www.maledatimes.com አቤ ጆቤና ሥጋቱ ይሄይስ አእምሮ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

አቤ ጆቤና ሥጋቱ ይሄይስ አእምሮ

By   /   June 23, 2016  /   Comments Off on አቤ ጆቤና ሥጋቱ ይሄይስ አእምሮ

    Print       Email
0 0
Read Time:7 Minute, 3 Second

    

ኢትዮጵያን መቀመቅ ከከተቱ ከሃዲ ልጆቿ መካከል አንዱ የሆነው አበበ ተ/ሃይማኖት የተባለ ፀረ-ዐማራ ወያኔ ሰሞኑን የገባበት ሥጋት ለዬት ይላል፡፡ በዘመነ ዴሞክራሲ መቃብሩን ፈንቅሎ የወጣውና ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ልዩ ጭካኔ ሀገር ምድሩን እያመሰ የሚገኘው የዐፄ ዮሐንስ ሥርወ መንግሥት እየተነቃነቀ ያለ መሆኑን በዚህ ሰውዬ ያልተለመደ የቀቢጸ ተስፋ እንቅስቃሴ መረዳት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን  ከወያኔያዊ የአፓርታይድ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት የሚደረገው ሁለገብ ትግል በተለይ ሥልጣን ከትግሬዎች መውጣት የለበትም ብለው የደመደሙና ይህንንም ትግሬያዊ ወርቃማ ዕድል ዘላለማዊ ለማድረግ የሚታገሉ ወገኖች በአሁኑ ወቅት የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንዳይኖር አድርጓቸዋል፡፡ የማይቀረው የኢትዮጵያ ነፃነት የፍየል ሥጋ ሆኖባቸው በህልምም በውንም እያስቃዣቸው ነው፡፡ ጆቤም የዚሁ የፍየል ሥጋ ሰለባ ነው፡፡ እርሱ እንዲያውም በቂ ጊዜና የመመገብ ፍላጎት የነበረው ይመስለኛልና አንዷን ፍየል ለብቻው ሳይቀረጥፋት አልቀረም፡፡ የፍየል ሥጋ በሽታን ይቀሰቅሳል፤ የሠራ አካልን እየበረበረ ቁርጥማት ይለቃል፤ ሸርተቴ በሸርተቴም ያደርጋል፡፡ ዐመልን እንደውኃ ያቀጥናል፡፡ ጆቤ ከወንድሞቹና ከትግል አጋሮቹ ጋር በአሁኑ ወቅት የሚናጨውና የሚጋጨውም ለዚህ ነው፡፡ “ለምን አደብ ገዝታችሁ የትግሬን የበላይነት አስጠብቃችሁ አትኖሩም? ለምን እሰው ጥርስ ትከቱናላችሁ? ተቃውሞዎች እየተነሱ ያሉት እኮ ከአመራር ግድፈት ነው፡፡” በሚል እየመከራቸው ይመስላል፡፡ ግን አልሰሙትም፤ ግጭታቸው ደግሞ እየተባባሰ እንደሚሄድ ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡ ተረቱ “ሲያልቅ አያምር” ብሎ ዱሮውን ጨርሶታል፡፡ የክፉ ነገር መጨረሻ ብዙውን ጊዜ አያምርምና፡፡

እንዲህ የምለው አንዱን ጽሑፉን ከደቂቃዎች በፊት ስላነበብኩ ነው፡፡ ጆቤ  ከ25 ዓመታት መሪር የሆነ ሂትለራዊ፣ አፓርታዳዊ፣ ሙሶሊኒያዊ፣ መንገሥቱ ኃይለማርያማዊ፣ መለሳዊ፣ ዐፄ ቦካሳዊና ኢዲያሚኒያዊ አገዛዝ በኋላ ዛሬ ድንገት እንደልዩ ራዕይ ተከስቶለት “ደርጋዊነት እያቆጠቆጠ ነው” ይለናል፡፡ ይህን የአጋንንት ውላጅ ጆቤ የሚሉት ወያኔ አንዳች ነገር ሰውነቱ ላይ ያቆጥቁጥበትና የኛን ሞት የሚያጸድቅ፣ የወያኔን ተሃድሶ የሚያረጋግጥ ቱሪናፋውን ይለቅብናል፡፡ በርሱ ቤት ወንድሞቹን በማናደድ ምክሩን ሰምተው አገዛዛቸውን እንዲያሻሽሉና ወያኔ ዕድሜ ልኳን እኛን እንደቀጠቀጠች እንድንትኖር ነው፡፡ እርሱ በሚመክራቸው ተስተካክለው ቢሄዱ የኛ ችግር ለርሱ ሠርግና ምላሽ ነውና ምንም የሚሰማው ነገር አይኖርም፡፡

ሜቴክ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ በትግራይ ተወላጆች መያዙን እናውቃለን – ጥሬ እውነቱ ይሄው ነው፡፡ ይህ አስመሳይ ጆቤ ግን እንዲህ ይለናል፤ “…ሜቴክ አመራር ላይ በርከት ያሉ የትግራይ ተወላጆች ሊኖሩ ይችላሉ።” [ልብ አድርጉ! ያውም ‹ሊኖሩ ይችላሉ› ነው የሚለን ራሱ ተጠራጥሮ አንባቢን ሊያጠራጥር!] ይቀጥል እንስማው እስኪ – “ በትግራይ ይሁን በሌላው ኢትዮጵያ እንደ ትግራይ ተቛም አድርጎ ማየቱ ( percieve  ማድረጉ) መሰረታዊ ስህተት ነው።” ይላል የኢትዮጵያ ተቆርቋሪ ልጅ አበበ ተ/ሃይማት በወያኔን አድን ድርሣኑ፡፡ እንግዲህ ሜቴክን የማን ንብረት እንበል?

ውድ ቀልማዳው ወያኔያችን አበበ ጆቤ ሆይ! እንኳንስ ሜቴክ እኔ ድሃው ይሄይስ አእምሮ እንኳን ሳልቀር የወያኔ አንጡራ ሀብት ነኝ፡፡ ተንፍስ ሲሉኝ የምተነፍስ፣ ተኛ ሲሉኝ የምተኛ፣ታሰር ሲሉኝ የምታሰር፣ ቢገድሉኝ የምሞት፣ ከእንስሳትም ያነስኩ የነሱው ድኩማን ነኝ፡፡ ይህን ደግሞ ጆቤ ራሱ ያውቃል – እንኳንስ የኢትዮጵያን በወያኔ ወለድ አገድነት መያዝ፡፡ የመንግሥት ተብዬዎቹ መሥሪያ ቤቶች ሁሉ በኃላፊነትና በፈላጭ ቆራጭነት ብቻ ለብቻ የተያዙት በትግራይ ተወላጆች ነው፡፡ ይህን እውነት መካድ የኅሊና መታወር ወይም አነስ ሲል ደግሞ አድርባይነት ነው፤ እርግጥ ነው ከዚህ ነጥብ አንፃር ብዙ ሰው እየፈራ ይህን መናገር አይፈልግም – የምንናገረውንም ይቆጣናል – እንዴ ፍርሀትና ይሉኝታ እኮ ገደብ ሊኖረው ይገባል፡፡ በበኩሌ ከዐይኔ ወዲያ ማንንም አላምንም፡፡ ስለዚህ ዋናው የጥቅም ቦታ ሜቴክ ቀርቶ ተራው የማዘጋጃ ቤት የቆሻሻ ገንዳ ጠባቂና አስጠባቂ ሳይቀር የትግሬ ነው፤ በዚህ ጉዳይ ምንም ዓይነት መደባበቅ ሊኖር አይገባም፡፡ እነሱ ለአስነዋሪ ድርጊታቸው ያላፈሩ እኔ ያን ቆሻሻ ድርጊታቸውን ስናገር ልወቀስ አይገባም፡፡ ስለዚህ ጆቤም አፈር በል (‹አፈር ብላ› ያልኩ እንዳይመስልብኝ – ‹እፈር‹ ነው ያልኩት)፤ ይሉኝታ ይኑርህ፡፡ በነገራችን ላይ ከበረሃ ጀምሮ በባዶ ስድስት የወያኔ ኦሽትዊዝ (በፈረንሣዊ አቻው ጊሎቲን) ጆቤ እንዴት ያለ የተዋጣለት ገራፊና ገዳይ የነበረ መሆኑን ሰሞኑን ካነበብኩት አንድ ጽሑፍ የተገነዘብኩና በሰዎች የመለዋወጥ ባሕርይ የተገረምኩ መሆኔን እዚህ ላይ ላስታውስ አልሻም፡፡ ሰው ጉደኛ ፍጡር ነው፡፡

ጆቤ ይቀጥልና፣ “ሜቴክ ተጠያቂነት፣ ግልፅነት፣ የሕግ የበላይነት የማይመለከተው አካል ሆኖ የአገራችንን ከፍተኛ ሃብት ሲያጠፋፋ ግን እንደ ኢትዮጵያዉያን ራሳችንን ደፍተን እናዝናለን።” ካለን በኋላ “እዛ ያሉ የትግራይ ተወላጆች ጥቂት ቀጣፊዎችና ከነሱ ጋር የሚቀራረቡትን ይጠቀማሉ እንጂ የትግራይ ህዝብን እየበደሉት ነው፤[ቂቂቂ…] ለዛዉም ባለ ሁለት ስለት በደል። ባንዱ በኩል እንደ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የሃገራቸው ሃብት እየተዘረፈ ነው[ቂቂቂ…]፤ በሌላ በኩል በስሙ እየነገዱ ነው፣ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ደግሞ ወደ አላስፈላጊ ጥርጣሬ እንዲገቡ ሊያደርግ ይችላል።[ቂቂቂ…]” በማለት በአገም ጠቀም አነጋገር ትግራውያን ወንድምና እህቶቻችን ከደሙ ንጹሕ መሆናቸውን ሊሰብከን ይንደፋደፋል – እኛ ደናቁርት ማይማን ሆነን(ሣቆች ከኔው የተጨመሩ ናቸው)፡፡

አላስፈላጊው ጥርጣሬ ምንድነው? “ወያኔዎች ይህችን ሀገር ከደርግ ኢ–ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ነፃ ካወጡ በኋላ ለሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች እኩል ማርና ወተት ማዝነብ ጀመሩ” ከሚል ትክክለኛ ወያኔያዊ ግንዛቤ ወጥተን “እነዚህ ስግብግብና ቀትረ ቀላል ወያኔዎች  በየዋህነትና በደርግ ምሬት ሳቢያ በተገኘ የሕዝቡ ድጋፍና በአሜሪካን ቡራኬ የደርግን ኢትዮጵያዊ ግን ጨካኝ መንግሥት ከሥልጣን ካስወገዱ በኋላ ሀገሪቱን ለራሳቸው ጥቅም ብቻ አዋሏት፤ ሌሎችን ገፍተው ባይተዋርና የበይ ተመልካች አደረጓቸው፤  በሥልጣን ይቀናቀነናል የሚሉትን የዐማራ ሕዝብ በተለይ ዕልቂትና የዘር ማጥፋት ዐወጁበት…” ወደሚል የነፍጠኛ ግንዛቤ ማምራታችን ዕውቅና አግኝቶ ይሆን “አላስፈላጊ ጥርጣሬ” የተባለው? ጀቤ ሆይ ለይልን፡፡ የወያኔ ሁሉም ነገር መቆጣጠር ጥርጣሬ ውስጥ የገባው በሩብ ምዕተ ዓመቱ የዘረፋና የስርቆት ረጂም ጊዜ ሳይሆን ገና ከመነሻው ነው – የጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ጄኔሬተርና የሕክምና ቁሣቁስ ያኔ አዲስ አበባ በገባችሁ ሰሞን መብራት አጥፍታችሁ ነቃቅላችሁ በጨለማ ስትወስዱ ሁሉ ሌብነታችሁንና ለሀገር ውድመት እንጂ ለልማት አለመምጣታችሁን ሕዝቡ አውቆት ነበር – ለዚያም ነበር በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በኅቡዕ አጻጻፍ “ትግራይ እስክትለማ ሌላው ሀገር ይድማ” ተብሎ ተጽፎ የነበረው – ያን የጻፈ ሰው ልጅ ይውጣለት – ትዝ ይለኛል በግጥም ስንኞች ውስጥ ቁልቁል በሚነበብ ሥልት ነበር ያስቀመጠው፡፡ ዛሬ ምን አዲስ ነገር ተገኘና ነው የምንጠራጠረው? ስለኛ መጠራጠር ሣይሆን ስለናንተው መፃዒ ዕድል ተጨነቅ ይልቁንስ፡፡ “የሰው በልቶ አያድሩም ተኝቶ” ይባላል – ብፃይ አቤ ጆቤ፡፡

ጆቤ የወያኔን ሕገ መንግሥት በሚመለከት እንዲህ ይለናል፤ “በቅርቡ ኢታማዦር ሹሙ ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ግንቦት ሃያን አስመልክተው በመቐለ ከተማ ያካሄዱት ዉይይት ላይ ያነስዋቸው ሃሳቦችና እና የተናገርዋቸው ነገሮች በጣም እሚያሳዝኑና ሕገ መንግስቱን ገደል ግባ ያሉበት መድረክ ነበር።” አዎ፣ ሣሞራ የሚያሳዝን ንግግር መናገር ብርቁ አይደለም፤ እርሱ ለጣፊ ወይ ለዳፊ እንጂ ተናጋሪ አይደለም፡፡ እርሱ እንደመለስ ትምህርት ስለሌለው ቃሉ ሁሌም የማም ነው – በቂም በቀልባ በጥላቻ የተሞላ ማይም ደግሞ ሲናገር ልብን ይሰብራል፡፡ “ዐማራንና ኦርቶዶክስን ገድለን ቀብረናቸዋል” ብሎ የአንዲት የጋራ ሀገር ኤታ ማዦር ሹም ሲናገር የት ነበርክ ጆቤ? ያኔ ግን ስቀህ አጨበጨብክለት አይደል? ግም ለግም አብረህ አዝግም ነዋ፡፡  አሁን ግን ሥልጣናችሁ እንደአህያ ጭነት እየተንጋደደ ሲመጣ “የትግራይ ሕዝብ ማለት ሕወሓት ነው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማለት ደግሞ ኢሕወደግ ነው” በማለቱ ብቻ ታዘብከው፡፡ ምን አጠፋ? እውነቱን ነው፡፡ እኔ እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ኢሕአዲግን “እወክላለሁ” – አንተ ጆቤ ደግሞ እንደትግሬነትህም እንደታጋይነትህም ሕወሓትን ትወክላለህ፡፡ ይህ ንግግሩ ከቀደሙ ፀያፍና ብልግና የተሞላባቸው ንግግሮቹ ጋር ሲወዳደር የመልአክ ንግግር ያህል ነው፡፡ አንተን ያሳሰበህ ግን የሕወሓት እየተዳከመች መምጣት ነው – አንወሻሽ፤ ያንተና የሪፖርተር ጋዜጣ ጭንቀት ይገባናል፡፡ አይዞህ ሕወሓት ሞታም ከሆነ ሰማይ ቤት በአንደኛው ጥጋት ላይ ታገኛታለህ – የገደልካቸውንም ሰዎች ቢያንስ በአሻጋሪ ታያቸው ይሆናል፡፡ ስናገር የግምባር ሥጋ ነኝ ጆቤ፡፡ እርግጥ ነው ግልጽነት ባልተለመደበት ሥፍራ በግልጽ መናገር ነውር መሆኑን አላጣውም፡፡ ቢሆንም  ይሁን ግዴለም፡፡

አንዱ ቦታ ላይ ደግሞ “ፖለቲካዊ ሚና የማይኖረው ሕገ መንግስታዊ ተልእኮዉን ብቻ የሚወጣ የመከላከያ ሃይል ለመገንባት የኢትዮጵያ ህዝቦች ከፍተኛ መስዋእትነት ክፍለዋል።” [ቂቂቂ…] ትልና የወያኔ መዳከም የእግር እሳት እንደሆነብህ ትደሰኩራለህ፡፡ በመሠረቱ ጽሑፍህ ሲታይ የተደበላለቁ ስብዕናዎች የሚንጸባረቅበት ይመስላል፡፡ ምን ህገ መንግሥት አለና ነው አንተም አሥሬ “ህገ መንግሥት፣ ህገ መንግሥት” የምትለው ጆቤ? ይህን እንደፈለጋችሁ የምትደፈጥጡትንና አንድን ሰው ለማሰር ወይ ለመፍታት በአንድ ጀምበር አዲስ ህገ መንግሥት ጽፋችሁ ነባሩን ፌዘኛ ህግ ተብዬ ውዳቂ ሰነድ በቅጽበቶች ውስጥ አፈር ድሜ የምታሉትን ከባዶ ወረቀት የማይሻል ዶሴ ነው ህገ መንግሥት የምትለን ? ሰዎች “በህገ መንግሥቱ ይሁንባችሁ” ሲሏችሁ “እንትንህን ጥረግበት” የምትሏቸውን ይሄን የውሸት ህገ መንግሥት ማለትህ ይሆን? የኢትዮጵያ ሕዝብስ ለዚህ ነው የታገለው? የትኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ? እኛና አንተ የምናውቃቸው የተለያዩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ካሉ ለይልን እስኪ፡፡  (ሣቅ በኔ ወጪ የተጨመረ)

የጆቬ ዋና ሥጋት የወያኔ ሠራዊት- ከጽሑፉ እጠቅሳለሁ – “የሲቪሉን አስተዳደር ህዝባዊ ስልጣን አክብሮና ለሕገ መንግስቱ ተገዢ ሆኖ ግዴታዉን የሚፈፅም፣ አገሩን በብቃት የሚከላከል፣ ጥቃትን የሚያስቀር ወይም በቂ ምላሽ መስጠት የሚችል ሃይል ሆኖ” አለመገኘቱ ሲሆን ይህን  መሰረታዊ ተልእኮ የዘነጋ ኃይል ተፈጥሮ “ በከፍተኛ አመራሮቹ እየታየ ያለው ነገር አንዳንድ ስጋቶችን እየጫረ” መታየቱ ነው፡፡ ሌላ ሥጋት የለበትም ጆቤ፡፡ የኛ ጆቤ፡፡ ሕዝቡ ላይ እንደመርግ የተጫነው የኑሮ ውድነት፣ አለህግ መፈናቀልና መጋዝ፣ በገፍ መሰደድና በሰው አገር መንገላታት፣ የድንበሮች መሸጥና ወደሌሎች ሀገራት ግዛት ውስጥ መካተት፣ ወያኔ ባመጣው ጦስ የዜጎች በዘርና በሃይማኖት ተከፋፍሎ  በጆቤ ዐማርኛ በየክልሉ “መበሳበስ”፣ እስር ቤቶች ከአፍ እስከገደፋቸው በዜጎች መሞላት፣ የሙስና ከጫፍ እጫፍ መንሰራፋት…. የጆቤ ችግሮች አይደሉም፡፡ አይ ጆቤ!

ፀረ-ዐማራው ጆብነት ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግሮች በስፋት ባተተበት አንቀጽ “የኢትዮጵያ ህዝቦች ከህግ ዉጪ አንገዛም ማለት ጀምረዋል። የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራስያዊ እንቅስቃሴ፣ የቅማንት ህዝቦች ዴሞክራስያዊ ትግል፣ በትግራይ ደግሞ እንደ እምባሰነይቲ ዓይነት ዴሞክራስያዊ እንቅስቃሴ፣ የኮንሶ ህዝቦች ዴሞክራስያዊ ጥያቄን እንደ ምሳሌ ሊወሰዱ ይችላሉ። ገዢው ፓርቲ ቆሟል ወይም ወደ ኃላ እየነጎደ ነው፤ ባጭሩ ጥልቕ ፖለቲካዊ ችግር (political crisis) አለ። ሆኖም ይህንን ችግር መፈታት ያለበት ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ እንጂ [ቂቂቂ…]ከዛ ዉጪ በሆነ መንገዶች መሆን የለበትም።” ይለናል፡፡(‹የኢትዮጵያ ሕዝቦች‹ በማለታቸው ስንደነቅ ቆይተን አሁን ደግሞ በመጨረሻው ‹የኦሮሞ ህዝቦች፤ የቅማንት ህዝቦች› ማለትም ጀመሩ – ከደነቆሩ አይቀር እንዲህ ነው፤ ስኬታማ ድንቁርና!)

በነገራችን ላይ ጆቤን ፀረ-ዐማራ ብዬ የፈረጅኩት በዚህ የችግሮች ዝርዝር ውስጥ ስለወልቃይት ዐማሮች በጨረፍታ እንኳን ለመጥቀስ የሚዘገንነው መሆኑን ከመረዳት አንጻር ነው፤ ስለነሱ ማንሳት የትግራይን ታላቅነት እንደመዳፈር ያህል ተሰማው፡፡ የኛ ጆቤ እንዲህ ነው፡፡ በሌላው ረገድ እኔ ለምሣሌ ስለኮንሶ “ህዝቦች” ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ብዙም የተለዬ ነገር አላውቅም፤ ምናልባት ብዙ አልተወራለት ሆኖ ይሆናል፡፡ ስለወልቃይት ግን ብዙ ተብሏልና ብዙ አውቃለሁ – ጆቤ ግን እስካሁን ምንም አልሰማም፡፡ ወደፊትም አይሰማ ይሆናል፡፡ ለተጠናወተው የጆሮ ህመም እባካችሁን እንጸልይለት፡፡ ሸንኮራ ጠበል ቢሄድና ጥቂት ቢጠመቅ ሳይሻለው አይቀርም፤ ፈቃደኛ ከሆነ፡፡

ይቺ ንግግሩ ደግሞ ፈገግ አስደርጋኛለች – ደግሞም አልገባችኝም፡፡ “በኤርትራ በኩል የሚመጣ ተከታታይነት ያለው ዜጎቻችንን የማበሳበስ ሁኔታ እያስተዋልን ነው።” የማበሳበስ ሲል ምን ማለቱ ነው? ይቺ ቃል ሴማዊ መሆኗ ያስታውቅባታል፡፡ እዚህ ላይ ያላት ትርጉም ግነ ግልጽ አይደለም – ቢያንስ ለኔ፡፡ እኔ እማውቀው በሶ ማበስበስ ነው፡፡ እ… ዝናብም ያበሰብሳል፡፡ ኤርትራም ዝናብ ሆና ይሆን እንዴ እንዲህ የምታበሰብሰን? ሰው በስንቱ ይቸገራል? ላልጠፋ ቃል?

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 8 years ago on June 23, 2016
  • By:
  • Last Modified: June 23, 2016 @ 9:43 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar