ይድረስ ለውዳጅቷ ልዥ ጠጋያ ነሽ፡- ልዥዋ እንደምን፣ እንዴት ሰንብተሻል? ሙሊያው ውብ ነው!?… እንዴት ባጀሽ አከላቴ? መቼም የኔውን ተይው፣ የምታውቂው ነው፡፡ ….ተʼህሉ ይልቅ በቀን ስንትʼዜ፣ ወደ አፌ እምልሽ አንችኑ ነው!? “..እንዲህ ብላ፣ እንዲህ ሁና” እያልሁ በየደብሩ፣ በየዋይታው፣ በየገበያ ስፍራው ሁል አነሳሳሻለሁ፡፡ …ብቻ ምን ምልሽ ነኝ፣ ከጉንጬ ለይቸሽም አላውቅ… እረ ወዲያልሽ!! አልፎ ሃጂ አግዳሚውም ቢሆን ያሳደገሽ መንደርተኛው ሁል .. ስምሽን ጠርቶ .. ሳይመርቅሽ፣ ሳይጠይቅሽ፣ሳይኩራራብሽ አያልፈኝም፡፡ እኔ ደሞ ይሄንዜ ይጀንነኛል፡፡ አንዳንድዜ ደሞ ማንም ባያነሳሽ! እኔ እራሴም ብሆን! “ምነ?” ብትይኝ.. ታሰቀልይ፣ ትባቢ… ከንፈርሽን፣ ጉንጭሽን ተነክሽ፣ ልብሽ ድንግጥ፣ ድንግጥ ይል ይሆን? እያልሁ መቱን እየሳሳሁ!! እህ! መቼስ ያላንቺ ምን አለም አለኝ ጠጋዬ ነሽ?! ትምህርቱ እንዴት ሚያደርግሽ ነው? በዕውቀቱ እየላቅሽ ነው እመዋ!? የእኔይቱ ትኩሽት አየለሽ፣ ማን ያህልሻል፡፡ መችስ ሰው ተወገን ተዘመድ ተረርቆ፣ አላማውን እግብ ሲያደርስ አየል ልቅናው..እንዲያ ነው እመ፡፡ እኔም ሰማያን አጉኜ ስመለከት፣ አየሪት አሞራ አክላ ስትበር ሳይ… አንቺን ታስተያየኝ ይመስል .. ፍክ ትይኛለሽ፡፡ “እንዴት ሰነበታችሁ?” ብለሽ ለጠየቅሽኝ መችስ ምስጋና ይግባው – ትንሹም፣ ትልቁም ሙሉያው ደህና ነው፡፡ ብቻ ቀየውን ሁል ለልቀት ያበቁ፣ አንቺንም ሀሁ፣ አቡጌዳ፣ መልክተ ..ንባብ ያስተማሩሽ እንዴት ያሉ ሰው መምሬ አርፈው. . . ይኸው ዋይታ ሰነበትነ፡፡ የሰውነት ልኩ ተብሎ፣ ተብሎ መቺስ .. ተሞት አይቀር አየል እመ!? አይ ወዲያልኝ!! እንዳክመው ብዬ ነው ዓለሜ ነሽ፡፡ ወዲህ ግድም የለለሽ ሁኖ.. ቤቱ ህው ብሎ ሊውጠኝ ይዳዳው ነበር፡፡ አሁን ሞሳ ልቤ ተግ ብሏል፡፡ አንቺም ሚያህል ባይገኝም… የፊት የፊቱን ተመስገን ነው፡፡ ምነ? ብትይኝ ተቆላ ያሉ ዘመዶችሽ ከቤታቸው ያኖሯት የነበረችት … ድበርየለሽ ፍክ ትልሽ ሰውነቴ? ከብት ምትደንብላቸው እንኳን? እንደውም ከአባትሽ ዘመዶች ቤት በእንግድነት ዘልቀን ስንሰነብት፣ እግርሽን እንዴት ሙሽልቅ አርጋ ነበር ያጠበችሽ . . . ታወሰችሽ? እሷ ከታች ላይ ስትል ጸነሰይ…. ሰውዬውም ዘመድ አልሆናት፡፡ ደርሶባት ሲያበቃ “ቅሪት ሆንኩ፣ ደሜ ቀረ” ስትለው “ኸት ማውቅልሽ ነኝ” ብሎ ሲልስ ግምኛ ከፍቷት ሰንብቶ ነበር፡፡ የአባትሽ ዘመዶች ደርሰውና ደርሰው የማይበጃትን ሹክሹክ ሲሉ ሰምቼ አንጀቴ እጥፍ አለ፡፡ እነሱም ኩነኔ ተሚገቡ፣ እኔም ብቻዬን ተምሆን በጉልበትም ሆነ በቤት ጥበቃው ተረዳኛላይ ብዬ.. መውለጃዋ ተመቃረቡ ፊት ከቤት አምጥቻት፣ ይኸው ምጧም ሳይጠናባት የመስቀል ማግስት እንዴት ያል ወጠምሻ፣ አበባ ልዥ በሰላም ተገላገለይ፡፡ ይኸውልሽ በአሁኑ ሰዓትም መጫቲቱን እያረስሁ እገኛለሁ እመ፡፡ እናስያ . . . ከአንችውስ እንዴት አርጎሽ ሰነበተ ሰውነቴ? “ይህን ሰሞን አየሩ ግምኛ ከረሰሰኝ፣ የበረዶው ጭቃ ክምር ሊመጣ እየዳዳው ነው” ብለሽ አውግተሸኝ ነበር? እህ መጣ ወይ? ነው ወይስ እንደኛው አገር ሰማይ በረዶውንም፣ ዝናቡንም ነፈገችሁ? እህ ከየት ይመጣል፡፡ ሰማዩ እንደሁ አንድ! “አማሪካኖች አንድኛውን በቴክኖሌጂ የመጠቁ፣ በብልጥግና የረቀቁ ናቸው” ማለትሽ ፍክ ይለኛል፡፡ “እንኳን የየከርሞውን የፊቱን የአስር፣ የመቶ ዓመቱ ሁኔታቸውን አበክረው ያውቁታል” ማለትሽ ትውስ ይለኛል፡፡ መቼስ ለዝናቡም፣ ለበረዶውም ቢሆን ብልሃት አያጡም ብዬ?! ሰውነቴ የእኛውንስ ተይው. . .ዘንድሮ ሌላ ነው፡፡ አንድና አንዱ ታለየ፣ አያያዙስ ግመኛ ነው፡፡ ስንትና ስንትዜ ፊት መጥቶብን የኖረውን ችጋር ያስታውሰኛል፡፡ ሰማይ ዝናብ ነፈገ… ሰደድ እንዳይሆን ሰጋነ ሰውነቴ፡፡ “እንደፈቀደው” ተብሎ ሚታለፍ ዘመን አልሆነም እመ፡፡ በየደብሩ እግዞታው ቀልጧል፡፡ አየለም ሌላ ተሜ እንኳን በየጉበኑ እየኸደ “በይንተ እግዚአብሄር” ብሎ ሲለምን እንደወትሮው እንጀራውን እጥፍ አርጎ ቀርቶ፣ እርም ታህል ሚሰጠው ጠፋ፡፡ የሰንበት ዱጨት ሚለምኑት እሙሃይ ይታይሽ፣ ከቤት ቤት ተጓለው፣ ተጎታው ዱጨት አፍሶ ሚሰጣቸው ቢጠፋ “ተቁርባን ኋላ፣ ለቆራቢው ሁል ምኑን ጋግሬ ነው መክለፍት እማቃምስ” በሚል ግር ብሏቸው አወጉኝ፡፡ወረንታ፣ ቁና፣ ሰፌድ ቀርቶ እፍኝ ታህል ሰሰተ ስልሽ፡፡ ተይውና ሌላውን በእንግድነት ሰው ቤት ስትዘልቂ በቁም መልክትሽን አድርሰሽ ልትወጪ – ታልተበላ፣ ቅራሪ ካልተጠታ ማይሰድሽ ገበሬ፣ የስንቱ ጄታ ዛሬ “ይደቃሃል” ብሎ ጥሬ እንኳን አያቃምስ ጊዜ ላይ ነነ፡፡ መችም ልዤዋ ያደግሽበትን ምኑን ማጫውትሽ ነኝ፡፡ እንደወትሮው ቡና ተርቲ መጠራራት፣ እኔ ቤት የታረደ እንደሁ፣ እራት እንቃመስ ማለት ወጉ ሁል ኮስምኗልኝ፡፡ ገበያ ወጥቼ ስመለስ አተር ክኩ፣ ቅባኑጉ፣ አሻቦ፣ ሽኳር በአቅሙ የትየለሌ ሁኖ፤ የሸመቱ ነገር እማይሞከር ሁኖ ሳይ፣ “ከተሜው ምን ይውጠው ነው፤ አይ እድሉ” እላለሁ፡፡ “የልማት አርበኛ ነኝ” እያለ የሚወሸክተው ማህደር አከናዋኙ – እሱባለው ተላይ ላይ ቱሪናፋውን ሲል ይውላል፡፡ አችችች.. እንደ ሞኝባገኝ አይበጡት ነገር ሁኖብነ፣ ችለነው ተቀምጠናል፡፡ የቀየውን አኳኋን ላጫውትሽ ብዬ እንጂ እኔማ ለአንድ ነፍሴ ምን ቸገረኝ ብለሽ ሰውነቴ፡፡ እውሊ ስጋት እንዳይገባሽ፡፡ ደሞም አንቺ ደህና ሁኝልኝ እንጂ እንደቢሻው … ከቆላው ያሉ ዘመዶችሽም ይቸግረኝ መስሏቸው. . . ምኒቱን ምኒቱን እየቋጠሩ ይጠይቁኛል፡፡ “ተው” ብላቸው አልሆነም፡፡ በይ መጭውን ቅዳሜ የወሩ ጆርጂስ እለት፣ ከገበያ መልስ . . . ከዘመዶችሽ ምዘልቅ ነኝ፡፡ እንደቀጠሮዋችን ስልኪቱን ምችልኝና ድምጥሽን እንደስማው ይሁን፡፡ እናትሽ አስማር እምሩ
“አችችች.. እንደ ሞኝባገኝ አይበጡት ነገር ሁኖብነ፣ ችለነው ተቀምጠናል፡፡”
Read Time:3 Minute, 0 Second
- Published: 9 years ago on November 21, 2015
- By: maleda times
- Last Modified: November 21, 2015 @ 8:19 pm
- Filed Under: Ethiopia, ባላገሯ በአሜሪካ
Average Rating