎ ያደርግበት በነበረው ኢሳት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ላይ ጭምር የሥራ ግንኙነት ያለው አቶ ነዓምን ዘለቀም ስለ አቶ ሙሉጌታ ተናግሯል።
አቶ ሙሉጌታ ከልጅነት እስከ አዋቂነት ድረስ በንባብ የማውቀው ቢሆንም በተለይም ላለፉት 18 ዓመታት አሜሪካ ከመጣ ጀምሮ እንደ አባት ወንድም መካሪና ጥሩ ወዳጄም ነበር። ኢትዮጵያን በልዩ ሁኔታ ከሚያፈቅሯትም ልዩ ሰዎች እንደ አንዱ አድርጌ የማየው ሰው ነው። ታላላቅ ሰዎች ቢያልፉም ሥራዎቻቸው አያልፍም እንደሚባለው የጋሽ ሙሉጌታ ሥራዎች የሚያልፉ አለመሆናቸው የሚያጽናና ነው። ወጣቶቹን የኢሳት ጋዜጠኞችን በአርአያነትና በሙያ በመግራት ያደረገው አስተዋጽኦም ቀላል የሚባል አይደለም። እንደ ኢሳት ባልደረባ በትንታኔዎቹ ኢንሳይክሎፒዲክ በሆነ እውቀቱ ሚሊዮኖቹን አስተምሯል። ብሏል።
ከቅርብ ወዳጆቹና የሥራ ባልደረቦቹም መካከል አንዷ የሆነችው አርቲስት ዓለም ፀሐይ ወዳጆም ጧት ጧት ሁሌም ወደ ሥራው ስትገባ አቀርቅሮ እንደምታገኘው ተናግራለች። ጋሽ ሙሉጌታ ሁሌም አጎንብሶ ወይ ሲያነብ ወይ ሲጽፍ ነው የማየው ብላለች። እንደሱ ያለመታከት ሲያነብ የኖረ ሰው አይቼ አላውቅም። ያም በመሆኑ ይመስለኛል የኢንፎርሜሽን ባህር የሆነልን። አንድ ጊዜ በአንድ ፕሮጀክት ስለ አፄ ዮሐንስ ሲያነብ ተመልክቼው ነበር። ሌላ ጊዜም እንደገና ሳየው አሁንም ሌላ ጊዜ ስለ አጼ ዮሐንስ ሲያነብ አየሁና፣ “እንዴ ይህን መጽሐፍ እስካሁን አልጨረስከውም እንዴ? ስለው አይይ ይህኛው ደግሞ ሌላ ነው- ሲለኝ ገረመኝ እንደ ብዙዎቻችን አንድ መጽሐፍ አንብቦ ሰለሷ ብቻ የሚያወራ አይደለም አይበቃውም።
ጋሽ ሙሉጌታ ምንም ነገር ቢጠቀስ ወይ እዚያ ነገር ውስጥ አለበት ወይም ስለሆነው ነገር ያነበበው ነገር አለ። ወይ ይኖርበታል ወይ አንብቦታል። ይህን ሰው እንዴት እናጣዋለን?
ጋሽ ሙሉጌታ ስሙ እንደተራራ የገዘፈ ቢሆንም በኑሮው የተመቸው አልነበረም። በስደት ሕይወቱ ከተለያዩ አገራት የሚመጡትን እንግዶችን ሲያስተናግድ ሲያበላ ሲያጠጣ መመልከቱ የሚያሳዝነኝ ህይወቱ ነበር። በዚያ ላይ በስደት ዓለም ለማይገባው ሰው ይገባዋል ብሎ ሲደክም የሚውለው ውሎ ሁሌም ያሳዝነኛል ብላለች።
ጋሽ ሙሉጌታ ከ1ሺ500 በላይ የሚደርሱትን አብዛኞቹን የመ/ቤቱ ሠራተኞች ስልክ ቁጥር በቃሉ ሲያውቅ ስመለከት አንድ ነገር የመያዝ ችሎታው ከኛ ጋር የማይመጣጠን ልዩ ፍጡር ያስመስለዋል ብላለች።
አቶ ከበደ አኒሳ ለአዲስ ኦብዘርቨር እንደተናገሩት “ሙሉጌታ የትውልድ ጋዜጠኛ ነው።” ከ-የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መመሪያ ኃላፊ የነበሩት መርዕድ በቀለም የአቶ ሙሉጌታሞት “አገሪቱ ትልቅ ሰው ያጣችበት” ብለዋል።
ከፀጋዬ ገ/መድኅን አርአያ
“የፖለቲካውን ፋሽን” ሳልፈራ ሁለት የተከበሩ ዜጐች መኖሪያ ቤት ሄድሁ። አንደኛው ኮሎኔል ዓለሙ ቂጤሳ ነበሩ። ሁለተኛው ደግሞ ቢተወደድ ዘውዴ ገብረ ሕይወት ሲሆኑ ከጠላት በፊት ጀምሮ በአስተማሪነት፣ በዲፕሎማሲና በአገር አመራር ሰፊ ልምድና እውቅት ያካበቱ አባት ነበሩ። ሁለቱንም በተለያዩ ጊዜያት ቀጠሮ ይዤ አነጋገርኳቸው። ያን ጊዜ በአርሲ፣ በሐረርጌ፣ ዲማ የሚባል ሰብአዊ ፍጡር አማራ እያባረረ ይገድላል፤ በሐረርጌ በአሰቦት ነፍጠኛ ሁሉ እየተረሸነ ነው የሚባልበት ጊዜ ነበር። ያንን ደግሞ የሚያራግቡ፣ ትልልቁንና በጀግንነቱ የሚታወቀውን ኦሮሞ ጄኔራልና ራስ ሳይቀር በዘላን ቋንቋ የሚዘልፉ ጋዜጦች ወጣ ወጣ ማለት የጀመሩበት ነበር። ይኸ አካሄድ ለቢትወደድም ለኮሎኔል ዓለሙም አልጣማቸውም ነበርና ሊመጣ የሚችለውን አደጋ በማሰብ በሰፊው ተወያየንበት። ሁለቱንም ጐምቱ ዜጐች ገጽ ለገጽ ማገናኘት አልቻልሁም። ዓላማችን ግን ኮሎኔሉ በኦሮሞ አባትነት፣ ቢተወደድ ደግሞ በአማራ አባትነት አደባባይ ወጥተው “ሕዝቡን ለማጫረስ የተጠነሰሰውን ሴራ በሚያጋልጥ መልክ እንዲያወግዙ ነበር። ሁለቱም የሚወክሉትን ኅብረተሰብ ባሕልና ሥርዓት ስለሚያውቁ ተቃቅፈው ፍቅራቸውን በመግለጥ፣ የሁለቱንም ታሪክና የደም ትስስር በማብራራት እያሳሰበ የመጣውን የፖለቲካ ደመና እንዲያከሽፉት ለመሞከር ነበር። በሦስተኛው ቀን ኰሎኔል ዓለሙ “ሁሉም ነገር ጥሩ ነበር። ትናንትና ከበቀለ ነዲ ጋር ስንነጋገርበት ከእኛ መካከል ወደ እብደት የወሰዳቸው አክራሪዎችን ይጠንቀቁ። እዚሁ አጠገባችን ያለውን..ሰው ይህን ቢያዋዩት ሊገድልዎ ይችላል። አላወቁትም መሰለኝ እንጂ አለኝ” አሉ። በዚህ የተነሣ ፕሮጀክቴ ወደቀ። እኔም አሜሪካ ከሚሉት አገር ገባሁ። ከአንድ የብስጭትና የጭንቅ መንፈስ፣ ከአንድ ማንም ያለመልሰልኝ ጥያቄ ጋር ቀረሁ። እንዲህ ያለውን ጭካኔና ጥላቻ ከቶ ከየት አመጡት? የተወሰኑ ባለስልጣኖች ልትጠላ ትችላለህ። አገር ሙሉ ሕዝብ- ግዑዝዋ አገር..እንዴት የጥላቻ ዒላማና የእልቂት ሰላባ ይሆናሉ? ለመሆኑ እነዚህ ዛሬ በወያኔ ገፋፊነት ከፍልፈል ዋሻ ወጥተው የሚጫጩት ትንንሽ ነፍሳት መጫረስና መፋጨት ለሕዝብ አንዳች መፍትሔ ይሰጣል ብለው እንዴት ሊያስቡ ቻሉ? ወይስ አጀንዳቸውንና የወደፊት ጉዞአቸውን ለምን በግልጽ አይነግሩንም?
የኢትዮጵያ ድምጽ፣ ኢትዮጵያ (አስመራ) ፣ አዲስ ዘመን፣ ኢትዮጵያን ሄራልድ፣
የዛሬዪቱ፣ መነን፣ የካቲት፣ ጦቢያ፣ ልሳነ ሕዝብና የመሳሰሉት የህትመት ውጤቶች አቶ ሙሉጌታ አሻራውን የተወባቸው ያነጻቸው የታነጸባቸው ናቸው። የምስራች ድምጽ፣ ዓለም አቀፍና ብሔራዊ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያዎች፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ (ኢቲኤን) በመጨረሻም የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ (ኢሳት) ጋሽ ሙሉጌታ የታየባቸው መስታውቶቹ ናቸው። በ1984 አጥፍቶ መጥፋት የሚል መጽሐፍም አሳትሟል።
እንግዲህ እሱ አቶ ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ ነው። ታላላቅ ስሞች እንኳ ቀድመውና ተሽቀዳድመው የሚያነሱት ትልቅ ስም ነው። ድንኮች ተንጠራርተው ያልደረሱበት፣ ጊዜ በሰጣቸው የቅል ዘመንተኞች ያልተደረመሰ የአለት ቋጥኝ ነበር። እንደ አባቶቹ ጦር ጎራዴ ጠላቶቹን በሰላ ብዕሩ ቃላት እየመዘዘ የሚያደባይ፣ ስዶችን በስድ ንባብ እየተቀኘ ልክ ማስገባት የሚችል ጀግና ነበር። ቃልና አንደበት ለቸገረው እየደረሰ የተበደለና የተገፋን አንጀት እንዳራሰ የኖረ የቀለም አንበሳ ነበር።
ብዙዎች እንደተስማሙበት አቶም ጋሼም የሆነው ሙሉጌታ ሉሌ ታሪክና ሁነትን በሰዓታትና ደቂቃዎች ቆጥሮ ማስረከብ የሚችል አዋቂ ነው። ያውቃል። በተፈለገው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለመናገር ተቀባብሎ የተቀመጠ መዝገብ ነው። ማንበብና መጻፍ ብቻ እንደሚችሉት ምሁራን ማንበብና መጻፍ ብቻ ይችላል የሚባል ሰው አይደለም። አገር አንብቦ አገር የሚጽፍ ታሪክ አብልቶ የሚያጠጣ የእውቀት ገበታና ማዕድ ነበር።
እንደ ጽሑፉ አለባበስና ነገረ ሥራውም ሽክ ያለና ወግ ያለው ነው። የተቆጠበ ጨዋ ዝግ ብሎ የሚናገር እዚህም እዚያም ጥልቅ የማይል የጋዜጠኝነትን መስመር አልፎ ያልሄደ አውቃለሁ አውቅላችኋለሁ የማይል፣ በተሰመረ የሙያ መስመር መጓዝ የሚችል ታላቅ ሰው ነበር። ከሚገባው በላይ ያነበበ ውጥንቅጡን ዓለም መልክ አስይዞ የተገነዘበ በሳል የፖለቲካ ሰው ነበር። ከሁሉም በላይ ደግሞ ቀርበው ላወቅቱ ገርና መልካም ሰው!
በቅርብ ቤተስቦቹ ላሉዬ በሚል የቁልምጫ ስም የሚታወቀው አቶ ሙሉጌታ፣ የአቶ ዮሐንስ ሙሉጌታ፣ አቶ ሉሌ ሙሉጌታ፣ የወ/ሮ ኤዶም ሙሉጌታ፣ እና የወ/ ት ሄርሜላ ሙሉጌታ አባት እና የ6 የልጅ ልጆች አያት ነው። እምንወዳት ህይወቱ እስካለፈችበት መስከረም 23 ቀን 2008 ድረስ በአሜሪካው የቨርጅኒያ ግዛት ከ 19 ዓመታት በላይ ኖሯል። በ75 ዓመቱ አንቀላፍቷል። ነፍስ ይማርልን!
Average Rating