www.maledatimes.com የነፃነት ዘይቤ! በሰሎሞን ተሠማ ጂ.(semnaworeq) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የነፃነት ዘይቤ! በሰሎሞን ተሠማ ጂ.(semnaworeq)

By   /   October 2, 2012  /   Comments Off on የነፃነት ዘይቤ! በሰሎሞን ተሠማ ጂ.(semnaworeq)

    Print       Email
0 0
Read Time:37 Minute, 42 Second

“ነፃ-አውጪ” ነን ባዮችና “የነፃነት ታጋዮች/ተጋዳላዬች” ናቸው የሚባሉት ወገኖች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ለአብነት ያህል እንኳን “ሕወሐት- ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ” (ወያኔ)፣ “ሕሐኤ- ሕዝባዊ ሐርነት ኤርትራ” (ሻዕቢያ)፣ “ኦነግ- የኦሮሞ ነፃነት ግንባር”፣ “ኦብነግ- የኦጋዴን ብሔራዊነፃነት ግንባር”፣ “ግ7ፍነን- የግንቦት 7፣ ለፍትሕና ለነፃነት ንቅናቄ”፣ “እኦነግ- የእስላማዊ ኦሮሚያነፃነት ግንባር (ጃራ)”፣ “አሕነግ- የአማራ ሕዝብ ነፃነት ግንባር” እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህም “ነኢጦ- ነፃየኢትዮጵያዊያን ጦር” የሚባል እንቅስቃሴም ስለመኖሩም ተሰምቷል፡፡ ከወያኔ በስተቀር፣ ብዙዎቹ “በሽብርተኝነት” የተፈረጁ ድርጅቶች ናቸው፡፡ የብዙዎቹም ድርጅቶች አመራር አባላት አንድም በውጭ አገር ስደት ላይ ናቸው፣ ወይም በዱር-በገደል ስለነፃነታቸው በመታገል ላይ ናቸው፡፡ ቀን የጎደለባቸውም የነዚህ ድርጅቶች አባላት ገሚሱ ሲሰው፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ለእስርና ለግዞት ተዳርገዋል፡፡
ለመሆኑ እነዚህ ድርጅቶች “ነፃነት” ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? የኤርትራ ሐርነት/ነፃነት  ሲባል ኤርትራን መገንጠልና ማስገንጠልም እንደነበረ በይፋ ታይቷል፡፡ የፈረደበትን ምኒሊክንና የአድዋ ድልን የተቀዳጀውን ኢትዮጵያዊ ሠራዊት ለምን ከጣሊያን ቅኝ-ገዢ “ነፃ-አላወጣንም” በሚል መረራ-ቂምና ብስጭት ተነሳስተው ነበረ፣ ወደነፃነት የተደረገ ትግል ነው ያሉትን ደም-አፋሳሽ ጦርነት ያካሔዱት፡፡ ስለዚህም፣ ምኒሊክና የምኒሊክ ነው ያሉትን ሁሉ ለማፈራረስ መራራ ጦርነት አካሂደው በመጨረሻም “ነፃ-ወጣን” አሉን፡፡ የሆነው ሆኖ፣ “የትግራይ ሐርነት/ነፃነት”፣ ወይም “የኦሮሞ ነፃነት”፣ “የአማራ ነፃነት”፣ ፣ ስንል ምን ማለታችን ነው? ከማነው አማራው፣ ትግሬውና ኦሮሞው ነፃ የሚወጡት? እንዴትስ ነው ነፃ የሚወጡት? እንዚህንና እነዚህን መሰል ጥያቄዎች በእጅጉ ያስነሳል፡፡ ስለሆነም የነፃነትን ሙሉ ትርጉም (ዘይቤ) እንድንጠይቅም ያስገድደናል፡፡
ከሁሉ አስቀድመን፣ ኢትዮጵያም በጥንታዊነታቸው ከታወቁት አገሮች መካከል የታወቀች አገር መሆኗን እናስታውስ፡፡ በጥንታዊነታቸውና በሥልጣኔያቸውም የታወቁት አገሮችና ህዝቦች መለዮ “ትእምርት” አላቸው፡፡ ለአብነትም ያህል፣ የግብፃዊያን መለዮ “ትእምርታቸው” ስነ-መለኮት ነው፡፡ የሄሮግላፊክስ ጽሑፎቻቸውና ፒራሚዶቻቸው ከታች ወደ ላይ ነው የሚወጡት፡፡ ከምድር ወደ ፀሐይ ሽቅብ ይወጣሉ፡፡ ፀሐይ እንደተባዕት፣ ምድርም እንደእንስት ናቸው፡፡ ፍጥረታትም/ሕያዋንም ሁሉ ከሁለቱ ተራክቦ/ግብረ-ንክኪ ተወልደው አርአያ ጽላሎት ይሆናሉ፡፡ ፀሐይ፣ ምድርና ፍጥረታት ባንድነት ተፃምረው ሥላሴ ይሆናሉ፡፡ የአባት፣ የልጅና የመንፈስ ቅዱስ “ትእምርት” መሰረቱ የግብፃውያኑ ስነ-መለኮት ነው፡፡ አለቀ-ደቀቀ!
ጥንታዊያኑ ግሪካውያንም የሚታወቁበት ልዩ “ትእምርት” ከሥነ-ፍጥረትና የፍጥረታቱን መልካምነት አይተው በመፈላሰፍ ዝንባሌያቸው ነው፡፡ በኦሪት ዘፍጥረት የመጀመሪያው ምዕራፍ፣ አራት ጊዜ ተደጋግሞ የተፃፈው “ወርአየ እግዚአብሔር ከመ ሠናይ” ወይም “እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ፤” (ኦሪት ዘፍ. 1/13፣19፣25፣31) በሚለው ሃተታ ተነሳስተው፣ “መልካሙን ሁሉ ለመድገም” በፅርዓዊ የእውቀት ጎዳና ስለሔዱ ገናና ሆኑ፡፡ በሥልጣኔ የቀደሟቸውን ሕዝቦች መጽሐፍት ማንበብና መቅዳትም ጀመሩ፡፡ የሥነ-ፍጥረታትንም አምሳያ በሥዕል መሳል፤ በንድፍም መንደፍ፤ በቅርፃ-ቅርፆችም መቅረፅ፤ ሕንፃዎችንም ማነጽ ጀመሩ፡፡ የሠሯቸው ሁሉምመልካም እንደሆኑ አዩ፡፡ ተደነቁም፡፡ የመልካምነትም ምንጩ ረቂቅ ሃሳቦችን መመራመር ነውና በጂኦሜትሪ፣ በትሪጎኖሜትሪ፣ በስነ-ጽሑፍና በሌሎችም ጥበቦች ተጠቃሽ የሆኑትን ሃይለ-ሃሳቦች ለዓለም መምህራኖች በር-ከፋች በመሆን አስተዋወቁ፡፡ ጎዳናውን በሰፊው ጠረጉ፡፡ ፋናውን ከፍ አድርገው ወጉ፡፡
የሮማውያን መለያ “ትእምርታቸውም” የዓለምን ሕዝብ ለመግዛትና ለማስተዳደር መነሳሳታቸው ነበር፡፡ መጀመሪያ ኃይልን ይጠቀማሉ፤ ሁለተኛም ሕግን ተመርኩዘው አገዛዛቸውን ለማጠናከር የመጣራቸው ዘዴ የታወቀ ነው፡፡ “እሺ!” ብሎ ለተገዛላቸው “ይቅር ባዮች” ሆኑ፤ “እንቢ!” አንገዛም ላሏቸው ደግሞ ተበቃዮችና ጨፍጫፊዎች መሆናቸው ልዩ ትእምርታቸው ሆነ፡፡ በየካቲት 12 ቀን 1928 ዓ.ም የፈፀሙት ግፍ ከዚሁ “መለዮአቸው” የመነጨ ጭፍን የጨፍጫፊነት አባዜያቸው ነበር፡፡
አልገዛም ባዮቹ ኢትዮጵያዊያን ግን ራሳቸውን “ብሔረ-አግአዚያን” ብለው ሰይመው፣ “ነፃነት” ልዩ “ትእምርታችን” ሆነ፡፡ ኢትዮጵያዊያን “ለኔ ከዘላለም ባርነት፣ ይሻለኛል የአንድ ቀን አርነት!” ብለው የመጣውን ወራሪ ሁሉ ቅስሙን ሰበሩት፡፡ “ብሔረ-አግአዚነት” ከቅጽልነትም አልፎ፣ የኢትዮጵያዊያን ተጸውዖ ስም ሆነ፡፡ “ኢትዮጵያ” ማለት “ብሔረ-አግአዚ”፤ “ብሔረ-አግአዚም” ማለት “ኢትዮጵያ” ማለት ሆነ፡፡ “አግአዚ” ማለት የአድራጊነት ስም ነው፡፡ ምንም ነውር የለበትም፡፡ ቃሉ ግዕዝ ነው፤ ትርጉሙም “ነፃ-አውጪ/አጋዥ” ማለት ነው፡፡ትግሪኛው ከግዕዙ የተዋሰው ቃል እንጂ መሰረቱ “ግዕዛን” ነው፡፡ (የኪዳነ ወልድ ክፍሌን፣ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ፣ ገጽ 327፤ እና የደስታ ተክለ ወልድን፣ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት (1962) ገጽ 148 እና 293 ይመልከቱ)፡፡ (የዛሬዎቹን የፖለቲካ ብልጣ-ብልጦችና በትራቸው የሆነውን “የአግዐዚ ምንትስ” የተባለውን “ነገር” ጨርሰን እንተወው፡፡ ጊዜያዊ ነው፡፡)
ይህንኑ ስሜት ለማጠናከር፣ ቅድስ ያሬድ ሐዋርያው ጳውሎስን ጠቅሶ “ኢኮነ ነግድ ወፈላሴ፣ ሀገሪቶሙ ለቅዱሳን ንሕነ ሰብአ ቤቱ ለእግዚአብሔር ኩልነ” ይላል (ኤፌ 2/29)፡፡ የኢትዮጵያዊ ተፈጥሮ መግለጫ ተብሎ የተደረሰ ያሬዳዊ ዜማ ነው፡፡ “ኢትዮጵያ ሆይ ደብተራ ግዕዛን” ነሽ ሲልም ዜማውን ያሳርገዋል፡፡ (“የነፃነት ድንኳን ነሽ”፣ ማለቱ ነው፡፡) ታዲያን ለዚህች “ነፃነት” መለዮዋ ለሆነች አገር የምን “ነፃ-አውጪ” ነው የሚያስፈልጋት? እራሷ የነፃነት መንትያ ለሆነች አገር ከወዴት ነው “ነፃነት” ተጭኖ የሚመጣላት? ስለዚህም “በነፃነት ዘይቤ” ዙሪያ በቅጡ መነጋገር አለብን፡፡ እጅግ አሳሳቢና ብርቱ ጉዳይ ነው፡፡ ይዋል – ይደር የማይባል ጉዳይ ነው፡፡……….
ጆን ሎክ የተባለው ፈላስፋ፣ “ተፈጥሮአዊ በሆነው ሰብዓዊ ነፃነትና በመንግስታት ተጽዕኖ ስር ባለው ሰብዓዊ ነፃነት” መካከል ሰፊ ልዩነት መኖሩን ያብራራል፡፡ “ሰው በተፈጥሮው ሙሉ ነፃነትን ተጎናጽፎ ቢፈጠርም ቅሉ፣ ሰው ባለው የማህበራዊ ግጭት ዝንባሌው የተነሳ መንግስትን በላዩ ላይ አቋቋመ፡፡ በዚህም ሳቢያ ተፈጥሮአዊ የሆነውን ነፃነቱን ተገፈፈ፤” ይላል (Two Treaties of Government):: እንደጆን ሎክ አባባል ከሆነ፣ “ተፈጥሮአዊ የሆነ ሰብዓዊ ነፃነት ያለው “ሰው”፣ በገዛ ነፃ ፈቃዱ ለራሱ ደህንነትና ለራሱ ሰላም ሲል፣ በሕጋዊ አኳኋን ሕግንና መንግስትን ወደሚያቆምበት ውል/ስምምነት (contract) ዘው ብሎ ገባ፡፡” ከዚያን ጊዜ ጀምሮም፣ ተፈጥሮአዊው ነፃነቱን በመንግስት ቁጥጥር ስር በሚገደብ ነፃነት ተካው-ይለናል፡፡
ለፍሬድሬክ ሄግል፣ “ነፃነት ማለት ከግለ-ባይተዋርነት ተላቆ፣ ከፍተኛውን የሕሊናዊነት ብቃት መጎናጸፍና እግዚአብሔርን በታሪክ ሕሊና ውስጥ ማወቅ መቻል ነው፡፡” በክርስቲያናዊ አስተምህሮት ውስጥ ለተማረው ሄግል፣ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 8/32 ላይ ያለው ሃተታ፣ “እውነትም አርነት/ነፃ ታወጣችኋለች” ልዩ ትርጉም አለው፡፡ አምላካዊ እውነትና ነፃነት ለሄግል የአንድ አላድ ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ እውነትን ማወቅ ነፃነትን ማወቅ ነው፡፡ በመሆኑም፣ ሄግል መንግስትን የሚያየው በመለኮታዊ ሃይል የተጫነ ወኪል (Agent) አድርጎ ሲሆን፣ ይህም የእግዜር ወኪል፣ የሰው ልጅን እድገትና ነፃነት ለመጠበቅ በአምላክ የተሰጠ ሃይል ነው፣ ሲል ይሟገታል (Hegel, G.W.F; The Philosophy of History)፡፡
ሄግል እንደሚለው ከሆነ “ነፃነት ከድንቁርናና ከብዥታ አርነት ወጥቶ የላቀ ዕውቀትን የማግኘት ጸጋ ነው፡፡” ሆኖም ይህንን የሄግል ሃሳብ ጆን ስትዋርት ሚል አይቀበለውም፡፡ ሚል እንደሚገልጸው ከሆነ፣ የነፃነት ጠንቅ የሆነው “የብዙኃኑ አምባገነንነት” በግል-ነፃነት ላይ ሲጫን ነው፡፡ ምናልባትም፣ የብዙኃኑ ሕገ-ደንብ (Code of Conduct) ለግለሰቡ ምክንያት-አልቦ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም የብዙኃኑ አፈናና ጭቆና ከፖለቲካዊ ጭቆናና አፈናም የባሰ የማይሆንበት ምክንያት እንደሌለ፤” ይገልፃል (On Liberty, ገጽ 126-145)፡፡
የጆን ስትዋርትን ሚልን ሃሳብ በምሳሌ እናለሳልሰው፡፡በብዙኃኑ/በጎሳው አምባገነንነት የሚመራ አንድ ግለሰብ በግዳጅ ከዘራ ወይም ምርኩዝ እንዲይዝ ሊገደድ ይችላል፡፡ እድሜው ከዘራ ለመመርኮዝ ደረሰም-አልደረሰ፣ የእግሩና የወገቡ ጤንነት ምርኩዝ ቢያስፈልገውም-ባያስፈልገው የብዙኃኑ/የጎሳው ሕገ-ደንብ ነውና ከዘራ/ምርኩዝ መያዝ ግዴታው ነው፡፡ አለበለዚያ፣ በጎሳው/በብዙኃኑ ዘንድ እንደአፈንጋጭ ወይም ወፈፌ ተቆጥሮ የግል-ነጻነቱን በአጓጉል ሁናቴ ይገፈፋል፡፡ አልፎ ተርፎም በድንጋይ ሊወገር ወይም ሊገደል ይችላል፡፡ ይኼው ነው፡፡
ሚል እንደ ጋሊሊዮ ጋሊሊና እንደ ሶቅራጥስ ያሉትን ግለሰቦች “ነፃነት” ልናከብር የምንችለው፣ የእያንዳንዱን በነፃ የማሰብ፣ የመናገር፣ ሃሳብን የመግለጽና የፈለጉትን የማከናወን ግላዊ ነፃነቱ ሲከበር እንደሆነ በተደጋጋሚ ያብራራል፡፡ ኢየሱስ “ያለ ወንጀሉ” የተሰቀለው በዚሁ የብዙኃኑ/የአይሁድ ካህናት አምባገነንነት እንደነበረም በምሳሌ ያትታል፡፡ በመሆኑም በግለ-ነፃነት ላይ፣ የብዙኃኑ አምባገነንነት ከፖለቲካዊው ጭቆና የባሰና የከፋም እንደሆነ ያምናል፡፡ ስለዚህም፣ “የማሰብ ነፃነት ለምንጠላውም ሃሳብ ጭምር” አስፈላጊ እንደሆነ የአሜሪካን ሕገ-መንግስትም ይደነግጋል (Freedom of thought for the thought that we hate) እንዲል፡፡
ኤማ ጎለድማን የተሰኘችው ሩሲያዊትም፣ “በዜጎች ላይ የተጫነውንና የተዋቀረውን የሹማምንትና የባለሥልጣናት የተዋረድ እርከኖችን ለመናድ አብዮት/አመጽ አስፈላጊ ነው” ትላለች፡፡ ለኤማ በስርዓት-አልበኝነት ተቋማዊ በሆነው የሹማምንቶች ተቋም ላይ ማመጽ አግባብነት አለው፡፡ ምክንያቱም፣ “የዜጎችን የእምነትና ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት የሚሸረሽረው ማንም ሳይሆን ተቋማዊ የሆነው ኃይል ነውና” ብላ ታምናለች፡፡ በተጨማሪም፣ ኤማ የሄግልን “መለኮታዊነት የተላበሰችውን መንግሥትንም” ሆነ የጆን ስ.ሚልን “የብዙኃኑን አምባገነናዊነት” ሙሉ ለሙሉ የሰውን ልጅ የእኩልነት መብት ይነፍጋሉ ስትል ታጣጥላቸዋለች፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ፣ የኤማ የነፃነት ዘይቤ ከስርዓት-አልበኝነትና በተቋማዊ ገዢዎች ላይ ከማመጽ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የኤማ ዘይቤ በመሠረቱ ስር-ነቀል ነው፡፡
ጆን ሎክ፣ “ተፈጥሮአዊ የሆነውን የሰው ልጅን ነፃነት “መንግሥት” የሚባል ብል በላው” – ሲል ይንገበገባል፡፡ ሄግል በበኩሉ፣ “መንግሥት” ማለት መለኮታዊ የሆነ የነፃነትና የእድገት ወኪል ነው፡፡ “ሰውን ከባርነት ነፃ የሚያወጣው እውነትን ማወቁ ብቻ ነው” ሲል ይሟገታል፡፡ ጆን ስትወርት ሚል በበኩሉ፣ የነፃነት ፀሯ “መንግሥት” ሳይሆን “የብዙኃኑ አንባገነንነት ነው” ሲል ይከራከራል፡፡ ኤማ ጎልድማንም፣ የሄግልንም ሆነ የሚልን ሃሳቦች አጣጥላ ስታበቃ፣ “የነፃነት ፀር” የሆነው በሹማምንትና በባለስልጣናት የተዋረድ እርከን የተዋቀረው ተቋማዊ “ነገር ሁሉ” ነው ስትል ትደመድማለች፡፡ ስለሆነም፣ “በሃይል/በአብዮት ወይም በአመፅ የነፃነት ፀር የሆኑት ተቋማት በሙሉ መወገድ አለባቸው” ትላለች፡፡
በሌላ በኩል፣ የማህተማ ጋንዲ የነፃነት እሳቤና ፍልስፍና የምዕተ-ዓመቱ ብቸኛ ንጥረ-ሃሳብ ነው፡፡ ጋንዲ እንዳስተማረው ከሆነ፣ “ነፃነት ስነ-ልቦናዊ ነው፤ ከድንቁርናና ከፍርሃት ጽልመት አርነት የሚወጡበት፡፡ አልቦ-ፍርሃትና እውነተኛነት ወደ ድል የመራሉ፡፡ ስለሆነም፣ ለውጥ አንድን ሕዝብ ከአመጽና ከጭቆና ነፃ የሚያወጣ ስነ-ልቦናዊ ሃይል ነው” (Selected Political Writings of Mohandas K. Gandhi):: በጥቅሉ፣ ጋንዲ ፖለቲካዊ ነፃነት የሚመነጨው ከግለሰባዊ ነፃነትና በያንዳንዱ ሰው የሕይወት ተሞክሮ ውጤትነት እንደሆነ ያምናል፡፡ “ነፃነት ማለት ራስን-ወደ-ማወቅ (journey to self-realization) የሚደረግ ጉዞ ነው” ሲልም ይደመድማል፡፡ ስለሆነም፣ ለጋንዲ “የነፃነት ዘይቤ” ማለት ከሰላማዊ ትግል ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡
በማስከተልም የምናየው የማሪቲን ሉተር ኪንግ (Jr./ትንሹን) የነፃነት ዘይቤ ነው፡፡ ማርቲን “ታላቅ እርምጃ ወደ ነፃነት” (Stride Toward Freedom፡ The Montgomery Story) የሚል በጽሐፍ እስከመጻፍም ደርሶ ነበር፡፡ በዚህ መጽሐፉ ውስጥ ስለነፃነት ሦስት ብያኔዎችን አስቀምጧል፡፡ አንደኛ፣ “እውነት አርነት/ነፃ ታመጣችኋለች፤ ማለትም፣ ሁላችንም የእግዚአብሔር ልጆች ነንና ከሃጢያትና ከመነጣጠል አርነት የምንወጣው እውነትን ብቻ በመከተል ነው” ሲል ይሰብካል፡፡ በሁለተኛነትም፣ የማይቃረነውንና ዘመናዊውን የሎክንና የሚልን የነፃነት እሳቤ ያስተጋባል፡፡ “የብዙኃኑን አንባገነንነት” ለፍትህና ለእኩልነት መታገል ይገባል ሲልም ያትታል፡፡ በመጨረሻም፣ ማርቲን ከማህተማ ጋንዲ የቀሰመውን የሰላማዊ ትግል ስልትና በእርሱ ዕዝነ-ልቦና ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ጭምር በመጽሐፉ ውስጥ አካቷል፡፡ ይህም መጽሐፍ በሞንትጎመሪ የተደረገውን የአውቶቡስ አለመሳፈር አድማ በተሳካ ሁኔታ አነሳስቷል፡፡
ጆን ሎክ፣ ሄግል፣ ሚልና ኤማ የነፃነትን ጠላቶች ውጫዊ አድርገው ሲያስረዱ፤ ጋንዲና ማረቲን ሉ/ኪንግ ደግሞ የነፃነት ጠሮች ውስጣዊ ናቸው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የሁለቱን ወገን ሙግት ለማስታረቅ የሞከረውና ተጠቃሽ የሆነው “የነፃነት ዘይቤ” የሰር አይዛያ በርሊን (Sir Isaiah Berlin) በ1969 የሳተመው፣ The “TWO CONCEPTS OF LIBERTY”  የተሰኘው ጥናታዊ ጽሑፍ ነው፡፡ በዚህ ጥናቱ ውስጥ ነፃነትን በሁለት ጎራ ይከፍለዋል – አዎንታዊ ነፃነት(Positive Freedom)ና አሉታዊ ነፃነት(Negative Freedom) ናቸው ይላል፡፡
“በአዎንታዊ ነፃነት” ሰው የራሱ ጌታ ነው፡፡ የራሱ አዛዥና ናዛዥ “ሰው ራሱ” ነው፡፡ ከዚህ ተመለስ የለበትም፡፡ “እኔ እንዲህ ነኝ!” ወይም “እንዲህ መሆን እፈልጋለሁ፤ ማድረግም እችላለሁም!” እያለ የራሱን እድል በራሱ ይወስናል፡፡ ለምሳሌ፣ “እኔ ትግሬ ነኝ፡፡ ጥህሎ የሚባል ገንፎ አለኝ፡፡ እርሱን መመገብ እፈልጋለሁ፡፡ ልሸጠውም ስለፈለግኩ በሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ በጋዜጣና በፖስተርም ማስተዋወቅ እፈልጋለሁ!” ብል ማንም ከልካይ የለብኝም፡፡ ወይም ደግሞ፣ “እኔ ሙስሊም ነኝ፡፡ አንዋር መስጊድ ወይም አወሊያ መስጂድ ሦላት ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ መንዙማዬን እዘይራለሁ፡፡ ጌ-መድረሳ ከፍቼ ሕፃናት ማስተማር እፈልጋለሁ፤” ብል ማንም ከልካይ የለብኝም፡፡ ወይም ደግሞ አንድ ቀን ተነስቼ፣ “እኔ ሙርሲ ነኝ፡፡ ስለሆነም፣ እራቁቴን እሄዳለሁ፡፡ ከፈለኩም ደግሞ የግልገል ቆዳ ገፍፌ አገለድማለሁ፡፡ ያንንም፣ አገር አቋርጦ ለመጣ ጎብኚ/ቱሪሰት አሳየዋለሁ፤” ብል ማን ከልክሎኝ!? ምክንያቱም፣ በትግሬነቴ ወይም በሙስሊምነቴ ወይም ደግሞ በሙርሲነቴ ባህሉና እምነቱ በግሌ-ለግሌ ያጎናፀፈኝን ነፃነት መንግስትም ሆነ ሌላው ተቋም አይነፍገኝም! ለምን ብሎ?! ለማንስ ፋይዳ!? ይኼንን አዎንታዊ ነፃነቴን ማንም ሆን ብሎ አይነካው፡፡ ቢፈልግ እንኳን ትርፉ ኢምንት ነው፡፡
ሆኖም ግን አሉታዊ የሆነውን ነፃነቴን ለመጠቀም ስነሳ መፈናፈኛም አላገኝ፡፡ አሉታዊ ነፃነቴ በሌሎች መልካም ፈቃድ ስር ነው፡፡ ሌሎች ጌቶች አሉብኝ፡፡ ለምሳሌ፣ “እኔ ትግሬ ነኝና የትግራይን ልማት ነፃና ገለልተኛ ድርጅት አቋቁሜ ላለማው እፈልጋለሁ፡፡ የትግራይ ሕዝብን መብት ለማስጠበቅ እታገላለሁ፡፡ ወይም ትግራይን ለማዘመን እፈልጋለሁ!” ብል ገዢዎቹና ሹማምንቶቻቸው “ምናባክ ቆርጦህ! ማነኝ ብለህ?!” ሲሉ እስከመጨረሻዋ ጠብታ ድረስ ይፋለሙኛል፡፡ ወይም ደግሞ “እኔ ሙስሊም ነኝ፡፡ የራሴን ወኪሎች መጅሊስ አቋቁማለሁ፡፡ የራሴን ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ጋዜጣ እንዲሁም ድረ-ገጽ ከፍቼ ሃሳቤን እገልፃለሁ፤” ብል ጨሰ-አቧራው ጨሰ ይባላል፡፡ አለዚያም፣ “እኔ ሙርሲ ነኝና የራሴን መብት በራሴ እወስናለሁ፤ የራሴን ወረዳ በራሴ ወታደሮች አስጠብቃለሁ፡፡ የራሴን ወረዳ ዕድል በራሴ እወስናለሁ….!” ብል ማንም ለአፍታ እንኳን አይታገሰኝም፡፡ የዚህም ጊዜ፣ “መጀመሪያውኑስ እንደ ሙርሲነትህ እንድታስብስ ሆነ የራስህን ቋንቋና ባህል እንድታስተዋውቅ የፈቀድንልህ እኛ አይደለንም እንዴ!? አንተ ከየት አመጣኸው!?” እባላለሁ፡፡ ነፃ ጋዜጣ፣ ነፃ ሬዲዮ ጣቢያም ሆነ ነፃ ማህበር ስለማቋቋም ጉዳይማ “አሉታዊ ነፃነትን የሚፈቅዱት ወገኖች በጭራሽ አይታገሱኝም፡፡ “ሃሳቡን ራሱን ስለሚፈሩትም ነቅተው ይጠብቁታል” – ይላል አይዛያህ በርሊን፡፡
ለማጠቃለያነት የምጠቅሰው ሌላኛው ጥናት በቢ.ኤም.ላይንግ (1929፡480) የተጻፈውን “Freedom and Determinism” በተባለውን ጥናታዊ ጽሑፍ ውስጥ ያለው ሃይለ-ሃሳብ ነው፡፡ እጠቅሳለሁ፣ “Freedom is quite frequently asserted to consist in the power of choosing, and to be evidenced by the fact of choice. In the process of willing there is a stage where two or more lines of action lie open to the individual; after comparing the two or more lines, s/he comes to a decision that one is better than the other, or the one is the best.” የምን ትርጁማን ወይም መተርጉማን ያስፈልገዋል?እንግሊዝኛ ለሚያነብ ሰው ሁሉ መልዕክቱ ግልጽ ነው፡፡ እስከ ቀጣዩ ሳምንት ድረስ – ቸር እንሰንብት!!!
ማሳሰቢያ፤በዌብሳይታችን ላይ ለሚወጡ ማናቸውም ጽሁፎች ቀዳሚ የሆነ የዌብሳይታችንን አርትኦት ስራን ለማክበር ሲባል በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በማለዳ ታይምስ የመረጃ ማእከል ® ላይ ለሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የማለዳ ታይምስ የመረጃ ማእከል ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዌብሳይቱን  ጠቋሚ (አመልካች ) (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.maledatimes.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን(የማለዳ ታይምስ ህግና ደንብ በንግድ በተመዘገቡበት ሁለት አገሮች የረቀቀ ሲሆን በሁለቱም አገሮች አንድ አይነት የሆነ አሰራር ይዞ ይከተላል ።ይህንን ህግ ማንኛውም ሰው መቅዳት የማይችል መሆኑን እንገልጻለን።ንብረትነቱ እና ህገ ደንቡ የማለዳ ታይምስ ብቻ ነው!)፡፡ይህ ካልሆነ ግን በህገ ደንባችን መሰረት አስፈላጊውን የህጋዊ ጥያቄ ለማቅረብ የምንገደድ መሆኑን እንጠቁማለን::በዚህ አጋጣሚ በግለሰብ ለሚላኩ ጽሁፎች ሁሉ ተጠያቂው ስሙ የተገለጸው ግለሰብ እንጂ የማለዳ ታይምስ መረጃ ማእከል ሃላፊነቱን እንደማይወስድ እናሳስባለን ::
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on October 2, 2012
  • By:
  • Last Modified: October 2, 2012 @ 10:35 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar