ከብራስልስ፣ ቤልጂየም
ነሐሴ 06፣ 2016 እ.አ.አ
ኢትዮጵያ ዛሬ መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች፡፡ የወያኔ ግትርነትና መረን የለቀቀ አንባገነናዊነት፣ በሥርዓቱ ተስፋ የቆረጠና የተበሳጨ ሰፊ ሕዝብ፣ ለ25 ዓመታት የተጎነጎነ የጎሣ ፖለቲካና ጥላቻ፣ መገለጫ የሌለው ድህነትና ችጋር አገሪቱን ሰንገው ይዘዋታል፡፡ በአገዛዝ ሥርዓቱ በኩል የሚታየው ሕዝብን የመናቅና ከሕግ በላይ የመሆን ዝንባሌ እየከፋ መምጣቱ በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች አንድም ልባቸው መደፈኑን አለያም ጥልቅ ድንቁርና የተጫጫናቸው መሆኑን ወይም መካር ማጣታቸውን ነው የሚያመላክተው፡፡ ሥርዓቱ የአፈና መዋቅሩን ዕለት ከዕለት እያሰፋና እያጠነከረ በአፈ ሙዝ ብቻ ሳይሆን በሙስና በተግበሰበሰ የሕዝብ ሃብትም ያፈረጠመውን ጡንቻውን መጠቀሙ ከተራ ጨቋኝነት ወደ ከበርቴ አንባገነንነት ከፍ አድርጎታል፡፡ የዛሬ ሃያ መት የነበረው ወያኔ ከዛሬው ወያኔ የተለየ ነው፡፡ የቀድሞው ወያኔ ጠመንጃና የፖለቲካ መዘውሩን ቢይዝም አንባገነን ብቻ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ያለው ወያኔ ከጠመንጃና ከፖለቲካ ስልጣን በተጨማሪ የአገሪቱን ሃብት ጠቅሎ የያዘ ከበርቴ አንባገነን ሆኗል፡፡ ‘ልማታዊ ዝርፊያ’ ውስጥ የገቡት የሥርዓቱ ባለሥልጣናት ከተራ ደሞዝተኝነት ተነስተው የብዙ ሚሊዮኖች ሃብት ባለቤት ሆነዋል፡፡ በጡረታ የተገለሉት ጀ/ር ጻድቃን ወልደተንሳይን ጨምሮ በርካታ የወያኔ የጦር ጀነራሎች እንኳ የትላልቅ ኩባንያዎችና በብዙ ሚሊዮኖች ገንዘብ የሚገመቱ ሕንጻዎች ባለቤት ሆነዋል፡፡ ስለዚህም ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ ባለሃብቶችም ስለሆኑ የሞት ሽረት ትግሉ ለፖለቲካ ሥልጣን ብቻ ሳይሆን በዘረፋ ያፈሩትን ሃብት ዋስትና ማስጠበቅንም ይጨምራል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝብ የወያኔ ሥርዓት አገሪቱን ይዞ ከገባበት ቅርቃር ውስጥ እንዲወጣና ወደ ተሻለ ጎዳና እንዲያመራ ሆደ ሰፊ ሆኖ፤ የስቃይ እንቆቆውን እየተጋተና ግፍና መከራውን ሁሉ እንዳላየና እንዳልሰማ ሆኖ ለ25 ዓመታት ሲጠብቅ ቆይቶ ተስፋው የተሟጠጠበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአንባገነናዊ ሥርዓት እንግዳ ባይሆነም እንዲህ አይነት ፈተና ግን ገጥሞት የሚያቅ አይመስለኝም፡፡ ወያኔም ሆነ ደርግ አፋኝና ግፈኛ ስርዓቶች ቢሆኑም ደርግ እያበላ፣ ለድሃው መጠለያ እየሰጠ፣ ሁሉንም የአገሪቱን ክፍል ወጥ በሆነ የአፈና መዋቅር ሲጨፈልቅ፤ ወያኔ ደግሞ ሕዝብን በኑሮ ውድነት እያመሰ፣ እያስራበና ለዘመናት ከኖረበት ቀየውም እያፈናቀለ፣ ከአገር እያሰደደና በዘር ፖለቲካ ሃገሪቱንና ሕዝቡን ከፋፍሎ እያመሰ ተጠቃሚና ተገላይ መደብ የፈጠረ ጨፍላቂ ሃይል ነው፡፡ በመሆኑም በደርግ የተንገሸገሸ ሕዝብ ለወያኔ የ25 ዓመት እድሜ መስጠቱ ቢያስገርምም ዘግይቶም ቢሆን ተቆጥቶ መነሳቱ ግን ‘ከቀረ የዘገየ ይሻላል’ እንደሚባለው ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
ወያኔ ለለውጥ ያልተዘጋጀና እያደር ጥሬ የሆነ ድርጅት መሆኑን በዚህ አንድ አመት ውስጥ በኦሮሚያና በወልቃይት የታዩት ችግሮች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በእርግጥ ከስህተት ለመማርና የጎበጠውንም ለማቅናት የሁለት መሰረታዊ ነገሮች መሟላት ግድ ይላል፡፡ አንዱ መሳሳትንና መስመር መሳትን ማወቁ ላይ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከስህተት ለመማር ድፍረት ወይም ጨዋ መሆንን ይጠይቃል፡፡ የወያኔ ሹማምንት ሥርዓቱ አቅጣጫውን መሳቱን በየጊዜው ሲነግሩን ቆይተዋል፤ በአደባባይ እየወጡ በሙስና ውስጣችን በስብሷል፣ የመልካም አስተዳደር እጦት አለብን፣ ነቅዘናል ወዘተ … ይሁንና ከገቡበት ቅርቃር ለመውጣት አንዳችም ምልክት አለማሳየታቸውና እያደርም የአፈና መዋቅሩን እያጠበቁ ሙሉ ለሙሉ ወደለየለት አፋኝና አንባገነናዊ ሥርዓት መቀየራቸው ለመታረም አለመፈለጋቸውን ነው የሚያሳየው፡፡ ሕዝብ በሥርዓቱ ላይ የነበረችውን ጭላንጭል ተስፋ አሟጧታል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔንና ልበ ድፍን የሆኑትን ሹማምንት የሚያስታምምበት ትዕግስትና ብልሃቱ ተሟጧል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋነትና ሆደ ሰፊነት የአገዛዝ ሥርዓቱን ቆም ብሎ እንዲያስብና እራሱንም እንዲያርቅ አልረዳውም፡፡
በመሆኑም መረን የለቀቀውን የወያኔን የግፍ ተግባር መቋቋም ያቃተው ሕዝብ ድርጅትና መሪ ሳይፈልግ ብሶቱ ፈንቅሎት ወደ አደባባይ መውጣት ጀምሯል፡፡ ከእንግዲህ የሚመልሰው ነገር ያለም አይመስለኝም፡፡ በተለይም የአሁኑን የሕዝብ ንቅናቄ የተለየ የሚያደርገው አመጾቹን በኃላፊነት የሚመራ አንድም የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ሌላ ድርጅት ያለመኖሩ ነው፡፡ ሕዝብ መሪዎቹን ሲነጠቅና በነሱም ላይ ተስፋ ሲቆርጥ፤ እንዲሁም መብቱን ለማስከበር የመደራጀት መብቱን ሲነፈግ ወደ ‘መሪ አልባ አመፅ ወይም ንቅናቄ’ (leaderless resistance) የሚሸጋገር መሆኑን በተግባር እያሳየ ነው፡፡ ማንም ሳይጠራውና የአገዛዙንም ፍቃድ ሳይጠይቅ በመንደር የጎበዝ አለቆች እየተመራ አደባባይ ወጥቷል፡፡ ይህ መሪ አልባ ሕዝባዊ ንቅናቄ ወዴት ያመራል? የሚለውን መገመት ቢያስቸግርም ወያኔን አጣቢቂኝ ውስጥ ሊከት እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ለ25 ዓመታት የተዘራው የዘር ፖለቲካና በአገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋው አስከፊ ድህነት በእንዲህ አይነቱ አመጽና ቁጣ ላይ ሲታከል ግን የሕዝቡ ቁጣ አቅጣጫውን ሊስት ይችላል፡፡ ያንጃበበው አደጋ ሥርዓት ከመለወጥ አልፎ የአገርና የዜጎችን ደህንነትም የከፋ አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል፡፡ ‘ግርግር ለሌባ ይመቻል’ እንደሚባለው ይህን አጋጣሚ የሚጠብቁ እኩይ ኃይሎች ስለሚኖሩ ለወያኔ፣ ለተደራጁ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች እና ለሕዝብ ያለኝን ጥሪና መልክት እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
- የወያኔ ባለሥልጣናት ሆይ ቢዘገይም እንኳን ልብ ልትገዙ ይገባል፡፡ የህዝብን ቁጣ ጥቂቶች የፈጠሩት ሁከት ነው እያሉ በሕዝብ ላይ መሳለቃችሁን አቁሙና ከማናቸውም የኃይል እርምጃ በመታቀብ ሕዝብ የሚላችሁን ብታደምጡ ይበጃል፡፡ በቃችሁኝም ካለ የ25 አመቱን የገዢና ተገዢ ፍጥምጥም ያለ ደም መፋሰስ የሚያበቃበትን መንገድ ማሰላሰያው ጊዜያችሁ አሁን ነው፡፡ ለዚህም ያለው ጊዜ አጭር ይመስለኛል፡፡ ከረፈደ ይሄንንም እድል የምታገኙት ስለመሆኑ እጅግ እጠራጠራለሁ፡፡ ‘ሲስሙዋት ቀርቶ ሲስቧት’ እንዳይሆንና አገሪቱም ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ከማምራቷ በፊት ለሕዝብ ጥያቄ ልትረቱ ይገባል፡፡
- በየሥፍራው የሚነሱ ‘መሪ አልባ ሕዝባዊ አመጾች’ አንዱ ክፍተታቸው መቀናጀትና አንድ አይነት አገራዊ ራዕይ ወዳለው አቅጣጫ ለማምራት አለመቻላቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሁሉም ኢላማ ያደረጉትን አፋኝ ሥርዓት ሊያንበረክክ፤ አልፎም ሊያስወግድ ቢችልም አገርን የመበታተን አደጋም አብሮ ይዞ ይመጣል፡፡ በመሆኑም የተደራጁ የፖለቲካ ኃይሎች ከዋጧችው ድርጅታዊ ጉዳዮች በመውጣት በአገር ላይ ያንጃበበውን አደጋ ለማስቆምና የሕዝቡንም ቁጣና አመጽ አግጣጫውን ስቶ ወደ ለየለት እልቂት እንዳያመራ ምክክርና ዝግጅት ልታደርጉ ይገባል፡፡ ለእዚህም ያለው ጊዜ አጭር ነው፡፡ የፖለቲካ ኃይሎች እኔ ልቅደም እኔ ልቅደም ከሚለው የተለመደ ቧልትና መጠላለፍ ወጥተው ይህ ሕዝብ የጀመረውን ትግል በግንባር ቀደምትነት ሊቀላቀሉት ይገባል፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ልዩነቶቻቸው እንደተጠበቆ ሆኖ አገርና ሕዝብን ከጥፋት የማዳን የቀውጢ ጊዜ መርሃ ግብር ሳይውሉ ሳያድሩ ሊነድፉ ይገባል፡፡ ላለፉት በርካታ አመታት ጥቂት የፖለቲካ ኃይሎች፣ የሲቪክና የሙያ ማህበራት፤ እንዲሁም ጋዜጠኞችና ምሁራን ሊያነቁትና ሊቆሰቁሱቱ ሲጥሩ በትዝብት ይመለከት የነበረው ሕዝብ ዛሬ ያለ ማንም መሪነት ብሶት ፈንቅሎት አደባባይ መውጣቱ ሕዝብ የሚቆጣበትና ቁጣውን የሚገልጽበት የራሱ ጊዜና ቀመር እንዳለው ነው የሚያሳየው፡፡ ስለዚህ ፓርቲዎች የራሳቸውን ጥያቄ ወደጎን አስቀምጠው በሕዝብ ጥያቄ ላይ ያተኮረ የትግል አቅጣጫ ሊይዙ የሚችሉበት ወቅት አሁን ነው፡፡
- የተከበርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፤ እቢኝ ለአንባገነኖች፣ እቢኝ ለዘረኞችና ለከፋፋዮች፣ እቢኝ ለሙሰኞች፣ እምቢኝ ለድህነት፣ እምቢኝ ለስቃይና እርዛት፣ እምቢኝ ለስደት፣ እምቢኝ ተዋርዶ መኖር፣ እምቢኝ ለነጻነቴ ብለህ የጀመርከውን የእንቢተኝነት እንቅስቃሴ ሁሉንም ሕዝብ አሰባሳቢ በሆነው በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር እንዲቀጥል የትግልህን አቅጣጫ ከወዲሁ አስምር፡፡ ለአመጽ በወጣህበት ሥፍራ ሁሉ ከጎንህ ያለውን ኢትዮጵያዊ ዘርና ኃይማኖቱን ሳትጠይቅ እጅ ለእጅ ተያይዘህ በአብሮነት ቁም፡፡ የአገርህና የሙሉ ነፃነትህ ባለቤት እስክትሆን ድረስ ትኩረትህ በዘር ወይም በፖለቲካ ምልከታ በተለየህ ወገንህ ላይ ሳይሆን የአገዛዝ ሥርዓቱ ላይ ብቻ ይሁን፡፡ ይህ አይነቱ የሰከነ አካሄድ የትግል ጉዞህን ጠባብ አጀንዳ ባላቸው ቡድኖች ወይም በወያኔ እንዳይደናቀፍና ካለምከው ሳትደርስ ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዳታመራ ኃይልና ብርታት ይሆንሃል፡፡ ትግልህ ከስሜትና ከበቀል ወጥቶ ኢትዮጵያን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከወያኔ አፈና እና ወያኔንም ከመሰሉ ሌሎች ኃይሎች ነፃ እንድትወጣ፤ አንባገነናዊ ሥርዓትም ታሪክ ሆኖ እንዲያልፍ የሚያደርግ ሊሆን ይገባል፡፡ በአመጽ የግፍ ሥርዓት ይወገዳል፤ ስክነት ሲታከልበት ደግሞ ግፈኛን በሌላ ግፈኛ፣ ዘረኛን በሌላ ዘረኛ፣ ሙሰኛን በሌላ ሙሰኛ፣ አፋኝን በሌላ አፋኝ ከሚተካበት የዘመናት አዙሪት ያወጣሃል፡፡ ሁሉም ታሪክ ሆነው የሚቀሩበት ለውጥ ይመጣል፡፡ ኢትዮጵያም የጥቂቶች ሳትሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ አገር ትሆናለች፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገሩና የነፃነቱ ባለቤት የሚሆንበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም!
የሕዝብ ድምጽ ይሰማ!
ያሬድ ኃይለማሪያም
Average Rating