www.maledatimes.com አርትዖትና ኢሣት (Editing and ESAT) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

አርትዖትና ኢሣት (Editing and ESAT)

By   /   November 7, 2015  /   Comments Off on አርትዖትና ኢሣት (Editing and ESAT)

    Print       Email
0 0
Read Time:10 Minute, 26 Second

ይሄይስ አእምሮ

የአርትዖት ሥራ በጣም ፈታኝና አሰልቺ መሆኑን የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ በተለይ መሰላቸትና ሥራውን የመጥላት ነገር እንዲሁም ድካምና የአለቆች ንትርክ ከታከለበት እንደ አርትዖት ያለ አስቸጋሪ ሥራ ያለ አይመስለኝም፡፡ “የምታየው”ን የተበላሸ ነገር ትክክል እንደሆነ አድርጎ አእምሮህ ስህተቱን በስህተት ይሞላውና በምታርመው ጽሑፍ ወይ ንግግር ላይ እንከን የለውም ብለህ ታ(ሳ)ልፈዋለህ፡፡ ታትሞ ወይ ተነግሮ ካለቀ በኋላ ግን ብዙ የአርትዖት ችግሮችን ልታይ ትችላለህ፡፡ ማለት የፈለግኸው ማለት ባልፈለግኸው ነገር ተለውጦብህ ሁሉ ልታገኝና ብዙ ጣጣ ውስጥ ልትገባም ትችላለለህ – በዚህ ሥራ ጦስ እንጀራቸውን ያጡ፣ ለእሥርና እንግልት እንዲሁም ከዚያ ለከፋ አደጋ የተዳረጉና በየጊዜው የሚዳረጉ ሰዎች በተለይም ጋዜጠኞች መኖራቸውን ከግምት ባለፈ መረዳት እንችላለን፡፡ ባጭሩ የእርትዖት ሰራ ማት ጨጓራና ሽንፍላ የማጠብ ያህል ነው – አሁን እዚህች ቦታ ላይ እንኳን “ሥራ ማለት” ለማለት ፈልጌ “ሰራ ማት” ማለቴንና የእርትዖት ችግር ማሣየቴን ልብ ይሏል፡፡ እኔማ ስቸኩል በተለይ በጣም ነው ግድፈቶችን የምሠራው – ሁሌ፡፡

አንድን ጽሑፍ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ማረምና ማስተካከል ይቻላል፡፡ ከቋንቋ አጠቃቀም አንጻር የሚደረግ አርትዖት አለ፡፡ ይህ ደግሞ ከልዩ ልዩ የቋንቋው ገጽታዎች አኳያ የሚደረግ አርትዖት ነው፡፡ ከሆሄያት ትክክለኛ አጠቃቀም ( የዛሬን ጠፍ ዘመን አያድርገውና “አመት” ሣይሆን “ዓመት”፣ “እለት” ሣይሆን “ዕለት” መባል አለበት እያሉ ጥንታውያኑ እንደሚያስተምሩን ዓይነት )፣ ከሰዋስው ፣ ከዐረፍተ ነገር ምጣኔ ፣ ከቃላት አጠቃቀም፣ ከሥርዓተ ነጥብ አጠቃቀም፣ ከአንቀጽ አወቃቀር ፣ ከፈሊጣዊ፣ ዘይቤያዊና ምሣሌያዊ  አነጋገሮች፣  ወዘተ. አንጻር አርትዖት ይደረጋል፡፡ አንድ ሰው ማለፊያ ሃሳብ ኖሮት የኣጻጻፍ ሥልትና የቋንቋ ዕጥረት ከገጠመው በባለሙያ  ዕገዛ አንቱ የተባለና ቀልብን የሚስብ ጥሩ ጽሑፍ ወይ ንግግር ሊያበረክት ይችላል፡፡ ለማገዝና ለመታገዝ ግን ሁለቱም ወገኖች ፈቃደኛና ዝግጁ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ “ከኔ በላይ ዐዋቂ ላሣር” በሚል “የኔን ጽሑፍ ማንም ሊያርመው የማይችል ምሉዕ በኩልሄ ነው፤ እሱ ማን ነውና ነው የኔን ጽሑፍ የሚተች/የሚያርም?” የሚል ሰው ካለ በኔ እምነት ሞቱን በገዛ እጁ ጋብዞ በቁሙ መሞት የጀመረ ያህል ሊቆጠርለት እንደሚገባ መጠቆም እፈልጋለሁ፤ ትምህርት የማያቋርጥ ሂደት እንጂ አንድ ሰው በህጋዊም ይሁን ኢ-ህጋዊ በሆነ መንገድ ጥሮ ግሮ በሚያገኛቸው ወይም በገንዘብ በሚገዛቸው የዲፕሎማና የዲግሪ ወረቀቶች የሚገደብ አይደለም፡፡ የዚህችን ዓለም ጓዳ ጎድጓዳ ሙሉ በሙሉ ዐውቆ ከምድራዊ ሕይወት የተሰናበት ሰው የለም ብዬ ደግሞ አምናለሁ፡፡ ዐይኑን የትዕቢትና የዕብሪት ሞራ ያልሸፈነው ማንኛውም የምድራችን ዜጋ ከናቱ ማኅጸን ሳለ ጀምሮ ተወልዶና አድጎም እስኪሞት ድረስ ካልተማረና ለመማርም ዝግጁ ካልሆነ አንዳች ዘረመላዊ ችግር እንደተጣባው መገመት አይከብድም፡፡ (ከ”ስለዚህ” ጋር ፍጹም የማይገናኝ አንድ አሁን ትውስ ያለኝን እውነት በቅንፍ ልግለጽ እባካችሁን፡- እኔ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያምን ብሆን በቅርብ ለንባብ የበቃውን “አዳፍኔ – ፍርሀትና መክሸፍ” የሚል ግሩም መጽሐፍ ለአንድ የቋንቋ ባለሙያ ሰጥቼ እንዲያይልኝ አደርግ እንደነበር በዚህች አጋጣሚ ካልተነፈስኩ ከዚህ የተሻለ ሌላ አጋጣሚ የማገኝ አይመስለኝምና ይሄውና ተነፈስኩ፡፡)

በሌላም ረገድ ከሙያ ዕውቀት አኳያ አርትዖት ይደረጋል፡፡ ቋንቋን መቻል በራሱ የሁሉም ዕውቀት ባለቤትነትን አያሣይም፡፡ ጥሩ የቋንቋ ችሎታ ኖሮት ከሙያው ውጪ ሁለገብ ዕውቀት የሌለው አንድ የሥነ ልሣን ምሁር – ለምሣሌ የምህንድስናን ጥበብ በሚመለከት የተደረሰን አንድ ጽሑፍ እንዲያርም ቢጠየቅ ከቋንቋ አንጻር እንጂ ከሙያ አንጻር ከሆነ ያስቸግረዋልና ለሌላ ተመሣሣይ ባለሙያ ተሰጥቶ ነው ጽሑፉ መቃኘት ያለበት፡፡ ከዚህ አኳያ ከታሪክ፣ ከሥነ ሕዝብ፣ ከሣይንስና ከመሣሰሉት የዕውቀት ዘርፎች አኳያ አንድን ጽሑፍ ወይ ንግግር በሚመለከታቸው የሙያው ባለቤቶች እንዲታረም ማድረግ ከአስተዋዮች ይጠበቃል – ለአብነት የአንድ አካዳሚያዊ ጆርናል መጣጥፎች በተለያዩ ባለሙያዎች እንዲታይ የሚደረገውም ለዚህ ነው፡፡ በምንቸገረኝነት ወይም በ”ማን ምን ያመጣል?” ትምክህት ተኮፍሰው እውነቶችን ወይም ሃቆችን ቢያዛቡ ለትዝብት መዳረግ ይከተላል፤ ሰውን ማስቀየምም አለ፡፡ ትንሽ ዕውቀት ይዞ ደግሞ የማያውቁትን ነገር ለማረም በድፍረት መነሣት ለትዝብትና አለፍ ሲልም ላልተጠበቀ ችግር ይዳጋል – መዋረድን ጨምሮ፡፡ በዚህ አቅጣጫ ብንጓዝ መስመር እንስታለንና ወደ ጅምራችን እንመለስ፡፡ ግን ደግሞ በዚህች ቅጽበት ባጭሩ  ወደጀመርኩት የኢሣት ጉዳይ ባንመለስና ጥቂት ብንቆይስ?

ከባህላዊ ዕሤቶችና ማኅበራዊ ወግ ልማዶች አንጻር፣ ከሃይማኖት አንጻር፣ በቀድሞው ኋላ ቀር የሚባል ዘመን ይስተዋል ከነበረው ጋብቻ ከልክል ስደቦችና ግሣፄዎች አንጻር፣ ከዘርና ከቋንቋ ልዩነት አንጻር፣ ከፆታ አንጻር፣ ከልዩ ልዩ በሽታዎችና የአካል ጉድለት አንጻር፣ ወተዘ. በንግግርም ሆነ በጽሑፍ አንዱን ያስደሰቱና በሣቅ ያፈነዱ መስሎ ሌላውን እንዳያስከፉ መጠንቀቅ ተገቢ በመሆኑ ከነዚህ ማኅበረሰብኣዊ ጉዳዮች አኳያም አንድ ንግግር ወይ ጽሑፍ በሚመለከተው ባለሙያ መፈተሽና መስተካከል ይገባዋል፡፡ አማካሪዎች አዘጋጅተው የሚሰጧቸውን ንግግር ወደ ጎን በመተው በስሜት እንደሚዘላብዱትና አንዱን ወይ ሌላውን የማኅበረሰብ ክፍል እንደሚያስቀይሙት የሀገራችን አምባገነን መሪዎች ለመሆን እስካልተፈለገ ድረስ ከዚህ ካነሣነው ዋና የአርትዖት ጭብጥ አንጻር መጠንቀቅ ብልህነት ነው፡፡ አያ እንደልቡ መለስ ዜናዊ “እንኳን ከናንተ ተፈጠርን” የሚለውን “ታሪካዊ ንግግር” ስናስታውስ አንድ አምባገነን በራሱ ላይ አርትዖት ለማድረግ ግድ እንደሌለውና በዕብሪት ተወጥሮ እስከለተ ሞቱ ድረስ ሕዝብን እንዳሣዘነ እንደሚኖር እንገነዘባለን፡፡ ይህ ዓይነቱን ዕብሪት በአርትዖት ልንመልሰው አንችልም፡፡ መንግሥቱም የመለስን ያህል አይሁን እንጂ ይህን መሰል የድንቁርና ችግር ነበረበት፡፡ አሁን ሰክኖ ይሆን? አየ ኢትዮጵያ! ምን ምን ዓይነቶቹ የአእምሮ ድውያን ናቸው እንዲመሩሽ ፈጣሪሽ የሚልክብሽ? መንግሥቱና መለስን የመሰሉ ርህራሄ ብሎ ነገር ያልፈጠረባቸው ጭራቆች እየነዱን አብዛኛውን ዜጋ የመጨረሻ ቦቅቧቃ ፈሪ አድርገውን ቀሩ – ድንዙዛን ሆንንና አይሞቀን አይበርደን፡፡ እግዜር ይይላቸው፡፡ (ይህን ነገሬን ግን ከአርትዖት ጋር ምን አያያዘው በል?)

የአርትዖትን ችግር ለመለየት ከተራው የገረፍ ገረፍ አነባበብ ባለፈ ጥልቅ ንባብን ማድረግ ይገባል፡፡ የሚከተሉትን የዚህ ችግር ውጤት የሆኑ (በአብዛኛው) ከእውነተኛ ገጠመኛ የተቀነጨቡ ምሣሌዎችን አንብቡና ፈገግ በሉ፡፡ ከዚያ ቀጥለን ወደመነሻችን እንመለሳለን፡፡

“ ‹ግማዊ› ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ …” (አንድ ወዳጄ የነገረኝ በአፄው ዘመን የተፈጸመ የአርትዖት ችግርና 10ሺህ አዲስ ዘመን ጋዜጣ የተቃጠለበት ኹነት ነው)፡፡

“ጓድ መንግሥቱና ባለቤታቸው ጓድ ውባንቺ በሥፍራው ‹ተኝተው› የተገነባውን ፋብሪካ ሲመርቁ”(የፎቶ ሥር ጽሑፍ)

“በቅናሽ ዋጋ ጆሮ እንበላለን፡፡” “እንበሳለን” ለማለት፡፡

“ለጠቅላላ ጉባኤ … ከብድ ኮሚቴ…” (በደርግ ዘመን በአንድ መሥሪያ ቤት ትልቅ የብድርና ቁጠባ ስብሰባ ላይ የታዬና ነገሩ የገባውን ተሰብሳቢ ሁሉ በሣቅ የፈጀ እውነተኛ ክስተት ነው፡፡ ከ”ብድር” ከሚለው “ር”ን ገድፋችሁ አንብቧት …)

“You are quiet right!” (quite ለማለት)

“She is my sinister.” (sister ለማለት)

“She don’t know anything at all.” (doesn’t ለማለት) ይበቃናል፡፡

 

መቼስ “ወይ መሬት ያለ ሰው!” ብላችሁ ካላሽሟጠጣችሁኝ ኢሣት ላይ የሚታዩ አርትዖታዊ ችግሮች እንዲህ በቀላሉ የሚታለፉ አልሆኑም፡፡ ዛሬ ይህን ጽሑፍ እንድጽፍ የወዲያው ምክንያት የሆነኝን ክስተት ብናይ ለምሳሌ “እንዴ! ምን ነካቸው?” የሚያስብል ነው፡፡ እርግጥ ነው “ድክመታችንን ለኛ፣ ጥንካሬያችንን ለሌሎች (ይንገሩልን)” የሚለውን የንግድ ቤቶችን የግድግዳ ላይ ማሳሰቢያ አልረሳሁም፡፡ ቢሆንም አንዳንዴ ከአእምሮህ በላይ የሆነ ስህተት ስታይ አያስችልህም፡፡ እናም እንዲታረም እናገራለሁ፡፡

ዛሬ የታዘብኩት ትልቅ ስህተት የተፈጠረው ጋዜጠኞች ፋሲል የኔዓለምና መሣይ ከበደ ማለቴ መሣይ መኮንን አምና ኤርትራ ሄደው ከተመለሱ በኋላ ተዘጋጅቶ በነበረው የጥያቄና መልስ ወቅት የተከሰተ ነው፡፡ አንድ ተሣታፊ “የአየር ኃይል ጀግናችንን የኮሎኔል በየነ ጴጥሮስን ጉዳይ ጠየቃችሁ ወይ?” ብሎ ይጠይቃል፡፡ ያ ሰው ሊሳሳት ቢችል አንድ ሰው ነው – ከሀገርና ከፖለቲካም የራቀ ሊሆን ይችላልና ምንም አይደለም፡፡ ግን የገረመኝ ጋዜጠኛውም ልክ እንደሰውዬው “ኮሎኔል በየነ ጴጥሮስ…” ብሎ መልስ ሲሰጥ እኔም ራሴን ተጠራጠርኩ፡፡ “ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል” ነውና ጊዜውም ረዘም ስለሚል ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ወደ ወንድሙ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ተለውጦ ይሆን እንዴ? ብዬ ለአፍታ ማሰቤ አልቀረም፡፡ ግን በዛብህን የማስታውስበት የራሴ ምክንያት ስላለ ስህተቱ ጎልቶ ታየኝና የደረሰብኝ ውዥንብር በተሎ ጠፋልኝ፡፡ እየተስተዋለ እንጂ …

ከዚህ ኹነት በተያያዘ የገረመኝ ሌላው ነገር ከዚያ ሁሉ ተሰብሳቢ እንዴት አንዱ እንኳን ይህችን ስህተት ሊያርም አልሞከረም የሚለው ነው፡፡ ቀላል እኮ ነው፡፡ በብጫቂ ወረቀት ጻፍ አድርጎ ወደመናገሪያው መድረክ መላክና ቆይቶም ቢሆን ዕርምቱ እንዲነገር ማድረግ ነው – ፕሮግራሙን ሳልጨርስ ወደጽሑፌ ስለገባሁ ተነግሮ ከሆነ ይቅርታ፤ ግን አይመስለኝም፡፡ እንዲያው በዚህ አጋጣሚ በሀገራችን “ይቅርታ” ማለት እንደሽንፈትና እንደነውርም የምትቆጠር በመሆኗ ይህችን ቃል በስፋት ስንጠቀም ለማየት በጣም የምጓጓ መሆኔን ብገልጽ ደስ ይለኛል – ፈረንጆች ግን ተበድለውም እንኳን ሣይቀር ይህችን ቃል እንደውዳሤ ማርያም ካፋቸው አይነጥሏትም፡፡ ብዙዎቻችን በሀበሻዊ ግድርድርነትና እጅን በቀላሉ ያለመስጠት ጀብድ ምክንያት የምንጠየፋቸውን “ይቅርታ”ና “አመሰግናለሁ” የመሳሰሉ ወርቃማ የዕርቅና የይቅርታ ቃላትን ሥልጡናኑ ፈረንጆች በተለያዩ አገላለጾች  “sorry, excuse me, pardon me, apologies, thanks, thank you,…” እያሉ ያሞናድሏቸዋል – ሲያስቀኑ፡፡

ያ ስህተት ተሸፋፍኖ መቅረቱና እንደቅቡል እውነት መቆጠሩ የሰነቀረብኝ ሃሳብ ብዙዎቻችን የምንጓዘው በደመ ነፍስ እንደሆነ ያህል እንዲሰማኝ ነው – በጣም አዝኛለሁ፡፡ ከልብ እንሁን እንጂ፡፡ አቅል ይኑረን፡፡ ልብ ካለማለት ወይም ከቸልተኝነት ካልሆነ በስተቀር ከዚያ ሁሉ ሕዝብ መሀል ይህን ቀላል የሚመስል ግን ትንሽ የማይባል ስህተት ማረም የሚችል ሰው ጠፍቶ አይመስለኝም፡፡ ለማንኛውም ለእናት ሀገሩ ኢትዮጵያ ከአንድ ጊዜ በላይ በጠላት እጅ ወድቆ መከራውን ያየውና ትዳሩን፣ ልጆቹንና ቤት ንብረቱን በትኖ ለዚህች ለማያልፍላት የወንበዴዎች ዋሻ ለሆነች ሀገር ለኢትዮጵያ ራሱን መስዋዕት ያደረገው ኮሎኔል በየነ ጴጥሮስ ሣይሆን ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ነው – ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከአ.አ.ዩ መምህርነታቸው በተጨማሪ ደከመኝ ሰለቸኝ ሣይሉ ላለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት የአንድ ወይም ከዚያ በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊቀ መንበር እንጂ የጦር ጀት አብራሪ ሆነው አያውቁም፡፡ ይህን መጣጥፍ ኢሣቶች ካነበባችሁ ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ ብትጠይቁ ትከበራላችሁ እንጂ አትዋረዱም፡፡(እንደወያኔ ይቺን ቃል ለምን ወደድኳት ግን?)

በተረፈ የግርጌ ዜና (News Bar) ላይ የሚታዩ የሆሄያትና የሌላም ነገር የአርትዖት ችግሮችን ለመቅረፍ ብትሞክሩ ለናንተም ለኛም ክብር ነው – የግርጌ ዜና ደግሞ ጠቋሚ እንጂ ዘክዛኪ አይደለም፡፡ ዋና ዋና የዕለቱ ዜናዎች ተመርጠው በጣም ባጭሩ የሚቀርቡበት እንጂ ጋዜጣው እንዳለ ተገልብጦ ለንባብ የሚቀርብበት አይደለም – ባናርስ እኮ አጣምደናል፡፡ እርግጥ ነው ችግራችሁ ይገባናል፡፡ ግልጽም ነው፡፡ በቂ የሰው ኃይል ከተገቢው የገንዘብ አቅም ጋር የላችሁም – አዘውትራችሁ የምትገልጹትና ወደመዘጋት እንዳንሄድ የምታስጠነቅቁትም ለዚህ ይመስለኛል፡፡ ውጪም ሆነ ሀገር ውስጥ ያለች ምድረ ሀበሻ ደግሞ መኪና እየገዛችና ሕንፃ እየገነባች አንዲት ቀን አንሶላ ለተጋፈፈቻት ሸርሙጣ (ይቅርታ ለቃሉ) ትሰጣለች እንጂ ለዚህ ዓይነቱ ቁም ነገር ዱዲ አይወጣትም – ይሄኛው ወጪ ያንገበግባታል፡፡ ደህና ቀን ቢመጣ ግን የፊተኛውን ወንበር ለመሻማትና የድል አጥቢያ አርበኛ ለመሆን የሚቀድማት የለም – ከዚህ በላይ ምን የሚያሣፍር ነገር አለ? ያን ጥቅስ ምን በላው? “ነብር ዥንጉርጉርነቱን – ኢትዮጵያዊ ኢትየጵያዊነቱን ሊለውጥ ይቻለዋልን?” የሚለው ጥቅስ የት ገባ? በውነቱ ብዙዎቻችን የምንገርም ፍጡራን ነን፤ ኢትዮጵያዊነት እንደዚህ ዘመን አስጠሊታ ሆኖ የሚያውቅ አይመስለኝም – ክፉኛ ተለያይተናል፡፡ ማሰብ ያቆምንም ብዙ ነን፡፡ አንዱ ስለሀገር ሲጨነቅና በረሃ ለበረሃ ሲንከራተት ሌላው በሕዝብ ላብና ደም በአንድ ሌሊት ከብሮ ገንዘቡን የት ልጣለው ይላል፡፡ ከራሱ የተንደላቀቀ ኑሮም አልፎ ለመሸታና ለወሲብ በሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ እሳት ውስጥ ጨምሮ ሲያጋየው ይታያል – ልክ እናደነእንትናዬና መሰሎቹ (በዚህ የጃጀ ዕድሜው ያቺን አር ቲስት ያስቀምጣል? እሷስ አታፍርም? ለገንዘብ ብላ ትቀላለች? አየ ሴት! ወንድም ጭምር!)፡፡ ፈጣሪ ሆይ የት አለህ? ፍርድህስ ለምን ዘገየ? የአንጎላችንንስ የማሰብ ችሎታና የግንዛቤ መጠን ለምን እስከዚህን ድረስ አለያየኸው? ይህን ሁሉ ጉድ የምታሳየን በየትኛው ኃጢኣታችን ይሆን?

እውነት ለመናገር ይህን ጣቢያ -ኢሣትን – ግፋ ቢል አሥር ሀብታም ኢትዮጵያውያን ቢተባበሩ ካላንዳች ልመና ሥራውን በሚገባ ባስኬዱት ነበር – አስፈላጊውን ሰብኣዊና ቁሣዊ አቅርቦት አሟልተው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ የዜግነት በረከት ግን አልታደልንም፡፡ የአእምሮ መካንነት ነው ከያቅጣጫው ጠፍንጎ የያዘን፡፡ ስስት፣ ግዴለሽነት፣ ራስ ወዳድነትና የምንአገባኝ ስሜት ብዙዎቻችንን እግር ከወርች አሥረውን የሀገራችን ጉዳይ ለጥቂት ዜጎች ብቻ የተተወ ግዴታ ይመስል እኛ ማለትም አብዛኛው ዜጋ ህልም ላይ እንገኛለን፡፡

ለማንኛውም ከልብ ካለቀሱ ዕንባ አይገድም ይባላልና ኢሣቶች ትንሽ ትኩረት ከሰጣችሁት ይህን አምስት ዓመታትን ሊደፍን ምንም ያህል ጊዜ ያልቀረውን የጠነነ የአቀራረብና የአርትዖት ችግር ማቃለል የማትችሉ አይመስለኝም፡፡ ደግሞም ዘመኑ የቴክኖሎጂ ስለሆነ ማንም የትም ሆኖ ሊያግዛችሁ ይችላልና ሙያዊ ዕርዳታን መጠየቅ የምትችሉ ይመስለኛል – ለያዛችሁት የተቀደሰ ዓላማ ሙያውን ቀርቶ ሕይወቱን የሚሰጥ ቅን ዜጋ ሊኖር እንደሚችል አትጠራጠሩ፡፡ ገንዘብ አላፊ ጠፊ ነው – ለሀገር መሥራት ግን ኅያው ታሪክ ጥሎ ማለፍ ነው፡፡ እንደተከታተልኩት እኔ ብቻ ሣልሆን ብዙ አስተያየት ሰጪዎችም በዚህ የአርትዖት ችግርና የፕሮግራም አለልክ መደጋገም  ዙሪያ ብዙ ጊዜ ይተቻሉ – በእስካሁኑ ሁኔታ ግን ሰሚ ያገኙ አይመስልም፡፡ (እኔ የማግዛችሁ ነገር ቢኖር – አለርጂኬ እንዳይነሣብኝ ገንዘብ አትበሉኝ እንጂ – በምችለው ሁሉ በተጠንቀቅ እቆማለሁ፡፡)

ኢሣት የሕዝብ ዐይንና ጆሮ መሆኑን ማንም አይክድም፡፡ ኢሣት ባይኖር የሕዝቡ ተስፋ እንደጨለመ በቀረ ነበር፡፡ “ትልቅ ጦር ባይወጉበት ያስፈራሩበት” እንዲሉ ነውና ኢሣት ባይኖር ከአሁኑ የከፋ ጽልመታዊ አገዛዝ በሀገራችን በሠፈነ ነበር፡፡ ግን ደግሞ በወዲያኛው ጫፍ የምንገኝ ዜጎችም መደመጥን እንፈልጋለንና እስከዚህ ጆሮ ዳባ ልትሉን አይጠበቅባችሁም፡፡ የገንዘብ አቅም ማነስ ጥራትን ሊገዳደር አይገባም፡፡ ባለው ውስን አቅም ጥርት ያለ ዝግጅት ማሰናዳት ይቻላል፡፡ አስፈላጊም ከሆነ ሰዓትን በመቀነስ ያልተደጋገመና ቅልብጭ ያለ ዝግጅት ማቅረብ ይቻላል – የግል አስተያየቴ ነው፡፡ በበኩሌ በግድ 24 ሰዓት መሆን አለበት ብዬ አላምንም፡፡ እንኳንስ 24 ሰዓት መለስ ዜናዊ በአበበ ገላው መብረቃዊ ጩኸት ደንግጦ ፀጥ ረጭ ያለባት የጥቂት ሴከንዶች ጊዜም በፀጥታ ከተሸፈነች ታስጨንቃለች፤ እንደፀጥታ የሚያስጨንቅ ጩኸት የለምና፡፡ ደግሞስ 24 ሰዓት ቲቪ ከተባለ ዘንዳ አልፎ አልፎ የሚገባው የሬዲዮ ሰዓት መደቡ ምን ሊሆን ነው? በየትኛው ሰዓትስ ሊመዘገብ ነው? ቢታሰብበት ጥሩ ነው፡፡ ማሰብም ይቻላል፡፡

እንዲህ የምለው ኢሣት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብቸኛ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደመሆኑ ሚሊዮኖች በከፍተኛ ጉጉት የሚጠብቁት መሆኑን ስለምረዳ ነው፡፡ ሌላ የመረጃ ምንጭ በሌለበት ሁኔታ ኢሣትን እንደዐይን ብሌን የሚያየው ዜጋ እጅግ ብዙ ነው፤ በውነቱ ብዙዎቻችን ለሀገርኛ ዜናና መረጃ ከኢሣት ሌላ ምንም ዓይነት የረባ አማራጭ ስለሌለ አንከታተልም – የሱስ ያህል ሆኖብናል ማለትም ይቻላል፤ የዛሬ ሦስት ዓመቱን ዝግጅት እየተከታተልን መሆናችንን እያወቅን እንኳን አዲስ የሆነ ያህል እንዲቀበለው አእምሯችንን የምናስገድድ ብዙዎች ነን – ምርጫ ስለሌለን፡፡ ድረ ገፆቻችን የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ቢያደርጉም ተደራሽነታቸው ግን እንደሬዲዮና ቲቪ አይሆንም፡፡ ቲቪው የትም ሸጥና ጎጥ ውስጥ ይታያል፤ ይሰማል፡፡ ከፍቶ ለማድመጥ ወይም ለመመልከት ደግሞ አቅሙ ያለው ዲሽ አስገጥሞ አንዲት “በተን” መጫን እንጂ በ‹ፕሮክሲ ሳይት› እየገቡ በወያኔው ጁንታ የታፈነን ዌብሣይት (ድረገፅ) ለማግኘት ሌት ከቀን እንቅልፍ እያጡ መኳተንን አይጠይቅም፡፡ እኔን ጨምሮ ስንቱ ዜጋ የቤተሰቡን ፍላጎት ተጭኖ ኢሣት ላይ ተደቅኖ እንደሚውልና እንደሚያመሽ እገምታለሁ፡፡ ከዚህ ሕዝብ አብዛኛው በቀን ሁለቴ እንኳን በአግባቡ ራሱን መመገብ የማይችል መሆኑንም እረዳለሁ (“ዝናብ ጣለ ወይ?”  ቢሉት “እንደደጅህ እየው” አለ አሉ አንዱ የችግሮችን መመሳሰል ሲገልጽ)፡፡ ይሁንና ይሄው ከርታታ የማኅበረሰብ ክፍል ተመችቶት ኢሣትን መርዳት ባይችልም – መርዳት የሚችል ደግሞ የመርጃውን መንገድ ባያውቅም – የኢሣት ተቀዳሚ ዓላማ ሕዝብን ነፃ መረጃ በነፃ በመስጠት ማገልገል ነውና ተቋሙ የዚህን ምሥኪን ሕዝብ ፍላጎት የመጠበቅ አስተያየቱንም እንዳስፈላጊነቱ ተቀብሎ የማስተናገድና ተግባራዊ የማድረግ የሞራል ግዴታ አለበት፡፡ (በነገራችን ላይ በከተማም ሆነ በገጠር በባለስድስትና ስምንት ቆርቆሮ ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ዲሽ ታያላችሁ፡፡ ዜጎች ከምግባቸው ይልቅ ለመረጃ ቅድሚያ እንደሚሰጡ የተረዳሁት በነዚህ ከሰዎቹ ባልተናነሰ ምሥኪን በሆኑ ትናንሽ ዛኒጋባዎች አናት ላይ ከጣሪያዎቹ ስፋት ያልተናነሰ ስፋት ያለው ዲሽ ተገጥሞ ስመለከት ነው – ይህንንም የሚያደርጉት ኢሣትን ለመከታትል እንጂ “አልጀዚራ ቢቢሲ” ወይም “ዱባይ ዋን”ና “ፎክስ ቲቪ” ናፍቀዋቸው አይደለም፡፡)

እኔ በጣም ፈሪ ነኝ፡፡ አንዳንድ ደመ ሞቃት ነውጠኛ ተቺዎች “ወያኔ ነው” እንዳይሉኝ በመሥጋትይህን ደብዳቤ የጻፍኩት ነፍስና ሥጋየ እየተሟገቱ ነው – በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ውስጥ መፈራረጅ ማለት እፊታችን የቀረበን ምግብና መጠጥ የመብላትንና የመጠጣትን ያህል ቀላል መሆኑን አውቃለሁ – ግን በፍጹም አይጠቅምም፡፡ በመሠረቱ እውነትን በመነጋገር መግባባትና መተማመን ላይ መድረስ የሚያመጣው ዕድገትንና ልማትን እንጂ ጥፋትን አይደለም፡፡ መጥፎው መደባበቅና በከንቱ መወዳደስ ነው፡፡ ሃሳብን በነፃነትና ያላንዳች ገደብ ግን በጨዋነት ማንሸራሸርንም መልመድ ጠቃሚ ነው፤ ሁሉን ነገር ከአንድ አቅጣጫ ብቻ እየተመለከትን ፍረጃ ውስጥ ከገባን አናድግም ብቻ ሣይሆን አሮጌውን ወይን በአዲሱ አቅማዳ እየከተትን ጉዟችን የኋሊት እንደሆነና በምንም ማርሽ የማይወጡት አረንቋ ውስጥ እንደዳከርን እንቀራለን፡፡ ግልጽነትንና በፍቅር ተግባብቶ ችግርን ማስወገድን የባሕርይ ገንዘባችን ካላደረግን “እንዲህ ካለማ እንዲህ መሆን አለበት!” በሚለው ነባር ሸውራራ አካሄድ የትም አንደርስም፡፡ በዚህ አጭር መጣጥፍ ውስጥ የምለው ነገር ስህተት ቢኖርበት ለመታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ ውይ! ፍርሀት እንዴት መጥፎ ነው ለካንስ ወንድሞቼ! ስንቱን አስቀባጠረኝ ጃል፡፡ ለማንኛውም ቸር እንሰንብት፡፡ የነገ ሰው ይበለን – “ነገም ሌላ ቀን ነው” ይባላልምና፡፡

yiheyiseaemro@gmail.com

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 9 years ago on November 7, 2015
  • By:
  • Last Modified: November 7, 2015 @ 10:40 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar