www.maledatimes.com የዲሞክራሲ ቀለሞች – ከሽግግር እስከ ችግግር! ዳዊት ከበደ ወየሳ (አትላንታ – አሜሪካ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የዲሞክራሲ ቀለሞች – ከሽግግር እስከ ችግግር!   ዳዊት ከበደ ወየሳ (አትላንታ – አሜሪካ)

By   /   August 26, 2016  /   Comments Off on የዲሞክራሲ ቀለሞች – ከሽግግር እስከ ችግግር!   ዳዊት ከበደ ወየሳ (አትላንታ – አሜሪካ)

    Print       Email
0 0
Read Time:8 Minute, 59 Second
ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ… የ”አትነሳም ወይ?!” መዝሙሮች ተደምጠዋል፤ በርካታ የተቃውሞ ሰልፎች እና የስራ ማቆም አድማዎች ተደርገዋል። የተቃውሞ ሰልፉ ከመብዛቱ የተነሳ ሁሉንም መዘርዘር ያታክታል። ለምሳሌ “የአጼ ምኒልክ ሃውልት ይፍረስ” የሚሉ ሰዎች ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ። ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የሃውልቱን ዙሪያ በጥቁር ጨርቅ ሸፈኑት። ይህ ዜና ተብሎ በሬድዮ እና በቴሌቪዥን ቀረበልን።
ከዚህ በኋላ የኢህአዴግ ሹማምንት የህዝቡን የጩኸት ትርታ ለማዳመጥ ጸጥ ሲሉ፤ እኛ ደ’ሞ ‘ሃውልቱን በመድፍ እናፍርሰው ወይስ በቦንብ እንናደው ወይስ ዲሞክራሲያዊ መብቱን ጠብቀን በገመድ ጎትተን እንጣለው?’ እያሉ ብበምት የሚንሾካሾኩብን መሰለን። እንደእውነቱ ከሆነ ግን… ኦህዴድ እና ህወሃት በሃውልቱ መፍረስ ቢስማሙም፤ ኢህዴን (የአሁኑ ብአዴን) ሃሳቡን በመቃወም የራሱን ስብሰባ አደረገ። በዚህ ታሪካዊ ስብሰባ ላይ፤ “እኛ የታገልነው የምኒልክን ሃውልት ለማፍረስ ነው ወይ?” የሚል በሲቃ የታጀበ ንግግር ተደመጠ።
በዚህ ሁሉ ውዝግብ መሀል ግን… እኛ ጋዜጣችንን ለማሳተም የብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤትን ደጀ ሰላም ስንጠና፤ በድንገት ታይቶ የማይታወቅ የኦሮሞ ፈረሰኞች ከኮተቤ፣ ከሱሉልታ እና ከሰላሌ ተሰባስበው… የአጼ ምኒልክ እና የእቴጌ ጣይቱን ፎቶ ከፊት ለፊት ይዘው፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማን እያውለበለቡ አራት ኪሎን አቋርጠው፣ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በኩል አድርገው፤ ራስ መኮንን ድልድይን ተሻግረው፤ ወደ ምኒልክ ሃውልት  ተጓዙ። ብዙዎቻችን የዚህን ጉድ መጨረሻ ለማየት ፈረሰኞቹን ተከተልናቸው። ፈረሰኞቹ አራዳን አልፈው ከአጼ ምኒልክ ሃውልት ዘንድ ሲደርሱ ሃውልቱን ክብ እየዞሩ ቀረርቶ እና ጌራርሳ እያሰሙ፤ ከጥቂት ቀናት በፊት ሃውልቱ የተሸፈነበትን ጥቁር ጨርቅ ቀደው እና ቀዳደው ጣሉት። (ይህን ለምስክርነት የምንናገረው በወቅቱ  ኢዜአ ያልዘገበው… ህዝቡ በአይኑ የታዘበው፣ የሴቶች እልልታ የወንዶች ፉጨት ያጀበው ታሪካዊ ትእይንት ስለነበር ነው)
ከዚያ በኋላ እንኳንስ ሃውልቱ ሊፈርስ ቀርቶ፤ ጭራሽ ወርቃማ እና ብርማ ቀለም እንዲቀባ አደረጉ – ህዝቡና የልጅ እያሱ ልጅ።
አጼ ምኒልክ በያዙት ጦርም ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ተደርጎበት፤ ቢያንስ ለብዙ ወራት ቆየ። በጨዋታችን መጀመሪያ ላይ ይህን ጉዳይ የምናነሳሳው… የህዝብን ሃያልነት ማሳያ ምስክር እንዲሆነን ጭምር ነው። ሆኖም የዲሞክራሲ ቀለም ደምቆ እንዲዋብ ህዝቡ መብቱን አውቆ ማስከበር መቻል አለበት። አስቡት። በሽግግር መንግስቱ ዘመን የአጼ ምኒልክ ሃውልት ፈርሶ ቢሆን ኖሮ፤ እንደሌኒን ሃውልት የት እንደደረሰ ላይታወቅ ይችል ነበር። ክብር ሃውልቱን ለታደጉ ጀግኖች ሁሉ ይሁን።
እንዲህ የአገር ቅርስን በሰላማዊ ሰልፍ የማስተረፍ ስራ የመሰራቱን ያህል፤ ፈገግ የሚሰኙ አይነት ሰልፎችም ተካሂደው ነበር። ከእነዚህ አንዱ ጭር ሲል የማይወደው ኢህአዴግ ያዘጋጀው የህጻናት ሰላማዊ ሰልፍ ነው። ሰልፉ በሴቶች ቢሮ በኩል አድርጎ ለአደባባይ የበቃው፤ የእናት ጡት ወተትን አስፈላጊነት ግንዛቤ ለመፍጠር በሚል ነበር። እናም አንድ ቀን የአካባቢው ትምህርት ቤቶች ተዘግተው… የህጻናት ሰልፍ አራት ኪሎን እንዲያጨናንቅ ተደረገ። የህጻናቱም ጥያቄ አንድ እና አንድ ብቻ ሆነ። አንዷ “የእናት ጡት ለህጻናት!” ስትል ሁሉም በአንድ ድምጽ “የእናት ጡት ለህጻናት” እያሉ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ግቢ ደረሱ።
ከያዙት መፈክር ጎን፤ የተዘቀዘቁ ትላልቅ የጡጦ ስዕሎች አሉ። ሁሉም ደግመው ደጋግመው “የእናት ጡት ወተት ለህጻናት፡፡” የሚለውን መፈክር እንደውዳሴ ማርያም ይደጋግሙታል። እንዲህ እንዲህ እያሉ በጠቅላዩ ሚንስትር ደጃፍ ትንሽ ቆዩ። በኋላ ላይ የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች በስፍራው መኖራቸውን ካረጋገጡ በኋላ የጠቅላይ ሚንስትሩ ተወካይ ሽክ ብለው መጡ። እንዲህም አሉ።
 “እርግጥ ነው። ህጻናት የእናት ጡት ወተት ያስፈልጋቸዋል።” ካሉ በኋላ የጠቅላይ ሚንስትሩ ተወካይ…የእናት ጡት ወተት ለህጻናት አስፈላጊ መሆኑን አስረዱ። “አሁንም የእናት ጡት ለህጻናት አስፈላጊ መሆኑን ስለተረዳን፤ የሽግግር መንግስቱ አስፈላጊውን ሁሉ ያደርግላችኋል።” ሲላቸው ከህጻናቱ ጋር የመጡት እናቶች አጨበጨቡ፤ ህጻናቶቹም ተንጫጩ። የሽግግር መንግስቱን አመስግነው ከመበተናቸው በፊት፤ ጋዜጠኞች ለአንዳንድ ህጻናት ጥያቄ አቀረብን።
“ጥያቄያቹህ የእናት ጡት ወተት ማግኘት ነው። አሁን እንደሰማነው ‘የሽግግር መንግስቱ አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል’ ተብሏል። እንዴት ታዩታላቹህ?” አልናቸው።
አንደኛው ህጻን ተገርሞ እኛንም ጓደኞቹንም እያየ፤ “የሽግግር መንግስቱ ጡት አለው እንዴ?” ሲል፤ እኛም ሆንን ጓደኞቹ ዛሬም ድረስ ያልመለስነውን ጥያቄ አቀረበልን።
እንዲህ አስቀው የሚያስቁንን ሰላማዊ ሰልፎች ወደ ጎን ትተን… ወደኋላ ተመልሰን ስንመለከት ግን… ከምንወቃቀስበት ጉዳይ ይልቅ የምንሞጋገስባቸው ጉዳዮች ብዙ አሉን። ከምንም በላይ “ጨርቅ” ተብላ የተንቋሸሸች ሰንደቅ አላማችን፤ ከወደቀችበት ተነስታ ከፍ ብላ መውለብለቧ ይሰመርበት።
በሽግግሩ ዘመን… የወቅቱ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ ቡትሮስ ቡጥሮስ ጋሊ አዲስ አበባ መጥተው ነበር። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም “ኢትዮጵያ ህጋዊ የባህር በር ያስፈልጋታል” የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ያነገበ ደብዳቤ አዘጋጅተው ሰላማዊ ሰልፋቸውን ስድስት ኪሎ ላይ ጀመሩ።
ሰልፉ ተጀምሮ ገና ከግቢው እንደወጡ አንድ ተማሪ ተገደለ (ተስፋሁን ይመስለኛል የተማሪው ስም)። ይህን ተከትሎ ብዙዎች ተደበደቡ፤ አካላቸውም ጎደለ። ምሽቱን በተላለፈው ዜና፤ የተገደለው የዩኒቨርስቲ ተማሪ የቀድሞ ደርግ ኢሰፓ የነበረ መሆኑን ሳያፍሩ ተናገሩ። ከዚያ ሁሉ ሺህ ህዝብ መሃል… “ኢሰፓ የሆነውን ነጥሎ የሚገድል ጥይት አለ እንዴ?” ብለን ተገርመን ሳናበቃ፤ “እንዲያውም ሟቹ ትምክህተኛ አማራ ነበር” አሉን። ቀጥሎም የወቅቱ ፕሬዘዳንት መለስ ዜናዊ በቲቪ ቀርበው እንዲህ አሉ።
“እኛ ሰልፈኞቹን በአስለቃሽ ጢስ ብንበትናቸው ደስ ይለን ነበር። ሆኖም ከደርግ መንግስት የተረከብነው አስለቃሽ ጢስ ሳይሆን፤ ታንክ እና ሚሳየል ነው።” ብለው የመጀመሪያ ቀልዳቸውን ከምር ነገሩን። እንደሳቸው አባባል፤ “እንደውም እኛ ሰልፉን በጥይት ስለበተንን ልንመሰገን ይገባል። ደርግ ቢሆን በታንክ ይረመርማቸው ነበር” የሚል አንደምታ ያለው ንግግር ነበር – ያሰሙን።
በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሚከፈተው የጠመንጃ ላንቃ ግን፤ በተስፋሁን ላይ ተጀመረ እንጂ አላበቃም። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ፤ ምንም ያላደረጉ ሰላማዊ ዜጎች በጠራራ ጸሃይ ጥይት እየተርከፈከፈ ተገድለዋል – “ክብር ለነሱ ይሁን” ሌላ ጉዳይ እናውጋ።
ከሽግግሩ ዘመን በኋላ “አባይ ተገንብቶ ለልማት ይዋል።” ስንል፤ በረከት ስምኦን ራሱ ቃል በቃል እንዲህ ብሎን ነበር። “በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ ስሩ የሚሉ ቅዠታሞች አሉ። አባይ ቢገነባ ኢትዮጵያ በውሃ ተጥለቅልቃ እናልቃለን እንጂ፤ ምንም አናተርፍም።” ብሎ መግለጫ ጭምር ሰጥቶ ነበር። በኋላ ላይ የአባይ ግድብ ግንባታ ሲታወጅ፤ በረከት ስምኦን ዋና ተዋናይ ሆኖ፤ ጉዳዩን ለፖለቲካ ጥቅም ሲመነዝረው እያየን… “ወይ ግዜ” ያልንበት ወቅት እሩቅ አይደለም። በዚያም ተባለ በዚህ ግን ለሰንደቅ አላማችን ከፍ ማለትም ሆነ፤ ለአባይ መገደብ ትልቁ ምክንያት ሳያሰልስ ይታገል የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲ አለመሆኑን እነሱም ያውቁታል፤ እኛም እንመሰክራለን። በመሆኑም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ህዝባዊ መብቱን ተጠቅሞ  የዲሞክራሲው ቀለም እንዲደምቅ፤ የህዝብ ፍላጎት እንዲጠበቅ ያደረገው የኢትዮጵያ ህዝብ… ከምንም በላይ ሊመሰገን ይገባዋል።
ከሽግግር መንግስት እስከ ችግግር ዘመናችን ድረስ ብዙ አሳልፈናል። አሁንም በትዝታ ወደ ሽግግሩ መንግስት ዘመን እንውሰዳቹህ። ከሃያ አመታት በፊት ነው። ብዙዎቹ ሰልፈኞች መፈክር እያሰሙ ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ያመራሉ። በወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ናቸው። ሰልፈኞቹ በመፈክራቸው መጀመሪያ  እና በደብዳቤያቸው መጨረሻ ላይ “የሽግግር መንግስቱን ቻርተር እንደግፋለን” የሚል ሙሻሙሾ የሚያወርዱ ከሆነ፤ የሰልፈኞቹ ተወካዮች ወደ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጉና ያናግሯቸዋል።
ሰልፉን እራሱ ኢህአዴግ ያቀናበረው ከሆነ ደግሞ ሃያ እና ሰላሳ ሰው ያለበትም ቢሆን፤ በሬድዮ፣ በቲቪ፣ በጋዜጣም ጭምር ስለሰላማዊ ሰልፉ ብዙ ይባልለታል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኑት መካከል፤ “ፓትርያርኩ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ሰላማዊ ሰልፈኞች ጠየቁ” የሚለው ዜና አንደኛው ነበር።
በምሽቱ ዜና ላይ… “ፓትርያርኩን በመቃወም ከወጡት ሰልፈኞች መካከል አንዳንዶቹ እንዲህ በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።” ይባልና… በቃለ መጠይቁ ላይ የሚቀርቡት ሰዎች፤ “ፓትርያርኩ በደርግ ዘመን ያገለገሉ ስለሆኑ አንቀበላቸውም” ይላል አንደኛው። ሌላኛው አስተያየት ሰጪ… “የደርግ ኢሰፓ አባል ናቸው” ብሎ ይከሳቸዋል። ቀጥሎ ያለው ደግሞ “ከስልጣናቸው ወርደው ለፍርድ ይቅረቡ” በማለት ይደነፋል። አቡነ መንቆርዮስም ይህን ድራማ አዘል የተቃውሞ ሰልፍ ማታ ላይ በቲቪ ሲመለከቱ ልባቸው ተሰብሮና መንፈሳቸው ተሸብሮ፤ በንጋታው ኢትዮጵያን ለቀው ወደ ጎረቤት አገር እንዲሰደዱ የተደረጉበትን፤ በ’ሳቸውም መንበር አባ ጳውሎስ እንዲተኩ የተደረገበትን ድራማ እንደትላንት የምናስታውስ ብዙዎች ነን።
በሌላ በኩል ደግሞ… የኢትዮያን ህዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች…  በማንም በምንም አይነት ተቀባይነት አይኖቻውም ነበር። ከኤርትራ የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ፤ ከስራ የተባረሩ ሰራተኞች፤ ጡረታቸውን የተነጠቁ አባቶች፤ በብሄራቸው የተገፉ ዜጎች፤ ኢትዮጵያዊነትነት ከፍ አድርገው የዘመሩ የሌላ ብሔር አባሎች… የ’ነዚህ ሰዎች ጩኸት የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። “መብታችን ይከበር” የሚሉ ድምጾች በአራት ኪሎ ጎዳና ላይ ብዙ ተደምጠዋል። አንዳንዶቹ ምላሽ ሲያገኙ፤ የተቀሩት ደግሞ ጩኸት ብቻ ሆነው ቀርተዋል። በኋላ በኋላ ላይ… የማይቀረው ህዝባዊ መዝሙር እና መፈክር የአራት ኪሎን ግቢ ሲያነቃንቀው “ጠቅላይ ሚንስትሩ ስራ ላይ ናቸው… አትጩኹ” በሚል የታጠቁ የወያኔ ሰዎች ወደላይ እየተኮሱ ጩኸቱን ይብሱን አባብሰው ሰልፍ መበተን ጀመሩ።
በጋዜጠኝነታችን የህዝቡን ድምጽ ለማሰማት፤ በስፍራው ተገኝተን ክፉና ደግ መታዘባችን አልቀረም።  ሰላማዊ ሰልፈኞች ሰፈር አቋርጠው ሲመጡ በእጃቸው መፈክር ተሸክመው፤ አንዳንዶችም ዘንባባና የዛፍ ቅጠል ይዘው ‘ሆ’ እያሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሰፈር ይደርሳሉ። እዚያ ሲደርሱ መጮህ ስለማይቻል ተወካዮቻቸው ወደ ውስጥ እስከሚገቡ ወይም ደብዳቤውን እስከሚያስረክቡ ድረስ፤ አገር ሙሉ ሰልፈኛ ጥላ ፍለጋ በየአጥሩ ጥግ ለሰአታት ያህል ይቀመጣል። በዚህ አይነት መሰላቸት ሰአታት ያልፉና ሰልፈኞች ወደየጉዳያቸው ይበተናሉ። ከየመንደሩ ይዘዋቸው የመጡት ቁሳቁሶች፤ የካርቶን ላይ ጽሁፎች፣ የወረቀት ስእሎች፣ የጨርቅ ላይ መፈክሮች እዚያው ይጣሉና አካባቢው እብድ የጨፈረበት ገበያ ይመስላል። ሰልፈኞቹ ከተበተኑ በኋላ ወረቀትና ጨርቁን የሚሰበስቡ ሰዎች ይመጡና ያን ሁሉ ግሳንግስ ሰብስበው ያቃጥሉታል። ልክ እንደተቃጠሉት የመፈክር ካርቶኖች… በሽግግር መንግስቱ እና ከዚያ በኋላ የተነሱ በርካታ ህዝባዊ ጥያቄዎች፤ ምላሽ ሳያገኙ ዶግ አመድ ሆነዋል። ብዙዎቹ የ”መብታችን ይከበር” ጥያቄዎች ግን ከወረቀት ባለፈ፤ በህዝብ ልብ ላይ  የታተሙ በመሆናቸው በውድ ሳይሆን በግድ ተከብረዋል።
እነዚህ ተሸራርፈውም ቢሆን… ለአጭር ግዜም ቢሆን… ብልጭ ድርግም እያሉም ቢሆን… ህዝቡ እንዲከበሩለት ያደረጋቸው መሰረታዊ የመብት ጥያቄዎች… ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፤ የመሰብሰብ እና የመደራጀት፣ በነጻ ዳኝነት ፍርድ ማግኘት፣ የሰብአዊ መብት ጥበቃ እና የህዝባዊ ስልጣን መረጋገጥ ናቸው። “እነዚህ የመብት ጥያቄዎች በተገቢው መልክ ተግባራዊ ሆነዋል” ብሎ ክርክር የሚገጥም ካለ ውሸታም እንጂ ሌላ ስም አይሰጠውም። ነገር ግን እነዚህ የዲሞክራሲ ደማቅ ቀለም የሆኑ የመብት ጥያቄዎች፤ መንግስት በቸርነቱ ሳይሆን፤ ህዝብ በእምቢ ባይነቱ ያገኛቸው የትግል ስጦታዎች ሆነዋል፤ ይህ እውነት ነው። ‘እነዚህ መብቶች በመንግስት በኩል ከመከበር ይልቅ ተሸርሽረው ተሸርሽረው እያለቁ ናቸው።’ ብንል ይህም ሌላ እውነት ነው።
እውነትን መደርደር የሚያስጣላ እና የሚያከራክር ነገር አይደለም። ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መንግስት የሚያሳስበው ባይሆን ኖሮ፤ ሌላ ተዛማጅ እና ግራ ተራማጅ ህጎች ማውጣት ባላስፈለገው ነበር። ህገ መንግስቱ ሲረቅና ሲጻፍ ሁሉንም ወገን የሚያረካ ሆኖ አልተዘጋጀም። ቢያንስ ቢያንስ ግን… የሰው ልጅ ሰብአዊ መብቶች እንደሚከበሩ ይደነግጋል። ይህ ደግሞ በቀዳማዊ ኃይለስላሴም ሆነ በደርግ ህገ መንግስት ላይ በግልጽ የተካተተ ነው። ነገር ግን እነዚህ መሰረታዊ መብቶች በጽሁፍ እንጂ በተግባር ባልተረጋገጡባት አገር… በአሳዛኝ መልኩ ትውልድ አልፎ ትውልድ በመተካት ላይ ይገኛል። እንደእውነቱ ከሆነ… ሰብአዊ መብት፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ የፍትህ፣ የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብት ሙሉ ለሙሉ ያልተረጋገጠባት  አገር፤ “ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ” የሚለውን ስም ለመሸከም አቅም አይኖራትም። ይህን እያልን… መብታችን እየተበዘበዘ፤ የዲሞክራሲ ቀለም እየደበዘዘ ሊሄድ ይችል ይሆናል። ይህ ግን ለዘላለሙ አይቀጥልም። የሰው ልጅ… እስከልጅ ልጁ እየተረገጠ ሊገዛ አይችልምና… ጨለማ በጠዋት ጮራ እንደሚገፈፍ ሁሉ… የደበዘዘው የዲሞክራሲ ቀለም የሚደምቅበት ምዕራፍ ቀስ በቀስ መምጣቱ የተፈጥሮ ግዴታ ነው።
ከማጠቃለላችን በፊት የዚህን ጽሁፍ ዋና መልእክት እዚህ ላይ ለማስፈር ወደድን። ኢህአዴግ አዲስ አበባ እንደገባ ጥቂት ግዜ ቆይቶ የሽግግር መንግስት አቋቋመ። እኛም (አብዱራህማን አህመዲን እና ሙሼ ሰሙ) ጋር በመሆን “የኢትዮጵያ ወጣቶች ህብረት” የሚባል ሊግ አቋቋምን። አላማችን ወጣቱን በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ ማሰባሰብ ነበር። እንደታሰበውም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ህብረቱን ተቀላቀሉ። እንቅስቃሴው አዲስ አበባን አዳረሰ። ስብሰባ የምንጠራባቸው አዳራሾች እስከአፍንጫቸው ድረስ እየሞሉ ህዝቡ በውጭ ሆኖ ስብሰባውን ይከታተል ጀመር። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ከመንግስት የምዝገባም ሆነ የስብሰባ ፈቃድ ተሰጥቶን አያውቅም። (በ’ርግጥ  ኢህአዴግ፤ በኋላ ላይ ሊጉን በጉልበት አፈረሰው) ወጣትነት ደፋር ያደርጋል። የመሰብሰብ እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታችንን መንግስት እንዲሰጠን ስላልፈለግን እኛም በህዝብ ጉልበት መብታችንን አስከበርን። ከምንም በላይ ግን፤ “መንግስት መብት ይሰጥሃል እንጂ፤ መብትህን አያስጠብቅልህም።” የሚለው መመሪያችን ተስማምቶናል። እውነት ነው። መንግስት መብትህን በህግ እና በህገ መንግስት ላይ ጽፎ ይሰጥሃል እንጂ፤ መብትን የማስጠበቅ ሃላፊነት የሚጣለው በ’ያንዳንዱ ግለሰብ እና ማህበረሰብ ላይ ይሆናል።
መሰረታዊ መብቶቻችን በህጉ እና በህገ መንግስቱ ላይ እንዲሰፍሩ ትውልድን የተሻገረ ትግል ተካሂዷል። እነዚህን መብቶች በውድም ሆነ በግድ ተግባራዊ ስናደርግ፤ አምባገነናዊ አስተዳደር እየወደቀ፤ የዲሞክራሲ ቀለም እየደመቀ ይሄዳል። ከሽግግሩ መንግስት እስከ ችግግሩ ዘመን ድረስ የሄድንበት መንገድ… የግል እና የወል መብትን የማስጠበቅ ታሪክን የያዘ ባለብዙ ምእራፍ ታሪክ ነው። በሁሉም ምእራፎች መብታችንን ለመጨፍለቅ ጥረት ሲደረግ እንጂ ስንወድቅ አልታየንም። አሁንም ከመጨረሻው ምእራፍ በፊት የመጨረሻውን ጩኸት እየጮሁ፤ “በህግ አምላክ!” የሚሉ ደፋሮች አልታጡም። የ’ነሱ ጩኸት ከዳር እስከዳር እንዲደመጥ፤ የለኮሱት ሻማ ብርሃን እንዲሰጥ… የዲሞክራሲ ቀለሞች በብዕሮቻቸው ጫፍ እንዲደምቅ ለሚያደርጉት ትግል ህዝቡ ሊያግዛቸው ይገባል። 
በአጠቃላይ ከሽግግር መንግስት እስከ ችግግር ዘመናችን ድረስ ብዙ ግዜ ወድቀን፤ ብዙ ግዜ ተነስተናል። በዚህ የቀራንዮ መንገድ ላይ ብዙዎች ወድቀው ቀሩ፣ ሌሎች መንገዳቸውን ቀየሩ። አንዳንዶች ሞቱ፤ ሌሎች ታሰሩ፤ ቀንበሩ የከበደን አገር ለቀን ተሰደድን። እንዲህም ሆኖ ከያለንበት የምንጮኸው ወድቀን እንዳልቀረን ለማብሰር ጭምር ነው። የዲሞክራሲ ቀለሞች እስከሚደምቁ ድረስ ድምጻችንን እናሰማለን። እንደዘፈን አዝማች፤ “መንግስት መብት ይሰጥሃል እንጂ፤ መብትህን አያስጠብቅልህም።” እንላለን። ጎበዝ! እንግዲህ ለራስህ እወቅበት።
 
(ይህ ጽሁፍ ከወራት በፊት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚታተመው አዲስ ገጽ ጋዜጣ ላይ ወጥቷል። ጽሁፉ በተዘጋጀበት ወቅት፤ በኦሮሚያ ተጀምሮ በአማራ ክልል እየተቀጣጠለ ያለው፤ ህዝባዊ አመጽ አሁን ያለበትን አይነት መልክ ገና አልያዘም። ይህ ጽሁፍ ሰሞኑን የተዘጋጀ ቢሆን ኖሮ፤ የ’ነዚህን ህዝባዊ አመጾች ቀለም ያካትት ነበር። አሁንም ቢሆን “መንግስት መብት ይሰጥሃል እንጂ፤ መብትህን አያስጠብቅልህም። መብቱን የሚያስከብረው እያንዳንዱ ዜጋ በግል፤ ህብረተሰቡን በወል ሆኖ ነው።” የሚለው ቀለም ደምቆ ወጣ እንጂ አልደበዘዘም። ስለሆነም ከትላንት እስከዛሬ በሰላማዊ መንገድ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ለነበሩ፤ በዚህ ሂደትም መስዋዕት ለሆኑ ውድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ… ይህ ጽሁፍ ለነሱ መታሰቢያ ይሁንልን። ክብር ለ’ነሱ ይሁን!)
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 8 years ago on August 26, 2016
  • By:
  • Last Modified: August 26, 2016 @ 11:48 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar