www.maledatimes.com ፍትሐት (ለአቶ መለስ የተደረገው ፍትሐት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እይታ) ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ፍትሐት (ለአቶ መለስ የተደረገው ፍትሐት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እይታ) ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

By   /   October 4, 2012  /   Comments Off on ፍትሐት (ለአቶ መለስ የተደረገው ፍትሐት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እይታ) ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

    Print       Email
0 0
Read Time:102 Minute, 21 Second

ፍትሐት (ለአቶ መለስ የተደረገው ፍትሐት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እይታ) ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ click here maledatimes.com/pdf
(ለአቶ መለስ የተደረገው ፍትሐት በኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እይታ)
ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ
nigatuasteraye@gmail.com
መስከረም ፳፻፭ ዓ.ም.
(የተደበተውን ነገር ቀስቅሶ እንደሚያስነሳ አውሎ ነፋስ፤ የአቶ መለሰ ሞት የብዙ ሰዎችን ስሜት ቀስቅሶ ብዙ የተለያዩ ሐሳቦችን እያነሱ እንዲነጋገሩ አድርጎ ሰንብቷል። እኔም በኢትዮጵያዊነቴና በተለይም በኦሪቱ ለስልሶ በክርስትና ተቀርጾ ከሁለት ሽህ ዓመታት በላይ እየተጓዘ ከኛ የደረሰውን ኢትዮጵያዊውን ስነ መለኮትና ስነ ልቡና ሲመረምሩ ሕይወታቸውን ባሳለፉት ኢትዮጵያውያን እቅፍ በማደጌ፤ ከነሱ የሰማሁትን በልደት፡በጥምቀትና በሞት ላይ የተመሰረተውን ኢትዮጵያዊ ስነ ልቡና ለመግለጽ ይህ ጊዜ መልካም አጋጣሚ መስሎ ስለታየኝ፤ ይህችን ጦማር ለመላ ኢትዮጵያውያን አቀረብኳት።)
መግቢያ
ኅብረተ ሰብ፤ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያለ ኅብረተ ሰብ የድርሰቶች ምንጭ ነው። የቅኔ ሰወችም አንህብት ሆነው ቅኔያቸውን ለመስራት የሚቀስሙት አበባ ነው። እርቦን ምግብ ለማግኘት ኮፌዳችንን ይዘን ወደ መንደር ስንወጣ፤ “የምትሄዱበት ህብረተ ሰብ ምንጭነቱ ለአካላዊ ምግባችሁ ብቻ አይደለም። ሕዝቡ የሚሰጣችሁን ምግብ ለመቀበል ኮፌዳችሁን ብቻ አትክፈቱ። ለአዕምራችሁም ምንጭ ነውና ለምትቆጥሩት ቅኔ ሰም ለመቅሰም፤ መስነቅተ አዕምሯችሁንም ክፈቱ” መምህራን ይሉን ነበር። ቅኔ ለመቀመር ሀሳብ ሲያጥረን አዕምሯችንም ማመስጠር ሲያቅተው፤ ሰም ሆኖ የሚያገለግለን የሚያሳዝን ያሚያስተክዝ የሚያስቅና የሚያስደስት ነገር ለመፈለግ ወደ መንደር ጎራ እንል ነበር።

2 እሬት በበዛበት፤ ግራዋ ከተንሰራፋበት አካባቢ ጣፋጭ ማር ማምረት እንደማይቻል አሁን አገራችንና ቤተ ክርስቲያናችን ካሉበት ሁኔታ ደህንነት ሰላምን ጤንነትንና መረጋጋትን የሚያንጸባርቅ ቅኔ ማፍለቅ አይቻልም እንጅ፤ በዚህ ዘመን ያሉ የቅኔ ዘራፊወችና ተማሪዎች ቅኔ ለመዝረፍና ለመቀመር ምስጢር እየፈሰሰ ነው።
የአቡነ ጳውሎስና የአቶ መለስ ባንድ ሳምንት መሞት የሀዘንና የትዝብት፤ የድንጋጤና የመገረም ስሜት በመቀላቀል ህዝቡን ሲያምሰው ከመሰንበቱ ጋራ፤ የኢሀደግ መንግስት ይህን መታመስ ላቶ መለሰ ፍቅርና አክብሮት እንደተደረገ አስመስሎ የኢትዮጵያዊነትን ስሜት ለማይረዳው ዓለም ለማቅረብ እንደሞከረ፤ የቤተ ክርስቲያናችንን ስርዓት አስወግደው አቶ መለሰ የፈጠሩትን የፖለቲካ መርሆ በመከተል ላይ ያሉት አንዳንድ የዘመናችን ጳጳሳትም፤ በክርስቶስ አምኖ፤ የበደለውን ይቅርታ ጠይቆ፤ ንስሀ ገብቶ፤ ቆርቦ ለተሰናበተ ክርስቲያን በሚደረገው የክብር መሸኛ፤ አቶ መለሰን አማኝ ክርስቲያን አድርጎ ለውጭ ተመልካች ለማቅረብ ሲሉ ብቻ፤ ከአቶ ስብሀት ነጋና ከገብረ ኪዳን ደስታ ጋራ በመተባበር በቤተ
ክርስቲያኒቱ ላይ የዘመቱትን የአቶ መለሰን ሬሳ ‘በክብር’ ወደ ግብአተ መሬት ሸኝተውበታል።
በቀደሙ መሪዎቿ አማካይነት ብዙ ታሪክ የተመዘገበላት እንደ ኢትዮጵያ የመሰለችውን ጥንታዊት አገር፡ ካንድ መንደርና ጎሳ ባንድ ወቅት ተጠራርተው መጥተው ለ፳፩ አመታት በዓለማዊውና መንፈሳዊ አስተዳደር ሲያተራምሱ የነበሩ ሰዎች ተጠራርተው በመጡበት መንገድ በተፈጥሮ ሞት ተገደው ባንድ ሳምንት ሲለቁ፤ ዓለም ያነበው ዘንድ የኢትዮጵያዊነትን ስነ ልቡና ከፈተው። በአሜሪካዊቷ Susan Rice  እና በአውሮፓዊቷ Ana Gomez (ሐና ጎበዜ) መካከል ተከስቶ እንደታየው፤ በባእዳን ታዛቢወች ላይም ሳይቀር የተራራቀና የተለያያ ግንዛቤ ፈጥሯል። እነ አቶ ስብሀት ነጋ ባሰለጠኗቸው አስመሳዮች ቤተ ክርስቲያናችን ባትወረር፤ “ወበዛቲ ዕለት ካዕበ አዕረፈ”እያለ ሰንክሳራችን መዝግቧቸው የሚነበቡት
ተአምራትና ትንግርቶች ሁሉ፤ አሁን በቤተ ክርስቲያናችንና በአገራችን ከሚታየው ፈታኝ የበለጡ አስገራሚዎችና አነጋጋሪዎች አይደሉም።
የኛናታችንን ስነ ልቡና ያስነበበው የነ አቶ መለስ ግብአተ መሬት ይህን መሳይ አስመሳይ ትንግርት ሲፈጥር፤ ከዚህ ባነሱ ነገሮች እየተደነቁ ቅኔውንና ጽሑፉን ያፈልቁ የነበሩ ሊቃውንት ስታፈራ የኖረችው ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬ አንድ ሰው እንኳ ይበል የሚያሰኝ በስንክሳራችን ቅኔ ወይም ጽሑፍ የሚያስመዘገብ መጥፋቱ፤ “ኦርቶዶክስንና አማራን ሰበርነው” ብለው በአማራው ህብረተ ሰብና በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ስብሀት ነጋ የፎከሩትን የሚያረጋግጥ ይመስላል። (‘የነ ፋሌቅ ወጥመድ’ በሚል ርዕስ
ከአሁን በፊት ያቀረብኳትን ጦማር የሚቀጥለውን በመጫን ይመልከቱ http://www.ethiomedia.com/2012_report/yene_faleq_wetmed.pdf)
ከሰናፍጭ ቅንጣት ባነሰችው አቅሜ በቤተ ክርስቲያናችንና በአገራችን ያለፉትን በንጽጽር ስመለከት፤ የሚሰማኝን በተደራረበ አካል እንደተፈጠረ ቀይ ሽንኩርት መሳይ ኢትዮጵያዊው ቅኔያችን ባቀረብኩት እጅግ በረካሁ ነበር:: ግን ይበልታ ማሰማት የሚችሉ የቤተ ክርስቲያኑቱ ልጆች አንገታቸውን የደፉበት ዘመን ስለሆነ ቅኔውን ትቼ ወደ አማረኛው ስነ ጽሑፍ እሻገራለሁ። የጦማሯ መነሻ በቪዲዮ የታየው የአቶ መለስ ግብአተ መሬት የተሸኘበት ፍትሐት ነው። ቤተክርስቲያችን ይህን አይነት የመሸኛ ፍትሐት የምታደርገው መመሪያዋን ፈጽመው ለሚሸኙ አማኞች ነው። በቦታው ላይ ተገኝተው ስነ ስርዓቱን የፈጸሙ ሰዎች ከኢ.ኦ.ተ. ቤተ ክርስቲያናችን መርሆ ውጭ መሆናቸውን ለመጠቆም ነው:: እግር
መንገዴንም ከሞት ጋራ የተገናኘውን ኢትዮጵያዊውን ስነ ልቡና እና ህዝባዊውን (በኢትዮጵያ ባህል) አሸኛኘት ካየሁት ከጎረቤት አገር ጋራ በማነጻጸር ለማቅረብ ነው።
o ፍትሐት ምንድነው?
ክፍል ፩
o የኢ.ኦ.ተ. ቤተ ክርስቲያን መመሪያ
o ሕጉን ለፈጸሙ ክርስቲያኖች የሚደረግ የክብር መሸኛ3
o በመጽሐፍ ላይ የተመሰረተው ኢትዮጵያዊ ባህላዊ ፍትሐት
o ለኢ.ኦ .ተ. ምእመናን የተሰጠ መመሪያ
ክፍል ፪
• ኬንያ ላይ የገጠመኝ
• መደምደሚያ
በነዚህ አንቀጾች ያዘጋጀኋትን ይህችን ጦማር ፍትሐት ምንድን ነው? በሚለው አንቀጽ እጀምራለሁ።

ፍትሐት ምንድነው?

የፍትሐት ትርጉም መለያየት ነው። ከጸሀይ በታች በዚህች ምድር እንደገና የመገናኘትን ተስፋ ጨርሶ በሚዘጋው ሞት የሚደረገውን መሸኛ ኢትዮጵያዊው ነገረ መለኮት (ፍትሐት) ፍች ብሎታል። ዘመድ፤ አዝማድና ወዳጅ በአካለ ሥጋ ሲለያየ ፍትሐትን በትርጉሙ ተክተን ተለያየን እንላለንን። ትዳር ሲፈርስ፤ ገብያ ሲበተን፤ አገር ሲናጋ ተፈታ እንላለን። ለምሳሌ በኤርትራ፤በአሰብና በኢትዮጵያ፤ እንደገና ለ፺ አመታት ለባእዳን በተሰጡ መሬቶችና እየተፈናቀሉ በፈለሱት ኢትዮጵያውያን ዜጎች መካከል ያለው ሁኔታ ፍትሐት ይባላል። እንግዲህ ፍትሐት የሚለው ቃል ለከባድ ነገር የምንጠቀምበት መሆኑ ነው።

በሞት የተከሰተውን ከባድ መለያየት የምናከናውንበትን ስርዓት ፍትሐት የሚለውን ቃል የሰሩልን ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አበው “ወነአምር ከመ ለእመሂ ተነስተ ቤተ ማሕደርነ ዘበምድር ብነ ሕንጻ በኅበ እግዚአብሔር በሰማያት ዘኢገብሮ እደ ሰብእ”(፪ ቆሮ ፭፡፩) ከሚለው ማለትም፦ የየነፍሳችን ማደሪያ የሆነው ምድራዊ ሥጋችን፤ አንድም የነፍስና የሥጋችን ማደሪያ የሆነው የዚህ ዓለም ኑሯችን በሞት ቢፈርስ ሰማያዊ ቤት አለን የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን ቃል ካብራሩበት ቃል በመንደርደር ነው። ቅዱስ አትናቴዎስም በሞት በመበታተን ስለሚፈታው አካላችን “ዘከመ ኀብሩ ፬ቱ ጠባያት ውስቴቶሙ መንፈሰ ህይወት እንዘ ኢይኀብር እሳት ምስለ ማይ ወመሬት ምስለ ነፋስ ፡ ወእግአዚአብሔር ከሀሊ ገብረ ዘንተ
ኩሎ አስተናቢሮ ዘከመ የአምር”(ሃ፡ አ፡ ምዕ ፳፰፡፴፩፡፴፪)። ይህም ማለት፦ የማይስማሙትን እሳትንና ውሀን ነፋስንና አፈርን ፬ቱን ጠባያት አስማምተህ በውስጣችን የህይወት እስትንፋስህን ሰጥተህ ፈጠርከን”  እንዳለው፦ ዲዮናስዮስ የተባለው ሊቅም “እስመ ክዋኔሁ ለሰብእ ውእቱ እምግብራት እለ ኢይትማሰሉ በበይናቴሆሙ ወኢየኀብሩ”(ሃ፡ አ፡፺፱፡፳) ብሎ እንዳጠናከረው፤ ተሰርተንባቸው ሰው ያደረጉን ባህርያት ተለያይተው ወደ ሸክላነት የተለወጠውን ሰውነት ወደ ግብአተ መሬት የምንሸኝበት ስርዓት፤ ፍትሐት ተባለ።
ኦርቶዶክዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ስርአቷን ጠብቀው ለሞቱ ሰዎች ብቻ የምታከናውነውን በእግዚአብሄር ለማያምን ለነፍሰ ገዳይና ንስሀ ሳይገባ ለሞተ ሰው እንዳይደረግ ቤተክርስቲያናችን የምታዝዘውን ማስጠንቀቂያ ከዚህ በታች ለማሳየት እሞክራለሁ።

4
ክፍል ፩፦ ኢትዮጵያዊዩ መንፈሳዊና
ባህላዊ ግንዛቤ
፩(ሀ). የኢ.ኦ.ተ. ቤተ ክርስቲያን መመሪያ
ከላይ የተገለጹትን መመሪያዎች ከማይፈጽሙ ሰዎች ጋራ ቤተ ክርስቲያናችን ምንም አይነት ንክኪ እንዳይኖራት “ኢትትወከፍ መብአ እምነ ሐራዊ ግዙፈ ልብ ወኢእምነ ነሀቢ ሰራቂ፡ወኢ እምነ ነጋዲ መሐሊ በሀሰት በእንተ ረባህ ወኢእምነ ሰዱቃውያን ጸራፊ ወዐላዊ ወኢእምነ ባዕል ዘይሰክይዎ  አግብርቲሁ ከመ ውእቱ ኢትሁቦሙ መፍቅዶሙ”(ሃ.አ. ፳፪።፮-፲) የሚል መመሪያ አላት። ይህም ማለት “ቀፈተ ልቡን በብዝኃ ኃጢአት አደንድኖ፤ የንስሀ ስሜት ለሌለ፡ በተደጋገመ ጭካኔ ነፍስ መግደልን፡መዝረፍን፡ በሀሰት መማልን ፡መዋሸትንና ሰው መዝለፍን የመሳሰሉትን ከሚፈጽም ሰው መባ (ገንዘብ)  አትቀበል።
ማነኛውም ክርስቲያን በዚህ ስርዓት እንዲኖር “ዛቲ ይእቲ ሃይማኖት ቅድስት እንተ ሰርእዋ ወወሰንዋ አበው በሀገረ ኒቅያ ትኩን ብርሃነ ለእለ ኢተምህሩ ከመ ያእምሩ ምንት ምክንያቱ ዘውስተ ክፍላት እንተ ለኩሉ ነገር ይእመኑ ቦቱ”(ሃ.አ. ምዕ ፲፱፡፲፩)::: ማለትም፦ “ክርስቲያኖችን እንድትመራበት በኒቅያ የተሰበሰቡ ሰለስቱ ምዕት የወሰኗት ናት።”
ቤተ ክርስቲያናችን አባላቷ ከዚህ መመሪያ ዝንፍ ሳይሉ በጥምቀት የጀመሩትን ክርስቲያናዊ ሕይወት በመቃብር እንዲፈጽሙ “ፍኖት ርትዕት እንተ ትወስድ ለገቢረ ሠናይ ዘ ንትዌደስ ባቲ በደኃሪትነ ወከመ ይህንጹ ደሀሪትነ በሠናይ ሕንጻ ላዕለ መሰረት ጽኑዕ ዘኢያንቀለቅል እንተ ይርቲ ሕንጻ መምህራን ትሩፋን ወባቲ ናጽንዕ ሃይማኖተነ እስከ ተፍጻሚተ ህይወትነ” (ሃ. አ.ምዕ ፻፰፡፳፫) ማለትም፦ “በዘመናችን ፍጻሜ የምንመሰገንባትን በጎ ስራ ለመስራት የምታበቃንን መንገድ ለማግኘት ወደ ቀናች ሃይማኖት እንድንመራ ፍጻሜያችን በማይናወጥ በጸና ሃይማኖት ላይ በተመሰረተ በጎ ምግባር እንድንጸና ፍጹማን መምህራን ያስተማሯት ትምህርት ናት። እስከ ዘመናችን ፍጻሜ ድረስ በሷ እንጽና።” ብሎ መመሪያችን ያስጠነቅቃል።
በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች ህሊናቸው ለሚወቅሳቸው በደል ፈጥነው ሃላፊነቱን በመውሰድ የበደሉትን ሰው ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው። ከይቅርታ በኋላ በተበደሉበት ምክንያት የበቀል ርምጃ መውሰድም ፈጽሞ ክልክል ነው። ክርስቶስ ትሁት፡ መሐሪ፤ ሰው አክባሪና አፍቃሪ ቢሆንም፤ ከኃጢአት ጋራ ህብረት የሌለው ቅዱስ አምላክ ነው። ክርስቶስ የማይወዳቸው የኃጢአት አይነቶች የሚፈጸሙት በትእቢት በጭካኔ፤ እግዚአብሔር በአርያው የፈጠረውን ሰው በመናቅና በመጥላት መንፈስ ስለሆነ፤ ህሊናችንን ከእነዚህ በማስወገድ፤ ድንጋይ ተሸክመን፤ ራሳችንን ዝቅ አድርገን ከበደልነው ሰው እግር ስር በመውደቅ ይቅርታ መቀበል አለብን። ክርስቲያን ከሆን በኋላ ከላይ
የተዘረዘሩትን በደሎች በሰው ላይ ፈጽመን የክርስቶን አማላጅነት መንተራስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስተዋህዶ ስነ መለኮት አይቀበለውም።
፩(ለ). የኢ.ኦ.ተ. ምእመናን

5
ክርስቲያናዊ መመሪያ
ማንንም ሰው በኃጢአት ከሚመጣ ፍርድ ነጻ የሚያወጣው እውነት ነው። እውነት የምትለካው ለራሳችን ሊደረግልን በምንፈልገውና በራሳችን ሊደረግብን በማንፈልገው ነገር ነው። ይህንንም “እውነት እኔ ነኝ” እያለ የተናገረው የክርስትና እምነት መስራች የሆነው ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የክርስቶስ ተከታይ የሆነ ሁሉ ክርስቲያን ለእውነት ጠበቃ ለመሆን ከክርስቶስ ጋራ በጥምቀት ለሀሰት ሞቶ፤ከክርስቶስ ጋራ ለጽድቅ (ለእውነት) የቆመ ነው። ቅዱስ ያዕቆብ “እውነትን ለይቶ አውቆ ለማያደርገው ኃጢአት ነው”(ያዕ ፬፡፲፯) እንዳለው፤ ከበደልና ከኃጢአት አንዲት ነጥብ እንዳታመልጠው በመቃተት ዕድሜውን ያሳለፈ ሰው ይቅርና፤ ሰዎች የፈጸሙትን በደል አውቀን እንዳላወቅን፡ አይተን እንዳላየን፡ሰምተን እንዳልሰማን ሳንናገርና ልክ አይደለም ሳንል ያሳለፍን እያንዳንዳችን ክርስቲያኖች ሁሉ፤ ቅዱስ ያዕቆብ በተናገረው መሰረት ኃጢአተኞች ነን።
• ሆኖም ክርስቲያኖች በደል የፈጸሙትን ሰዎች ባለመገሰጻቸው በደለኞች ቢሆኑም፤ ተስፋ ቆርጠው ጠፍተው እንዳይቀሩ ክርስቶስ የከፈተላቸው በር አለ። “ከመ ኢይስህት መኑሂ በስህተተ ኃጢአት ዘውእቱ ቀቢጸ ተስፋ ዘበአማን። እስመ ቀቢጸ ተስፋ እምስህተተ ሰይጣን ውእቱ። ወይሬስዮ ለሰብእ ከመ ይበል አልቦ ትንሳኤ ለግሙራ፡ ወኢመንግስተ ሰማያት ወኢኩነኔ ለግሙራ; ማለትም፦ተስፋ በመቁረጥ ጠፍቶ እንዲቀር ተስፋ መቁረጥ በሰው ልቡና የሚዘራ ሰይጣን ነው። ከዚያም ባሻገር ጽድቅና ኩነኔ የለም ወደሚለው ሀሳብ ጎትቶ በመክተት የበለጠ ኃጢአተኛ ያደርጋልና፤ የተሳሳተ ክርስቲያን ፈጥኖ ወደ ራሱ ህሊና በመመለስ ንስሀ መግባት አለበት።” አለ ዮሐንስ አፈወርቅ። (ሃ፡አ፡ ምዕ ፷፭፡ ፳፫)
• “እለ ሀለው ህየ ጻድቃነ ሙቁሐነ በኃጢአተ አዳም አቡሆሙ ወአንስአነ በጽድቀ ትንሣኤሁ እምነሙታን ወአርሀወ ለነ ኆኃተ ንስሐ” ማለትም፦ባባታቸው አዳም በገባው የኃጢአት ብክለት ምክንያት ቅዱሳን ክርስቲያኖች ቢወድቁ፤ ክርስቶስ ወድቀው እንዳይቀሩ ተጠንቆቆላቸዋል። ይህም ህሊናቸው ለሚወቅሳቸው አዕምሯቸው ላልዘነጋው ኃጢአትና በደላቸው ትእቢትን በማስወገድ ራሳቸውን ዝቅ አርገው አምላክንና ሰውን ይቅርታ በመጠየቅ ተመልሶ የመቆምን በር ንስሀን ከፈተ” አለ ቅዱስ ጎርጎርዮስ (ሃይ ምዕ ፴፮፡፴) ።
• “እምቅድመ ህልፈተ ዕለት ናፍጥን ወንግድፍ ርእሰነ ቅድሜሁ እንዘ ንብል አበስነ በቅድሜከ . . . . ንትባደር ለንስሐ”(ሃይ አበ ው ፶፯፡ ፲፩) በፊትህ በድለናል ይቅር በለን ብለን ክርስቶስ በከፈተልን ንስሀ በጸጸት በጸሎትና በስግደት ከአምላካችን ፊት በመውደቅና የበደልናቸውን ይቅርታ በመጠየቅ የምንሞትባትን እለት መቅደም አለብን” ሲል ሌላው ቅዱስ ተናገረ።
• “ኢታጽንኡ ልበክሙ ኢትትሀከዩ ወኢትኩኑ እንበለ ተስፋ በእንተ መድኃኒነ ሶበ ንኤብስ ለእግዚአብሔር ኩሎ ዕለተ ንትነሣእ እንከ ለንስሐ እንዘ ሕያዋን ንሕነ በውስተ ዝ ዓለም” (ሃ
አበው ፷፭፡፲፮) እግዚአብሔር የማይቀበለውን ሰው ያሳዘነውን በደል ሰርተህ ልብህን በማደንደን የበደልከውን ይቅርታ ሳትጠይቅ ደቂቃ አታሳልፍ” ብሎ ቅዱስ ዮሐንስ አጥንክሮ ተናገረ።
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት መመሪያወች፡ የመሸኛው ፍትሐት ለሚፈጸምለት ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን፤ በህወቱ ሳለ ሊያደርጋቸውና ሊፈጽማቸው የሚገቡ የህይወት መመሪያወች ናቸው።

፩(ሐ). ሕጉን ለፈጸሙ ክርስቲያኖች የሚደረግ
የክብር መሸኛ
ከምዕራባዊው ክርስትና ትምህርትና እምነት የኦርቶዶክስን ትምህርትና እምነት ልዩ ከሚያደርጋቸው አንዱ፤ የልደት የጥምቀት እና የሞት ተቆላላፊ ምሥጢር ነው። ሰው ከማያውቃቸውና ካልመረጣቸው ወላጆቹ ያለ አንዳች ግንዛቤ ወደ ዚህ ዓለም እንደ ሚመጣ ሁሉ፤ ያለ አንዳች ግንዛቤ በማያውቃቸው ሰወች እቅፍ ወደ ጥምቀት መጥቶ፡ በማያውቃቸው ሰዎች የማያውቀው የጥምቀት ምስጢር በመቃብር ይፈጸምበታል። (ሮሜ ፮ ፡፩-፲፩ ) ኢትዮጵያዊውያን ሁላችን እምነታችንን ታሪኩንንና ባህላችንን በእቅድ በታትኖ በሚያሳይ ዘዴ አይቅረብልን እንጅ፤ የክርስትና መሰረታውያን የሆኑትን የስላሴን አንድነትና ሶስትነት የክርስቶስን መድኃኔዓለምነት “ከሕጻንነትህ ጀምረህ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን መዳን
የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻህፍትን አውቀሀል። ከማን እንደተማርከው ታውቃለህ”(፪ ጢሞ ፫፡፲፫-፲፭) እንደተባለው እንደ ጢሞቲዎስ፤ ከቤተ ሰቦቻችን እየተማርን አድገናል።
በተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለልጆች የሰንበት አስተማሪዎች ወላጆች ናቸው።
• ከዚያም እንደ ዛሬው Globalization ከውጭ በሚያመጣው አሰር ገሰስ ሳይቀላቀልበት ከቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር ከሚኖሩት መናኞች ጀምሮ በየመንደሩ በምናየው ንጹህ ኢትዮጵያዊ ስነ ልቡና እያደበርነው እናድጋለን። በዚህ መንገድ “የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ እያወቅን ኃጢአት ብናደርግ ክርስቶስ ያማልደናል ማለት ክርስቶስን እንደጋና መስቀል” መሆኑን እንማራለን (ዕብ ፲፡፳፮)።
• በክርስትና የመጽደቅን ፍላጎት በህሊናችን ካሳደርን በኋላ እንደገና ክርስቶስ የማይወደውን ኃጢአት ዝሙትን ስርቆትን ሀሰትንና ነፍስ መግደልን የመሳሰሉትን እየሰራን ክርስቶስ
ያማልደኛል ማለት ክርስቶስን የኃጢአት አገልጋይ አንዳደረግው ይሰማናል። (ገላ ፪፡፲፯)
• ህይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ ከተቃራኒ ጾታወች ጥምረት የሚመነጭ ቢሆንም ፤እግዚአብሄር ሰባዊ ጥምረትን በህገ ተፈጥሮ መስርቶ እንደገና በወንጌል አጠንክሮ በማወጅ ደግሞታል። ጋብቻ በፈቃድ ከምንቀበለው ከምንኩስና በላይ የተከበረ ነው። ከተቀደሰው ጋብቻ ውጭ የሚደረግ ሩካቤ፤ በተዋህዶ በከበረው ቅዱስ ሰውነት ላይ ኃጢአት መቅረጽ ነውና ለዚህም ክርስቶስ አያማልድም። (፩ኛ ቆሮ፮፡ ፲፰ )
• ማንም ክርስቲያን ለጣኦት ከተሰዋ ከዝሙትና ከደምና ሞቶ የተገኘ ሥጋ ከመብላት የተከለከለ ነው (የሐ ፲፭፡፳፱)።
• እያወቀ ኃጢአት የሚያደርግ ክርስቲያን ሁሉ ክርስቶስን በግብሩ አላውቅህም ብሎታል ና የዲያብሎስ ሰራዊት እንጅ ከክርስቶስ ጋራ ምንም የተዋህዶ ዝምድና የለውም (፩ኛዮሐ ፫፡፬-
፲)።
• ሐዋርያት “ኃጢአታችሁ ይሰረይላችሁ ዘነድ ንስሐ ግቡ” (የሐዋ ፪፡፴፯) እያሉ እንዳስተማሩ ማነኛውም ክርስቲያን ራሱን እየፈተነና በንስሀም ህሊናውን እየታዘበ ሥጋውንና ደሙን መቀበል አለበት (፩ኛ ቆሮ ፲፩፡፳፯)።
• በዚህ ዓለም ስንኖር፤ ከመቃብር ተሻግሮ የሚመጣውን ዘላለማዊ ህይወት “መንግሥትህ ትምጣለን”(ማቴ ፮፡፲) እያልን በጸሎት የምንመኘውን ህይወት በመለማመድ እንቆይና፤ ከዚህ ዓለም በሞት ስንለይ ወደ ከርሰ ምድር ለመውረድ በሰው ትክሻና እቅፍ የሚደረገው የአሸኛኘት ፍትሐት ሳናውቀው ይፈጸምብናል።
ሰው ወደ ዚህ ዓለም ሲመጣ በህብረተ ሰቡ የታሪክ ስንክሳር የጻፈው ነገር ስለሌለ የሚነበብለት ዝክረ ነገር የለውም። ያለ አንዳች ግንዛቤ በማያውቃቸው ሰወች እቅፍ ወደ ጥምቀት መጥቶ፡

በማያውቃቸው ሰዎች ከክርስቶስ ጋራ ሞቶና ተቀብሮ መነሳቱን የሚገልጸው የጥምቀት ምስጢር እንደታወጀበት፤ ኑሮው ሲበተን አካሉ ሲፈርስ ትዳሩ ሲፈታ በፍትሐት ወደ ማይመለስበት ዓለም ይሸኛል። በህብረተ ሰቡ አእምሮ ጽፎ ያስቀመጠው ከፉም ሆነ ደግ ሳይቀነስበትና ሳይጨመርበት መልካሙ ይነበብለታል፤ መልካም ያልሆነው ይነበብበታል።
፩(መ). በመጽሐፍ ላይ የተመሰረተው  ኢትዮጵያዊ የባህል ፍትሐት  የደስታና የሀዘን መግለጫዎቻችን ሁሉ ኢትዮጵያውያን ክስተቶች ከአምልኮታችን ያልራቁ በቅዱሳት መጻህፍት ላይ ከተመሰረቱ ከስነ መለኮት ጥናታንችን ጋራ የተሳሰሩ ናቸው። ለማስራጃ ሶስቱን  እጠቅሳለሁ።
o ፩ኛ፡ የሰውን ሞት ስንሰማ ደንግጠን የግል ተግባራችንን እርግፍ አርገን ጥለን በህብረት ወደ
ቀብር መሮጣችን፤
o ፪ኛ፡ በቀብራችን ሥርዓት እጃችንን መታጠባችን።
o ፫ኛ፡ በጥለት ተጀምሮ በጥለት የተደመደመው ኩታችን ከምዕራቡ ክርስትና የምንለይበትን
አምልኮታችንን፤ የትርጓሜ ስልታችንን፤ በሀዘንና በደስታ የሚፈራረቁብንን ኩነቶች የምንገልጽበት ነው።
በእነዚህ ነጥቦች ውስጥ ተካተው ያሉት ስነ ባህል፡ ዓለም አቀፋዊ እውቀትና የንጽጽር ነገረ መለኮት በሚሰጥባቸው ዩኒቨርሲቲዎች የማናገኛቸው ናቸው። በአገራችንም ታትመው ከቀረቡት ያንድምታ መጻህፍቶቻችንም የማናገኛቸው እንደነ የኔት ፍስሀ ከመሰሳሉት ጥቂት ሊቃውንት አበው ጭንቅላት የነበሩና አብሯቸው የተቀበሩ ናቸው። በነዚህ ነጥቦች ላይ ተመስርተው ለዘመናት በኢትዮጵያ ሲደረጉ ስለኖሩትና አሁንም ሲደረጉ ስለምናያቸው፤ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት በተዘረጋው ፖለቲካ ለሚናጠው ትውልድ ለምሳሌ ያህል ጥቂት መግለጹ ተገቢ ይመስለኛል።
1ኛ. የሰውን ሞት ስንሰማ የግል ተግባራችንን እርግፍ አርገን ጥለን በህብረት ወደ ቀብር መሮጣችን፤በመጽሀፈ ጦቢት ተመዝግቧል። ጠላትም ይሁን ወዳጅ ዘመድ ሞተ የሚለውን ቃል ስንሰማ ሁሉን ጥለን የምንሄደው የተጠየቅነውንም ሁሉ ያላንዳች ማቅማማት የምንሰጠው፤ ”ወአንተኒ አመ ትቀብር አብድንተ። አሜሃ ሀሎኩ ምስሌከ፡ ወእመኒ ኢተሐየይከ ወተንሣእከ ኀዲገከ ምስሀከ።
ወሆርከ ትቅበር በድነ፡ ወኢረሳእከ ገቢረ ሠናይ አሜሃ ሀሎኩ ምስሌከ”(ጦቢያ ፲፪፡፲፫) ይህም ማለት፦ “ሰው ሞተ ተብሎ ስትሰማ ደንግጠህ ልትጎርሰው በጣትህ የያዝከውን እርግፍ አርገህ ለቀብር መጣደፍህን አልተውክም ይህንንም ተገቢ የሆነ አገልግሎትህን ባለመተውህ ካንተ ጋራ ነበርኩ” የተባለው በሚገባ ተሰብኮ በደማችን ሰርጿል።
2ኛ. በቀብራችን ሥርዓት እጃችንን መታጠባችን። ከቀብር በኋላ እጃቸውን የሚታጠቡት አፈሩ ሲመልሱ የነካቸውን እድፍ ጉድፍ ለማጽዳት አይደለም። ትዝ ይበለንና በቀብሩ ላይ ቆሞ ከራሱ ሞት ጋር ሲታገል የነበረ ሁሉ ይታጠባል። ምክንያቱም በኦሪቱ ”ይትሀጸቡ እደዊሆሙ . . . . ይንብቡ ወይበሉ ኢከአዋ እደዊነ ደሞ ለዝንቱ ወአዕይንቲነ ኢርአያ(ዘዳ ፳፩፡፭᎗፰) የሚል ትእዛዝ አለ። ይህም ማለት ሰው ሞቶ ቢገኝ እንዴት እንደሞተ አናውቅም አልገደልነውም ከደሙ ንጹሀን ነን” ለማለት ነው። በተለይ በመግደል በመደብደብ በማሰርና በማሳደድ ላይ ያሉ ሰዎች ድንገት ሞተው ሲገኙ፤ ኢትዮጵያዊውን ሁሉ በደሙ የገባው ባህል እጁን በመታጠብ ስሜቱን
እንዲገልጽ ያስገድደዋል።

3ኛ. በጥለት ተጀምሮ በጥለት የተደመደመ ኩታችንን ሴቶች ጥለቱንና ጥለቱን አጋጥመው በማጠፍ ከራሳቸው ላይ ጣል አርገው፤ ወንዶችም በትክሻቸው ላይ ደርበው ይወጣሉ። ይህም በኦሪቱ ”ይግበሩ ዘፈረ ውስተ ጽንፈ አልባሲሆሙ በመዋዕሊሆሙ ወይደዩ ውስተ ዘፈረ ጽነፊሁ ደርከኖ ፍቱለ፡፡ ወትሬእይዎ ወትዜከሩ ኩሎ ትእዛዞ ለእግዚአብሔር” (ዘኁል ፲፭፡፴፮᎗፴፰) ማለትም፦ የእግዚአብሔር ሰዎች በጫፉ ላይ ጥለት ያለበት ኩታ ልበሱ። ጥለቱን ባያችሁ ጊዜ ትእዛዜን ታስታውሳላችሁ” ባለው መሰረት በመነሻውና በመድረሻው ጥለት ያለውን ኩታ አገናኝተን በማጠፍ በትክሻችን ላይ አድርገን “አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህ”(ዘፍ ፫፡፲፱) የሚለው ትእዛዝ በማስታወስ የዚህ ዓለም ኑሮህ ታጠፈ እያልን እናነባለን። የኩታው ሁለንተና ብሉያቱንና ሀዲሳቱን አጠቃሎ ይወክላል። የእግዚአብሄርን ቃልና ትእዛዝ የሚያስታውሱን በዳርና በዳር ያሉ ጥለቶች ሌላም ምልክት አላቸው። ይህም ብሉይ ኪዳን “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድር ፈጠረ”( ዘፍ ፩፡፩) እንዲል፤ የመጀመሪያው ሰማይንና ምድር አልፎ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ”(ራዕ ፳፩፡፩) እንዳለው የሚተካውን ያሳያል። በሁለቱ ጥለቶች መካከል ያለው ዝሀውና ማጉ በባህል በቋንቋ በሰውነት በተፈጥሮ ተቆላልፎና ተወሳስቦ የሚኖረውን ህይወታችንን ያመለክታል።
4ኛ. ከምዕራቡ ክርስትና ከምንለይባቸው ብዙ ነገሮች አንዱ ስርአተ አምልኮታችን ነው። ኩታችን ቃሉን በሚያስታውሰን በጥለት ተጀምሮ በጥለት እንደሚፈጸም፡ ስርአተ አምልኳችንም “ሰውን ከምድር አፈር አበጀው”(ዘፍ፪፡፯) በማለት የሚጀምረውን ብሉይ ኪዳን ለማንጸባረቅ በስግደት እንጀምራለን።“አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህ”(ዘፍ ፫፡፲፱) የሚለውን ለማንጸባረቅም በስግደት እንፈጽማለን። በስግደት ተጀምሮ በስግደት የሚደመደመው አምልኮታችን በተፈጥሮ ላይ የተመሰረተ የክርስትና ጥምቀታችንን ምስጢር የተሸከመና ሰውነታችንን እያንጸባረቀ የአምላካችንን ዘላለማዊነትና ኃያልነት የሚገልጽ ነው። በመነሻውና በመድረሻው ጥለት ያለውን ኩታ አገናኝተን በማጠፍ በትክሻችን ላይ አድርገን “አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህ”(ዘፍ ፫፡ ፲፱) የሚለውን ትእዛዝ በማስታወስ የዚህ ዓለም ኑሮህ ታጠፈ እያልን እናለቅሳለን። “ለልቅሶ ጊዜ አለው”(መክብብ ፫፡፬) ብሎ ሰሎሞም የተናገረውንም ባንድምታቸው አምጥተው ይተረጉሙታል።
ክርስቶስም “የልቅሶ ዜማ አቀነቀንላችሁ አላለቀሳችሁም” (ማቴ ፲፩፡፲፯) ሲል በወቀሳና ክስ ንግግር መልክ የተናገረውን ጊዜ ከሚጭንብን ልቅሷችን ጋራም የኩታችን ዘርፍ ተገናኝቷል።
ጎጃም አዘነ የተባለው ልብስ የኩታን ቦታ የተካበትን የዛሬውን አያርገውና ይህ ኢትዮጵያዊ አለባበሳችን ለህይወት መጨረሻ ፍታት እንደምንጠቀምበት ሁሉ የህይወት ምንጭ (መጀመሪያ) የሆነውን የተቀደሰውን ጋብቻ እናከብርበታለን።
የእግዚአብሄርን ቃልና ትእዛዝ በሚያስተውሰን ጥለት ተጀምሮ ሰማይና ምድር ያልፋል ቃሌ ግን አያልፍም የሚለውን የመደምደሚያውን ጥለት አጋጥመን ዓለም ታጠፈችበት እያልን የሞተብንን ሰው እንደምንሸኘው በደስታችንም ጊዜ ጥለቱን በእጃችን ይዘን እየወዘወዝን “አብበው አሽተው እስኪያፈሩ ድረስ፤ሞትና በሽታ ከመንገድ ተመለስ” እያልን የህይወት ምንጭ፡ በክርስቶ ስና በምእመናን መካከል ያለውን ምሥጢር የሚያንጸባርቀውን ቅዱስ ጋብቻን እናከብርበታለን። “ለዘፈን ጊዜ አለው” (መክ ፫፡፬)ሲል ሰሎሞን የተናገረውን ያብራሩታል። ክርስቶስም “የዘፈን ዜማ አቀነቀንላችሁ፡ አልዘፈናችሁም” (ማቴ ፲፩፡፲፯) ብሎ በተናገረው ያጎላምሱታል።
የአምልኮታችንን ሥርዓት አካቶ የያዘው መጽሀፈ ቅዳሴያችን እንደሚያመለክተው አምልኮታችንን የምንጀምረው “ዘአንሣእከነ እምድር” ማለትም፡ አፈር ነበርኩ ከአፈር ሰራሀኝ እያልን
ወድቀን እንነሳለን። እንደገና “ወአልአልከነ እመሬት” በሞት ብወድቅም እንደገና በትንሳኤ ታነሳኛለህ እያላን እንሰግዳለን። በመጨረሻማ ለሶስተኛ ጊዜ “ ከመ ታንብረነ ምስለ መላእክቲከ ወምስለ መላእክተ  ሕዝብከ”(ሥ፡ ቅ፡ ገ፡ ፱ ቍ ፳፭) ይህም ማለት ከቅዱሳን ከመላእክት ጋራ በመንግስተ ሰማይ ለዘላለም ታከብረናለህ እያልን ወድቀን እንነሳለን። ቄሱ “ስብሀት ወክብር ለስሉስ ቅዱስ ይደሉ” ለሚለው አምልኮታዊ ማቀንቀን “ይደለዎሙ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ” እያሉ ምእመናኑ እየሰገዱ በመመለስ የሚያከናውኑት ማህበራዊ አምልኮት በሶስትነትና ባንድነት የምናመልከውን የአምላካችን ባህርይና የኛን ሰባዊ ተፈጥሮ ያንጸባርቃል።
እነ ቅዱስ አትናቴዎስ “ዘከመ ኀብሩ ፬ቱ ጠባያት ውስቴቶሙ መንፈሰ ህይወት እንዘ ኢይኀብር እሳት ምስለ ማይ ወመሬት ምስለ ነፋስ ፡ ወእግአዚአብሔር ከሀሊ ገብረ ዘንተ ኩሎ አስተናቢሮ ዘከመ የአምር”(ሃ፡ አ፡ ምዕ ፳፰፡፴፩፡፴፪) እያሉ የተናገሩትን ማለትም፡ የማይስማሙትን እሳትንና ውሀን ነፋስንና አፈርን አስማምተህ ፬ቱን ጠባያት አዋህደህ የፈጠርከን እያልን እንደምናመልከው፤ ፍትሐት የምንለው መሸኛችንም የነዚህን መበታተን መለያየትና መፈራረስ የሚያመለክት ህብረተሰቡ በሞት በተለየው አካል የሚውጀው የተፈጥሮ አዋጅ ነው።
በአቶ መለስ ፍትሐት ላይ ሙሽሮችም ነበሩበት ተብሏል። ይህንንም ኢትዮጵያዊው የነገረ መለኮትና የስነ ልቡና ጥናት ሳይዳስሰው እንደቀላል ነገር በመመልከት ታዝቦ አያልፈውምና እንደሚከተለው ይገልጸዋል። “ወርእዩ ደቂቀ እስራኤል ወተበሀሉ በበይናቲሆሙ፡ ምንት ውእቱ ዝ? እንዳኢ”(ዘጸአት ፲፮፡፲፭):: ማለትም: ከደመና እየወረደላቸው ስለሚበሉት መና ከየት እንደመጣና እንዴት እንደተዘጋጀ ባለማወቃቸው እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። መልሱን ባለማግኛታቸውም ስሙን ‘መና’ አሉት። ‘መና’ ማለትም ‘ይህ ነገር ምንድነው’ (ምንት ውእቱ) ማለት ነው። መልሱ ግን ‘እንዳኢ’ (እንጃ ኧረ) በተለምዶ አማረኛችን “እንጀራ” ማለት ነው። ሙሽሮቹ እየተመገቡ ስላሳደጋቸው እንጀራ ቢጠየቁ የሚመልሱት
በግእዙ እንዳኢ ባመረኛ እንጃ ኧረ ወይም እንጀራ ነው። እንደዚሁ ሁሉ ሙሽሮቹ በሙሽራ ልብሳቸው በአቶ መለስ ፍትሐት ላይ መገኘታቸው። ሳያውቁት ሳይረዱት የኩታቸውን ጥለት እየወዘወዙ በዘርፉ አፈሩን በመግፋት ያካነወኑትን ሥርዓት፤ ከስርጋቸው ጋራ ጊዜ ያገጣጠመውን የአቶ መለስን አካል፤ ፈር ለማልበስ ኢትዮጵያዊው mystery ጎትቶ ወስዷቸውል።
ሳልጠቅሰው የማላልፈው በነ አቡነ ማትያስ በተከናወነው ፍትሐት ያየሁት ጉድለት ነው። ይህም “ወይመጽኡ ካህናት ወሌዋውያን እስመ ኪያሆሙ ኀረየ እግዚአብሔር ይቁሙ ቅድሜሁ ወይባርኩ በስመ እግዚአብሄር ወበቃለ ዚአሆሙ ይቀውም ኩሉ ተስናን ወኩሉ ዘይትሀደግ” (ዘዳ ፳፩፡፬) የሚለው ትእዛዝ ነው። ይህም ማለት፦ በቀብር ስርዓት ላይ ካህናቱ የእግዚአብሄርን ስም በመጥራት በህዝቡ መካከል የታወቀ አለመግባባት ካለ አስወግደው ብለው ወደ አምላክ ጸሎታቸውን አድርሰው በአመጽ ልቡን ነፍቶ በመፎከር
ላይ ያለውን “አሰስል ጌጋየ ነፍስ እምላዕሌከ ወትከውን ሠናይት ላዕሌከ ለእመ ገበርከ ዘሠናይ ወዘአዳም ቅድመ እግዚአብሔር አምላክከ”(ሲራክ ፰) የሚለውን ማለትም፦ “ሰው የሚጎዳና የሚከፋፍል መንፈስ ከህሊናህ አስወግድ! ይህን ብታደርግ ለራስህ ለህይወትህ መርሆ ይጠቅምሀል። በእግዚአብሄር ዘንድም ተቀባይነትን አግኝተህ ሞገስ ክብርና ጸጋ ትጎናጸፋለህ” በማለት ምክርን ባዘለ ተግሳጽ ማስቆም ነበረባቸው። አላደረጉትም። እውነተኞች ቢሆኑ ኖሮ፤ ይህን ማድረግ በማይችሉበት መካከል በመቆም ፍትሐት ማድረግ ባልተገባቸውም ነበር።
እንደሚታወቀው ሁሉ አቶ መለስ የፈጠሩት የፖለቲካ መርሆ አገርን ሰነጣጥቆ ወደብ አሳጥቶ ህዝቡን በቋንቋና በዘር ከፋፍሎ ከሞቱም በኋላ ይቀጥላል እየተባለ እንደመልካም ነገር የሚፈከርለት ስርዓት ነው። በቅኝ ተገዥው በመጎዳት ከሚደሰቱት ከቅኝ ገዥወች በቀር፤ ህግ ቀርጸው መመሪያ አውጥተው ወደብ ማሳጣት ነፍስ መግደል አገር መክፈል መሬትን ከተወላጁ ነጥቆ ለባእድ መሸጥ ማንም ሰባዊ ፍጡር የሚቀበለው አይደለም። ይህን የሚቃወሙትን ያልታረሙ አመጸኞች የሚል ቅጽል በመስጠት የሚያስሩበትን
ወህኒ ቤት ማረሚያ ቤት የሚሉ የቅኝ ገዥዎች ናቸው። አቶ መለሰም ቅኝ ገዥወች የሚያደርጉትን በማድረግ የተቃወሟቸውን መታረም ያለባቸው ታራሚዎች ብሏቸዋል። የሚያሰቃዩባቸውን እስር ቤቶ ችንም ማረሚያ ቤቶች ብለው ሰይመዋቸዋል።
አንዳንድ የዘመናችን ጳጳሳትም የነአቶ መለስን መርሆ የሚቃወመውን ሁሉ እንዳልታረመ በመቁጠር በመረሚያ ቤት ያላችሁ እያሉ በመደጋገም ሲናገሩ ሰምተናል። እነ አቶ ወልደ ማርያምም ደሳለኝም ይህን መርሆ በመከተል “በቁጣ በብስጭትና በእልክ የአቶ መለስን መርሆ እንከተላለን” እያሉ በመፈከር ላይ ናቸው። ምእመናኑን ወክለው ሬሳውን ከበው በህዝብ ፊት ንስሀ ለገባ ክርስቲያን ክብር የሚገለጸውን ፍትሐት የፈጸሙ ሰዎች ያለ ጊዜው ለተቀጨው ለአቶ መለስ ሞት የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ ሀዘናችሁን ለመካፈል መጣሁ:: Susan Rice ከዚያም አልፋና ተርፋ “He was driven not  by ideology, but by his vision of better future for the land he loved” እያለች
መሬታችንን ለባእድ ሸጠብን አገራችንን ወደብ አልባ አደረገብን ከፋፈለን አሰረን ገደለን አሳደደን እያለ በሚያለቅስበትና በከንቱነቱም በሚየለቅስለት ህዝብ ፊት ቆማ ከተናገረችው የሰው አገር ሰው የባሱ ሆነው ቀርበዋል። ይህ ከቤተ ክርስቲያናችንና ከህዝባችን ስሜት እጅግ የራቀው ፍትሐት ኬንያ በነበርኩበት ጊዜ የገጠመኝን ትዝታ አስተወሰኝ።
ክፍል ፪፦ የኬንያው ትዝታ
፪(ሀ). ኬንያ ላይ የገጠመኝ
ነገርን ነገር ይስበዋልና በነ አቶ መለስ ቀብር ላይ የተፈጸመው ሥርዓት፤ ኬንያ በነበርኩበት ኮሌጅ የገጠመኝን ትዝታ ጎትቶ አመጣብኝ። ብጠቅሰው ለዚህች ጦማር አንቀጽ አጎላማሽ ይሆናል ብየ ገመትኩ። የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያና ጋራ በነበራት ወዳጅነት ለቤተ ክርስቲያናችናችን በምትሰጠው የትምህርት እድል ተሳታፊ ሆኘ በ St Andrew’s College of  Theology Embu, kerugoya, Kenya በነበርኩበት ዘመን ከባህላችን ጋራ የተጋጨ ነገር ገጠመኝ።የትምህርት ቤቱ አላማ በ British Commonwealth የተሳሰሩ ህዝቦች በሚኖሩባቸው አገሮች ውስጥ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ህብረተ ሰቡን በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው የሚያገለግሉትን ወጣቶች ማምረት
ነበር።
በኬንያ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ Bishop David Gitari ይባሉ ነበር። እኒህ ሊቅ Pastorology, anthropology & psychology በሚባሉት የእውቀት ዘርፎች የበለጸጉ በመሆናቸው፤የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን በመሰረተቻቸው ትምህርት ቤቶችና ስብሰባዎች እየተጋበዙ እውቀት የሚያካፍሉ ነበሩ። ከሳምንት አንድ ቀን በትምህት ቤቱ እየተገኙ በእነዚህ የትምህርት አይነቶች ላይ የተመሰረተ ትምህርት ይሰጡን ነበር። ከእለታት አንድ ቀን ቦታቸውን ኮሌጁ እንዲሰራበት የለገሱ ታላቅ የተከበሩ አዛውንት አረፉና፤ እኒህ ታላቅ ሊቅ David Gitari ማለቴ ነው። ወደ ኮሌጁ መጡና “society is a book which is open in time of sorrow like this, and happiness like wedding for those who are eager to read and learn” ማለትም፦ “ለመማር ምኞት ላላቸው ሰዎች፡ ህብረተ ሰብ በሀዘንና በደስታ የሚገለጥ መጽሀፍ ነው” እያሉ ንግግራቸው ከጀመሩ በኋላ፤ በቀብሩ ሥርዓት ላይ ተገኝተን የሚካሄደውን አስተውለን ከላይ በዘረዘርኳቸው ትምህርት አንጻሮች ተመዝነው የሚታረሙ ከአምስት ገጾች ያለነሰ ጽሑፍ እንድናዘጋጅ አዘዙን፡፡ የምናዘጋጀው ጽሁፍ ከፍተኛ ነጥብ (credit) ያዘለ እንደሚሆንና ይህ እድል እንዳያመልጠንም አጠንክረው ነገሩን። ቀጠሉና በትምህርት መስክና በክርስትና
አጠይሞ መናገር ኃጢአት ነው። ያለ ምንም ይሉኝታ ከምታውቁት ከመጣችሁበት ባህል ጋራ በማነጻጸር ነቅፋችሁ ጻፉ” አሉን። በበነጋው ከኔ በቀር ሁሉም ቁርሱን በልቶ ስርአቱ ወደ ሚካሄድበት ቦታ ሄድን።
እኔ ጠብቄ የነበረው የሟቹ ቤተሰብ ዘመድ አዝማድና ወዳጅ ካንደበታቸው በሚያፈልቋቸው ዋይታ ላይ መስርቼ ለመጻፍ ነበር። ነገር ግን ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሰዎች በሬሳው ዙሪያ ቆመው “Till We meet” የሚባል መዝሙር ብቻ በተረጋጋ መንፈስና በፈገግታ ተዘመረ። የሀዘን ፊት ሳይታይና የልቅሶ ድምጽ ሳይሰማ ቀብሩ ተፈጽሞ ወደ ኮሌጁ ተመለስን።
Professor Bishop Gitari ወደ ኮሌጁ ተመልሰው ሲመጡ የጻፍነውን ጨርሰን መቆየት ስለነበረብን ከሰኞ እስከ ዓርብ በሌሎች መምህራን የሚሰጡትን ትምህርቶችና ምንባባት ከማከናወን ጎን በቀብሩ ሥርዓት የተገነዘብነውን ጽፈን ለመጨረስ ሁላችንም ባቴሌዎች ሆነነ ሰነበትን።
ዮሐንስ ሁቄ የሚባል በስዊድን ሚሲዮናውያን ተሰብኮ ክርስቲያን የሆነ ኢትዮጵያዊ በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ እንደኔ የትምህርት እድል አግኝቶ በትምህርት ገበታ ላይ ነበር። እሱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ባጉል ባህል ህዝቡን አፍና ይዛ ሰው ሲሞት ከበሮ እየደበደበች እንደምታስለቅስ በሰፊው አትቶ፤ እኛ ፕሮቴስታንቶች ግን ወንጌል መስበክ ከጀመርን ወዲህ ግን ይህን አስቁመናል “ተስፋ እንደሌላቸው አታልቅሱ”(፩ኛ ተሰለ ፬፡፲፫) የሚለውን እየጠቀስን ተስፋ እንደሌላቸው ኦርቶዶክሶች አታልቅሱ እያልን በማስተማር አስተካክለነዋል” ብሎ ጽፎ አቅርቦ ኖሯል።

ፕሮፌሰሩ በሰጡን መመሪያ መሰረት ምንም ሳልደብቅ ተወልጄ ባደኩበት አካባቢ ህዝቡ ሲያደርግ ያየሁትንና ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አበውም የሰማሁትን በኬንያ ሲደረግ ካየሁት ጋር በማነጻጸር አቀረብኩ። የነ አቶ መለስ ሞት የተለያዩ ስሜት በህሊናችሁ ተፈጥሮባችህ ስትነጋገሩ የሰነበታችሁ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ሆይ! ከላይ የጠቀስኩትን ትዝታ በኔ ላይ የቀሰቀሰብኝን በእነ እነ አቶ መለስ ሬሳ ላይ የተካሄደውን ኢትዮጵያዊ የቀብር አሸኛኘት ያንጸባርቀዋል ብየ ስለገመትኩ በኮሌጁ እያለሁ ከጻፍኩት የማስታውሰው ከዚህ በታች እነሆ!
፪(ለ). ያቀረብኩት ጽሑፍ
“የሬሳ ሳጥን በመካከል ተጋድሞ ከማየቴና በመጨረሻም ወደ መቃብር ወርዶ አፈር ሲለብስ በማየቴ ሰው መሞቱን ከመገመቴ በቀር ከኢትዮጵያዊው የቀብር ሥርዓት ጋራ ሳነጻጽረው የሚገናኝ ነገር ላገኝ አልቻልኩም። በኢትዮጵያ ባህል የታወቀ ሰው ይቅርና አልፎ ሀጅ እንኳ ጠላትም ቢሆን ሞቶ ቢገኝ፤ልብስ በመቀየር በእንባ በአምልኮ “ዋ እኔን፡ ባልሰራ ሰው ባልሆን” እየተባለ በሰውነት ፈራሽነት በተፈጥሮ ግንዛቤ ላይ በተመሰረት አምልኮ እየተለቀሰ በእንባ ወደ ግብአተ መሬት ይሸኛል። የሰውን እንባ ቀስቅሰው እንዲፈስ ከሚያደርጉ ብዙ ነገሮች ሁለቱን እጠቅሳለሁ።
፩ኛ፦ ይህችን ዓለም ስንመለከታት እሳት በተሸከሙ ስንጥር እንጨቶች የተሞላች የክብሪት ሳጥን ትመስላለች። የክብሪት ሳጥን የእሳትን ባህርይ ተሸክሞ፡ የእሳትን ባህርይ በራሳቸው የተሸከሙ የተበታተኑ እንጨቶችን ሰብስቦ የያዘ ነው። እያንዳንዷ የክብሪት እንጨት ከራሷ ሳጥን ጋራ በመፋጨት ከባህርያዋ በሚነደው እሳት ተራ በተራ እየተቃጠለች ታልቃለች። ሰውም በዚህች ዓለም ሲኖር በባህርዩ በውስጡ የተዳፈነው እሳት እየተጫረበት ከዚህች ዓለም ህይወት እየተመዘዘ ተራ በተራ የሚያልቅ ነው።
አንድ ሰው ከመካከል ሲሞት፡ በሟች ሰውነት ላይ የተጫረው የተዳፈነ እሳታዊ ሞት በህይወት ባለው ሰው ሁሉ ሰውነት በቃል ልንተረጉመው የማንችለው እሳታዊ ስሜት ይጭራል። ይህ በሰውነታችን ላይ የተጫረው እሳት፡ በሞት ስለተለየን ሰው ያለቀስን ይምሰለን እንጅ፤ ተራችን ደርሶ በኛ ላይ በተከሰተ ጊዜ የምናለቅሰውን ልቅሶ ሳንወድ እንድናለቅስ ያስገድደናል። ኢትዮጵያውያን የነገረ መለኮት ሊቃውንት ክርስቶስ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ሞት ሲጓዝ እያለቀሱ ለተከተሉት ሰዎች “ብክያ ላእለ ርእስክን” ባለው ላይ የተመሰረተ ነው።
፪ኛ፦ ሰው በሞት ሲለይ፤ በህይወት ያለው የቀርብ ዘመድ ወዳጅ የሟቹን አካል ድምጽና ንግግር መፈለግ ይጀምራል። በእደ ህሊናው የሟቹን አካል ለመጨበና ለመዳሰስ ሲሞክር፤ ከነባራዊነት (objective matter ) ወደ ኢ-ነባራዊነት (illusion) ውስጥ የገባ የሟች ሰውነት፤ ሞትን በጽንስነት ተሸከሞ በህይወት በሚኖረው ሰውነት ውስጥ የሟችን አካል ወደተከሰከሰ ብርጭቆነት ይለውጥና ከሰውነቱ ጋራ ያፋጨዋል። የቋሚውን ህሊና እየበጠበጠ አንጀቱን ይሰብቀዋል። በሰውነት ውስጥ የሚካሄደው ስብቀት እንባን አስገንፍሎ እንዲፈስ ያደርጋል። በዚህ መሰረት እኛ ኢትዮጵያውያን ወዳጅም ይሁን ጠላት ሞተ መባልን ስንሰማ ሰውነታችን እየተሰበቀ የፈረሰ ይመስለናል። በስብቀቱ የገነፈለውን እንባ እያፈሰስን
በፍትሐት ወደ ግብአተ መሬት ለመሸኘት ወደ ቀብሩ እንሄደለን።
በግእዙ ሰዋሰው (grammar) ለነጠላ “ቦቱ” እና “ሎቱ” ለብዙ “ሎሙ እና ቦሙ ” በሚባሉት አገባቦች የሚከሰቱት የልቅሶ ባህርያትም አሉን። እነሱም በዮሴፍ የተገለጹት የልቅሶ አይነቶች ናቸው።
ዮሴፍ ሁለት ጊዜ አለቀሰ።
የዮሴፍ ልቅሶ
መጀመሪያ ያለቀሰው የሸጡት ወንድሞቹ በአገራቸው ረሀብ ገብቶ፡ በተሸጠበት አገር ሙሉ ባለ ሥልጣን ሆኖ በሚመራበት ዘመን፤ አገሩ እጅግ በለጽጎ ነበር። ወሬው ተሰማና ወንድሞቹ የሸጡት ወንደማቸው ወደሚኖርበት አገር እህል ፍለጋ ሄዱ። ከወንድማቸው ከዮሴፍ ጋራ የሚነጋገሩት ባስተርጓሚ ነበረ። እሱ የሸጡት ወንድሞቹ እንደሆኑ አወቋቸዋል። እነሱ ግን እንኳን ለይተው ሊያውቁት በህይወት መኖሩንም ረስተዋል። የናቱን ልጅ ትንሽ ወንድሙን ማግኘት ፈለገና የሚፈልጉትን እህል ሰጥቶ ትንሽ ወንድሙን እስኪያመጡት ድረስ ሌላውን እንደ መያዣ አድርጎ አንደሚቆይ ነገራቸው። ነገሩ ከበዳቸውና ወደ ጉድጔድ ሲወረወሩት ከጉድጔድም አውጥተው ሲሽጡት እባካችሁ ጨክናችሁ ይህን በደልና ግፍ
አትፈጽሙብኝ እያለ የተማጸናቸው ትዝ አላቸውና፤ በሱ ላይ የፈጸሙት ግፍ ከዚህ ፈተና ላይ እንደጣላቸው ተሰማቸው። “እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ። በእውነት ወንድማችንን በድለናል። ነፍሱ እየተጨነቀች እኛን በሚማጸነን ጊዜ መጨነቁን አይተን አልተውነውም። ስለዚህ ይህ መከራ መጣብን” ሲሉ ሰማቸው። እነሱ ግን ንግግራቸውን የሚሰማቸው አልመሰላቸውም። ከነሱ ዘወር አለና ዮሴፍ አለቀሰ። (ዘፍ ፵፪፡፳፩᎗፳፬)።
ለሁለተኛ ጊዜ ያለቀሰበት አባቱና ዘመዶቹ ሁሉ ወደሱ መጥተው ከሱ ጋራ መኖር ከጀመሩ በኋላ አባታቸው ያዕቆብ ሸምግሎ ሞተ። የከፋ በደል ፈጽመንበት ሳለ ያልተበቀለን ስለ አባታችን ይሆናል። አሁን አባታችን ከሞተ በኋል ያደረግንበት ክፉ ትዝታ ካገረሸበት ሊጎዳን ይችል ይሆናል ብለው በመጠራጠር፤ ያባታቸው የኑዛዜ ቃል በማስመሰል እንዲህ የሚል የተማህጽኖ መልእክት በሽማግሌ ላኩበት። “አባትህ በህይወት እያለ እንድንነግርህ ያደራ ቃለ አለ። “ወንድሞችህ እጅግ ከፍተው ጎድተውሀልና የወንድሞችህን በደል ጨርሰህ ከህሊናህ አጥበህ ይቅር በላቸው” የሚል ነበር። ወንድሞቹም “ከእንግዲህ ባሮችህ እንጅ ወንድሞችህ ልንባል አይገባንም እያሉ ከእግሩ ላይ በግንባራቸው ተደፍተው ወደቁ። ዮሴፍ ይህን ሲያይ እንደገና ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ። እንባውን እየጠረገ አይዟችሁ አትፍሩኝ። እኔ እናንተን እበቀል ዘንድ ማን ነኝ? የእግዚአብሄርን ቦታ የምወስድ ሰው አይደለሁም። እናንተማ እኔን
ለማጥፋት ወስናችሁብኝ ነበር። እግዚአብሄር ግን ክፉ ውሳኔያችሁን በውሳኔው ሻሮ ይኸው እንደምታዩት የህዝብ መዳኛ አደረገው። ይህን አምላካዊ ጥበብ ሳትረሱ ያለፍርሀትና መጨነቅ ኑሩ እኔ አልበቀላችሁም።
ይልቁንስ እናንተንም ልጆቻችሁንም እመግባችኋለሁ ተዝናንታችሁ እንድትኖሩ አጽናናችኋለሁ፡ደስም አሰኛችኋለሁ” አላቸው። (፶፡፲፭-፳፩)። ዮሴፍ “በፊትህ መቆም ያልቻልን ተግባረ ሙታን ነንና ይቅር በለን ቅበረን ብለው ከመሬት ወድቀው ባለቀሱበት ጊዜ፡ በጉድጓድ ሲጥሉት ከጉድጓድም አውጥተውም ሲሸጡት የተካሄደበት የጭካኔያቸው ተግባር አንጀቱን እየሰበቀው አለቀሰባቸው። ሌላው ሁኔታወች ተለውጠው አፈር እየላሱ ከመሬት መወድቃቸው የታላቅ ወንድመነት ርህራሄ ከመንፈሳቸው መጥፋቱ፤ ወንድማዊና ሰባዊ
ሃላፊነታቸውን ሳይጠቀሙበት በከንቱ በመቅረታቸው አለቀሰላቸው። እንደዚሁ የኢትዮጵያ ህዝብ ክፋት ፈጽሞበት በሞት ለተለየው ሰው ያንተን ነገር አያሳየኝ እያለ
ያለቅስበታል።

ታላቁ አርቲስታችን አቶ አያሌው መስፍን  “ተው ቻለው ሆዴ፡ሲቀር ለሚቀረው ምነው መናደዴ”  እንዳለውም እንዲህ ሁሉም ከንቱ ሊቀር በማለት ስለከንቱነቱ እያለቀሰ ፍትሐቱን ይፈጽምለታል ።ከላይ በተዘረዘሩት አንቀጾች በሞት ዙሪያ ያለውን የኢትዮጵያዊው ስነ መለኮት፤ ስነ ልቡናና ስነ ባህላዊ ግንዛቤ፤ ከኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የሰማሁትን ከውጭ ካየሁት ጋራም በማነጻጸር ከሞላ ጎደል ከዚህ በላይ ያቀረብኩትን ከዚህ በታች ባሰፈርኳቸው አረፍተ ነገሮች እደመድማለሁ።

መደምደሚያ
ፍትሐት በሕይወተ ሥጋ የለን ሰዎች፤ የሞተውን ሰው እስከ የሌለውን ምድራዊ መለያየት እያወጀን ወደ ግብአተ መሬት የምንሸኝበት አዋጅ ነው። ሰው በህይወት እያለ በቦታና በስአት የተወሰነ መራራቅ ሲገጥመው መለያየት ይባላል። ትዳር ሲፈርስ፤ ገብያ ሲበተን፤ አገር ሲናጋ ግን ተፈታ እንላለን። ሰው ነፍስና ሥጋው ተለያይተው ከዚህ ዓለም ሲለይ ሞተ እንልና፤ ለፈረሰ ነገር የምንጠቀምበትን ግሥ በመጠቀም፤ የግብአተ መሬት መሸኛችንን ፍትሐት ብለን እንገልጸዋለን። ይህም አካሉ በነፍስና በሥጋ እንዲንቀሳቀስ ተጠረቃቅመው የተሰራባቸው ባህርያቱ ተበታተኑ ፈረሱ፤ ወይም ባንድንት ይታይ የነበረው አካል ተፈታ ማለት ነው።ለምሳሌ በኤርትራ፤በአሰብና በኢትዮጵያ፤ እንደገና ለ፺ አመታት ለባእዳን በተሸጡ
መሬቶችና እየተፈናቀሉ በፈለሱት ኢትዮጵያውያን ዜጎች መካከል ያለው መለያየት ፍትሐት ይባላል። ፍትሐት የሚለው ቃል በሥጋ በነፍስ፤ በዚሕ ዓለም እና በሰው መካከል ለሚከሰተው ይልቁንም የሞት ማሰሪያ ከተባለው ከኃጢአት ለመለያየት ለምናደርገው ጥረትም የተሰጠ መግለጫ ነው።
ኃጢአት በስህተት ተግባራችን ከምንተባበራቸው ሰዎች ጋራና ከራሱ ጋራም እንድንተሳሰርበት ዲያብሎስ የፈተለው ወደ ዘላለማዊ ሞት ጎትቶ የሚከት ሰንሰለት ነው። በህወተ ሥጋ እያለን ከዚህ ሰንሰለት ያለያየን እንድፈታ ያደረገን “ፍትሐት ዘወልድ” በተባለው አንቀጽ ሰፍሮ እንደምናነበው “ዘበተከ እምኔነ ኩሎ ማእሰረ ኃጢአዊእነ በሕማምከ ማሕየዊት” (ቅ. ገጽ. ፴፯ ቁ ፶፮) ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይሁን እንጅ “ወበከመ ኢሐለይዎ ለእግዚአብሄር በልቦሙ ከማሁ እግዚአብሔርኒ ወሀቦሙ ልበ እበድ ከመ ይግበሩ ዘንተ ዘኢይደሉ” (ሮሜ ፩፡፳፰) እንዲል፦ እግዚአብሔርን ከህሊናቸው አውጥተው ያላንዳች ጸጸት ለመኖር ወስነው ሰው እየገደሉ እግዚአብሄርን እየበደሉ ህይወታቸውን በሞት ለፈጸሙ ሰዎች እግዚአብሄር እውነት ጽድቅ ማመንጨት የማይችል አዕምሮ ሰጣቸው” እኛ ክርስቲያኖች ይህን ሰንሰለት ክርስቶስ በጥሶ አላቀቀን ብለን ብናምንም፤ በዚህ ዓለም ስንኖር በሥጋ ፈቃዳችን አማካይነት መልሶ ሊያስረን ይፈትነናል። “ዘወሀብከነ ዚአከ ሃይማኖተ ቦቱ ገበርከ ለነንማእ ማእሰሪሁ ለሞት ዘኢይትነሰት” (ኪዳን)። የሞትን ማሰሪያ ክህደትን በሃይማኖት ድል እንድንነሳው
ያደረከን” እያልን የበደልነውን ሰው ከመሞታችን በፊት ይቅርታ በመጠይቅ በንስሀ፡በጸጸትና በትህትና እርስ በርሳችን እንድንፈታታ ስልጣን ስጥቶናል። በህወት እያሉ ከዚህ ለመፈታት ፈቃደኛ ላልሆኑ ሰዎች እስከ መጨረሻ በሞት ሰንሰለሰት እንዲተሳሰሩ ክርስቶስ ይፈቅድላቸዋል።
አቶ መለሰና አቡነ ጳውሎስ ባንድ ወቅት ካንድ መንደር ተጠራርተው መጥተው፤ ባንድ ወቅት ተጠራርተው እንዲሄዱ ያደረጋቸው ሞት፤ ከመላ ኢትዮጵያ ህዝብ ቢለያቸውም፤ ፈቅደውና ተስማምተው እርስ በርስ ከተሳሰሩበት ሰንሰለት እርስ በርሳቸው እንዳይፋቱ እስከ ሞት ድረስ እንዲቀጥሉ ክርስቶስ ትቷቸዋል። የተሳሰሩበትን ሰንሰለት ሞትም አልፈታውም። የዚህን ረቂቅ ምስጢር አብራርተው ሊረደቱና ሊገልጹት የሚችሉት ኢትዮጵያዊውን ነገረ መለኮትና ስነ ልቡና የተረዱና ለመማር ለመረዳት በዚህ ወቅት የተከፈተውን መጽሀፍ ለማንበብ ችሎታ ያላቸው ብቻ ናቸው።
የግብአተ መሬት አሸኛኘታችንን፤ ኢትዮጵያዊውን ስነ መለኮትን፤ ስነ ልቡናን ባህላዊውን የቀብር አሸኛኘትት ለማወቅ፤ ለመረዳትና ለመማር ፈቃደኛ ለሆን ሁሉ በጥሞናና በማስተዋል እንድንመለከተው እንዳናነበው ባትሮኑስ ላይ የተዘረጋ የስንክሳር መጽሀፍ ሆኖ አሁን ተገልጧል። የራሳችንንም ስሜትና ቤተ ክርስቲያናችንም በምን አይነት ሰዎች ቁጥጥር እንደወደቅች እንድናይበት መስተዋትም ሆኖ በፊታችን ተዘርግቷል።
ይህ በነ አቶ መለሰ ግብአተ መሬት አማካይነት የተከፈተው ስነ ልቡናዊ መጽሐፋችን፤ የኛን ብቻ ስነ ልቡና የምንገነዘብበት ሳይሆን፤ የኛን ስነ ልቡና ኢሀደግና የውጭ Susan Rice የመሳሰሉ ሰዎችና የኢሀደግ መንግስት መረዳት እንደተሳናቸው መረዳት ችለናል። “በቅኝ ለመግዛት መጥቶብን የነበረው ጣሊያን ያደረገብንን ኃጢአት፤ በደልና ግፍ አንዲት ሳትቀር ፈጸመብን እያለ አቶ መለሰን በመውቀስና በመክሰስ ላይ ባለው በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት በመቆም “He was driven not by ideology, but by his vision of better future for the land he loved” እያለች አሜሪካን ወክላ በታነገረችው አሜሪካ መረድ የተሰነው መሆኑን ገለጠ።
በሌላ በኩል ደግሞ የተከበሩ Ana Gomez የተባሉት “since Meles died in July much earlier than is totalitarian click announced to the people of Ethiopia in order to engineer in secret the perpetuation of their oppressive regime” ብለው ለግብአተ መሬት ያነበቡትን የጻፉበትን የወረቀት ጫፍ በጣታቸው እየወዘወዙ በማንበብ፤ የኩታውን ጫፍ በጣቱ እየወዘወዘ ከሸኘው ከሰፊው ኢትዮጵያ ህዝብ ጋራ መተባበራቸው በኢትዮጵያዊው ስነ ልቡናችን
(ስንክሳራችን) ውስጥ ተመዘገበ።
ኢትዮጵያዊ ሁሉ “ዓለም ታጠፈችብህ” ለማለት ኩታውን አጠፈ። መሬት ነህና ወደ መሬት ትመለሳለህ” የሚለውን መለኮታዊ ቃል የሚያስታውሰውን የኩታውን ጫፎች ይዞ እየወዘወዘ ወደ ግብአተ መሬት ሸኘው። ከደሙ ንጹህ ነን በማለትም በውሀ ብቻ አይደለም ርቆ በመሄድም በራሱ እንባ ታጠበ። በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸመው ደባ ሁሉም አለቀሰበት።ስለከንቱነቱም ሁሉም አለቀሰለት።
ስለሲኖዶሱ መወጋገዝና መተራረቅ በማቀርባት ጦማር እንገናኝ።
ይቆየን::
ለሌሎች ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ጦማሮች የሚከተለዉን ድህረ-ገጽ ይመልከቱ::
http://www.medhanialemeotcks.org/

ማሳሰቢያ፤በዌብሳይታችን ላይ ለሚወጡ ማናቸውም ጽሁፎች ቀዳሚ የሆነ የዌብሳይታችንን አርትኦት ስራን ለማክበር ሲባል በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በማለዳ ታይምስ የመረጃ ማእከል ® ላይ ለሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የማለዳ ታይምስ የመረጃ ማእከል ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዌብሳይቱን ጠቋሚ (አመልካች ) (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.maledatimes.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን(የማለዳ ታይምስ ህግና ደንብ በንግድ በተመዘገቡበት ሁለት አገሮች የረቀቀ ሲሆን በሁለቱም አገሮች አንድ አይነት የሆነ አሰራር ይዞ ይከተላል ።ይህንን ህግ ማንኛውም ሰው መቅዳት የማይችል መሆኑን እንገልጻለን።ንብረትነቱ እና ህገ ደንቡ የማለዳ ታይምስ ብቻ ነው!)፡፡ይህ ካልሆነ ግን በህገ ደንባችን መሰረት አስፈላጊውን የህጋዊ ጥያቄ ለማቅረብ የምንገደድ መሆኑን እንጠቁማለን::በዚህ አጋጣሚ በግለሰብ ለሚላኩ ጽሁፎች ሁሉ ተጠያቂው ስሙ የተገለጸው ግለሰብ እንጂ የማለዳ ታይምስ መረጃ ማእከል ሃላፊነቱን እንደማይወስድ እናሳስባለን ::

 

ማሳሰቢያ፤በዌብሳይታችን ላይ ለሚወጡ ማናቸውም ጽሁፎች ቀዳሚ የሆነ የዌብሳይታችንን አርትኦት ስራን ለማክበር ሲባል በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በማለዳ ታይምስ የመረጃ ማእከል ® ላይ ለሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የማለዳ ታይምስ የመረጃ ማእከል ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዌብሳይቱን  ጠቋሚ (አመልካች ) (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.maledatimes.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን(የማለዳ ታይምስ ህግና ደንብ በንግድ በተመዘገቡበት ሁለት አገሮች የረቀቀ ሲሆን በሁለቱም አገሮች አንድ አይነት የሆነ አሰራር ይዞ ይከተላል ።ይህንን ህግ ማንኛውም ሰው መቅዳት የማይችል መሆኑን እንገልጻለን።ንብረትነቱ እና ህገ ደንቡ የማለዳ ታይምስ ብቻ ነው!)፡፡ይህ ካልሆነ ግን በህገ ደንባችን መሰረት አስፈላጊውን የህጋዊ ጥያቄ ለማቅረብ የምንገደድ መሆኑን እንጠቁማለን::በዚህ አጋጣሚ በግለሰብ ለሚላኩ ጽሁፎች ሁሉ ተጠያቂው ስሙ የተገለጸው ግለሰብ እንጂ የማለዳ ታይምስ መረጃ ማእከል ሃላፊነቱን እንደማይወስድ እናሳስባለን ::

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on October 4, 2012
  • By:
  • Last Modified: October 4, 2012 @ 12:38 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar