ሀገራችን ኢትዮጵያ ቀደምት እና ታላቅ ከሚባሉት ሀገሮች አንዷ ብትሆንም፤በሚያጋጥሟት ጨቋኝ ገዢዎች ምክንያት የሀገሮች ሁሉ ጭራ ለመሆን ተቃርባለች፡፡ እስካሁን ድረስ በመረጣቸው መሪዎች ለመተዳደር ያልታደለው የኢትዮጵያ ህዝብ ለምርጫ እና ለዲሚክራሲ ሥርዓት ያለውን ቁርጠኝነት በምርጫ 97 አሳይቷል፡፡ ነገር ግን ትናንትም ሆነ ዛሬ የምርጫ ውጤት መገልበጥ እና ማጭበርበሩን የቀጠለው የህወሐት/ኢህአዴግ አገዛዝ በምርጫ 2007 መቶ በመቶ አሸንፊያለሁ ቢልም በአገዛዙ ላይ ለ6 (ስድስት) ወራት እንኳን ሳይቆይ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ተቃውሞ እያስጨነቀው ይገኛል፡፡ የህዝቡም ጥያቄ ግልጽ ነው፡፡ “መሰረታዊ የስርዓት ለውጥ!”
በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የተነሳው ህዝባዊ አመጽ እንደሰደድ እሳት እንዲቀጣጠል ያደረገው የ25 ዓመታት ዘረኝነት የግፍ አገዛዝ መሆኑ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡ በወልቃይት ጠገዴ፣ በኮንሶ፣ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት፣ በቢሾፍቱ እሬቻ በዓል ላይ እና በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች የሚደረገው ግድያ፣ እስራትና ማፈናቀል የአገዛዙ አስከፊነት እና የአገዛዙ ቁንጮዎች ያለ ህዝብ ይሁንታ በስልጣን ለመቀጠል የሚያሳዩት የጭካኔ ደረጃ በግልፅ የሚያመላክት መሆኑ በተለይ ሰማያዊ ፓርቲ በቀደምት መግለጫዎቹ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
ከታሪክም እንደምንረዳው የአምባገነንነት መጨረሻ የውርደት ሞት መሆኑን ነው! ከውድቀት ጥቂት ቀደም ብለው መንቃት የቻሉ አምባገነኖች ሀገራቸውን ከማፍረስ፣ ህዝቡን ከሞት እና ከስደት፣ እራሳቸውንም ከውርደት አድነው ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መሰረት ጥለው ስማቸው በክብር ሲወሳ መኖሩን ነው፡፡ ዛሬ በሀገራችን የምናየው አገዛዝ በመስቀለኛ መንገድ ላይ መቆሙን ነው፡፡ ምርጫውም የሚሆነው ችግሮችን አድበስብሶ ለውድቀት መብቃት ወይም የመሰረታዊ ለውጥ አጋዥ ሆኖ በክብር ስልጣኑን ለህዝብ ማስረከብ ነው፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ “እኔ ከሌለሁ ሀገር ትበታተናለች” የሚለውን የህወሐት/ኢህአዴግ ሟርት አይቀበልም፡፡ ከዚህ ይልቅ የተጀመረው ህዝባዊ አመፅ ተገቢውን ምላሽ ሳያገኝ እንደማይቆም በፅኑ ያምናል፡፡
ስለሆነም ጠቅላላ ጉባዓው የሚከተሉትን ባለሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
1ኛ. ገዢው ፓርቲ ሰላማዊ ተቃውሞ ባነሱ ዜጎች ላይ መተኮሱን እና መግደሉን፣ ማሰርና ማፈናቀሉን በአስቸኳይ እንዲያቆም፡፡ የመከላከያ ሰራዊ ተግባር የሀገርን ዳር-ድንበርና ሉዐላዊንት መጠበቅ መሆኑን ተገንዛቦ በአስቸኳይ ወደ ጦር ካምፑ እንዲመለስ፡፡
2ኛ. እስካሁን የተገደሉና የተጎዱ፣ የተፈናቀሉና የተንገላቱ ወገኖችን ጉዳይ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ፡፡ ለዚህ ጥፋት ትእዛዝ የሰጡ ባለሥላጣናትም ለህግ እንዲቀርቡ፡፡
3ኛ. መንግስት የዘጋውን ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በአስቸኳይ እንዲከፍት፡፡
4ኛ. የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት እና መገናኛ ብዙሃን ህዝብን ከሚያስቆጡ ተግባራትና ገለፃዎች እንዲታቀቡ፡፡
5ኛ. የተቃዋሚ መሪዎች እና አባላት በቀጣይ የሀገራቸው ሁኔታ ላይ ነፃ ስብሰባ እና ውይይት እንዲያደርጉ፡፡ ይህም መንግስት መሰናክል መፍጠሩን እንዲያቆም፡፡
6ኛ. ገዢው ፓርቲ ከህዝቡ ጋር በመወያየት በአሰቸኳይ ስልጣኑን ለህዝብ የሚያስረክብበትን መንገድ እንዲያመቻች፡፡
7ኛ. ሰማያዊ ፓርቲ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያገባኛል ከሚሉ ማናቸውም ኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን እየገለፀ፤ ስለሀገራችን ወቅታዊ ጉዳይም አዎንታዊ መፍትሔ የሚያስገኝ ውይይት እንዲጀመር ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘለአለም ትኑር!
መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም
Wondering where the comments are? We encourage you to use the share buttons below and start the conversation on your own!
- Click to email a link to a friend (Opens in new window)
- Click to share on Facebook (Opens in new window)
- Click to share on Twitter (Opens in new window)
- Click to share on LinkedIn (Opens in new window)
- Click to share on Pinterest (Opens in new window)
- Click to share on Tumblr (Opens in new window)
- Click to print (Opens in new window)
Average Rating