www.maledatimes.com የአቶ መለስ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ዘመናዊ ማድረግ ወይስ ማወላገድና ማዘበራረቅ ነበር ! (ፈቃዱ በቀለ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የአቶ መለስ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ዘመናዊ ማድረግ ወይስ ማወላገድና ማዘበራረቅ ነበር ! (ፈቃዱ በቀለ)

By   /   October 7, 2012  /   Comments Off on የአቶ መለስ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ዘመናዊ ማድረግ ወይስ ማወላገድና ማዘበራረቅ ነበር ! (ፈቃዱ በቀለ)

    Print       Email
0 0
Read Time:77 Minute, 32 Second

መግቢያ
ይህች አጭር ጽሁፍ ዶ/ር ቴዎድሮስ ኪሮስ በ Ethiopian Observer ላይ “Meles  Zenawi and the unfinished project of Ethiopian Modernity” በሚል ርዕስ ስር ያቀረቡትን አጭር ሀተታ፣ አቀራረቡ የቱን ያህል ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ፣ ከሳይንስና እንዲሁም ከአሰራር ስልት ጋር መጣጣሙን አለመጣጣሙን፣ የቱን ያህልስ ምሁራዊ ሀቀኝነት ያዘለና ያላዘለ መሆኑን ለመመርመር የቀረበ ትችታዊ መልስ ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ ከረዥም ዐመታት ጀምሮ ዶ/ር ቴዎድሮስ ኪሮስ በተለያዩ የኢትዮጵያ ድህረ-ገጾች ላይ ያወጡቱንና ለንባብ ያቀረቡትን ጽሁፎች አንብቤአለሁ።
ከአንዳንዶቹ በስተቀር ያነበብኳቸው ጽሁፎች በሙሉ በሳልና ሌላውም የበለጠ እንዲያውቅ ትምህርት ለጋሽ ጽህፎች ነበሩ። በስነጽሁፍ አቀራረባቸውና ህብረተሰብአዊ ሁኔታዎችን
አርቅቆና ትችታዊ በሆነ መልክ በማቅረብ የህብረተሰብአችንን ችግር ጠለቅ ብለን እንንረዳ ለማድርገ ጥረዋል። ከዚህም በላይ እኔ እስከማውቀው ድረስ የሶሻሊስትን ርዕይ
ከሰውነታቸው ጋር በማዋሃድ እስከአሁንም ድረስ ለእኩልነት የሚታገሉ „ብቸኛው“ ምሁር ናቸው ማለት እችላለሁ። ይሁንና ግን ይህንን ስለአቶ መለስ ልዩ የዘመናዊነት አራማጅ
ድርጊት የቀረበውን አዲስ የምስጋና ዐይነት ጽሁፍ ሳነብና፣ በጽሁፉ ውስጥ የቀረቡትን ርስበርሳቸው የሚቃረኑ አባባሎችን መስመር በመስመር ስሄድበት በጣም ነው የደነገጥኩት።
ከአንድ ከእንደዚህ ዐይነት የመሰለና፣ ቀደም ብሎ የበሰሉ ጽሁፎችን ከሚያወጣ ሰው እንደዚህ ዐይነት አቶ መለስን የሚያወድስ ጽሁፍ ይጽፋል ብዬም አልጠበቅሁም። ቀስ
በቀስ ግን እኝህ ምሁር የቱን ያህል በ90 ሚሊዮን ህዝባችን ላይ እንዳላገጡ ነው የተሰማኝ። ይህ ብቻ ሳይሆን አቶ መለስ ስልጣን ከያዙበት ቀን አንስቶ ብቻ ሳይሆን፣
ዊንጌት ትምህርት ቤትም ሆነ ዩኒቨርሲቲ በነበሩበት ጥቂት ዐመታት ለጠቅላላው ኢትዮጵያ ህዝብና በተለይም ለሸዋ አማራ ጥላቻ እንደነበራቸውና፣ በተለይም የአማራን ቅስም
ለመስበር ቆርጠው እንደተነሱ በግልጽ ተናግረዋል። ዩኒቭርሲቲ ውስጥ በአንድ ስብሰባ ላይ፣ በተለይም በአማራው ብሄረሰብ ላይ ያላቸውን ጥላቻ በግልጽ ተነስተው ሲናገሩ
የተወሰነው እዚያው ሊደበድቧቸው ሲነሳ፣ ሌሎች አማሮች ናቸው ገላግለው ያዳኗቸው።
ይህንን ድራማ አንድ በቅርብ ከማምነውና በፍጹም ሊዋሽ ከማይችል ጓደኛዬ ነው የሰማሁት። በአጭሩ አቶ መለስ ለጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ በተለይም ለአማራው
ቀና አመለካከት ያላቸው አልነበሩም። ኢትዮጵያን አጥብቀው እንደሚጠሉ በተለያየ ጊዜ አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያን ታሪክ በአዲስ መልክ ለማጻፍ ቆርጠው የተነሱ መሪ ነበሩ።
ተግባራቸው ሁሉ የሺህ ዐመት የቤት ስራ ሰጠተውን ለማለፍ የተዘጋጁ ነበር የሚያስመስላቸው።
አቶ መለስን ልዩ ዐይነት ስጦታና የተቀደሰ ተልዕኮ ያላቸው ምሁር ነበሩ ብለው ዶ/ር ቴዎድሮስ ብቻ ሳይሆኑ፣ ዶ/ር ገላውዴዎስ አርአያና ዶ/ር አሳየሀኝ ደስታ የሚባሉ
ምሁራንም እንደዚሁ በሚያስገርምና በሚያሳዝን መልክ ጽሆፎች በዚሁ በ Ethiopian Observer ላይ አቅርበዋል። የሁለቱም ጽሁፍ ከዕውነት የራቀ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም
ዐይነት የሳይንስ መለኪያ ሊመዘን የሚችል አቀራረብ አይደለም። ልክ እንደ ዶ/ር ቴዎድሮስ እነዚሁም ምሁራን በተለይም በአቶ መለስ ጥይት በተደበደበው ወጣት ላይና
በስንት መከራ እንዲሰቃይ በተደረገው አንድ ትውልድ ላይ ነው ያሾፉት። እንደገባኝ ከሆነ እነዚህ ምሁራን ባላፉት ሃያ አንድ ዐመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ምን እንደተካሄደና የኢትዮጵያ ህዝብ በምን ዐይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳለ የተከታተሉ አይመስለኝም። ወይንም ደግሞ የአገራችንን ህዝብ የኑሮ ሁኔታ በልዩ ዐይነት መነፅር ነው የሚመለከቱት ማለት ይቻላል። ምናልባትም በጎሳ መነጽር ! በሌላ ወገን ግን የተሰማቸውን ሀዘን መግለጽ ይችላሉ። ይህ መብታቸው ነው። ጠላትም ሆነ ወዳጅ ሲሞት ይታዘንለታል። ከዚያ በተረፈ
ግን አንድ መሪ ነኝ ብሎ ስንት ወንጀል ሰርቶና ህብረተሰብን አዘበራርቆ ከሄደ ልክ ጥሩ ስራ የሰራ ይመስል እሱን ማወደውስ ከምሁራዊ ሀቀኝነት የራቀ ነው። ኃላፊነት የጎደለው
ሀተታ መሳፍንት ነው። እንደዚህ ዐይነቱ ከሀቅ የራቀ ሳይንሳዊ ይዘት የሌለውና ከተጨባጩ የአገራችን ሁኔታ የራቀ አቀራረብ ዝም ብሎ መታለፍ የሚገባው አይደለም። ወደ ዋናው
ቁም ነገር ልግባ!
የአቶ መለስ ኢትዮጵያን ዘመናዊ የማድረግ ፕሮጀክት !
ስለዘመናዊነት ወይም በእንግሊዘኛው አጠራር Modernization ተብሎ ስለሚታወቀው ስለ ኢኮኖሚ ታሪክም ሆነ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት የጻፉ ምሁራን በተለያየ
መልክ አትተዋል። ሁሉም ስለዘመናዊነት ሲያትቱ የአንድን አገር ዕድገት ፊት ከነበረችበት ሁኔታ ጋር በማነፃፀር ያደረገችውን የቴክኖሎጂ ምጥቀት ወይም ያለችበትን የኢንዱስትሪ
ዕድገት ሁኔታ እንደመመዘኛ አድርገው በመውሰድ ነው። ዘመናዊነት እንዲያው በአጭር የሚገለጽ ሳይሆን፣ ወደዚያ ለመድረስ አገሮች የቱን ያህል ውጣና ውረድ የተሞላበት ጎዞ
መጓዝ እንደነበረባቸውና፣ የቱንስ ያህል የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት እንደነበረባቸው የሚያመለክት የአንድ ህብረተሰብ የዕድገት መግለጫ መመዘኛ ነው። የተለያዩ ህብረተሰቦች
ዛሬ ዕድገት ወይም ዘመናዊነት የሚባለው ደረጃ ላይ ለመድረስ የተለያየ መንገድ ተጉዘዋል። ለብዙዎቹ አሰቸጋሪና ዕልክ አሰጨራሽ ነበር። ለአንዳንዶቹ ደግሞ ቀድሞውኑ
ያለቀለት ቴክኖሎጂ ጋር ስለተጋጩ እሱን መቅዳትና የህበረተሰባቸውን ጉዞ ማሳመር ቀላል መንገድ ነበር። በተለይም የምዕራብ አውሮፓ የዘመናዊነት ወይም የዕድገት ፈለግ እጅግ
ዕልክ አስጨራሽና የብዙ ሚሊዮንን ህዝብ ህይወት የፈጀ ነው። ምክንያቱም በየታሪክ ወቅት በየህብረተሰቦች ውስጥ ያሉ የኃይል አሰላለፎችና በስልጣን ላይ ያሉት የገዢ መደቦች
አዲስ ነገር ከመጣ ጥቅማችን ይነካል በማለት ለዘመናዊነት ወይም ለዕድገት የተነሱ ኃይሎችን ይገድሉ ወይም ያሳድዱ ስነበር ነው። ለዚህ ነው በአውሮፓ ምድር ውስጥ
እዚያው በዚያው በአገዛዙ ውስጥ መተራረድ፣ ተንኮል መስራትና ቀናውን መንገድ ቶሎ ብሎ ለመቅጨት ትግል ይካሄድ የነበረው። ይህ ዐይነቱ አለመተማመን፣ ህብረተሰቦች
ባለህበት ዕርጋ ሆነው እንዲቆዩ ማድረግ ዕርስ በርስ ጦርነት እስኪፈታ ድረስ የብዙ ምዕራብ አውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክ ዕጣ እንደነበር ይታወቃል። ይሁንና የተገለጸላቸውና
ሰፋ ያለ ዕውቀት የነበራቸው፣ እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ ዋናው ተልዕኮ ጦርነት ሳይሆን ስልጣኔና በስምምነት ላይ የተመረኮዘ ህብረተስብ መገንባት ነው ብለው ቆርጠው
በተነሱ ግለሰቦች አማካይነት ነው የዘመናዊነት ፈለግ የተቀደደውና የሳይንስና የቴክኖሎጂ መሰረት የተጣለው። ወደ ጃፓንና ደቡብ ኮርያ ስንመጣ ብዙ ጥናት ቢያስፈልግም ነገሩ
ይህንን ያህልም የሚያከራክር አይደለም። ሁለቱም አገሮች አውሮፓ ያለፈበትን ጉዞ ሳይጓዙ በቁጭትና በዲሲፕሊን ታጥቀው በመነሳት የቴክኖሎጂ ባለቤት ሆነዋል። በአጭር
ጊዜ ውስጥ ህብረተሰባቸውን ወደ ዘመናዊነት ለውጠዋል። የመንፈስ ተሃድሶ አግኝተዋል።
እዚህ ላይ ዶ/ር ቴዎድሮስ ስላነሱት የገበያ ኢኮኖሚ ብዙም ሳላትት በመሰረቱ ዘመናዊነት በአውሮፓ ምድር ውስጥ የታየው በ17ኛው ክፍለ-ዘመን ሳይሆን ከአስራተኛው
ክፍለ-ዘመን ጀምሮ፣ በተለይም ጣሊያን፣ በአስራ አምስተኛውና በአስራ ስደስተኛው ክፍለ-ዘመን ደግሞ ሆላንድና እንግሊዝ ውስጥ ነው። ሁለቱም አገሮች የጣልያንን ፈለግ
በመከተል በሩቅ ንግድ አማካይነት ወደ ውስጥ ኢኮኖሚያቸውን ዘመናዊ እያደረጉ የመጡበት ሁኔታ አለ። እዚህ ላይ ስለዘመናዊነት ሲወራ የብዙ አውሮፓ አገሮች ዕድገት
ቀና መሆን የቻለው በየቦታው ከተማዎች መስራት፣ ቤተ መንግስትንና ካቴድራሎችን መገንባት የኋላ ኋላ ለገበያ ኢኮኖሚ፣ እንዲያም ሲል ለካፒታሊዝም ዕድገት መንገዱን
አመቻችቷል ማለት ይቻላል። በከተማዎች ማበብ የተነሳ፣ ንግድና ዕደ-ጥበብ ይስፋፋሉ። የሰዎች የፈጠራ ችሎታ ይጨምራል። ውድድር የዕድገት አንቀሳቃሽ መሆን ይጀምራል።
ይህ ዐይነቱ መፍጨርጨር በቲዎሪ ሲተነተንና መንግስታትም የውስጥ ገበያን ለማስፋፋት ምን ምን ዐይነት ፖሊሲዎች መከተል እንዳለባቸው ሃሳብና ክርክር ሲቀርብና ሲደረግ የገበያ
ኢኮኖሚ ከግብዛዊነት ወደ ዕቅድነት ያመራል። በተለይም የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ህብረ-ብሄርን  መመስረት ከጀመሩበት ከ17ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ውድድሩ በአገሮች
መሀከል የሚካሄድ ይሆናል። እያንዳንዱ አገዛዝና መንግስት የራሱን አገር በፀና መሰረት ላይ መገንባት እንዳለበት ይገነዘባል። ስለዚህም ይከተላቸው የነበሩ ፖሊሲዎች ህብረተሰቡን
ወይም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን የሚገፉ ሳይሆን እነሱን የሚያግዙ ነበሩ። ለዚህ ነው የገበያ ኢኮኖሚ ወደ ካፒታሊዝምነት ሊሸጋገር የቻለውና፣ ከአገር ውስጥ አልፎ ዐለምን
ለመቆጣጠር የቻለው። ይሁንና ግን የካፒታሊዝም ዕድገትና ምንነት በሳይንስና በቲኮኖሎጂ እንጂ በንግድ ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ስለሆነም ቀደም ብለው የተፈጠሩና
የተደረሰባቸው ምርምሮች በካፒታሊዝም ዘመን ወደ ተጨባጭ ሁኔታዎች መለወጥና የኛንም ሁኔታ መቀየር ችለዋል። ስለሆነም ካፒታሊዝም ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ግኝትና ተግባራዊነት ተነጥሎ ሊታይ የሚችል አይደለም። በነሱ አማካይነት ብቻ ነው በተከታታይ ጥራት ያለው ምርትና በብዛትም ሆነ በተለያየ መልክ ማምረት የሚቻለው። ካፒታሊዝም የፎጆታ ምርት ብቻ የሚመረትበት ህብረተሰብ አይደለም። ህብረተሰቡን ከአደጋ የሚከላከሉ ልዩ ልዩ መሳሪያዎችና የህክምና ዕቃዎች የሚመረቱበት ነው። ከዚህ ስንነሳና ባለፉት ሃምሳ ዐመታት የተካሄደውን የቴክኖሎጂ ምጥቀት ስንመለከት ካፒታሊዝም እንዲያው በብዝበዛነትና በሞራል-አልባነት የሚገለጽ አይደለም።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ፣ በዶ/ር ቴዎድሮስ ዕምነት ዘመናዊነት የተጀመረው በአቶ መለስ ዜናዊ አማካይነት ነው የሚል ዐይነት አባባል ይነበባል። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ
አፄ ቲዎድሮስንና አፄ ምኒልክን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ከጠላት መንጋጋ ለማዋጣት የተዋደቀውን ሺህ በሺህ የሚጠጋ ህዝባችንን እንደመስደብ ይቆጠራል። በአፄ ቴዎድሮስም
ዘመን ኢትዮጵያን ዘመናዊ ወይም የኢንዱስትሪ አብዮት ባለቤት ለማድረግ ጥረት እንደነበረ የታሪክ ማስረጃዎች አሉ። አፄ ቴዎድሮስ ሲነሱ የእሳቸው አስተሳሰብ አካባቢያቸው ካሉት
ቀሳውስትና ፊዩዳሎች ርቆ የሄደ ስለነበር ሃሳባቸውን የሚጋራና የሚደግፋቸው አልነበረም።
ራሱ የአገራችን የምሁር ሁኔታ በዜሮ ደረጃ ይገኝ ስለነበር ልክ እንደጃፓኖች የአውሮፓን ዕውቀትና ቴክኖሎጂ አስገብቶ ኢትዮጵያን ዘመናዊ ማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ ነበር።
ይህንን አስመልክቶ አቶ መለስ አንድ ሰሞን ለኢትዮጵያ የተሌቪዥን ጣቢያ እጅግ ጥራዝ ነጠቅ በሆነ አቀራረብ አፄ ቴዎድሮስንም ሆነ አፄ ምኒልክን ሲወነጅሉ ተደምጠዋል። ሃንስ
ጎርጅ ጋደማር የማባሉ ታላቅ ፈላስፋ ዕውነትና ስልት(Truth and Method) በሚለው ግሩም መጽሃፋቸው እንደሚያስገነዝቡት የአንድን ነገር ሁኔታም ሆነ የአንድን ሰው ድርጊት
ከነበረበት የታሪክ ሁኔታና የህብረተሰብ አገነባብ ውጭ ነጥሎ ማየት እንደማይቻል ያሳስባሉ። ስለዚህም ስለ ሁለቱ ንጉሶቻችን ድርጊት በሚጻፍበት ጊዜ ድርጊታቸውን መመዘን
የምንችለው በጊዜው ከነበሩበት ሁኔታ በመነሳትና ያለውን የዕውቀት ኃይል በመመርመር ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ የሚቀርብ ሀተታ ሳይንሳዊ አይደለም።
እንደገና ወደ ኢትዮጵያ ዘመናዊነት ስንመጣ ለመጀመሪያ ጊዚ በሚያረካ መንገድ ባይሆንም የአገራችንን የዘመናዊነት ፈለግ የቀየሱና ተግባራዊም ያደረጉ አፄ ምኒልክ ናቸው። ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን በአንድ አገዛዝ ጥላ ስር ያደረጉና ትምህርት ቤት፣ ባንክ፣ የባቡር ሃዲድና አንዳንድ ቴክኖሎጂዎችም ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ያደረጉ ታላቁ ንጉስ ናቸው። ይህ ድርጊታቸው ግን ገፋ ብሎ መሄድ አልቻለም። በአካባቢያቸው የተሰበሰበው ኃይል ይህንንም ያህልም የሳቸው አስተሳሰብ የገባው አልነበረም። የበለጠ ግን በተንኮልና በስልጣን ሽኩቻው ውስጥ የሚገኝ ነበር። ስለሆነም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንደጃፓኑ በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ ሳይሆን በቀላሉ ሊዳከም በሚችል መሰረት ላይ
የተገነባ ነው ማለት ይቻላል። ስለሆነም ሰፋ ያለ በቴክኖሎጂ ምጥቀት ላይ የተመሰረተ የአገር ውስጥ ገበያ መገንባት አልተቻለም።
ወደ አፄ ኃይለስላሴ ኢትዮጵያን ዘመናዊነት ወደ ማድረጉ ድርጊታቸው ስንመጣ የሳቸው አስተሳሰባቸው በጣም ጠባብ ነበር። ከትናንሽ ለጥቀማ ጥቅም ከሚውሉ
ቴክኖሎጂዎች በስተቀር አገርን ሰፋና በየጊዜው እያደገ በሚሄድ ቴክኖሎጂ ላይ መገንባት እንዳለበት የተረዱ አልነበሩም። እንዲያው በደፈናው ምንም ዐይነት የምርምር ጣቢያ ሳይከፈት ትምህርት ቤት ከፍተንላችኋል ገብታችሁ ተማሩ በማለት የዘመናዊነትን ጉዞ ያዘበራረቁ መሪ ነበሩ። ቢሮክራሲውም ሆነ አሪስቶክራሲው አገርና ህብረተሰብ ማለት ምን   ማለት እንደሆኑ ያልገባቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ አንድ ህብረተሰ እንዴት አድርጎ ደረጃ በደረጃ በመተሳሰር መገንባት እንዳለበት ጥረት የሚያደርጉ አልነበሩም። ፍላጎትም፣ ስሜትና
ዲሲፕሊን እንዲሁም ደግሞ ቴክኖሎጂን የመኮረጅ ፍላጎት አልነበራቸውም። ስለሆነም የኢትዮጵያን መልክና የውስጥ ሁኔታውን አበላሽተውና አዘበራርቅው የሄዱ ናቸው ማለት
እንችላለን።
የደርግን ትተን ወደ አቶ መለስ የዘመናዊነት ፖሊሲና ጥረት እንምጣ። በዶ/ር ቴውድሮስ ዕምነት አቶ መለስ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት የሶሻሊስት ዕምነት እንደነበራቸው
ነው። የቀድሞ አብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰባቸውን በመጣል የነፃ ገበያ መከትል ጀመሩ ይሉናል። በጊዜው የሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለምን ለታክቲክ ብለው ተቀብለውት ይሆን ወይም
ከደማቸው ጋር የተዋሃደ ለመሆኑ ማረጋገጫ የለንም። ግን አንዳንድ የማርክሲስት መጽሃፎችን ለማንበባቸው የሚክድ የለም። ይሁንና ግን እሳቸውን ከማርክስም ሆነ
የማርክሲዝምን አስተሳሰብ ተግባራዊ ለማድረግ ከሞከሩት ከሌኒንና ከስታሊን ጋር ስናወዳድራቸው እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። ሌኒንም ሆነ ስታሊን ራሺያን ቀጥሎ ደግሞ
ሶቭየትህብርትን የመጀመሪያው ዓለም ጦርነት ካደረሰባት ውድቀት ተነስታ እንድታገግም በማድረግ ታላቅ አገር እንድትሆን ያደረጉ ናቸው። በተለይም ስታሊን የጨረሰውን ምሁርና
ገበሬ ወደ ጎን በመተው፣ የጀርመንን የሁለተኛውን ዓለም ጦርነት ወረራ መክቶ በመመለስ ሶቭየትህብረት ኃያልና ተከብራ እንድትኖር ያደረገ መሪ ነው። የሳይንስ ቴክኖሎጂ ባለቤት
በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ህዋ እንድታመራ ያደረገ መሪ ነው። ሶቭየት ህብረት የአቶም ቦብ ባለቤት እንድትሆን ያበቃ መሪ ነው።
ያም ሆነ ይህ በመጀመሪያ ሁኔታ የማርክሲዝምን ዲያሌክቲክ ያነበበና የገባው መሪ የሚወስደው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተራ የነፃ ገበያ ፖሊሲ ሊሆን አይችልም። በአንፃሩ
ሌኒንና ስታሊን፣ እንዲሁም ሌሎች ጓደኞቻቸው የወጣላቸው ምሁራን ስለነበሩና የካፒታሊዝምን ዕድገት የገባቸው ስለነበሩ አነሳሳቸው እንዴት አድርገን የካፒታሊስት
አገሮችን መያዝና ከነሱ ጋር መወዳደር አለብን የሚል ነበር። ከዚህ አጭር ገለጻ ስነሳ አቶ መለስ ይህንንም ያህል የኢኮኖሚ ታሪክንና ቲዎሪን በደንብ ሳይረዱ፣-ፍላጎታቸውም
አልነበረም- በ1993 ዓ.ም የእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክን የመዋቅር መስተካከያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተቀበሉ ናቸው። እሳቸው ይህንን ፖሊሲ አሜን ብለው
ሲቀበሉ እነ ጋና ቢያንስ አስር ዐመት ያህል በዚህ ዐይነቱ ፖሊሲ ውስጥ በመጓዝ በዕዳ የተተበተቡበትና ኢኮኖሚያቸውም በካካኦ ምርት ላይ ብቻ እንዲያተኩር የተደረገበት ሁኔታ
ነበር። ናይጄሪያና ዚምባቤዌም ይህንን ፖሊሲ በመከተል ኢኮኖሚያቸውን መልክ ማሲያዝ አልቻሉም። ይህ ሁሉ ማስረጃ እያለ ነው አቶ መለስ ምንም ክርክርና ጥናት ሳይደረግ
የእነ አይ ኤምፍን የአገር አፍራሽ የኢኮኖሚ ፖሊስ ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት። የዚህን አሉታዊ ውጤት በተለያየ ጊዜ ባወጣሁት ጽሁፎች ለማሳየት ሞክሬአለሁ። ዶ/ር ቴዎድሮስ
ከዚህ ቀደም የታተሙ ጽህፎቼንና በሌሎችም ኢትዮጵያውያን ምሁራን የቀረቡትን ሀተታዎች ቢመለክቱ ስለ አቶ መለስ የገበያ ኢኮኖሚ ምንነት የተሻለ ስዕል ያገኛሉ።
ከዚህ ስንነሳ ዶ/ር ቴዎድሮስ የተለያዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ምንነት የሚረዱ ይመስለኛል፣ አንድ አገር በንጹህ የሞነቴሪ ፖሊሲ ዘመናዊ ልትሆን ወይም በሳይንስና
በቴክኖሎጂ ላይ የተገነባ የኢንዱስትሪ አብዮት ማካሄድ አትችልም። በመጀመሪያ ደረጃ ዳስ ካፒታልን የመጀመሪያውን ቅጽ ያነበበ የሚረዳው ካፒታሊዝም የራሱ የሆነ የውስጥ
ሎጂክና ህግጋት አለው። ይህም ማለት ገንዘብና የገንዘብ ዕድገት እንዲሁም በተለያዩ መልኮች መገለጽ ከስራ-ክፍፍል መዳበርና ከቴክኖሎጂ ምጥቀት ጋር የተያያዘ ነው።
ከስራ-ክፍፍል መዳበር በፊት ገንዘብ አልነበረም፣ ቢኖር እንኳ የገንዘብ ዐይነት ፕሪምቲቭ ባህርይ የነበረው ነበር። ማለትም አንድ ኢኮኖሚ ከአንድ የዕድገት ደረጃ ወደ ሌላ
ሲሸጋገር የገንዘብ ዐይነት ብቻ ሳይሆን ይዞታውም ይለወጣል። ለዚህም ነው ከአሞሌ ጨውና ከብረት የተሰራ የገንዘብ ዐይነት ወደ ወርቅና ብር፣ ከዚያው በኋላ ደግሞ ወደ
ወረቀት ብርነት ማድግ የተቻለው። ይህ ብቻ ሳይሆን ዛሬ በካፒታሊስት አገሮች የገንዘብ ተተኪ የሚባለው እንደ ክሬዲትና ቪዛ ካርድ የመሳሰለው የተስፋፋው የሚያረጋጠው
ካፒታሊዝም ቀድሞውኑ በተራ የሞኔተሪ ፖሊሲ የታቀደ አለመሆኑን ነው። ያም ሆነ በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዕምነት መውዕለ-ነዋይ ሳይሆን መቅደም ያለበት የገንዘብን
መሽከርከር በተለያዩ መሳሪያዎች ከኢኮኖሚው ውስጥ እየመጠጡ በማውጣት፣ በአንድ በኩል ሀብትን ከሰፊው ህዝብ ወደ ጥቂቱና አምራች ወዳልሆነው ማስተላለፍ፣ በሌላ ወገን
ደግሞ ኢኮኖሚውን ማነቆ ውስጥ በመክተት ህብረተሰቡን ወደድህነት መክተት ነው።
የግሪክን ሁኔታ መመልከቱ ብቻ ይበቃል። ከዚህም በላይ ለዓለም ገበያ የሚቀርብ ምርት ተወዳዳሪ ይሆናል በሚል ዕምነት የአገርን የውጭ ካረንሲ ከዶላር ጋር ሲወዳደር ዋጋው
እንዲቀንስ ማድረግ። የመንግስትን ሚናና በጀትን መቀነስ ዋናው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ መመሪያ ነው። ብዙ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት በሶስተኛው ዓለም አገሮች ብቻ
ሳይሆን በኢንዱስትሪ አገሮችም በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች የተካሂዱት የፖሊሲ ግፊት የሀብት መሸጋሽግን ብቻ ሳይሆን፣ ሰላሳና አርባ ዐመት ያህል ስርቶና የጡረታ አበል ከፍሎ
ወደ ድህነት የሚገፈተረው ህዝብ ቁጥር ከዐመት ወደ ዐመት እየጨመረ መጥቷል። የኒዎ-ሊበራሎች የኢኮኖሚ ፖሊስ እየረቀቀ በመምጣት ከትምህርት ቤት አልፎ ወደ ጤና መስኩ
በመሸጋገር ህብረተስብአዊ መዛባትን አስከትሏል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ የበለጠ እንዲረዱልኝ፣ በ1993 ዓ.ም የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ሲጀምር በቀጥታ የኢትዮጵያ ሀብት የወያኔ ካድሬዎች ቁጥጥር ስር
ውስጥ ነው መውደቅ የጀመረው። ምርታማነትንና ውድድርን ለማሳደግና ለመጨመር እየተባለ ወደ ግላዊነት የተዘዋወረው የመንግስት ሀብት የወያኔን ካድሬዎች ያደለበ ነው።
በአቶ መለስና በግብረ-አበሮቻቸው ዕምነት ኢትዮጵያን መቆጣጠር የሚችሉት ሀብቷን ሲቆጣጠሩ ብቻ ነው። ስለዚህም ድርጊታቸው ሁሉ በኢንዱስትሪ ተከላና በቴክኖሎጂ
ምጥቀት ላይ ያተኮረ ሳይሆን ቶሎ ቶሎ ትርፍን ወደሚያመጣ ወደ ንግድና ወደ አንዳንድ አገልግሎት መስኮች ላይ መሰማራት ነበር። ይህንን ለማድረግ ደግሞ የሚቀናቀኗቸውን
በሙሉ ማጥፋት፣ ወይም ደግሞ እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ብቻ እንዲሄዱ በማድረግ በሙስና ዓለም ውስጥ እንዲዘፍቁ ማድረግ ነበር።
በዚህ ዐይነት የሞነቴሪ ፖሊሲ ላይ የተመረኮዘ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከፍተና የሀብት ዘረፋን አስከትሏል። ከላምንም ዕቅድና ፍላጎት ውጭ ህንፃዎች በመገንባት
የተስተካከለና ሰፊውን ህዝብ ሊጠቅም የሚችል የቤት አሰራር ተግባራዊ እንዳይሆን እድርጓል። ትላልቅ ሆቴል ቤቶች በመገንባትና በማስፋፋት የህብረተሰቡን ሀብት መጣጮች
ሆነዋል። ሰፊና በቂ የውሃ ገንዳዎች ባልተዘጋጁበት አገር የአዲስ አበባ ህዝብ በውሃ ዕጦት እንዲሰቃይ ተደርጓል። በየጊዜው የሚከሰተው የመብራት መጥፋት የሚያመለክተው
ኢኮኖሚው በዕቅድና በጥናት ላይ ያልተመሰረተ መሆኑን ነው። ከዚህ ውጭ ስንመጣ በአቶ መለስ የዘመናዊነት ፖሊሲ በኢንዱስትሪና በዕደ-ጥበብ ላይ የተመረኮዘ ሰፋ ያለ
የውስጥ ገበያ መዳበር አልቻለም። ብዙ እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱት በአዲስ አበባና አካባቢው ነው። ይህ በራሱ ህዝብን ከገጠርና ከትናንሽ ከተሞች በመሳብ በአዲስ አበባ
ውስጥ የመኖሪያ ቤት ጥበት እንዲኖር ያደረገ ነው። ስለሆነም በአፄ ኃይለስላሴና በደርግ ዘመን ያልነበረ የቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎች በአዲስ አበባ ውስጥ በብዛት ተስፋፍተዋል።
ይህንን ነው ዶ/ር ቴዎድሮስ ዘመናዊነት ወይም የዴቬሎፕሚንታል ስቴት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ፈለግ እያሉ የሚያቆላምጡት። እሳቸው የሚሉንን እንመልከት። From the very beginning, Meles Developmental state seeks, to give Ethiopian modernity an original economic form which decouples the idea of development, the motor of modernity, from any moral limitations and worse, it seeks to develop bureaucrats whose task is to implement a singular leader`s vision of building an economic infrastructure that develop the agricultural center in the villages and also build roads, highways, universities and business centers… etc.etc ይህ
ዐይነቱን የዴቬሎፕሜንታል ስቴት ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ አቶ መለስ የቻይናውን የዕድገት መንገድ በደንብ አጥንተዋል ይሉናል። በዚያ መልክ ነው ተግባራዊ ማድረግ
የጀመሩት ተባልን። አቶ መለስ በእርግጥ የቻይናውን መንገድ ነው መከተል የጀመሩት?
የቻይናውስ መንገድ ምን ይመስላል ? ዶ/ር ቴዎድሮስ እነዚህን ጥያቄዎች በደንብ አላብራሩልንም። እንደሚታወቀው ከ1978 ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄደውን የቻይናው
የዴቬልፕሜንታል ስቴት የኢኮኖሚ ፖሊስ ለተመለከተ፣ አገርን በመሰነጣጠቅ ሳይሆን በአራት መሰረታዊ አስተሳሰቦች ላይ በመመርኮዝ ነው። ይኸውም 1ኛው) ኢንዱስትሪውን ዘመናዊ ማድረግ፣ 2ኛ) የእርሻውን መስክ ዘመናዊ ማድረግ 3ኛ) ሚሊታሪውን ዘመናዊ ማድረግና ጠንካራ የጦር ኃይል መገንባት 4ኛ) የትምህርት ተቅዋሙን ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ
ዕድገት ብቃት እንዲኖረው ማድረግ። እንደተገነዘብኩት ከሆነ ቻይናዎች በዚህ ብቻ ሳይመረቁ እንዴት አድርገው ቀስ በቀስ የበላይነትንም ሁኔታ የሚቀዳጁበትን ወይም ደግሞ
በፍጹም ሊጠቁ የማይችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው የተያያዙት። የቻይና መሪዎች አብዛዎች በሳይንስና በኢንጂነሪንግ የተመረቁ ስለሆነ ያደሉት ቴኮኖሎጂን ማስፋፋት ነው።
ለዚህም ነው በ30 ዐመት ውስጥ እንደዚህ ዐይነት ምጥቀት ሊያሳዩ የቻሉት።
ያልተሰተካከለ ዕድገትንና የአካባቢን መበከልን ወደ ጎን ትተን የቻይናን ዕድገት ስንመለክት ሂደታቸው በሙሉ በደንብ የተጠናና በቀላሉ ለውጭ ኃይል መፈናፈኛ መስጠት የማይችል
ነው። ስለሆነም የቻይና ዕድገት በተወሰኑ ከተማዎች ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ቀሰ በቀስ ከተማዎችን በማስፋፋት የውስጥ ገበያ ለማዳበርና ለማስፋፋት የሚቻልበት ሁኔታ
እየተነጠፈ ነው። በተለይም የተለያዩ ከተማዎችን ለማያያዝ የተሰራውና የሚሰራው የባቡር ሃዲድና መንገዶች ቻይናን ከጥገኝነት አላቋታል ማለት ይቻላል።
የአቶ መለስን ስትራቴጅ ስንመለከት በአነሳሳቸው ታላቋን ትግሬን ለማልማትና ሌሎችን ክፍለ-ሀገራት የጥሬ-ሀብት አምራቾች ለማድረግ ነው። አቶ ኢሳያስ ኤርትራን
ሲንጋፖር እናደርጋታለን ያሉት በአቶ መለስ ጭንቅላት ውስጥም ሳይብላላ የቀረ አይመስለኝም። ይህም ማለት ከተቻለ ከኤርትራ ጋር በመሆን፣ ካለበለዚያ ደግሞ ከሌሎች
ክፍለ-ሀገራት መሪት እየነጠቁ በመውሰድና የትግሬን መሬት በማስፋት የኢንዱስትሪ ተከላ እዚያው ለማካሄድና የተቀረውን የኢትዮጵያ ግዛት ኋላ ቀር ለማድረግ ነበር። ይህ ሁኔታና
ህልማቸው ግን በፍጽም አልተሳካላቸውም። በተለይም ደረቅ መሬት ተይዞና በሶስት ሚሊዮን ህዝብ ብቻ ታግዞ ዘመናዊ ኢኮኖሚ መገንባት በፍጽም አይቻልም። በዚህ ላይ
የአካባቢው ባህል በፍጹም አይፈቀድም። ከዚሁ ስንነሳና ከኢኮኖሚ ታሪክ አንፃር ስንገመግመው የአቶ መለስ አካሄድ የኢኮኖሚ ግንባታን ሎጂክ የተከተለ አይደለም።
ሳይንሳዊ መሰረት የጎደለው ነው። ቀስ በቀስ ከታች ወደላይ የሚካሄድ የኢኮኖሚ ግንባታ ሳይሆን ያለውን የበላይነት ሁኔታ በመጠቀም የትግሬን ኤሊት የበላይነት ማስቀደም ነው።
አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው ዶ/ር ቴዎድሮስ እንደሚሉን ኢትዮጵያዊነት ሳይሆን ትግሬያዊነት ነው። ለዚህ ደግሞ የግዴታ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲና የውስጥ ለውስጥ የጥላቻ
ዘመቻ ማካሄድ ነበረባቸው። ህዝቡ ርስ በርሱ እንዲናከስ ሁሉን ነገር ከማድረግ መቆጠብ የለብንም የሚለውን ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የጊዜ ቦምብ አዘጋጅተው ሄደዋል ማለት
ይቻላል። ይህንን ማየት የማይችል ምሁር አስተሳሰቡ የተዛነፈ ነው ከማለት በስተቀር ሌላ ማለት የሚቻል ነገር የለም።
በእርሻ ላይ የተመረኮዘ የኢንዱስትሪ ተከላ!
አቶ መለስ ሲሉ የከረሙትን አሁን ደግሞ ዶ/ር ቴዎድሮስ በጽሁፋቸው ውስጥ አስተጋብተዋል። በሌላ አነጋገር አቶ መለስ ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት የዘመናዊነት
ፖሊሲ በእርሻ ምርት ላይ ወይም Agricultural Lead Industrialization Strategy በሚለው ላይ ነው። ይህ ግን እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን አቶ መለስም ሆኑ ዶ/ር ቴዎድሮስ አላብራሩልንም። በታሪክ ውስጥ እርሻ ለዕድገት የራሱ የሆነ አስተዋጽዎ ቢኖረውም የእርሻ ምርት ሊስፋፋና ሊያድግ የሚችለው በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው። ይህም ማለት የእርሻ መሳሪያዎች፣ ማረሻ፣ ተባይ ማጥፊያ፣ ማጨጂያና መውቂያ እንዲሁም መሰብሰቢያና ሌሎች ነገሮች የቴክኖሎጂ ውጤቶች ናቸው። ትርፋማ ምርት ማምረት
የሚቻለው በየጊዜው ቴክኖሎጂዎች እየተሻሻሉ የቀረቡ እንደሆን ብቻ ነው። አቶ መለስ መከተል የጀመሩት የቻይናውን መንገድ ነው የሚለውን ስንመለከት፣ ከቻይናዎቹ ጋር
በፍጹም የሚመመሳሰል አይደለም። ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ቻይናዎች የእርሻውን መስክ ዕድገት ከኢንዱስትሪ ዕድገት ውጭ ነጥለው አላዩትም። በሁለተኛ ደረጃ፣ ቻይና
በእርሻ ላይ የተመረኮዘ የኢንዱስትሪ አብዮት ማካሄድ ነው የጀመረችው የሚል ጥናት የለም።ቻይና ያደረገችው በታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ብዙ ቴክኖሎጂዎችን
ከምዕራቡ ኮርጃለች። በተለይም ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በማቋቋም ቴክኖሎጂዎችን መስረቅ ችላለች። እያደገች ስትመጣ ደግሞ ከምዕራቦች ጋር ስምምነት ስታደርግ ዕውቀቱም
እንዲገባ ማስገደድ ችላለች። ይህም ማለት የቻይናዎች የዕድገት ጉዞ የተወሳሰበና ስርዓት ያለው ነው ማለት ይቻላል። ይህ ማለት ግን የራሱ ድክመት የለውም ማለት አይደለም።
በዚህ ዐይነት ሪሶርስ አጠቃቀም እንደዚህ ዐይነቱን ዕድገት በተከታታይነት መቀጠል ይቻላል ወይ የሚለው ወደፊት የምናየው ነው። እንደሚታወቀው የሰፊ ህዝብ የፍጆታ አጠቃቀም
እየተቀየረ ሲሄድ የግዴታ በተፈጥሮ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል። መዛባትን ያስከትላል ማለት ነው።
ያም ሆነ ይህ አቶ መለስ ሲከተሉ የነበረው በእርሻ ላይ የተመረኮዘ የኢንዱስትሪ ተከላ ነው የሚለው ምንም መሰረት የለውም። በብዛት አምርተን፣ ምርቱን እንዳለ ከነነፍሱ የዓለም ገበያ ላይ ሸጠን ከዚያ በሚገኘው ዶላር ወይም ኢሮ ኢንዱስትሪ ገዝተን እንተክላለን የሚባል ከሆነ ይህ ዐይነቱ አካሄድ ትልቅ ቀልድ ነው። አንደኛ ማንኛውንም ምርት አምርቶ በዓለም ገበያ ላይ መሸጥ አይቻልም። የዓለም ገበያ የሚፈለገውን ብቻ ነው ማምረትና ማቅረብ የሚቻለው። ሁለተኛ፣ የዓለም ገበያ የሚፈለገውን እናምርት የሚባል ከሆነ ያለን የተወሰነ ሀብት፣ መሬትንም ጨምሮ ለዚያው ማዋል ያስፈልጋል ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ወደ ውስጥ የግዴታ የተዛባ ዕድገት መኖሩ ብቻ ሳይሆን አስተማማኝ የሆነ ዶላርና ኢሮ ማግኘት አይቻልም ማለት ነው።
በሶስተኛ ደረጃ፣ ለዓለም ገበያ ላይ የሚቀርብ የእርሻ ምርት ላይ አትኩሮ ከተደረገ የህዝቡ የምግብ ጥያቄ ይዘነጋል ማለት ነው። ያልታቀደ ረሃብ ይፈጠራል ማለት ነው።
በአራተኛ ደረጃ፣ የእርሻ ምርት ወደ ውጭ ከነነፍሱ የሚላክ ከሆነ በእርሻና በኢንዱስትሪ መስክ መሀከል የሚኖረው ግኑኝነትና የማባዛት ኃይል ይኮላሻል ማለት ነው። በአምስተኛ
ደረጃ፣ እንደሚታወቀው የእርሻ ምርት የማደግና የመስፋፋት ኃይሉ ውስን ነው።
ኢኮኖሚስቶች Decreasing Returns የሚሉት ነገር አለ። በማዳበሪያና በተባይ ኃይል እንዲሁም በላቦራቶሪ ውስጥ በተዳቀለ ዘር ላይ ብቻ በበመርኮዝ ነው የእርሻውን ምርት
መጨመር የሚቻለው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ደግሞ ከፍተኛ ኢኮሎጂያው መዛባትን ብቻ ሳይሆን በሰው ጤንነትም ላይ ከፍተኛ ቀውስን ያስከትላል።
ይህንን ሁሉ ትተን ባለፉት ዐመታት መሬትን ለውጭ ከበርቴዎች ማከራየትን ስንመለከት ይህ ዐይነቱ አካሄድ የአቶ መለስን ስትራቴጅ የሚቃረን ነው። እንደሚታወቀው
በአገራችን መሬት ላይ የተሰማሩት ኢንቬስተርስ የሚባሉት የሚያመርቱት ምርት ለዓለም ገበያ ተብሎ ነው። ይህም ማለት የሚያገኙት ገቢ እነሱ ኪስ ውስጥ ወይም ባንካቸው
ውስጥ የሚገባ ነው። ቀረጥ ያስገባሉ የሚባል ከሆነ ደግሞ ከብዙ የሶስተኛው አገሮች ልምድ እንደምንማረው ኢትዮጵያም ተጠቃሚ መሆን አትችልም። ለኢንዱስትሪ ዕድገት
የሚያስፈልጋትን በቂ የገንዘብ ካፒታል ማግኘት አትችልም ማለት ነው።
በአጭሩ የአቶ መለስ በእርሻ ላይ ተመርኩዞ ይካሄዳል የሚባለው የኢንዱስትሪ ተከላ በኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ውስጥ የታየ አይደለም። ከላይ እንዳልኩትና ጥናቶችም
እንደሚያመለክቱት የግዴታ የማኑፋክቱር አብዮት መካሄድ አለበት። ለዚህ ደግሞ የግዴታ ስፋ ያለ ለሳይንስና ለቴኮኖሎጂ ዕድገት ብቻ ሳይሆን፣ ለሰብአዊነትና ለጠቅላላው
የህብረተስብ ዕድገት የሚያመች አጠቃላይ የሆነ፣ ጀርመኖች በአስራስምንተኛው ክፍለ- ዘመን መጨረሻ ላይ ያስገቡትና ጃፓኖች የኮረጁት ዐይነት አጠቃላይ የትምህርት ስርዓት
ተግባራዊ መሆን አለበት። ዞሮ ዞሮ ለዚህ ደግሞ የፖለቲካው ሁኔታ መልክ መያዝ አለበት። ለስራ የሚያመች፣ ሃሳብን የማያፍን፣ ለፈጠራና ለዕድገት የሚያመች መንግስታዊ መዋቅር ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ያለውን መንግስታዊ መኪና ከጭቆና ባህርይውና ከጨቋኞች ማላቀቅ አስፈላጊ ነው። ይህ ብቻ ሲሆንና፣ የአንድ ጎሳ አገዛዝ ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜም ከኢትዮጵያ ምድር ሲጠፋ ሁሉንም የሚጠቅም ዕድገት መቀየስና ማምጣት ይቻላል። ከዚህ ስነሳና የዶ/ር ቴዎድሮስን ጽሁፍ በጥንቃቄ ሳነበው ያለው የወያኔ አገዛዝ እንዳለ በዚያው መንፈስ መቀጠል አለብን እንደማለት ዐይነት አቀራረብ የሚያስተጋቡልን። ዘለዓለማችሁን እየታሻችሁ ኑሩ ነው የሚሉን። ይህ ደግሞ ዶክተሩ አራምደዋለሁ ከሚሉት የሰብአዊነትና የሶሻሊስት አስተሳሰብ ጋር በፍጹም ሊሄድ የሚችል አይደለም። ሶሻሊስታዊ አስተሳሰብ የጎሳ አስተሳሰብን የሚቃወም ነው። አዚህ ላይ ዶ/ር ቴዎድሮስ አስተሳሰባቸውን ግልጽ ቢያደርጉልን ደስ ይለኛል።
የእርሻውን መስክ አስመልክቶ ዶ/ር ቴዎድሮስም ሆነ አግያ ፎረም የተባለው የውሸት ፕሮፖጋንዳ ድህረ-ገጽ የውሸት ቅስቀሳ ያደርጋሉ። በነሱ አገለለጽ አቶ መለስ ወጣት በነበሩበት ዘመን በመላው ገጠሪቱ ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ መመሪያ በመስጠትና ዲሞኮራሲያዊ ውይይት በማድረግ ገበሬውን ያደራጁ ነበር ይሉናል። በሳቸው አገላለጽ፣ „ A recent video in Aiga Forum, presents the young Meles Zenawi, movingly grounded in the rural culturees of the Ethiopian counryside. There in the vast fields of the principled Ethiopian peasants, impressive democratic dialogues take place. The leader is seen teaching and learning, lecturing and being lectured at, instructing and being instructed, relentlessly attacking bureaucratic ineptness, praising the natural intelligence of the Ethiopian peasants.
እያሉ ይነግሩናል። ይህንን ውሸት ልበለው ወይንስ ቅጀት!! ወይስ ዶ/ሩ እኛ ስለማናውቃት ስለሌላይቱ ኢትዮጵያ ነው የሚያወሩልን። ይህን ዐይነቱን ቀልድ የምታውቁ ካላችሁ ወይም
ከአቶ መለስ ጋር የነበራችሁና በቅርብ ስራቸውን የተከታተላችሁ ሰውየው እንደዚህ የሚያደርጉ የአገር መሪ ነበሩ ብላቸሁ ብትመሰክሩልን ወይም ብታረጋግጡልን ደስ ይለናል።
ይህ ከሆነ እኔም ትልቅ ይቅርታ ጠይቃለሁ። ለማንኛውም በአይጋ ፎረም ላይ ተመርኩዞ ማስረጃ ማቅረብ በፍጹም አይቻልም። ራስ ሲያዩና ያንን ያዩትን አንስቶ ማሳየት የተቻለ
ለታ ብቻ ነው ማሳመን የሚቻለው።
እግረ መንገዴን ለመደምደሚያ ያህል!
የአቶ መለስን የ21 ዐመት ፖለቲካ በምሁራዊ መነፅር ስንመረምረው ከማንኛውም የምሁር መመዘኛ የራቀ አደገኛ ፖሊሲ ነው። በመጀመሪያ ምሁር የሚባል በተወሳሰበ መልከ ማሰብ የሚችልና ለአንድ ችግር ቀና መፍትሄ መስጠት የሚችል ማለት ነው። በራሱ አሳብ ብቻ የሚመራ ሳይሆን የሌላውንም በማካተት ለችግር መፍትሄ ሊሆን ይችላል የሚባለውን መንገድ ለመቀበልና ተግባራዊ ለማድረግ የተዘጋጀ መሆን አለበት።
ከዚህ ስንነሳ ምሁር የሚባል የራሱ መለኪያና ደረጃ ቢኖረውም፣ በተለይም አገርን እመራለሁ የሚል አንድን አገር እንደህበረተሰብ ማየትና፣ እንዴትስ ተደርጎ ህብረተሰቡ በፀና መሰረት ላይ መገንባት ይችላል የሚለውን ስትራቴጂ ማውጣትና ማውረድ የሚችል መሆን አለበት። እንደሚታወቀው አንድ ሰው የአንድ አገር መሪና ምሁርም ቢሆን ዕውቀቱ ውስን ነው። የፈለገው ሰው በአንድ ጊዜ ሁሉንም ነገር ሊያውቅ አይችልም።
ለዚህ ነው በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ ነገስታት በፈላስፎችና በህግ አዋቂዎች እንዲሁም በአርክቴክቸርና በልዩ ልዩ ሙያ በሰለጠኑ ሰዎች ይመከሩ የነበረው። ነገስታቱ ራሳቸው
አዋቂዎች ቢሆንም ከየአገሩ የታወቁ ፈላስፋዎችን በመሰብሰብ ጥበብና ሳይንስ እንዴት እንደሚዳብር ሃሳብ እንዲያካፍሏቸው ይጠይቁ ነበር። ይህም ማለት በማንኛውም ጊዜ
የአንድ ህብረተሰብ ግንባትና ዕድገት በአንድ ሰው ትከሻ ላይ የሚወድቅ አይደለም፤ ሊወድቅም አይችልም። ይሁንና ግን አንድ መሪ አጠቃላይ የሆነ ዕውቀትና ማገናዘብ
የሚችል መሆን አለበት። ከተንኮል የጸዳ መሆን አለበት። የአገርን ጥቅም የሚያስቀድም መሆን አለበት። በምንም ዐይነት ለውጭ ኃይል ተገዢ መሆን የለበትም። የህዝቡን የልብ
ትርታ ለማዳመጥ የሚችል መሆን አለበት። ሰፋ ያለ ምሁራዊና የዳበረ የህብረተስብ ክፍል እንዲኮተኮት ርምጃዎችን መውሰድ አለበት። የአንድ አገር መሪ መለኪያው ሞራልና ስነ-
ምግባር መሆን አለባቸው። በዚህ መልክ ብቻ ነው በአውሮፓ ውስጥ ታሪክ የተሰራው።
አቶ መለስ ግን እንደዚህ ዐይነት ብቃትና አስተዋይነት የነበራቸው መሪ አልነበሩም። የአቶ መለሰን የ21 ዐመት ተግባር ስንመለከት 1ኛ) ከፖለቲካ አንፃር አገሪቱን
አዳክመዋል። ህብረተሰቡ እየተፈራራ እንዲኖር ለማድረግ ሰላዮችና አሰማርተዋል። የሃማኖትና የጎሳ ቅራኔ እንዲጠናከር በማድረግ የሰፊው ህዝብ አትኩሮ ወደ ፈጠራና ወደ
አገር ግንባታ ላይ እንዳያተኩር አድርገዋል። 2ኛ) ከጎረቤት አገሮች ጋር ጠብ በመጫር የአካባቢውን ሰላም መረበሽና ለአገራችንም ጠላት እንዲበዛ አድርገዋል። ለዚህ ደግሞ
ለውጭ ኃይል የጦር ካምፕ በመስጠትና ከዚያ እየተነሳ ደሀ ህዝብ እንዲደበድብ በማድርገ በአገራችን ውስጥ የፓኪስታን ዐይነት ሁኔታ እንዲፈጠር አድርገዋል። በመሆኑም ብሄራዊ
ነፃነታችንን በከፍተኛ ደረጃ አስደፍረዋል። 3ኛ) የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማካሄድ ድህነትን በታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እንዲስፋፋ አድርገዋል። በተጨማሪም
በቴክኖሎጂ ላይ የሚሰማራ ብሄራዊ ከበርቴ እንዳይፈጠር ነጋዴውን አባልገዋል። ስለሆነም ሰፋ ያለ የኢንዱስትሪ አብዮት እንዳይካሄድ ዕንቅፋት በመፍጠር የስራ መስክ እንዳይከፈት
በሩን ዘግተዋል። ይህ ሁኔታ ትምህርቱን ጨርሶ የስራ መስክ ለሚፈልገው ትልቅ ዕንቅፋት ሆኖበታል። ይህንን አሳዛኝ ሁኔታ ለመቅረፍ አቶ መለስ በ21 ዐመት አገዛዛቸው ያወጡት
ስትራቴጂ የለም። ካለምንም ዕቅድና ካለበቂ አስተማሪ፣ ላቦራቶሪና መጻህፍት ቤቶች በጭፍን ዩኒቭርሲቲዎችን ማስፋፋቱ ብቻ ዋጋ የለውም። ከዚያ ተመርቀው የሚወጡት
ዲንጋይ አንጣፊዎች ሆነዋል። 4ኛ) ኢኮኖሚው ሰፋ ባለና በጸና መሰረት ላይ ስላልተገነባ ከፍተኛ የሆነ የማህበራዊ ቀውስ ተፈጥሯል። የወጣት ሴተኛ አዳሪዎች መብዛት፣ አፀያፊ
የዝሙት ተግባር እንዲካሄድ በሩን ከፍቶ መስጠት፣ ወጣቱን ለሃሺሽና ለሌላ ድረግ ሰለባ ማደረግና ራሱን ስቶ እንዲኖር አድርገዋል። 5ኛ) ለዕድገት የሚያመች፣ የማሰብ አድማስን
የሚያሰፋና ለህዝብና ለአገር ተቆርቋሪ የሚያደርግ በሳይንስ የተጠና ባህል ከማስፋፋት ይልቅ ቡና ቤቶችና ዲስኮቴኮች በማስፋፋት ወጣቱ እንዲባልግ አድርገዋል። 6ኛ) አገራችን
የሰከንድ ሃንድ ዕቃ መጣያ መሆንና ይህንን ለማስወገድ አለመቻል የአገዛዛቸው ሌላው ገጽታ ነው። እነዚህና አያሌ አስከፊ ስራዎች በአቶ መለስ ዘመን በማወቅም ሆነ አውቃለሁ
በማለት የተስፋፉና ስር የሰደዱ ናቸው። ለማንኛውም አዲስ ለሚመጣ አገዛዝ ለመቅረፍም ሆን ለማስወገድ የሚያስቸግሩ ናቸው።
በመሆኑም ዶ/ር ኪሮስንና አንዳንድ ጓደኞቻቸው አቶ መለስን አዋቂና አሳቢ፣ እንዲሁም መልአክ አድርጎ ለማቅረብ መሞከር ለማንም የሚጠቅም አይደለም። እንደዚህ
ዐይነት ውሸት አንድ ምሁርና ሶሻሊስት ነኝ ከሚል የሚጠበቅ አቀራረብ አይደለም። እንደዚህ ዐይነቱ በማስረጃ ያልተደገፈና፣ በተለይም ደግሞ በዐይን የሚታየውን ነገር
መዋሸት ራስንም ያስጠይቃል። ኃላፊነት የጎደለው፣ ዘለዓለሙኑ እየተጋጨን እንድንኖር የሚያደርገን እንጂ የሚያቀራርበንና በአንድነት ተነስተን አገራችንን እንድንገነባና ጠንካራ
አገር እንድንመሰርት የሚያደርግ አይደለም። የአንድ ምሁር ዋናው መመዘኛ ሀቀኝነት፣ስነ-ምግባርና ሞራል ናችው። ስለዚህ ድርጊቱ ሁሉ ከወገናዊነት የራቁ መሆን አለባቸው።
ፈቃዱ በቀለ

 

 

 

ማሳሰቢያ፤በዌብሳይታችን ላይ ለሚወጡ ማናቸውም ጽሁፎች ቀዳሚ የሆነ የዌብሳይታችንን አርትኦት ስራን ለማክበር ሲባል በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በማለዳ ታይምስ የመረጃ ማእከል ® ላይ ለሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የማለዳ ታይምስ የመረጃ ማእከል ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዌብሳይቱን  ጠቋሚ (አመልካች ) (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.maledatimes.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን(የማለዳ ታይምስ ህግና ደንብ በንግድ በተመዘገቡበት ሁለት አገሮች የረቀቀ ሲሆን በሁለቱም አገሮች አንድ አይነት የሆነ አሰራር ይዞ ይከተላል ።ይህንን ህግ ማንኛውም ሰው መቅዳት የማይችል መሆኑን እንገልጻለን።ንብረትነቱ እና ህገ ደንቡ የማለዳ ታይምስ ብቻ ነው!)፡፡ይህ ካልሆነ ግን በህገ ደንባችን መሰረት አስፈላጊውን የህጋዊ ጥያቄ ለማቅረብ የምንገደድ መሆኑን እንጠቁማለን::በዚህ አጋጣሚ በግለሰብ ለሚላኩ ጽሁፎች ሁሉ ተጠያቂው ስሙ የተገለጸው ግለሰብ እንጂ የማለዳ ታይምስ መረጃ ማእከል ሃላፊነቱን እንደማይወስድ እናሳስባለን ::

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on October 7, 2012
  • By:
  • Last Modified: October 8, 2012 @ 10:35 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar