www.maledatimes.com ነፃነት፣ ዲሞክራሲና የኢኮኖሚ ዕድገት -እንዴትና ለማን እንዲሁም ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ዕድገት- - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ነፃነት፣ ዲሞክራሲና የኢኮኖሚ ዕድገት -እንዴትና ለማን እንዲሁም ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ዕድገት-

By   /   October 7, 2012  /   Comments Off on ነፃነት፣ ዲሞክራሲና የኢኮኖሚ ዕድገት -እንዴትና ለማን እንዲሁም ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ዕድገት-

    Print       Email
0 0
Read Time:168 Minute, 33 Second

መግቢያ
እንደ አ.አ 2012 በግንቦት ወር ከ9-11 ድረስ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ሁኔታ አስታኮ የተካሄደውን የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ የቀረበውን የጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊን „
በዴሞክራሲና በኢኮኖሚ ዕድገት መሀከል ምንም ግኑኝነት የለም“ የሚለውን አቀራረብ በመተቸት በኢትዮ ሚዲያ ላይ የወጣውን የአቶ ኤፍሬም ማዴቦን ግሩም ትንተና
ብዙዎቻችን ሳናነብ አንቀርም። በዕውነቱ አቶ ኤፍሬም ግዜ ወስዶ፣ ብዙም ሳይታሰብ ዝም ብሎ ከሆድ የወጣውን የአቶ መለስን አባባል ተንትኖና ተችቶ ማቅረቡ የሚያስመሰግነው
ብቻ ሳይሆን፣ ለሰፊ ውይይት የሚያመችና፣ የአገራችንን የወደፊት የህብረተሰብ አወቃቀርና የኢኮኖሚ ዕድገት ከሌሎች አገሮች ጋር እያነፃፀርን እንድናጠናና ለተወሳሰበውም
የአገራችን ችግር መፍትሄ እንድንሻ የሚጋብዘን ነው። በተለይም ዛሬ እንደኛ ያሉ በብዙ ህብረተሰብአዊ ችግሮች የተተበተቡና የተወጠሩ አገሮች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሌሎችም ከኛ በብዙ
እጥፍ ቀድመውን የሄዱ አገሮች፣ በተለይም በመንግስታት ዕዳ የተጠመዱ እንደ ግሪክ፣ ስፔይንና ጣሊያን የመሳሰሉት የሚይዙትንና የሚጨብጡትን ባጡበት ወቅት በእንደዚህ
ዐይነቱ ለሰው ልጅ አስፈላጊ በሆነው የኢኮኖሚ ዕድገት ጥያቄ ላይ በሰፊውና በጥልቀት መወያየቱ ነገሩ ያገባናል የሚሉ ምሁራን ግዴታና ኃላፊነት ነው። አንድ ምሁር ኃላፊነቱን
መወጣቱ ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ የሚችለው ዲፕሎም፣ ዲግሪና ሌላም ማዕረግ ስለጨበጠ ሳይሆን ህብረተሰቡን ወጥረው የያዙትን ችግሮች ለመፍታት ራሱን ሲያስጨንቅና ለችግሩም መፍትሄ ይሆናል ብሎ መልስ ሲጠቁም ብቻ ነው። በፈለገው መልክ ይቅረብ ዋናው ቁም ነገር ግን „እኔ የማሰበው እንደዚህ ነው“ ብሎ ማቅረቡ የሚያስመሰግነው ነው።
እንደሚታወቀው ክርክርና ሰፋ ያለ የጭንቅላት ስራ በአውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክ ወስጥ የተለመደውን ያህል እንደኛ ባሉ በኢኮኖሚና በህብረተሰብ አወቃቀር ወደ ኋላ በቀሩ
አገሮች ውስጥ የህብረተሰብን ችግርና የወደፊት ዕድል አስመልክቶ መከራከር የተለመደ አይደለም። በተለይም ከ50ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የሶስተኛውን ዓለም አገሮች የኢኮኖሚ
ዕድገት አስመልክቶ በጣም ጥቂት ምሁራን ካልሆኑ በስተቀር አብዛኛው ክርክር ይካሄድ የነበረው ይህንን ወይም ያንን ርዕዮተ-ዓለም እናራምዳለን በሚሉ በአውሮፓና በአሜሪካን
ምሁራን ዘንድ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲውም ተረቅቆ ይህንን ተቀበሉ ተብሎ የሚመጣው ከውጭ ነው። በሁለትና ሶስት ወራት ወይም ሳምንታት ቆይታና፣ ከዚያ
በኋላ ደግሞ ይህንን ወይም ያንን መጽሀፍም ሆነ መጽሄት እያገላበጡ ከዚያ በመነሳት ፖሊሲ አውጥቶ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ እንደምናየው የኛንም ሆነ የሌሎችን አፍሪካ
አገሮች ሁኔታ የባሰውን አባባሰው እንጂ ስርዓት ያለውና ተከታታይ ማህብረሰብ እንዲመሰርቱ አልረዳቸውም። የብዙ አፍሪካ አገሮችን ሁኔታ ስንመለከት ከ1950ዎቹ
መጀመሪያ ጀምሮ በአወቅሁኝ ባይነት በጭንቅላታቸው ላይ እንዲቀመጥ የተደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የበሳውን መቀመቅ ውስጥ ነው የከተታቸው። የሳይንስና የቴክኖሎጂ
ባለቤት በመሆን ህብረተሰቦቻቸውን በስርዓት እንዲገነቡ አይደለም የረዳቸው።
ከዚህ ስንነሳ በኛ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከማያስፈልግ ንትርክ በስተቀር የህብረተሰብአችንን የባህል፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ፣ እንዲሁም ሌሎች ችግሮችን እያነሱ
መከራከር የተለመደ አይደለም። እንዲያውም የህብረተሰብአችን ዕጣና የወደፊት ዕድል ለዓለም ኮሙኒቲው እየተባለ ለሚጠራው የተጣለ ይመስላል። ስለሆነም የአቶ እፍሬም
ማዴቦ ጅምር የሚደገፍ ብቻ ሳይሆን፣ ያገባናል የምንል ሁሉ እንደ አመለካከታችን ሃሳባችንን መሰንዘሩና መከራከሩ ለአገራችን ዕድገት እጅግ ጠቃሚ ነው።
የነፃነት ትርጉምና ለነፃነት የተደረገው ትግል!
ለመሆኑ ነፃነት ማለት ምን ማለት ነው? ኢማኑኤል ካንት የሚባለው የጀርመኑ ታላቅ ፈላስፋ „ከሩሶ ስራ ጋር ከመተዋወቄ ወይም ጽሁፎቹን ከማንበቤ በፊት አምን የነበረው
በሰው ልጅ አርቆ አሳቢነትና ዕውቀት(Reason and Knowledge) ነበር። ስለዚህም ስለሰው ልጅም የነበረኝ አስተሳሰብ ለየት ያለ ነበር። ያልተማረውን ወይም ደንቆሮውን የምንቅና የተማረውን ብቻ የማከብር ነበር። ሩሶን ካነበብኩ በኋላ ግን ሁሉንም ነገር በነፃ ፍላጎት (Free Will) ስር መሆናቸውን ተገነዘብኩ። ስለዚህም በሩሶና በአይሳቅ ኒውተን መሀከል ያለውን ልዩነት በመገንዘብ የነፃነት ዓለም(The World of Freedom) ከተፈጥሮአዊ ዓለም (The World of Nature)የበለጠና ወርቃማ እንደሆነ ተማርኩ“ ይላል። በመቀጠልም “ሩሶው የነፃነትን የተደበቀ ምስጢር ለሰው ልጅ ሲያሰተምር፣ ኒውተን ግን የተፈጥሮን ህግ እንድንረዳ መንገዱን ከፈተልኝ። ሩሶው ኒውተናዊ የሰው ልጅ ሞራላዊ አባት ሲሆን ውዥንብር በሰፈነበት ዘመን ስርዓት እንዲሰፍን ያደረገ ነው“ በማለት የሰው ልጅ የግዴታ በነፃነት ዓለም ውስጥ መኖር እንዳለበት ያሳስበናል።
ይህ ብቻ ሳይሆን በካንት ዕምነት ሩሶው እንደሚለው የሰው ልጅ ዕውነተኛ ትርጉም በነፃነት ዓለም ሲኖር ብቻ ነው። ምክንያቱም ክብርና ነፃነት ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊ
ስለሆኑ ማንኛውም የሰው ልጅ የሌላ ሰው ፍላጎት ተገዥና በሱ እየታዘዘ መኖር የለበትም።
በሌላው ፍላጎት መኖርና ማጎብደድ የራስን የኑሮ ትርጉም አለመረዳት ብቻ ሳይሆን፣ ራስን እንዳልነበሩ አድርጎ መሰረዝና ማዋራድ ነው። ስለዚህም ይላል ካንት “በዚህ ዓለም ላይ
እጅግ የሚያስከፋው ነገር በራስ ፍላጎት አለመመራት ወይም የሌላው ተገዢ መሆን ነው“በማለት ነፃ ፍላጎት የቱን ያህል የሰውን ልጅ የመኖርና ያለመኖር፣ አንድ ህብረተሰብ
በስነ-ስርዓት መገንባት መቻሉንና አለመቻሉን የሚወስን መሆኑን ያረጋግጣል። ካንት  የሰውን ልጅ ነፃነት በሁለት ይከፍለዋል። የመጀመሪያ የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ
የሚቀዳጀው ነጻነት ሲሆን፣ ይህም ከደሙ ወይም ከሰውነቱ ጋር የተዋሃደ ነው።
ሁለተኛው ነጻነት ደግሞ አንድ ሰው በህጋዊ አካል የሚሰጠው ነጻነት ነው። የመጀመሪያው ከሁለተኛው የሚለየው ከዕውነተኛ ነጻነት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ የሰው ልጅ ማንነቱን
የሚገልጽበት ነው። ስለዚህም በካንት ዕምነት አንድ ዐይነት ነጻነት ብቻ ሲኖር፣ ማንኛም ሰው እንዲረዳው ማስተማር ያስፈልጋል ይላል። ይሁንና ግን ይህ ውስጣዊ ነጻነት ዕውነተኛ
ነጻነት የሚሆነው እያንዳንዱ ግለሰብ የሌላውን ነጻነት እስካልነካ ድረስ ብቻ ነው፤ ወይም ደግሞ አንደኛው ሌላውም ተመሳሳይ ነጻነት ያለው መሆኑን የተረዳ እንደሆን ብቻ ነው።
ይህም ማለት የሰው ልጅ ውስጣዊ ነጻነት እዚያው በዚያው በራሱ ላይ ገደብ ያደርጋል ማለት ነው። ማንኛውም ሰው የራሴ የሆነ፣ ሰው በመሆኔ ብቻ የተቀዳጀሁት ነጻነት አለ
በማለት የሌላውን ነጻነት መድፈር የለበትም። እንደነ ፕላቶ በካንትም ዕምነት መሰረት የሰው ልጅ አርቆ የማሰብ ባህርይ አለው። በዚህ ውስጣዊ የማሰብ ኃይሉ እስከምን ድረስ
መሄድ እንደሚችል ራሱን ይቆጣጠራል። አንድ ነገር ከማድረጉ በፊት ሌላውን ላለመጉዳት ያወጣል ያወርዳል። ይሁንና ግን ይህንን ዕውነተኛ ነጻነቱን እንዳይረዳ፣ እስከምን ድረስ
መሄድ እንዳለበትና፣ ተፈጥሮአዊ ነጻነት እንዳለው ተገንዝቦ የስልጣኔ ባለቤት እንዳይሆን የሚያግዱት ነገሮች አሉ። ማንኛውም ግለሰብ የሌላው ተገዢ አለመሆኑን እንዲረዳ
ከተፈለገና በዚህ ተፈጥሮ በለገሰው ውስጣዊ ነጻነት ራሱንና አካባቢውን እንዲለውጥ የዕውነተኛ ዕውቀት ባለቤት እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። ዕውነተኛ ነጻነትና ዕውነተኛ
ዕውቀት ሲጣመሩ ማንነቱን ይበልጥ ይገነዘባል፤ የመፍጠር ኃይሉም ይዳብራል። የራሱንና የሌላውን ነጻነት በመረዳት የበለጠ የተፈጥሮን ህግና ትርጉም ይረዳል። ኒውተን ተፈጥሮን
እንደበድን አድርጎ ሲቆጥር፣ ካንት ግን ይህንን በመቃወም ተፈጥሮ ህይወት ያለውና በየጊዜውም ውስጥ ባለው ኃይል ሊለወጥ እንደሚችል ያመለክታል። ስለሆነም የሰው
ልጅም የተፈጥሮምና የማይታየው ወይም የረቀቀው መንፈስ አካል ነው። ድርጊቱ ሁሉ የተፈጥሮን ህግ በመረዳት የሚካሄድ ነው። በካንት ዕምነት የሰው ልጅ አዕምሮ በብዙ
ቅራኔዎች የተወጠረ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት የሰው ልጅ ጭንቅላት ውስጥ ገብተው የሚብላሉ ብዙ ነገሮች ስላሉ አስተሳሰቡ በመወሰንና በነጻነት መሀከል ይዋልላል። ከዚህ
የአዕምሮ ጭንቀትና የአስተሳሰብ ቅራኔ ለመውጣት የሚችለው፣ ተግባራዊ በሚሆን የአርቆ አስትዋይነት ወይም አሳቢነት አማካይነት ብቻ ሲመራ ነው። ይህም ማለት እያንዳንዱ
ግለሰብ ለራሱ የሚሆን የአርቆ ማስበ መመዘኛ ያወጣል። ይህ መመዘኛውም ራሱን የሚጠቅም ወይም የማይጎዳው መሆን አለበት። ስለሆነም ይህ ለራሱ ብሎ የደነገገው
ሞራላዊ መመዘኛ ለሌላውም የሚያገለግል መሆን አለበት። ይህ ዐይነቱ የሞራል መመዘኛና ሌላውን እንዳይጎዳ መወሰድ ያለባቸው ዕርምጃዎች ዓለም አቀፋዊ ባህርይ
አላቸው። በካንት ዕምነት በአንድ አገር ውስጥ ያለ ህዝብ ብቻ ሳይሆን፣ በየአገሮች መሀከልም መከባበርና ሰላም እንዲሰፈን ከተፈለገ ይህንን የሞራል መመዘኛ መቀበል
ያስፈልጋል። የካንት አባባል ልክ መጽሀፍ ቅዱሱ ውስጥ የሰፈረውን „በራስህ ላይ ሊደረግ የማትፈለገውን መጥፎ ድርጊት ለሌላውም ሰው አትመኝ፣ ወይም አትፈፅምበት“ ከሚለው
ትምህርታዊ አባባል ጋር የሚጣጣም ነው። ይህ የካንት አቀራረብ የእንግሊዞቹን የሆበስ፣ ሎክና ሁምን አመለካከት የሚጻረር ነው። በእንግሊዞቹ ፈላስፋዎች ዕምነት የሰው ልጅ
የፍላጎቱ ተገዢ ነው። አርቆ አሳቢነቱም ከፍላጎቱ በታች የሚገኝ ነው። ስለዚህም ድርጊቱ ሁሉ አንድን ጥቅም ከማግኘት ጋር የተያያዘ ነው። በተለይም በሁም ዕምነት አርቆ
አሳቢነት የፍቅር ስሜት(Passion) ባሪያ ነች። ከዚህም በመነሳት እያንዳንዱ ግለሰብ በዚህ ሎጂክ የሚመራ ነው። በሰው ልጅ አስተሳሰብ ውስጥ ግብረ-ገብነትና(Morality) ስነ-ምግባር ቦታ የላቸውም። ግብረ-ገብነት ከአርቆ አሳቢነት ውጭ የሚገኝና በራሱ ህግ የሚተዳደር ነው። በመሆኑም በኢምፔሪሲስታዊ የሳይንስ አመለካከት ውስጥ ግብረ-ገብነትና ስነ-ምግባር የሰውን ልጅ ድርጊት የመቆጣጠር ኃይል የላቸውም። በተለይም በሆበስ ዕምነት የሰው ልጅ ልክ እንደቀበሮ ነው። አንዱ በሌላኛው ላይ ጦርነት ለመዝመት የተነሳ ይመስል
በመፈራራት የሚኖሩበትና፣ እያንዳንዱ ግለሰብ በራሱ ጥቅም በመገዛት ለራሱ የሚከንፍ ስለሆነ እንደዚህ ዐይነቱን የጦርነትና የሰዎች የርስ በርስ መፈራራት ሊገታ የሚቻለው
በመንግስት ኃይል ወይም በአንዳች ከውጭ ሆኖ በሚቆጣጠር ኃይል አማካይነት ብቻ ነው።
ይህ ዐይነቱን የነሆበስ አመለካከት በተለይም የአሜሪካኑ የሚሊታሪ ሳይንስ ስልጠና የሚመራበት ነው። በአሜሪካን የሚሊታሪ ርዕዮተ-ዓለም ዕምነት እያንዳንዱ ገለሰብ ራሱን
ከሌላው ለመጠበቅ ከፈለገ በመሳሪያ መታጠቅ አለበት። ይህ ዐይነቱ ዕምነት ከሚሊታሪ አልፎ ወደ ሌሎች ህብረተሰባዊ ነገሮች ላይ በመተላለፍ፣ እያንዳንዱ ገለሰብ በራሱ ዓለም
ብቻ እንዲሽከረከር አድርጎታል። ካንት ከሩሶ የተማረው የነፃነት ዓለም ከግሪኩ በቅደም ተከተል ደረጃ የሚለይ ነው። እንደሚታወቀው በግሪኩ ስልጣኔ ዘመን በእነ ሶክራተስና በፕላቶን ዕምነት የሰው ልጅ ችግር ሁሉ አርቆ አለማሰብ ወይም የዕውቀት ችግር ነው። በእነሱ ዕምነት በጊዜው ይታይ የነበረው ችግር፣ ረሃብ፣ ድህነት፣ ጦርነትና በውዥንብር ዓለም መኖር የዚህ ሁሉ ዋናው ምንጭ ዕውነተኛ ዕውቀት አለመኖርና፣ የሰው ልጅም የራሱን ምንነት ለመረዳት አለመቻል ነው። ስለዚህም አርቆ አሳቢነትን ከትክክለኛ ዕውቀት ጋር በማዋሃድ የሰው ልጅ ነፃነቱን እንዲቀዳጅ ማድረግ ይቻላል ይሉናል። በጥንት የግሪክ ፈላስፋዎች በአንድ በኩልና በሌላ ወገን ደግሞ በሩሶና በካንት መሀከል ተቃራኒ አስተሳሰብ ያለ ቢመስልም ሁለቱም
የሚደጋገፉ ናቸው። በሌላ ወገን ግን በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያሉ የገዢ መደቦች፣ወይም ደግሞ የተሻለ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታ ያላቸው የህበረተሰብ ክፍሎች
የተቀረው የህበረተሰብ ክፍል ለዘለዓለም ተገዢ ሆኖ እንዲቀርላቸው ዕውቀት የሚባለውን ነገር እነሱ በፈለጉት መልክ እየቀረጹ በማውጣትና በማስተማር ተቀባይነት እንዲኖረው
ያደርጋሉ። በመሆኑም እነሶክራተስና ፕላቶ የሶፊስቶችን አመለካከት ሲቃወሙ ያመለክቱ የነበረው የተሳሳተ አስተሳሰብ የሰው ልጅ ሚናውን እንዳይረዳ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣
በዕውነትና በውሸት መሀከል ያለውን ልዩነት እንዳይገነዘብ ያግደዋል። ይህ በራሱ ደግሞ ካንት ነፃ ፍላጎት(Free Will) ብሎ የሚጠራውን ተግባራዊ እንዳያደርግ ያግዳል። በእኔ
ዕምነትም ሆነ የካንትን ተከታታይ ስራዎች ላነበበ በትክክለኛ ዕውቀትና በነፃ ፍላጎት መሀከል ተቃራኒ አስተሳሰብ የለም። ሁለቱም የሚደጋገፉ ናቸው።
ከዚህ ስንነሳ የነፃነትን ትርጉም ለማያውቁ ወይም ደግሞ ስልጣን ላይ ቁጥጥ ብለው ሌላውን አምሳያቸውን እንደፈለጋቸው ልናሽከረክረው እንችላለን ለሚሉ፣ ነፃነት የሚለው
አስተሳሰብ በመጽሀፍ ቅዱስም በቀጥታ ባይሆንም በተዘዋዋሪ መንገድ ሰፍሯል። የብሉ ኪዳይ ሞሰስ ምዕራፍ ዘጠኝ ላይ፣ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በአምሳሌ ፈጠርኩት
ይላል።ይህም ማለት ማንኛውም የሰው ልጅ በእግዚአብሄር ፊት እኩል ነው ማለት ነው።
በሌላ አነጋገር መጽሀፍ ቅዱሱ የሚለን አንደኛው ሌላውን የመግዛትና እንደፈለገው የማድረግ መብት የለውም። የሰው ልጅ የነፃነት ደረጃ ይለያይ እንጂ የመጨረሻ መጨረሻ
ነፃነት የህይወት ትርጉም ነው። ይህንን የነጻነት ደረጃ በአናሎጊ መልክ መረዳት ይቻላል። የነፃነት ደረጃ ስል አንድ ከእናቱ ማህፀን ያለወጣ ወይም ገና ያልተወለደ እዚያው ውስጥ
ለማደግ ሙሉ በሙሉ ጥገኛነቱ ከእናቱ በሚያገኘው ምግብ ነው። ሲወለድና የመጀመሪያውን ብርሃን ሲያገኝ የመጀመሪያውን ነፃነት ተቀዳጅ ማለት ነው። አየር
መተንፍስ ይጀምራል። ይጮሃል ወይም ያለቅሳል። በመቀጠልም መዳህ ሲጀምር የተሻለ ነፃነት አገኘ ማለት ነው። እንደዚያ እያልን ስንሄድ አንድ ልጅ ለአቅመ-አዳም ሲደርስ
ሙሉ ነፃነቱን ተቀዳጀ ማለት እንችላለን። ይህ ግን ከአካል አንጻር ስናየውና፣ ከዚያ በፊት ራሱ ማድረግ የማይችላቸውን መፈፀም ከመቻል ጋር ስናያይዘው ነው። ይህ ዐይነቱ
የአካል ነፃነት ግን ከጭንቅላት ነፃነት ጋር የማይጣጣምበት ሁኔታ አለ። የአንድ ልጅ የአእምሮ ነፃነት በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በዳበረና ስር በሰደደ አጉል አመለካከት ሊወሰን
ይችላል። በሌላ አነጋገር በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚገኝ የማቴሪያልና የአስተሳሰብ ሁኔታ የአንድን ልጅ በአዕምሮ መዳበርና አለመዳበር ይወስናል። ለምሳሌ በዘልማድ
የአኗኗር ስልት በተጠመደ ህብረተሰብና፣ በሌላ በሰለጠነ ህብረተሰብ ውስጥ ተወልዶ ባደገ ልጅ ወይም ሰው መሀከል የነፃ አስተሳሰብና ፍላጎት የዕድገት ደረጃቸው አንድ አይደሉም።
በኢኮኖሚም ሆነ በባህል ወደ ኋላ በቀረ ህብረተሰብ፣ ወይም ነፃ አስተሳሰብ እንደልብ በማይሽከረከርበት ህብረተሰብ ውስጥ ተወልዶ የሚያድግ ልጅ ሳያውቀው የግዴታ
በህብረተሰብ ውስጥ የተነጠፉ አስተሳሰቦችን፣ የራስን ፍላጎት ወደ ውጭ አውጥቶ አለመናገር፣ ጥያቄ አለመጠየቅ፣ ለመከራከር አለመድፈር፣ አጎድብድዶ ወይም አጎንብሶ
መጥፎ ነገርም ቢሆን እሺ ብሎ ተቀብሎ መሄድ እንደተፈጥሮአዊ ተደርጎ የሚወሰድበት ሁኔታ አለ። በተለይም በአገራችን አሁንም ቢሆን ከላይ የተዘረዘሩ የኢትዮጵያውያን „ጨዋ
ባህል“ እየተባሉ የሚወራላቸው የሰውን አስተሳሰብ እንደወጠሩት ነው። ስለዚህም እንደዚህ ዐይነት ህብረተሰብ ውስጥ ጥቂት እናውቃለን የሚሉና፣ ስልጣን የጨበጡ ወይም ተማርን
የሚሉ ህብረተሰቡን አፉን እንደሚያሲዙትና አጎብድዶም የነሱን አሰተሳሰብ ብቻ እንዲቀበል የማድረጉ ኃይል ከፍ ያለ ነው። ይህ በራሱ ለስልጣኔ ዕንቅፋት ይሆናል። ምክንያቱም
ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው የሃሳብ ግጭት ሲኖርና አማራጭ አስተያየት ሲቀርብ ነው። ለዚህ ነው በአውሮፓ ውስጥ ከሙዚቃ እስከ ሊትሬቸር፣
ከአርክቴክቸርና እስከመንገድ አሰራርና ሊሎችም ህብረተሰቡን የሚመለከቱ ነገሮች በትችት መነጽር የሚታዩት። አየር ለመተንፈስ እንደሚያስፈልገንም፣ ህብረተሰብአዊ ትችት ለአንድ
ህዝብ ዕድገት እጅግ አስፈላጊ ነው። ክርክርና ትችት የማይደረግበት ህብረተሰብ የማደግ ኃይል አይኖረውም።
ስለሆነም ከጥንቱ የግሪክ ስልጣኔ ታሪክ ጀምሮ እስከ አውሮፓው የህብረተሰብ ግንባታ ድረስ ለዕውነተኛ ዕውቀትና ነፃነት የተደረገውን ትግል ስንመለከት ልማዳዊና ባህላዊ
የሚባሉ አኗኗሮች የቱን ያህል የሰውን ልጅ የተፈጥሮ ተገዢ ብቻ ሳይሆን፣ የሌላውም በስልጣን ላይ የተቀመጠው ኃይል ተገዢ በመሆን እግዚአብሄር የሰጠውን ዕውነተኛ ነፃነት
እንዳይጠቀምና ችግሩን እንዳይፈታ ያደረገው መሆኑን በመረዳት ነው። የግሪኩ ስልጣኔም አነሳስ የሰውን ልጅ መሰረታዊ ቦታ በመረዳት የተደረገ እንቅስቃሴ ነው። የመጀመሪያው
ታለስ የተባለው የግሪኩ ፈላስፋ 1ኛ) እግዚአብሔርን የማመሰግነው እንስሳ አድርጎኝ አለመፍጠሩ፣ 2ኛ) አረመኔ ሳልሆን የሰለጠንኩ በመሆኔ ነው ይላል። በዚያን ዘመን
ግሪኮች ራሳቸውን ከሌሎች ህዝቦች ጋር በማወዳደር እነሱ ብቻ የሰለጠኑ መሆናቸውን ያምኑ ነበር። የግሪክ ፈላስፎች አንዳንድ የፍልስፍናን አስተሳሰቦች በተለይም ከግብፅም ሆነ
ከህንድ ቢወስዱም፣ ፍልስፍና የዕውቀት ሁሉ አባት ሆኖ መዳበር እንዲችል መንገዱን ያመቻቹትና፣ በአደባባይ ላይ ህዝብ ወይም ተከተያዮቻቸው አንዲወያዩ ማድረግ የቻሉት
እነሱ ናቸው። በተለያዩ የግሪክ ፈላስፎች የዳበሩትን ዕውቀቶች ስናገላብጥ፣ የሰው ልጅ ዕድል ቀደም ብሎ እንደሚታመነው በአምላኮች የሚደነገግ አልነበረም። የጥፋቱም ሆነ
የጥሩ ዕድሉ ወሳኝ ራሱ የሰው ልጅ ብቻ ነው። ይህም ማለት የሰው ልጅ የማሰብ ኃይሉን መጠቀም ከቻለ ኑሮውን ለማሻሻል ሲል የግዴታ መሳሪያም የሚፈጥርና፣
እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ ተፈጥሮ የምታደርስበትን አደጋ በመቋቋም ወደፊት መራመድ እንደሚችል ነው። ከዚያም በመቀጠልም ስርዓትና የተረጋጋ ህብረተሰብ በመፍጠር ለተከታዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይችላል። የሰውን ልጅ የስልጣኔ ታሪክ ካለብዙ ጭንቀት ስንመለከት የበለጠ ነፃ በሆነ ቁጥር የማሰብ ኃይሉ ይዳብራል። የመፍጠር ኃይሉ ይጨምራል። ስርዓትና
ስምምነትን ከጭንቅላቱ ጋር በማዋሃድ የተሻለን ኑሮ ይመሰርታል። ነፃነት በሌለበት ቦታ ደግሞ የሰው ልጅ የተፈጥሮ አደጋ ሰለባ ይሆናል። ለበሽታና ለረሃብ ይጋለጣል።ተፈጥሮን
የመቆጣጠርና ልዩ ልዩ ነገሮችን እያመረተ ለመጠቀም ያለው ኃይል ይዳከማል። ይህ ሁኔታ በተለይም በአውሮፓ ምድር ውስጥ የካቶሊክ ሃይማኖት ባየለበት ከክርስቶ ልደት በኋላ
ከስድስተኛው ክፍለ-ዘመን እስከ አስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የአውሮፓ ህዝብ በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖር አድርጎታል። ይህ የጨለማ ዘመን ሊወገድ የቻለው
በሬናሳንስ እንቅስቃሴ፣ ቀጥሎ ደግሞ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ግኝት አማካይነት ነው።
ያረጀውና ህብረተሰቡን ተብትቦ የያዘው ስርዓት በአዲስ ዕውቀት ሲፈተንና ግፊት ሲገጥመው ለአዲሱ ቦታ በመስጠት የአውሮፓ ህዝብ፣ ዕደ-ጥበብን፣ ንግድን ማስፋፋት፣
ከተማዎችን መገንባትና ሌሎች ተዓምር የሆኑ ስራዎችን መስራት ቻለ። ይህ ሁሉ የተገኘው ከላይ በተወረወረ ወይም በገዢዎች ቡራኬ ሳይሆን፣ የዕውነተኛ ነፃነትን ትርጉም በተረዱና
ራሳቸውን ለመሰዋት በተዘጋጁ ምሁሮች አማካይነት ነው። የነፃነት ትግል አልፎ እልፎ ካልሆነ በስተቀር የተጀመረውና መስመርም መያዝ የቻለው በግለሰብ ታታሪዎች አማካይነት
ነው። ይህ ዐይነቱ ትግል በተገለጸላቸው ቄሶች፣ ፈላስፎችና ሳይንቲስቶች፣ እንዲሁም የልዩ ልዩ ጥበብ አዋቂዎች የተቀነባበረ የጭንቅላት ትግልና ተግባራዊ የሆነ ነው። ስለዚህም
ከጥንት ጀምሮ ለነፃነት የተደረገው ትግል ቁንጽል ሳይሆን ሁለንታዊና የሰውን ልጅ ብቁ(Perfect)እንዲሆን ከማድረግ ጋር የተያያዘ ነው። ካንት እንደሚለው የሰው ልጅ
ማቴሪያላዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም ነው። የመንፈስ ደስታውን የሚጎናፀፈው የግዴታ በሚያገኘው ገቢ ብቻ ሳይሆን መንፈሱ የሚያድስለትን ነገርም የተጎናፀፈ እንደሆን ብቻ
ነው። መንፈሳዊ ደስታዎች በልዩ ልዩ ነገሮች ነገር ግን ደግሞ በረቁቁም ሆነ በቀጥታ በሚታዩ ርካታን በሚሰጡ የሚገለጹ ናቸው። የተለያዩ ሰዎች አንድ ዐይነት ስሜት
ስለማይኖራቸው የሚረኩበት የመንፈስ ደስታም ይለያያል። እንዲሁም የንቃተ-ህሊናቸው ደረጃ የመንፈስ ርካታቸውን ሁኔታ ሊወስነው ይችላል።
አብዛኛውን ጊዜ ስለነፃነት የሚጽፉ ኢትዮጵያውያንም ሆነ አንዳንድ በኒዎ-ክላሲካል የኢኮኖሚ ትምህርት የተካኑ የአውሮፓ ምሁራን ነፃነትን ከገበያ ኢኮኖሚ ጋር ነው
ለማያያዝ የሚሞክሩት። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ የታሪክን ሂደት የዘነጋ ብቻ ሳይሆን ነፃነት የሚለውን ትርጉም እጅግ በጠባቡ ብቻ እንድንረዳና የንግድ ሰዎች ብቻ እንድንሆን
የሚገፋፋን ነው። ስለዚህም ነው ከአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በጀርመንና በእንግሊዝ ፈላስፋዎች መሀከል የጦፈ ትግል የተካሄደው። የጀርመን ፈላስፋዎችና
ሳይንቲስቶች መንገድ የበለጠ ነገሮችን ወደ ውስጥ ጠለቅ ብሎ በመረዳት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የእንግሊዞቹ ደግሞ በቀጥታ በምናየው ላይ ያተኮረ ነው። ለምሳሌ የአዳም
ስሚዝን የኢኮኖሚ ትምህርት ስንወስድ በኒውተን አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ነው።
በኒውተን ዕምነት ተፈጥሮና ህዋ ርስ በራሳቸው የተያያዙ አይደሉም። ማንኛውም ነገር ወደ ጥቃቅን ነገር፣ ለምሳሌ እንደ አቶም ተበጣጥሶ የሚቀነሰና የሚታይ ነው። እነዚህ
ተበጣጥሰውና ተሰበጣጥረው የሚገኙ ነገሮች በተፈጥሮ ውስጥ በሚገኝ ህግ የሚተዳደሩ ስለሆነ፣ እግዚአብሔር ከውጭ ሆኖ ድርጊታቸውንና እንቅስቃሴያቸውን የሚመለከት ነው።
ጣልቃ አይገባም። ተፈጥሮም ስርዓት ያላትና በተወሰነ የአርቆ አስተሳሰብ ሎጂክ ስለምትዳደር የሰው ልጅ ይህንን የተፈጥሮን ህግ የመረዳት ኃይል ይኖረዋል። የስው ልጅ
እየረቀቀና እያሰበ ሲሄድ በማቲማቲክስ መሳሪያ አማካይነት አንድን ነገር መረዳት ይችላል።
ልምምድና ነገሮችን ጠጋ ብሎ መመልከትና መመርመር ቦታ የላቸውም። ይህ አሰተሳሰብ ወደ ኢኮኖሚክስ ሲተረጎም በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚኖር እያንዳንዱ ግለሰብ በራሱ
ዓለም ብቻ የሚሽከረከር ነው። ለራሱ ጥቅም በሚያደርገው እሽቅድምድምና በማይታየው ወይም በረቀቀው እጁ አማካይነት በህብረተሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ መዛባቶችን ወደ ሚዛናዊነት እንዲመጡ ያደርጋቸዋል። ከፍ ብለን ስንሄድ ደግሞ በዛሬው የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ቲዎሪ መሰረት፣ እግዚአብሄር በፈጠረው ተፈጥሮ ላይ ጣልቃ የማይገባውን
ያህል፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በሚከሰትበትና ብዙ ህዝብን በሚያሰቃይበት ጊዜ መንግስታት ጣልቃ መግባት የለባቸውም፤ በገበያው ውስጥ ያሉ ኃይሎች በራሳቸው ኃይል ቀውሱን6
ስለሚያርሙ ዝም ብለው ነው መመልከት ያለባቸው ይሉናል። ኢኮኖሚውን ከገባበት ቀውስ ለማውጣት ጥረት ማድረግ የለባቸውም። ወደ አዳም ስሚዙ ስንመጣ ደግሞ የሰው ልጅ
ወደ ምርትና ወደ ፍጆታ(Homo Economicus) ተቀንሶ የሚታይ ነው እንጂ ሌሎች መንፈሱን የሚያድሱ ፍላጎቶች የሉትም።
ከዚህ ጋር በተያያዘና እንዲሁም ደግሞ የነፃ ንግድንም ሆነ ገበያን በህብረተሰብ ግንባታ ውስጥ ያለውን ቦታ በሚመለከት እንደዚሁ የጦፈ ትግል ተካሂዷል። በሌላ አነጋገር
የጀርመን ክላሲኮች የገበያን ኢኮኖሚ ባይቃወሙም ከህብረተሰብና ከአገር ግንባታ ውጭ ነጥለው ማየት አይፈልጉም ነበር። ምክንያቱም በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ በስራ
ክፍፍል ቢለያይምና፣ በገበያ አማካይነት የሚገናኝና የሚተሳሰር ቢሆንም ይህ ዐይነቱ ግኑኝትና የስራ ክፍፍል ጠንካራ አገርን ከመመስረት ተነጥሎ መታየት እንደሌለብት
ያሳስባሉ። ማንኛውም ግለሰብም በመነጣጠል ሳይሆን የራሱን ፍላጎት ማሟላት የሚችለው  በአንድ ባንዲራ ስርና ለአንድ ዓላማ የቆመ እንደሆን ብቻ ነው። ግለሰብአዊ ፍላጎቶች
በጠቅላላው የህብረተሰብ ፍላጎት ስር የሚጠቃለሉ ናቸው። ይህ ዐይነቱ አመለካከት ግለሰብአዊ ነፃነትን የሚፃረር ቢመስልም፣ ማንኛውም ግለሰብ ዕውነተኛ ፍላጎቱን ሊያረካ
የሚችለው እንደ ሮቢንሰን ክሩሶ በደሴት ላይ ብቻውን በመኖርና በመታገል ሳይሆን፣በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በተቀናጀ፣ ይሁንና ደግሞ ነፃነትን በማያፍን ውስጥ ሲንቀሳቀስ
ብቻ ነው። ከዚህ አንፃር ነው እነ ላይብኒዝ ሲያስጠነቅቁ የነበረው። በኢምፔሪሲዝምና በነፃ ገበያ ስም ተሳቦ የሚሰበከው ነፃነት የመጨረሻ መጨረሻ ግለሰቦችን ወደ ርስ በርስ
ጦርነት እንዲያመሩ የሚያደርግ፣ ወይም ደግሞ ዛሬ እንድምናየው ዓለም ጥቂት ኃይሎች የራሴ ጥቅም ተደፈረብኝ በማለት አገር የሚያተራምሱበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለው
በመስጋት ነው። የእነ አዳም ስሚዙ የነፃ ገበያ አሰተሳሰብና የነፃነት ትርጉም በጥቂት ኃይሎችና ፍላጎት በፎርማል ደረጃ የሚታይና የሚገለጽ ሲሆን፣ በመሰረቱ የሩሶንና
የካንትን አስተሳሰብ የሚቃወም ነው። ምክንያትም በግል ሀብት ሰበካ አማካይነት ጥቂት የናጠጡ ኃይሎች ከመንግስት መኪና ጋር በመቆላለፍ በነፃነት ስም ሌላውን የነሱ ተገዢና
በነሱ ፈቃድ ብቻ እንዲተዳደሩ ስለሚያደርጉ ነው። እዚህ ላይ የግል ሀብትን ለመቃውም ሳይሆን ቁጥጥር የሌለበት ሀብትና አድልዎ የግዴታ ዛሬ እንደምናየው ዓለም ዕውነተኛ
ነፃነትን አያጎናጽፍም። ከዚህ በመነሳት የነላይብኒዝ ትግል ከፍልስፍናና ከዕምነት ውጭ አልነበረም። ትግላቸውም ሚዛናዊና ህብረተሰብአዊ ሰላምን ከማስፈን ጋር የተያያዘ ነው።
የነፃ ገበያና ንግድ አስተሳሰብ በአሸናፊነት ከወጣ ከ18ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በዚያው መጠንም የኃይል አሰላለፍ ይለወጣል። የሀብት ቁጥጥርና ክፍፍልም መልክ እየያዘ
ይመጣል። በካፒታሊስት ህብረተሰብ ውስጥ ሁሉም በዕኩልነት ደረጃ ሀብት መቆጣጠርየማይችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል። ስለዚህም ህግና የህግ የበላይነት ከዚህ አዲስ የህብረተሰብ
ግኑኝነት አንፃር የሚነደፉ ሆነ። ቀስ በቀስ የተገነባውን የኃይል አሰላለፍ የሚያረጋግጡ ናቸው ማለት ነው። የገበያ ኢኮኖሚና የነፃ ንግድ ደግሞ የርዕዮተ-ዓለም ተቀባይነት
እንዲኖራቸው የሚሰበክባቸው መሳሪያዎች ናቸው።
ካፒታሊዝም የበላይነት ከተቀዳጀ ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ደግሞ በነፃ ገበያ ስም የተሰበከው ነፃነትን መቀዳጀት ተግባራዊ እንዳልሆነ በዘመኑ የተደረገውን ካፒታሊዝምን
የሚጻረር ትግል መመልከቱ ይበቃል። በኢንዱስትሪ አብዮት አማካይነት ከእርሻ መሬት እየተፈናቀለ ስራ ለመፈለግ ሲል ወደ ዋና ከተማዎች እንዲፈልስ የተደረገው ጉልበቱን
ከመሽጥ በስተቀር ሌላ ነፃነት እንዳልነበረው በዚህ አካባቢ የተጻፉ አያሌ መጽሀፎች ያረጋግጣሉ። ሰፊው ስራ ፈላጊ ህዝብ እንደ ቆሻሻ የሚታይና በየመንገዱ ላይ
የሚያድርና፣ ከመንገድ እየፈለገ የሚመገብ ነበር። በየፋብሪካው ተቀጥሮ የሚሰራው ሰራተኛ ደግሞ ለአሰሪው ታዛዥ ከመሆን በስተቀር በሙያ ማሀበር የመደራጀት መብት
እለነበረውም። እጅግ በሚያሰለች መልክ ከማሽን ጋር እየታገለ ከማምረት በስተቀር ብሶቱንና ፍላጎቱን የመግለጽ መብት አልነበረውም። እንደዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ሰፍኖ ይገኝ
የነበረው ከሶስት መቶ ዐመት በፊት የሰውን ጭንቅላት የሚያድስ የባህል አብዮት ከተካሄደና፣ በተከታዩ ደግሞ ኤላይንተሜንት የተባለው በፍጹም ሞናርኪዎች አገዛዝ ላይ
የተነሳው ምሁራዊ እንቅስቃሴ ብዙ የአውሮፓ አገሮችን ካዳረሰ በኋላ ነው።
በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ካፒታሊዝም በማያወላውል መልክ የበላይነትነትን ሲቀዳጅ የሰው ልጅ ነፃነት በፍጆታ ግዢና ጥቅምን ከማሳደግ አንፃር ብቻ የሚታይ ሆነ። ማንኛውም
ግለሰብ በገበያ ፊት ቢያንስ በፎርማል ደረጃ ነፃ ሆኖ የሚታይ ሆነ። ይህም ማለት ነፃነቱ ሊወሰን የሚችለው ባለው የመግዛት ኃይል ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር የነፃ ገበያ እዚያው
በዚያው የማግለል ባህርይም አለው ማለት ነው። በዚህ መልክ ካፒታሊዝም በአገር ደረጃ መወሰኑን ሲያቆምና ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ሲወስድ በትምህርት ቤት የኢኮኖሚክስ
ትምህርት የሰውን ልጅ የነፃነት ትርጉም በዚህ የአስተሳሰብ ክልል ውስጥ እንዲወድቅ አደረገ። በንግድ አማካይነት ሁሉም አገሮች የሚተሳሰሩበት ሁኔታ ተፈጠረ። በማምረት
አማካይነት ሳይሆን አንድ ህብረተሰብ የሚሻሻለው በንግድ አማካይነት ከሌላው ዓለም ጋር የተሳሰረ እንደሆን ነው የሚለው በሰፊው መሰበክ ተጀመረ። በአስራሰባተኛውና
በአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ ያሉት የእንግሊዝ ፈላስፎችና የነፃ ገበያ አራማጆች እዚያ በዚያው የቅኝ ግዛት አራማጆች የነበሩ ያዋቀሩት እንደ ኢስት-ኢንዲያን
ካምፓኒ(East Indian Company) የመሳሰሉት አዲስ በተፈጠረው ዓለም አቀፋዊ ግኑኝነት ልዩ አወቃቀር በመያዝ ዛሬ የሶስተኛው ዓለም ተብለው የሚጠሩ አገሮችን ወደ ተራ ጥሬ-ሀብት አምራችነት የሚለውጡበት ሁኔታ ተፈጠረ። የነፃነት ትርጉምም በዚህ የንግድ እንቅስቃሴ ክልል ውስጥ የሚታይ ሆነ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ቀደም ብለው የተዋቀሩ የስራ-ክፍፍሎችና የህብረተሰብ አደረጃጀቶች እንዲጨናገፉ በመደረግ ቀስ በቀስ እያለ በማደግ ላይ ባለው ግሎባል ካፒታሊዝም መዳፍ ስር
እንዲወድቁ የተደረገው። ልክ ሩሶና ካንት እንዳስተማሩን አንድ ሰው የሌላው ጥገኛና ታዛዥ ከሆነ ነፃንቱን ተገፈፈ እንዳሉን፣ በግሎባል ካፒታሊዝም ስር የተዋቀረው ዓለም አቀፋዊ
ንግድ በብዙ ሚሊዮን የሚጠጉ የሶስተኛውን ዓለም ህዝቦች ወደ ባርነት ለወጧቸው።
ይህም ማለት አንድ ሰው ወደ ተራ አምራችነት ከተለወጠ እግዚአብሔር የሰጠውን የመፍጠር ኃይል ይነጠቃል፤ ባርያ እንዲሆን ይደረጋል። በማሰብ ኃይሉ ልዩ ልዩ ነገሮችን
በመፍጠርና በማምረት ፍላጎቱን አሟልቶ ወደ ህብረተሰብ ኃይል ሊሸጋገር አይቸልም። ነፃ አገር ሊመሰርት አይችልም። ከዚህ በመነሳት ነው በኛና በሌሎች በተቀሩት የሶስተኛው
ዓለም አገሮች ያለውን የነፃነት ትርጉምና አስቸጋሪ የትግል ሁኔታ መረዳት የምንችለው።
ዓለም አቀፋዊ ካፒታሊዝምና የነፃነት ትግል አስቸጋሪ ሁኔታ!

በእኛ በኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ በተለይም ደግሞ ለስልጣን በሚታገሉ ኃይሎች ዘንድ ያለው ግንዛቤ፣ በብዙ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮችና፣ የእኛንም
ጨምሮ በግሎባል ካፒታሊዝም ወይም ይህንን በሚወክሉ መንግስታትና በኛዎች ፖለቲከኛ ባዮች ዘንድ ምንም ዐይነት ግኑኝነትና የጥቅም መተሳሰር እንደሌለ ነው። ለምሳሌ ባለፉት
21 ዐመታት በአገራችን ምድር ሲካሄድ የነበረው ፖለቲካና ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በእነ አቶ መለሰና ታዛዦቻቸው ዕውቀትና ኃይል ብቻ ነው። የውጭ ኃይሎች፣
በተለይም እንደ ቅዱስ የሚታየው ታላቁ አሜሪካን እንደ እግዚአብሔር ከውጭ ሆኖ እነ አቶ መለስ የሚሰሩትን ስራ ዝም ብሎ የሚያይ እንጂ ምንም ዐይነት ተፅዕኖና ጣልቃ-
ገብነት እንደሌለው ነው። በተጨማሪም እነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና ባንክ ብድር ሲጠየቁ ከመስጠት በሰተቀር በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ምንም ዐይነት ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ
ሚና የላቸውም። ከዚህ በመነሳት የሚካሄደው ትግል ስልጣን ለመያዝ የሚደረግና፣ እነ አቶ መለስን የማስወገድ ትግል ብቻ ነው። የነፃነቱም ትግል እነ አቶ መለሰን ከማስወገድ
ውጭ ሊታሰብ አይችለም። እነሱ ሲወገዱ ከውጭ ጋር በሚገኘው መልካም መቀራረብ ህዝባችን ዕውነተኛውን ነፃነት ሊቀዳጅ ይችላል የሚል የነጻነትን ትርጉም በቁንጽል መልኩ
እንድናየው የሚገፋፋን ነው። ይህም ማለት እስከአሁን ድረስ እነ አቶ መለስ ቢያንስ በርዕዮተ-ዓለም ደረጃ ከእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ህብረተሰብ
ያወላገዱበትናና ያዘበራረቁበትን ሁኔታ በትክክለኛው የቲዎሪ መነፅር እየተመለከትን መዋጋት የለብንም። በሌላ አነጋገር የዓለም ኮሙኒቲ የሚባለው በብዙ ሚሊዮን ህጎች የተበተባቸውን ስምምነቶችና አገሮችን በሱ ቁጥጥር ስር የማድረጉን ልዩ ልዩ ሴራዎች ሁሉ አምነን መቀበል አለብን ማለት ነው። ይህም ማለት ለነፃነት የሚደረገው ትግል የተወሰኑ ኤሊቶች በተረጎሙትና ዓለም አቀፋዊ ኮሙኒቲው በሚቀበለው መልክ ብቻ የሚካሄድ ነው። ይህ ዐይነቱ ዕምነት የግዴታ ተፈጥሮአዊውን የሰውን ልጅ ነጻነት የሚጻረር ነው። የካንትንና
የሩሶን፣ እንዲሁም የእነ ላይብኒዝንን ትክክለኛ አስተሳሰብ የሚጻረር ነው። ሰላም፣ ብልፅግናና ዕውነተኛ ስልጣኔ እንድንጎናጸፍ የሚያደርገን ሳይሆን፣ ልክ ዛሬ እንደምናያት
ኢትዮጵያና የተቀረው የሶስተኛው ዓለም ሁኔታ እየተፈራራን እንድንኖር የሚያደርገን ነው።
ተገዢዎች እንጂ ነጻ ህዝብ እንድንሆን የሚያደርገን አካሄድ አይደለም። የሆበስ ዐይነት ዓለም እንዲሰፍን ነው የምንታገለው ማለት ነው።
አማርታያ ሴን ያለውን በትክክል የተረዳሁት ከሆነ፣ አንደኛውና ዋናው የነፃነት እንቅፋት የሚመነጨው ከመንግስታት ነው። እንደዚህ ዐይነቱ በብዙ የሶስተኛው ዓለም
አገሮች፣ በአገራችንም ጨምር የተቋቋሙት የመጨቆኛ መሳሪያዎች የቱን ያህል ከውጭ ኃይሎች ጋር እንደተሳሰሩና እንደተዋቀሩ ግን ከሴን መጽሀፍ ውስጥ ፈልጌ ላገኝ
አልቻልኩም። በሌላ በኩል አያሌ ትችታዊ አመለካከቶች ያላቸው፣ በተለይም በስድሳኛው፣ በሰባኛውና እንዲሁም በሰማኒያኛው ዓ.ም የተጻፉ መጽሀፎች አብዛኛዎቹ
የሶስተኛው ዓለም መንግስታት፣ አገራችንንም ጨምሮ በዓለም አቀፍ የካፒታሊዝም ሎጂክና የጭቆና ሰንሰለት ስር የተዋቀሩ መሆናቸውን ነው። ከመንግስቱ ቢሮክራሲ፣ ከወታደር፣
ከጸጥታና እስከፖሊስ ኃይል ድረስ ያሉት አወቃቀሮች ቀድሞውኑ በታሰቡና በተዋቀሩት የጎሎባል ካፒታሊዝም ሎጂክ አወቃቀር ስልት የተደራጁ ናቸው። ይህም ማለት፣
አብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም የመንግስታት መኪናዎች ከታች ወደ ላይ ከማቴሪያላዊ ሁኔታዎች መዳበርና ከረዥም ጊዜ የህብረተሰብ ፍላጎት አንጻር እየተሻሻሉ የተዋቀሩ
ሳይሆን፣ በየአገሩ የሰፈኑትን የገዢዎች ጥቅም ለማሰጠብቅና ወደ ውጭ ደግሞ ታዥ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው። ዕውነተኛ የዕድገትና የስልጣኔ አጋዦች እንዳይሆኑ ነው። በዚህ
መልክ ምንም ዐይነት ጭንቅላትን የሚያድስና የሚከፍት ምሁራዊ እንቅስቃሴ በሌለበትና፣ የኃይል አሰላለፉም ውስን በሆነባቸው አገሮች ስልጣን ላይ ቁጥጥ የሚሉ ኃይሎች
የራሳቸውን ጥቅም ከማስጠበቅና የውጭ ኃይልን ፍላጎት ተግባራዊ ከማድረግ አልፈው ሊሄዱ የሚችሉ አይደሉም። የፈለገው ዐይነት የግለሰብ ሆነ የኃይል አሰላለፍ ለውጥ
ቢመጣም ቀድሞውን የተገነባው የመንግስት መኪና እንደገና በመዋቀርና በመርቀቅ ለአዲሱ ኃይል የጭቆና መሳሪያ ሊሆን ይችላል። በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ አገራችንንም
ጨምሮ አብዮት የተካሄደበትን ሁኔታ ወይም የአስተዳደር ለውጥ የተደረገበትን ስንመለከት የህዝብ እንቅስቃሴዎችና ምኞቶች ተጨናግፈው የሚቀሩት ይህንን የሚቀናቀን ወይም
የሚገታ ኃይል ከመጀመሪያውኑ ስለሌለ ነው። ለምሳሌ በኢትዮጵያ አብዮት ወቅት ዱዋል ፓወር የሚባል ህዝባዊ ድርጅቶች በየቦታው ተቋቋመው ነበር። ይህ ዐይነቱ በጣም ጥሩ
ጅምርና ቢሮክራሲውን የሚተካና የሚቆጣጠር ኃይል ሊሆን የታቀደ ስርዓት የራሳቸን ጥቅም ተነካብን የሚሉ ኃይሎች ከውጭው ዓለም ጋር በመቆላለፋ፣ በተጨማሪም ውስጥ
በተፈጠረው ጨቅላ አስተሳሰባ አላስፈላጊ ትግል ይህ ዐይነቱ የመጀመሪያው የዲሞክራሲ ፅንስስ በእንጭጩ እንዲቀጭ ተደረገ።። ወደ ሌሎች አገሮች ስንመጣ ደግሞ በተጨባጭ
ሲታይ እንደ አውሮፓው ዐይነት የምሁር እንቅስቃሴ ህብረተሰብን በሚመለከቱ ማንኛውም ጥያቄዎች ላይ ውይይትና ክርክር ስለማይደረግ በአንዳች ምክንያት ስልጣን ላይ የሚወጡ
ስልጣናቸውን የህዝብን ፍላጎት ማሟያና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንቢያ ከማድረግ ይልቅ የራሳቸው ጥቅም መሳሪያ በማድረግ ወደ ጨቋኝነት ይለውጧቸዋል። አብዮት መሰልና
ምርጫ የተካሄደባቸውን የብዙ አፍሪካ አገሮችን ሁኔታ መመልከት ያስፈልጋል።
በዚህ ብቻ ሳይወሰን፣ ህዝባዊ ፍላጎቶችና ዲሞክራሲያዊ ስርዓቶች ተግባራዊ እንዳይሆኑ ቢርክራሲውን በርዕዮተ-ዓለም መቆጣጠር ሌላው ስትራቴጂ ነው። የመጨቆኛ
መሳሪያውን ማጠናከርና አንዳንድ ግለሰቦችን በርዕዮተ-ዓለም ደረጃ ማስልጠን ለስልጣኔ የሚደረገውን ትግል ውስብስብ ያደርገዋል። በአንድ ፓሊሲ ላይ ሌላ የማይሰራ በማካተት
ከፍተኛ ውዥንብር እንዲፈጠር ይደረጋል። በዚህ መልክ ቢሮክራሲው ብቻ ሳይሆን ሌላውም ምሁሩ ዕውነተኛውን የስልጣኔ ጎዳና ለማግኘት ይሳነዋል። በተለይም የሲቪል ቢሮክራሲው
ከነፃ ገበያ ፍልስፍና ውጭ ማሰብ እንዳይችል በተወሰኑ የሞኔተሪ አስተሳሰቦች እንዲሰለጥን ይደረጋል። ይህም ማለት በመቆጠብና አንዳንድ አንጀት አጥብቅ ፖሊሲዎች ተግባራዊ
እንዲሆን በማድረግ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚመጣ ይመስለዋል። በጥቃቅን የመዋዕለ-ነዋይ ሂደቶች አማካይነት ብቻ ለውጥ ይመጣል ብሎ እንዲያስብ ብቻ ይደረጋል። በተለይም
ከ1950ዎቹ ጀምሮ ምንም ዐይነት ውይይት ሳይካሄድባቸው የተተከሉትን በፍጆታ ምርት ላይ ያተኮሩትን ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎች ስንመለከት የቱን ያህል የሲቪል ቢሮክራሲው፣
በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ተገዢ እንደሆነ እንገነዘባለን። ሰሞኑን በኢኮኖሚስቶች መሀከል የሚካሄደውን የጦፈ ክርክር ስንመለከትና፣ አንዳንዶች የነጻ
ገበያን እንደዋና ትምህርት ብቻ አድርገው ሲያስተምሩ የነበሩ የአሜሪካ ፕሮፌሰሮችን ኑዛዜ ስናነብ፣ የታወቁት የጀርመን የኢኮኖሚ ምሁርና የ2007 የፊናንስ ቀውስ መምጣቱን ቀደም
ብለው የጻፉት ፕሮፌሰር ማክስ ኦቶ እንዳሉት በየትምህርት ቤቱ የሚሰጠው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ብዙዎችን አስተሳሰባቸውን ሊያጠበው እንደቻለ ሁሉ፣ በአገራችንም በቢሮክራሲው አማካይነት ተግባራዊ ሲሆን የነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲና በዩኒቨርሲቲ የሚሰጠው ትምህርት ጠለቅ ብለው እንዳያስቡ አድርጓቸዋል። ከዚህም ስንነሳ በአገራችን
ምድር አብዮት ተካሂዷል ቢባልም በሚሊታሪውና በሲቪል ቢሮክራሲው ዘንድ ምንም ዐይነት የአስተሳሰብ ለውጥ ባለመደረጉ- ሊደረግም አይችልም ነበር- አብዮት ሊቀለበስ
የቻለው የውጭው የተሳሰተ የገበያ ኢኮኖሚ አስተሳሰብም ስር የሰደደ ስለነበር ነው።
የወታደሩን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስንመለከት ያወጡ የነበሩት የድሮው የአፄው ቢሮክራሲና፣ስርዓት ያለ የኢንዱስትሪ አብዮት ደረጃ በደረጃ መካሄድ እንዳለበት ለመረዳት በማይፈልጉ
ኃይሎች አማካይነት ነበር። በተለይም የጃፓንን በሜጂ ዲናስቲ ዘመን ይደረግ የነበረውን ክርክር ጠጋ ብለን ስንመለከት፣ በዚያን ጊዜ ጃፓንን የሰለጠነች አገር ለማድረግ ይታገሉ
የነበሩ ምህሮች ሲያሳስቡ የነበረው በውጭው ኃይል ላይ ዕምነት ያለውን ኃይል መዋጋት እንደሚያስፈልግና፣ በተለይም ደግሞ የንግድ እንቅስቃሴን አጉልቶ የሚያሳይን ኃይል
አጥብቆ መቃወም በማመልከት ነበር። በተጨማሪም ቢያንስ በዚያን ጊዜ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ልቆ ከሄደው ከምዕራቡ ዓለም ጋር ለመወዳደር እንዳለ የሱን መኮረጅና
እንደገና በሱ መሳሪያ መልሶ መዋጋት እንደሚያስፈልግ የሜጂ ዲይናስቲ ኤሊቶች አጥብቀው ያሳስቡ ነበር። ምክንያቱም እንደዚህ ዐይነቱ አቀባባይ ከበርቴና የሲቪል
ቢሮክራሲ ከራሱ ጥቅም አልፎ ለአገር ስለማያስብ የተወሳሰበን የኢንዱስትሪ ተከላ ዕቅድ ያጨናግፋል፤ የስልጣኔውንም መንገድ ያጨልመዋል ብለው በማሰብ ነበር። ከዚህ ስንነሳ
የደርግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ፈረንጆች እንደሚሉት በግማሽ ልብ የተካሄደ ነው፤ ወይም ደግሞ የተለያዩ አገሮችን ልምድ በማገናዘብና በመከራከር አማራጭ አውጥቶ በሱ ላይ
መረባረብ አልነበረም።
ይህንን ትተን ወደዛሬው የወያኔ አገዛዝ ስንመጣ የደርግን የአሰራር ስልት በመውሰድ የጭቆና ሰንሰለቱን በእዲስ መልክ መዘርጋት ችሏል። ይሁንና ደግሞ ይህንን
የጭቆናና የከፋፍለህ ግዛ አገዛዙን ለማጠናከር የምዕራቡ ዓለም፣ በተለይም እንግሊዝና አሜሪካ እንደተባበሩት ግልጽ ነው። በተለይም ሸበረተኝነት የሚለው ፈሊጥ ሌላው የትግል
መፈክር በሆነበት ዘመን በመሀከላቸው ያለው መተሳሰርና ወደ ውስጥ ደግሞ ጭቆናን አስፍኖ ነፃነትን መግፈፍና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዳይኖር ማድረግ ዋናው የትግል
ስትራቴጂ መሆኑን የኔ ትንተና ብቻ ሳይሆን ብዙ ጥናቶችም ያመለክታሉ። ወደ ኢኮኖሚ ፖሊስውም ስንመጣ፣ ኢህአዴግ ወይም ወያኔ 21 ዐመታት ያህል ሲከተል የነበረው
የኢኮኖሚ ፖሊሲ በ1980ዎቹ ዐመታት በፕሬዘደንት ሬገንና በማርግሬት ቴቸር ዓለምን ለመቆጣጠር የወጣውን የዋሽንግተን ኮንሰስ የሚባለውን ተግባራዊ በማድረግ ነው።ይህ
ዐይነቱ ፖሊሲ የመዋቅር ማስተካከያ ፖሊሲ ተብሎ ሲታወቅ፣ ዋና ዐላማውም የአንድን አገር ኢኮኖሚ በሰፊ የማኑፋክቱር ኢንዱስትሪ ላይ መገንባት ሳይሆን ወደ ወጭ
እንዲያተኩር ማደረግ ነው። ከዚህ ስንነሳ በተለይም እንደኛ ባለው ምሁራዊ ኃይል ደካማ በሆነበትና፣ የተወሳሰቡ የዓለም ሁኔታዎችን ማንበብ በማይቻልበት አገር ለነፃነት
የሚደረገው ትግል እጅግ አስቸጋሪና የተወሳሰበ ይሆናል ማለት ነው።
የኢትዮጵያ ምሁራን በርግጥም ለዕውነተኛ ነፃነት እንታገላለን የሚሉ ከሆን 1ኛ) የመንግስትን መኪና አወቃቀር ከቲዎሪ አንፃር በሰፊው በማጥናትና በመገምገም ውይይት
እንዲደረግ ግፊት ማድረግ አለባቸው። የመንግስትን ምንነትና ተግባር ከፕላቶን ጀምሮ እስከነ ሺለሩ ጥበባዊ መንግስት ድረስ ሰፊ ውይይትና ክርክር ተካሂዷል። የማርክሲስት
ምሁራንም፣ በተለይም እነ ፖላንትዛስ የካፒታሊዝምን መንግስት ምንነት በሰፊው ተንትነው አቅርበዋል። ከዚህ በሻገር በተለይም የፋይናንስ ካፒታሊዝም አይሎ በወጣበት ባሁኑ ወቅት
የብዙ ካፒታሊስት አገሮች የመንግስት መኪና በነሱ ቁጥጥር ስር እየዋለና የስለላ መዋቅሩንም እያጠናከረ በመምጣት ነፃነትን አፋኝ እየሆነ መጥቷል። በተለይም ይህ ዐይነቱ
ነፃነትን በዘመናዊ ቴክኒክና ቴክኖሎጂ ማፈንና ህዝብን መቆጣጠሩ በአማሪካን ምድር የተስፋፋ ነው። ሳልማድ ሩድሺ ስድሳ አምስተኛ ዕድሜውን ሲያከብር ባደረገው ንግግር
የነፃነት ትርጉም በተለይም በአሜሪካ ምድር እየታፈነ እንደመጣና፣ ማን ምን ዐይነት መጽሀፍን እንደሚያነብ እንደሚመዘገብ በንግግሩ ላይ ጠቅሷል። 2ኛ) የአገራችንን
የመንግስት አወቃቀር ከታሪክ አንፃር ማጥናትና ለምን ለኢኮኖሚ ዕድገት ጠንቅ እንደሆነ ማመልከቱ የምሁራን ተግባር ነው። ከዚህም በመነሳት ከ40ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በአገራችን
ምድር የተዋቀረው መንግስታዊ መኪና ከውጭው ኃይል ጋር መተሳሰር እንደነበረው ማጥናትና ለውይይት ማቅረብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ይህ ጥያቄ በሰፊው ሳይጠናና
ለክርክር ሳይቀርብ ወደ ስልጣን የሚደረግ ጉዞ የመጨረሻ መጨረሻ የነፃነቱንና የዕድገቱን ዘመን ያጨልመዋል። በተጨማሪም በዓለም ኮሙኒቲ የሚለፈፈውን የህግ-በላይነትና የገበያ
ወይም ንግድ ኢኮኖሚ ውስንነት መመርመርና፣ እኛ ከምናልመውና ከምንታገልለት ነፃነትና ዕድገት ጋር ይጣጣም አይጣጣም እንደሆን መወያዩቱና መከራከሩ እጅግ አስፈላጊ ነው።
የህግ የበላይነት ዛሬ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያገኘ ኖርም ነው ብሎ ማተቱ ብቻ የሚበቃ አይመስለኝም። ይህንን በሰፊው ከስልጣኔና ህብረተሰብአዊ ዕድገት፣ እንዲሁም ከረዥሙ
ሰላም መኖር ጋር እያያዙ መወያየት ያስፈልጋል። በሌላ አነጋገር ሃሳብን ለማጥበብ አለመመኮር፣ ወይም ለራስ እንዲያመች ብቻ አድርጎ አለማቅረብ የሀቀኛ ምሁራን
ኃላፊነትና ተግባር ነው።
የዲሞክራሲ ትርጉምና ተግባራዊነቱ !
በጥንታዊቱ ግሪክ ዘመን ዲሞክራሲ ማለት የህዝብ አገዛዝ ማለት ነው። ዲሞክራሲ ከተወሰነ የጎሳ አገዛዝ ጋር የተያያዘ ሳይሆን በአንድ ክልል ይኖሩ የነበሩ እንደ
ነፃ ዜጋ ይታዩ የነበሩትን የአገዛዝ ስልትና ጥቅማቸውን የሚያንፀባርቅ ነው። ከዚህም በመነሳት ዲሞክራሲ በአንድ ህዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተግባራዊ የሚሆን፣ የዚያን
ህዝብ ጥቅም የሚያስጠብቅ አገዛዝ ማለት ነው። ይሁንና ግን በግሪክ ስልጣኔ ዘመን የሰፈነው ዲሞክራሲ ውስንነት የነበረው ሲሆን፣ ከክርስቶ ልደት በፊት በሶሎን አማካይነት
የተዋቀረው ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በዕዳ የተተበተበውንና በባላባቱ ስር ጥገኛ የሆነውን ገበሬ ነፃ በማውጣት ሰፋ ያለ የስልጣኔ ፈለግ የቀደደ ነው። በእርግጥ
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ፍልስፍናንም ሆነ ማቲማቲክስ፣ እንዲሁም ጥበብና አርክቴክቸር ቀጥሎም ድራማ የበለጠ በሰው የመፍጠር ኃይል ተግባራዊ የሆኑበት። ስለሆነም ዲሞክራሲ
በመምረጥና በመመረጥ ወይም ጥቅምን በማስጠብቅ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ በተቀደደው የነፃነት ፈለግ የማሰብና የመፍጠር ኃይል በመዳበር የሰውን ልጅ ሚና ለመጀመሪያ ጊዜ
ማረጋገጥ የተቻለበት ስርዓት ነው። ከዚያን ጊዜም ጀምሮ የስራ-ክፍፍል የዳበረበትና፣በስራ ክፍፍል አማካይነት የንግድ ልውውጥ ግልጽ ሆኖ የታየበት ነው። ስለሆነም ይህ
አዲሱ የስራ ክፍፍልና በሌሎች ማቴሪያላዊ ባልሆኑ ነገሮች መሳተፍና የራስን ምንነት መግለጽ የበለጠ ህዝባዊ ግኑኝነት በማዳበር በአንድ ክልል የሚኖር ህዝብ እንደ ኃይል
የሚታይበት ሁኔታ መፈጠር ቻለ።
ከኢንላይተሜንት ጀምሮ የተደረገውን የፍጹም ሞናርኪዎችን አገዛዝ የተቃውሞ ትግል ስንመለከት ሪፑብሊክን መመስረትና ገበሬውን ከአርስቶክራቲውና ከፊዩዳሉ መደብ
ጭቆና ለማላቀቅ የተደረገ ትግል ነው። በዚህ ዐይነቱ ትግል ውስጥ በቀጥታ ህዝብን በአገዛዝ ውስጥ ማሳተፍ ያስፈልጋል የሚለው እንድ አጀንዳ ባይቀርብም፣ በመንግስትና
በህዝብ ወይም በህብረተሰብ መሀከል ሊኖር የሚገባውን ግኑኝነትና መተሳሰብ በግልጽ ያቀስቀመጠ ነው። በዚህም መሰረት መንግስት ሶቨሬን ሲሆን፣ የአንድ ህዝብ የፖሊቲካ
ትሩጋሜ በመንግስት ሶቨረኒት ወይም ነጻነት አማካይነት የሚገለጽ ነው። በተለይም የአንድ ህብረተሰብ ጥቅም ወይም ፍላጎት በህግ አውጪው አማካይነት ተግባራዊ የሚሆን ነው።
ሩሶ ይህንን ዐይነቱን ፍላጎት አጠቃላይ ፍላጎት(General Will)ብሎ ይጠራዋል። ይህም ማለት አንድ ህዝብ በሚመሰርተው ማህበረሰብ አማካይነት ፍላጎቱ የሚገልጽበት ነው።
ስለዚህም አንድ ህብረተሰብ እንደ ህዝብና እያንዳንዱ ደግሞ እንደ ግለሰብ መብትና ሙሉ ነጻነቱን የሚቀዳጅበት ነው። ሩሶ እንደሚለው በዚህ ዐይነቱ የህብረተሰብ ስምምነት(Social
Contract) መንግስትና ህዝብ ተፋጠው የሚገኙበት አይደለም፤ ወይም ደግሞ መንግስት ነኝ የሚለው አካል ራሱን ከህዝብ በማግለል የፈለገውን ርምጃ የሚወስድበት ሁኔታ አይደለም። ይህ የመጀመሪያው ደረጃ ለዛሬው የፓርላሜንተሪ ዲሞክራሲ በር ከፍቷል ማለት ይቻላል።
ይሁንና ግን በ19ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ ላይ በሰራተኛው የተደረገው የቀጥታ ህዝባዊ ተሳትፎ(Direct Democracy) ትግል ስልጣኑን በማጠንከር ላይ ያለውን የከበርቴ መደብ የግዴታ ከወዛደሩ ወይም ከተጠሪዎቹ ጋር የተወሰነ ስምምነት ማድረግ እንዳለበት አስገደደው። በቢስማርክ ተግባራዊ የሆነው የሶሻል ሪፎርም የዚህ ቀጥተኛ ዲሞክራሲን
ተግባራዊ እንዳይሆን፣ ወይም እያየለ የመጣውን አብዮት ለመቀልበስ እንደሆነ አንዳንድ የታሪክ ጸሀፊዎች ያስረዳሉ። ያም ሆነ ይህ ዲሞክራሲያዊ ነጻነቶች ለቀቅ እያሉ ሲመጡ
የበለጠ የሃሳብ መንሸራሸርና በልዩ ልዩ መልኮች የሚገለጹ ዕድገቶች እየዳበሩ እንደመጡ መረዳት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ ዕድገት፣ ህብረተሰባዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም
በልዩ ልዩ ነገሮች የሚገለጽ ነው።
በዘመናችን የዲሞክራሲን ትርጉም ስንመለከት፣ ተግባራዊነቱ ተወካይን በመምረጥና በመመረጥ የሚገለጽ ቢሆንም፣ ይህ ዐይነቱ ሂደት ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው
በሶስት ኦርጋኖች መሀከል ባለው የስራ ክፍፍል አማካይነት ነው። እነዚህም ኢክስኪዩቲቭ፣ የህግ አውጭና ህግ አስፈጻሚ ናቸው። ሌሎች ዲሞክራሲያዊ ኢንስቲቱሽኖች በሙሉ በዚህ
ስር ሲጠቃለሉ፣ በተለይም ከ1980ዎች ጀምሮ እያየለ የመጣውን መንግስትንና ፓርላሜንትን የሚቆጣጠር ሰፋ ያለ የሲቪክ ማህበራት አለ። ስለሆነም በነጻ መደራጀት፣
ሃሳብን መግለጽ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግና ህዝብንና አካባቢን የሚጎዱ ነገሮች እንዲቆሙ ማድረግ በትግል የተገኙ ብቻ ሳይሆኑ፣ የጠቅላላው የህብረተሰብ ጉዞና ዕድገት አጋዥ
እንደሆኑ ማየት ይቻላል። በነቁ ኃይሎች አማካይነት አንዳንድ ጥያቄዎች ሲነሱና፣ ሰፋ ያለውን ማህበረሰብ ሲያካትቱ ለሚነሱና ተቃውሞ ለሚገጥሙት ጥያቄዎች መንግስት
የግዴታ መልስ ለመስጠት ይገደዳል። እዚህ ላይ ሚዲያ የሚጫወተው ሚና አለ።
በተለይም በአሁኑ ወቅት ሚዲያ የመንግስት አባላትን በማፋጠጥ ስነ-ምግባር የሚጥሱ ነገሮችን ሲሰሩና፣ መስራት የሚገባቸውን መፈጸም በማይችሉበት ሁኔታ በተዘዋዋሪ
ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ግፊት ያደርጋል። እዚህ ላይ አስቸጋሪ የሚሆነው የዲሞክራሲ አነሳሰና ትግል፣ የጥያቄው አቀራረብ በጣም ስፊና ውስብስብ ስለሆነ በማቲማቲካል
ሞዴሎች ማቀረብ አይቻልም። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ እጅግ አሳሳች ከመሆኑም የተነሳ ወደ ማይሆን አቅጣጫ እንድናመራ በማድረግ ለዕውነተኛ ነፃነት የሚደረግውን ትግል እንድንዘነጋ
ያደርገናል። በሌላ አነጋገር ዲሞክራሲ የሚጨበጥና የሚዳሰስ አይደለም፤የምንለማመድበት፤ የምንኖርበት፤ ስሜታችንንና ቅሬታችንን የምንገልጽበት፣ የሚያሳስበንና
የሚያስጨንቀንን ወደ ውጭ አውጥተን ለመወያየት የሚያስችለን መሳሪያ ነው። ስለዚህ ነው ዲሞክራሲን አታየውም፣ ትኖርበታለህ፣ ትለማመድበታለህ፣ የህይወትህ አንደኛው
አካል እንዲሆን ታደርገዋለህ የሚባለው። ስለዚሁም በቁጥር የሚለካ ወይም በማቲማቲካል ሞዴል የሚረጋገጥ አይደለም።
ወደ ኢትዮጵያችን እንምጣ። በአገራችን ምድር በስልጣን ላይ የሚወጡ ኃይሎች ስለዲሞክራሲ ሲነሳ የሚያስፈራቸው ነገር አለ። ይኸውም ከስልጣናቸው እንባረራለን ብለው
ስለሚፈሩ ነው። በኢትዮጵያ አብዮት ዘመን የነበረውን መገዳደሉን ትተን፣ ወርቃማ ጎኑን ስንመለከት ለመጀመሪያ ጊዜ ህዝባዊ ድርጅቶች እንደ አሸን የፈለቁበትና፣ እንዲሁም
የዕደ-ጥበብ ሙያዎችና የልዩ ልዩ ብሄረሰብ ባህሎች ይፋ የወጡበት ዘመን ነበር። ውስጥ ባለው የአገዛዝ ቅራኔና፣ በተለይም ደግሞ ተራማጅ ነኝ በሚለው ኃይል መሀከል ሽኩቻ
ባይፈጠር ኖሮና፣-ባይኖር ኖር እንበልና- የታሪክ ግንዛቤም ቢኖር ኖሮ የዲሞክራሲው ጥያቄ ሌላ መስመርን ይዞ ይጓዝ ነበር። በሌላ ወገን ደግሞ በጊዜው የህዝቡን በነፃ
መደራጀት የሚቀናቀኑ፣ በአሜሪካንና በተቀረው የምዕራብ ዓለም የሚደገፉ ፀረ-ዲሞክራሲያዊና ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች በብዛት ነበሩ። በእርግጥ የቅራኔዎችን ህግ
አያያዝና ደረጃ በደረጃ መፈታት ያለባቸውን እንደ መሬት ላራሹ የመሳሰሉትን አዋጆችና የከተማ ቤቶችን በጭፍን መውረስ ስንመለከት ተገድዶ ወደ ፀረ-ህዝብ ካምፕ የገባ አለ።
ከዚህ ውጭ ግን በቀጥታና በድጋፍ ታግዞ የህዝቡን መብቶች ለማፈንና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተግባራዊ እንዳይሆኑ፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዳይመጣ የዛሬው
የኢህአዴግ ወይም የወያኔ አገዛዝ የፀረ-ዲሞክራሲያው ትግል አንድ አካል ነበር።
ከመጀመሪያውኑ እንደነመሬት ላራሹን የመሳሰሉትን መሰረታዊ ዲሞክራሲያዊ መብቶች መዋጋት ብቻ ሳይሆን፣ ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር የኢትዮጵያን አንድነት በጥያቄ
ያስቀመጠ ኃይል ነው። የተፈታተነ ነው፤ ህዝቡ እንዳይተሳሰር ለማድረግ ብዞ አሻጥሮችን የሰራ ነው። በከፍተኛ ቂም በቀልነት የተወጠረ ነው። ዕውቀትን ያስቀደመ ሳይሆን ጦርነትን
መሰረት በማድረገ ብዙ የትግሬ ወጣቶችን ያሳሳተና ጭንቅላታቸው እንዲሽፈን ያደረገ ነው።
ከዚህ ባሻገር በህዝቡ መደራጀትና ንቃተ-ህሊና ማደግ የፈራው የወታደር አገዛዝ ቃል ኪዳን የገባውን የዲሞክራሲ መብቶችን ጥያቄ ያለገደብ መለቀቅ ማፈኑ ለዲሞክራሲያዊ
ኢንስቲቱሽን መዋቀርና ለንቃተ-ህሊና መዳበር የሚደረገውን ትግል አኮላሽቶታል። ህዝባዊ አንቅስቃሴውንና ድርጅቶችን በራሱ ቁጥጥር ስር ለማድረግ መጣሩ ቀደም ብሎ መዳበር
የጀመረው ነፃ አስተሳሰብ እንዲታፈን አድርጎታል። ይህ ሁኔታ አጎብዳጅ ለሆኑ ካድሬዎች ቦታ ያመቻቸ ነው። ልዩ ዐይነት የአድርባይነትና የእንካስላንቲሃ ባህል እንዲስፋፋ በር
የከፈተ ነው። ህዝቡ ነፃነትን መቅመስ መልመድ ሲጀምር ወደ መሸማቀቅና ወደፍርሃት እንዲሽጋገር የተደረገበት ሁኔታ ነው። በዚህ መልክ አዲስና ልዩ ዐይነት ፋሺሽታዊ አገዛዝ
የተፈጠረበት ሁኔታም እንደነበር መመልከት እንችላለን።
ነገሩን ለማሳጠር፣ የአቶ መለስ ስለ ዲሞክራሲና ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸው የተወላገደ አስተሳሰብ ዛሬ የመነጨ ወይም አዲስ ነገር ሳይሆን፣ ከድርጅታቸውና
ከደማቸው ጋር የተዋሃደ፣ በተወሰነ አካባቢና የህብረተሰብ አወቃቀር የሚገለጽ ነው። ይህም ማለት ወደ ሰሜን እየተጠጋህ በሄድክ ቁጥር፣ አይበገሬነት፣ ጦረኛነትና፣ ከሁሉም
በላይ ነኝ ማለትና ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ያየለ መሆኑን መገንዘብ እንችላለን። በተለይም ከዚያ አካባቢ የመጡ ግለሰቦች የመጡበትን ህብረተሰብ በሰፊው ከሁሉም አንጻር
የማጥናት ግዴታ አለባቸው። ብዙም ሳንጨነቅ ወደ ደቡብ ስንሄድ ደግሞ የተለያዩ ጎሳዎች ሪጂድ የሆነ አመለካከት የላቸውም። ለመማር፣ ለማዳመጥና ሃሳብ ለሃሳብ ለመለዋወጥ
የሚያመቹ ናቸው። በተለይም እኛ ከደቡብ የመጣንና- እዚህ ላይ እኔ በአባቴም ሆነ በእናቴ አማራ ብሄረሰብ ከሚባለው የተወለድኩኝ ነኝ- ከተለያዩ ጎሳዎች ከተውጣጡ
የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ያደግን ዛሬ ባለን የቲዎሪና የኢምፔሪካል መነጽር ለማረጋገጥ የምንችለው ለኢትዮጵያ አንድነትና ነጻነት እጅግ አደገኛ፣ አገሩን ለውጭ ኃይሎች
የሚያጋልጥና ለመበታተን የተዘጋጀው በተለይም ከሰሜኑ ጫፍ ክፍል የመጣ ኤሊት ነኝ የሚል አጉል ትቢተኛ ኃይል ነው። ሌላውን የሚንቅ ዘረኛ ኃይል ነው። እንደዚህ ዐይነቱ
በጥሩ ዕውቀት ያለተገራ ጭንቅላት ነው አብዛኛውን ጊዜ ለአገሮች መከስከስ፣ ለመወረርና ነፃነት ለማጣት የሚያመቸው። ይህ ዞሮ ዞሮ የዘር ወይም የጎሳ ጥያቄ ሳይሆን፣
የህብረተሰብ አወቃቀር ችግር፣ የማቴሪያል ሁኔታ አለማደግ፣ የተሻለ የስራ-ክፍፍል አለመዳበር፣ የተወሰነ መንፈስን ወይም አዕምሮን ክፍት የማያደርግ ርዕዮተ-ዓለም
በጭንቅላት ውስጥ ደንድኖ መቅረት ነው። በተለይም ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር በጋብቻ አለመዋሃድ፣ ርስ በርስ መጋባት ለዕድገትና ለሃሳብ መንሸራሸር ፀር እንደሚሆን ብዙ
የቲዎሪና የኢምፔሪካል ጥናቶች ያረጋግጣሉ። የሌላውን ሃሳብ ለመቀበል ዝግጁ የማይሆን፣እኔ በምላችሁ ብቻ ሂዱ የሚል፣ አገርን አያፈራረሰ ይኸኛው መንገድ ነው ትክክል
የሚል፣ ህዝቡ ተራብኩ ሲል ኢኮኖሚው እያደገ ነው የሚል አዕምሮው የተዘጋ ነው ከማለት ሌላ የሚባል ነገር የለም። የግሪክ ፈላስፎች የሚሉት አንድ አባባል አለ። አዕምሮ
ከተዳፈነ ዐይንም ማየት ይሳነዋል ይላሉ። ማየት የማይችል አዕምሮ ለሰው ልጅና ለተፈጥሮ ምንም ደንታ የለውም። አፀያፊ ተግባር ወይም ቆሻሻ ስርዓት እንደትክክል ሆኖ
ይታያዋል። ይህ ደግሞ በመሰረቱ የፍልስፈናን መሰረተ-ሃሳብ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሄርንም ዓለም የሚጻረር፣ ተፈጥሮንና ጠቅላላውን የሰውን ልጅ ነፃነት የሚቀናቀን
አስተሳሰብ ነው።
የወደፊቱ የዲሞክራሲ ፕሮጀክትም ስንመጣ እንዲያው የዓለም ኮሙኒቲው የተቀበለው የህግ የበላይነት ነው ብለን ነገሩን አድፈንፍነን መሄድ አንችልም። በመጀመሪያ
ደረጃ ይህ የዓለም ኮሙኒቲ የሚባለው ማን ነው? ብለን መጠየቅ አለበን። ሰባት ቢሊዮን ህዝብ፣ ይህንን እወክላለሁ የሚለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ወይም ሰለጠንኩኝ
የሚለው የምዕራቡ ዓለም። በግልጽ መቀመጥ አለበት። ፕሮፌሰር አለማየሁ ከሶስት ሳምንት በፊት ባወጣው ጽሁፍ ውስጥ የኤሊት ዲሞክራሲ ብቻውን እንደማይበቃ አመልክቷል።
ነገሩን ባያብራራውም፣ በተለይም በብዙ የአፍሪቃ አገሮችና በላቲን አሜሪካ ተግባራዊ የሆኑ የምርጫ ሂደቶች የየህዝቦቻቸውን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት ያስቻሉ አይደሉም።
ሰፊውንም ህዝብ በቀን ተቀን የአገር ግንባታ ውስጥ ማሳተፍ የቻሉና የሚያስችሉ አይደሉም። የብዙዎች አገሮች ዲሞክራሲያዊ ምርጫዎች እንዲያውም የኒዎ-ሊበራል
አጀንዳዎች ናቸው። በረቀቀ መንገድ ነፃነትን የሚያሰገፍፉና፣ ሀብት እንዲበዘበዝ የሚያደርጉ ናቸው። የመንግስት መኪና መሳሪያዎችና የስለላ ድርጅቶች በመጠናከር
በአዲሱ የአሜሪካን ስትራቴጂ ውስጥ በመካተት አሸባሪዎችን ለመዋጋት በሚል በሽብር ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ የተደረጉብት ሁኔታ እንደሰፈነ እንመለከታልን። ስለዚህም
የምንታገልለት ዲሞክራሲ ህዝባዊ ተሳትፎና ህዝባዊ አስተዳደርንም ለማካተት የሚችል መሆን አለበት። ጥቂቶች ወሳኝ መሆን የለባቸውም። በህዝብ የተመረጡ ተጠሪዎች በሙሉ
ለሚሰሩት ስራ ሁሉ ተጠያቂ መሆን አለባቸው። በእኛ አገር ቀርቶ ሰለጠንኩኝ በሚለው የምዕራቡ ዓለምም የዲሞክራሲ ጥያቄ በአዲስ መልክ ተነስቶ የሚያከራክር ነጥብ ሆኗል።
ስለሆነም የዲሞክራሲ ጥያቄ ተቀባይነት ባገኘው የህግ የበላይነት ብቻ የሚዘጋ አየደለም። እንደዚህ ብለን የምናስብ ከሆነ የታሪክ መጨረሻዋ ላይ ደርሰናል ማለት ነው። ስለዚህም
ነገሩን በጥልቀትና በሰፊው መመልከት ያስፈልጋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ፕሮፌሰር ኢሪክ ራይነረት ስለ ስልጣኔና ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ባቀረቡት ሰፊና ግሩም ጽሁፎቻቸው ወደድንም
ጠላንም ማንኛውም አገር ስልጣኔና ነጻነትን እንዲቀዳጅ ከተፈለገ የግዴታ በሬናሳንስ ስር ማለፍ አለበት ይሉናል። እኔም የማምነው በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ሁለ-
ገብ የሆነ የሬናሳንስ ዐይነት እንቅስቃሴ ማካሄድ ካልቻሉ እንደ ህብረተሰብና እንደ አገር መኖር ይሳናቸዋል። የተስተካከለ ዕድገት ማምጣት አይችሉም። የሳይንስና የቴክኖሎጂም
ባለቤት መሆን በፍጹም አይችሉም።
ወደ ብሄርሰብ ጥያቄ ስንመጣ የአገራችን የተወሳሰበ ችግር ብሄረሰቦች የሚፈልጉትን ነጻነት ስለሚሰጣቸው የሚፈታ አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ የብሄረሰብ ነጻነት ብሎ ነገር
የለም። በፍልስፍና ዓለም ውስጥ የነበረው ግለሰብአዊና ህዝባዊ ነጻነት ነው። በታሪክ ውስጥ ጎሳዊ ሶሊዳሪቲ አንድን ጎሳ ለነጻነት ያበቃበት ጊዜ አልነበረም። በኢትዮጵያ ቅርብ ግዜ
የትግል ታሪክ ውስጥ የብሄረሰብ ጥያቄ በሰፊውና በጥልቀት ከህብረ-ብሄር ምስረታና ከምሁር እንቅስቃሴ አንፃር ታሪክ ሳይጠና እንዲያው በደፈና በመወርወሩ በብዙ ሺህ
የሚቆጠሩ የዋህ ወጣቶችን አሳስቷል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ህብረ-ብሄርን ለመመስረት የተደረገውን አስቸጋሪ ጉዞ፣ በተለይም ከአውሮፓው የህብረተሰብ አገነባብ ጋር ለማነፃፀር
በላመቻሉ በተለያዩ ወቅት የተነሱ አገዛዞችን ስነወነጅል ይሰማል። ይህ የታሪክ ግንዛቤ እጥረት በተለይም ብዙም ርቆ ለመሄድ የማይቸልውን የራሳቸውን አጀንዳ ተግባራዊ
ለማድረግ ለሚሯሯጡ ኃይሎች አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሀብረተሰብ ታሪክና ጉዞ የምሁር እንቅስቃሴ ታሪክ አይደለም። የነገስታቱን ጭንቅላት
የሚቀርጽና ሰብአዊ የሚያደርጋቸው በስዕል፣ በድራማ፣ በአርክቴክቸርና በሙዚቃ የሚገለጽ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ይካሄድ ስላለነበር አንድን አገር ለመመስረት በአማዛኙ
ጦርነት ነበር ይካሄድ የነበረው። በአውሮፓ ምድርም ቢሆን ብዙ ምሁራዊ እንቅስቃሴዎች ተካሄደው በተለያዩ መሳፍንት መሀከል የማያቋርጥና እልክ አስጨራሽ ትግል ይካሄድ ነበር።
የኋላ ኋላ ይህ የማያዋጣ መሆኑን የተረዱ የፊዩዳል አገዛዞች በአንድ ፍጹማዊ ሞናርኪ አስተዳደር ውስጥ በመጠቃለልና ሰፊ ገበያ በመመስረት ከውጭ የሚመጣባቸውን ወረራ
መከላከል ጀመሩ። በኢንዱስትሪና በማኑፋክቱር አብዮት አማካይነት ህዝብ መተሳሰር ሲጀምር የብሄረሰብን ገበና በመቅደድ ህዝቡ መጋባት ጀመረ። ቀስ በቀስም ነጻነትን
ተቀዳጀ። ከዚህ ስንነሳ ትግላችን ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ አንጻር መሆን ያለበት እንጂ ዘለዓለም እየተፋራራንና እየተናናቅን እንድንኖርና የውጭ ኃይሎች መሳሪያ ወደ
ሚያደርገን ማድላት የለብንም። እያንዳንዱ ከዚህ ሆነ ከዚያኛው ብሄረሰብ ወጣሁ የሚል የበለጠ በራሱ ላይ በመተማመን ለግለሰብና ለህዝብ ነጻነት መታገል አለበት። በእኔ ዕምነት
ትክክለኛውና የነጻነቱ መንገድ ይህ ብቻ ነው። የአቶ መለስንም የነጻነትን ትርጉም የመረዳት ችግር ከዚህ አኳያ መገምገም የምንችለው።
ከዚህ ስንነሳ አቶ መለስ ከጭንቅላታቸው ሳይሆን ከሆዳቸው እያወጡ የሚናገሩትና በዲሞክራሲና በነፃነት እንዲሁም በዕድገት መሀከል ያለውን ግኑኝነት እንደቁም ነገር
መውሰድ የለብንም። በሌላ ወገን ግን ከዚህ ተነስተን የምንከራከር ከሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት አለን ግን የጎደለን ነገር ዲሞክራሲና ነፃነት ነው ብለን አምነን እንድንቀበል እንገደዳለን።
የአቶ ኤፍሬም ማዴቦም ጽሁፍ ሳይወድ በግድ ወይም ሳያስብበት ወደዚያ የሚያመራን ይመስላል። ከዚስ ስንነሳ ምን ዐይነት ዕድገትና ለማን ወደ ሚለው ጋ እንመጣ።
ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ዕድገትና ለማን!
ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት የተጻፉ ሊተሬቸሮች ሺህ በሺህ የሚቆጠሩ ናቸው። ቁጥራቸውም ከመብዛቱ የተነሳ ትክክለኛውን ሃሳብ ለመጨበጥ በጣም ያዳግታል። በሌላ
ወገን ግን ሰለ ኢኮኖሚ ዕድገት በሚወራበት ወይም በሚጻፍበት ጊዜ ከተወሰነ ርዕየተ-ዓለም ክልልና የኃይል አሰላለፍ ውጭ ነጥሎ ማየት አይቻልም። በታሪክ ውስጥ
የህብረተሰብ ግንባታንም ሆነ የኢኮኖሚ ዕድገትን ታሪክ ለተመለከተ ዕድገት የሚባለው ነገር ስልጣን ላይ ባለው ኃይልና ከሱ ጋር በጥቅም ከተቆላለፉ ጋር የተያዛዘ ነው። ለዚህም ነው
ከጥንታዊቱ የግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ ዕኩልነትና(Justice) ሚዛናዊነት ለአንድ ህብረተሰብ መረጋጋትና በሰላም ለመኖር አስፈላጊ ናቸው እየተባለ ትግል የተጀመረው። ምክንያቱም
ስልጣን ላይ የሚወጡ አብዛኛውን ጊዜ በፍልስፍናና በሳይንሳዊ ህግ ስለማይመሩ የተወሰነ የኢኮኖሚ ፖሊሲን በመከተል የግዴታ ለድህነት መፈልፈል በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን
ደግሞ ጥቂቱ ሀብት በመቆጣጠር የጠቅላላውን ህዝብ የመኖርና ያለመኖር ዕድል እንደሚወስኑ ስለተገነዘቡ ነው። የኢኮኖሚ ታሪክን መጽሀፎች ላገላበጠ በዚህ ዙሪያ
የተደረገውን ዕልክ አስጨራሽ ትግል መመልከት ይቻላል።
ወደ ቲዎሪ ጥያቄ ስንመጣ ደግሞ፣ አንድ አገር ሀብት መፍጠር የምትችለው እንዴት ነው? በሚለው ዙሪያ የተለያዩ አስተሳሰቦች ይስፋፉ ነበር። በፊዚይክራቶች፣
የመጀመሪያው የነጻ ገበያ ፍልስፍና አፍላቂዎች ወይም ላሴዝ ፌር አሳቢዎች አመለካከት የአንድ አገር ሀብት ምንጭ እርሻ ነው የሚል ነው። ከገበሬው በስተቀር ሌሎች
የህብረተሰብ ክፍሎች ምርታማ(Unproductive) ያልሆኑና፣ ከእርሻ የሚመጣው ትርፋማ ምርት(Surplus product) ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተከፋፍሎ የተቀረው እንደገና ለመዋዕለ-ነዋይ በመዋል በዚህ አማካይነት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ይመጣል ይሉናል።
በመርካንትሊስቶች ዕምነት ደግሞ የአንድ አገር ሀብት ዋናው ምንጭ ተፈጥሮ ወይም ምድርና የሰው ጉልበት ናቸው። የሰው ጉልበት ወይም ኃይል ወይም ስራ ከተፈጥሮ ውስጥ
ቆፍሮ የሚያወጣውን ንጥረ-ነገር በኃይል አማካይነት ወደ ፍጆታ ጠቀሜታ ከለወጠውና፣የተወሰነው ደግሞ ለመዋዕለ-ነዋይ ከዋለ በዚህ አማካይነት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ይመጣል
ይላሉ። በኋላ ብቅ ያሉት የመርካንትሊስት ኢኮኖሚስቶች ነገሩን በማስፋፋት፣ አንድ ህብረተሰብ በኢኮኖሚ ዕድገት አማካይነት እንዲተሳሰር ከተፈለገ የማኑፋክቱር አብዮት
ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ያረጋግጣሉ። ምክንያቱም ከእርሻ ይልቅ የማኑፋክቱር መስክ የሚስፋፋና የሚያድግ፣ እንዲሁም የማባዛት ኃይል ስላለው ዕውነተኛ የስራ-ክፍፍልና
የኢኮኖሚ ዕድገት በዚህ አማካይነት ብቻ ነው ሊዳብር የሚችለው ይሉናል።
ወደ ተጫባጭ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስንመጣም ከአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ የመጣው የመርካንትሊስቶች የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ለካፒታሊዝም
ዕድገትና መስፋፋት መንገድ የቀደደው። በጊዜው ቢያንስ ማደግ ለሚፈልጉ ኃይሎች መንገዱ ክፍት ነበር። እንደ አገራችን ሁኔታ በጎሳ የተገደበና አፋኝ አልነበረም።
እንዲያውም ንቁ የሚባሉ ኃይሎችን(Active Forces) በተለያየ መንገድ መርዳትና፣ የውስጥን ገበያ ደግሞ ከውጭ በሚመጣ ዕቃ እንዳይጥለቀለቅ አስፈላጊ የጉምሩክ ፖሊሲ ይካሄድ ነበር። ይህ ዐይነቱ በብዙዎቹ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ተግባራዊ የሆነ ፖሊሲ ነው።
ከዚህ በኋላ ነው የእነ አዳም ስሚዙ የነፃ ገበያና ንግድ ፖሊሲ መስፋፋት የጀመረው። በእነ አዳም ስሚዝ ቲዎሪ መሰረት አንድን ምርት ለማምረት ሶስት ነገሮች መጣመር
አለባቸው። ይኸውም፣ የሰው ኃይል፣ ካፒታልና መሬት ናቸው። በተጨማሪም የረቀቀው የሰው እጅ ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ አዳም ስሚዝ ያትታል። ይህ እንዳለ
በመወሰድ የትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ በዚህ መልክ ረቀቀ። ሁላችንም በዚህ መልክ ሰለጠን።
ወደ ማርክስ ቲዎሪ ስንመጣ ደግሞ፣ የመርካንትልሲቶችን ሃሳብ በመቀበልና ሰፋ በማድረግ፣ ዋናው(Value) የዋጋና ተከታታይ የካፒታል ክምችት ዕድገት ምንጭ የስራ
ኃይል እንደሆነ ያበስራል። ከዚህ ጋር በማያያዝ፣ የካፒታሊዝምን አፀናነስና ዕድገት ደረጃ በደረጃ ካተተ በኋላ ውድድር(Competition) የካፒታሊዝም ዋናው የዕድገት አንቀሳቃሽ ኃይል መሆኑን ያመለክታል። በዚህም አማካይነት የምርት ኃይሎች ወይም የማምረቻ መሳሪያዎች በየጊዜው እየተሻሻሉ በመምጣት ለካፒታሊዝም ዕድገት ምጥቀትና መስፋፋት ይሰጡታል ይላል። የደሞዝ ዕድገትና፣ የኑሮ መሻሻል፣ እንዲሁም የፍጆታ ዋጋ መቀነስ ከማምርት ወይም ከማሺኖች ምርታማነት ጋር የተያያዙ ናቸው። በመሆንም በማርክስ ሀተታ መሰረት ገንዘብ ልዩ ሚና መጫወት የሚችለው የተለያዩ የማምረቻ መስኮችን ማያያዝ የቻለ እንደሆን ብቻ ነው። ልክ እንደ ሰውነታችን የደም ዝውውር ዐይነት የተለያዩ የኢኮኖሚ
መስኮች በገንዘብ አማካይነት ይተሳሰራሉ። ገንዘብ ከአንደኛው መስክ ወደ ሌላው በመተላለፍና ወደ ውስጠ-ኃይልና ህብረተሰብአዊ ኃይል በመሸጋገር ለአጠቃላይ
የካፒታሊስት የሀብት ክምችት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። በዚህም መሰረት ብድር ወይም ክሬዲት ልዩ ቦታን በመያዝ የሰው በሰው ግኑኝነት በገንዘብ ብቻ እንዲገለጽ ያደርጋል።
እንደምናየው የማርክስ የኢኮኖሚ ትንተና አቀራረብ ውስጠ-ኃይል ያለው ብቻ ሳይሆን በንጹህ የኢኮኖሚ ሂደት ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ሶስዮሎጂያዊ ወይም ህብረተሰብአዊም
ነው። ስለሆነም በማርክስ ዕምነት የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በግልሰብ ግኑኝነት ብቻ የሚገልጽ ሳይሆን መደባዊም ባህርይ አለው። ማንኛውም ምርታዊ ግኑኝነት በግለሰብ ደረጃ የሚካሄድ ሳይሆን በጋርዮሽ ወይም በብዙ ሰራተኞች አማካይነት ነው። ከዚህም ጋር በተያያዘ የሰራተኛው የመደራደር ኃይል በየጊዜው ከኢኮኖሚው ዕድገት ዝቅና ከፍ ማለት ጋር
የተያያዘ ነው።
ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የተስፋፉት የኢኮኖሚ ቲዎሪዎች የኬይንስንም ጨምሮ እንደቀደሙት ቲዎሪዎች ሀብት ፈጣሪ አይደሉም። ካፒታሊዝም አንድ የዕድገት ደረጃ
በሚገኝበት ወቅተና፣ ቀውስ ሲከሰት ማረሚያ መሳሪያዎች ሆነው የዳበሩ ናቸው። በይዘታቸው አዲስ ሀብትን ከመፍጠር ይልቅ የማከፋፈል(Distributive) ባህርይ ያላቸው
ናቸው። ለምሳሌ የገቢ ታክስን መቀነስ ወይም መጨምር፣ አንደኛውን ሲጠቅም ሌላውን ይጎዳል። ሌሎችም የደሞዝ ቅነሳ መሳሪያዎች ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ማስተላለፍ አንዱን
ሲጠቅም ሌላውን ይጎዳዋል። ወደ ኬይንሱ ስንመጣ ደግሞ በብድር አማካይነት የስራ መስክ በመክፈት ሰፋ ያለ የመግዛት ኃይል ይፈጠራል። ከዚህ ስንነሳ እነዚህ ቲዎሪዎች
እንደመጀመሪያዎቹ መሰረታዊ በሆኑ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ላይ የሚያተኩሩ አልነበሩም።
ወደ ሌሎች ቲዎሪዎች ስንመጣ፣ የአንድ አገር ሀብት(Wealth) የሚወሰነው ወይም የሚመነጨው በሶስት ነገሮች አማካይነት ነው። 1ኛ) ተፈጥሮአዊ ኃይል(Energy)
2ኛ) ፈጠራ 3ኛ) ታታሪነት፣ እነዚህ አንድ ላይ ሲጋጠሙ ወይም ሲጣመሩ አንድ አገር ተከታታይነት ያለው ሀብት መፍጠር ትችላለች ይላሉ። በተለይም የዚህ ቲዎሪ አራማጅ
የስኮቲሽ ተወላጅና በኬሚስትሪ የኖቭል ዋጋ ተሸላሚ የነበሩት ፕሮፌሰር ፍሪድሪሽ ሶዲ ናቸው። በተለይም ስለ ኃይል በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ያለውን ሚና በማስፋፋት፣ ኃይልን
በመጠበቅና ኃይልን በመለወጥ( Conservation and Transformation of Energy) መሀከል ያለውን ዲያሌክታዊ ግኑኝነት በማስመር፣ የአንድ አገር ዕድገት ሊወሰን የሚችለው በኃይል አማካይነት ብቻ እንደሆነ በግሩም መልክ ያብራራሉ። በተለይም ፀሀይን እንደ ምሳሌ በመውሰድ በጠቅላላው የሰው ልጅና ለተፈጥሮ ዕድገት ከፀሀይ የሚገኝ ኃይል ያለውን ከፍተኛ ቦታ በመዘርዘር የሰው ልጅ ችግርና ከዚህ ጋር የተያያዘው ድህነት ይህንን የተፈጥሮና ሳይንሳዊ ህግ ካለመረዳት የመነጨ መሆኑን ግልጽ በሆነ መንገድ ያብራራሉ።
ከዚህ በመነሳት የአንድ አገር ዋናው እንቅፋት ድንቁርና እንደሆነ ያመለክቱናል።
ምክንያቱም በተፈጥሮ ውስጥ ያሉትን ፀሀይንም ሆነ ውሃ እንዲሁም ልዩ ልዩ ንጥረ-ነገሮችን በስነ-ስርዓት መጠቀም ያለመቻል አንድን አገር ወደ ዘለዓለማዊ ድህነት
እንደሚመራው ነው። ፕሮፊሰር ኤሪክ ራይነትም በሌላ መልክ ለአንድ አገር ዕድገቱ ጥሬ- ሀብት ተትረፍርፎ መገኘቱ ሳይሆን የሰው የማሰብ ኃይልና ለስራ ወይም ለስልጣኔ ያለው
ፍላጎት ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት ያሳስባሉ። በሌላ አነጋገር የአንድ አገር የኢኮኖሚና የዕድገት ችግር የሚመነጨው ከአስተሳሰብ ችግር ነው። በፕሮፌሰር ራይነርት አተናተን
በተለይም በጥሬ-ሀብትና በእርሻ ላይ ብቻ የሚያተኩሩ አገሮች በተከታታይ ተጨማሪ ምርትን ለማምረትና ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ችግር ያጋጥማቸዋል። የማሰብ ኃይላቸውን
እንዳይጠቀሙ ስለሚታጋዱ በኢኮኖሚ በአደጉ አገሮች እንዲጠቁና የመኖርና ያለመኖራቸው ዕድል በዓለም ገበያ እንዲወሰን ይገደዳሉ ይሉናል።
ለመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ካለሳይንስና ቴኮኖሎጂ ውጭ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ወይ? አብዛኛውን ጊዜ ስለሶስተኛው ዓለም የኢኮኖሚ ዕድገት ችግርም ሆነ ውጤት
የሚጽፉ የሚዘነጉት ነገር ሳይንስና ቲኮኖሎጂ በኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ያላቸውን ሚና በመዘንጋት ነው። በተለይም የኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ለሳይንስና ለቴኮኖሎጂ ቦታ
አይሰጡትም። ያም ሆነ ይህ ብዙ ሳናወጣና ሳናወርድ የሰው ልጅ ዕድገት ከቲክኖሎጂ ጋር ነው። የተሻሉ የምርት መሳሪያዎች መጠቀም ሲጀምር የበለጠና በብዛት ማምረት
ይችላል። ስራውንም ያቃልላል። በዚህም ምክንያት ሳይንስና ቴክኖሎጅ ተግባራዊ መሆን ከጀመሩ ከ18ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የምርት መሳሪያዎች መብዛት ብቻ ሳይሆን
በጥራትም እየመጠቁም መምጣት ችለዋል። በዚያውም መጠንም የዛሬ ሁለት መቶ ዐመት የማይታዩ የምርት ዐይነቶችና ምግቦች ተስፋፋተው ይገኛሉ። ይህም ማለት በቴክኖሎጂዎች
ማደግና መስፋፋት የሰው ልጅም የማሰብና የማምረት ኃይል ሊያድግ በቅቷል።
ከላይ አጭር በሆነ መልክ ከተዘረዘረው አስተሳሰብ ስንነሳ በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት በምናወራበት ጊዜ ግልጽ ማድረግ ያለብን ነገሮች አሉ ማለት ነው።
በደፈናው የኢኮኖሚ ዕድገት ብሎ ነገር የለም። ከዚህ ጋር መያያዝ ያለበት ጉዳይ፣ ኢኮኖሚ ዕድገት ለምንና ለማን ብለን መጠየቅ አለብን። ኢኮኖሚ ዕድገት ለዕድገት
ሲባል፣ ወይስ ኢኮኖሚ ዕድገት የሰውን የማቴሪያል ፍላጎት አሟልቶ በአስተሳሰብም ደረጃ እንዲያጎለምሰውና ፈጣሪም እንዲያደርገው። ይህንን በሚመለከት የትምህርት ቤት
ኢኮኖሚክስ የሚለው ወይም የሚሰጠው መልስ የለም። እንዲያው በደፈናው ሁሉም በገበያ አማካይነት ብቻ የሚወሰን አድርጎ ያቀርባል። ለምሳሌ በትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ
ማንኛውም ህብረተሰብ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ምግብ፣ ንፁህ ውሃና መጠለያ ማሟላት እንዳለበትና፣ ከዚያ በመነሳት አንድን አገር መገንባት እንዳለበት አያሰተምርም። በሁለተኛ
ደረጃ በትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ፣ ከተማ ምን እንደሆነ አይታወቀም። የሚታወቀው ገበያ ብቻ ነው። ማለትም ገበያ ካለ ቦታና ሰዓት የሚካሄድ ነው። በሶስተኛ ደረጃ፣
የትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ ህብረተሰብ ማለት ምን ማለት ነው? እንዴትስ ነው የሚተሳሰረው? እንዴትስ ነው የስራ ክፍፍል የሚቀናጀውና የሚዳብረው? የሚለውን
መሰረታዊ ጥያቄ አያነሳም። ከዚህ ስንነሳ የኢኮኖሚ ዕድገት በራሱ ብቻ እንደሚጓዝ አድርገን መመልከት ከፍተኛ ስህተት ነው። ፕላቶን እንደሚያስተምረን፣ የነገሮችን
መተሳሰር ለመረዳት የግዴታ ከውጭ በሚታየው ላይ ሳይሆን ወደ ውስጥ ጠለቅ ብለን ስንመረምር ለችግሮቻችን ተቀራራቢ መልስ ማግኘት እንችላለን።
ከዚህ ስንነሳ ለአገራችን የሚበጀው የኢኮኖሚ ጎዳና የትኛው ነው? ሴን አንድ ቦታ ላይ ያስቀመጠው ትክክለኛ አቀራረብ አለ። ይኸውም የገበያን ኢኮኖሚ ምንነት ወይም
በገበያ አማካይነት በሰዎች መሀከል የሚደረገውን የንግድ ልውውጥ አስፈላጊነት በማስመር ነው። ወደድንም ጠላንም ከዚህ ልናመልጥ አንችልም። ጥያቄው ምን ዐይነት የገበያ
ኢኮኖሚና እንዴትስ እናደራጀዋለን የሚል ነው። እንደሚታወቀው አንድ ህብረተሰብ ውስብሰብ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ጥቅሞች የሚጋጩበትና የሚገናኙበት መድረክ ነው።
ስለሆነም ተፈጥሮአዊ ህግ ሆኖ ሁሉም አንድ ዐይነት ዝንባሌ የለውም። የስራ-ክፍፍል ይፈጠራል ማለት ነው። በስራ ክፍፍልና በልዩ ልዩ ምርቶች አማካይነት ሰው ፍላጎቱን
ያሟላል ። ከዚህ በመነሳት ነው የገበያን ትርጉም መረዳት የምንችለው። በተለይም አሁን ባለንበት ዓለም የገበያ ኢኮኖሚ ተጣሞ ስለሚቀርብ ኢኮኖሚ አደረጃጀትና ዕቅድ
እንደማያስፈልገው ተደርጎ ይቀርባል። በተለይም ካለስትራቴጂያዊ ዕቅድ የገበያ ኢኮኖሚ ተግባር ሊሆን አይችልም። ይህ ዐይነቱ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በግለሰብ፣ በማህበረሰብና
በመንግስት ደረጃ የሚካሄድ ነው። ይህም ማለት መንግስትም ራሱ በገበያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚጫወተው ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ሚና አለ። በተለይም አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠር
የኢኮኖሚ ኃይሎች ምርት በብዛትና በጥራት ለህብረተሰቡ እንዲያቀርቡ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። ከዚህ ባሻገር ግን የመንግስት ዋና ሚና የገበያ ኢኮኖሚ እንዲዳብር ከተፈለገ
በተለይም ከተማዎችና መንደሮች በዕቅድ እንዲሰሩ አሰፈላጊውን ኢንስቲቱሽኖች ማዘጋጀት አለበት። ምክንያቱም የገበያ ኢኮኖሚ በተወሰነ ክልል ብቻ መዳበር ስለማይችል በአገሪቱ
ውስጥ የተሰተካከለ ዕድገትና የሀብት ስርጭት እንዲስፋፋ የታቀደ ዕርምጃ መውሰድ አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ የነቁ ኃይሎች በአንድ ዘርፍና አካባቢ ከመረባረብ ተቆጥበው
ድርጊታቸውን በአገር ደረጃ ያደርጋሉ። ሰፋ ላለና ለጠለቀ፣ ይሁንና ደግሞ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ለተደገፈ ኢኮኖሚ አስተዋፅዖ ያደርጋሉ። በዚህ ዐይነቱ የገበያ እንቅስቃሴ
ውስጥ የባንክና የክሬድት ሲስተም ከፍተኛ ሚና ሲኖራቸው ከኢኮኖሚው ጋር እንዲተሳሰሩ ይደረጋል።
ይህ ዐይነቱ የገበያ ኢኮኖሚ ከጠቅላላው የህብረተሰብ ፍላጎት ውጭና ከረዥሙ የስልጣኔ ሂደት አንጻር ተነጥሎ መታየት የለበትም። አንድ ህዝብ በማቴሪያል ብቻ ፍላጎቱን
ማሟላት አይችልም። አንድ ህዝብ ህብረተሰብአዊ ትስስርና የመንፈስ ዕደሳን ሊጎናጸፍ የሚችለው ለመንፈሱ ግንባታ ጥንካሬ የሚሆኑ የባህል ግንባታ ሲያካሄድ ብቻ ነው።
ካለባህል እንቅስቃሴና ዕድገት ጥሩ የኢኮኖሚ ግንባታ ሊኖር አይችልም። ሰፋ ያለ የባህል እንቅስቃሴ ሲኖር አንድ ህዝብ የሚያደርገውን ነገር ያውቃል። ከማያስፈልጉና በተለይም
ታዳጊውን ትውልድ ከሚያበላሹ ነገሮች እንዲቆጠብ ይደረጋል። ስለሆነም ከአንግሎ-አሜሪካኑ የገበያ ኢኮኖሚ ፍልስፍና በመላቀቅ የተሰተካከልና ፍርዳዊ ወደ ሆነ የኢኮኖሚ
ግንባታ ማድላቱ ለአንድ አገር ዘላቂ ሰላም ይሰጣታል።
ከዚህ አንፃር የ21 ዐመቱን የእነ አቶ መለሰን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንቃኝ። እንደሚባለው ባለፉት 21 ዐመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ የመጣ ነው
ወይ? ይህንን ጥያቄ መመለስ የሚቻለው ከየትኛው ሁኔታ በመነሳት ነው የምንገመግመው ወይም የምንለካው የሚለውን ጥያቄ ካስቀመጥንና ለመመለስ የቃጣን እንደሆን ብቻ ነው።
ሌሎች እጅግ እብስትራክት የሆኑ የጂዲፒ አሰላልና የምርት ጭማሪና ከውጭ የሚመጣን ልዩ ልዩ ወደ ምርት ውስጥ የሚገቡ በግማሽ የተፈበረኩና የጥሬ-ሀብትን ትተን እንዲያው
በደፈናው ስንመለከት ከተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል አንጻር በስተቀር፣ ምናልባት 1%ለሚጠጋው ዜጋ የኢኮኖሚ ዕድግት መጥቷል ማለት እንችላለን። ይህ ዕድገት በትላልቅ
ህንጻዎች፣ በሆቴል ቤቶች ጋጋታ፣ በመንገድ ስራ፣ የስኳርና የቢራ ፋብሪካ የሚገለጽ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከመንግስት ጋር በሺህ ድሮች የተቆላለፉ የአየር በአየር ንግድ
ውስጥ በመሰማራት፣ የውስጥን ጥሬ-ሀብት በመሸጥ የገቢያቸው መጠን በፍጥነት የተተኮስ ኃይሎች አሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ የዚህ ህብረተሰብ ክፍል የፍጆታ አጠቃቀም በከፍተኛ
ደረጃ አድጓል። ከውጭ የሚመጣው የቅንጦት ዕቃ የማህበራዊ ስታተሱን ከፍ አድርጎለታል። ይህንና ከዚህ ጋር የተቆላለፈውን ሀብት ጨራሽ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ
ነው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተብሎ የሚወደስልን። ይህንን ዐይነቱን የኢኮኖሚ ዕድገት በመርካንትሊስቶችም ሆነ በፕሮፌሰር ፍሪድርሽ ሶዲና ፕሮፌሰር ኤሪክ ራይነርት የኢኮኖሚ
ቲዎሪ መነፅር ስንመረመረው አዲስ ሀብት የፈጠረ አይደለም። ሊፈጥርም የሚችል አይደለም። ቲክኖሎጂያዊ ምጥቀትን ያመጣ አይደለም። የውስጥ ገበያ እንዲስፋፋና
እንዲዳብር ያደረገና የሚያደርግ አይደለም። ለስራ ፈላጊው ሰፊ ህዝብ የስራ መስክ የከፈተና የሚከፍት አይደለም። የባሰ ጥገኝነትንና፣ ኢኮኖሚያዊ መዝረክረክን ያስከተለና
የሚያስከትል ነው። ሀብትን የሚያባክን ነው። በተፈጥሮና በሰው ልጅ ላይ ዘመቻ የከፈተ የኢኮኖሚ ዕድገት ነው። ይህንን ዐይነቱን ዕድገት ጥፋት እንለዋለን። የተወሰነውን
የህብረተሰብ ክፍል በማባለግ፣ ሰፊውን ህዝብ አቅመ-ቢስና ደሀ ያደረገ ነው።
እንደሚታወቀው አንድ አገር እንደ አገር የምትከበረው ከሁሉም አንፃር ማደግ ስትችል ብቻ ነው። ግርማ ሞገስ ያላቸው ከተማዎችና የመኖሪያ ቤቶች ሲሰሩና ለሰፊው ህዝብ
ሲዳረሱ ነው። ህዝቡ የመፈጥር ችሎታው ሲዳብር ነው። እንደ አንድ ዜጋ ሲተሳሰር ነው። ልዩ ልዩ መናፈሻ ቦታዎችና ሲዘጋጁለትና የኬነትና የቤተ-መጻህፍት ሁኔታዎች ሲቋቋሙለት
ነው። የሰው ልጅ በዳቦ ብቻ አይኖርም እንደሚባለው አአነጋገር፣ ፍቅርና ልዩ ልዩ መንፈሱን የሚያረኩ ነገሮችም ያስፈልጉታል። ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በልዩ ልዩ ነገሮች
የሚገለጽ መሆን አለበት። ሰፊው ህዝብ ከማያስፈልጉ ነገሮች እንዲቆጠብና አንዱ ሌላውን እንደወንድሙና እንደሰው እንዲያይ የሚያደርገው መሆን አለበት። የዛሬው በእነ አቶ
መለስና ግብረ-አበሮቻቸው እንዲሁም የኒዎ-ሊበራል ኤክስፐርቶች አማካሪዎቻቸው ተግባራዊ የሆነውና የሚሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማጅራት መቺዎችንና ማፊያ መሳዮችን
የሚፈለፍል ነው። በቅርብ ቀን ኢትዮጵያ ውስጥ በሚታተመው በሪፖርተር ላይ የወጣውን ዘገባ መመልከት ያስፈላጋል። በዘገባው መሰረት አስፈሪ ሁኔታዎች በተለይም በአዲስ አበባ
ከተማ ውስጥ እንደሰፈኑ ዘገባው ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጣል።
ከዚህ በመነሳት እኛ ኢትዮጵያውያን ምሁር ሆን አልሆን ለምን ዐይነት ሀብረተሰብና ለምን ዐይነት አኮኖሚ ነው የምንታገለው ብለን መከራከር አለብን። እኛን
የሚያሳሰብን የዚህኛው ወይም የዚያኛው ብሄረ-ስብ ነፃነት መውጣትና አለመውጣት አይደለም። እኛን የሚያሳስበብን ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው የኦሮሞው፣ የአማራው፣
የትግሬው፣ የወላይታው፣ የጉራጌው… ወዘተ ሁኔታ ነው። እኛን የሚያሳስበንና አንጀታችንን የሚያቃጥለን ሺህ በሺህ እየተቆጠሩ ለአረብ አገሮች በመንግስት የሚሸጡት
ልጆቻችንና እህቶቻችን ህይወት ነው። የሚያሳስብን በመንገድ ላይ የሚያድረው፣ ከቆሻሻ እየለቀመ የሚበላው፣ የዕፅ ሱሰኛ እንዲሆን የተገደደው ልጃችን ህይወት ነው። እኛን
የሚያስጨንቀን የህዝባችን ኑሮ መጨለሙ ነው። እኛን የሚያሳስበን የአገራችን ውድመትና መቸብቸብ ነው። ህዝቡ እንደ አንድ ዜጋ እንዳይተሳሰር መደረጉ ነው። እኛን የሚያሳስበን
ህዝባችን ዕውነተኛ ነፃነቱን እንዳይጎናፀፍና ዕድሉን ወሳኝ እንዳይሆን መደረጉ ነው። በዚህ ዐይነቱ ውጥቅንጡ የወጣ ስርዓት ግለሰብአዊ መብቶች መጣሳቸው ነው። የሚያቃጥለን
ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ መሪ የሌለው መደረጉ ነው። የሚያሳስበን ያረጀ የብሄረ-ሰብ ጥያቄ ሳይሆን የሰማንያ ሚሊዮኑ ህዝብ ዕድል ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከ50ና ከ100
ዐመት በኋላ ኢትዮጵያችን ምን ትመስላለች የሚለው ነው የሚከነክነን። የዚኸኛው ወይም የዚያኛው ፓርቲ ለስልጣን መውጣት መራወጥ አይደለም የሚያቃጥለን። ባጭሩ የአገርና
የህዝብ ደህንነት፣ ከሁሉም አቅጣጫ ዕድገት አለመኖር፣ ዕድገት እንዳይኖር ከውጭ የተሸረበብን ሴራና በጣም የደከመው ምሁራዊ እንቅስቃሴ ነው የሚያሳሰብን።
ከዚህ አሳዛኝ ሁኔታ በመነሳት ማንኛውም ምሁር ወደ ኋላ ተመልሶ ሰውን ሀዘን ውስጥ ከመክተት ይልቅ በአዲስ ኃይልና በእዲስ ቲዎሪ ተመርኩዞ፣ በተለይም ወጣቱን
ለማስተማር እራሱን ከአዲስ ጭንቅላትን ከሚያድሱ ነገሮች ጋር ማስተዋወቅ አለበት። የአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን የጀርመኑ ሳይንቲስትና ፈላስፋ ላይቢንዝ ስለ አረጀውና
ስለድሮው ነገር ማውራት የለብንም ይላል። መወያየት፣ መከራከርና መፍትሄም መፈለግ ያለብን ስለዛሬውና ስለነገው ነገር ነው። ማንኛውንም ከአስራሶስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ
የተደረጉትን ምርምሮችና የሳይንስ ፈለጎች ለተመለከተ ህብረተሰብን ለመለወጥ አዲስን ነገር በመፈለግ ላይ የተመረኮዘ ትግል ነው። ይህ ትግል የጭንቅላት ነው። በጉልበት ላይ
የተመሰረተ ግብግብ ወይም ንትርክ አይደለም። ቀናውና ትክክለኛው መንገድ ይህ ብቻ ነው የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም እንዲሉ፣ የድሮው አልፏል። ስለዚህም እንዴትና በምንስ መልክ፣
ለምንስ ነው የምንታገለው ብለን መወያየት አለብን። ከቲዎሪ አልባ ትግል መላቀቅ አለብን። እንደሚባለው ማንኛውም ነገር ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት በቲዎሪ ደረጃ
መመርመር፣ መጠናትና መተንተን አለበት። በዚህ መልክ ብቻ ነው የታሪክን አደራ መወጣት የምንችለው።
ፈቃዱ በቀለ
fekadubekele@gmx.de
ጠቃሚ መጽሀፎቸ !
Chytry, Josef (1989): The Aesthetic State; Berkeley, Los Angeles
Georgescu-Roegen, Nicholas (1971): The Entropy Law and the Economic Process;
Cambridge, Masschusetts
Lonergan, Bernard (1991): Macroeconomic Dynamics: An Essay in Circulation Analysis;
London
Lowe, Adolph (1977): On Economic Knwoledges: Toward a Science of Polictical Economics;
New York & London
Mrcus, Lyn (1975): Dialectical Economics; Toronto & London
Poulantzas, Nichos (1978): State Theory; Hamburg
Seung, T.K (1994): Kant`s Platonic Revolution in Moral and Political Phislosophy; London
Soddy, Frederick (1983): Wealth, Virtual Wealth and Debt: The Solution of the Economc
Paradox; London

 

 

 

ማሳሰቢያ፤በዌብሳይታችን ላይ ለሚወጡ ማናቸውም ጽሁፎች ቀዳሚ የሆነ የዌብሳይታችንን አርትኦት ስራን ለማክበር ሲባል በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በማለዳ ታይምስ የመረጃ ማእከል ® ላይ ለሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የማለዳ ታይምስ የመረጃ ማእከል ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዌብሳይቱን  ጠቋሚ (አመልካች ) (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.maledatimes.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን(የማለዳ ታይምስ ህግና ደንብ በንግድ በተመዘገቡበት ሁለት አገሮች የረቀቀ ሲሆን በሁለቱም አገሮች አንድ አይነት የሆነ አሰራር ይዞ ይከተላል ።ይህንን ህግ ማንኛውም ሰው መቅዳት የማይችል መሆኑን እንገልጻለን።ንብረትነቱ እና ህገ ደንቡ የማለዳ ታይምስ ብቻ ነው!)፡፡ይህ ካልሆነ ግን በህገ ደንባችን መሰረት አስፈላጊውን የህጋዊ ጥያቄ ለማቅረብ የምንገደድ መሆኑን እንጠቁማለን::በዚህ አጋጣሚ በግለሰብ ለሚላኩ ጽሁፎች ሁሉ ተጠያቂው ስሙ የተገለጸው ግለሰብ እንጂ የማለዳ ታይምስ መረጃ ማእከል ሃላፊነቱን እንደማይወስድ እናሳስባለን ::

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on October 7, 2012
  • By:
  • Last Modified: October 8, 2012 @ 10:46 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar