www.maledatimes.com ለሁሉም ጊዜ አለው ማስተዋል በለጠ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ለሁሉም ጊዜ አለው                                                                              ማስተዋል በለጠ

By   /   August 26, 2016  /   Comments Off on ለሁሉም ጊዜ አለው                                                                              ማስተዋል በለጠ

    Print       Email
0 0
Read Time:11 Minute, 10 Second

                          

በመላዋ ሀገራችን ለነፃነታችን እየተዋደቁ የሚገኙ ዜጎች ውድ ሕይወታቸውን እየሰው የነፃነት ቀንዲሉን በማብራት ላይ ናቸው፡፡ ታሪክ ሲዘክረው የሚኖር ታላቅ መስዋዕትነት እየከፈሉ በመሆናቸው በአልሞ ተኳሽ የወያኔ አጋዚ ጦር አንገታቸው እየታረደና ጭንቅላታቸው እየተገመሰ ሕይወታቸውን የሚያጡ ውድ ወገኖቻችንን ነፍሳቸውን ፈጣሪ ይማርልን፡፡

በዚያን ሰሞን ካነበብኳቸው መጣጥፎች አንዱ በ16 የትግራይ ተወላጆች የተጻፈው በወያኔ ላይ የተወሰደ አቋም ነው፡፡ ኪዳነ ምሕረት ትባርካቸው፡፡ ፕሮፌስር መስፍን አንድ ወቅት ጥሩ ኢትዮጵያውያን ተጋሩን መቁጠር ጀምረው የቀኝ እጅ ጣቶቻቸውን ተጠቅመው (ይመስለኛል) አንድ ሁለት ሦስት ያህል እንደተጓዙ አምስትን እንኳን መዝለል አቃታቸውና “አሥር ቢሞሉልኝ ደስ ባለኝ” ብለው መቁጠሩን ትተውታል፡፡ አሁን 16 መድረሳቸው ተስፋን የሚያጭር ነው፡፡ እየበዙ እንደሚሄዱ ደግሞ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ዕድሉን ስላላገኙት እንጂ በቁም ነገር ከተጫወትን ኢትዮጵያውያን ተጋሩ ቁጥራቸው ከዚህ እንደሚበልጥ መገመት አይከብድም፡፡ አገዛዙ ከትግሬ አይውጣ እንጂ ወያኔ ሥልጣን ቢለቅ የሚወዱ ትግሬዎች ደግሞ ጥቂት አይደሉም፤ ይህን ወያኔ የተከለብንን የዘር መዘዝ ለማጥፋት ማርከሻውን በቶሎ ካላፈላለግንና በ“ሜሪቶክራሲ” መተካት ካልቻልን ገና ወደፊትም ብዙ እንጎዳለን፡፡

በመሠረቱ ከኢትዮጵያዊነት በወረደ ከዚህኛው ወይም ከዚያኛው ጎሣ እየተባባሉ ማናቸውንም ዓይነት ተቃውሞን መግለጹ ዘመናዊነትን ሊገልጽና የሥልጡን ፖለቲካ መታወቂያ ሊሆን እንደማይገባው አምናለሁ፤ በሃይማኖትና በአካባቢ ልጅነት መደራጀትም እንደዚሁ ተገቢ አለመሆኑ ይገባኛል፡፡ ቢሆንም ቅሉ … ከዐማራ ተወላጆች፣ ከኦሮሞ ተወላጆች፣ ከትግራይ ተወላጆች … የምንለው ነገር ለጊዜው ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ ማለትም እየወረደ ያለውን በላ ከማለዘብ አኳያ አንዳች አስተዋፅዖ ካለው ቢያንስ በመርኅ ደረጃ ባልቃወመው ደስ ይለኛል፡፡ እናም አብላጫውን ደሜን ያገኘሁት ከሦስቱም በጥባጭ ዘውጎች መሆኑን ከሕይወት ተሞክሮ የተረዳሁት እኔ ማስተዋል በለጠ ከዚህ በላይና ከዚህ በታች ያለውን አስተያየት በቀናነት የምሰነዝረው አድማጭ አገኛለሁ ከሚል ትልቅ ተስፋ ነው፡፡

ስለኔ ትንሽ ብናገር ደስ ይለኛል – ታሪኬን ብዙዎች የሚጋሩት ስለሆነ፡፡ መነሻየ ግምት እንጂ ጥናት አይደለም፡፡ የብዙ ጥናቶች መሠረት ለእውነት የቀረቡ ግምቶች መሆናቸውንም አንዘንጋ፡፡ እናም የእኔ ዘውጋዊ ቀመር እንደሚመስለኝ 30% ዐማራ፣ 30% ኦሮሞ፣ 30% ትግሬ እና 10% ከሌሎች ነው፤ እንዲህ የሆንኩ ያህል ይሰማኛል፡፡ እንደዚህ ስል ደግሞ የሚያምነኝ እንደማላገኝ ብቻ ሣይሆን ጥቂት የማይባሉ ሰዎች እንደሚያላግጡብኝም ይገባኛል፡፡ የእኔ እውነት መነሻ ግን ይሄውላችሁ፡፡

መልኬን አሁን ላሳያችሁ ባለመቻሌ አዝናለሁ፡፡ ትግሬ ጋ ስሆን ፊቴን ያዩና “ደምህ ወደደቡብና ወደ ኦሮሞ ይሄዳል” ይሉኛል፡፡ ኦሮሞ ጋ ስሆን “መልክህ የዐማራና የትግሬ ይመስላል” ይሉኛል፡፡ ዐማሮች ጋ ስሆን “አባትህ ከደቡብ የተቀጠሩ ወታደር ነበሩ እንዴ?” ብለው ይጠይቁኛል፡፡ እኔ ራሴን በመስተዋት ስመለከት አንዱንም የማልመስል ከሁሉም ግን ጥቂት ጥቂት እንደወሰድኩ ይሰማኛል፡፡ ትልቁ ማስረጃየ ግን ሦስቱም ዘውጎች ከየተነሱበት መጥተው የሚያልቁበት ቦታ ላይ መወለዴ ነው፡፡ አዎ፣ የአማራ፣ የትግሬና የኦሮሞ ጠቅላይ ግዛቶች የሚጫፈሩበት(overlap የሚያደርጉበት) ሥፍራ ላይ ነው የትውልድ መንደሬ፡፡ ለዚህም ነው ቁርጥ ባለ ሁኔታ ይህን ወይ ያን ልመስል ያልቻልኩት፡፡

ስለዚህ አንዱ በዐማራነቴ አህያ ቢለኝ ወይም ዛሬ ጧት እንዳነበብኩት የፕሮፌሰር አልማርያም መጣጥፍ “የአእምሮ ዘገምተኛ” ቢለኝ ወይም በኦሮሞነቴ ሽብርተኛና ወንጀለኛ ብባል ወይም በትግሬነቴ ዘረኛና ጎጠኛ ብባል ብዙም የሚሰማኝ አልሆንም፡፡ ሁሉን መሆን አንዳንዴ ዕዳ አንዳንዴ ደግሞ በረከትም ነው፡፡ የሆንኩትን እንድሆን የመምረጥ ዕድል ያልተሰጠኝ መሆኔ ግን በከንቱዎች ከንቱ አባባል እንዳልቆጣ ትልቅ የትግስት ጋሻ አስጨብጦኛል፡፡ ለመሆንና ላለመሆን ምርጫ ባልተሰጠኝ ሁኔታ በሆንኩት ነገር መበሳጨትም ሆነ ከሰው ጋር ትርፍ ንግግር ውስጥ መግባት ትልቅ ሞኝነት ነው፡፡

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሣ ሰሞኑን በጻፈው መጽሐፍ የትውልድ አካባቢየና ተፈጥሮ ቀድመው ያቆራኙትን ዐማራነቴንና ኦሮሞነቴን በተመለከተ ብዙ ነገር አትቷል፡፡ የፕሮፌሰሩ ልፋትና ድካም ይገባኛል፤ በሕዝቡና በሀገሩ ሰላምንና ፍቅርን፣ ወንድማማችነትንና እትማማችነትን ለማስፈን በመፈለጉ ብዙ ርቀቶችን ተጉዞ በእምቅድመ ዘመነ ታሪክ በአዳምና ሔዋን አንድ የሆንነውን ግን የዘነጋነውን እኛን አንድ አድርጓል፡፡

በመሠረቱ ታዲያ ጥቁሮች ኢትዮጵያውያንን ቀርቶ የሰውን ዘር በሞላ በሥነ ፍጥረት አንድ ያደረገ ፈጣሪ ከአዳምና ከሔዋን አንስቶ አሁን የምንገኝበትን የሰባት ቢሊዮን የሕዝብ ቁጥር ለበረከትም ይሁን ለእርግማን እንደሰጠን ለምናምን ሰዎች የሰውን ልጅ አንድነትና የዘር ሐረግ ወጥነት ለመረዳት አንዳችም ምርምር አያስፈልገንም ነበር፡፡ ይሄ አንድ የመሆን ወይም ያለመሆን ችግር አይደለምና ዋናው ችግራችን፡፡

(እንደኔ አስተሳሰብ) የሰው ልጅ ዋና ችግር የዘር ሐረጉ መለያየት አይደለም፡፡ ትልቁ ችግር የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ከመከፋፈል አንጻር የሚታየው ኢ-ፍትሃዊነት ነው፡፡ ምክንያቶቹ የፈለገውን ያህል በቅርጽ ቢለያዩም ዋናው ችግራችን የሀብት ክፍፍል ላይ የሚፈጠር የ“ያንተ በዛ፣ የኔ አነሰ” ዓይነት መፎካከርና ያን ተከትሎ የሚፈጠር ቀውስ ነው፡፡ አንዱ በጉልበቱ ወይም በብልጠቱ ቢሊዮን ሲወስድ ሌላው መቶም አያገኝም፡፡ አንዱ ያለ የሌለ ዘዴና ብልኃቱን ተጠቅሞ ወደሀብትና ሥልጣን ማማ በአቋራጭ በመውጣት ዕድሜ ልኩን ሲጎለት ይህን ቅጥፈት የታዘበ ሌላው ባለወር ተራ ደግሞ ወደዚያ ሥፍራ ለመጓዝ የንጹሓንን ደም እየገበረ ሌት ከቀን በእውኑም በህልሙም ይባዝናል፡፡ እንጂ የመለስ ዜናዊ የ17 ዓመታት ጉዞና የቢሊዮን ዶላሮች ክምችት ለእንደርታው ገበሬ ለአቶ ሐጎስ ፀጋዝኣብ የፈየደለት አንድም ነገር እንደሌለ ቢያንስ ኅሊናችን ይረዳዋል – ይህን የምለው ታዲያ አጠቃላዩን እውነታ ለመግለጽ እንጂ የመለስ ሸፋፋና ወልጋዳ አስተሳሰብና አመራር ተጋሩ ወንድምና እህቶቼን አልጠቀመም እያልኩ አይደለም፡፡ የተጠቀመ ተጠቅሟል፤ የተጎዳም እንዲሁ፡፡

ሁላችን እናውቀዋለን፤ የሰው ልጅ ዘር አንድ ነው፡፡ ነጭና ጥቁር የመጣው ከጊዜ በኋላ እንደሆነ መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡ የመልክና የቁመት ልዩነት እንደሆነ በማኅበረሰብ ደረጃ ይቅርና በኔ ቤትም ጎልቶ የሚታይ ግን ተዓምራዊ ያልሆነ ተራ ክስተት ነው፡፡ በኔ ቤት እኔ ወደጥቁርነት የማደላ የቀይ ዳማ ስሆን አንዱ ልጄ ቆንጆ ቀይ፣ አንዱ ከኔ የባሰ አሻሮ ናቸው፤ ሌሎቹም እንዲሁ የተለያዬ መልክ፣ ቁመትና ጠባይ አላቸው፡፡ እነዚህን ልዩነቶች እኔና እናታቸው አልሰጠናቸውም – ባልሰጠናቸው ልዩነት ደግሞ አይጣሉም፡፡ ስለዚህ ልዩነትን ለጠብ ማዋል የከይሲዎች ተግባር እንጂ የደግ ሰው ጠባይ አይደለም፡፡

ይህን የልዩነት ሰበዝ በኦሮሞነትና በዐማራነት ካየነው እርግጥ ነው “ይህ ሰው ኦሮሞ ነው”፣ “ይህ ሰው ጉራጌ ነው” የምንልባቸው ልማዳዊ የሰውነት ቅርፆች ሊኖሩ እንደሚችሉ በበኩሌ እረዳለሁ፡፡ ለዚህም ነው ከፍ ሲል የኔ የሰውነት ቅርጽና የመልክ ይዘት የዚህ ወይ የዚያ ሣይሆን ድብልቅ ነው ለማለት የደፈርኩት – ለፖለቲካ ፍጆታ አይደለም፡፡ To my belief, there are some typically subtle features of ethnics if they are not mixed up and diluted through intermarriage. And, in most cases, the Ethiopian societies are said to be interwoven to the extent of not being able to be clearly and unmistakably identified as this or that ethnic group, excepting some incidents especially in remotest rural areas where there is less chance of intermingling through interarriage.

እውነት እንነጋገር ካልን ታዲያ ከሥነ ልሣናዊ ተቀራራቢነትም ይሁን ከአካላዊ ቅርጽ አኳያ አንድ ትግሬና አንድ ዐማራ የሚለዩበትን ገጽታ(ፊቸር) ለመለየት በበኩሌ እቸገራለሁ – ተፈጥሯዊ ዝምድናቸው በጣም ያቀራርባቸዋል፡፡ ይህንን ስል ፕሮፌሰር ፍቅሬ ያለውን የኦሮሞና የአማራ ጎሣዎች የመባቀያ ተመሳሳይነት ጨብጬ ይህን እኔ የምለውንም በተጨማሪነት ለማስገንዘብ ፈልጌ እንደሆነ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ዐማራና ኦሮሞ አንድ መሆናቸው የሚያስደስተኝን ያህል ትግሬና ዐማራም አንድ ብቻ ሣይሆኑ እንደኔ እንዲያውም ሁለቱ ጎሣዎች ከፋፋይ ሰይጣን በመካከላቸው ገብቶባቸው እንጂ በልይት ዘውግነት መለያየት ራሱ ይበዛባቸዋል ባይ ነኝ – በአንድ ዘውግ ሥር መመደብ ነበረባቸው እያልኩ ነው፡፡ የአሁኑን ባላውቅም በኔ የወጣትነት ዘመን አንድን ትግሬ ከአንድ ዐማራ ለመለየት ምናልባት በትግሬው ግምባር ላይ ይቺ 11 ቁጥር የምንላት ታርጋ ኖራ በሷ ካልለየነው በስተቀር በምንም መንገድ አይለዩም ነበር – በነገራችን ላይ የሌላቸውም አሉ (ባይገርማችሁ ባለ 11 ቁጥር ዐማራ አለ፤ 11 ቁጥር የሌለው ትግሬም አለ)፡፡ ወያኔ እንደጣዖት የሚያመልክባትን የብሶተኞች የምትመስል 11 ቁጥርን በድንበር አካባቢ ያለን ሰዎችም አለችን፡፡ ለዐይን ህመም ተብሎ ብዙዎቻችን እንቀነደብ እንደነበር የኔም ግምባር ኅያው ምሥክር ነው፡፡ በኔ አካባቢ የባህሎች መዋሃድ ስላለ የብዙ ማኅበረሰቦች አሻራ በሁሉም ሰው ላይ ይታያል፡፡

በተረፈ ግን ዱሮ ትግሬን ከዐማራ ለመለየት የሚቻል አልነበረም፡፡ ሥነ ልቦናዊ ቀመራቸው፣ ሥነ ልሣናዊ ዳራቸው፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው፣ አመጋገባቸውና አለባበሳቸው፣ እንግዳ አቀባበላቸው፣ ሰውን አክባሪነታቸው፣ ባህላቸውና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸው ሲታይ አንዳቸውን ከሌላኛቸው መለየት የማይቻልበት ሁኔታና ወቅት ነበር – የዛሬውን ዘመነ ጥልሚያኮስ አያድርገውና፡፡ ለምሣሌ ሁለት ኦሮሞዎች እዚህ አጠገቤ እያወሩ ነው ልበል፡፡ በዚህኛው ሌላኛው አጠገቤ ደግሞ ሁለት ትግሬዎች እያወሩ ነው ልበል፡፡ አንድ ኦሮምኛም ትግርኛም የማይችል ሰው ቢያዳምጥና ከየትኛዎቹ ምን እንደተረዳ/እንደሰማ ይህን ሰው  ብንጠይቅ በርግጠኝነት ከትግርኛ ተናጋሪዎቹ በአነስተኛ ግምት ወደ 25 በመቶ የሚጠጋውን ሊረዳ ሲችል ከኦሮምኛ ተናጋሪዎች ግን 5 በመቶውን እንኳን ስለመረዳቱ እጠራጠራለሁ – ይህ ሰው ግን የሴም ቋንቋዎች ተናጋሪ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ታዲያ ይህን የትግሬ-ወያኔዎችን በዐማሮች ላይ መጨከን ምን አመጣው? ይህ ነው ትልቁ የዘመናችን ዕንቆቅልሽ፡፡ ፍቺ ያጣንለት የክፍለ ዘመን ጥያቄ ነው፡፡ ምን ዓይነት ሰይጣን በወንድማማቾች መካከል ገባ? በውነቱ ይህን የምለውን እውነት የሚያስታውስ ጠፍቶ ነው ወይንስ ማስታወስ አስፈላጊ ሣይሆን ቀርቶ ይሆን? ለምን? ማንን ለመጥቀም? እነዚህን ወንድማማች ማኅበረሰቦች በማፋጀት የሚገኘው ጥቅም ምንድን ነው? ጥላቻን ዘርቶ ዐመፃን ማጨድ ማንን ነው የሚጠቅመው?

የዚህ ሁሉ ጥያቄ መልስ ቀላል ነው – እሱም ጥቅም ነው፡፡ ጥቅም አይደለም ጎሣና ነገድን ወንድምና እህትን ያገዳድላል፡፡ አባትና ልጅን ያባላል፡፡ ቤተ ዘመድን ያጨራርሳል፡፡ ጥቅምና ሥልጣን በጣም አደገኛ መርዝ ነው፡፡ የአቦይ ስብሃት ሀብት ከሚነካ የትግራይ ሕዝብ ጥንቅር ይበል፤ የአባይ ፀሐዬ ሥልጣን ከሚሸረሸር የትግራይና ዐማራ ሕዝብ ሚና ለይቶ ይጨራረስ፡፡ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ሥልጣኑን ከሚያጣ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ባፍ ጢሟ ትደፋ፡፡ ይህ ነው የግለሰቦች የሥልጣንና የሀብት አምልኮ፡፡ እንጂ ሕዝብና ሕዝብ በየትም ሀገር ለጠብና ለፍጅት ተፈላልጎ አያውቅም፡፡ የዕልቂት ከበሮ የሚጎስሙ ወገኖች በሀብትና በሥልጣን ሱስ ናላቸው የዞረ ጥቂት ግለሰቦችና በሥራቸው የሚኮለኩሏቸው አጥፊ ጀሌዎች ናቸው፡፡ ይህ ዓይነቱ የትያትር መድረክ ደግሞ መጋረጃው ሲዘጋ አብሮ የሚዘጋና በሌላ ወርቃማ ታሪክ የሚተካ ነው – እስካሁን እንዲህ ነበር ወደፊትም እንዲሁ ነው፡፡ እናም ውድ ኢትዮጵያውን አይዞን ይህ ወያኔዊ የጥፋት ዘመን አልፎ የፍቅርና የመተሳሰብ ዘመን በቅርብ ይመጣል፡፡ ጸሎታችን መሆን ያለበት መስዋዕትነቱ እንዲቀንስልን “ጌታ ሆይ ዕርዳን” ነው፡፡ ደግሞ በከንቱ ጥላቻን አናባብስ፡፡ የሚተርፈን ትዝብቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደሆነች ጠፍታ የማትጠፋ የፈጣሪ ቃል ኪዳን የሚጠብቃት ሀገር ናት – በወረት የዘረኝነትም እንበለው የትምክህተኝነት ንፋስ አንወሰድ፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ምንም ዓይነት ጥጋብ አይፈታተነን፡፡ ብናገኝ አንኩራ፣ ብናጣም አንፍራ፡፡ “ሁሉም በርሱ ሆነ – ያለርሱ በሰማይም በምድርም ምንም አልሆነም፡፡” ስለዚህ ለምኑ እንጨነቃለን? የተወሰደ እንደሚመጣ፣ የመጣም እንደሚወሰድ አናውቅምን? ማን ነው እንደኮራ እንደደራ የኖረ? ማን ነው እንዳነሰ እንደኮሰመነ ኖሮ ከምድር የተሰናበተ? ጠቢቡ አስቀድሞ “ለሁሉም ጊዜ አለው” ብሏል፡፡

ከአዳም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ይህ የጥቅምና የሆድ ጉዳይ የዓለም ሕዝቦችን እያፋጀ ነው፡፡ እንጂ ዐማራ ከማንም የበለጠ “አህያና ደደብ” ወይም “የአእምሮ ዘገምተኛ” ሆኖ አይደለም – ሰፊው ኦሮሞ ከትግሬ በልጦ ጠባብ ሆኖ አይደለም፡፡ ትግሬ ከማንም በልጦ ጀግናና አልሞ ተኳሽ ሆኖ አይደለም፡፡ ይህን ሁሉ ዕልቂትና ፍጅት እያስከተለ ያለው ከፀሐይ በታች ያለ የሸርና የተንኮል ጉንጉን የተላበሰ የወያኔዎች የሀብትና የሥልጣን ጉጉትና የዓለም አቀፉ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሤራ ድምር ውጤት ነው፡፡ ከወያኔዎች ጋር ተሰልፎ ጃዝ ሲሉት እየገደለና እየዘረፈ የሚተመው የጥፋት ሠራዊት ደግሞ ከዕውቀትም ከባህልም ከሃይማኖትም የወጣ ወፍ ዘራሽ ጀሌ ነው – አብዛኛ ከእረኝነት በቀጥታ የመጣና ማኅበራዊ እንስሳነቱ የተጓደለበት ከመሆኑም ባሻገር ዐማራን እንዲጠላና ከጥላቻውም ብዛት የተነሣ በጭካኔ እንዲፈጀው ሥነ ልቦናዊ ጫና የተደረገበት አሳዛኝ ፍጡር ነው፡፡ ሳይፈልግ በተደረገበት ተፅዕኖ ምክንያት ስለሆነ ይህን ሁሉ ግፍ የሚፈጽመው ሙሉ በሙሉ በርሱ ለመፍረድም ይከብዳል፤ በዚያ ላይ የውጭ ጠላቶቻችን ለውስጥ ምንደኞች ያሸከሙት ታሪካዊ የጥፋት ተልእኮም ቀላል አይደለም – የየትኛውንም ሀገር ባለሥልጣናት ብሔራዊ ስሜት በማጥፋት የነርሱ አሽከሮች የሆኑ መሪዎችን በማፍራት የሚታወቁት የዐውሬው ልጆች ምዕራባውያንና አውሮፓውያን ካልጠፉ ወይም ሰይጣናዊ ተፈጥሯቸውን ካልቀየሩ አለዚያም እኛ ይህን መርዝነታቸውን ነቅተንባቸው በኅብረት ካልታገልናቸውና ድል ካልነሳናቸው ደግሞ ዕረፍት እንደሌለን መረዳት ተገቢ ነው፡፡

ጥቂት ታገሱኝ – አንዲት ነገር ብቻ ትቀረኛለች፡፡ የትግራይ የወቅቱ መሣፍንት መኳንንት ትግራይን ይዘን እንሄዳለን ቢሉ ጥርሳችንን ተነቅሰን እንስቅባቸዋለን፡፡ በርግጥም ዓለም ይስቅባቸዋል፡፡ “እውነት እውነት እላችኋለሁ” ብሎ ይጀምር ነበር ክርስቶስ የመረረ እውነት ሲናገር፡፡ እኔም ልዋሰውና – “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ትግራይን መገንጠል ቢያስፈልግ ኖሮ ይቻል የነበረው የዛሬ 25 ዓመት ገደማ በ1983ዓ.ም ወርኃ ግንቦት ላይ ነበር፡፡” አሁን እጅግ መሽቷል፤ “ቢያዩኝ እስቅ፣ ባያዩኝ እሰርቅ“ የሚለው ብሂል የማይሠራበት የመጨረሻው ሰዓት ላይ ስላሉ ያን ቅዠታቸውን ዘመን ሽሮታል፡፡ “ዕድላችንን እንሞክር” የሚባልበት ጠባብ የተስፋ ጭላንጭል እንኳን የለም፡፡ አንድ የትግርኛ ብሂል ላስታውስ – ወዳማርኛ ልመልሰው ፡- “የሚበቃትን ያህል ጥሬ ከፈጨች በኋላ የማርያም በዓል ነው ትላለች” ይላል፡፡ ግሩም ብኂል ነው፡፡ በልጆች ጨዋታ ጊዜ “ጨዋታው ፈረሰ፣ ዳቦው ተቆረሰ” ሊባል ይችል የነበረው ዛሬ ሣይሆን ከዛሬ 25 ዓመታት ገደማ በፊት ነው፡፡

ወልቃይትንና አካባቢዋን ከጎንደር፣ ራያዎችን ከወሎ፣ የአባይ ግድብን ከቤንሻጉል፣ እንትናን ከአፋር … ከዘረፉና ወደ “ታላቋ የትግራይ ሪፐብሊክ” ካካለሉ በኋላ፣ ሰፊ የዐማራ ግዛትን ለሱዳን ከሸጡ በኋላ፣ የኢትዮጵያን ሀብትና ንብረት ለ40 እና 25 ዓመታት ካለተቆጣጣሪ እንደልብ ከመዘበሩና ወደሚፈለጉት ቦታ ካዘዋወሩ በኋላ፣ በሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ በልዩ ልዩ ዘዴ ከምድረ ገፅ ካጠፉ በኋላ፣ የኢትዮጵያን አስተዳደር በአንድ ጎሣ ቁጥጥር ሥር አውለው የሀገሪቷ አንጡራ ሀብት እንሻቸው ከቦጠቦጡና መዋቅሮቿን ሁሉ ካፈራረሱ በኋላ፣ የሚንቀሳቀስንም ሀብትና ንብረት ወደ አሳቻ ቦታ ካሻገሩ በኋላ… ለዚህ ሁሉ ዘመን በአንዲት ሉዓላዊት ሀገርና በአንድ ሕዝብ ላይ እንደልብ ከፈነጠዙ በኋላ አሁን ሲመሽ “የያዝኩትን ይዤ የራሴን ግዛት እመሠርታለሁ” የሚለው ብልጣብልጥነት ከማሣቅም ያልፋል – ወያኔ ከኢትዮጵያ የአንበሣውን ድርሻ ዝቆ ወደራሱ ጎተራ ካስገባ በኋላ ለመሆኑ ለሌላው ሕዝብ ምን የቀረለት ነገር አለ? የመረጃ ቋቱ ሳይቀር ተጉዞ መቀሌ ገባ ከተባለ በኋላ ሌሎቹን  እንደፍጥርጥራችሁ ብሎ “ትግራይ ሪፐብሊክ” የምትመሠረተው በየትኛው ሥሌት ነው? የዋህነት ወይንስ ድምበርን የማያውቅ ብልጠት? ሀገርን ማስተዳደርና ሀገርን መመሥረት የልጆች የቃቃ ጨዋታ አይደለም፡፡ አንድን ሀገር አፍርሶም ሌላ ሀገር መገንባት የሚታሰብ አይደለም፡፡ ቂልነት ነው፡፡

የወያኔዎች አጀማመር ሁሉ እንዳይሆን ነው፤ ሲጀምር ትልቅ ሀገርን እየገዙ የ”ገዛ ሀገር”ን መሬት ለባዕድ መሸጥና በነሱው አጠራር ካንዱ ‹ክልል‹ ወደሌላው ‹ክልል‹ ቁርጥራጭ መሬት እየቀደዱ መስፋት ጥንቱንም አላስፈላጊ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውን እስከሆነች ድረስ በግዛት መካለልና ያንንም ተከትሎ በመጣ ዕልቂት የሰውና የንብረት ውድመት መከሰት አልነበረበትም፡፡ ማንም ዜጋ የትም ሄዶ መሥራትና ሀብት ንብረት ማፍራት ስለሚችል አዲስ አከላለል ወይም የመሬት ዝርፊያ ባላስፈለገም ነበር፡፡

ወያኔ ግን የነገን ሣይሆን የዛሬን ብቻ ስለሚያስብ የሆነው ሁሉ ሳንወድ በግዳችን ሆነ፡፡ ግዴለም – “በዚሁ ይለፍ፡፡” ዋናው ነገር ግና ከዚህ ሁሉ የሰው ዕልቂትና የንብረት ውድመት በኋላ የ“ታላቋን ትግራይ ሪፐብሊክ” ለመመሥረት ማሰብ ዕብደት እንጂ ሌላ ሊሆን አለመቻሉን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ወያኔዎች እንደዚህ ያለ ጅል አስተሳሰብ ውስጥ የሚገኙ ከሆነ ከፍ ሲል በዐማርኛ የጠቀስነውን የትግርኛ ብሂል ደግመን በማስታወስ ”ዝአኽለን ጥሂነን በዓል ማርያም ትብላ” ብለን እንተርትባቸዋለን፤ በአግራሞትም እንስቅባቸዋለን፡፡ ይህን ቅዠት ማንም ወያኔም ይሁን የትግራይ ክፍለ ሀገር ሰው ሊያስበው አይገባም፤ አይችልምም፡፡ ሁለት ተቃራኒ ነገሮች ኅብረት የላቸውም፡፡ ብርሃንና ጨለማ በአንድ ጊዜ አይገኙም፡፡ ኢትዮጵያዊነትና ትግራዊነትም እንዲሁ፡፡ ጤናማ ተጋሩ ከዚህ ወያኔያዊ ቅዠት ባፋጣኝ ውጡና የሚሻለውን ለማድረግ ተመካከሩ፡፡ ይህ “ወርቃማ” ዕድል የዛሬ 25 ዓመት አለፈ፡፡ አሁን ቀሪው ዓለምም እንደኛው ተወቅሮ ይስቃል፡፡

ይልቁንስ በትግራይና ለትግራይ የሚያዋጣው ብቸኛ መንገድ መፈንቅለ መንግሥት ማድረግና ያን ተከትሎ ጤናማ ትግሬዎች የያዙት “የክልሉ መንግሥት” ከሌሎች ጤናማ ወገኖች ጋር አዲስ ድርድር ማድረግ ነው፡፡ ይህ ሣይሆን ቀርቶ ወያኔ የትግራይን መፃዒ ዕድል እንደእስከዛሬው ሁሉ እንዲወስን ከተደረገ በርግጥም የትንቢቱ ፍጻሜ ይሆንና መቀሌ ጥሻ ትሆናለች – ይህን እውነት አሁን ሳይመሽ በጊዜ እንዲህ ባልተለመደ ድፍረት የምናገረው ሌላውን ተውትና ከነባራዊው ዓለም ተጨባጭ ወይም ገሃድ እውነት በመነሳት የተበደለ ሲነሳ የሚያቆመው ነገር እንደሌለ በመረዳት ነው፡፡ (ምን ፈርተው እንደሆነ ባይገባኝም ነሐሴ እኩሌታ 2008 ዓ.ም አካባቢ ይህን ጽሑፍ ለድረ ገፆች ልኬ አንዳቸውም አላወጡትም፡፡ እኔ ግን በሕይወት ካለሁ  ከሌሎች ሥራዎቼ ጋር ወደፊት ለሕዝብ አቀርበዋለሁ፡፡ እውነት ውሸትነቱ ያኔ ይታያል፡፡ እውነትን ቢሸፍኗት መውጫ አታጣም፡፡ ጊዜ ግን ወሳኝ ነው – በሦስቱ ኑባሬያት ዘንድ ያለው የጊዜ እርዝማኔ እንደተጠበቀ ሆኖ ትናንትናና ዛሬ እንደሚለያዩ ሁሉ ዛሬና ነገም በርግጠኝነት አንድ አይሆኑም፤ ይለያያሉ፡፡…)

እዚህች ላይ አንዲት ጠቃሚ ነጥብ ላንሳ፡፡ … ደጋግ ሰዎች ለፈጣሪ ከጮኹና የፈጣሪን ልብ ካራሩ ትንቢት ሊለወጥ ወይም የሚከሰት ውድመት ሊለዝብ እንደሚችል መገንዘብ ተገቢ ነውና ለፈጣሪ የቀረባችሁ ዜጎች የእንቅልፍ ሰዓትን በመቀነስ ሌት ተቀን ጩኹ፤ እየመጣ ያለው የመከራ ዶፍ ሰው ቀርቶ ምድር አትችለውም – በዓለም ታሪክ ወደር የሌለው የወያኔዎች ዐረመኔነት የሚያስከትለው ጦስ እንዲህ በቀላሉ የሚገመት ነው ብሎ የሚያስብ ሰው ካለ ስለወንጀል ዕዳ አከፋፈል ምንም የማያውቅ የዋህ ሰው መሆን አለበት፡፡ ይህን የማይም ማስጠንቀቂያ እየተናገርኩ ያለሁት በዱባ ጥጋብ ለታበዩትና በዕብሪት ጉሽ ጠላ ለሰከሩት ወያኔዎችና መሰሎቻቸው አይደለም፤ ተፈጥሮን ተመክሮ አይመልሰውምና እነሱ መቼም ሊለወጡ አይችሉም – እንዲለወጡ የሚጠብቅም ሰው ካለ የአእምሮ ህክምና የሚያስፈልገው የለዬለት ገልቱ ነው፤  እነሱና ጋዳፊ ሊለወጡ እንደማይችሉ በበኩሌ በደንብ አውቃለሁ – ጋዳፊ ስምንት ቀን ተሸሽጎበት ከነበረው የቆሻሻ ቱቦ ወጥቶ “ምን ሆናችሁ? ሊቢያ ውስጥ ምን ተፈጠረ?” እያለ መሪው እርሱ የሆነ ያህል ቆጥሮ በባትሪ እየፈለጉት የነበሩትን ተቃዋሚዎች ለማዘዝ ቃጥቶት ነበር አሉ – ግን ወዲያው ያዙትና በመቀመጫው በኩል ሣንጃቸውን ወድውደውበት አንጀቱን በጣጥሰው ገደሉት – የአምባገነኖች መጨረሻ እንዲህ ነው፡፡ እኚህን መሰል ደናቁርት ከአህያ የማይሻል የማየት ችሎታ ነው ያላቸው፤ የጅልነታቸው መጠን የጨካኝነታቸውን ያህል ነው፡፡ …

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 8 years ago on August 26, 2016
  • By:
  • Last Modified: August 26, 2016 @ 11:28 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar