ከተመሰረተ 70ኛ አመቱን ያከበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ ካስገባቸው አስራ አምስት Dreamliner 787 አውሮፕላኖች ውስጥ በመለስ ስም የተሰየመው አውሮፕላን አዲስ አበባ ገብቷል። ከዚህ በፊት የሰሜን ተራሮች፣ የአክሱም እና ታሪካዊ የሆኑ ቦታዎች ስም የተሰጣቸው Dreamliner አውሮፕላኖች ገብተዋል። ስያሜው የአገርን ቅርስ አመላካች በመሆኑ ብዙ የሚያወዛግብ ጉዳይ አይደለም። ባለፈው ሳምንት ግን ET-ATK የሚል የመዝገብ ቁጥር (Registration Number) ያለው፤ በመለስ ዜናዊ ስም “መለስ” የሚል ስያሜ የተሰጠው አውሮፕላን ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ገብቷል።
(ሙሉውን በPDF ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)
አውሮፕላኑ የገባበት ሳምንት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ህዝባዊ ንቅናቄ የተነሳበት ሰሞን በመሆኑ፤ “ሆድ የባሰውን ህዝብ ይባስ ያነሳሳል” በሚል ስጋት በኢትዮጵያ ዜናዎች ጭምር ዘገባው እንዳይቀርብ ተደርጓል። ድርጊቱ ግን የአየር መንገዱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ገለልተኛ ሳይሆኑ፤ የአንድ ዘር እና ፓርቲ ደጋፊ ለመሆናቸው ማረጋገጫ ሆኖ አልፏል። እነሆ ከዚህ በታች የምናነሳቸው ጉዳዮች በአየር መንገዱ ውስጥ የሚፈጸሙ የስራ ግድፈቶችን በጥቅል የሚያሳዩ ናቸው።
መለስ የሚል ስያሜ የተሰጠው Dreamliner 787
የኢትዮጵያ አየር መንገድ መለስ ዜናዊ ከመወለዱ ዘጠኝ አመት በፊት በ1946 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን፤ በወቅቱ የመጀመሪያ በረራዎቹን ወደ ካይሮ፣ ጅቡቲ እና የመን ያደርግ ነበር። በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጥረት እና ክትትል ተጀምሮ፤ አሁን ሰባ አመቱን ያከበረው አየር መንገድ ሰባ ያህል አለም አቀፍ በረራዎችን ለማድረግ የበቃ ነው። ወደኋላ መለስ ብለን ካስተዋልን ደግሞ… ለዚህ ካበቁት ውስጥ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በዋናነት የሚጠቀሱ ቢሆንም፤ ድርጅቱ በስማቸው አውሮፕላን ሊሰይምላቸው ቀርቶ፤ የሳቸውን ጥረት እና ድካም የሚያሳይ ማስታወሻ እንኳን አልተወላቸውም።
ይህ በ’ንዲህ እንዳለ ነው እንግዲህ፤ አየር መንገዱ ቦይንግ ካምፓኒ ያደሳቸውን Dreamliner 787 አውሮፕላኖች አዲስ አበባ ማስገባት የጀመረው። እኛም ይህን ምክንያት አድርገን በአየር መንገዱ ውስጥ የሚታዩትን ብልሹ አሰራሮች በወፍ በረር እንቃኝ።
እርግጥ ነው። መለስ ዜናዊ የህወሃት እና የኢህአዴግ ፓርቲ ሊቀመንበር ነበር። የፖለቲካ ፓርቲው አባላት መለስ ዜናዊን ከሰው በላይ ከአምላክ በታች አድርገው ያዩታል። በስሙ ልዩ ልዩ ድርጅቶችን ከፍተዋል፤ ፋውንዴሽንም አቋቁመዋል። በቀብሩ ሰሞን… “ከአቡነ አረጋዊ ያልተናነሰ ስራ ሰርቷልና በስሙ ታቦት ሊቀረጽለት ይገባል…” ማለታቸውን ሰምተን፤ አማትበን ሳንጨርስ በመለስ ስም አውሮፕላን እንዲሰየም መደረጉ አስገርሞናል። ደጋግመን እንደምንለው… ይህ የአየር መንገዱ ከፍተኛ አካል የፖለቲካ ፓርቲ ጥገኛ እየሆነ ለመምጣቱ ዋነኛው አመላካች ነው። በአሁኑ ወቅት ከዋና ሴኩሪቲ ጀምሮ እስከ ስራ አስኪያጅ ድረስ የአየር መንገዱ ሰራተኞች የትግራይ ተወላጆች እንዲሆኑ እየተደረገ ነው።
ለምሳሌ የሴኩሪቲ የጥበቃ ስራውን ሙሉ ለሙሉ የሚያከናውኑት የትግራይ ተወላጆች ናቸው። በውጭ አገር ተመድበው አየር መንገዱን በመወከል የሚሰሩት ሰዎች አብዛኞቹ እነሱ ናቸው። የበረራ አስተናጋጅ ሆነው እንዲሰሩ ምልመላ የሚደረገው ትግራይ ድረስ እየተኼደ ጭምር ነው። የግራውንድ ቴክኒሺያንነት እና የበረራ ስራውን እንዲያደርጉ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው፤ ስልጠና እየወሰዱ ያሉት የትግራይ ልጆች ናቸው። ይህ በአየር መንገዱ ውስጥ በግልጽ የሚታይ፤ ከውጭ ሆነው ለሚታዘቡ ሰዎች ደስ የማያሰኝ አካሄድ ነው።
ሲጀመር… የአየር መንገዱ የቦርድ ሊቀመንበር አርከበ ዕቁባይ፤ የህወሃት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበረ ነው። ሲቀጥል… የአየር መንገዱ ስራ አስኪያጅ ተወልደ ገብረማርያም የህወሃት ፓርቲ አባል ነው። ሲሰልስ… በከፍተኛ ቁልፍ ቦታዎች የተቀመጡ የስራ ሃላፊዎች በተመሳሳይ ሁኔታ የትግራይ ህወሃት ወይም የኢህአዴግ አባላት ናቸው። የዚህ ሁሉ መነሻው ደግሞ፤ ጠባብ ብሔረተኝነት ነው።
ተወልደ ገብረማርያምን እንደምሳሌ እንውሰድ። ኢህአዴግ ስልጣን ከተቆናጠጠ ግዜ ጀምሮ በአየር መንገዱ ውስጥ በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ እንዲሰራ እየተደረገ ስራውን ሲለማመድ ቆይቷል። አቶ ግርማ ዋቄ CEO ሆነው ሲሰሩ፤ ለአምስት አመት የስራ ኮንትራት ነው አየር መንገዱን የተቀላቀሉት። በወቅቱ ተወልደ CFO ሆኖ በመስራት የአቶ ግርማ ዋቄ ኮንትራት እስከሚያበቃ ድረስ፤ አልጋ ወራሽ ሆኖ እንዲቆይ ነው የተደረገው። አቶ ግርማ ዋቄ አየር መንገዱን ለቀው ከወጡበት ግዜ ጀምሮ ተወልደ ላልታወቁ አመታት፤ ባልታወቀ የኮንትራት ቅጥር በሃላፊነት ቦታ ላይ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል።
ተወልደ በአየር መንገዱ ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ በማን አለብኝነት የሚሰራቸው ስራዎች የሚያስደነግጡ ናቸው። ለምሳሌ የዛሬ አምስት አመት ግድም MD11 የተባለ አውሮፕላን በድንገት መጣ። ስለአውሮፕላኑ ሰራተኞች ስለማያውቁ፤ “የምን አውሮፕላን ነው?” ይላሉ።
“በተወልደ ትእዛዝ የመጣ ነው!” ይባላል። ከዚያ በፊት ስለዚህ አውሮፕላን ማኔጅመንቱ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። ድንገተኛ ዱብእዳ ነው የሆነባቸው። በኋላ ላይ ለዚህ አውሮፕላን መወጣጫ እና ማሳለጫ እንዲሆን እስከ አስር ሚሊዮን ብር ድረስ ወጪ ተደርጓል። እንዲህ እንዲህ አይነቱ ብዙ ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል።
ለምሳሌ የቦይንግ 757 ጉዳይ እንመልከት። እነዚህ አውሮፕላኖች “የአገልግሎት ግዜያቸው አብቅቷል” ከተባለ በኋላ፤ በወረደ ዋጋ ለመከላከያ ድርጅት የርጥባን ያህል በትንሽ ዋጋ ተሽጠዋል። በአየር መንገዱ ውስጥ ግልጽነት የለም። ማኔጅመቱ ወይም ሌላ የስራ ሃላፊ ሊሰራ የሚገባውን ነገር፤ ተወልደ በጎን ተነጋግሮ የሚሊዮን ዶላር ጉዳይ በጓሮ በር ሲያስጨርስ ይታያል። በምሳሌ ላይ ሌላ ምሳሌ ማቅረብ እንዳይሆንብን እንጂ ሌላም ጉዳይ እዚህ ላይ ማከል ያስፈልጋል።
አብዛኞቹ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ አውሮፕላኖች የኢትዮጵያ አይደሉም። ይልቁንም ከሌላ አገር በኪራይ መልክ የሚሰራባቸው ናቸው። ጨዋታውን ልብ ብለው ይከታተሉ። በቅድሚያ አየር መንገዱ ለቦይንግ የስራ ትእዛዝ ይሰጣል። (የአንድDreamliner ዋጋ እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ልብ ይበሉ።) አውሮፕላኖቹ ተሰርተው ሲያልቁ፤ ሌላ ነጋዴ ድርጅት አውሮፕላኑን እንዲገዛው ይደረግና ለሃያ አመታት መልሰን እንከራየዋለን። ነገሩን በቀላሉ ለማስረዳት… ለምሳሌ ባለፈው ወር AWAS የተባለው የአየርላንድ ድርጅት ሶስት 787-8 Dreamliner ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ገዛ። ግዢውን የፈጸመበት የፊርማ ቀለም ሳይደርቅ፤ እነዚያኑ አውሮፕላኖች መልሶ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አከራየው።
አንዳንዶች “ምን የሚሉት አሰራር ነው?” ይሉ ይሆናል።
በዚህ ጉዳይ… አየር መንገዱ መልስ እንዲሰጥ ቢጠየቅ፤ “ይህ የኛ ቢዝነስ ስትራቴጂ ነው” የሚል የተለመደ መልስ አለው። ነገር ግን ከዚህ ጀርባ ሊኖር የሚችለውን የጓዳ በር ገንዘብ ቅብብሎሽ ከነተወልደ በቀር አየር መንገዱም አያውቀውም። ልብ ይበሉ። AWAS የተባለው የአየርላንድ ካምፓኒ የአንድ ቤተሰብ የግል ሃብት ነው። ግለሰብ እና የአየር መንገድ ስራ አስኪያጅ መለኪያቸውን እያጋጩ የሚያወጡትን እቅድ፤ ከህወሃት እና ከነተወልደ በቀር አየር መንገዱ ዝርዝር ጉዳዩን ሊያውቀው አይችልም። በነገራቹህ ላይ… ከኢትዮጵያ ተገዝቶ፤ እንደገና ለኢትዮጵያ የሚከራየው አውሮፕላን በሃያ አመት የኪራይ ዘመኑ ወቅት፤ አውሮፕላኑ ስራውን ቢያቆም ክፍያው አይቋረጥም… አውሮፕላኑ ቢበላሽ የጥገናውን ወጪ አከራዩ ሳይሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው የሚሸፍነው። (ሊመጣ የሚችለውን ኪሳራ አስባችሁታል?)
በሌላ በኩል ደግሞ የተወልደን ፈሪነት ወይም ለፓርቲው ሲል ምንም ከማድረግ እንደማይመለስ የሚያሳይ፤ እያሳዘነ የሚያስቅ ነገር እንመልከት። ከቅርብ አመታት በፊት… የኢህአዴግ ስበሰባ ሲደረግ ተወልደ ገብረማርያም ተገመገመ።
“ኢህአዴግ አንተን ለዚህ አብቅቶሃል።” የተደረገለት ውለታ ተዘረዘረና በመጨረሻ፤ “አንተ ግን የዚህ ትልቅ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ሆነህ፤ ለኢህአዴግ በተጨባጭ ምን አድርገሃል?” የሚል ጥያቄ ቀረበለት።
ተወልደ ፈጠን አለና፤ “ባለስልጣናት ወደ ውጭ ሲሄዱ…” ብሎ ሲጀምር አቋረጡትና…
“ጥያቄው ለፓርቲው እና ለባላቱ ምን አደረግክ? የሚል ነው?” በሚል ተስተካከለለት። ይሄኔ…
ተወልደ ምላሽ ሰጠ፤ “በየሰፈሩ ለተደራጁ ወጣቶች ከጽዳት እስከ ሻንጣ ጎታች ድረስ ስራ እንዲቀጠሩ አደርጋለሁ።” አለና ተጨበጨበለት።
ተወልደ ገብረማርያም
በሚቀጥለው ቀን… እንዳለው አደረገ። በሚገርም ሁኔታ ቀደም ሲል በኮንትራት የተቀጠሩት ሰራተኞች በሙሉ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ተባረሩ። በነሱ ምትክ ስለስራው ምንም የማያውቁ፤ በየመንደሩ ተደራጅተው ለኢህአዴግ የሚያሳብቁ፤ የወጣት ሊግ አባላት ኤርፖርቱን ሞሉት። ሻንጣ ተሸክሞ ማውረድ፤ አውርዶ መጎተት፣ ጎትቶ መጫን ከባድ ሆነባቸው። የመንገደኛው ሻንጣ በአግባቡ ባለመጫኑ፤ አውሮፕላኖች ከመንሻ ሰአታቸው እያረፈዱ… Delay በ delay ሆኑ። ይህ ቀን በአየር መንገዱ ሰራተኞች ብቻ ሳይሆን፤ በመንገደኛውም ጭምር የማይዘነጋ ሆኖ አለፈ።
በመጨረሻ… ከቀድሞዎቹ ሰራተኞች አንዳንዶቹ ወደ ስራ እንዲመለሱ ተደርጎ፤ የወጣት ሊግ አባላቱን አለማመዷቸው። እነዚያ ከየሰፈሩ እንደ ንፍሮ ተዘግነው የመጡ ወጣቶች፤ አንዳንዶቹ ሲቀሩ አብዛኞቹ ቀስ በቀስ ስራው እየከበዳቸው ወደቀድሞ የማሳበቅ ስራቸው ተመለሱ። እግዜር በቸርነቱ እንደደመና በተናቸውና ጥቂት ወጣቶች ብቻ በዚህ ስራ ቀጠሉበት። ይሄን እንደምሳሌ ያነሳነው ተወልደ ገብረማርያም በማናለብኝነት የሚፈጽመውን ብልሹ አሰራር ለመግለጽ ያህል ነው።
ሌላም ነገር እንጨምር። ተወልደ ስልጣን ከያዘ በኋላ፤ ሰራተኞች የሚሞሉት ቅጽ ተላለፈ። በቅጹ ላይ ሰራተኞች ብሄራቸውን፣ ማንነታቸውን እና የየትኛው ፖለቲካ ድርጅት አባል ወይም ደጋፊ እንደሆኑ የሚጠይቅ ቅጽ ተሰራጭቶ የአየር መንገዱ ሰራተኞች እንዲሞሉ ተደረገ። አሁን ታዲያ የስራ እድገትም ሆነ ንፍገት ሲያስፈልግ፤ ያቺ የሞሏት ቅጽ ካለችበት ትወጣና… የሰራተኛው ማንነትና ብሄሩ እየታየ ወደላይ ያድጋል ወይም ወደ ታች እንዲወርድ ይደረጋል። በ’ርግጥ ይህ አይነቱ አሰራር በአንዳንድ ትላልቅ ድርጅቶች ውስጥ የሚታይ ቢሆንም፤ በአየር መንገዱ ውስጥ እየጎላ የመጣ ችግር ሆኗል። እንዲህ አይነቶቹን የአስተዳደር ችግሮ አውርተን ስለማንጨርስ ወደ Dreamliner 787 ጨዋታችን እንመለስ።
ቀደም ሲል በነበረው አሰራር፤ ለአውሮፕላን ስም ሲወጣ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ሰራተኞች ዝርዝር ስሞችን ለተወልደ ያቀርቡለትና ውሳኔውን እሱ ይሰጣል። አሁን ግን… በምን መስፈርት አዲሱ Dreamliner በመለስ ዜናዊ ስም እንዲሰየም እንዳደረጉ ማንም አያውቅም። ምናልባት የህዝብ ግንኙነት ክፍሉም ይህን ስም ለተወልደ አላቀረበም ይሆናል። ድንገት በመለስ ስም አውሮፕላኑ ሲገባ ግን ሁሉም ደንግጠዋል።
መለስ የሚል ስያሜ የተሰጠው Dreamliner 787
በመለስ ስም አውሮፕላን እንደሚገባ ሰራተኞች የማያውቁትን ያህል፤ የአውሮፕላን ግዢ ሊዝ አፈጻጸሙን ስራ አስኪያጁ ተወልደ እና የቅርብ ሰዎች ካልሆኑ በስተቀር ሌሎች በጉዳዩ ላይ አይመክሩበትም። የዛሬው ጨዋታችን ላይ ምሳሌ ማቅረብ አብዝተናል። ቢሆንም “ለምሳሌ” ብለን በምሳሌ ብለን ጨዋታችንን እንቀጥል። ለምሳሌ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት Dreamliner ውስጥ መጀመሪያ የገቡት 5 አውሮፕላኖች ፍጥነት እና ድሎታቸው ተደማምሮ፤ “የተገዙበትን ዋጋ ይመጥናሉ” ብለን እንለፋቸው። ቀጥሎ የገቡት አራቱ “ደህና ናቸው” እንበል። አሁን (በመለስ ስም የተሰየመውን ጨምሮ) ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ያሉት ስድስት አውሮፕላኖች ግን፤ ከጀርባቸው ሙስና ከሌለ በቀር አትራፊ አይደሉም። በመረጃ እንነጋገር።
አሁን ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ያሉት ስድስት Dreamliner 787 አውሮፕላኖች… ቦይንግ ለሙከራ ሰርቷቸው የነበሩ ናቸው። በ2011 ተመርተው፤ ለጃፓኑ ANA አየር መንገድ ለሙከራ ተሰጡ። ሆኖም አውሮፕላኖቹ Boeing የዲዛይን specification ላይ ያለውን የክብደት መጠን (Delivery Empty Weight) የማያሟሉ ስለሆኑ የጃፓኑ ANA “አልፈልጋቸውም” ብሎ ለቦይንግ ካምፓኒ የመለሳቸው ናቸው። የድሮ ዋጋቸው 150 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፤ ባለባቸው እንከን ምክንያት ዋጋቸው በጣም ዝቅ ተደርጎ እያንዳንዳቸው በ80 ሚሊዮን ዶላር የተገዙ ናቸው። (መጨረሻቸውን ያሳምረው እንጂ፤ ዋጋቸው ደህና ነው)
ጠቅለል ለማድረግ ያህል… አየር መንገዱ 15 Dreamlineሮች አሉት። አሁን እየታደሱ የሚገቡት ስድስቱ ላይ፤ የጃፓኖቹን ያህል ባይሆንም ከትርፍ አኳያ፤ ጥናት ተደርጎ ለስራ አስኪያጁ ተወልደ ወልደማርያም ሰነዱ ተሰጥቶታል። በዚህ ጥናት ላይ የቦይንግ 767 እና 787ንፅፅር ተደርጓል። ንፅፅሩ የተደረገው ተሳፋሪ እና ጭነት የመሸከም አቅማቸው በሂሳብ ተሰልቶ፤ ከDreamlineሮቹ ይልቅ አየር መንገዱ መጨረሻ ላይ የገዛቸው ሶስት 767 አውሮፕላኖች የተሻሉ መሆናቸውን ባለሙያዎች ስሌቱን ሰርተው፤ ሰነድ አደራጅተው ለበላይ አካል አቅርበዋል። ይህ ሁሉ ጥናት ተደርጎም፤ ደረጃቸውን ስላላሟሉ ለቦይንግ የተመለሱት ስድስት አውሮፕላኖች፤ ቀለማቸው ተቀይሮ ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። የአስተዳደሩን ብልሹነት ማሳያ እንዲሆን በሚመስል መልኩ፤ 13ኛውን አውሮፕላን Meles የሚል ስያሜ ሰጥተውታል። ሌላ ሁለት የሚገቡ አሉ። “የነሱ ስም ደሞ ማን ይሆን?” በማለት፤ “አዜብ ወይም ኃይለማርያ ደሳለኝ ይሏቸው ይሆን?” እያልን በጭንቅ አለን።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ከሚታዩት የዘረኝነት እና የአስተዳደር ብልሹነት ባሻገር፤ ግልጽ ያልሆኑ አሰራሮች ይስተዋላሉ። ቸልተኝነት በጣም እየታየ ነው። ለምሳሌ የጥገና ሰራተኞችን ክፍል ብንመለከት… ከቅርብ ግዜ ወዲህ የሚቀጠሩት የጥገና ሰራተኞች ወደስራ ሲሰማሩ፤ ስራውን የሚያሳያቸው ወይም የሚያስተምራቸው ሰው በሌለበት ለአውሮፕላን የሚያደርጉት ክትትል እና ጥገና ደረጃውን የጠበቀ አይደለም። አንዳንዴ በተራ የሜካኒክ ቸልተኝነት (Human error) ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ይባክናል – ይሄ ሁሉም የሚያውቀው የአየር መንገዱ ኪሳራ ነው።
ማጠቃለያውን ለማጠቃለል ያህል… በየአመቱ “አየር መንገዱ አትራፊ ነው።” ከሚል ዜና ውጭ ውስጡን የሚመረምር “ተው ባይ” የሌለበት፤ የአንድ ብሄር እና ድርጅት አባላት የገዘፈበት መስሪያ ቤት እየሆነ መጥቷል – የኢትዮጵያ አየር መንገድ።
ይህ ብቻ አይደለም። ባለስልጣኖች ለአስቸኳይ ጉዳይ ወይም ህክምና ወደደቡብ አፍሪቃ፣ እና ኤዥያ መሄድ ሲፈልጉ በአየር መንገዱ ወጪ ቻርተር አውሮፕላን ተዘጋጅቶላቸው ይሄዳሉ፤ ይመለሳሉ።
እናም ከምንሳፈርበት አውሮፕላን ጀርባ፤ ይህንና ይህን የመሳሰሉ ታሪኮች አሉ። እዚህ ላይ ለመጥቀስ የተሞከረው እጅግ በጣም ጥቂቱ ጉዳይ ነው። ወደ ውስጥ ገብቶ ጉዳዩን ለሚከታተል ሰው፤ የአየር መንገዳችን ነገር “ውስጡን ለቄስ” የሚያሰኝ ነው። አሁን መለስ የሚል አውሮፕላን ገባ። ነገ ከነገወዲያ ደግሞ በነአዜብ እና ሳሞራ ስም የሚሰየሙ አውሮፕላኖች ሊመጡ እንደማይችሉ ምንም ዋስትና የለም።
ወጋችንን የምናጠናቅቀው ስለኢትዮጵያ መርከቦች ጥቂት ነገር ብለን ነው። ከዚያ በፊት ግን አቶ ግርማ ዋቄ የቀድሞው የአየር መንገዱ ስራ አስኪያጅ የስንብት ንግግር ሲያደርጉ ያሉትን እናጋራቹህ። “እስካሁን በነበረኝ ቆይታ መንግስት ጣልቃ ሳይገባብን፤ ስራችንን በነጻነት እንድንሰራ ስለተደረገ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ወደፊትም አየር መንገዱ ከፖለቲካ እና ከመንግስት ተጽእኖ ውጪ ሆኖ እንዲሰራ እመኛለሁ።” ሲሉ ሰራተኛው ከዳር እስከዳር በጭብጨባ ነበር ያጀባቸው። በመጨረሻም ሰራተኛው ገንዘብ አዋጥቶ የገዛላቸውን አዲስ ኒሳን መኪና እየነዱ ነው አየር መንገዱን ተሰናብተው የወጡት።
አቶ ግርማ ዋቄ በተለይ የሚታወቁት “ቪዥን 2025” በሚል ባወጡት የአየር መንገዱ የረዥም ግዜ እቅድ ነው። አሁን አየር መንገዱ እየተገበረ ያለው የአቶ ግርማ ዋቄን የ15 አመት እቅድ ሲሆን፤ “ልጆቼ ከፖለቲካ ነጻ ሆናቹህ ስሩ” ያሉትን አደራ ግን – እነተወልደ የሚጋሩት አይነት አይመስልምም።
ከላይ እንደገለጽነው… የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት ጉዳይ አንስተን በዚሁ እንለያይ። እንደኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁሉ የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት በተመሳሳይ የዘር ባህር ላይ እየተንሳፈፈ ይገኛል። እንደታወቀው ቀይባህር ለኤርትራ ከተሰጠ ወዲህ “ለኢትዮጵያ መርከብ አያስፈልጋትም” ተብሎ፤ ያሉት በቁማቸው ተሸጡ። አንዳንዶቹም ስማቸውን ለወጡ። እነአባይ፣ ሰላም እና አንድነት የሚባሉት የንግድ መርከቦች አሁን በሌላ ተተክተዋል። አሁን ኢትዮጵያ ካሏት 11 የንግድ መርከቦች መካከል ዘጠኙ የተገዙት በ2013 ላይ ነው። ሁሉም የከተማ ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። ጋምቤላ፣ ባህርዳር፣ ሀዋሳ፣ ሃረር፣ መቐለ፣ ሰመራ፣ ጅጅጋ፣ አሶሳ የሚባሉ መርከቦች አሉን። በኢትዮጵያ እና አፍሪቃ መዲና – አዲስ አበባ ስም የተሰየመ አንድ መርከብ ቢኖር… እሱንም ፊንፊኔ ተብሎ እንዲጠራ ነው የወሰኑት። እንደው አንዳንዱ ድርጊት “መንግስት ነኝ” ከሚል አካል የማይጠበቅ ስለሆነ እንደምሳሌ አነሳነው እንጂ፤ አዲስ አበባ ራሷ ዋስትና ያጣች ከተማ ሆና የለችምን?
እንደው “ኢህአዴግ የተፈጠረው የአዲስ አበባ ልጆችን ለማናደድ ነው” የሚለውን ለማረጋገጥ ካልሆነ በስተቀር፤ ለአዲስ አበባ የመርከብ ስም መንፈግ አስፈላጊ አልነበረም።
ቸር ያሰማን።
Average Rating