www.maledatimes.com በነፃ ገበያ ዙሪያ የሚነፍሰው የተሳሳተ አመለካከት !(ፈቃዱ በቀለ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

በነፃ ገበያ ዙሪያ የሚነፍሰው የተሳሳተ አመለካከት !(ፈቃዱ በቀለ)

By   /   October 5, 2012  /   Comments Off on በነፃ ገበያ ዙሪያ የሚነፍሰው የተሳሳተ አመለካከት !(ፈቃዱ በቀለ)

    Print       Email
0 0
Read Time:123 Minute, 7 Second

በነፃ ገበያ ዙሪያ የሚነፍሰው የተሳሳተ አመለካከት !
የእነቶ መለስ ኢኮኖሚ የገበያ፣ የካፒታሊስት ወይስ ሌላ ኢኮኖሚ!
በቅድሚያ ለዚህ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ፣ በአለፉት ሃያ ዐመታት በአገራችን ምድር የነፃ ገበያ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ በተሳሳተ መልክ የሚናፈሰውንና በአንዳንድ መጽሄቶች የሚወጣውን የተሳሳተ አመለካከት ለመዳሰስ ነው። በተለይም በገዢው መደብ አንዳንድ አባላት ወይም ሚኒስተሮች ስለ ነፃ ገበያ የተሳሳተ አባባል ስለሚነፍስ እንደዚህ ዐይነቱን የተዛነፈና የአንድን አገር ዕድገት የሚያዛባ አነጋገር መዋጋት ያስፈልጋል። በሳይንስና በህብረተሰብ ዕድገት ታሪክ ባልተደገፈ መረጃ፣ በአንዳንድ የመንግስቱ ተጠሪዎች፣ “ በነፃ ገበያ መርህ እዚህ አምርተህ እዚሁ ሽጥ የሚባል ነገር የለም። አምርቶ የፈለገበት መሸጥ ይችላል።“ የሚለው አነጋገር ሃላፊነት የጎደለው አባባል ብቻ ሳይሆን ልቅነትንና ብልግናን የሚያስፋፋ ይሆናል።

በዚያው መጠንም ጥቂቶች ሊናጥጡ የሚችሉበት፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሰፊው ህዝብ የሚገፋበትና በጣም ዝቅተኛ ኑሮ እንዲኖር የሚገደድበት ሁኔታ እንዲፈጠር የሚጋብዝ አባባል ነው። በተግባርም እንደምናየው በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነው ነፃ ገበያ አዳዲስ ችግሮችን በመፍጠርና በድሮው ላይ በመደረብ ህዝባችን የባስውኑ እንዲደኸይ መደረጉ ብቻ ሳይሆን ሌላ ኃይል ስልጣን ቢጨብጥ ችግሩን ለመፍታት እንደሚቸገር ግልጽ ነው። ዛሬ በአገራችን የተስፋፋው ድህነትና የጥቂቶች ማበጥ የዚህ የተሳሳተ ግንዛቤና የፖሊሲው ውጤት ነው ማለት ይቻላል። አንዳንድ ባለስላጣናት ይህንን በደንብ ሳይታኘክ፣ ፈረንጆች እንደሚሉት ከጭንቅላት ሳይሆን ከሆድ የወጣ አነጋገር የትኛው የኢኮኖሚክስ መጽሀፍ ላይ ተጽፎ እንዳነበቡ ቢነግሩን በጣም ጥሩ ነበር። ሃሳቡን ከዚህኛው መጽሀፍ ላይ ነው የወሰድነው ቢሉን እንኳ፣ ይህ ዐይነቱ አባባል የተፈጥሮ ህግ፣ ወይም ደግሞ እንደ እግዜአብሄር ቃል ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ትምህርት ቤት ገብተን የምንማረው ዝም ብለን የሚነገረንን እንደ ዕምነት ለመቀበልና እሱን መልሰን ለማስተጋባት ሳይሆን፣ ከኮመን-ሴንስም ሆነ ከሳይንስ አንፃር አንድ ነገር ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን በመመርመር የራሳችንን ፍርድ ለመስጠትምና ትክክለኛውን መንገድ ለመያዝና ለሌላው ደግሞ ለማሳየት ነው።
በተለይም ባለፉት ስድሳ ዐመታት የኒዎ-ክላሲካል፣ ወይም በዘመኑ አባባል የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚክስ ትምህርት የበላይነትን ከተቀዳጀ ወዲህ፣ በብዙ መቶሺህ የሚቆጠሩ
ምሁራንን በማሳሳት ለብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ድህነትና ኋላ-መቅረት ዋና ምክንያት እንደሆነ፣ በየአገሩ የሰፈኑት ተጨባጭ ሁኔታዎች ብቻ ሳይሆኑ እሱን የሚቀናቀኑ አያሌ
መጽሀፎችም ያረጋግጣሉ። በተለያዩ አዋቂዎች ታትመው የወጡትን የተለያዩ አስተሳሰቦችን ያዘሉና፣ በየአገሩ የሰፈኑትን በጣም አስከፊ ሁኔታዎች ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ ማወዳደርና
እንዲሁም ደግሞ ማውጣትና ማውረድ ባልተለመደበት አገር ከአንድ ወገን የሚቀርቡ ትምህርቶችን እንደ ዕውነተኛ ወስዶ እነሱን መስበኩ እንደልማድና ዕምነት ይወሰዳል። ይህን
የመሰለ የተሳሳተ አባባል በተፈጥሮ ሳይንስም ውስጥ ተቀባይነትን በማግኘት የሳይንስን ዕድገት ሁለት ሺህ ያህል ዐመታት አፍኖ እንዳስቀረ ይታወቃል። ለምሳሌ የፕላኔቶችን፣
ምድርንም ጨምሮ በፀሀይ ዙሩያ መሽከርከር በብዙ የግሪክ ፈላስፎች የታወቀ ቢሆንም፣ አርስቲቶለስና ፖትሌመዎስ ደግሞ ይህንን በመገልበጥ፣ ፀሀይ ሳትሆን በአንድ ቦታ ቆማ
የምትገኘው፣ ምድር ናት በማለትና ፀሀይና ሌሎች ፕላኔቶችም በምድር ዙሪያ ነው የሚሽከረከሩት ብለው የሳይንስን ዕድገት እንደቀጩት ይታወቃል።

በኮፐርኒከስ ምርምር ይህ ዐይነቱ፣ በተለይም በካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎች ተቀባይነት ያገኘው የተሳሳተ ዕምነት ውድቅ ከሆነ ወዲህ፣ ጳጳሶች በሳይንቲስቶች ላይ በመነሳት አንዳንዶችን እንዳቃጠሏቸውና፣ ጋሊልዮን ደግሞ እስር ቤት እንደወረወሩት ይታወቃል። በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ዕውቀትን በሚመለከት የተለያዩ አመለካከቶች እንደመኖራቸው ሁሉ፣ በአንድ የታሪክ ወቅት የበላይነትን የተቀዳጀው ኃይል የሰው ልጅ ዕውነተኛውን የነፃነት መንገድ እንዳይከተልና፣ ሰላምና ብልጽግና የሰፈነበት ኑሮ እንዳይመሰርት በተወሰኑ ምሁራን እንደ
ዕውቀት የዳበሩትን ወደ ርዕዮተ-ዓለምነት በመቀየር የሰውን ልጅ አስተሳሰብ እንዲጠብ ያደርጋሉ። ወደ ውስጥ ጠልቆ እንዳይመራመር በማድረግ ለህብረተስባዊ ውዝግብ ዋና
ምክንያት ይሆናሉ። ዕውነተኛ ስልጣኔን የመቀዳጀቱ ጉዳይ እየተራዘመና እየጨለመ ይሄዳል።
ወደ ኢኮኖሚክስ ስንመጣ ዛሬ በየትምህርት ቤቱ የሚሰጠውና እንደቀኖና የተወሰደው የኒዎ-ክላሲካል ትምህርት ከመፍለቁ በፊት ብዙ የአውሮፓ መንግስታት፣ኋላም አሜሪካ ህብረ-ብሄርን(Nation-State) መገንባት የቻሉት የኔዎ-ክላሲካል ቲዎሪን መሰረት በማድረግ ሳይሆን -በጊዜው እንደዚሁ ዐይነቱ ቲዎሪ በፍጹም አይታወቅም ነበር-የመርከንታሊዝምን ወይም ቀጥተኛና ንቁ የሆነን የኢኮኖሚ ፖሊሲ መመሪያ በማድረግ ነበር። የኋላ ኋላ ሌሎች ቲዎሪዎች ቢፈልቁም ከአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን እስከ አስራዘጠናኛው ክፍለ-ዘመን ማገባደጃ ድረስ የብዙ አውሮፓ መንግስታት የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማኑፋክቱር ግንባታ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ የውስጥ ገበያን በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት፣ ከተማዎችን ማስፋፋት፣ የካናል ሲይስተሞችንና የባቡር ሃዲድን በመስራትና በመገንባት ህዝቡን ማስተሳሰር ነበር። በ18ኛው ክፍለ-ዘመን የአዳም ስሚዙ የነፃ ገበያ መመሪያ ተቀባይነት እንዲኖረው በተለይ እንግሊዝ ከፍተኛ ትግል ብታካሂድም፣ የጀርመን ፈላስፎች፣ የህብረተሰብ ሳይንስ ምሁሮችና ኢኮኖሚስቶች በመቃወምና የራሳቸውን ቲዎሪ በማፍለቅና በማስፋፋት ጀርመን በጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት ላይ እንድትገነባ መሰረት ጥለው አልፈዋል።
የዩሊታሪያን አስተሳሰብ ከተስፋፋ በኋላ የነፃ ገበያ ፍልስፍና እንዳለ እንግሊዝ አገር ተግባራዊ ቢደረግም ከፍተኛ ህብረተሰብአዊ ቀውስ በመፈጠሩና ድህነትም ስልተስፋፋ
በጊዜው የድህነት ፖሊሲን መዋጊያ (Poor Law) በማውጣት ሊሰራ የሚችል ሰው ሁሉ ስራን ሳያማርጥ በዝቅተኛ ደሞዝ እንዲሰራ ተገደደ። ልቅ የሆነ የነፃ ገበያ ፖሊሲ ውድቅ
ከተደረገ በኋላም እንግሊዝም ሆነች ሌሎች የአውሮፓ አገሮች በመንግስት የተደገፈን የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲከተሉ ተገደዋል። በሌላ ወገን ግን በ19ኛው ክፍለ-ዘመን
በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይና በጀርመን መሀከል የነፃ ንግድ ስምምነት ቢደረግም፣ ይህ ዐይነቱ የነፃ ንግድ ስምምነት በጀርመንና በፈረንሳይ ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ስላደረሰ ሁለቱም አገሮች
ስምምነቱን በማፍረስ ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ግንባታ ላይ እንዲሰማሩ ተገደዋል። የኢኮኖሚ ታሪክን ሊትሬቸርና፣ በተለይም በኋላ በማርክስ የተደረሰውን የዳስ ካፒታልን
ስራና የሹምፔተርን የኢኮኖሚ ዕድገት መጽሀፍና እንዲሁም ሌሎች ትችታዊ አመለካከት ያላቸውን መጽሀፎች ላገላበጠ የሚረዳው በአውሮፓ ውስጥ የተካሄደው የኢኮኖሚ ግንባታ
በፍጹም አዳም ስሚዝም ሆነ በኋላ የወጣው የትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ እንደሚነግሩን አይደለም። ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሊታይ የቻለው በስምምነት ላይ ወይም ደግሞ እያንዳንዱ
ግለሰብ የራሱን ጥቅም በማስቀደምና ኢኮኖሚያዊ አርቆ አሳቢነትን መመሪያ በማድረግ አይደለም። የካፒታሊዝም ዕድገት፣ ወይም ደግሞ በማሳመር የነፃ ገበያ ተብሎ ስም
የተሰጠው ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ብዙ ውጣ ውረድን አሳልፎ እዚህ የደረሰና በተወሰኑ ህብረተሰቦች ውስጥ ብቻ ተግባራዊ የሆነ ክንውን ነው። በተለይም የኢንዱስትሪ አብዮት
በተካሄደባት እንግሊዝ አገር የካፒታሊዝም አፀናነስና አስተዳደግ ከውስጥ የገበሬውን መፋናቀልና ወደ ከተማ በመሰደድ ስራ እስኪያገኝ ድረስ እጅግ በአስከፊ ሁኔታ ይኖር
እንደነበር ይታወቃል። ካፒታሊዝም ወደ ገጠር ሲስፋፋ በእርሻ ላይ የተሰማራው የፊዩዳል መደብ በዕድገት ላይ የሚገኘውን የሱፍ ኢንዱስትሪ የጥሬ-ሀብት ፍላጎት ለማሟላት ሲል
በበግ እርባታ ላይ ተሰማራ። ይህ ሁኔታ የትናንሽ ገበሬዎችን አስተራረስ ሁኔታ እንዲቀይር ማድረጉ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ከሚያርስበት እንዲፈናቀል በመደረጉ፣ በተለይም
እንደለንደን ወደ መሳሰሉት ከተማዎች እንዲሰደድ ተገደደ። በኢንዱስትሪ ውስጥ ተቀጥሮ የመስራት ዕድል ያገኘው ሰራተኛ ደግሞ የስራው ሁኔታ እጅግ አሰቃቂና አሰልቺ፣
እንዲሁም ደግሞ በጣም አድካሚ እንደነበር በኢኮኖሚ የታሪክ ምሁራን በደንብ ተተንቶን ተቀምጧል። ይህ ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪ ውስጥ ተቀጥሮ የመስራት ዕድል ያላገኘው ሰፊ
የሰራተኛው ወታደር(reserve army) የግዴታ በመንገድ ስራ፣ በካናልና በድልድይ እንዲሁም ትላልቅ ቤተመንግስቶችንና ካቴድራሎችን ለመስራት ይገደድ ነበር። ዛሬ በብዙ ምዕራብ አውሮፓ ዋና ዋና ከተማዎች የምናያቸው የሚያማምሩ ትላልቅ ህንፃዎች በሰፊው ህዝብ ደም የተገነቡ ናቸው። የትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ እንደሚለን እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ጥቅም ከፍ ለማድረግ ሲል በኢኮኖሚ ክንዋኔ ውስጥ በመሳተፍ የገነባው አይደለም። በሌላ ወገን ድግሞ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር በኒዎ-ክላሲካል የትምህርትቤት ኢኮኖሚክስ ውስጥ ከተማዎችና ህንፃዎች ምን እንደሆኑ አይታወቁም። ምክንያቱም ኢኮኖሚያዊ ክንውን ካለቦታና ጊዜ የሚካሄድ ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው። ይህ ዐይነቱ አመለካከት ደግሞ ፀረ-ሳይንስና ፀረ-ታሪክ ነው። ይሁንና በሪናሳንስ አማካይነት የተካሄደው ጭንቅላትን የማደስ ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ ለግለሰብአዊ ፈጠራነት መንገዱን እንዳመቻቸ የማይታበል ሀቅ ነው። የገበያ ኢኮኖሚ እንደ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መመሪያ ከመወሰዱ በፊት ታውቆም ይሁን ሳይታወቅ በተለይም በብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች የተካሄደው ቅድመ-ስራ የአሪስቶክራሲውንም ሆነ በማደግ ላይ የነበረውን የከበርቴ መደብ እንዲሁም ደግሞ ሰፊውን ህዝብ ጭንቅላቱን በአዲስ ዕውቀት አድሶታል። ኋላ-ቀር ከሆነ የፊዩዳልና ሌሎች ስልጣኔን ከሚቀናቀኑ አስተሳሰቦች እንዲላቀቅ ከፍተኛ የጭንቅላት ስራ ይሰራ ነበር። ስለሆነም ስለካፒታሊዝም ወይም ደግሞ በብዙዎች አነጋገር ስለገበያ ኢኮኖሚ ሲወራ ከላይ ባጭሩ
የሰፈረውን ሀተታ ከቁጥር ውስጥ ሳያስገቡ ዝም ብሎ የነፃ ገበያ እያሉ መወትወት እንዲያውም የባሰውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዳይመጣ እንደመታገል ነው የሚያስቆጥረው። ይህም ማለት ስለ ገበያ ኢኮኖሚ ከመወራቱ በፊትና፣ ካለዚህ ፍቱን መፍትሄ የለም እያሉ ከመወትወት በፊት በመጀመሪያ ለካፒታሊዝም መፀነስ ቅድመ-ሁኔታዎች ከሆኑ ነገሮች ጋር መተዋወቅ ያስፈልጋል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ካፒታሊዝም ደረጃ በደረጃ ያለፈባቻውን የታሪክ ሁኔታዎች መመርመርና ዛሬ ደግሞ እንዴት አድርጎ የብዙ ሚሊያርድን ህዝቦች ዕድል መወሰን እንደቻለ በሰፊው ማጥናት ያስፈልጋል። ይህንን ሳያጠኑ ተግባራዊ የሚሆኑ የኒዎ-ሊበራል የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ከፍተኛ ህብረተሰብአዊ ምስቅልቅልነትን ነው የሚያስከትሉት።
ነፃ ገበያ ወይስ ካፒታሊዝም !
የነፃ ገበያ የሚለው ጽንሰ-ሃስብ ብቅ ከማለቱ በፊት ብዙ ህብረተሰቦች ከሞላ ጎደል የገበያን ኢኮኖሚ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ አዳብረዋል። ገበያ ከህብረተሰቦች ዕድገትና ከስራ-ክፍፍል መዳበር ጋር የተያያዘ ነው። ህዝቦች እንደማህበረሰብ ሲደራጁና ፍላጎታቸውም እያደገ ሲመጣ፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተመሳሳይ ምርት ስለማያመርቱ፣ ፍላጎቱን ለማሟላት ሲባል አንደኛው የህብረተሰብ ክፍል ማምረት የማይችለውን ለማግኘት ሲል ከሌላው ጋር መገበያየት ተገደደ። በገበያ ውስጥ በሚደረግ የተለያዩ አምራቾች ግኑኘነትና፣ በኋላ ደግሞ በነጋዴዎች አማካይነት እያንዳንዱ ግለሰብ፣በመጀመሪያ ዕቃን በዕቃ(Natural Exchange)፣ በኋላ ደግሞ ገንዘብ የዕቃዎች ወይም እህል መለዋወጫ መሳሪያ ሆኖ ሲዳብር ተጠቃሚው የፈለገውንና የቻለውን በመግዛት ፍላጎቱን ያሟላ ነበር። እንደዚህ ዐይነቱ የገበያ ልውውጥ እንደ አገር በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ውስጥ በተወሰነ ክልል በመካሄድና በማደግ፣ በኋላ ደግሞ በተለያዩ አገሮች መሀከልም በመስፋፋት የሩቅ ንግድ እየተባለ ለሚጠራው በር ከፈተ። በሩቅ ንግድ አማካይነትም በተለያዩ ማህበረሰቦች ዘንድ የዕቃ ልውውጥ ብቻ ሳይሆን የባህልም ግኑኝነት በመፈጠር፣ በጋብቻና በመዋለድ ለአንዳንድ አገሮች የህብረተሰብአዊ ለውጥ እምርታን አምጥቷል።
በተለይም በእንደዚህ ዐይነቱ ልውውጥ ተጠቃሚና፣ ህብረተሰብአዊ ለውጥን በማምጣት የሩቅ ንግድ ዐይነተኛ ሚና የተጫወተባቸው አገሮች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ናቸው።
በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ነው በሩቅ ንግድ አማካይነት ቀስ በቀስ የስራ ክፍፍል መዳበር የቻለውና፣ ነጋዴዎችም ብዙ ገንዘብ በማከማቸትና የዕደ-ጥበብ ስራዎችን በመቆጣጠርና
የፊዩዳሉን መደብ በዕዳ በመተብተብና ልዩ የፍጆታ አጠቃቀም በማስለመድ ቀስ በቀስ ወደ ኢንዱስትሪ ከበርቴነት ሊለወጡ የቻሉት። በአውሮፓ የኢኮኖሚ ግንባታ ታሪክ ውስጥ
ከፊሉ የነጋዴ መደብ ወደ ኢንዱስትሪ ከበርቴነት ሲቀየር ዝም ብሎ ሀብት ማጋፈፍ ብቻ ሳይሆን ስራው፣ በባህላዊ እንቅስቃሴና በከተማ ግንባታዎች ስራ በመሰማራት የህብረተስቡ
አኗኗር በዕውቅ(Rationalize) ላይ እንዲገነባና እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ጀመረ። በዕውቅ ላይ ያልተመሰረተው የፊዩዳሉ ስርዓት፣ በከተማዎች ግንባታ፣ በዕደ-ጥበብ ሙያ መስፋፋትና
በንግድ ማበብ መልክ እየተዳከመና ለሌላና ለተሻለ የአኗኗር ስርዓት መንገዱን እንዲለቅ ተገደደ። ፍልስፍና፣ ድራማና አርክቴክቸር ሲያብቡ፣ በተለይም የከበርቴውና የአርስቶክራሲው የአኗኗር ስልት ከራስ በማለፍ ህብረተሰቡ ሊተሳሰር የሚችልበትን ሁኔታ እንዲያዘጋጁ ተገደዱ። በነሼክስፔር፣ በሼሊና የኋላ ኋለ ደግሞ በጀርመን ክላሲኮች የድራማና የክላሲካል ሙዚቃ አማካይነት በማደግ ላይ የነበረውን የከበርቴ መደብና የአርስቶክራሲ አገዛዝ ጭንቅላት እንዲታነጽ በማድረግ የከበርቴው ሰብአዊነት ቀስ በቀስ ሊስፋፋ ቻለ። ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከህብረተሰብአዊ ዕድገት ተነጥሎ ሊታይ የማይችል ሆኖ ተቀባይነትን በማግኘት ስራዎች በሙሉ ጥበብንና(aesthetic)  ስርዓትን እንዲይዙ ተደረጉ።
ከዚህ ባሻገር፣ በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ በየጊዜው የህዝብ ቁጥር እያደገ ሲሄድና ፍላጎትም ሲጨምር ብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በአንድ ዐመት ውስጥ ሶስት ጊዜ ሊያመርቱ የሚችሉበትን ሁኔታ(The Three Field Farming System) አዳበሩ።
በተጨማሪም በበሬ ከማረስ ይልቅ በፈረስ እየታገዙ በማምረት ምርት ሊያድግ የሚችልበት ሁኔታ ተዘጋጀ። በአገር ውስጥ ምርት ብቻ የህዝብ ፍላጎት ማሟላት ባልተቻለበት አገሮች
ውስጥ መንግስታት ከውጭ እህል በማስመጣት የህዝቡን ፍላጎት ያሟሉ እንደነበር፣ የተገደዱበት ጊዜ ነበር። ይህንን ጉዳይ ፕሮፌሰር ሚስኪሚን ሃርይ የመጀመሪያውና
የመጨረሻው ዘመን የሬናሳንስ ኢኮኖሚ(The Economy of Later Renaissance Europe, 1460-1600) በሚለው መጽሀፋቸው ውስጥ በዝርዝር ያስረዳሉ። በተጨማሪም ፕሮፌሰር ጞልድትዋይት፣ የሬናሳንስ ኤኮኖሚ በፍሎሬንሰ( The Economy of Renasissance Florence)  በሚለው ግሩም መጽሀፋቸው የኢጣሊያን ኢኮኖሚ በዘፈቀደ ሳይሆን በዕውቅ ላይ የተገነባና፣ ጣሊያንም በተለይም በኢንዱስትሪ ምርት አይላ ትገኝ እንደነበር ነው የሚነግሩን። ከነዚህ መጽሀፎችም ሆነ ከሌሎች አያሌ የኢምፔሪካል ጥናቶች መረዳት የሚቻለው፣ በነፃ ገበያ አማካይነት ሁሉም እንደፈለገው እህሉን ውጭ እያወጣ መቸብቸብ ይችላል የሚል ሳይሆን፣ በዕውቅና በመጀመሪያ ደረጃ የየህበረተሰቡን ፍላጎት ማሟላት ያስፈልጋል የሚለውን መመሪያ በመውሰድ ነው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ህብረተሰብአዊ ግንባታ ሊካሄድ የተቻለው። ማንም እንደፈለገው መሸጥ ይችላል እየተባለና የውጭ ካረንሲ ለመቃረም ሲባል በአገር ውስጥ የሚመረትን ምርትም ሆነ ፍራፍሬዎች እየሟጠጡ ወደ ውጭ በመላክና መሬትን ለውጭ „እንቬሰተሮች“ በማከራየት አልነበረም በአውሮፓ ምድር ውስጥ ካፒታሊዝም ማደግ የቻለው። በአውሮፓ ምድር ውስጥ የካፒታሊዝም ዕድገት በውስጥ ኃይሎች የተካሄደ ሲሆን፣ ከውጭ የመጣውን አስተሳሰብ ደግሞ ቀስ በቀስ ውስጣዊ ባህርይ(intermalize) እንዲኖረው በማድረግና በማገናኘት ለህብረተሰብና ለኢኮኖሚ ግንባታ ጠቃሚ እንዲሆን ተግባራዊ ማድረግ ነበር። ይህም ማለት የውጭው ባህልና የአሰራር ኖርሞች፣ እንዲሁም ከውጭ የተቀዱ የተክኖሎጂ አሰራርና ፈጠራ የግዴታ በሰው ጭንቅላት ውስጥ እንዲቀረጹ ከፍተኛ ትግል ይደረግ ነበር። ከውጭ የሚመጡ አሰተሳሰቦች የራሳቸውን ደሴት በመስራት በራሳቸው ክልል ብቻ እንዲሽከረከሩ የሚደረጉ አልነበሩም። የአውሮፓን የካፒታሊዝም ዕድገት ለተመለከተ፣ አንደኛው አገር ከሌላው አገር እየኮረጀ ሁለ-ገብ ዕድገትን እንዳመጣ መገንዘብ እንችላለን። እንደአገራችን ዕውቀት የጋን መብራት በመሆንና የራስን ዓለም በመመስረት ከሰፊው ህዝብ ጋር ሳይገናኙ አይደለም ካፒታሊዝም በአውሮፓ ምድር ውስጥ ማደግ የቻለውና፣ ዓለምን መቆጣጠርና አልፎ አልፎም ማዳረስ የቻለው።
ገበያ በህብረተሰብ የታሪክ ዕድገት ውስጥ ግዴታ የሆነውን ያህል፣ የኋላ ኋላ በተለይም የእነ ጆን ሎክና የሌሎች ዩቲላቴሪያን አስተሳሰብ በአሸናፊነት ሲወጣ፣ካፒታሊዝምና የግል ሀብት ተያይዘው በመውጣት በህብረተሰብ ውስጥ የመደብ አከፋፈል ግልጽ እየሆነ መጣ። የምርት መሳሪያዎችና ሌሎች ሀብቶች የሌለው የግዴታ የስራ ጉልበቱን እንዲሸጥ ተገደደ። ተቀጥሮ በመስራት ብቻ ገንዘብ በማግኘት የቀን ተቀን ፍላጎቱን ማሟላት ቻለ። አዲስ በተፈጠረውና ውስብስብ እየሆነ በመጣው ግኑኝነት መሰረት፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ኃይሎች በምርት የስራ ቦታና በገበያ የሚገናኙ ሁኑ።
ገንዘብም ከዕቃ ባህርዩ(Commodity Character) በመላቀቅ እቃዎችን በፍጥነት ማሽከርከሪያ መሳሪያ በመሆን ህብርተሰብአዊ ኃይል እየሆነ መጣ። ለብዙ መቶ ዐመታት ወርቅ፣ ብርና መዳብ እንዲሁም ሌሎች ለፍጆታ ጠቀሜታ የሚያገለግሉ እንደገንዘብም በማገልገል ለገበያ ዕድገት ዕምርታን መስጠት ችለዋል። ካፒታሊዝም እያደገና እየተወሳሰበ ሲመጣ ግን እነዚህ የፍጆታ ባህርይ ያላቸው ገንዘቦች እያደገ የመጣውን ፍላጎት ማሟላት አልቻሉም።ለዕቃዎች በሰፊው መሸከርከር የሚያመች፣ በቀላሉ ካለብዙ ወጪ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ
ሊሽከረከር የሚችል በመንግስት የተደገፈ የወረቀት ገንዘብ አስፈላጊ እየሆነ መጣ። ስለሆነም፣ በመንግስት የተደገፈ የወረቀት ገንዘብና ሳንቲም በብዛት በመታተም የካፒታሊዝምን ዕድገት ማፋጠን ቻሉ። የወረቀት ገንዘብ የበለጠ ተቀባይነትን እያገኘ ሲመጣም የሰው በሰው ግኑኝነትም እየተለወጠ መጣ። ገንዘብ የህበረተሰብአዊ ግኑኝነት መለኪያ ሆነ። ተራ የገበያ ኢኮኖሚ ወይም የነፃ ገበያ የሚለው አባባል አዲስ በተፈጠረው የሀብት ቁጥጥርና የህብረተሰብ ግኑኝነት አማካይነት ወደ ካፒታሊዝምነት ተለወጠ።
ካፒታሊዝምም ህብረተሰብአዊ ስርዓትን መግልጫና ብዙ ነገሮችን ያካተተና የያዘ ሆነ። ለዚህ ነው ማርክስም ሆነ ሹምፔተር ካፒታሊዝምን ዝም ብለው ነፃ ገበያ ወይም የገበያ
ኢኮኖሚ ብለው የማይጠሩት። ምክንያቱም እንደዚህ ዐይነቱ አባባል ያልተሟላና ብዙ ነገሮችን ስለማያካትት ነው። ይህም ማለት ካፒታሊዝም ህብረተሰብአዊ ግኑኝነትንም
ሲገልጽ፣ በህብረተሰቡ ውስጥ በገቢ አከፋፈልና ምድብ የሚገለጽና፣ አንዲሁም በህብረተሰብ የኑሮ ሁኔታ(Social Status) የሚታይ ህብረተሰብአዊ አወቃቀር የካፒታሊዝም
አንደኛው ገጽታ መሆን ቻሉ። በሌላ ወገን ግን የእነ አዳም ስሚዙ አገላለጽ ታሪካዊ አይደለም፤ የማርክስም ሆነ የሹምፔተር እንዲሁም የሌሎች የታሪክን ዕድገት ያካተተና
ካለ ምርት ኃይሎች ዕድገት(Production Forces)፣ ማለትም ካለቴክኖሎጂ ምጥቀት ሊገለጽ አይችልም። በተጨማሪም የአዳም ስሚዙ የገበያ ኢኮኖሚ፣ በተለይም ደግሞ የኒዎ-
ክላሲካል የገበያ ኢኮኖሚ ፅንሰ-ሃሳብ ውስጣዊ ኃይል የሌለውና፣ ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ የማይሸጋገር ሲሆን፣ የማርክስም ሆነ የሹምፔተሩ በዚያ ባለህበት ቆሞ የሚቀር አይደለም። ለዚህም ነው የአራት መቶ ዓመትን የካፒታሊዝምን ዕድገት በጥብቅ የተከታተለ፣ ምርት በዐይነትና በብዛት መመረቱ ብቻ ሳይሆን፣ የምርት ማምረቻ መሳሪያዎችም ምጥቀትን በማግኘት የሰው ልጅ ከቴክኖሎጂ ጋር ያለውን ግኑኝነት መለወጥ እንዲችል የተገደደው። በቴክኖሎጂ መሻሻል የስራ ሰዓት መቀነሱ ብቻ ሳይሆን፣ ሰራተኛው ከአዲሱ ቴክኖሎጂ ጋር ለመስተካከል ሲል በፍጥነት መስራት ተገደደ። አጠቃላይና የተስፋፋ የሀብት ክምችት (Expanded Capital Accumulation) በመዳበር ካፒታሊዝም በአገር ብቻ እንዳይወሰን ተገደደ። ቀሰ በቀስ እያለ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ እየያዘ መምጣት ቻለ።
አዲሱና የተሻሻለው የቴክኖሎጂ ለውጥ አሰራር አንድ ሰው ብቻውን ሆኖ የተወሰኑ በተኖችን ብቻ በመንካት የምርትን ሂደት እንዲያፋጥን አስቻለው ። በዚያውም መጠን በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አማካይነት የሰው ኃይል ትርፍ(Redundant) እየሆነ እንደመጣ እንመለከታለን። በቴክኖሎጂዎች ምጥቀትና ውድድር አማካይነት የካፒታል ክምችትና(Concentration of Capital) የኢንዱስትሪና የባንክ ካፒታል እየተቆላለፉ በመምጣት፣ ፋይናንስ ካፒታል የኢንዱስትሪን ዕድገትና የቴክኖሎጂን ምጥቀት መወሰን
ቻለ። በተጨማሪም፣ የኢንዱስትሪ ካፒታል እየመጠቀ የመጣውን ያህልና የካፒታል ክምችት ያደገውን ያህል፣ በአንድ በኩል መጠነኛና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወይም ባህላዊ የዕደ-ጥበብ ስራዎች እየተዳከሙና እየጠፉ ሊመጡ ችለዋል። ከዚህም በላይ የማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ዕድገት፣ መኖርና ያለመኖር በትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ውስጠ-ኃይለ የሚወሰን መሆን ቻለ። ምክንያቱም መጠነኛና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ተለዋዋጭ ዕቃዎችንና(Spare parts) መጠገኛዎችንም ሆነ ዋና ዋና ክፍሎችን አምራች ስለሆኑ፣ ለምሳሌ የመኪና ገበያ በሚቀዘቅዝበት ጊዜ ትናንሽ ኢንዱስትሪዎችም ይዳከማሉ ማለት ነው። ይህም የሚያመለክተው የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ርስበራሳቸው የተያያዙና(Value-added chain)አንደኛው በሌላው ላይ የተመካና፣ የአንደኛው መዳከም ወይም መጠንከር በሌላው ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል ማለት ነው። ይሁንና ግን በዘመነ-ግሎባላይዜሽን፣ ለምሳሌ የአንድ
መኪና የተለያዩ ክፍሎች እዚያው ፈጣሪው አገር ብቻ አይመረቱም። የማምረቻን ዋጋ ለመቀነስ ሲባል የተወሰነው የመገጣጠሚያ ክፍል በተለያዩ አገሮች በመመረት የመጨረሻ
መጨረሻ ዋናው አምራች አገር ምርቶቹ በመገጣጠም የመጨረሻው ምርት ውጤት ገበያ ላይ ይቀርባል። ስለሆነም የዛሬው የገበያ ኢኮኖሚ ወይም ደግሞ ካፒታሊዝም ከሶስት
መቶና አራት መቶ ዐመት በፊት ከነበረው በብዙ መቶ እጅ ልቆ የሚገኝ ነው።
ካለምንም የጭንቅላት ማስጨነቅ ዛሬ የቴክኖሎጂዎችን ዕድገት ስንመለከትና የፍጆታ ዕቃዎችንም ስንጠቀም ሁሉም ነገር በጤናማ መልክና ካለ ውስጣዊ ቅራኔ የሚካሄድ ነው
የሚመስለን። በመጀመሪያ በምዕራብ የካፒታሊስት አገሮች የሰራተኛው መደብ መብቱን ለማስጠበቅ ሲል በሙያው ማህበሩ አማካይነት ከፍተኛ ትግል ያደርጋል። በተለይም ባለፉት
ሰላሳ ዐመታት በካፒታሊዝም ዕድገት ውስጥ የታዩት አሉታዊ ክስተቶች የሰራተኛውን መደብ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያሸጋሽግ አድርገውታል። ትላልቅ ኩባንያዎች ትርፍ ለማካበት ሲሉ
የተወሰነውን የኢንዱስትሪ ክፍል ርካሽ የስራ ጉልበት ባለበት አገር እየወሰዱ በመትከል ወደ ውስጥ ብዙ ስራተኞች እንዲባረሩና የባህልም ውድቀት እንዲመጣ አድርገዋል። የትራዲሽናል ኢንዱስትሪዎች በግሎባላይዜሽን አማካይነት መዳከማቸው ብቻ ሳይሆን፣ ካፒታል ወደ ሌሎች አገሮች ተወስዶ እንዲተከል በማድረግ በየአገሮች ውስጥ ከኢንዱስትሪ መስክ ጋር የተያያዙ ሌሎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችም እንዲዳከሙ ተደርገዋል። በዚያው መጠንም በተለይም በትናንሽ ከተሞች ውስጥ በኢንዱስትሪዎች መፈናቀልና በሰራተኛው ከስራው ቦታው መባረር የተነሳ የሎካል አስተዳደሮች ከህዝብ የሚሰበስቡት ግብር(Tax) እጅግ እየቀነሰ መጥቷል። ይህ ማለት ደግሞ ትምህርት ቤቶችን ለማደስ፣ ከተማዎችን ለማፅዳትና ሌሎች የሶሻል መስኮችን ለመደጎም የሚያስፈልገው ወጪ እየቀነሰ ሊመጣ ችሏል ማለት ነው።
በተለይም የፊናንስ ካፒታል በከፍተኛ ደረጃ ማደግና ራሱን ከኢንዱስትሪ አግሎ በገንዝብ አማካይነት ብቻ ትርፍ ማካበት መቻል ብዙ መንግስታትን ከቁጥጥር ውጭ እያደረጋቸውና በተራ የሞኔተሪ ፖሊሲ ብቻ የኢኮኖሚውን ዕድገት ሊቆጣጠሩና የኢኮኖሚውን መዛባትም ሊያርሙ የሚችሉበት ሁኔታ እጅግ እየጠበበ መጥቷል። የዚህ ዐይነቱ የፊናንስ ካፒታል ማደግና በተለያዩ ዐይነቶች መገለጽ፣ ለምሳሌ ሄጅ ፈንድስ ወይም ኢንቬስሜንት ካፒታል በሚባሉት መልኮች የሚሽከረከረው የፊናንስ ካፒታልና፣ ይህ ደግሞ እንደገና ከትላልቅ ባንኮች ጋር መቆላለፍ የብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮችንና አንዳንድ የደቡብ አውሮፓን ኢኮኖሚዎችንም ከመቆጣጠር አልፎ እያፈራረሰቸውም እንደመጣ እንመለከታለን። ዛሪ ግሪክን እዚህ መቀመቅ ውስጥ የከተታት ከራሷ የውስጥ ኢኮኖሚ አወቃቀር ድክመት ባሻገር የፊናንስ ካፒታል አይሎ መውጣትና በዕዳ ወጥመድ ውስጥ እንድትገባ በማድረጉም ጭምር ነው። በተጨማሪም እጅግ ልፍስፍስ የሆነ የፖለቲካ ኤሊት ለፊናንስ ካፒታል አጎብዳጅ በመሆኑም ጭምር ነው። የአውሮፓው አንድነትን የአንጀት አጥብቅ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጠጋ ብሎ ለተመለከተ የባሰውን የግሪክን ኢኮኖሚ የሚያዳክምና የባሰ የውስጥ ካፒታል ወደ ውጭ እንዲወጣ የሚያግዝ ነው። ግሪክ ከፋይናንስ ገበያ ላይ የምትበደረው ተጨማሪ ብድር ወይም ከአውሮፓ አንድነት የምታገኘው ብድር የጀርመንንና የፈረንሳይ ባንኮችን ከኪሳራ ለማዳን የሚውል ነው። በዚህ መልክ ብዙ አገሮች መቀመቅ ውስጥ እንዲገቡና እንዲራቆቱ ሆነዋል።
ይህ የካፒታሊዝም አንደኛው ገጽታ ሲሆን፣ በምርት አማካይነት በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተስፋፋው የምርት ክንውን ለእነዚህ አገሮች በምንም ዐይነት ዕድገትንና
ስልጣኔን ሊያጎናጽፋቸው አልቻለም። ከአስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የሚካሄደውን የካፒታሊዝምን በዓለም አቀፍ ደረጃ መስፋፋት ስንመለከት ዋናው ዓላማው ስልጣኔና
እንዲሁም ደግሞ ሳይንስንና ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት ሳይሆን የጥሬ ሀብትን ማካበት ነው።
ለዚህ ደግሞ በተወሰኑ መስኮች ላይ ብቻ መረባረብ ሲሆን፣ እንዲዚህ ዐይነቱ በጥሬ ሀብት ማውጣት ላይ ያተኮረ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ፣
በተለይም በአፍሪካ ውስጥ የሀብት ዘረፋ በማካሄድ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዳይመጣ አግዷል። ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀልና፣ ከተማዎች ካለምንም ዕቅድ መሰራትና መቆሽሽ
የብዙ አፍሪካ አገሮች ዕጣ ሆኗል ማለት ይቻላል።
በዘመነ-ግሎባላይዜሽን ደግሞ ከኢንዱስትሪ አገሮች እየተነቀሉ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የሚተከሉት ኢንዱስትሪዎች ከውስጥ ዕውነተኛ ሀብት ፈጣሪዎች ያልሆኑና ህዝቡም
ቴክኖሎጂን እንዳይማር የሚያግዱ ናቸው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኢንዱስትሪዎቹ በትላልቅ ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር ያሉና ከላይም የሚቀመጡ ማኔጀሮች የራሳቸው ነፃነት የሌላቸው
ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ቴክኖሎጂዎቹ ከምርምርና ከዕድገት ጋር የተያያዙ አይደሉም።
ቀጥታ ግኑኝነታቸው ከእናት አገሮቻቸው ጋር ነው። በሶስተኛ ደረጃ፣ የሚመረቱት ምርቶችለዓለም ገበያ ተብለው ስለሆነ ወደ ውስጥ በእነዚህ አገሮች ውስጥ ለገበያው ማደግና
መስፋፋት የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ እጅግ ዝቅተኛ ነው። በአራተኛ ደረጃ፣ በየፋብሪካው ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ሰራተኛ ደሞዝ በጣም አነስተኛ ስለሆነ ሰራተኛው ምርቶችን
ገዝቶ የመጠቀም ኃይሉ በጣም ዝቅተኛ ነው ማለት ነው። በአምስተኛ ደረጃ፣ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ የሚከተሉት ኢንዱስትሪዎች ከየአገሩ ባንክ ጋር ምንም
ግኑኝነት የላቸውም። ይህ ማለት ደግሞ የገንዘብን በፍጥነት መሽከርከርና ህብረተሰብአዊ ኃይል ማግኘት በከፍተኛ ደረጃ ያግደዋል ማለት ነው። በኢንዱስትሪና በባንክ ማሀከል
ግኑኝነት ሲኖር ብቻ ነው የገበያ ኢኮኖሚ ማደግ የሚችለው። በስድስተኛ ደረጃ፣የሰራተኞችንና የስራ ቦታ ሁኔታ ለተመለከተ እጅግ በአሰቃቂ ሁኔታ ነው የሚሰሩት።
የምንለብሳቸው ጂንሶችና የምንጠቀምባቸው የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች በሙሉ በርካሽ ጉልበት የተመረቱ ብቻ ሳይሆኑ፣ ብዙ ወጣት ሴቶች ጤንነታቸው በከፍተኛ ደረጃ እየተቃወሰ
የሚመረቱ ምርቶች ናቸው። አብዛኛዎቹ በሰላሳና በአርባ ዐመታቸው በጤንነት መቃወስ የተነሳ ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ። ኑሮን ሳይኖሩ ይሞታሉ። ብዙዎችም የአልጋ ቁራኛ
ይሆናሉ። ይህንን ነው እንግዲህ የዛሬው ካፒታሊዝም የሚመስለውና፣ በአገራችን ደግሞ ዘመኑ የግሎባላይዜሽን ዘመን ነው እየተባለ የሚወደስለትና ካለቡዙ ቅራኔዎች በዓለም አቀፍ
ደረጃ ይስፋፋ ይመስል የሚነዛው። ብዙዎች ካለማውቅ በሚያናፍሱት ወሬና በፊናንስ ካፒታል ግዳጅ በሚያካሂዱት የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተነሳ የብዙ መቶ ሚሊዮኖች ህዝብ
እየተረበሸና ጤናማና ለስልጣኔ የሚያመች ረጋ ያለ ኢኮኖሚ እንዳይገነቡ እየታገዱ ነው።
ዛሬ በአገራችን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚያወጡትና እነሱ የሚሉትን የገበያ ኢኮኖሚ የሚያራምዱ በነሱ ባልበሰለ ሁኔታ በሚካሄድ ፖሊሲ አማካይነት የተፈጸመውና የሚፈጸመው ወንጀል የማይታያቸው ይህንን የካፒታሊዝምን ውስጣዊ ቅራኔና ሂደት በቅጡ ካለመራዳት የተነሳ ነው። አላዋቂ ሳሚ … እንደሚሉት አነጋገር።
ውድድርንና የካፒታሊዝም ዕድገት !
የገበያ ኢኮኖሚ ወይም ካፒታሊዝም እንደ አገራችን በተራ ነጣቂነት ወይም ዐይን ባወጣ ዘራፊነት የሚደነገግና ውስጠ-ኃይል የሚያገኝ አይደለም። ማርክስ እንደሚለውና በትክክልም እንደሚረጋገጠው ውድድር(Competition) የካፒታሊዝም ዋናው አንቀሳቃሽ ኃይል ነው። ቴክኖሎጂያዊ ምጥቀትም የሚታየው በውድድር አማካይነት ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ
በከፍተኛ ምርምርና ፈጠራ እየታገዙ ማምረት ያስፈልጋል። እያንዳንዱ በገበያ ላይ ምርት እያመረተ የሚያቀርብ ካፒታሊስት ተወዳዳሪውን በመርዝ ወይንም በአንዳች ነገር ህይወቱን
ለማጥፋት ወይም ለመግደል ተንኮል የሚያብሰለስል ሳይሆን፣ በምን መንገድና እንዴት አድርጌ ምርት ባመርት ተወዳዳሪዬን ለማሸነፍ እችላለሁ፣ ወይም የበለጠ የገበያ ድርሻ
ይኖረኛል ብሎ ታጥቆ በመነሳት የእንቬስትሜንት ስትራቴጂውን ይቀይሳል። ከዋጋ አንፃር የማምረቻ ዋጋን በመቀነስና ምርትን በነፍስ ወከፍ ሲተመን በማሳደግ(Productivity)፣
እንዲሁም ደግሞ ምርቱ ጥራት እንዲኖረው በማድረግ ብቃትነቱን በማሳየት በገበያ ውስጥ ለመቆየት ጥረት ያደርጋል። በየጊዜው የምርቱን ሁኔታ ይለዋውጣል። ለምሳሌ በአንድ
ወቅት የተወሰነ ምርት፣ መኪና ወይም ማቀዝቀዣ የተወሰነ የፍጆታ ዘመን ነው ያላቸው።
በመጀመሪያው ወቅት አዲስ ምርት ገበያ ላይ ሲወጣ እንደብርቅ ይታያል። ቀስ በቀስም ሰው እየለመደው ሲሄድ ገዝቶ ይጠቀማል። በገበያ ላይ የመሸጡ ኃይል እያደገ ይመጣል።
ሌላው ተመሳሳይ ምርት የሚያመርት ካፒታሊስት ውበቱንና የአጠቃቀሙን ዘዴ በመለወጥ ተመሳሳይና የተሻሻለ ምርት ለገበያ ያቀርባል። የድሮውም ምርት ገበያ ላይ ተገዢነቱ
እየቀነሰ በመምጣት ከገበያ ላይ እየተስፈናጠረ ይወጣል። በዚህ መልክ በስድሳኛውና በሰባኛው ዓ.ም ይመረቱ የነበሩ መኪናዎችም ሆነ ማቀዝቀዣዎች ዛሬ በፍጹም አይገኙም።
በተጨማሪም የኃይልን አጠቃቀምና የአካባቢን ብክለት ለመቀነስ ሲባል በተለይም የረዥም ጊዜ ዕድሜ ያላቸው ምርቶች በጥራትም ሆነ በአጠቃቀም ደረጃ እጅግ እየተሻሻሉና
ለምችቶም አጋዥ እየሆኑ መጥተዋል።
ውድድር ለካፒታሊዝም ዕድገት አንቀሳቃሽ ኃይል የሆነውን ኃይልና፣ የገበያ ኢኮኖሚ የሚለው ተራ አነጋገር በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን ያህል፣ ይህ ዐይነቱ በውድድር ላይ የተመሰረተ የገበያ ኢኮኖሚ ከህግ ውጭ የሚሰራ ነው ማለት አይደለም። በአምራችና በነጋዴ መሀከል ያለው ግኑኝነት በአንድ ወገን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በነጋዴውና
በተጠቃሚው መሀከል ያለው ግኑኝነት በህግ ላይ ተመርኩዞ የሚንቀሳቀስ ነው። በመጀመሪያ አምራቹ ካለምንም ማጭበርበር ምርቱን አምርቶ ለነጋዴው ያቀርባል። ነጋዴው በአምራቹ
ላይ ሙሉ ዕምነት አለው ማለት ነው። የሚያጭበረብር አምራችና ነጋዴ በህግ ተጠያቂዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ምናልባት በምርቱ አጠቃቀም ላይ የተወሰነ ኖርምን ተከትሎ ያልተሰራ
ምርት አደጋ የሚያደርስ ከሆነ አምራቹ እንደ አደጋው ዐይነት ፈቃዱን እስከመነጠቅ ይደርሳል። ይህ ዕይነቱ ህግ ጠቅላላውን የገበያ ሂደት የሚመለከትና ብዙ ነገሮችን የሚያካትት ነው። ከዚህም በላይ በአለፉት ሰላሳና አርባ ዐመታት ተጠቃሚው በዕውቀት እየዳበረ ሰለመጣና፣ የተጠቃሚዎችም ማዕከል(Consumer Protection Agency) ወይም ድርጅት ስላለ፣ ተጠቃሚው በምርት አጠቃቀም የሚደርስበት ጉዳትም ሆነ ያለተሰተካከለ አጠቃቀም ዘዴ አቤቱታ ሊያሰማና ሊከስም ይችላል ማለት ነው። ይህም ማለት በአገራችን በዘልማድ አነጋገር እንደሚናፈሰውና እንደሚሰራበት የገበያ ኢኮኖሚ ሳይሆን፣ የምዕራቡ የገበያ ኢኮኖሚ ስርዓትን ይዞ የሚጓዝና በጣም የተወሳሰበ ነው። ከዚህም በላይ በስርዓቱ ውስጠ-ኃይልነትና የሰዎችም የፈጠራ ችሎታ የተነሳ ከአንድ ዐይነት ነገር የተለያዩ ብዙ ነገሮችን ማምርት ይችላል። ለምሳሌ ከእንጨት፣ እንደ ባህርይው ከልጆች መጫዎቻ አንስቶ የተለያዩና የሚያማምሩ መቀመጫዎችና ወንበሮች እንዲሁም ልዩ ልዩ ነገሮች ማምረት ይቻላል። እንዲሁም ከተለያዩ የፍራፍሪ ወይም ጥራጥሬ ነገሮች በመቶዎች የሚቆጠሩ ለመቀቀያና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚያገለግሉ የዘይት ጭማቂ ማምረት ይቻላል። በካፒታሊስት አገሮች እንደኛ አገር ኑግን፣ ተልባን፣ ሰሊጥን፣ ሱፍንና ሌሎች ነገሮችን የውጭ ካረንሲ ለመቃረም ሲባል እስከነነፍሳቸው አይላኩም። ይህንን የሚያደርግ ስለኢኮኖሚ ዕድገት ምንነትና በኢንዱስትሪዎች መሀከል ስለሚኖረው ውስጣዊ ግኑኝነት የማያውቅ መሆን አለበት። እንደዚህ የሚያደርግ መንግስት በዚያውም መጠንም የውስጥ ገበያን ዕድገት ይዘጋል። ነጋዴው እዚያው ቀጭጮ እንዲቀር ያደርገዋል። በአጠቃላይም ህብረተሰብአዊ ለውጥ እንዳይመጣ መንገዱን ሁሉ ያፍናል። የህዝቡን የፈጠራ ስራ ከማፈኑም የተነሳ ኑሮው የተዘበራረቀ እንዲሆን ያደርጋል።
ስለዚህም ስለውድድር በምናወራበት ጊዜ የኢኮኖሚው ኤጀንቶችን የፈጠራ ችሎታና በየጊዜው እንደገበያው መለዋወጥ ከሁኔታው ጋር ሊኖር የሚችለውን መጣጣምና በፍጥነት መጓዝ ማጤን ያስፈልጋል። በዚህ ላይ ለውድድሩ መጧጧፍ የጊዜ ኢኮኖሚና ቦታ(Time &Space) ከፍተኛ ሚናን ይጫወታሉ። አንድን ዕቃ አምርቶ ወደ ሌላ ቦታ በፍጥነት ለማድረስ ፈጣንና በቀላሉ አደጋ ሊያደርስ የማይችል የትራንስፖርቴሽን ማገልገያ ያስፍልጋል። እንደዚሁም በመርከብ፣ በባቡርና በመኪና ሊጫኑ የሚችሉ ዕቃዎችን መለያየት ያስፈልጋል። ጤናማና ጥንቃቄ የተሞላበት የማከማቻ ቦታ ለዕቃዎች መከማችትና ለረዥም ጊዜ መቆየት ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። ወደ ቦታ ስንመጣ ይህ ዐይነቱ አገላለጽ በደንብ ከተደራጀ ገበያና መደብር ጋር የተያያዘ ነው። በሚያማምሩ ከተማዎችና መንደሮች የሚገለጽ ነው። ስርዓት ያለው የቤት አሰራርና የተለያዩ ተግባር ያላቸውን ቤቶችና አዳራሾች የሚመለከት ነው። የገበያ አዳራሾች ውብና ሰፋ ብለው እንዲሁም ማራኪ ሆነው መሰራት አለባቸው። በዘመኑ ሁኔታ ደግሞ ከመናፈሻና ከልጆች መጫዎቻዎች እንዲሁም በአካባቢው ማራኪ ከሆኑና ሰውን ከሚጋብዙ ቡና ቤቶች፣ የቲያትርና የሲኒማ እንዲሁም ልዩ ልዩ የመዝናኛ ቦታዎች ጋር የመሰራትንና የመዘጋጀትን እንዲሁም መያያዝን ጉዳይ ይጠይቃል። በዚህ መልክ የሚዘጋጅና በአካባቢው አንድ ወጥ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የምርት ዐይነቶች ተደራጀተው የሚገኙ ከሆነ ለገበያው ዕድገትና ለውድድር ከፍተኛ ዕምርታን ይሰጣል ማለት ነው። ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ምድር የሚነዛው ስለገበያ ኢኮኖሚ ሳይንሳዊ ባህርይ የሌለው በተራ ችርቻሮ ላይ የተመረኮዘና ተዋንያኖችን የበለጠ የሚያንቀዠቅዥና አጭበርባሪ የሚያደርጋቸው ነው። እነ አቶ መለሰና ግብረ አበሮቻቸው እንደዚህ ዐይነቱን ኢኮኖሚ ነው አንዳንዴ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ እያሉ የሚነግሩን። አልፎ አልፎ ደግሞ የለም እኛ ኒዎ-ሊበራሊዝምን የምንዋጋና በመንግስት የተደገፈ(Developmental  State) የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው የምንከተለው እያሉ እዚያው በዚያው የሚላግጡብንና ግራ ለለማጋባት የሚሞክሩት። ይህም የሚያመለክተው ተዩን ያህል የገዢው መደብና ተከታዮቹ እንደተምታታባቸው ነው።
ከዚህ ባሻገር ተመሳሳይ ምርት በሚያመርቱ ካፒታሊስቶች መሀከል የሚካሄደው ውድድር በአገር ውስጥ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። እንደሚታወቀው ዛሬ የካፒታሊስት የምርት ክንውን ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ብቻ ሳይሆን ያለው የፍጆታ አጠቃቀሞችም ዓለም አቀፍ ባህርይ ይዘው መጥተዋል። ይህም ማለት በአገር ውስጥ የሚካሄደው የካፒታሊስት የሀብት ክምችትና ዘዴ በአገር ውስጥ ገበያ ብቻ የሚመካ አይደለም። እያንዳንዱ ካፒታሊስ አገር ህብረተሰቡ ገዝቶ ከሚጠቀመው በላይ ስለሚያመርት ትርፉን ምርቱን ለመሸጥ ሲል ወደ ውጭ ገበያ ያስፈልገዋል። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ሁኔታ በተለያዩ አገሮች መሀከል ባሉ ካፒታሊስቶች ዘንድ የግዴታ ውድድር ይፈጥራል ማለት ነው።የተለያዩ ካፒታሊስት አገሮች ምርቶቻቸውን፣ ለምሳሌ መኪና ወይም የኤሌክትሮኒክ ዕቃ በዓለም ገበያ ላይ ለመሸጥ ይችሉ ዘንድ በተቻለ መጠን ለምርት የሚያወጡትን ወጪ እንዲቀንሱ ይገደዳሉ። በሌላ ወገን ደግሞ አንዳንድ ምርቶች የውጭ ገበያ ላይ ለመሸጥ እንዲችሉ መንግስታት ከኤክስፖርት ቀረጥ ነፃ ያደርጓቸዋል።
የምርትን ዋጋ እንደልባቸው አገር ውስጥ መቀነስ ካልቻሉ የተለያዩ አካሎች(Spare parts) ሌሎች የሰው ጉልበት ርካሽ የሆኑ አገሮች እንዲመረት በማድረግ ምርቶቻቸውን በርካሽ
ዋጋ ሊሸጡ የሚኦችሉበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ ማለት ነው። ስለዚህም የዛሬው ካፒታሊዝም ከሁለት መቶ ዐመት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር በብዙ እጅ ይለያያል። ውድድሩ
በትናንሽ ካፒታሊስቶች መሀከል ብቻ የሚደረግ ሳይሆን የዓለምን ገበያ ለመቆጣጣር በሚሽቀዳደሙ ጥቂት ያበጡ ካፒታሊስቶች(Oligopolies) መሀከል ነው። ይህ ዐይነቱ
በተወሳሰበ የአደራጃጀትና የአመራረት ስልት የሚንቀሳቀስ የምርት ክንውን እንዲያው በተራ የነፃ ገበያ ሊገለጽ የሚችል አይደለም።
ካፒታሊዝም፣ ሳይንስና እንዲሁም ቴክኖሎጂ !!
አንዳንድ ስለኢኮኖሚ ዕድገት የሚጽፉትንም ሆነ የሚያወሩትን የኒዎ-ክላሲካል የኢኮኖሚ ምሁራንና፣ እንዲሁም ስለ ኢኮኖሚ እናውቃለን ብለው አፋቸውን የሚሰዱትን አንዳንድ የወያኔን ደጋፊዎች ስንመለከትና ስናዳምጣቸው እነዚህ ሰዎች ስለምን እንደሚያወሩ ነው ግራ የሚገባን። በታሪክ ውስጥ የገበያ ኢኮኖሚ ከግብታዊ ባህርዩ ከተላቀቀና ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከተሸጋገረ ወዲህ መሰረታዊ ምርምርና ከዚያ በኋላ ደግሞ ይህንን ቀስ በቀስ ተግባራዊ ማድረግ የካፒታሊዝም ዐይነተኛ ባህርይ ሊሆኑ በቅተዋል።
በመጀመሪያ ደረጃ ሳይንስ መዳበር የቻለው በታላላቅ ተመራማርዎች፣ በአስራ አምስተኛው፣ በአስራስድስተኛውና በአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ሲሆን፣ ወደ ቴኮኖሎጂ
ማፍለቂያነትና ወደ ተግባራዊነት እየተለወጠ ሊመጣ የቻለው ከአስራስምንተኛው ክፍለ- ዘመን ጀምሮ ነው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው ሳይንሳዊ ግንኝነት ብቻ ሳይሆን ተግባራዊነትና
ቴክኖሎጂዎችን ፈጥሮ ወደ ምርት ማምረቻ መሳሪያነት መለወጥ የታቸለው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው ምርት በዕውቅ መመረትና ምርትን ማሳደግና እንዲሁም የተለያዩ ምርቶችን
ማመረት የተቻለውና ቀስ በቀስም ዛሬ ለማየት የበቃነውን ቴክኖሎጂያዊ ምጥቀት ማየት የቻልነው። በአንዳንዶች አባባል ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው በቴክኖሎጂ አማካይነት ተፈጠሮን
እስከተወሰነ ደረጃ መቆጣጠርና በተፍጥሮ ውስጥ ተደብቀው የሚገኙ ነገሮችን በልዩ መሳሪያዎች መመርመርና ማየት የተቻለው። ስለሆነም ሰለ ገበያ ኢኮኖሚ ወይም ስለ
ካፒታሊዝም በምናወራብት ጊዜ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ደግሞ በየጊዜው ከሚካሄድ ፈጠራ(Innovation) ውጭ ማየትና ማተት ስህተት ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛም
ነው። ስለሆነም የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በከፍተኛ የሳይንስና የቴኮኖሎጂ ( A Science and Technology Driven Economic Development) መሰረት ላይ በመመርኮዝ የሚንቀሳቀስና፣ ከተወሰኑ ዐመታት በኋላ ደግሞ አሮጌው ከገበያው በመውጣት በአዲስ የሚተካበት ልዩ ዐይነት ኢኮኖሚያዊ ክንውን ነው።
የሳይንስና የቴክኖሎጂን አስፈላጊነት ከተራ የኢኮኖሚ ስሌት አንፃር ማየቱ እጅግ ስህተት ብቻ ሳይሆን እንደዚህ ዐይነቱ አመለካከት የማሰብ አድማሳችንን ያጠበዋል።ሳይንሳና ቴክኖሎጂ በቀጥታ ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን የፍጆታ ዕቃዎች ለማምረት የሚያገልግሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ ከአደጋ የሚከላከሉንን፣ ለምሳሌ እንደ እሳት አደጋ መኪና፣ውሃ ሲሞላ መምጠጫና ስውን በቀላሉ ማዳኛ፣ ልዩ ልዩ ለመንገድ ስራ የሚያገለግሉ መኪናዎችና መዳመጫዎች፣ እንዲሁም አፈር ዛቂዎች፣ ዲንጋይ ተሽካሚዎች፣በሀይድሮሊክ እየታገዙ ከባድ ከባድ እቃዎችን ማንሳትና በተለይም በገደላማ ቦታ ድልድይን መስራት የሚቻለው የሳይንስን ትርጉም የተረዳን ከሆነ ብቻ ነው። ከዚህም በተጨማሪ፣ዘመናዊ የህክምና መስሪያ መሳሪያዎችን፣ መድሀኒቶችንና ልዩ ልዩ ለሰው ልጅ ሊያገለግሉና ከአደጋም ሊከላከሉት የሚችሉትን መሳሪያዎች መስራት የሚቻለው በተለይም የፊዝክስንና የኬሚስትሪን ህግና ምስጢር የተረዳን ከሆን ብቻ ነው።
ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ምድር ኢኮኖሚው በአስራአንድ በመቶ አድጓል፣ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ እያካሄድን ነው የሚለው ተራ አባባል ሳይንሳዊ መሰረት የለውም። ይህ ዐይነቱ አነጋገር የኢኮኖሚ ፖሊሲ አውጭዎቻችንን የዕውቀት ደረጃ የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፣ እንደዚህ ዐይነቱ የሽቃዮች ኢኮኖሚ የቱን ያህል በሚሊዮን የሚቆጠረውን ታዳጊ ወጣት አእምሮውን እንደሚያበላሽው ነው መረዳት የሚቻለው። እንደዚህ ዐይነቱ ግራ መጋባትና አላዋቂነት የፈረንጆች መጫወቻ፣ መሳቂያና መሳለቂያ እንድንሆን አድርጎናል። የተለያዩ ግን ደግሞ ሳይንሳዊ ይዘት የሌላቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚባሉ ነገሮች ተግባራዊ በመሆን ከፍተኛ የሆነ የውንብድና ስርዓት ተዘርግቷል። ድህነት ተስፋፍቷል። ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሳይሆን፣ ገንዘብ ከዚህና ከዚያ በመቃረምና ትላልቅ ኢኮኖሚያዊ መሰረት የሌላቸው ሆቴል ቤቶችና ቡና ቤቶች በመስራት ውድ እናት አገራችን ወደ አስረሽ ምችውነት ተለውጣች።
ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ የሀብት ክምችትና ካፒታሊዝም አብዛኛውን ጊዜ በአገራችን ኢኮኖሚው ይህን ያህል በመቶ አድጓል ሲባል ከስሌት ውስጥ የማይገቡ ብዙ መሰረታዊ ነገሮች አሉ። ይህ ጉዳይ ተቃዋሚ ነኝ የሚለውንም አስተሳሰቡን እንዲያወላግድ አድርጎታል ብል እንደተራ ውንጀላ አይቆጠርብኝም። ስለ ካፒታሊዝም ዕውነተኛ ዕደገት በደንብ ሳንመረምር በተራ የጂዲፒ(GDP) አሰላል የሚቀርበው የኢኮኖሚው አደገ አላደገም እያሉ መከራከር የካፒታሊዝምን ዐይነተኛ ባህርይ እንዳንረዳ ያግደናል።
ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ ካፒታሊዝም ካለ ንፁህ ውድድርና የቴክኖሎጂ ምጥቀት እንዲሁም ደግሞ ተከታታይነት ከሌለው የሳይንስና የምርምር ውጤት ውጭ በፍጹም ሊሰራ አይችልም። ከዚህ በተረፈ ግን ስለካፒታሊስት ኢኮኖሚ ዕድገት በምናወራበት ጊዜ ሌላ እጅግ አስፈላጊ መሰረታዊ ቅድመ-ሁኔታም አለ። ይኸውም ማርክስ ክፍል አንድና(Department one) ክፍል ሁለት(Department Two) እያለ የሚጠራው ነው። ይህንን የማርክስን፣ የሹምፔተርንና የሎነርጋንን የዕድገት ኢኮኖሚ አሰላል ወደ ሶስትና አራት ክፍሎችም ማስፋፋት ይቻላል። ለምሳሌ ጥሬ ሀብቶችን የሚያጣሩና ወደ መጀመሪያው የምርት ክንውን የሚለውጡ ኢንዱስትሪዎች፣ ወይም ደግሞ ልዩ ዐይነት
የቅንጦት ምርቶች የሚያመርቱ እያልን ልናስፋፋው እንችላለን። አንባቢን ግራ ላለማጋባት በሁለቱ ክፍሎች(Departments) ብቻ ላይ ማትኮሩ ነገሮችን ለመረዳት ቀላል ይሆናል።
በማርክስ የዕውነተኛ የካፒታሊስት ዕድገት ውስጥ በክፍል አንድ ውስጥ የምርት ማምረቻ መሳሪያዎች ይመረታሉ። ማሽኖች ማለት ነው። እነዚህ ቀደም ብለው በኢንጂነሪግ ዴፓርትሜንት ዲዛይን ይሆናሉ። ለምርት ማምርቻ እንዲያገልግሉ ሆነው ይቀረጻሉ፣ ይዘጋጃሉ ማለት ነው። በዚህ ዴፓርትሜንት አማካይነት ነው የፍጆታ ዕቃ አምራቾች
አስፈላጊው ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ተዘጋጅቶ የሚቀርብላቸው። በሁለተኛው ክፍል ወይም ዴፓርትሜንት ሁለት እየተባለ በሚታወቀው ውስጥ የተለያዩ የፍጆታ ዕቃዎች፣ ከረዥም
ጊዜ ዕድሜ እስከ አጭር ጊዜ ዕድሜ ያላቸው ይመረታሉ። መኪናዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ ልብስና ጫማ፣ የልጆች መጫዎቻዎችና እንዲሁም ምግብና መጠጥ በክፍል
ሁለት ውስጥ ነው የሚመረቱት። በሁለቱ ዴፓርትሜንቶች ውስጥ ዲያሌክታዊ ግኑኝነት አለ ማለት ነው። አንደኛው ካለሌላው በፍጹም ሊያድግና ሊንቀሳቀስ አይችልም።
ይህ ማለት ምን ማለት ነው? የምርት ማምረቻው ክፍል በተከታታይ እንዲያመርት የግዴታ በፍጆታ ምርት ማምረቻ ተሰማርቶ የሚንቀሳቀስ ውስጠ-ኃይሉ ከፍተኛ የሆነ
የካፒታሊስት መደብ መኖር አለበት። በዴፓርትሜንት ሁለት የምርት መሳሪያዎች ሲገዛ በባንክ አማካይነት አካውንቱ ላይ ለዴፓርትሜንት አንድ ገንዘብ ይተላለፍለታል። በዚህ
አማካይነት በሁለቱ ክፍሎችና(Departments) በባንክ መሀከል የሶስትዮሽ ግኑኝነት ይፈጠራል። ይህ ልዩ ግኑኝነት ለባንኮች መጠናከርና ለገንዘብ በፍጥነት መሽከርከር አመቺ
ሁኔታን ይፈጥራል። ይህ አንደኛው ጉዳይ ሲሆን፣ በምርት ማምረቻ ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ሰራተኛ በሚያገኘው ገቢ በክፍል ሁለት የሚመረቱትን የረዥምና የአጭር ጊዜ
ዕድሜ ያላቸውን ዕቃዎች እየገዛ ይጠቀማል። ገንዘብ በባንክም ሆነ በቀጥታ ለዴፓርትሜንት ሁለት ይተላለፋል። በዚህ መልክ በጠቅላላው ኢኮኖሚክ ውስጥ ልክ እንደ ደም ዝውውር
የማያቋርጥ ግኑኝነትና መሽከርከር ይፈጠራል። በዚህ አማካይነትም አጠቃላይ የሀብት ክምችትና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ይታያል ማለት ነው። ይህ ዐይነቱ የአመራረት ስልት
ሲደራጅና ኢንዱስትሪዎች በዚህ መልክ ሲቀናጁ ስለ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ዕድገት ማውራት ይቻላል።
የመንግስት ሚና በካፒታሊስት ኢኮኖሚ ውስጥ !
በአብዛኛዎቹ ለዩኒቨርሲቲ ተብለው በተዘጋጁ የኢኮኖሚ መጻህፍቶች ውስጥ፣ ለምሳሌ ስለ ማክሮና ስለ ሚክሮ ኢኮኖሚክስ የሚያትቱ መጽሀፍቶችን ለተመለከተ፣የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ካለምንም የመንግስት ጣልቃ-ገብነት በራሱ ኃይል እንደሚንቀሳቀስ ተደርጎ ነው የተማርነው። የሚሰበከውምና የሚለፈፈውም ሁሉንም ገበያው ይቆጣጣረዋል፤
ያስተካክለዋል፤ ኢኮኖሚው ሲዛባ ራሱ ውስጥ ባለው ኃይሉ ሚዛናዊ እንዲሆን ያደርገዋል እየተባልን ነው የተማርነው። እንደሚነገረንና ለማሳመንም እንደሚሞከረው የመንግስት
ጣልቃ ገብነት የገበያን ኢኮኖሚ ያዛባል፤ በተለይም በፊስካል ፓሊሲ የሚወሰድ ኢኮኖሚያዊ ጣልቃ-ገብነት የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል። መንግስት ከባንክ ወይም ከካፒታል
ገበያ ላይ እየተበደረ የሚወስዳቸው እርምጃዎች የግዴታ ከካፒታሊስቶች ጋር እንዲወዳደር ያደርገዋል። በካፒታሊስቶች ላይ ግፊት(Crowding out) ስለሚያደርግ ከገበያው እየተስፈናጠሩ እንዲወጡ ይገደዳሉ እየተባልን ነው ሲነገረን የከረመው።
ሀቁ ግን በኢኮኖሚ የግንባታ ታሪክ ውስጥ በተለያዩ መልኮች መንግስት ጣልቃ ሳይገባ አጠቃላይ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የታየበት የምዕራብ አውሮፓ አገር የለም።በኋላ አሜሪካ፣ ቀጥሎ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ፣ ከሰላሳ ዐመት ጀምሮ ደግሞ ቻይና በመንግስት ጣልቃ ገብነት ነው የተወሳሰበና አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳየት የቻሉትና የአገር ውስጥም ገበያ መገንባት የቻሉት። በመጀመሪያ፣ ለካፒታሊስት ኢኮኖሚ መሰረት የተጣለው በማኑፋክቱር አብዮት አማካይነት በፍጹም ሞናርኪዮች ነው። በኢኮኖሚው ውስጥ ጣላቃ ገብነታቸውም ዕውቅና ለራሳቸው የግል ሀብት ለማካበት ሳይሆን፣ ንቁ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጣዊ-ኃይል እንዲያገኙ በክሬዲትና በኢንስቲቱሽናዊ የጥገና ለውጥ መስመር በማሲያዝና በመደገፍ ነው። በጊዜው የነበረው ጠንካራ ህብረ-ብሄርን የመመስረቱ ጉዳይ እንደ ቅድመ-ሁኔታ በመታየቱ በተለያዩ የምዕራብ አውሮፓ አገሮችም ዘንድ ውድድር ስለነበረ ሁሉም በየፊናው የአገሩን ገበያና የአገሩን ከበርቴ ማጠናከር ነበረበት።
ስለሆነም የአገር ውስጥ ገበያ እንዲዳብርና ጠንካራ ኢኮኖሚ እንዲገነባና ዕቃዎችና ካፒታል ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በቀላሉ እንዲሽከረከሩ ለማድረገ እንቅፋት የሆኑ ነገሮች ሁሉ
ቀስ በቀስ መወገድ ነበረባቸው። የሰው አስተሳሰብ ከክላዊነት ወጥቶ ወደ ማዕከላዊነት እንዲያተኩር በማድረግ ኢኮኖሚው ህብረ-ብሄራዊ ባህርይ እንዲኖረው ማድረጉ ብቻ
ሳይሆን፣ ህዝቡም በተለያዩ ድሮች መተሳሰርና እንደ አንድ ህዝብ መነሳት አለበት። ካፒታሊዝምና ጠንካራ የውስጥ ገበያ ክልላዊ አስተሳሰቦች በሰፈኑበት አገር ውስጥ ማደግ
አይችሉምና። ይህ በሞናርኪስቶች የተመራው የመርካንትሊዝም የኢኮኖሚ ግንባታ ነው የኋላ ኋላ ለእነ አዳም ስሚዙ የረቀቀው እጅ(Invisible Hand) መንገድ የከፈተው።
የነስሚዝ የነፃ ገበያ መሰበክ ከተጀመረም በኋላ የመንግስታት ጣልቃ ገብነት እየተወሳሰበና መልኩን እየቀየረ መጣ እንጂ መንግስት ኢኮኖሚውን ለተዋንያኖች በመልቀቅ ምሽግ ውስጥ
የገባበት ቦታ አልነበረም።
በመሀከሉ የተወሰዱትን እርምጃዎች ሁሉ ትተን የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ከተገባደደ በኋላ በመንግስታት የተወሰዱትን መልሶ የመገንባት እርምጃ ስንመለከት ኢኮኖሚው
መንሰራራት የጀመረው እንደሚነገረን በገበያ ተዋንያን አማካይነት አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የምዕራብ አውሮፓ መንግስታት የፈራረሱ ከተማዎችን መልሰው በመገንባት ለህዝቡ
መጠለያ መስጠት ነበረባቸው። በሁለተኛ ደረጃ የምግብን ችግር መቅረፍ ነበረባቸው። ቀጥሎም የንጹህ ውሃና የኃይል ጉዳይ መፍታት ነበረባቸው። እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች
ሲሟሉ ብቻ ነበር ኢኮኖሚውን መገንባት የሚቻለው። ይህንን መሰረታዊ ጉዳይ የተረዱት የምዕራብ አውሮፓ መንግስታት ስራ ለመስራት የሚችለውን ኃይል በሙሉ ማሰማራት
ነበረባቸው። ለዚህ የሚሆን ደግሞ ልዩ ዐይነት የክሬዲት ሲስተም ማቋቋም ነበረባቸው።
ስለሆነም ምዕራብ ጀርመን ብቻ ከ70-80% የሚጠጋው ከተማዎቿና ኢንዱስትሪዎቿ እንዲሁም ድልድዮቿ ከወዳደሙ በኋላ ከአስራአምስት እስከ ሃያ ዐመት ባለው ጊዜው
ውስጥ ነው አገሯን መልሳ የገነባቸው። የገበያ ተዋንያን መልሰው ይጠግኑታል ተብሎ እጅን አጣጥፎ አለተቀመጠም።
ይህ ዐይነቱ ኢኮኖሚውን መልሶ የመገንባት እርምጃ ቀጥተኛና ግልጽ ነበር። ኢኮኖሚው እያደገና ውስጠ-ኃይል እያገኘ ሲመጣ ደግሞ በሞኔተሪና በፊስካል ፖሊሲ አማካይነት የእርማት እርምጃዎች መውሰድ ጀመሩ። እዚህ ላይ ነው ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገር ተማሪዎች የሚምታታበቸውና ስልጣን ላይ ቁጥጥ ሲሉ ብዙ ነገሮችን የሚያበላሹት። ያም ሆን ይህ የመንግስት ሚና የተወሰነውን ሀብት ከመቆጣጠር አልፎ በፖሊሲ አማካይነት ጣልቃ እስከመግባት ድረስ ለካፒታሊዝም አጠቃላይ የሀብት ክምችት አመቺ ሁኔታዎችን የሚፈጥር ነበር። ለምሳሌ የምዕራብ ጀርመንን ኢኮኖሚ ስንመለከት፣ እስከ 90ዎቹ መግቢያ ድረስ፣ የአየር መንገድ(ሉፍታንሳ)፣ ፓስታ ቤት፣ የውሃ ክፍፍል፣ የመብራት ስርጭት፣ የባቡር ሃዲድ፣ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች፣ ስልክ… ወዘተ በመንግስት ቁጥጥር ስር ሆነው በአውቶነመስ ደረጃ በግሩም ሁኔታ የሚንቀሳቀሱ ነበሩ።
አሁንም በአብዛኛዎቹ ላይ መንግስት ከፍተኛውን ድርሻ ሲይዝ፣ ወደ ግላዊነት የተዘዋወሩት ደግም ከሃያ ዐመት ሙከራ በኋላ በተለይም በሎካል ደረጃ ያሉት የሎካል አስትዳዳሪዎች
እንደገና መልሰው እየገዟቸው ነው። ምክንያቱም እንደ ንጹህ ውሃ ስርጭትና መብራትና ጋዝ የመሳሰሉት ካፒታሊስቶች ዋጋውን ስለሚያስወድዱና ትርፋማ ያልሆኑትን ስለሚዘጓቸው
ይህ ጉዳይ አስቸጋሪ ሁኔታ ስለፈጠረና የህዝብንም ጩኸት ለመቀነስ ሲባል የግዴታ መልሶ መግዛቱ አስፈላጊነቱ ታየ። ከዚህ በተረፈ፣ በጀርመን አገር ብቻ ሶስት ዐይነት የባንክ
ቁጥጥር አሰራርና ዘዴ አለ። 1ኛ) በግል ቁጥጥር ስር ያሉ ባንኮች(Private Banks)፣2ኛ) በጋርዮሽ ስር ያሉ(Cooperative Banks)፣ 3ኛ) በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ። ከዚህ በተረፈ ልዩ ዐይነት በዝቅተኛ ወለድ ብድር የሚሰጥ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለ፣ ከሃምሳኛው ዓ.ም ጀምሮ የሚንቀሳቀስ የባንክ ሲስተም አለ። በዚህ መልክ እነዚህ የተለያዩ ባንኮች የተለያየ ተግባር በመውሰድ ደንበኞቻቸውን ያስተናግዳሉ። በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ባንኮች ለትናንሽና ለማዕከለኛ አምራቾች ከረዥም ጊዜ አንፃር በዝቅተኛ ወለድ የሚከፈል ብድር ያበድራሉ። በጋርዮሽ ስር ያሉት ደጎሞ ለአባሎቻቸው ብድር የሚያበድሩ ናቸው።

ከላይ በአጭሩም ቢሆን የተዘረዘረው ጉዳይ የሚያሳየው ካፒታሊዝም በንጹህ መልክ በገበያ ኢኮኖሚ ህግ ብቻ የሚካሄድ ኢኮኖሚያዊ ስርዓት አይደለም። የተወሳሰበና ብዙ ተዋንያን በህበረተሰብ ውስጥ ባላቸው ቦታ አማካይነት የሚካፈሉበትና፣ ሁሉም የተሻለ ድርሻ ለማግኘት ሲል በግልጽም ሆነ በይፋ ትግል የሚያደርግበት መድረክ ነው። እዚህ ላይ ነው ብዙ የሶስተኛው ዓለም መንግስታት እስከዚህም የካፒታሊዝምን ውስጣዊ ባህርይና እንቅስቃሴ በሚገባ ሳይረዱ በዓለም አቀፍ ኢንስቲቱሽኖች እየተመከሩ የሚወስዱት ፖሊሲ
ህዝቦቻቸው መቀመቅ ውስጥ ሲገቡ አንድ ቦታ ላይ ቆም ብለው የማይጠይቁት። ከላይ አንድ ቦታ ላይ እንደተተነው ካፒታሊዝም ኢኮኖሚያዊ ክንውን ብቻ ሳይሆን ፓለቲካዊ፣ማህበራዊና ርዕዮተ-ዓለማዊ እንደመሆኑ መጠንና፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የእያንዳንዱን የሰው ህይወት ሰለሚነካ የሚወሰዱት እርምጃዎች በሙሉ በዘፈቀደ አይደሉም። በጉልበትና በአወቅኹኝ ባይነት በሚወሰዱበት ቦታ ደግሞ የግዴታ የሲቪክ ማህበራትን እንቅስቃሴና ጩኸት ያስከትላሉ። ስለሆነም እንደኛ አገር ዐይነቱ መንግስታት በየዋሁ ህዝባችን ላይ እንደሚጭነውና አገርን እንደሚያተራምሰው ዐይነት ፓሊሲ አይደለም በካፒታሊስት አገሮች ተግባራዊ የሚሆነው ፖሊሲ። ከዚህ በመነሳት ነው የአገራችንን የኢኮኖሚ ዕድገት ሁኔታ ማየት ያለብን። የሃያ ዐመቱን የኢህአዴግን የኢኮኖሚ ዕድገት ጉራ መንሳት በዚህ ዐይነቱ የካፒታሊስት ዕድገት መነፅር ስንመረምር በፍጹም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያሰኘው አንዳችም ምክንያት የለም። ምክንያቱም ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚያስፈልጉ ከላይ የተዘረዘሩት መሰረታዊና ቅድመ-ሁኔታዎች ስለሌሉ ነው። ከላይ የተዘረዘሩት ቅድመ-ሁኔታዎች በሌሉበት ሁኔታ ውስጥ የገበያን ኢኮኖሚ ወይም ካፒታሊዝምን ማስፋፋት በፍጹም አይቻልም። ጤናማና ነፃ ውድድር፣ ሳይንስና የቴክኖሎጂ ምጥቀት፣ ከዚህም ባሻገር ሁለቱ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ዴፓርትሜንቶች በሌሉበት አገር ውስጥ ሰፋ ያለ የስራ መስክ መክፈት አይቻልም። ሰፋ ያለ የስራ መስክ መክፈት የማይችል ኢኮኖሚ ደግሞ ውስጠ-ኃይሉ ውስን ስለሆነ የህዝቡም የመግዛት ኃይል በጣም የደከመ ይሆናል ማለት ነው። የህዝቡ የመግዛት ኃይል በደከመበት ኢኮኖሚ ውስጥ ደግሞና፣ኢንዱስትሪዎች ርስ በርሳቸው ባልተያያዙበት አገር ውስጥ ገንዘብ ከአንድ የኢኮኖሚ መስክ ወደ ሌላው በመሽከርከር ህብረተሰብአዊ ኃይል(Social Power) ሊያገኝ አይችልም። የአንድ አገር ገንዘብ መጠንከርና የመግዛት ኃይሉም ሊወሰን የሚችለው የውስጡ ኢኮኖሚ ከላይ በተዘረዘረው መልክ የተደራጀ እንደሆን ብቻ ነው። የተገላቢጦሽ ሊሆን በፍጹም አይችልም። የገንዘብን የዕድገት ታሪክ ለተከታተለ ከስራ ክፍፍል መፈጠርና ማደግ እንዲሁም መዳበር ቀደም ብሎ ገንዘብ አለተፈጠረም። ዕድገቱ፣ በፍጥነት መሽከርከሩና ጥንካሬው ከጠቅላላው ኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የተያያዘ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።

በገንዘብ ጥንካሬ ውስጥም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ምጥቀት፣ የከተማዎች ማደግና መስፋፋት፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ የመገናኛና የመመላለሻ ዘዴዎች መገናኘት ለገንዘብ ጥንካሬና በፍጥነት መሽከርከር የራሳቸው ሚና አላቸው። እነዚህ ግን በገንዘብ አተማመን ስሌት ውስጥ ስለማይገቡ ስለአንድ ገንዘብ ጥንካሬ የሚኖራቸው ውስጣዊ አስተዋፅዖ ግንዛቤ ውስጥ አይገቡም። ለዚህ ሁሉ ዋናው ምክንያት ምንድ ነው ? ዋናው ምክንያት ብዙ ነገሮችን እየነጣጠልን እንድናይ ስለተማርን አንዱን ከሌላው ውጭ የሚያድግና የሚንቀሳቀስ መሆኑን ካለምንም ማውጣትና ማውረድ እንድንቀበል ተገደናል።
ከዚህም በመነሳት ነው የኢህአዴግን/ወያኔን የውንብድና የትራንስፎርሚሽንና የዕድገት ፖሊሲ መመርመር የምንችለው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ አንድን አገር እንደዚህ ዐይነቱ በታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ውስጥ መቀመቅ ውስጥ በከተተ አገዛዝ ትራንስፎርሜሽንና ዕድገት በፍጹም ተግባራዊ ሊሆኑ አይችሉም። በሁለተኛ ደረጃ፣ ለዕውነተኛ ትራንስፎርሜሽን የግዴታ ህብረተሰብአዊ ሬናሳንስ ወይም የመንፈስ ተሀድሶ ያስፈልጋል። ይህም ማለት በሁሉም መስክ የሚካሄድ፣ በአማማሩ የህንፃ ስራና ጋርደኖች የሚገለጽ የከተማዎችና የመንደሮች አገነባብ፣ የዕደ-ጥበብ ሙያ መስፋፋት፣ የስራ ክፍፍል በሁሉም መስክ መዳበርና ቀስ በቀስም በየመስኩ መሀከል ኢኮኖሚዊ ግኑኝነት እንዲፈጠር ማድረግ፣ የስዕልና የድራማ መስፋፋት፣ ሃሳብን በነፃ መግለጽና ለሊትሬቸር መዳበር አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠር…ወዘተ. ወዘተ. ለዕውነተኛ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን በሩን ይከፍታሉ። በሶስተኛ ደረጃ፣ የግዴታ ፖለቲካዊና ልዩ ልዩ ኢንስቲቱሽናዊ ሪፎርሞች ያስፈጋሉ። ትራንስፎርሜሽንና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በአየር ላይ የሚካሄዱ አይደሉም። በተወሰነ አካባቢና በሰዎች አማካይነት ነው የሚካሄዱት። ይህም ማለት ብቃት ያላቸው ሰዎች መኖራቸው ብቻ ሳይሆን ስራዎችም ካለምንም ቢሮክራሲያዊ መሰናክሎች እንዲሰሩ ከተፈለገ የአሰራር ዘዴዎችን የሚያቀላጥፉ ሁኔታዎች መዘርጋት አለባቸው። ይህም ሁኔታ የመንግስትን አወቃቀር በአዲስ መልክ ማዘጋጀትን ይጠይቃል።
መንግስት ለኢኮኖሚና ለማህበራዊ እንዲሁም ለባህል ዕድገት አጋዥ የሚሆን መሆን አለበት እንጂ ተቀናቃኝ ከሆነና ታታሪ ግለሰቦችን ጭንቅላት ጭንቅላታቸውን የሚመታ መሆን
የለበትም። ስለሆነም አገዛዙን ከታች እስከ ላይ ድረስ ሙስና የሚባል ትልቅ የወረርሽኝ በሽታ በመታው አገር የትራንስፎርሜሽንና የዕድገት ፖሊሲ በምንም ዐይነት ተግባራዊ ሊሆን
አይችልም። ከዚህም ባሻገር አገዛዙና ኢፈርት የሚባለው የኢኮኖሚ አውታሩ ሌሎች ዜጎች በነፃ እንዳይንቀሳቀሱ ጭንቅላት ጭንቅላታቸውን እያሉ ከገበያ እንዲወጡ በሚደረግበት
አገር ውስጥ ምን ዐይነት ትራንስፎርሜሽን ነው ሊካሄድ የሚችለው? ይህ የሚያመለክተን ምንድነው? አንደኛ አገዛዙ እጅግ ተምታቶበታል። የሚይዘውንና የሚጨብጠውን በፍጹም
አያውቀውም። በሁለተኛ ደረጃ፣ ኢኮኖሚውን እየተቆጣጠረ በሄደ ቁጥር የውስጥ ገበያ እንዳያድግ መንገዱን ሁሉ እያጠበበ መምጣቱን በፍጹም የተረዳ አይመስልም። በዚህ
መልክ የሚካሄድ ኢኮኖሚ ደግሞ ድህነት ፈልፋይ ከመሆኑም ባሻገር አገሪቱ በቀላሉ ልትወጣው የማትችለው የውንብድና ስራ እንዲስፋፋ ሁኔታውን የበለጠ ያመቻቻል። በሌላ
ወገን ደግሞ በራሳቸው ደሴት ውስጥ የሚኖሩ አዳዲስ ተዋናዮች እየተፈጠሩ አገሪቱን የባሰ የባህልና የኢኮኖሚ ውድመት ውስጥ እንድትገባ ያደርጋሉ። ከዚህ ስንነሳ የአቶ መለስ
የትራንስፎርሜሽንና የዕድገት የጉራ ፖሊሲ ከወረቀት የሚያልፍ አይደለም።

ፈቃዱ በቀለ
fekadubekele@gmx.de

 

 

 

ማሳሰቢያ፤በዌብሳይታችን ላይ ለሚወጡ ማናቸውም ጽሁፎች ቀዳሚ የሆነ የዌብሳይታችንን አርትኦት ስራን ለማክበር ሲባል በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በማለዳ ታይምስ የመረጃ ማእከል ® ላይ ለሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የማለዳ ታይምስ የመረጃ ማእከል ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዌብሳይቱን  ጠቋሚ (አመልካች ) (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.maledatimes.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን(የማለዳ ታይምስ ህግና ደንብ በንግድ በተመዘገቡበት ሁለት አገሮች የረቀቀ ሲሆን በሁለቱም አገሮች አንድ አይነት የሆነ አሰራር ይዞ ይከተላል ።ይህንን ህግ ማንኛውም ሰው መቅዳት የማይችል መሆኑን እንገልጻለን።ንብረትነቱ እና ህገ ደንቡ የማለዳ ታይምስ ብቻ ነው!)፡፡ይህ ካልሆነ ግን በህገ ደንባችን መሰረት አስፈላጊውን የህጋዊ ጥያቄ ለማቅረብ የምንገደድ መሆኑን እንጠቁማለን::በዚህ አጋጣሚ በግለሰብ ለሚላኩ ጽሁፎች ሁሉ ተጠያቂው ስሙ የተገለጸው ግለሰብ እንጂ የማለዳ ታይምስ መረጃ ማእከል ሃላፊነቱን እንደማይወስድ እናሳስባለን ::

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on October 5, 2012
  • By:
  • Last Modified: October 5, 2012 @ 4:15 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar