www.maledatimes.com የጎንደር አማራ ሰላማዊ ሰልፍ፣ (አስተያየት) ከዶ/ር ከፍያለው አባተ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የጎንደር አማራ ሰላማዊ ሰልፍ፣ (አስተያየት) ከዶ/ር ከፍያለው አባተ

By   /   August 6, 2016  /   Comments Off on የጎንደር አማራ ሰላማዊ ሰልፍ፣ (አስተያየት) ከዶ/ር ከፍያለው አባተ

    Print       Email
0 0
Read Time:7 Minute, 9 Second

cropped-Maleda-Times-Logo.jpg

 

በቅርቡ የጎንደር አማራ ሕዝብ በጎንደር ከተማ ያካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ (በኔ እይታ) የአማራን ታላቅነት፣ የማያወላውል የኢትዮጵያዊነት ስሜት የሚያረጋግጥ እና በራሱ በአማራ ሕልውና ላይ የተነሳውን (የመኖርና ያለመኖር) ጥያቄ የመለሰ ይመስለኛል።

 

የኢትዮጵያን መንግሥት በበላይነት የሚቆጣጠረው ታሕት፣ 1) ትግራይን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ራሱን የቻለ የትግራይ መንግሥት ለማቋቋም ሲታገል/ሲዋጋ የነበረ በመሆኑ፣ 2) ኤርትራን፣ ኦሮሚያንና ኦጋዴንን እንገነጥላለን ብለው ከተነሱ ገንጣይ ኃይሎች ጋር አብሮ የመጣ በመሆኑ፣ 3) አንድን ሕዝብ (አማራን) ከባሕልና ከልማዱ ጋር አጠፋለሁ ብሎ በተደጋጋሚ በግልጽ በማወጁና ሥልጣን ከጨበጠም በኋላ በተለያየ ምክንያት (በጡረታ፣ በቅነሳ) በማሳበብ አማራውን ከሥራ በማፈናቀሉ፣ 4) እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የደርግን ሥርዐት ጠልቶ ያፈገፈገለትን የኢትዮጵያ ሠራዊት በመበተኑ፣ 5) የኢትዮጵያን ባንዲራ “ጨርቅ ነው” በማለቱና “የአክሱም ሀውልቶች ለከምባታው ምኑ ነው?” በማለቱ፣ 6) በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ይገኙ የነበሩትን ፋብሪካዎች፣ የመብራት ጀኔሬተሮች፣ የትምህርት ቤቶችን ወንበሮችና ጠጴዛዎች፣ የጣራ ቆርቆሮ ክዳኖች እየነቀለ ወደ ትግራይ በማጓዙ፣ 7) የመንግሥት ሥልጣን እንደጨበጠ ኤርትራን በማስገንጠሉና ኢትዮጵያን ያለ ባሕር በር በማስቀረቱ፣ 8) በዘርና በቋንቋ ላይ የተመሠረቱ (በልዩነት ላይ ያተኮሩ)፣ ኢትዮጵያዊያንን የሚያራርቁና የሚያለያዩ ፌዴራላዊ ያስተዳደር ክልሎች በመፍጠሩ፣ ከዚያም ጋር አያይዞ በዘርና በቋንቋ ላይ የተመረኮዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲፈለፈሉ በማድረጉ፣ 9) “በጦርነት ለተጐዱ አካባቢዎች ቅድሚያ እንሰጣለን” በሚል ሽፋን ለትግራይ ልማትና ማሕበራዊ አገልግሎቶች የተለየ ትኩረት በመስጠቱ፣ 10) የመንግሥት ቢሮዎችን፣ የሠራዊት አዛዦችን፣ የስለላ ሰራተኞችንና ጸጥታ አስከባሪዎችን ከትግሬዎች መካከል እየመለመለ በመመደቡ፣ 11) በንግዱና በተለያዩ የኢኮኖሚው ዘርፎች ባመዛኙ ትግሬዎች ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ በማድረጉና በመሳሰሉት አድላዊ አሠራሩ የተነሳ ኢትዮጵያዊነቱ ጥያቄ ውስጥ የገባ፣ “የኢትዮጵያን መሬት ቆርሶ ለሱዳን ሰጥቷል” ተብሎ እስከ መወገዝ የደረሰ በትግሬ ሕዝብ ስም የሚነግድ ፓርቲ ነው።

 

ታዲያ ይህ የኢትዮጵያን መንግሥት በበላይነት የተቆጣጠረ ፓርቲ ኢትዮጵያዊነቱን ጥያቄ ላይ በጣለበት ወቅት፣ “ቅስሙን እሰብረዋለሁ”፣ “አንገቱን አስደፋዋለሁ” በማለት የዘመተበት የአማራ ሕዝብ ሰሞኑን ጎንደር ላይ ባካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ (ባነገባቸው መፈክሮች አማካይነት) ታላቅነቱንና ትክክለኛ ኢትዮጵያዊነቱን በግልጽ አሳየ። ቅስሙ እማይሰበር፣ አንገቱ የማይደፋ ጥኑ/ብርቱ ሕዝብ መሆኑን አረጋገጠ።

 

የጎንደር አማራ ሕዝብ የኦሮሞው ሕዝብ በደል በደሉ መሆኑን በመግለጽ የኢትዮጵያዊነት ስሜቱን በግልጽ አስመሰከረ። አማራን፣ ባህልና ልማዱንም ጭምር በማርከስ/በማጣጣል፣ የአማራው ሕዝብ የድሮው ስርዓቶች ልዩ ተጠቃሚ እንደነበረ በማስመሰል፣ በኦሮሞው ሕዝብ ውስጥ የጥላቻ መርዝ ሲነዙ የቆዩትን (የአንዳንድ ኦሮሞ) ፖለቲከኞች እኩይ ተግባር በመናቅ፣ የኦሮሞው ሕዝብ በደል በደላችን ነው፣ ሞቱ ሞታችን ነው፣ ስቃዩ ስቃያችን ነው በማለት፣ የጎንደር አማራ ሕዝብ ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ያለውን ፍቅርና ተቆርቋሪነት በመግለጽ (ትምክህተኝነቱን ሳይሆን) ታላቅነቱን አስመሰከረ። ይህን የመሰለው ፍቅርና መተሳሰብ ነው የሀገራችን ብሔረሰቦች አንድነት የሚያጠነክረው።

 

የጎንደር አማራ “ቅማንትና አማራ አንድ ነን” ብሎ በመጮኽ አብሮ መኖርንና አንድነትን የሚወድ፣ ከጠባብነትና ከጐጠኝነት የነፃ ሕዝብ መሆኑን አሳየ።

 

የጐንደር አማራ ከየትኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ይልቅ ከትግሬው ሕዝብ ጋር  (ተጋብቶ፣ ተዋልዶ፣ ተዛምዶ) ለረዥም ጊዜ ተከባብሮ ኑሯል። በኩታ ገጠምነቱም በመልካም ጉርብትና ለዘመናት አብሮ የኖረ ነው። ለወልቃይትና ጠገዴ አማራ ሕዝብም ትግሬዎች አዲስ/እንግዶች አይደሉም። አዲስና እንግዳ ያስመሰላቸው የዚህ መንግሥት ቀንደኛ መሪዎች ኢትዮጵያዊነት አጠያያቂ መሆኑ ነው ብቻ ነው።

 

ሥልጣን ጨምድደው የያዙት ቀንደኛ የሀገራችን መሪዎች ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ ባንድ ዓይን የማያዩ አድላዊ ወገንተኞች ናቸው። የነዚህ ቀንደኛ መሪዎች ኢትዮጵያዊነት (ስሜት) አጠያያቂ መሆኑ እስከሚወገድ ድረስ የወልቃይትና ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ሊወገድም ሊቀዘቅዝም አይችልም። እንዲያውም ይኸው አሁን እንደምናየው እየተጋጋለና እየተስፋፋ ይሄዳል። እነዚህ ሥልጣን የጨበጡ ቡድኖች ለወልቃይትና-ጠገዴ ጥያቄ ባስቸኳይ መልስ ካልሰጡ፣ የጎንደር አማራ እንኳን እትብቱ ለተቀበረበት ለወልቃይት-ጠገዴ ቀርቶ ለባድመ ሙቷል። እስካሁንም ሙቷል፣ ወደፊትም እየሞተ ትግሉን ይቀጥላል።

 

የጐንደር አማራና ትግሬ በጋብቻም በጉርብትናም በኢኮኖሚም በጣም የተቆራኘ ስለሆነ እርስ በርሱ ሲደጋገፍ ኑሯል። ወደፊትም ሊደጋገፍና ሊተዛዘን ይገባል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ድሆች ብንሆንም ኩርማን እንጀራ ተካፍለን፣ ቡና ተጠራርተን በፍቅር ስንኖር ያምርብናል። ይህንን ተከባብሮና ተሳስቦ መኖር ደግሞ ከማንም የበለጠ ትግሬውና የጎንደሩ አማራ ሕዝብ ያውቅበታል። እንደገና ልድገመውና የወልቃይትንና የጠገዴን ጥያቄ ያስነሳው በመሬቱ ትግሬዎች ተጠቃሚ መሆናቸው አለመሆኑን ሰፋሪዎቹ ትግሬዎች ራሳቸው ያውቁታል። ጥያቄው (አማራ፣ ትግሬ፣ ማንትሴ … ብላችሁ ከከፋፈላችሁን በኋላ) ያማራውን ክልል መሬት (ሌላ ኅቡእ እቅድ ወደ አቀዳችሁለት) ወደ ትግራይ ክልል አሳልፈን አንሰጥም ነው። ስለዚህ ጥያቄው ጐጠኛ በሆነው በታሕት ላይ እምነት የማጣት ጥያቄ እንጂ በወልቃይትና ጠገዴ ውስጥ ሰፍረው ተጠቃሚ የሆኑትን ትግሬዎች በመመቅኘት የተነሳ ጥያቄ አይደለም።

 

አልፎ አልፎ ባንዳንድ ጽሐፊዎች እንደሚገለጸው አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ የዚህ ጐጠኛ ፓርቲ ሰለባ እንጂ ተጠቃሚ አይደለም። ይህ እውነት ከሆነ የትግራይ ሕዝብ እንዳማራው፣ እንደ ኦሮሞው፣ እንደ ጎፋው፣ እንደ ጋምቤላውና እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የደረሰበትን በደል እየዘረዘረ በይፋ በማውጣት ተቃውሞውን ሲያሰማ መታየት አለበት።

 

የትግራይ ሕዝብ የዚህ መንግሥት ተጠቃሚ ከሆነ ደግሞ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተለይቶ የሚያገኘው ጥቅም ዘለቄታ ሊኖረው አይችልም። በትምህርቱ መስክ ለትግሬዎች ብቻ የሚሰጥ አድልዎ ካለ ወደፊት (ሥራም ሆነ ሹመት የሚሰጠው በችሎታ ቢሆን) የተሻለ ምሁር ሁኖ የሚወጣውና ለሥራና ለሥልጣን ዝግጁ የሚሆነው ትግሬው ብቻ ሊሆን ይችላል። ይህ ግን ለምን ያህል ጊዜ ያዋጣል? የትምህርት መስኩ ያለ አድልዎ በእኩልነት ለሀገሪቱ ዜጐች ሁሉ ካልተዳረሰ/ካልተሰራጨ፣ “ሥራና ሥልጣን በችሎታ ይሁን” ቢባል ተቀባይነት እንደማይኖረው መታወቅ አለበት።

 

ኢንዱስትሪዎች መንገዶች ትግራይ ውስጥ ቢስፋፉ፣ ጥሬ እቃው የሚገኝባቸው ሌሎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በመገናኛ በመንገድና በትራንስፖርት አብረው ካልለሙና ካልዳበሩ፣ ትግራይ ብቻዋን ልታድግና ልትበለጽግ አትችልም። ትግሬዎችም ብቻቸውን ባለጸጋ ሁነው በሀገራቸው (በትግራይ) ውስጥ በደስታ ሊኖሩ አይችሉም። ከሌላው ኢትዮጵያዊ መንጋጋ ተወስዶ የሚገኘውን ጥቅም ደግሞ የትግራይ ሰፊ ሕዝብ በንጹሕ ሕሊና ይቀበለዋል የሚል እምነት የለኝም። ያላግባብ (እኩይ በሆነ ተግባር) በብቸኝነት መበልጸግ የሚያስከትለው ጦስ ምን እንደሚመስል ሰሞኑን ጎንደር ላይ የተቃጠለው አውቶቡስ ጠቋሚ ሊሆን የሚችል ይመስለኛል።

 

ይህን የመሰለውን (ከስግብግብነትና ከዝርፊያ የሚመነጭ) ብልጽግና የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገውና የሚመኘው አይመስለኝም። ሌላው ቢቀር ኢትዮጵያዊው ሁሉ ኢፍትሕአዊ በሆነ መንገድ ብቻዋን ወደ አደገቺው ‘ወደ ለሚቱና ወደ ባለጸጋይቱ’ ትግራይ እየተሰደደ እንደሚያጨናንቃት መገንዘብ ያሻል። ከዚህ ደረጃ ግን የሚደረስ አይመስለኝም። ምክንያቱም (የወደፊቷ ኢትዮጵያ እጣ-ፈንታ ምን እንደሚመስል ባላውቅም) የሕዝቡ ትዕግሥት ተሟጦ ያለቀበትና የለውጥ ጭላንጭል የሚታይበት ወቅት ላይ ያለን ይመስለኛል።

 

በውጭ ሀገር ተደራጅታችሁ የምትገኙ ትግሬ ኢትዮጵያዊያንም ሰሞኑን ጎንደር ላይ በተከሰተው የሰው ሕይዎት መጥፋትና የአውቶቡስ መቃጠል ሳቢያ በስሜት ተነሳስታችሁ፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በሀገር ውጪ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ሁሉ (በእስራኤል የሚገኘው ቤተ እስራኤል ሳይቀር) የደገፈውንና ያደነቀውን የጎንደሩን አማራ (ሕዝብ) እንቅስቃሴ በመቃወም የትግራይ ሕዝብ በተቃራኒው እርምጃ እንዲወስድ ብትቀሰቅሱ፣ የትግራይን ሕዝብ ብቸኛ ታደርጉታላችሁ። ሳይገነጠል ትገነጥሉታላችሁ። “ያላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል” እንዲሉ፣ ይህ አላዋቂ አገዛዝ ለትግራይና ለትግሬዎች በማድላት ትግሬዎችን በሌሎች ኢትዮጵያውያን ጥርስ ውስጥ ያስገባቸው አንሶ፣ እናንተ ደግሞ አጋር ሁናችሁ የኢትዮጵያዊያን ክፉ ዓይን በትግሬ ዎገኖቻችን ላይ እንዲያተኩር እንዳታደርጉ አስተያየቴን በትህትና ማቅረብ እወዳለሁ። ቀደም ብየ እንደ ገለጽኩት እሚያምርብን (በድህነትም ቢሆን) ያለቺንን እኩል ተካፍለን፣ አንተ ትብስ፣ አንተ ትብስ ተባብለን በሕብረት ስንኖር ነው።

 

የጎንደሩ አማራ (ሕዝብ) ሰላማዊ ሰልፍ ሌላ ነገርም አስይቶናል። አማራ የሚባል “ነገር” መኖሩን።

 

በገዛ ሀገሩ (የመንግሥት) መሪዎች አንደበት “አማራን ከነባህሉና ልማዱ እናጠፋዋለን፣ አንገቱን እናስደፋዋለን፣ ቅስሙን እንሰብረዋለን” ተብሎ በይፋ በተዛተበትና፣ ጥላቻው በሰፊው ተሰራጭቶ አማራው በያለበት በተስኪያን እንደገባች ውሻ በያቅጣጫው በሚዋከብበት ቀውጢ ጊዜ፣ ሀገሪቱን በዘርና በቋንቋ ከፋፍለው፣ ዘርና ጐሳን ሽፋን አድርገው በመንግሥት ከፍተኛ ስልጣን ላይ የተቀመጡት ባለጊዜዎች፣ ይህንን “ትዕቢተኛና ትምክህተኛ ሕዝብ ድምጹንና አንደበቱን እንዘጋዋለን ብለው፣ ያለ የሌለ ዘመቻ በሚያካሂዱበት ወቅት፣ “የአማራ ሕዝብ የሚባል ‘ነገር’ መኖሩን” አማራው ሰሞኑን ጎንደር ላይ ባደረገው ሰላማዊ (በወልቃይትና ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ላይ) የተቃውሞ ሰልፍ አረጋገጠ።

 

በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር ደረጃ ትልቅ ተደማጭነት ያላቸው፣ አንጋፋው ምሁር (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም) “አማራ እሚባል ነገር የለም” ያሉት ሕዝብ መኖሩን ጎንደር ላይ ሰሞኑን ባካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ አስመሰከረ።

 

የአማራ አለመኖር የኢትዮጵያን አንድነት እሚያስጠብቅና እሚያስከብር ይመስል፣ “ለኔ አማራ የሚባል ነገር አለመኖሩ ይሻለኛል”፣ “አማራን እወክላለሁ ብሎ የሚናገርም ካለ እርሱ እብድ መሆን አለበት”፣ (ቆየት ብለውም በተደጋጋሚ ከተለያዩ ግለሰቦች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ) “አማራ እሚባል ነገር የለም፣ ቢኖር ኖሮ እኮ እስካሁን አንድ ነገር ሲሆን እናይ ነበር፣ ግን አላየንም።” ብለው ነበር። አሁን በአማራው ስም ጎንደር ላይ አንድ ነገር ሲሆን ታየ። ግፍና በደል ቀስቅሶ አማራውን አወጣው።

 

አማራ ማለት ክርስቲያን ማለት ነው ተብሎም ነበር። ሰሞኑን ጐንደር ላይ “ወልቃይትና ጠገዴ የአማራ ነው፡ ሕዝቡም አማራ ነው” ብለው ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉት (የጎንደር) አማሮች ግን ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ እስላሞችም ጭምር ናቸው። የሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊ የሆነው ሕዝብ የትውልድ ሐረግ ቢመዘዝ (በተለያየ የታሪክ አጋጣሚ) ከትግሬው፣ ከቅማንቱ፣ ከአገው፣ ከፈላሻው፣ ከኦሮሞው፣ ከጉራጌው፣ ከሀዲያው፣ ከአፋሩና ከኢሳው፣ ወ.ዘ.ተ. ጋር የተዳቀለና የተዛመደ ሁኖ እንደሚገኝ መገመት አያዳግትም። ግን ኩታ-ገጠም በሆነ አካባቢ እየኖረ፣ አማርኛ ቋንቋ እየተናገረ፣ ተድላና መከራውን ባንድ እየተካፈለ፣ የተፈጥሮንም ሆነ ሰው-ሰራሽ ችግር አብሮ እየተቋቋመ፣ በምግቡም በመጠጡም፣ በስራ መሳሪያውም ጭምር ተመሳሳይ ይትብሃል ይዞ የኖረው (አንድነት ያለው እማይመስለው) አማራ የጋራ ግፍና በደል አጣምሮት፣ “አማራ ነን” ብሎ ብቅ አለ።

 

እንደሚመስለኝ አንጋፋውን ምሁር “አማራ የሚባል ነገር የለም” ያሰኛቸው፣ ከተለያዩ የጐሳ አባላት ጋር የተዋለደ በመሆኑ፣ እርስ በርሱ ተፈላልጐ እማይሰባሰብና እማይረዳዳ በመሆኑ ሊሆን ይችላል። አሁን ግን በያለበት መገለሉ፣ አድልኦውና ጥቃቱ ሲበዛበት፣ እርስ በርሱ ወደ መፈላለግና ወደ መሰባሰቡ ያዘነበለ ይመስላል። አንድነቱን (cohesive) ቀስ በቀስ ወደማጠናከሩ ያዘመመ ይመስላል። ይህም ማለት ወደ ጠባብ (የጐሳ) አስተሳሰብ አቅጣጫ እንዲያዘነብል የተገደደ ይመስላል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ለሀገራችን አንድነት እማይበጅ እሚያሳዝን አቅጣጫ ነው። የሀገራቸው ሥርዐት (ለዘመናት) የረሳቸውና በደል የጸናባቸው ሕብረተሰቦች በራሳቸው ፈቃድ አዲስ የአይሁዳዊነት ማንነት (Jewish identity) እስከ መያዝ የደረሱና ባንድ አካባቢ ተሰባስበው መኖር የጀመሩ በርካታ ጥቁር አፍሪካውያን አሉ። ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቶቹን ብቻ ለመጥቀስ ያህል፣

  • The Zakhor and Gombou Jews of Timbuktu, Mali
  • The Sefwi community in Ghana
  • The Igbo of Nigeria
  • The Tutsi Hebrews of Havilah
  • The Abayudaya of Uganda
  • The Lemba of South Africa and Zimbabwe

 

ኢትዮጵያዊው አማራም ተበታትኖ ከሚኖርባቸው የተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በተለያየ ምክንያት ተበሳጭቶ/ተማ(ር)ሮ እየለቀቀ ወደ ሰሜን ሸዋ፣ ወደ ምእራብ ወሎ፣ ወደ ጎንደርና ወደ ጐጃም እንዲሰፍርና በጊዜ ብዛት ጠባብ የጐሳ ስሜትን እንዲያዳብር የተፈለገ ይመስላል። ይህም የኢትዮጵያዊያንን አንድነት የማዳከም አንደኛው እርምጃ ነው። ይህ እንዳይሆን የኢትዮጵያዊያንን አብሮ መኖር የሚሹ ዜጐች ሁሉ በንቃት ሊከታተሉትና ሊያወግዙት ይገባል።

 

ለማጠቃለል ያህል፣ ይህ መንግሥት በእብሪት የሕዝብን ድምጽ አፍኖ ለሕዝቡ ብሶትና ሰቆቃ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ የሚቀጥል ከሆነ፣ የሕዝቡ ተቃውሞና አመጽ እንደ ሰደድ እሳት ባጭር ጊዜ በመላ ሀገሪቱ መቀጣጠሉ እንደማይቀር እሙን ነው። ሥልጣን ያደነዝዛል መሰል እንጂ፣ ይህን የሕዝብ አመጽ ጉዳይ ከኔ ይልቅ ስልጣንን የሙጥኝ ብለው የያዙት የበለጠ ያውቁታል። ማር እንኳን “ሲበዛ ይገለማል” ይባላል።

 

 

 

 

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 8 years ago on August 6, 2016
  • By:
  • Last Modified: August 6, 2016 @ 7:37 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar