በሰሞነኛው የአዲስ አቤ ቀልድ ልጀምር። ወጣቱ፣ ሱሪ ለመግዛት ወጥቶ አንድ የልብስ ሱቅ ወስጥ ገባ። ባለ ሱቁ ጠየቀው። “የቻይና ይሁንልህ ወይንስ የአውሮፓ ሱሪ?” ወጣቱም መለሰ። “የለም የለም… የጎንደሩን ሱሪ ነው የምፈልገው።”
እስረኞችን የማስፈታቱ ሰላማዊ ጥያቄ የእብሪት መልስ ሲያገኝ፤ ጨዋታውም ተቀየረ። “እንዲያውም አናውቅህም። ከህዝብ ጫንቃ ላይ ወረድ” ሲል ነበር የጎንደር ሕዝብ ብረትን ሰብሮ ዙፋኑን የነቀነቀው። “ወንዱን በምርቃና ሴቱን በቃና አደንዝዘን ይዘነዋል!” ያሉት ሕዝብ ከቶውንም እንዳልተዘናጋ አሳየን…. የመናገር እና ሃሳብን ያለፍርሃት የመግለጽ መብትን ህወሃት ሲፈልግ የሚሰጥ ሲያሻው ደግሞ የሚነፍገው የግል ሃብቱ አድርጎ ለ25 አመታት ሰንብቶ ነበር። ይህ መብት በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ አሸብርቆ ጎንደር ላይ ተከበረ። በባህርዳር፣ በደሴ፣ በኦሮምያ፣ በመቀሌ…. ላይም ይቀጥላል..
ከአርባ አመት በፊት የቬትናም ህዝብ ባዕዳን ያነገሱትን አሻንጉሊት መንግ
ስት በሃይል ሲነቀንቀው፤ አሻንጉሊቱ ስርዓት ለሕዝብ እጅ ከመስጠት ውጭ አማራጭ አልነበረውም። የህዝብ ያልነበረው ይህ መንግስት ወደ አመሻሹ ላይ ካመሸገበት የአይጥ ጉድጓድ ሆኖ መግለጫ ሰጠ። እንዲህ ሲል፣
“ስልጣኑን ለህዝብ ለማስረከብ ከንጋት ጀምሮ እየጠበቅኩ ነው።…“
የሰሜኑ ህዝብም ምላሽ የተጠበቀው ነበር፣ “ይህን ለማድረግ ትንሽ ዘገየህ።… የሌለህን ስልጣን እንዴትስ ልታስረክብ ትችላለህ?…“
ይህ ተላላኪ መንግስት ወድቆ የነበረው ከህዝባዊው አመጽ እና እንቢተኝነት በፊት መሆኑን አላስተዋለውም። ስርዓቱ የወደቀ ራሱ ያወጣውን ህግ ራሱ ሲሽረው ነበር። ሕዝብ “መንግስት የለም!” ማለት የጀመረው ለአፋኝ አዋጆች አልንበረከክም ብሎ አደባባይ በወጣ ግዜ ነበር። ይህ መንግስት የተወገደውም ለዜጋው የመብት ጥያቄ የጥይት ምላሽ በሰጠ ግዜ ነው።
“የዘመናችን ትልቁ ክስተት!” ብሎታል የኩባው ፊደል ካስትሮ።
ባለፈው እሁድ በጎንደር የታየው የሕዝብ እንቢተኝነትም የዘመናችን ትልቁ ክስተት ነበር። ሕዝብ የተፈጥሮ መብቱን ተነጥቆ በጫንቃው ላይ ተጭኖ የነበረውን ቀንበር ያስወገደበት ክስተት! ስልጣን የህዝብ እንጂ የጥቂቶች መፈንጫ አለመሆኑ የታየበት ክስተት። በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ወርቃማ አሻራ ጥሎ ያለፈ፤ ለሀገር የፍቅር፣ ለዜጎች የፍትህ እና የህብረት ሃውልትን የተከለ ክስተት። የማይቻል የሚመስለውን ተራራ ደርምሶ የናደ ሃይል ስለነበር ታሪክ ይህንን ሰልፍ ይዘክረዋል።
ግዙፉ የጎንደር ሕዝብ ሰላማዊ ሰልፍ እንደተተናቀቀ፣ የህወሃት መገናኛ ብዙሃን የሆነው ፋና ራዲዮ ሲዘግብ፤
“የጎንደሩ የተቃውሞ ሰልፍ በሰላም ተጠናቀቀ።…” ነበር ያለው። “ጋዜጠኛው” ከምጥ እንደተገላገለች ሴት በረጅም ተነፈሰ። በስፍራው ያልነበረው መገናኛ ብዙሃን በስፍራው የነበረውን ክስተት ሲደሰኩር፣ ለሰላማዊ ሰልፍ ፍቃድ የተከለከለ ህዝብ በራሱ ፈቃድ መውጣቱን፤ በሰልፉም ላይ እነሱ የከለከሉትን ባንዲራ ብቻ መያዙን ጨምሮ አበሰረ።
ይህንን የዜና እወጃ ያዳመጠው የጎንደር ሕዝብ “ይህን ለማድረግ ትንሽ ዘገየህ።… “ ሳይለው አልቀረም። ልክ እንደ አሻንጉሊቱ የቬትናም መንግስት፣ የህወሃት የአፈና ግዜ ማብቃቱን እያረጋገጡት ይመስላል። አንድ ስርዓት መንግስትነቱ የሚያከትመው ራሱ ያወጣውን ህግ ራሱ ሲረግጠው እና ሕዝብም ለሱ አዋጅ ተገዥ አለመሆኑን ሲያሳየው ነው። አላስተዋልነው ይሆናል እንጂ ህወሃት እድሜውን ጨርሶ በባከነ ሰዓት እንደሚንገዳገድ “የልማቱ” ተጠቃሚዎች ሳይቀሩ ነግረውን ነበር። እነ ፃድቃን ገ/ትንሳኤ እና አበበ ተ/ኃይማኖት (ጆቤ) ከማጀታቸው ወጣ ወጣ ብለው አገሪቱ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ፣ መንግስት በሚባለው እና በፓርቲ መሃል እንኳን ልዩነት እንደጠፋባቸው ነግረውናል። ይህ ጉዳይ ጻድቃንን ግራ ካጋባው ሌላው ምን ይበል? ጆቤ የህወሃት ሙስና እና የፍትህ እጦት ካስፈራው ተራው ህዝብ ምን ይሰማው? የሚገርመው ነገር፣ እያየነው ያለው ቀውስ የነ ፃድቃን እና የነ ጆቤ “ሌጋሲ”ም ጭምር መሆኑ ነው።
የጎንደሩ አመጽ ሁለት አበይት ነገሮችን ጥሎልን አልፏል። አንደኛው መተባበር እና መደጋገፍን ማስተማሩ ነው:: አፍንጫ ሲመታ አይን ያለቅሳል እንዲሉ፤ በተለይ የኦሮሞ ወገናችን ደም የሁላችንም ደም ነው ማለታቸው የህወሃትን ከፈፍሎ መግዛት እቅድ የሚያፈርስ መፈክር ነበር። የአኙዋክ መገደል ከአማራው መገደል ተለይቶ አለመታየቱን፣ የሲዳማው ሰቆቃ.. የሁሉም ወገን ስእቆቃ እንደሆነ… የሚያሳይ ትእይንት ነበር። በማን አለብኝነት የሚጫኑ አዋጆችን መስበር መቻሉ ደግሞ ስልጣን ዛሬ በህዝብ እንጂ በአንባገነኖች እጅ አለመሆኑን አሳይቶናል። ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ለመብቱ ፈቃድ እንደማያስፈልገው ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ጥንት አባቶቹ በአደራ ያስረከቡትን ባንዲራ ይዞ በመውጣቱም የስርዓቱን ማክተም አሳይቶናል።
የማይነካ የመሰለው ጉልበቱ ሲፈታ፣ የማይሰበር የመሰለው ሃይል ሲሰበር ይህ የመጀመርያው አይደለም። በዘረፉት ሃብት እና በሰራዊታቸው ጉልበት ብቻ እየተማመኑ የገዛ ወገናቸውን ሲበድሉ የኖሩ አንባገነኖች ከቶውንም መቶ አመት ሲቆዩ አላየንም። በአለማችን የተነሱ ብርቱ የሚባሉ አንባገነኖች በህዝብ ሃይል እየተዋረዱ መውደቃቸውን የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ።
የማያልቅ መንገድ እና የማይነጋ ጨለማ የለም። በአንጻሩ የማይመሽ ቀን የለም። የብዙዎ አንበገነኖች ችግር በጉልበታቸው ብቻ በመተማመን ዙፋናቸውን ዘላለማዊ ለማድረግ ማሰባቸው ነው። በዚህች ተለዋዋጭ አለም ውስጥ ለውጥ የሰው ልጅ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ግደታም ነው። ዘገምታኛም ይሁን ቅጽበታዊ፣ እኛም በተራችን ለውጥን የምናይበት ወቅት ላይ ደርሰናል።
ይህ ሊሆን ግድ ነው። ጽዋ እስኪሞላ የሚጨመርለትን ሁሉ ይሸከም እና ከሞላ በኋላ መፍሰሱ ሳይንሳዊም፤ ተፈጥሯዊም ህግ ነውና ከአቅሙ በላይ ሲሞላ ሁሉም ነገር ይፈስሳል። ከየአቅጣጫው ሕዝቡን ገፍተው እዚህ አደረሱት። እነሆም የሕዝብን የቁጣ ወላፈን ትላንት በኦሮሞ ወንድሞቻችን፣ ዛሬ ደግሞ በጎንደር አዩት። ነገ በደቡብ፣ ከዚያም በምስራቅ እና በምእራብ ይቀጥላል። ይህ ቁጣ የመጀመርያው እንጂ የመጨረሻው አይደለም።
“የዚህን መንግስት ያህል በህዝብ ክፉኛ የተጠላ ስርዓት በህይወት ዘመኔ አይቼም ሆነ ሰምቼ አላየሁም።” ሲሉ አንድ ከፍተኛ የኢህአኤግ ባለስልጣን ሲናገሩ አድምጫለሁ። ከውስጣዊ ሰዎች እንደምንሰማው ከሆነ 90 በመቶ የሚሆኑት የኦህዴድ እና የብአዴን አመራር አባላት ከህወሃት ጋር ሆድና ጀርባ ከሆኑ ሰንበትበት ብለዋል፤ የህዝቡ በደል አንገሽግሿቸው ህዝባዊውን አመጽ ለመቀላቀል በመጠባበቅ ላይም ናቸው። በራሱ በአገዛዙ ውስጥ ያሉ ሁለተኛ ረድፈኞች ሳይቀሩ እንደሚመሰክሩት፤ የህወሃት ወንጀል ደርግ ከሰራው ወንጀል እንኳን ሊወዳደር አይችልም። የበደሉን ብዛት እና የዝርፊያውን ግዙፍነት የሚመሰክሩት ሁሉ ይህ ስርዓት በቅርጽ እንጂ በይዘት እንደሌለ ነው እየመሰከሩ ያሉት። “በአሁን ሰዓት በመንግስት ስም የሚነግድ የማፍያ ቡድን እንጂ መንግስት የለም!” ነው ያለው አንድ ከፍተኛ የብአዴን ሰው።
ሕዝቡ ይህንን ሰርዓት ለምን አይጥላው? ሁሉም ስለታፈነ ሕዝብ ነው የሚናገሩት። አንድ ለአምስት ተጠረንፎ የተያዘ ሕዝብ፣ እስከውስጥ ገመናው በኢህአዲግኛ መስፈርት እየተገመገመ የሚሰቃይ ሕዝብ፣ ሌት ተቀን በሙስና እንደመዥገር እየተበዘበዘ ያለ ሕዝብ። ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል እንኳን ለመጥራት እየተጸየፉ፣ ሀገርን እና ታሪካዊ ባንድራዋን እየጠሉ፣ … እንዴት ሊቆዩ ይችላሉ?
ለችግሮች ሁሉ መፍትሄያቸው ጠመንጃ ነው። የጎንደሩንም ችግር በጠመንጃ ለመፍታት እየመከሩ ይገኛሉ። በመጀመርያ ከህዝቡ መሳርያ መንጠቅ። ከዚያም እንደ በኦሮሞ ወጣቶች እንዳደረግነው በአልሞ ተኳሾች አማጺውን መልቀም ይኖርብናል ሲሉ ዶ/ር ደብረጽዮን መናገራቸው እየተሰማ ነው። ከ500 ያላነሱ የኦሮሞ ወገኖቻችንን ጨርሰው ሲያበቁ፤ እርምጃው ተመጣጣኝ እና ፍትሃዊ ነው ሲሉ ቀለዱብን። ለመሆኑ ከአንድ ሰብዓዊ ፍጡር እንደዚህ አይነት ፍጹም አረመኔያዊ ነገር ይሰማል? የጭካኔ ጣርያው የት ድረስ ነው?…
መገናኛ ብዙሃን ላይ እየወጡ በህዝብ ላይ የሚያላግጡት ነገር ደግሞ እጅግ ያሳምማል። ለጥያቄዎች ሁሉ አንድ መልስ ነው ያላቸው። መልሱም “ሻዕቢያ”
Average Rating