www.maledatimes.com በጳጳሣት ሹመት ዙሪያ አንዳንድ ነጥቦች ይሄይስ አእምሮ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

       በጳጳሣት ሹመት ዙሪያ አንዳንድ ነጥቦች ይሄይስ አእምሮ

By   /   June 23, 2016  /   Comments Off on        በጳጳሣት ሹመት ዙሪያ አንዳንድ ነጥቦች ይሄይስ አእምሮ

    Print       Email
0 0
Read Time:3 Minute, 3 Second

 

ሰሞኑን ዘሃበሻ ድረገፅ በሰበር ዜናነት እንደዘገበችው በስደት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ስድስት ኤጲስ ቆጶሣትን በሙሉ የጵጵስና ማዕረግ ሾሞ በስድስት የዓለም ግዛቶች በሃይማኖታዊ የኃላፊነት ቦታ መድቧል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይቺ ቅመም የሆነች ዘሃበሻ የምትባል ድረገፅ ዜናውን ተከታትላ በወቅቱ ስላደረሰችን ከፍተኛ ምሥጋና ይገባታል፡፡ ሌሎቹ ድረገፆችም እንዲሁ፡፡ ሁሉም የዘጠኝ ወር ልጆቻችን ናቸውና ምሥጋናየ ለሁሉም ነው፡፡ “ከጣት ጣት ይበልጣል”ን አለቦታው ልተርት አልፈልግም፡፡ ቢሆንም….

ይህ ሹመት በወያኔ ሤራ ምክንያት በካልቾ ተጠልዛ መሬት ላይ በመዘረር ነፍሷ አልወጣ ብሎ እያንቋረረች ለምትገኘው የሀገራችን ታሪካዊት ሃይማኖት ትንሣኤ የሚያበረክተው አወንታዊ ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህ ማንሰራራት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ያደረጉና በማድረግም ላይ የሚገኙ አባቶች፣ ወንድሞች፣ እናቶችና እህቶች ታላቅ ክርስቶሳዊ ምሥጋና ይገባቸዋል፡፡ ይህችን የክርስቶስ መሠረት የሆነች ሃይማኖታችን በሁለት እግሯ እንድትቆምና የቀድሞውን ሕዝብን በአንድነትና በፍቅር የማሰባሰብ ሚናዋን እንድትጫወት እግዚአብሔር ያግዛት ዘንድ በበኩሌ እየጸለይኩ በሰሞኑ የሹመት አሰጣጥ ሂደት ላይ ከዜናው የታዘብኳቸውን አንዳንድ ነጥቦች ማንሳት ወደድኩ – እንዲያው አልሁ ለማለት ያህል እንጂ እስከዚህ ከባድ ሆነው አይደለም፡፡

ከአዲሱ ዜና ከዛሬው በመነሳት ስለስያሜያቸው ትንሽ ልበል፡፡ በአዲሱ ስያሜ አቡነ ቴዎፍሎስ የተባሉ አንድ አባት አሉ፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም በደርግ ፋሽሽት (ደርግን ከወያኔ ጋር ሳነጻጽረው ይህንን ቃል መጠቀም ከብዶብኝ መቸገሬን ተረዱልኝ) የተገደሉትን ሁለተኛውን የኢ.ኦ.ተ.ቤ/ክርስቲያን ፓትርያርክን ያስታውሰናል፡፡ ቀደም ሲል ለሌሎች አባቶች የተሰጡ ሌሎች ተመሳሳይ ስያሜዎችም አሉ፡፡

እኔ እምለው ታዲያ አዲሱን አባት በሌጣው “አቡነ ቴዎፍሎስ” ብለን ከምንጠራ “አቡነ ቴዎፍሎስ ዳግማዊ(2ኛ)” ብለን ብንጠራ አይሻልም ነበር ወይ? ነው፡፡ አንድ ነገር ከታመነበት ምን ጊዜም ማስተካከል ይቻላልና የሚመለከታቸው ወገኖች ቢያስቡበት መልካም ይመስለኛል፡ ምክንያት አለኝ –  ምክንያቴ ደግሞ ለማንም ግልጽ ነው፡፡

ተራ ስሞችን ማንም ቢጠቀምባቸው ችግር የለውም፡፡ ለምሣሌ  በመቶዎች የሚቆጠሩ “ይሄይስ” የሚባሉ ስሞች በኢትዮጵያ ውስጥና ውጪ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ያ ምንም ችግር የለውም፡፡ የማዕረግና የሹመት ስሞች ግን አንዱን ከሌላው እንዳያምታቱ ተጨማሪ መግለጫ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለዚህም ነው ለምሣሌ ዳግማዊ ቴዎድሮስ፣ ዳግማዊ ምንሊክ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ፣ አፄ ዮሐንስ አራተኛ፣ ሉዊስ 16ኛ፣ ጆን ፖል ሁለተኛ፣ ቤኔዲክት 16ኛ… እየተባለ የሚጠራው፡፡ አንድ ሰው ተነስቶ “አቡነ ቴዎፍሎስ እጅግ የተከበሩና በሕዝብ የተፈቀሩ ሊቀ ጳጳስ ነበሩ፡፡ በስማቸውም አንድ የበጎ አድራት አቋቁመው ደሞዛቸውን እንዳለ ወደዚያ ድርጅት ነበር ፈሰስ የሚያደርጉት፡፡…” ብሎ ቢጽፍ ስለየትኛው ቴዎፍሎስ እየተናገረ እንደሆነ ተጨማሪ መግለጫ ወይ ማብራሪያ በግርጌ ማስታወሻ መስጠት ይጠበቅበታል፤ አለበለዚያ አንባቢን ያደነጋግራል፡፡ ስለዚህ ሌላ አሳሳች መጠሪያ ያለባቸው አዲሶቹ ተሹዋሚዎች በስማቸው ላይ ቁጥር ቢደረብ ጥሩ ነው እላለሁ – ተለይተው እንዲታወቁ፡፡

በበቀደሙ ዜና ደግሞ በ10 ዓመታቸውና በ12 ዓመታቸው የዲቁና ማዕረግ የተሰጣቸው የቀድሞ ሕጻነት የአሁን አባቶች እንደነበሩ ተገልጾኣ፡፡ የአሥር ዓመት ልጅ የዲቁና ማዕረግ ይሰጠዋል? ከሆነ ጥሩ፡፡ ካልሆነ ግን መረጃው በውል መፈተሸ ነበረበት ወይም አለበት፡፡ የዕድሜ ነገር አወዛጋቢና አስተዛዛቢም ስለሆነ ይህ ዓይነቱ ነገር  ቢያንስ ለወደፊቱ ይታሰብበት፡፡

ከዚህ በተያያዘ አንድ አባት በ17 ዓመት ዕድሜያቸው መንኩሰው ለቅስና ክህነት እንደበቁ ተዘግቧል፡፡ በዚህ እኔም በጣም ግር ብሎኛል፡፡ ባለኝ ግርድፍ ሃይማኖታዊ ዕውቀት አንድ ሰው ቄስ ለመሆን ቢያንስ የ30 ዓመት ጎልማሣ ሊሆን ይጠበቅበታል – እንኳን ምንኩስና፡፡ ምንኩስና ደግሞ ብዙ የጥሞናና የእውነተኛ ጥሪ ማስተማመኛ ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ “ነገሩ ካንገት ነው ወይንስ ካንጀት” – “ጥሪው መለኮታዊ ነው ወይንስ ሰይጣናዊ” ተብሎ መጣራት አለበት፡፡ “በ17 ዓመት ይመነኮሳል፣ በ17 ዓመት የቅስና ክህነት ይሰጣል” ብዬ ደግሞ አላምንም – ሆኖም ከሆነ አንድ ቦታ ላይ ስህተት መኖር አለበት፡፡ ይህም መረጃ ይጣራና ማስተካከያ ወይም ማስተባበያ ይሰጥበት – አንድ ዜጋ ጠየቀ -እኔ፡፡ የ17 ዓመት ታዳጊ ምን ያውቅና፣ ምንስ የሕይወት ተሞክሮ አለውና ነው ምንኩስና ላይ የሚደረብ ቅስና የሚሰጠው? አስረዱኝ፡፡

አንድ ዲያቆን ከደቆነ በኋላ በርከት ላለ ጊዜ በዚህ ማዕረግ ያገለግላል፡፡ ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት 30 ዓመት ሲሞላውና አስፈላጊውን ዕውቀትና ትምህርት አሟልቶ ሲገኝ የቅስና ማዕረግ ይጠይቃል፡፡ ይሄኔ አንድም ማግባቱ አንድም መመንኮሱ ይረጋገጥና ተፈትኖ ክህነቱ ይሰጠዋል፡፡ የ17 ዓመት ልጅ እንግዲህ አንድም ለጋብቻ አንድም ለምንኩስና አልደረስምና ጥያቄ ያስነሳል፡፡ (የቃል ፈተናው ላይ ሦስቱ ሥላሦችን አስረዳ የተባለ የቅስና ማዕረግ ለመቀበል ያመለከተ አንጋፋ ዲያቆን  የሥላሤ ጽላቶች የሚገኙባቸውን ሦስት ደብሮች እንደጠቀሰና ፈታኞቹን በሣቅ እንደገደላቸው ሰምቻለሁ – “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” የተባለውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መሰለኝ፡፡)

የአራቱ አባቶች የትውልድ ቦታ በደምሳሳው “ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ዓመተ ምሕረት ተወለዱ” ይልና ሁለቱ ግን ከአራቱ በተለዬ የተወለዱበት ሥፍራ አንዱ በትክክል ሌላው “ሰሜን” በሚል በገደምዳሜ ተጠቅሷል፡፡ የአራቱ በጣም ተስማምቶኛል – ካህን ሀገር ስለሌለው፡፡ የሌሎቹ የሁለቱ ግን እንደሌሎቹ እንዳራቱ መሆን ነበረበት – ተለጣጣቂነቱ እንዳይፋረስ (consistence እንዲኖረው)፡፡ በቃ፡፡ አንዳንድ ነጥቦች አልኩ – እነሱንም እንደነገሩ ጨረስኩ፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 9 years ago on June 23, 2016
  • By:
  • Last Modified: June 23, 2016 @ 9:11 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar